የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwyp ርዕስ 12
  • ጉልበተኞች ቢያስቸግሩኝ ምን ላድርግ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጉልበተኞች ቢያስቸግሩኝ ምን ላድርግ?
  • የወጣቶች ጥያቄ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?
  • ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት ለምንድን ነው?
  • ጉልበተኞች ብዙውን ጊዜ የሚያጠቁት እነማንን ነው?
  • ጉልበተኞች የሚያስቸግሩህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?
  • ከጉልበተኝነትና ከጥቃቱ መገላገል
    ንቁ!—2003
  • ጉልበተኝነት—አንዳንዶች ጉልበተኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ይህስ ሌሎችን የሚጎዳው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2003
  • ጉልበተኝነት—ዓለም አቀፍ ችግር
    ንቁ!—2003
  • ልጄን ጉልበተኞች ቢያስቸግሩት ምን ላድርግ?
    ለቤተሰብ
ለተጨማሪ መረጃ
የወጣቶች ጥያቄ
ijwyp ርዕስ 12

የወጣቶች ጥያቄ

ጉልበተኞች ቢያስቸግሩኝ ምን ላድርግ?

  • ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

  • ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት ለምንድን ነው?

  • ጉልበተኞች ብዙውን ጊዜ የሚያጠቁት እነማንን ነው?

  • ጉልበተኞች የሚያስቸግሩህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

በተጨማሪም እኩዮችህ የሰጡትን ጠቃሚ ምክር እንዲሁም አንዲት መምህርት ጉልበተኞችን በተመለከተ የተናገረችውን ሐሳብ አንብብ፤ ከዚያም ጉልበተኞች—ጥያቄዎች የሚለውን መልመጃ ሥራ።

ጉልበተኞች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንደ ቀላል የሚታይ ነገር አይደለም። በብሪታንያ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን ሕይወታቸውን እንዳጠፉ ከዘገቧቸው ወጣቶች መካከል ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ምክንያት ከሆኗቸው ነገሮች ውስጥ የጉልበተኞች ጥቃት ተጠቃሽ ነው።

ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

ጉልበተኞች የሚያደርሱት ጥቃት አካላዊ ብቻ አይደለም። የሚከተሉትን ነገሮችም ሊጨምር ይችላል።

  • መጥፎ ንግግር። የ20 ዓመቷ ሴሊን እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ሴቶች ልጆች በጣም የሚጎዳ ነገር ይናገራሉ። ይሰድቡኝና ይናገሩኝ የነበረውን ነገር መቼም አልረሳውም። ዋጋ ቢስ፣ የማልፈለግና የማልረባ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርገውኛል። ከዚህ ሁሉ ቢመቱኝ ይሻለኝ ነበር።”

  • ማግለል። የ18 ዓመቷ ሄሊ እንዲህ ብላለች፦ “አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ያገልሉኝ ጀመር። ምሳ ሰዓት ላይ ከእነሱ ጋር ተቀምጬ እንዳልበላ ሲሉ ጠረጴዛው ላይ ያለው ቦታ ሁሉ እንደተያዘ ያስመስላሉ። ዓመቱን ሙሉ ብቻዬን ለመብላት የተገደድኩ ሲሆን በዚህ የተነሳ አለቅስ ነበር።”

  • ሳይበርቡሊ።a የ14 ዓመቱ ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ኮምፒውተር ላይ ጥቂት ቃላትን በመጻፍ ብቻ! የአንድን ሰው ስም ማጥፋት አልፎ ተርፎም ሕይወቱን ማበላሸት ይቻላል። ነገሩ የተጋነነ ቢመስልም እንኳ እውነታው ይኸው ነው” ሳይበርቡሊ የሚያደርጉ ሰዎች በሞባይል ስልክ አማካኝነትም ጎጂ የሆኑ ፎቶግራፎችን ወይም የጽሑፍ መልእክቶችን ሊልኩ ይችላሉ።

ጉልበተኞች ሌሎችን የሚያስቸግሩት ለምንድን ነው?

ከዋነኞቹ ምክንያቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

  • እነሱ ራሳቸው በሌሎች ጉልበተኞች ጥቃት ደርሶባቸዋል። “እኩዮቼ የሆኑ ልጆች ያስቸግሩኝ ነበር፤ ነገሩ በጣም ስላንገሸገሸኝ ተቀባይነት ለማግኘት ስል ብቻ እኔም ሌሎችን ማስቸገር ጀመርኩ” በማለት አንቶኒዮ የተባለ ወጣት ተናግሯል። “ከጊዜ በኋላ ነገሩን መለስ ብዬ ሳስበው ግን ያደረግሁት ነገር ስህተት መሆኑን ተገነዘብኩ!”

  • ጥሩ አርዓያ የሚሆናቸው ሰው አላገኙም። ጄይ መግሮው ላይፍ ስትራቴጂስ ፎር ዲሊንግ ዊዝ ቡሊስ በተባለው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ጉልበተኛ የሆኑ ትናንሽ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በሌሎች ላይ የሚያደርጉት . . . ወላጆቻቸው፣ ታላላቅ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ወይም ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ሲያደርጉ ያዩትን ነገር ነው።”

  • የሌሎች የበላይ እንደሆኑ ለማሳየት ቢሞክሩም በራሳቸው አይተማመኑም። “በሌሎች ላይ ጉልበተኛ የሚሆኑት ስሜታቸውን የሚጎዳ ነገር ያጋጠማቸው ወይም የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ልጆች ናቸው፤ ይህንን ስሜታቸውን ለመሸፈን ሲሉ በሌሎች ላይ ጉልበተኛ በመሆን የበላይ መስለው ለመታየት ይጥራሉ” በማለት ባርብራ ኮሎሮሶ ዘ ቡሊ፣ ዘ ቡሊድ ኤንድ ዘ ባይስታንደር በተባለው መጽሐፏ ላይ ተናግራለች።

ጉልበተኞች ብዙውን ጊዜ የሚያጠቁት እነማንን ነው?

  • ብቸኛ የሆኑ ልጆችን። አንዳንድ ወጣቶች ከሌሎች ጋር መቀላቀል ስለሚቸግራቸው ብቻቸውን ይሆናሉ፤ በመሆኑም ጉልበተኞች በቀላሉ ያጠቋቸዋል።

  • ከእኩዮቻቸው ለየት ብለው የሚታዩ ልጆችን። አንዳንድ ልጆች በጉልበተኞች ጥቃት የሚደርስባቸው በመልካቸው፣ በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው ሌላው ቀርቶ የአካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ምክንያት ነው፤ ጉልበተኛው በእነሱ ላይ ለማሾፍ ሰበብ የሚሆነውን ማንኛውንም ምክንያት ይጠቀማል።

  • በራሳቸው የማይተማመኑ ልጆችን። ጉልበተኞች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ ልጆችን ማወቅ አይቸግራቸውም። እንደዚህ ያሉት ልጆች ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ብዙውን ጊዜ ዝም ስለሚሉ በቀላሉ ለጉልበተኞች ጥቃት ይጋለጣሉ።

ጉልበተኞች የሚያስቸግሩህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

  • ችላ ብለህ እለፈው። “ጉልበተኞች ስለ ራሳችሁ መጥፎ እንዲሰማችሁ ማድረግ እንደቻሉ ሲያውቁ ደስ ይላቸዋል” በማለት ካይሊ የተባለች ወጣት ተናግራለች። “የሚያደርጉትን ነገር ችላ ብላችሁ የምታልፉት ከሆነ እናንተን ማስቸገር ይሰለቻቸዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋዮች ግን በትዕግሥት ቍጣቸውን ይገታሉ” ይላል።​—ምሳሌ 29:11 የ1980 ትርጉም

  • ብድር አትመልስ። መበቀል ችግሩን ያባብሰው ይሆናል እንጂ መፍትሔ አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ” ይላል።​—ሮም 12:17፤ ምሳሌ 24:19

  • ጥቃት እንዲደርስብህ የሚያደርግ ሁኔታ ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቅ። ከጉልበተኞች እንዲሁም እንዲህ ያሉ ልጆች እንዲያስቸግሩህ መንገድ ከሚከፍቱ ሁኔታዎች በተቻለ መጠን ለመራቅ ጥረት አድርግ።​—ምሳሌ 22:3

  • እነሱ ያልጠበቁትን ምላሽ ስጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” ይላል።​—ምሳሌ 15:1

  • ቀልደህ ለማለፍ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጉልበተኛ በውፍረትህ ቢያሾፍብህ፣ ከመበሳጨት ይልቅ “እንዲያውም አስታወስከኝ፤ ሰሞኑን ስፖርት ልጀምር አስቤያለሁ” ልትለው ትችላለህ።

  • ምንም ምላሽ አትስጥ። የ19 ዓመቷ ኖራ እንዲህ ብላለች፦ “ነገሩን በዝምታ ማለፋችሁ ብስለት እንዳላችሁና ከሚያስቸግራችሁ ሰው የበለጠ ጠንካራ እንደሆናችሁ የሚጠቁም ነው። ከጉልበተኛው በተለየ እናንተ ራሳችሁን መቆጣጠር እንደምትችሉ እያሳያችሁ ነው።”

  • በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር ጥረት አድርግ። “ጉልበተኞች እንደፈራህ በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ፤ ይህን ሲመለከቱ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትህን ይበልጥ ማዳከም ይፈልጋሉ” በማለት ሪታ የተባለች ወጣት ተናግራለች።

  • ጉዳዩን ለሌላ ሰው ተናገር። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ጉልበተኞች በኢንተርኔት ከሚያስቸግሯቸው ልጆች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚደርስባቸውን ነገር ለማንም አይናገሩም፤ ከመናገር ወደኋላ የሚሉት ጉዳዩ ስለሚያሳፍራቸው (በተለይ ወንዶች ልጆች) ወይም ቢናገሩ የባሰ እንደሚሆንባቸው ስለሚፈሩ ነው። ይሁን እንጂ ጉዳዩን በሚስጥር መያዝህ ለጉልበተኞቹ እንደሚመቻቸው አትርሳ። ጥቃቱ እንዲያቆምልህ ከፈለግህ ልትወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ስለ ጉዳዩ ለሌሎች መናገር ነው።

እኩዮችህ የሰጡት ጠቃሚ ምክር

“ጉልበተኞች በቀላሉ እንዲያጠቁህ ከሚጋብዙ ሁኔታዎች ወይም ለእንዲህ ዓይነት ጥቃት ከሚያጋልጡህ ቦታዎች ራቅ። በተጨማሪም ጉልበተኞችም የራሳቸው ችግር እንዳላቸው አስታውስ። ይህን ካሰብህ በሚናገሩት ነገር ያን ያህል አትጎዳም።”​—አንቶኒዮ

“በራስህ ተማመን። ለምታምንበት ነገር አቋም ለመያዝ አትፍራ። ብዙ ጉልበተኞች በአንተ ላይ የበላይ መሆን እንዳልቻሉና እንደማትፈራቸው ሲገነዘቡ አንተን ማስቸገራቸውን ያቆማሉ።”​—ጄሲካ

የአንዲት መምህርት አስተያየት

“ጉልበተኞች የሚያደርሱት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። አስተማሪ እያለሁ ልጆቹ በክፍል ውስጥ እያሉ ይደባደቡ ነበር፤ ሌላው ቀርቶ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳ እንዲህ ያደርጉ ነበር። አንዳንድ ልጆች በሌሎች ላይ ጉልበተኛ መሆናቸው ታዋቂና የበላይ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ስለሚያደርጋቸው ደስ ይላቸዋል።

“ብዙውን ጊዜ፣ ጥቃት የሚደርስባቸው ልጆች ጉዳዩን ቢናገሩ ችግሩ እንደሚብስ ወይም ሌሎቹ ልጆች እንደ ወሬኛ እንደሚቆጥሯቸው በመፍራት የደረሰባቸው ነገር ከመናገር ወደኋላ ይላሉ። አሊያም ደግሞ መናገራቸው ጥቃቱን ለማስቆም እንደማይረዳቸው ያስቡ ይሆናል። እኔ ግን እንዲህ ዓይነት ጥቃት የሚደርስበት ሰው ጉዳዩን ለሌሎች መናገር እንዳለበት ይሰማኛል። እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ከመሆኑም ሌላ ጉልበተኛው ሌሎችን እንዳያስቸግር ለመከላከል ይረዳል።”​—ጄኒሊ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ መምህርት የነበረች

ጉልበተኞች—ጥያቄዎች

እውነት ወይም ሐሰት

  1. በሺህዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊትም ጉልበተኞች ነበሩ።

  2. ጉልበተኞች የሚያደርጉት ነገር ያን ያህል የማይጎዳ ቀልድ ነው።

  3. ጉልበተኞችን ለማስቆም የተሻለው ዘዴ ኃይል መጠቀም ነው።

  4. ጉልበተኞች የሚያስቸግሩህ ከሆነ ጥፋቱ የአንተው ነው።

  5. ጉልበተኞች የሚያስቸግሯቸው አንዳንድ ልጆች እነሱ ራሳቸው በሌሎች ላይ ጉልበተኛ መሆን ይጀምራሉ።

  6. ጉልበተኞች ሌላ ሰውን ሲያስቸግሩ ብታይ የተሻለው እርምጃ ነገሩን እንዳላዩ ማለፍ ነው።

  7. ጉልበተኞች በሌሎች ላይ የበላይ ለመሆን ቢሞክሩም ብዙውን ጊዜ በራስ የመተማመን ስሜት ይጎድላቸዋል።

  8. ጉልበተኞች ሊለወጡ ይችላሉ።

መልስ

  1. እውነት። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኔፊሊም ስለተባሉ ሰዎች ይናገራል፤ የስማቸው ትርጉም “አንስተው የሚያፈርጡ” ማለት ነው።​—ዘፍጥረት 6:4

  2. ሐሰት። ጉልበተኞች የሚያደርሱት ጥቃት የሚያስከትለው ውጤት ሕይወትን የሚነካ ሊሆን ይችላል። በጉልበተኞች ተደጋጋሚ ጥቃት የደረሰባቸው አንዳንድ ልጆች ሕይወታቸውን አጥፍተዋል።

  3. ሐሰት። ብዙውን ጊዜ ጉልበተኞች የሚያስቸግሩት ከእነሱ የሚያንስ ጥንካሬ ያላቸው ልጆችን ነው፤ ስለዚህ ከእነሱ ጋር ግብግብ መፍጠር አያዋጣም።

  4. ሐሰት። ማንም ሰው ቢሆን የጉልበተኞች ጥቃት ሊደርስበት አይገባም! ጥፋተኛው ጥቃቱ የደረሰበት ሰው ሳይሆን ጉልበተኛው ራሱ ነው።

  5. እውነት። የሚያሳዝን ቢሆንም አንዳንዶች፣ ራሳቸው የሚደርስባቸውን ዓይነት ጥቃት በሌሎች ላይ በማድረስ ብስጭታቸውን በእነሱ ላይ ይወጣሉ።

  6. ሐሰት። በጉዳዩ እስካልተካፈልኩ ድረስ እንዳላየሁ ሆኜ ባልፍ ስህተት የለውም ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም። ጉልበተኞች አንድን ሰው ሲያስቸግሩ እያየህ ምንም ባታደርግ የመፍትሔ እርምጃ ስላልወሰድህ ችግሩ እንዲባባስ አስተዋጽኦ አድርገሃል።

  7. እውነት። አንዳንድ ጉልበተኞች ራሳቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ቢሆኑም አብዛኞቹ በራሳቸው አይተማመኑም፤ እንዲያውም ሌሎችን ዝቅ የሚያደርጉት ስለ ራሳቸው ጥሩ እንዲሰማቸው ብለው ነው።

  8. እውነት። ጉልበተኞች እርዳታ ከተደረገላቸው አመለካከታቸውንና ባሕርያቸውን መለወጥ ይችላሉ።​—ኤፌሶን 4:23, 24

a በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ