የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwyp ርዕስ 19
  • ሰውነቴን የምቆርጠው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰውነቴን የምቆርጠው ለምንድን ነው?
  • የወጣቶች ጥያቄ
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰውነትን መቁረጥ ሲባል ምን ማለት ነው?
  • ምክንያቱ ምንድን ነው?
  • እንዲህ ያለ ችግር ካለብሽ ይህን ለማሸነፍ ምን ሊረዳሽ ይችላል?
  • በገዛ አካሌ ላይ ጉዳት የማደርሰው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2006
  • ጥሩ ገንዘብ ያስገኝልኝ የነበረውን ሥራዬን የተውኩበት ምክንያት
    ንቁ!—2010
  • የገዛ አካሌን ከመጉዳት መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2006
  • በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወጣቶችን መርዳት
    ንቁ!—2013
ለተጨማሪ መረጃ
የወጣቶች ጥያቄ
ijwyp ርዕስ 19

የወጣቶች ጥያቄ

ሰውነቴን የምቆርጠው ለምንድን ነው?

  • ሰውነትን መቁረጥ ሲባል ምን ማለት ነው?

  • ምክንያቱ ምንድን ነው?

  • እንዲህ ያለ ችግር ካለብሽ ይህን ለማሸነፍ ምን ሊረዳሽ ይችላል?a

  • ቃለ መጠይቅ

  • ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች

  • ጥቅሶች የምጽፍበት ማስታወሻ

ሰውነትን መቁረጥ ሲባል ምን ማለት ነው?

ሰውነትን መቁረጥ የሚለው አገላለጽ፣ በሰውነት ላይ ሆን ብሎ በስለት ጉዳት የማድረስ ልማድን ያመለክታል። ይህ፣ ራሳቸውን የመጉዳት ልማድ ያላቸው ሰዎች የሚጠቀሙበት አንዱ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች፣ ሰውነታቸውን ሊያቃጥሉ ወይም እስኪበልዝ ድረስ ራሳቸውን ሊመቱ ይችላሉ። በዚህ ርዕስ ላይ የሚብራራው፣ ሰውነትን ስለ መቁረጥ ቢሆንም ነጥቦቹ በሌሎች መንገዶች በሰውነታቸው ላይ ጉዳት ለሚያደርሱ ሰዎችም ይሠራሉ።

እውቀትሽን ፈትሺ፦ እውነት ወይስ ሐሰት?

  1. ሰውነታቸውን የሚቆርጡት ሴቶች ብቻ ናቸው።

  2. ሰውነትን መቁረጥ፣ በዘሌዋውያን 19:28 (የ1980 ትርጉም) ላይ ከሚገኘው “ሰውነታችሁን አትቈራርጡ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር ይጋጫል።

መልስ፦

  1. ሐሰት። ይህ ችግር በአብዛኛው የሚታየው በሴቶች ላይ ቢሆንም አንዳንድ ወንዶችም ሰውነታቸው ይቆርጣሉ ወይም በሌሎች መንገዶች በራሳቸው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ።

  2. ሐሰት። ዘሌዋውያን 19:28 የሚናገረው በጥንት ዘመን ይከናወን ስለነበረ የጣዖት አምልኮ ሥርዓት እንጂ በዚህ ርዕስ ላይ ስለሚብራራው በሰውነት ላይ ጉዳት የማድረስ ልማድ አይደለም። ያም ቢሆን አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን በራሳችን ላይ ጉዳት እንድናደርስ አይፈልግም ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 6:12፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1፤ 1 ዮሐንስ 4:8

ምክንያቱ ምንድን ነው?

እውቀትሽን ፈትሺ፦ ትክክል የሆነው ዓረፍተ ነገር የትኛው ነው?

ሰዎች፣ ሰውነታቸውን የሚቆርጡት . . .

  1. ሀ. በውስጣቸው ያለውን የስሜት ሥቃይ እንደሚያስታግሥላቸው ስለሚያስቡ ነው።

  2. ለ. ሕይወታቸውን ለማጥፋት አስበው ነው።

መልስ፦ ሀ. ሰውነታቸውን የሚቆርጡ አብዛኞቹ ሰዎች መሞት አይፈልጉም። ይህን የሚያደርጉት በውስጣቸው የሚሰማቸውን ሥቃይ ለማስቆም ስለሚፈልጉ ነው።

ሰውነታቸውን የመቁረጥ ልማድ የነበራቸው አንዳንድ ወጣቶች የተናገሩትን ተመልከቺ።

ሲልያ፦ “እፎይ እንድል ያደርገኝ ነበር።”

ታማራ፦ “ከሥቃዩ የሚገላግለኝ ይመስለኝ ነበር። በውስጤ ከሚሰማኝ ሥቃይ ይልቅ ሰውነቴ መቆረጡ የሚያስከትለውን ሕመም እመርጥ ነበር።”

ካሪ፦ “የሚሰማኝን የሐዘን ስሜት በጣም እጠላው ነበር። ሰውነቴን ስቆርጥ፣ ስለ ሐዘኔ ማሰቤን ትቼ ቁስሉ በሚያስከትልብኝ ሕመም ላይ አተኩራለሁ።”

ጄሪን፦ “ሰውነቴን መቁረጤ በዙሪያዬ ያለውን ነገር ለመርሳት ያስችለኛል፤ እንዲህ ሳደርግ፣ ችግሮቼን መጋፈጥ እንደሌለብኝ ይሰማኛል። ትኩረቴ በሌላ ነገር ላይ እንዲያርፍ ስለሚያደርግ ደስ ይለኛል።”

እንዲህ ያለ ችግር ካለብሽ ይህን ለማሸነፍ ምን ሊረዳሽ ይችላል?

ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለይ፣ ችግሩን ለማሸነፍ ከፍተኛ እገዛ ያደርግልሻል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል” ይላል።​—1 ጴጥሮስ 5:7

እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ ችግሩን ለማሸነፍ መጀመሪያ አካባቢ አጠር ያለ ጸሎት ማቅረብ እንኳ በቂ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ “ይሖዋ፣ እባክህ እርዳኝ” ማለት ትችያለሽ። እያደር ግን፣ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ለሆነው ለይሖዋ በልብሽ ያለውን በሙሉ አውጥተሽ መናገር ትችያለሽ።​—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

ጸሎት፣ ለሚሰማሽ ሥቃይ ጊዜያዊ ማስታገሻ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም። በሰማይ ለሚኖረው አባትሽ የልብሽን አውጥተሽ መናገር የምትችዪበት መንገድ ነው፤ እሱ እንዲህ ብሎ ቃል ገብቶልናል፦ “እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።”​—ኢሳይያስ 41:10

ሰውነታቸውን የመቁረጥ ችግር ያለባቸው ብዙዎች፣ የሚሰማቸውን ነገር ለወላጆቻቸው ወይም ለሚተማመኑበት ሌላ አዋቂ ሰው መናገራቸው እንዲጽናኑ ረድቷቸዋል። እንዲህ ያደረጉ ሦስት ወጣቶች ከዚህ በታች የተናገሩትን ሐሳብ እንድታነብቢ እንጋብዝሻለን።

ቃለ መጠይቅ

  • ዳያና፣ 21

  • ካቲ፣ 15

  • ሎሬና፣ 17

ሰውነታችሁን መቁረጥ ስትጀምሩ ስንት ዓመታችሁ ነበር?

ሎሬና፦ ይህን ማድረግ የጀመርኩት በ14 ዓመቴ ገደማ ነበር።

ዳያና፦ በወቅቱ 18 ዓመቴ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ወይም ለሁለት ሳምንት ያህል በየቀኑ ሰውነቴን እቆርጥ ነበር፤ ከዚያ ደግሞ ጨርሶ እንዲህ ሳላደርግ አንድ ወር ያህል ያልፋል።

ካቲ፦ የጀመርኩት በ14 ዓመቴ ነው። ችግሩ አሁንም አልፎ አልፎ ያገረሽብኛል።

ራሳችሁን መጉዳት የምትፈልጉት ለምን ነበር?

ካቲ፦ ራሴን እጠላው ነበር። ማንም ሰው ጓደኛው ሊያደርገኝ እንደማይፈልግ ይሰማኝ ነበር።

ዳያና፦ አንዳንድ ጊዜ፣ የሚሰማኝ ሐዘን እየበረታ ሲሄድ በጭንቀት እዋጣለሁ። ጭንቀቱ እየባሰ ይሄድና ከአቅሜ በላይ ይሆንብኛል። አንድ ትልቅ አውሬ በውስጤ ሆኖ የሚታገለኝ ያህል ይሰማኛል፤ ይህ አውሬ ከውስጤ እንዲወጣ መፍትሔው ሰውነቴን መቁረጥ እንደሆነ አስባለሁ።

ሎሬና፦ በጭንቀትና በሐዘን እዋጥ እንዲሁም በራሴ እበሳጭ ነበር። ፈጽሞ የማልረባ እንደሆንኩ ስለሚሰማኝ በውስጤ የሚታገለኝን መጥፎ ስሜት ለመገላገል እፈልግ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አካላዊ ሥቃይ ሊደርስብኝ እንደሚገባ አስብ ነበር።

ራሳችሁን መጉዳታችሁ፣ ቀለል እንዲላችሁ ይረዳችሁ ነበር?

ዳያና፦ አዎ። ከላዬ ላይ ከባድ ሸክም የወረደልኝ ያህል ተንፈስ እላለሁ።

ካቲ፦ ልክ እንደ ማልቀስ ነው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ሰዎች በደንብ ካለቀሱ በኋላ ሐዘናቸው እንደሚወጣላቸው ሁሉ እኔም ሰውነቴን ስቆርጥ ቀለል ይለኛል።

ሎሬና፦ በሰውነቴ ላይ ጉዳት ማድረስ፣ በውስጤ የታመቀውን መጥፎ ስሜት ለማስተንፈስ ይረዳኛል፤ ሁኔታው አንድን የተወጠረ ፊኛ ከመብሳት ጋር ይመሳሰላል። ፊኛው ከመፈንዳት ይልቅ ቀስ በቀስ እየተነፈሰ ይሄዳል፤ እኔም ሰውነቴ ላይ ጉዳት ሳደርስ በውስጤ የታፈነው መጥፎ ስሜት ቀስ እያለ ይወገዳል።

ስለ ችግራችሁ ለሌላ ሰው መናገር ያስፈራችሁ ነበር?

ሎሬና፦ አዎ። ‘ሰዎች ስለ ችግሬ ቢያውቁ ስለ እኔ ምን ያስባሉ’ የሚለው ሐሳብ ያስፈራኝ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ሌሎች ስለ ግል ሕይወቴ እንዲያውቁ አልፈለግሁም።

ዳያና፦ ሰዎች፣ ጠንካራ እንደሆንኩ ሁልጊዜ ይነግሩኝ ነበር፤ እኔም ይህ አመለካከታቸው እንዲለወጥ አልፈለግሁም። እርዳታ መጠየቅ ሽንፈት እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።

ካቲ፦ ችግሬን ብናገር ሰዎች፣ ከባድ የስሜት ቀውስ እንዳለብኝ ይሰማቸዋል ብዬ እሰጋ ነበር፤ እንደዚያ ብለው ማሰባቸው ደግሞ ስለ ራሴ ይበልጥ መጥፎ እንዲሰማኝ ያደርገኛል። ከዚህም ሌላ በራሴ ላይ ጉዳት በማድረስ ራሴን መቅጣት እንዳለብኝ አስብ ነበር።

በሰውነታችሁ ላይ ጉዳት ማድረሳችሁን እንድታቆሙ የረዳችሁ ምንድን ነው?

ሎሬና፦ ስለ ችግሬ ለእናቴ ነገርኳት። ከዚህም ሌላ አንዲት ሐኪም በውስጤ ያለውን መጥፎ ስሜት መቋቋም እንድችል ረዳችኝ። ችግሩ እንደገና ያገረሸብኝ ጊዜ ነበር፤ ያም ቢሆን ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም እንዲኖረኝ ጥረት ማድረጌ ረድቶኛል። በክርስቲያናዊ አገልግሎትም በንቃት እካፈላለሁ። እርግጥ ነው፣ አልፎ አልፎ ብቅ እያለ ከሚያስቸግረኝ የዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር ሁልጊዜ መታገል ይኖርብኝ ይሆናል፤ ያም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ ስሜት እንዲቆጣጠረኝ አልፈቅድም።

ካቲ፦ አሥር ዓመት ገደማ የምትበልጠኝ አንዲት ክርስቲያን፣ አንድ ችግር እንዳለብኝ አስተዋለች፤ ውሎ አድሮም ችግሬን ለእሷ ማማከር ጀመርኩ። ይህች እህት በአንድ ወቅት ሰውነቷን የመቁረጥ ችግር እንደነበረባት ሳውቅ ተገረምኩ። እሷ ራሷም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስላለፈች የውስጤን አውጥቼ ለእሷ መናገር አልከበደኝም። ከዚህም ሌላ አንዲት ሐኪም፣ እኔም ሆንኩ ወላጆቼ ስለ ችግሩ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረን ረዳችን።

ዳያና፦ አንድ ምሽት፣ የምተማመንባቸው አንድ ባልና ሚስት ጋ እያለሁ ባልየው የሆነ ችግር እንዳለብኝ አስተዋለ። የሚያስጨንቀኝን ነገር እንድነግራቸው በደግነት አበረታታኝ። ትንሽ ልጅ እያለሁ እናቴ ታቅፈኝ እንደነበረው ባለቤቱም እቅፍ አደረገችኝ። በዚህ ጊዜ ማልቀስ ጀመርኩ፤ እሷም አብራኝ አለቀሰች። በራሴ ላይ ሳደርግ የነበረውን ነገር ለእነሱ መንገር በጣም ቢከብደኝም ነገርኳቸው፤ ይህን በማድረጌም ደስተኛ ነኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ የረዳችሁ እንዴት ነው?

ዳያና፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ያለብኝን ችግር በራሴ ልወጣው እንደማልችል እንድገነዘብ ረድቶኛል። የይሖዋ አምላክ እርዳታ የግድ ያስፈልገኛል።​—ምሳሌ 3:5, 6

ካቲ፦ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤና በውስጡ ያለው መልእክት ከአምላክ የመጣ መሆኑን መገንዘቤ በጣም ያጽናናኛል!​—2 ጢሞቴዎስ 3:16

ሎሬና፦ ልቤን የሚነኩ ጥቅሶች ሳገኝ፣ በሌላ ጊዜ እንዳሰላስልባቸው ስል በማስታወሻዬ ላይ እጽፋቸዋለሁ።​—1 ጢሞቴዎስ 4:15

ከሁሉ የበለጠ የረዳችሁ ጥቅስ የትኛው ነው?

ዳያና፦ ምሳሌ 18:1 “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” ይላል። አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር መሆን ይከብደኛል፤ ይሁንና ይህ ጥቅስ ራስን ማገለል አደገኛ መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል።

ካቲ፦ በጣም የምወደው ጥቅስ ማቴዎስ 10:29 እና 31 ነው፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ፣ አንዲት ድንቢጥ እንኳ ይሖዋ አምላክ ሳያውቅ እንደማትሞት ገልጿል። አክሎም “አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ” ብሏል። አሁንም እንኳ ይህን ጥቅስ ማንበቤ በይሖዋ ዘንድ ውድ እንደሆንኩ እንዳስታውስ ይረዳኛል።

ሎሬና፦ በኢሳይያስ 41:9, 10 ላይ የሚገኘውን ይሖዋ ለሕዝቡ የተናገረውን ሐሳብ እወደዋለሁ፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አልጣልሁህም። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ . . . አበረታሃለሁ።” ይህ ጥቅስ ኃይል ይሰጠኛል፤ ይሖዋ እንደሚወድደኝና ምንጊዜም ከአጠገቤ እንደሆነ እንዲሰማኝ ያደርገኛል።

ልታስቢባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች

  • የሌሎችን እርዳታ ለመጠየቅ ስትፈልጊ ማንን ማነጋገር ትችያለሽ?

  • ያለብሽን ችግር በተመለከተ ወደ ይሖዋ አምላክ ምን ብለሽ መጸለይ ትችያለሽ?

  • ጭንቀትሽ ቀለል እንዲልሽ የሚረዱ ሁለት መንገዶችን (በራስ ላይ ጉዳት ማድረስን ሳይጨምር) መጥቀስ ትችያለሽ?

ጥቅሶች የምጽፍበት ማስታወሻ

እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ ይሖዋ እንደሚወድሽ የሚያረጋግጥልሽ ወይም ስለ ራስሽና ስላሉብሽ ድክመቶች ሚዛናዊ አመለካከት እንድትይዢ የሚረዳሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ስታገኚ በማስታወሻ ደብተር ላይ ጻፊው። ጥቅሱ የሚረዳሽ እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ አጠር ያለ ሐሳብ አስፍሪ። ዳያናን፣ ካቲንና ሎሬናን የረዷቸው ጥቅሶች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

  • ሮም 8:38, 39

    “ይህ ጥቅስ፣ በጣም መጥፎ ስሜት በሚሰማኝ ወቅትም እንኳ ይሖዋ እንደሚወደኝ እንዳስታውስ ይረዳኛል።”​—ዳያና

  • መዝሙር 73:23

    “እንዲህ ያሉ ጥቅሶች ብቻዬን እንዳልሆንኩ እንድተማመን ይረዱኛል። ይሖዋ አጠገቤ ያለ ያህል ይሰማኛል።”​—ካቲ

  • 1 ጴጥሮስ 5:10

    “ከችግራችን ወዲያውኑ መገላገል አንችል ይሆናል፤ ‘ለጥቂት ጊዜ’ መከራ መቀበላችን የማይቀር ነው። ይሁንና ይሖዋ ማንኛውንም ነገር በጽናት መቋቋም እንድንችል ያጠነክረናል።”​—ሎሬና

ልታስቢባቸው የሚገቡ ተጨማሪ ጥቅሶች

  • መዝሙር 34:18

  • መዝሙር 54:4

  • መዝሙር 55:22

  • ኢሳይያስ 57:15

  • ማቴዎስ 11:28, 29

a በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ