ኤልፍሪደ ኧርባን | የሕይወት ታሪክ
በሚስዮናዊነት አገልግሎት ያሳለፍኩት አርኪ ሕይወት
የሕይወቴ የመጀመሪያ ዓመታት በመከራ የተሞሉ ነበሩ። የተወለድኩት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ ከሁለት ወራት በኋላ ታኅሣሥ 11, 1939 በቼኮስሎቫኪያ ነው። እናቴ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የጤና እክል የተነሳ ከተወለድኩ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሞተች። ከዚያ አስቀድሞ አባቴ ሥራ ፍለጋ ወደ ጀርመን ሄዶ ነበር። ደስ የሚለው፣ የእናቴ ወላጆች ወስደው አሳደጉኝ። በወቅቱ አያቶቼ የእናቴን ሦስት ታናናሽ እህቶች ማለትም አክስቶቼን እያሳደጉ ነበር።
ከአያቶቼ ጋር
ጦርነቱ በ1945 አበቃ፤ ሆኖም ሕይወት ከጦርነቱ በኋላም በጣም ከባድ ነበር። ጀርመናውያን ስለሆንን ከቼኮስሎቫኪያ ተባረን ወደ ጀርመን ተላክን። የጀርመን ከተሞች ፈራርሰው የነበረ ሲሆን ሕዝቡም በድህነት ይማቅቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ አክስቶቼ በጣም ትንሽ ምግብ ለማግኘት ሲሉ ሌሊቱን ሙሉ ተሰልፈው ያድሩ ነበር። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ጫካ ውስጥ ገብተን እንጆሪና እንጉዳይ በመልቀም በዳቦ እንቀይረው ነበር። ምግብ ከመጥፋቱ የተነሳ እንደ ውሻና ድመት ያሉ የቤት እንስሳት በድንገት ይሰወሩ ነበር፤ ምክንያቱም ሰዎች ሰርቀው ይበሏቸዋል። ብዙውን ጊዜ የምናድረው ጦማችንን ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያገኘንበት መንገድ
አያቶቼ ካቶሊክ ነበሩ፤ ግን መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረንም። የቤተ ክርስቲያናችን ቄስ ለአያቴ መጽሐፍ ቅዱስ ለመሸጥ ፈቃደኛ አልነበረም፤ ምዕመናን ቅዳሴ ካዳመጡ በቂ እንደሆነ ነገረው። በዚህም የተነሳ አያቴ ስለ አምላክ ለነበሩት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አልቻለም።
የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጡ። አያቴ ስለ ሥላሴ፣ ስለ ገሃነመ እሳት፣ ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ስለመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ያሉትን ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመው መለሱለት። አያቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘው መልስ ግልጽና አጥጋቢ እንደሆነ ተሰማው። እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ ሆነ። በመሆኑም መላው ቤተሰባችን ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማጥናት ጀመረ።
ሕይወቴን የምመራበት ግብ አወጣሁ
ገና ከትንሽነቴ አንስቶ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ነበረኝ። ርቀው በሚገኙ የዓለም ክፍሎች ይሖዋን ስለሚያገለግሉ ሚስዮናውያን የሚናገሩ ተሞክሮዎችን ማንበብ ያስደስተኝ ነበር። ‘ሕይወታቸው ምን ይመስላል? የይሖዋን ስም ሰምተው ለማያውቁ ሰዎች መስበክ ምን ስሜት ይፈጥራል?’ እያልኩ አስብ ነበር።
በሚስዮናዊነት ለማገልገል ግብ ከማውጣቴ ከተወሰነ ጊዜ በፊት
አሥራ ሁለት ዓመት ሲሆነኝ ሚስዮናዊ ለመሆን ወሰንኩ፤ እዚያ ግብ ላይ ለመድረስም ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። በመጀመሪያ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ለመሆን ጥረት አደረግኩ። ከዚያም ታኅሣሥ 12, 1954 ተጠመቅኩ፤ በኋላም አቅኚ ሆንኩ። በዚህ መንገድ ወደ ግቤ እየተጠጋሁ ሄድኩ!
ለሚስዮናውያን በተዘጋጀው የጊልያድ ትምህርት ቤት ለመካፈል እንግሊዝኛ መቻል እንዳለብኝ ስለተገነዘብኩ ቋንቋውን ለመማር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ። በወቅቱ በጀርመን ከነበሩት የአሜሪካ ወታደሮች ጋር በመነጋገር የቋንቋ ችሎታዬን ማሻሻል እንደምችል ተሰማኝ። አንድ ቀን ወደ አንድ ወታደር ቀረብ ብዬ “ክርስቶስ ነኝ” አልኩት። እሱም አየት አደረገኝና በደግነት “‘ክርስቲያን ነኝ’ ማለት ነው የፈለግሽው?” አለኝ። ለካስ በእንግሊዝኛ ያሰብኩትን ያህል ጎበዝ አልነበርኩም!
በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳለሁ ወደ እንግሊዝ ተዛወርኩ፤ በዚያም አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ጠዋት ጠዋት በሞግዚትነት እንድሠራ ቀጠሩኝ። ከሰዓት በኋላ ደግሞ ከቤት ወደ ቤት እሰብክ ነበር፤ ይህም እንግሊዝኛዬን ለማሻሻል ጥሩ አጋጣሚ ሰጠኝ። አንድ ዓመት እንግሊዝ ካገለገልኩ በኋላ የቋንቋ ችሎታዬ በእጅጉ ተሻሻለ።
ወደ ጀርመን ከተመለስኩ በኋላ ጥቅምት 1966 በሜከርኒሽ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ሆኖም በዚያ ክልል የነበሩት ሰዎች ለመልእክታችን የሚሰጡት ምላሽ የአየሩን ያህል ቀዝቃዛ ነበር። ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች በነበረበት ጊዜ እንኳ ወደ ቤታቸው እንድንገባ ጋብዘውን አያውቁም። በዚህም የተነሳ “ሚስዮናዊ ሆኜ እንዳገለግል ከፈቀድክልኝ እባክህ ወደ ሞቃት አገር ላከኝ” እያልኩ አዘውትሬ ወደ ይሖዋ እጸልይ ነበር።
ግቤ ላይ ደረስኩ
ለጥቂት ወራት በልዩ አቅኚነት ካገለገልኩ በኋላ ይሖዋ የልቤን መሻት ሰጠኝ! በጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት 44ኛ ክፍል እንድማር ተጋበዝኩ፤ የተመረቅነው መስከረም 10, 1967 ነበር። የት የተመደብኩ ይመስላችኋል? በማዕከላዊ አሜሪካ በምትገኘው ውብና ሞቃት በሆነችው ኒካራጓ ነው! በዚያ የነበሩት ሚስዮናውያን ለእኔና ለሦስት የአገልግሎት ጓደኞቼ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልን። ሐዋርያው ጳውሎስ እሱን ለማግኘት የመጡትን ወንድሞች ሲያይ ‘አምላክን እንዳመሰገነና እንደተበረታታ’ ሁሉ እኔም እንደዚያው ተሰማኝ።—የሐዋርያት ሥራ 28:15
በጊልያድ ትምህርት ቤት (በስተ ግራ ያለሁት እኔ ነኝ)፣ አብረውኝ ከተማሩት ከፍራንሲስና ከማርጋሬት ሺፕሊ ጋር
ሊዮን በተባለች የተረጋጋች ከተማ እንዳገለግል ተመደብኩ። በተቻለኝ ፍጥነት ስፓንኛ ለመማር ቆርጬ ነበር። ለሁለት ወራት ያህል በቀን ለ11 ሰዓት ያህል ቋንቋውን ሳጠና ብቆይም ስፓንኛ መማር ከብዶኝ ነበር!
አንድ ቀን አገልግሎት ላይ ያገኘኋት ሴት ፍሬስኮ የተባለ ከፍራፍሬ የተዘጋጀ መጠጥ እንድጠጣ ጋበዘችኝ። እኔም “የተጣራ ውኃ ብቻ ነው የምጠጣው” ብዬ መለስኩላት። ሴትየዋ ግን ግራ ተጋባች። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ እንደተገነዘብኩት ለካስ በተሰባበረ ስፓንኛ “ጠበል” ብቻ እንደምጠጣ ነው የነገርኳት! ደስ የሚለው፣ ውሎ አድሮ ስፓንኛዬ እየተሻሻለ ሄደ።
ለ17 ዓመት በሚስዮናዊነት አብራኝ ካገለገለችው ከማርገሪት ጋር
በቤተሰብ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናቸው ብዙ ጥናቶች ነበሩኝ። ሊዮን ሰላማዊ ከተማ ስለነበረች ምሽት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ያስደስተኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ጥናት እመራለሁ። የከተማውን ሰው ሁሉ በስም አውቃለሁ ማለት ይቻላል። ወደ ቤቴ ስመለስ፣ በረንዳቸው ላይ ቁጭ ብለው የምሽቱን ነፋስ ከሚያጣጥሙት ጎረቤቶቼ ጋር ሰላም እባባልና እጨዋወት ነበር።
ሊዮን ሳለሁ ብዙዎች እውነትን እንዲማሩ ረድቻለሁ። ከእነሱ መካከል አንዷ፣ የስምንት ወንዶች ልጆች እናት የሆነችው ኑቢያ ነች። በ1976 ማናጓ እስከተመደብኩበት ጊዜ ድረስ አስጠንቻታለሁ። ከኑቢያና ከልጆቿ ጋር ለ18 ዓመት ያህል አልተገናኘንም ነበር። ከዚያም ለስብሰባ ሊዮን በሄድኩበት ወቅት ምሳ ሰዓት ላይ በርካታ ወጣት ወንድሞች መጥተው ከበቡኝ። ለካስ የኑቢያ ልጆች ናቸው! ኑቢያ ልጆቿን እውነት ውስጥ በማሳደግ ረገድ ስለተሳካላት በጣም ተደሰትኩ።
በአደገኛ ጊዜ በሚስዮናዊነት ማገልገል
በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ኒካራጓ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ነውጥ መታመስ ጀመረች። የቻልነውን ያህል እንሰብክ ነበር። በተመደብኩበት ክልል ማለትም ከመዲናዋ በስተ ደቡብ በምትገኘው በማሳያ ብዙውን ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍና የትጥቅ ትግል ይካሄድ ነበር። አንድ ምሽት የጉባኤ ስብሰባ እያደረግን ሳለ በሳንዲኒስታ ተዋጊዎችና በመንግሥት ወታደሮች መካከል ተኩስ በመከፈቱ ተባራሪ ጥይት እንዳይመታን በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ መሬት ላይ መተኛት ነበረብን።a
ሌላ ቀን ደግሞ አገልግሎት ላይ ሳለሁ ፊቱን የተሸፋፈነ የሳንዲኒስታ ተዋጊ በአንድ ወታደር ላይ ሲተኩስ አየሁ። ለመሸሽ ሞከርኩ፤ ሆኖም ፊታቸውን የተሸፈኑ ብዙ ሰዎች መጡ። መንገድ ቀይሬ ለማምለጥ ሞክሬ ነበር፤ ግን ወዴትም መሸሽ አልቻልኩም። ከመንግሥት ሄሊኮፕተሮች የጥይት ናዳ መዝነብ ጀመረ። በድንገት አንድ ሰው የቤቱን በር ከፍቶ ወደ ውስጥ ጎትቶ አስገባኝ። ይሖዋ ራሱ እንዳዳነኝ ተሰማኝ!
ከአገሪቱ ተባረርኩ!
በማሳያ ያገለገልኩት እስከ መጋቢት 20, 1982 ነበር፤ ያን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም። በዚያ ቀን ማለዳ ላይ ከአምስት ሚስዮናዊ ጓደኞቼ ጋር ሆነን ቁርስ ልንበላ ስንል የተወሰኑ የሳንዲኒስታ ተዋጊዎች ከባድ መሣሪያ ይዘው ወደ ሚስዮናውያን ቤታችን መጡ። ተንደርድረው ወደ መመገቢያ ክፍላችን ከገቡ በኋላ አንደኛው እንዲህ ሲል አዘዘን፦ “አንድ ሰዓት እሰጣችኋለሁ፤ እያንዳንዳችሁ አንድ አንድ ሻንጣ ሸክፋችሁ ተከተሉን።”
ወታደሮቹ ወደ አንድ እርሻ የወሰዱን ሲሆን በዚያም ለበርካታ ሰዓታት አቆዩን። ከዚያም አራታችንን በትንሽ አውቶቡስ ወደ ኮስታ ሪካ ድንበር ወስደው ከአገሪቱ አባረሩን። ቀስ በቀስ፣ በድምሩ 21 ሚስዮናውያን ከአገሪቱ ተባረሩ።
በኮስታ ሪካ የሚኖሩት ወንድሞች ጥሩ አቀባበል አደረጉልን። በቀጣዩ ቀን በሳን ሆዜ ወዳለው ቅርንጫፍ ቢሮ ደረስን። እዚያ ብዙ አልቆየንም። ከአሥር ቀን ገደማ በኋላ ስምንታችን በሆንዱራስ አዲስ ምድብ ተሰጠን።
በሆንዱራስ ማገልገል
ሆንዱራስ ሳለሁ በቴጉሲጋልፓ እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያ ባገለገልኩባቸው 33 ዓመታት ውስጥ አንዱ ጉባኤ አድጎ ስምንት ጉባኤዎችን አፍርቷል። የሚያሳዝነው ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በቴጉሲጋልፓ ወንጀል እየተበራከተ መጣ። ብዙ ሌቦች ነበሩ፤ እኔንም ብዙ ጊዜ ዘርፈውኛል። በተጨማሪም የወሮበሎች ቡድን አባላት ‘ገንዘብ አምጪ’ ይሉኝ ነበር፤ ገንዘቡን “የጦርነት ግብር” ብለው ይጠሩታል። እኔም “ከገንዘብ የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር አለኝ” እላቸውና ትራክት ወይም መጽሔት እሰጣቸዋለሁ። እንደዚህ ስላቸው ወዲያውኑ ይለቁኛል!
አብዛኞቹ የቴጉሲጋልፓ ነዋሪዎች ሰላማዊና ደግ ነበሩ። ከእነሱ መካከል የተወሰኑት እውነትን እንዲማሩ ረድቻለሁ። ለምሳሌ ቤቲ የተባለች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ጥሩ እድገት እያደረገች ነበር። ሆኖም አንድ ቀን፣ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን እንዳሰበች ነገረችኝ። በወቅቱ በጣም አዝኜ ነበር፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ቤቲ ቤተ ክርስቲያኑን ለቃ በመውጣት ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን ቀጠለች። ለምንድን ነው የተመለሰችው? በጉባኤ ውስጥ ያለው እውነተኛ ፍቅር ስለናፈቃት ነው። (ዮሐንስ 13:34, 35) “እናንተ ሀብታም ድሃ ሳትሉ ሁሉንም ሰው ሞቅ አድርጋችሁ ትቀበላላችሁ። በጣም የተለያችሁ ናችሁ” አለችኝ። ከጊዜ በኋላ ቤቲ ተጠመቀች።
በቴጉሲጋልፓ የነበረው የሚስዮናውያን ቤት በ2014 ተዘጋ። ከዚያም በፓናማ እንዳገለግል ተመደብኩ። አሁን የምኖረው ረጅም ዓመታት በሚስዮናዊነት አገልግሎት ከተካፈሉ አራት ሚስዮናውያን ጋር ነው።
መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ እውነተኛ ደስታ ያስገኛል
በሚስዮናዊነት አገልግሎት መካፈል ከጀመርኩ አሁን 55 ዓመት ገደማ ሆኖኛል። እርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለብኝ የጤና ችግር የተነሳ የቀድሞውን ያህል ማገልገል አልችልም። ሆኖም ይሖዋ ሌሎችን ስለ እሱ ማስተማሬን እንድቀጥል ረድቶኛል።
ሕይወቴን ሌላ ነገር ለማከናወን ልጠቀምበት እችል ነበር? አዎ። ግን በጣም ብዙ በረከት ያመልጠኝ ነበር! መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ የረዳኋቸው ከ50 በላይ መንፈሳዊ ልጆች አሉኝ፤ ብዙ ጓደኞችም አፍርቻለሁ። ከዚህ “ታላቅ ቤተሰብ” በተጨማሪ በጀርመን የምትኖረው ውዷ አክስቴ ስቴፊም አለች፤ የእሷ ፍቅርና ድጋፍ አልተለየኝም።
ትዳር ባልመሠርትም ብቸኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም። ይሖዋ ምንጊዜም አብሮኝ ነው። እንደ ማርገሪት ፎስተር ያሉ ግሩም ጓደኞችም አፍርቻለሁ፤ ከማርገሪት ጋር ለ17 ዓመት በሚስዮናዊነት አብረን አገልግለናል። ብዙ ነገር አብረን አሳልፈናል፤ እስካሁን ድረስ የቅርብ ጓደኛሞች ነን።—ምሳሌ 18:24
በመላው ሕይወቴ ይሖዋን በማገልገል ዕድሜዬን ከሁሉ በተሻለ መንገድ በመጠቀሜ በጣም ደስተኛ ነኝ። የልጅነት ሕልሜን አሳክቻለሁ፤ ብዙ ግሩም ተሞክሮዎችም አግኝቻለሁ! እውነተኛ ደስታ አግኝቻለሁ። ለዘላለም ይሖዋን የማገለግልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።
a የሳንዲኒስታ ነፃ አውጪ ግንባር በ1970ዎቹ በኒካራጓ ተወዳጅነት አትርፎ ነበር፤ ውሎ አድሮም ከ40 ዓመታት በላይ አገሪቱን ያስተዳደረውን ሥርወ መንግሥት መገልበጥ ችሏል።