ዋረን ሬኖልድስ | የሕይወት ታሪክ
ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና በመምረጤ ደስተኛ ነኝ
በሰሜን ምዕራብ አውስትራሊያ ርቆ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ከተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር እሳት አንድደን ተቀምጠናል፤ በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን በረከት ስላየንባቸው አጋጣሚዎች እየተጨዋወትን ነው። ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር እንዲህ ያለ ጊዜ ሳሳልፍ የመጀመሪያዬ አይደለም፤ ልዩነቱ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ጊዜ ያሳለፍኩት ከአውስትራሊያ ውጭና ሌላ ቋንቋ ከሚናገሩ ሰዎች ጋር መሆኑ ነው። ከሚነደው እሳት ባሻገር በፈገግታ የተሞላው የውዷ ባለቤቴ ፊት ይታየኛል። እኔና እሷ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል፤ ወጣት ሳለሁ እንዲህ ባሉ ቦታዎች አገለግላለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም። እንዲያውም ከዚህ በጣም የተለየ የሕይወት ጎዳና የምመርጥበት አጋጣሚ ነበረኝ። እስቲ ታሪኬን ላጫውታችሁ።
ያደግኩት በገጠሪቷ አውስትራሊያ ነው። በ1950ዎቹ ወላጆቼና አያቶቼ እውነትን ሰሙ። በ6 ዓመቴ መስበክ ጀመርኩ፤ ከዚያም በ13 ዓመቴ ተጠመቅኩ። ትምህርት ቤት ሲዘጋ በአብዛኛው ረዳት አቅኚ ሆኜ አገለግላለሁ። ይሖዋን ስለምወደው እሱን ለዘላለም የማገልገል ፍላጎት ነበረኝ።
ከወላጆቼና ከአራት ወንድሞቼ ጋር
በ15 ዓመቴ የትምህርት ቤታችን የስፖርት አሠልጣኞች ጥሩ ብቃት እንዳለኝ አስተዋሉ። በዚህም የተነሳ የአንድ ታዋቂ የራግቢ ቡድን ተወካዮች ነፃ የትምህርት ዕድል ሊሰጡኝ ግብዣ አቀረቡልኝ። ታዋቂ የራግቢ ተጨዋች ልሆን እንደምችል ሳስበው ደስ አለኝ፤ ግን ደግሞ ራሴን ለይሖዋ ወስኛለሁ። አባቴ በስፖርቱ መስክ ለመሰማራት ከመወሰኔ በፊት ራሴን ለይሖዋ ስወስን በገባሁት ቃል ላይ እንዳሰላስል ሐሳብ አቀረበልኝ። እኔም እንዳለኝ አደረግኩ፤ በዚህ ጊዜ በሁለቱም ነገሮች ስኬታማ ልሆን እንደማልችል ስለተገነዘብኩ ግብዣውን እንደማልቀበል ነገርኳቸው። ከወራት በኋላ በካንቤራ የሚገኘው የአውስትራሊያ የስፖርት ተቋም ሌላ ነፃ የትምህርት ዕድል አቀረበልኝ፤ ይህን ግብዣ ከተቀበልኩ የማራቶን ተወዳዳሪ ሆኜ መሠልጠን እንዲሁም በኮመንዌልዝ አገራት መካከል በሚደረጉ ውድድሮች ወይም ኦሎምፒክ ላይ አውስትራሊያን ወክዬ መሳተፍ እችላለሁ። ሆኖም ለምወደው አምላክ የገባሁትን ቃል የመፈጸም ልባዊ ፍላጎት ስለነበረኝ በዚህ ወቅትም ቢሆን መልሴ ተመሳሳይ ነበር።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ትምህርቴን ጨርሼ ለረጅም ጊዜ ስመኝ የነበረውን የአቅኚነት አገልግሎቴን ጀመርኩ። ሆኖም ቤተሰቦቼ የገንዘብ ችግር ስለገጠማቸው አቅኚነቴን አቁሜ ሙሉ ጊዜዬን የትራክተር ሹፌር ሆኜ ተቀጠርኩ። በወቅቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ነበርኩ፤ የምኖረውም ብቻዬን ነበር። ብዙም ሳይቆይ አምልኮዬ የዘልማድ ሆነ። ተስፋ እየቆረጥኩና በመንፈሳዊ እየተዳከምኩ መጣሁ። ከዚያም ብዙ ከሚጠጡና ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ጓደኞች ጋር በመግጠም ጥበብ የጎደለው ምርጫ አደረግኩ፤ ይህም የእነሱን አካሄድ የመከተል ምኞት እንዲያድርብኝ አደረገ። ከይሖዋ ጋር ያለኝን ግንኙነት ችላ በማለት ጊዜያዊ ደስታ ማሳደድ ጀመርኩ።
የትኩረት አቅጣጫዬን ማስተካከል ነበረብኝ፤ ስለዚህ የቀድሞ ጓደኞቼን ወደማላገኝበት ሩቅ አካባቢ ተዛወርኩ። ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ጥረት ያደረግኩ ከመሆኑም ሌላ ያቋረጥኩትን አቅኚነት መልሼ ለመጀመር ዕቅድ አወጣሁ። ከዚያም በአቅኚነት ከምታገለግል ሊያን ማክሻሪ የተባለች ዓይናፋር የገጠር ወጣት ጋር ተዋወቅኩ፤ እኔና ሊያን ጓደኛሞች ሆንን። ስለ ወደፊት ግባችንም በግልጽ ተነጋገርን፤ ሁለታችንም ሚስዮናዊ መሆን እንፈልግ ነበር። በ1993 ተጋባን። ምኞታችን፣ ይሖዋ በመራን መንገድ መሄድ ነበር።
ወደ ግባችን የሚወስዱ እርምጃዎች
በዚያ ዓመት እኔም እንደ ሊያን አቅኚ ሆንኩ። ቀላልና ከዕዳ ነፃ የሆነ ሕይወት ለመምራት ወስነን ስለነበር አሮጌ ተጎታች ቤት ገዝተን እዚያ ውስጥ መኖር ጀመርን። ለስድስት ዓመት ያህል፣ ወጪያችንን ለመሸፈን ተባራሪ ሥራዎችን እየሠራን የይሖዋ ድርጅት ወደላከን ቦታ ሁሉ እንጓዝ ነበር። ከትናንሽ ጉባኤዎች ጋር አብረን በመሄድ ኩዊንስላንድ ውስጥ ርቀው በሚገኙ ሰፋፊና በረሃማ አካባቢዎች እንሰብክ ነበር። በአብዛኛው ጭር ባሉ ቦታዎች ተጎታች ቤት ውስጥ ነበር የምናድረው፤ ጫካ ውስጥ ወይም በአካባቢው ባለ የሕዝብ አዳራሽ ደግሞ ስብሰባ እናደርጋለን። ደስተኞች ነበርን። ያም ሆኖ ‘ለይሖዋ ተጨማሪ ነገር ማድረግ እንችል ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሯችን ይመላለስ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ለጥያቄያችን መልስ አገኘን።
በአውስትራሊያ ርቆ በሚገኝ አካባቢ ለመስበክ በሄድንበት ወቅት ጫካ ውስጥ ያደረግነው ስብሰባ
የይሖዋ ድርጅት በሌላ አገር በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ግብዣ አቀረበልን! ሆኖም ይህን የአገልግሎት ምድብ ለመቀበል ፈራን፤ ምክንያቱም ጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተን ስላልሠለጠንን ጥሩ ሚስዮናዊ ለመሆን ብቃቱን እንደምናሟላ አልተሰማንም። አገልግሎት ብንወድም ባገለገልንባቸው ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ብዙ ጥናቶች አልነበሩንም፤ ስለዚህ ራሳችንን ውጤታማ አስተማሪ እንደሆንን አድርገን አንቆጥርም ነበር።
የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ለሆነው ለወንድም ማክስ ሎይድ ያሳሰበንን ነገር ነገርነው።a እሱም ብቁ እንዳልሆንን እየተሰማንም ቢሆን ራሳችንን ካቀረብን ይሖዋ እሱ የሰጠንን ማንኛውንም ሥራ ለማከናወን ብቁ እንደሚያደርገን አረጋገጠልን። ይህን አባታዊ ምክር ተቀብለን ወደተመደብንበት ወደ ስሪ ላንካ ለመሄድ ወሰንን።
ፈታኝ የአገልግሎት ምድብ
በ1999 የስሪ ላንካ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ኮሎምቦ ሄድን። በዚያ የጠበቀን በገጠሪቷ አውስትራሊያ ከነበረን የተረጋጋ ሕይወት ፍጹም የተለየ ሁኔታ ነበር፦ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድህነት፣ የተጨናነቀች ከተማ፣ ለማኞች ብሎም ውስብስብ የሆኑ ቋንቋዎች። ሆኖም ስሪ ላንካ ውስጥ ውድ ሀብትም ነበር—ውብ የሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ገና ስለ ይሖዋ ያልተማሩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትሑት ሰዎች።
ዙሪያዋን በሻይ እርሻና ጥቅጥቅ ባለ ደን በተከበበች ካንዲ በተባለች ውብ ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። ይህች ከተማ ብዙ የቡድሂስት መቅደሶች ያሉባት በመሆኗ ትታወቃለች። አብዛኞቹ ነዋሪዎች አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ ስለመኖሩ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ጉባኤያችን የሲንሃላ እና የታሚል ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉበት ስለሆነ ስብሰባዎችን የምናደርገው በሁለቱም ቋንቋዎች ነበር። ሲንሃላ ቋንቋን መማር ቀላል አይደለም፤ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን በተደጋጋሚ በምንሠራቸው ስህተቶች ቢስቁም ጥረታችንን ከልብ ያደንቁ ነበር!
በስሪ ላንካ የሲንሃላ እና የታሚል ቋንቋ አስተርጓሚዎች አጠገቤ ቆመው ንግግር ስሰጥ
ሆኖም ቋንቋውን ከመማር የሚበልጡ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። በሕይወታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከባድ ተቃውሞ ያየነው በዚህ ቦታ ነው። አንድ ቀን በቁጣ የተሞሉ ረብሸኞች ከበቡን። አንዳንዶቹ ጽሑፎቻችንን ሲያቃጥሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ እኔንና አብሮኝ ያለውን ወንድም በእርግጫ ይሉንና ይደበድቡን ጀመር። በዚህ ከባድ ሁኔታ ሥር፣ ይሖዋ እንዲያረጋጋንና ከሞትንም እንዲያስታውሰን ጸለይን። ደስ የሚለው ረብሸኞቹ ተበተኑ። ላደረገልን ጥበቃ ይሖዋን በማመስገን እየተንቀጠቀጥን ከዚያ ሰፈር ወጣን።
በጊዜ ሂደት በስሪ ላንካ ያለውን ሕይወት ወደድነው። አገሪቱ በጦርነት ብትከፋፈልም ይሖዋ እውነትን የተጠሙ ሰዎችን አንድነት ወዳለው ቤተሰቡ ሲሰበስብ ማየት አስደሳች ነበር። በዚህች ውብ ደሴት ብዙ ደስ የሚሉ ትዝታዎች አሉን። ይሁንና የቆየነው ሁለት ዓመት ብቻ ነው፤ ባለሥልጣናቱ የሃይማኖት መሪዎች በሚያደርሱባቸው ተጽዕኖ ስለተሸነፉ አብዛኞቹ ሚስዮናውያን አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላለፉ።
ከዚያ በኋላ የነበሩት ሳምንታት ግራ በመጋባትና በስጋት የተሞሉ ነበሩ። የት እንመደብ ይሆን? የበላይ አካሉ በፓፑዋ ኒው ጊኒ እንድናገለግል መደበን። መስከረም 2001 በአገሪቱ ዋና ከተማ ፖርት ሞርዝቢ ደረስን።
ፓፑዋ ኒው ጊኒ—ብዙ ገጽታዎችን የተላበሰች አገር
ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከየትኛውም አገር የበለጠ ለአውስትራሊያ ቅርብ ብትሆንም በአኗኗርና በባሕል በጣም የተለየች ናት። በድጋሚ ከአዲስ ሁኔታ ጋር መላመድ ግድ ሆነብን። በአገሪቱ በስፋት የሚነገረውን ቶክ ፒሲን የተባለውን ቋንቋ ተማርን፤ የሚገርመው በዚህች አገር ውስጥ ከ800 በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ!
ፖፖንዴታ በተባለች ከተማ ሦስት ዓመት ከቆየን በኋላ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። ይሖዋ በዚህ መንገድ ይጠቀምብናል ብለን ፈጽሞ አስበን አናውቅም! ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚሰጡት አመራር፣ ብስለታቸውና የማስተማር ችሎታቸው ሁሌም ያስደንቀኝ ነበር፤ እኔ ግን በዚህ መልኩ ጉባኤውን ለማገልገል ብቁ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ አያውቅም። ከድሮ ጀምሮ የእኔ ግብ ሚስዮናዊ መሆን ነው። ተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ጨርሶ የማላስበው ነገር ነበር! ይሖዋ እንዲህ ያለ መብት የሰጠኝ መሆኑ አሁንም ድረስ ያስደንቀኛል።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ በዌስት ሴፒክ ግዛት ርቆ የሚገኝን አንድ ቡድን ስንጎበኝ
በፓፑዋ ኒው ጊኒ ርቆ የሚገኝን አንድ ቡድን ከጎበኘን በኋላ ለቅርንጫፍ ቢሮው የሚላክ ሪፖርት ሳዘጋጅ
ከተሞችን ስንጎበኝ በአብዛኛው ኤሌክትሪክና ውኃ እንዲሁም አልጋ ያለው ማደሪያ እናገኛለን። በገጠራማ አካባቢዎች ግን እነዚህ ነገሮች እምብዛም አይገኙም። የምናድረው ትናንሽ ጎጆዎች ውስጥ ነው፤ ምግባችንን የምናበስለው ደጅ እሳት አንድደን ነው። ገላችንን ለመታጠብ ደግሞ ወደ ምንጭ ወይም ወንዝ እንወርዳለን፤ ወንዙ ውስጥ አዞዎች ካሉ ግን ውኃ በባልዲ ቀድተን እዚያው ጎጇችን ውስጥ እንታጠባለን።
ይህ የአገልግሎት ምድብ ከዚያ በፊት ካደረግናቸው ነገሮች ሁሉ ይበልጥ አካላዊ ጥንካሬ የሚጠይቅ ነበር። ሆኖም ‘ባለን ኃይል ከሄድን’ ይሖዋ ስኬታማ እንደሚያደርገን አልተጠራጠርንም። (መሳፍንት 6:14) የጎበኘናቸው አብዛኞቹ ጉባኤዎችና ቡድኖች ጥቅጥቅ ባሉ ጫካዎች፣ በረግረጋማ አካባቢዎች ወይም በተራሮች ላይ የሚገኙ ስለነበሩ ወደ እነዚህ ቦታዎች ለመድረስ እንቸገር ነበር። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለማግኘት ከፍ ባለ መኪና፣ በጀልባ፣ በአውሮፕላን፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ በእግር መጓዝ አስፈልጎናል።b
ሊያን በመስክ አገልግሎት ላይ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ተፈታታኝ ነገር ለመጋፈጥ ምንጊዜም ዝግጁ ናት
በኢንዶኔዥያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኝን አንድ ጉባኤ ለመጎብኘት ከ350 ኪሎ ሜትር በላይ እንነዳ ነበር፤ አብዛኛው መንገድ ደግሞ በደንብ ያልተስተካከለ ነው። በዚያ ጉዞ ላይ ከ200 ጊዜ በላይ ጅረቶችንና ወንዞችን እናቋርጣለን፤ የሚገርመው ደግሞ የምናቋርጣቸው አብዛኞቹ ወንዞች ድልድይ የላቸውም። መኪናችን በተደጋጋሚ ጭቃ ውስጥ ይቀረቀርብን ስለነበር ገፍተን ለማውጣት ስንታገል ብዙ ሰዓታት እናጠፋለን። በመጨረሻ ግን፣ ምግብ አዘጋጅተው በፈገግታ የሚቀበሉንን ውድ ወንድሞቻችንን ስናገኝ ደስ ይለናል።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ በመኪና መጓዝ ቀላል አልነበረም!
በትናንሽ አውሮፕላኖች ወደ ተራራማ አካባቢዎች ስንጓዝ አውሮፕላን አብራሪው በአብዛኛው ማረፊያውን የሚያገኘው እንደ ምንም በደመና መካከል ወደ ታች አይቶ ነው። ከዚያም ዝቅ ብሎ በመብረር ልጆች ወይም እንስሳት አለመኖራቸውን ያጣራል። በኋላም ከ2,100 ሜትር በላይ ከፍታ ባለው ተራራ ላይ፣ ያውም ጭቃማና ወጣ ገባ በሆነ መሬት ላይ ያርፋል፤ የሚያርፈው በሚያስፈራ መንገድ ስለሆነ አስቀድመን ራሳችንን ማዘጋጀት ያስፈልገናል። አንዳንዴ አውሮፕላኑ እንዲህ ካሉ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች ለመነሳት ያለው ብቸኛ አማራጭ ተንደርድሮ ልክ ገደል አፋፍ ላይ ሲደርስ መብረር ነው።c
አንዳንዴ በጽሑፎችና መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች የተሞላ ቦርሳ ተሸክመን ሞቃታማ በሆነ አየር ቀጥ ያሉ ተራራዎችን ወይም ረግረጋማ ቦታዎችን እናቋርጣለን። ሆኖም እንዲህ ያሉ ጉዞዎችን ስናደርግ ታማኝ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አብረውን ስለሚኖሩ እየተናነጽንና እየተሳሳቅን እንጓዛለን።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ በኬራም ወንዝ ላይ ተጉዘን ወደ አገልግሎት ስንሄድ
ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ተሰሎንቄ 2:8 ላይ የተናገረው ሐሳብ ስሜታችንን ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል፦ “ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን . . . ራሳችንን ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።” ወንድሞችና እህቶችም ለእኛ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ አይተናል፤ እንዲያውም እኛን ከታጠቁ ወሮበሎች ለማስጣል ሲሉ ሕይወታቸውን ጭምር አደጋ ላይ የጣሉበት ጊዜ አለ። በአንድ ወቅት ቆንጨራ የያዘ አንድ ሰው ሊያንን ያስፈራራት ጀመር። እኔ ሌላ አካባቢ ስለነበርኩ ልረዳት የምችልበት ሁኔታ አልነበረም። አንድ ወንድም ሮጦ በሊያን እና በሰውየው መካከል ቆመ። ደግነቱ ሰዎች ተሯሩጠው የተቆጣውን ሰውዬ ስለያዙት ወንድማችን ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም። ሥርዓት አልበኝነት እየተባባሰ በነበረበት በዚያ አገር ይሖዋ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ እንክብካቤ እንዳይቋረጥባቸው ሲል ለእኛ በየዕለቱ ጥበቃ ያደርግልን ነበር።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕክምና እንደ ልብ ስለማይገኝ ጤንነታችንን መጠበቅ ቀላል አልነበረም። በ2010 ሊያን ለሕይወት አስጊ የሆነ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን ስላጋጠማት ለድንገተኛ ሕክምና ወደ አውስትራሊያ ሄድን። በዚያ ወቅት ይሖዋ እንድንረጋጋ ረድቶናል። በመጨረሻ ሐኪሞቹ ውጤታማ የሆነ መድኃኒት አገኙላት። እንዲያውም አንዱ ሐኪም “እስካሁን ለአምላክ ብዙ ነገር አድርጋችኋል። እሱ ደግሞ በተራው አስደናቂ ነገር እያደረገላችሁ ነው” አለን። ከወራት በኋላ ወደ ምድባችን ተመለስን።
ወደ አገራችን ተመልሰን በሥራ ተጠመድን
ሊያን የሕክምና ክትትል ማድረግ ስለነበረባት ለአንድ ዓመት ገደማ ወደ አውስትራሊያ ስንመላለስ ቆየን። በመጨረሻም በ2012 እዚያው አውስትራሊያ ሆነን ጤንነታችንን እንድንንከባከብ ተነገረን። ለብዙ ዓመታት ርቀን ከቆየን በኋላ ስንመለስ በጣም የከበደን የጤናችን ሁኔታ ሳይሆን ለውጡን መቀበልና ደስተኛ መሆን ነበር። ከልብ የምንወደውን የአገልግሎት ምድብና መንፈሳዊ ቤተሰብ ትተን ስለመጣን በጣም ነበር ያዘንነው። የሚጠበቅብንን ያህል እንዳላደረግንና ይሖዋ የድሮውን ያህል ሊጠቀምብን እንደማይችል ተሰማን። ደግሞም ከአውስትራሊያ ከወጣን ብዙ ጊዜ ስለሆነን በገዛ አገራችን እንግድነት ተሰማን። በዚያ ወቅት ያቆመን መንፈሳዊ ቤተሰባችን ያደረገልን ድጋፍ ነው።
ሊያን ከሕመሟ ካገገመች በኋላ በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ከሲድኒ በስተ ደቡብ በምትገኝ ዎሎንጎንግ የተባለች ከተማ በልዩ አቅኚነት ማገልገል ጀመርን። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ፣ ለክርስቲያን ባለትዳሮች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት (አሁን የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ይባላል) እንድንማር ስንጋበዝ በጣም ተደሰትን። ከዚያም የአውስትራሌዢያ ቅርንጫፍ ቢሮ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል መደበን። ሰዎች በሚበዙባቸው ከተሞች፣ ርቀው በሚገኙ በረሃማ አካባቢዎች እንዲሁም ዓሣ አጥማጆች በሚኖሩባቸው መንደሮች የሚገኙ ጉባኤዎችንና ቡድኖችን በመጎብኘት የተወሰኑ ዓመታትን አሳለፍን። አሁን ደግሞ የምናገለግለው በሰሜን ምዕራብ አውስትራሊያ በሚገኘው ቆላማ አካባቢ እንዲሁም በመላው ቲሞር ሌስተ ነው።
በቲሞር ሌስተ ስንሰብክ
በጣም የምትደግፈኝና መንፈሳዊ የሆነችው ባለቤቴ በዚህ ሁሉ ከጎኔ አልተለየችም፤ እሷ ከይሖዋ የተቀበልኳት ውድ ስጦታዬ ናት። ሊያን የአገልግሎት ምድባችን የቱንም ያህል አስቸጋሪ ወይም የማይመች ቢሆንም ምድቡን ከመቀበል ወደኋላ ብላ አታውቅም። ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዴት እንደምትቋቋም ሰዎች ሲጠይቋት “ሁሉንም ነገር ለይሖዋ እነግረዋለሁ” ትላለች። ከጸለየች በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ይሖዋ አስተሳሰቧን፣ ስሜቷን ወይም ድርጊቷን እንዲመራላት ትፈቅዳለች።
በስፖርቱ ዓለም ከመሰማራት ይልቅ ይሖዋ ሕይወቴን እንዲመራልኝ በመፍቀዴ ፈጽሞ ተቆጭቼ አላውቅም። ይሖዋ የሰጠንን ሥራ በፈቃደኝነት እስከተቀበልን ድረስ እሱ የፈለገውን ማንኛውንም ነገር እንድናከናውን ሊያሠለጥነን እንደሚችል በገዛ ሕይወቴ አይቻለሁ። ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ወይም ውሳኔ ማድረግ ሲኖርብኝ በየዕለቱ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ጥበብና ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠኝ መጠየቅ እንዳለብኝ ተምሬአለሁ። አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንድንመራ ረድቶናል፤ ወደፊትም ደግሞ እንደ እኛ ባለ ‘የሸክላ ዕቃ’ ምን ተጨማሪ ነገሮችን እንደሚያከናውን ለማየት እንጓጓለን።—2 ቆሮንቶስ 4:7
a የማክስ ሎይድ የሕይወት ታሪክ በሐምሌ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-21 ላይ ይገኛል።
b በወረዳ ሥራ ላይ በጀልባ ተጉዘን ስላደረግነው ጉብኝት ለማንበብ የ2011 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ከገጽ 129-134ን ተመልከት።
c በመጋቢት 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16-17 ላይ የወጣውን “በደመና ውስጥ የሚገኝ ኮራል ሪፍ” የሚለውን ርዕስ አንብብ።