የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች

የግርጌ ማስታወሻ

a አንድ ትምህርት ቤት በቂ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ አቅኚዎች ከሌሉት ሥልጠናውን ካገኙ ከአምስት ዓመት በላይ የሆናቸው አንዳንድ አቅኚዎች በድጋሚ እንዲካፈሉ ሊጋበዙ ይችላሉ።

የጉባኤ ሽማግሌዎች ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶቻቸውን እንዲወጡና መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጎለብቱ መርዳት።

የሚፈጀው ጊዜ፦ አምስት ቀናት።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ።

ብቃት፦ የጉባኤ ሽማግሌዎች መሆን አለባቸው።

ምዝገባ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው ሽማግሌዎችን ይጋብዛል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በትምህርት ቤቱ 92ኛ ክፍል የሠለጠኑ ተማሪዎች የሰጧቸው አስተያየቶች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦

“ትምህርት ቤቱ ራሴን በደንብ እንድፈትሽ ስላደረገኝና የይሖዋን በጎች እንዴት መንከባከብ እንዳለብኝ ስላስገነዘበኝ በጣም ጠቅሞኛል።”

“ቅዱሳን መጻሕፍትን ስጠቀም ዋና ዋና ነጥቦች ላይ በማተኮር ሌሎችን ይበልጥ ለማበረታታት ተነሳስቻለሁ።”

“ይህን ሥልጠና በሕይወቴ ሙሉ እጠቀምበታለሁ።”

ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች “በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ” እንደመሆናቸው መጠን ጉባኤዎችን በማገልገል ረገድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ መርዳት።​—1 ጢሞ. 5:17፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ።

ብቃት፦ የወረዳ ወይም የአውራጃ የበላይ ተመልካቾች መሆን አለባቸው።

ምዝገባ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስቶቻቸውን ይጋብዛል።

“ኢየሱስ ድርጅቱን ስለሚመራበት መንገድ ያለን አድናቆት ጨምሯል። የምናገለግላቸውን ወንድሞች ማበረታታትና እያንዳንዱን ጉባኤ ማጠናከር እንዳለብን ተገንዝበናል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ምክርና ተግሣጽ ቢሰጡም ዋነኛ ዓላማቸው ወንድሞች ይሖዋ እንደሚወዳቸው እንዲሰማቸው መርዳት እንደሆነ በማይረሳ መንገድ ትምህርት ቤቱ አስገንዝቦናል።”​—ጆኤል፣ 1ኛው ክፍል፣ 1999

ለነጠላ ወንድሞች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ ነጠላ የሆኑ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ማዘጋጀት። በርካታ ተመራቂዎች፣ በሚኖሩበት አገር ውስጥ ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ይመደባሉ። ሌሎች ደግሞ ከአገራቸው ውጪ ለማገልገል ፈቃደኞች ከሆኑ በሌላ አገር ሊመደቡ ይችላሉ። አንዳንድ ወንድሞች ደግሞ ገለልተኛና ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች አዳዲስ ክልሎችን እንዲከፍቱና ሥራውን እንዲያስፋፉ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ ሆነው ይመደባሉ።

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።

ቦታ፦ ቅርንጫፍ ቢሮው በወሰነው ቦታ፤ ብዙውን ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ።

ብቃት፦ ከ23 እስከ 62 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ጥሩ ጤንነት ያላቸው እንዲሁም ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ለማገልገል ፍላጎት ያላቸው ነጠላ ወንድሞች። (ማር. 10:29, 30) ለሁለት ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት የዘወትር አቅኚ የሆኑና ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው እያገለገሉ ያሉ መሆን አለባቸው።

ምዝገባ፦ በዚህ ትምህርት ቤት መካፈል የሚፈልጉ ሁሉ በወረዳ ስብሰባ ወቅት ከአመልካቾች ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ በመገኘት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ23ኛው ክፍል የሠለጠነው ሪክ እንዲህ ብሏል፦ “ትምህርቱ በጥልቅ ስለነካኝ የይሖዋ መንፈስ ከፍተኛ ለውጥ እንዳደርግ ረድቶኛል። ይሖዋ አንድ ኃላፊነት ከሰጣችሁ ያን ኃላፊነት እንድትወጡ ድጋፍ ያደርግላችኋል። የራሴን ፍላጎት በማስቀደም ላይ ሳይሆን በአምላክ ፈቃድ ላይ ትኩረት ካደረግኩ እሱ እንደሚያበረታኝ ተገንዝቤያለሁ።”

በጀርመን የሚያገለግለው አንድሬአስ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ከሥልጠናው በኋላ የአምላክ ድርጅት እያከናወነ ያለውን ነገር በዘመናችን እየተፈጸመ እንዳለ አንድ ተአምር መመልከት ጀምሬያለሁ። ሥልጠናው ከፊቴ ለሚጠብቀኝ ሥራ አዘጋጅቶኛል። በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንድ መሠረታዊ የሆነ እውነት እንድገነዘብ ረድተውኛል፤ ይህም ወንድሞቼንና ይሖዋን ማገልገሌ እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልኝ መሆኑ ነው።”

ለባለትዳሮች የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ ሊጠቀሙባቸው እንዲችሉ ለባለትዳሮች ልዩ ሥልጠና መስጠት። አብዛኞቹ ተመራቂዎች በሚኖሩበት አገር ውስጥ ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልግበት ቦታ ይመደባሉ። ሌሎች ደግሞ ከአገራቸው ውጪ ለማገልገል ፈቃደኞች ከሆኑ በሌላ አገር ሊመደቡ ይችላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ገለልተኛና ሩቅ በሆኑ አካባቢዎች አዳዲስ ክልሎችን እንዲከፍቱና ሥራውን እንዲያስፋፉ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚ ሆነው ይመደባሉ።

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።

ቦታ፦ ይህ ትምህርት ቤት ከመስከረም 2012 ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ መካሄድ ጀምሯል፤ ትምህርት ቤቱ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የተወሰኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የሚካሄድ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ትምህርቱ የሚሰጠው በመንግሥት አዳራሽ ወይም የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ ነው።

ብቃት፦ ከ25 እስከ 50 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣ ጥሩ ጤንነት ያላቸው፣ እርዳታ ይበልጥ በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ሁሉ ለማገልገል ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውና “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” የሚል ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ባለትዳሮች። (ኢሳ. 6:8) በተጨማሪም ከተጋቡ ቢያንስ ሁለት ዓመት የሆናቸውና ለሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ መሆን አለባቸው። እንዲሁም ባልየው ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ያለ መሆን ይኖርበታል።

ምዝገባ፦ በዚህ ትምህርት ቤት መካፈል የሚፈልጉ ሁሉ በአውራጃ ስብሰባ ወቅት ከአመልካቾች ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ በመገኘት ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይችላሉ። በአገራችሁ እንዲህ ያለው ስብሰባ የማይደረግ ከሆነና በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የምትፈልጉ ከሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፍ ትችላላችሁ።

“እነዚህ ስምንት ሳምንታት ሕይወትን የሚያድሱ ናቸው፤ በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ለመሥራት ለሚፈልጉ ባለትዳሮች ትልቅ አጋጣሚ ነው! ሚዛናዊ የሆነ ሕይወት መምራታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል፤ ይህ ደግሞ ጊዜያችንን በጥበብ እንድንጠቀም ያስችለናል።”​—ኤሪክ እና ኮሪና፣ 1ኛው ክፍል፣ 2011

ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ ተማሪዎች ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ሚስዮናውያን ሆነው እንዲያገለግሉ እንዲሁም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ቤቴላውያን እንዲሆኑ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና መስጠት። ይህም ለመስኩ ሥራ ድጋፍ እንዲሰጡና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እንዲያደራጁ ያስችላቸዋል።

የሚፈጀው ጊዜ፦ አምስት ወር።

ቦታ፦ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል።

ብቃት፦ በአንድ ዓይነት የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ የተሰማሩ ባለትዳሮች ማለትም ጊልያድ ያልገቡ ሚስዮናውያን፣ ልዩ አቅኚዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ወይም ቤቴላውያን መሆን አለባቸው። ከላይ በተጠቀሱት የአገልግሎት ዘርፎች ቢያንስ ሦስት ዓመት ያለማቋረጥ አብረው ያገለገሉ መሆን አለባቸው። እንግሊዝኛ አቀላጥፈው መናገር፣ ማንበብና መጻፍ ይኖርባቸዋል።

ምዝገባ፦ ባለትዳሮች ለዚህ ትምህርት ቤት እንዲያመለክቱ የሚጋብዛቸው ቅርንጫፍ ኮሚቴው ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ ይኖሩ የነበሩት ላዲ እና ሞኒክ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ እያገለገሉ ነው፤ ላዲ እንዲህ ብሏል፦ “የጊልያድ ትምህርት ቤት በየትኛውም የዓለም ክፍል ብንመደብ ለመሄድና ከውድ ወንድሞቻችን ጋር ለመሥራት ራሳችንን እንድናዘጋጅ አድርጎናል።”

ሞኒክ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከአምላክ ቃል የተማርኩትን ተግባራዊ ለማድረግ ስጥር በተመደብኩበት ቦታ ይበልጥ ደስታ አገኛለሁ። ይህም ይሖዋ እንደሚወደኝ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሆኖልኛል።”

ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት

ዓላማው፦ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች የቤቴል ቤቶችን የመምራት፣ ጉባኤዎችን የሚመለከቱ የአገልግሎት ጉዳዮችን የመከታተል እንዲሁም በክልላቸው ውስጥ ያሉ ወረዳዎችንና አውራጃዎችን በበላይነት የመምራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መርዳት። በተጨማሪም ከትርጉም፣ ከኅትመትና ጽሑፎችን ከመላክ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንዴት በበላይነት መከታተል እንዳለባቸው ይማራሉ።

የሚፈጀው ጊዜ፦ ሁለት ወር።

ቦታ፦ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል።

ብቃት፦ የቅርንጫፍ ወይም የአገር ኮሚቴ አባል የሆኑ አሊያም እንዲህ ባሉ ኃላፊነቶች እንዲያገለግሉ የታጩ።

ምዝገባ፦ የበላይ አካሉ ወንድሞችንና ሚስቶቻቸውን ይጋብዛል።

ከ25ኛው ክፍል የተመረቁት ሎዌል እና ካራ በአሁኑ ጊዜ በናይጄሪያ እያገለገሉ ነው፤ ሎዌል እንዲህ ብሏል፦ “ምንም ያህል ሥራ ቢበዛብኝ ወይም የትኛውም ዓይነት ሥራ ቢሰጠኝ ይሖዋን ለማስደስት ቁልፉ ነገር መንፈሳዊነትን መጠበቅ እንደሆነ ተረድቻለሁ። ሥልጠናው ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይሖዋ ያሳየውን ፍቅር ማንጸባረቅ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝቦናል።”

ካራ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ሁሌም የማልረሳው አንድ ሐሳብ ተሰጥቶን ነበር። ይህም አንድን ትምህርት ቀለል ባለ መንገድ መግለጽ ካልቻልኩ ሌሎችን ከማስተማሬ በፊት በጉዳዩ ላይ ምርምር ማድረግ እንዳለብኝ የተሰጠው ሐሳብ ነው።”

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ