ቅዳሜ፣ ጥቅምት 11
ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ።—ኢሳ. 26:20
“ውስጠኛው ክፍል” የተባለው ጉባኤዎቻችንን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ ቃል የገባውን ጥበቃ የምናገኘው ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነት ካለን ነው። እንግዲያው ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መቻል ብቻ በቂ አይደለም፤ ከአሁኑ ከልብ ለመዋደድም ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው! “ታላቁ የይሖዋ ቀን” ለመላው የሰው ዘር አስጨናቂ ጊዜ ይሆናል። (ሶፎ. 1:14, 15) የይሖዋ አገልጋዮችም ፈተናዎች እንደሚያጋጥሟቸው ግልጽ ነው። ከአሁኑ ከተዘጋጀን ግን ያን ጊዜ አንረበሽም፤ እንዲያውም ሌሎችን ለመርዳት እንበቃለን። ምንም ዓይነት ፈተና ቢመጣ እንጸናለን። የእምነት ባልንጀሮቻችን ሲቸገሩ ርኅራኄ እናሳያለን፤ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። ደግሞም ከአሁኑ ፍቅርን ካዳበርን ያን ጊዜ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተቀራርበን መኖር አይቸግረንም። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርከናል፤ ያን ጊዜ አደጋና መከራ ታሪክ ይሆናሉ!—ኢሳ. 65:17፤ w23.07 7 አን. 16-17
እሁድ፣ ጥቅምት 12
[ይሖዋ] ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
የአምላክ ቃል ታማኝ ሰዎች ጠንካራ እንደሆኑ ይናገራል። ይሁንና በጣም ጠንካራ የሆኑት የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ጠንካራ እንዳልሆኑ የተሰማቸው ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ‘እንደ ተራራ ጠንካራ’ እንደሆነ ተሰምቶት ያውቃል፤ ሆኖም ‘የተሸበረበት’ ጊዜም አለ። (መዝ. 30:7) መንፈስ ቅዱስ ለሳምሶን ለየት ያለ ጥንካሬ ሰጥቶታል፤ ያም ቢሆን አምላክ ኃይል ባይሰጠው ኖሮ ‘አቅም እንደማይኖረውና እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እንደሚሆን’ ያውቅ ነበር። (መሳ. 14:5, 6፤ 16:17) እነዚህ ታማኝ ሰዎች ጠንካራ ሊሆኑ የቻሉት ይሖዋ ኃይል ስለሰጣቸው ብቻ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እሱም ከይሖዋ ኃይል ማግኘት እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። (2 ቆሮ. 12:9, 10) ከጤና ችግሮች ጋር ይታገል ነበር። (ገላ. 4:13, 14) ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የከበደው ጊዜም አለ። (ሮም 7:18, 19) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይጨነቅና ስጋት ያድርበት ነበር። (2 ቆሮ. 1:8, 9) ያም ቢሆን ጳውሎስ ሲደክም ያን ጊዜ ብርቱ ሆኗል። እንዴት? ይሖዋ ለጳውሎስ የጎደለውን ኃይል ስለሰጠው ነው። ጳውሎስን አጠንክሮታል። w23.10 12 አን. 1-2
ሰኞ፣ ጥቅምት 13
ይሖዋ . . . የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
አልፎ አልፎ ከዋጋ ቢስነት ስሜት ጋር የምንታገል ከሆነ አንድ እውነታ እናስታውስ፤ ይሖዋን እያገለገልን ያለነው እሱ ራሱ ስለሳበን ነው። (ዮሐ. 6:44) እኛ እንኳ እንዳለን የማናውቀውን መልካም ነገር በውስጣችን አይቷል፤ ልባችንንም ያውቃል። (2 ዜና 6:30) ስለዚህ በፊቱ ውድ እንደሆንን ሲነግረን ልናምነው ይገባል። (1 ዮሐ. 3:19, 20) አንዳንዶቻችን እውነትን ከመስማታችን በፊት ባደረግናቸው ነገሮች የተነሳ አሁንም የበደለኝነት ስሜት ይደቁሰን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3) ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ ከኃጢአት ዝንባሌዎች ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል። አንተስ ልብህ እየኮነነህ ይሆን? ከሆነ አይዞህ፤ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ ከእንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር ታግለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ስላሉበት ድክመቶች ሲያስብ ስሜቱ ተደቁሶ ነበር። (ሮም 7:24) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ ተጠምቋል። ያም ቢሆን ስለ ራሱ ሲናገር “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ” እንዲሁም “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” ብሏል።—1 ቆሮ. 15:9፤ 1 ጢሞ. 1:15፤ w24.03 27 አን. 5-6