ረቡዕ፣ ጥቅምት 15
እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ።—ራእይ 1:8
“አልፋ” የግሪክኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ፊደል፣ “ኦሜጋ” ደግሞ የመጨረሻው ፊደል ነው። ይሖዋ “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” ማለቱ አንድ ነገር ከጀመረ በተሳካ ሁኔታ ዳር እንደሚያደርሰው ያመለክታል። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው። (ዘፍ. 1:28) በዚህ ወቅት ይሖዋ “አልፋ” እንዳለ ሊቆጠር ይችላል። ፍጹምና ታዛዥ የሆኑ የአዳምና የሔዋን ዘሮች ምድርን የሚሞሉበትና ገነት የሚያደርጉበት ጊዜ እንደሚመጣ በግልጽ ተናግሯል። ወደፊት ይህ ዓላማው ሲፈጸም ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ “ኦሜጋ” ይላል። ይሖዋ “ሰማያትንና ምድርን እንዲሁም በውስጣቸው ያለውን ነገር ሁሉ” የመፍጠሩን ሥራ ሲያጠናቅቅ አንድ ዋስትና ሰጥቷል። ለሰዎችና ለምድር ያወጣው ዓላማ በእርግጥ እንደሚፈጸም ዋስትና ሰጠ። በሰባተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ዓላማው ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።—ዘፍ. 2:1-3፤ w23.11 5 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ጥቅምት 16
የይሖዋን መንገድ ጥረጉ! በበረሃ ለአምላካችን አውራ ጎዳናውን አቅኑ።—ኢሳ. 40:3
ከባቢሎን ወደ እስራኤል የሚወስደው መንገድ አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ አራት ወር ገደማ ይወስዳል። ሆኖም ይሖዋ ወደዚያ እንዳይመለሱ ሊያግዳቸው የሚችለውን ማንኛውንም እንቅፋት እንደሚያስወግድላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። በታማኞቹ አይሁዳውያን ዓይን ወደ እስራኤል መመለስ የሚያስገኘው ጥቅም ከሚከፍሉት ከማንኛውም መሥዋዕት እጅግ የላቀ ነው። የሚያገኙት ትልቁ በረከት ከአምልኳቸው ጋር የተያያዘ ነው። በባቢሎን የይሖዋ መቅደስ አልነበረም። እስራኤላውያን በሙሴ ሕግ መሠረት የሚጠበቅባቸውን መሥዋዕት ማቅረብ የሚችሉበት መሠዊያ አልነበረም፤ እንዲሁም እነዚህን መሥዋዕቶች የሚያቀርብ የተደራጀ የክህነት ሥርዓት አልነበረም። በተጨማሪም በዚያ የነበሩት ጣዖት አምላኪዎች ቁጥር ከይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር በእጅጉ ይበልጣል፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ለይሖዋም ሆነ ለመሥፈርቶቹ አክብሮት አልነበራቸውም። በመሆኑም ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ንጹሕ አምልኮን መልሰው ለማቋቋም ጓጉተው ነበር። w23.05 14-15 አን. 3-4
ዓርብ፣ ጥቅምት 17
የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:8
‘ከብርሃን ልጆች’ የሚጠበቀውን ምግባር እያሳየን ለመኖር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ሥነ ምግባር በጎደለው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው። (1 ተሰ. 4:3-5, 7, 8) መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ ፍልስፍናዎችንና አመለካከቶችን ጨምሮ የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን በምናደርገው ትግል ያግዘናል። “ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት [እና] ጽድቅ” እንድናፈራም ይረዳናል። (ኤፌ. 5:9) መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ ነው። ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን [እንደሚሰጣቸው]” ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:13) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ስናወድስም መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን። (ኤፌ. 5:19, 20) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ይረዳናል። w24.03 23-24 አን. 13-15