ዓርብ፣ ጥቅምት 17
የብርሃን ልጆች ሆናችሁ መመላለሳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:8
‘ከብርሃን ልጆች’ የሚጠበቀውን ምግባር እያሳየን ለመኖር የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ሥነ ምግባር በጎደለው በዚህ ዓለም ውስጥ ንጹሕ ሆኖ መኖር በጣም ከባድ ነው። (1 ተሰ. 4:3-5, 7, 8) መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ ፍልስፍናዎችንና አመለካከቶችን ጨምሮ የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን በምናደርገው ትግል ያግዘናል። “ሁሉንም ዓይነት ጥሩነት [እና] ጽድቅ” እንድናፈራም ይረዳናል። (ኤፌ. 5:9) መንፈስ ቅዱስን ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ ነው። ይሖዋ “ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን [እንደሚሰጣቸው]” ኢየሱስ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:13) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር ሆነን ይሖዋን ስናወድስም መንፈስ ቅዱስን እናገኛለን። (ኤፌ. 5:19, 20) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ አምላክን በሚያስደስት መንገድ ለመኖር ይረዳናል። w24.03 23-24 አን. 13-15
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 18
ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታሰልሱ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።—ሉቃስ 11:9
ይበልጥ ትዕግሥተኛ መሆን ትፈልጋለህ? ከሆነ ጸልይ። ትዕግሥት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። (ገላ. 5:22, 23) በመሆኑም ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን እንዲሁም የመንፈስ ፍሬ ለማፍራት እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን። ትዕግሥታችንን የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን ትዕግሥተኛ ለመሆን የሚረዳንን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ይሖዋን ‘ደጋግመን እንለምነዋለን።’ (ሉቃስ 11:13) በተጨማሪም ይሖዋ ሁኔታውን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። ከጸለይን በኋላ ደግሞ በየዕለቱ ትዕግሥተኛ ለመሆን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። ትዕግሥት ለማዳበር በጸለይን እንዲሁም ትዕግሥተኛ ለመሆን ጥረት ባደረግን መጠን ይህ ባሕርይ በልባችን ውስጥ ይበልጥ ሥር በመስደድ የማንነታችን ክፍል እየሆነ ይሄዳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንም ይጠቅመናል። መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት ያሳዩ በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ ማሰላሰላችን ትዕግሥት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች ለማወቅ ይረዳናል። w23.08 22-23 አን. 10-11
እሁድ፣ ጥቅምት 19
መረቦቻችሁን ጥላችሁ አጥምዱ።—ሉቃስ 5:4
ኢየሱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ እንደሚደግፈው አረጋግጦለታል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በድጋሚ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲያጠምዱ አድርጓቸዋል። (ዮሐ. 21:4-6) ይህ ተአምር፣ ጴጥሮስ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ሁሉ ይሖዋ በቀላሉ ሊሰጠው እንደሚችል አረጋግጦለት እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ‘ከሁሉ አስቀድመው መንግሥቱን ለሚፈልጉ’ ሁሉ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያሟላላቸው ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታውሶ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 6:33) በዚህም የተነሳ ጴጥሮስ ዓሣ ከማጥመድ ሥራው ይልቅ ለአገልግሎቱ ቅድሚያ መስጠት ጀመረ። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በድፍረት ምሥክርነት በመስጠት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ ረድቷል። (ሥራ 2:14, 37-41) በኋላ ደግሞ ሳምራውያንና አሕዛብ ክርስቶስን እንዲቀበሉ ረድቷል። (ሥራ 8:14-17፤ 10:44-48) በእርግጥም ይሖዋ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ጉባኤው ለማምጣት ጴጥሮስን አስደናቂ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። w23.09 20 አን. 1፤ 23 አን. 11