ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
ስለ ውፍረት የሚሰማኝን ጭንቀት እንዴት ማሸነፍ እችላለሁ?
“ሳንድዊቼ ውስጥ ማዮኔዝ ላድርግ አላድርግ እያልኩ ሁልጊዜ እጨነቃለሁ። ሁልጊዜ ስለ ማዮኔዝ እያሰብኩ መች ስለሌላ ነገር ማሰብ እችላለሁ? ይህ የመጨረሻ ውሳኔዬ ይሆን? ማዮኔዝ ብዙ ካሎሪ ስላለው ካሁን በኋላ ማዮኔዝ አልበላም። እንደገና በአኖሬክሲያ ጥቃት ተሸነፍኩ።”—ጄይሚ
የተዛባ የአመጋገብ ልማድ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያጠቃል።a አብዛኞቹ ራሳቸውን በረሃብ የማሰቃየት (አኖሬክሲያ) ወይም ቁንጣን እስኪይዛቸው የመብላትና የማስመለስ ልማድ (ቡሊሚያ) የማዳበር ዓላማ ይዘው አይነሱም። ከዚህ በተቃራኒ ብዙዎች ትንሽ ውፍረት የመቀነስ ግብ ይዘው ይጀምራሉ። ሆኖም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ከመገንዘባቸው በፊት ቀጣይ በሆነ የመራብ ወይም የማስመለስ አጓጉል ወጥመድ ይያዛሉ። “ምግብ የቀነስኩት ውፍረቴን ለመቆጣጠር ስል ነበር፤ አሁን ግን ከልክ በላይ ስለ አመጋገብ ጉዳይ ማሰቤ ሕይወቴን ይቆጣጠረው ጀመር” ስትል ጄይሚ ተናግራለች።
ስለ ምግብና ምግብ በሰውነትሽ ክብደት ላይ ስለሚያስከትለው ለውጥ ከልክ በላይ እንደምትጨነቂ ከተገነዘብሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ? በመጀመሪያ ደረጃ ሌሎች ብዙ ወጣቶች የአመጋገብ ሥርዓት መዛባትን ታግለው እንዳሸነፉ አስታውሺ! ግን እንዴት?
ራስን በመስተዋት መመልከት
ከአንድ ዓይነት የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት ጋር የሚደረግን ትግል ለማሸነፍ የሚረዳሽ አንዱ ዓቢይ እርምጃ ስለ ቁመናሽ ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ነው። “የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት የሚከተሉ አብዛኞቹ ሰዎች ስለቁመናቸው የተዛባ አመለካከት አላቸው” ሲል ቼንጂንግ ቦዲስ፣ ቼንጂንግ ላይቭስ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። “ስለ ሰውነታቸው ቅርጽ ያላቸው አመለካከት ከእውነታው የራቀ ሲሆን ራሳቸውን በተለይ ደግሞ ቁመናቸውን ክፉኛ ይጠላሉ።”
በእርግጥም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች ስለ ራሳቸው ያላቸው ግምት ሙሉ በሙሉ በሰውነታቸው ቅርጽ ላይ የተመካ ነው። በሰውነት ቅርጻቸው ላይ ትንሽ እንከን ካገኙ እንደ ትልቅ ውድቀት ይቆጥሩታል። “በጣም ወፍራም ነኝ፤ እንዲህ ወፍራም መሆን ደግሞ አልፈልግም” ስትል የ17 ዓመቷ ቪኪ ተናግራለች። “ወገቤ በጣም ወፍራም ስለሆነ አንድም ነገር ሱሪዬ ውስጥ ከትቼ መልበስ አልችልም።” ቪኪ 10 ኪሎ ግራም መቀነሷ እንኳ አላረካትም ነበር። ወይ ጨርሶ አትበላም ከበላች ደግሞ የበላችውን መልሳ ታስወጣዋለች።
በተወሰነ መጠን ስለ መልክሽ መጨነቅሽ ስህተት እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ሣራ፣ ራሄል፣ ዮሴፍ፣ ዳዊትና አቢጋኤልን ጨምሮ በርካታ የሆኑ ሴቶችና ወንዶች ያላቸውን የሰውነት ቁመናና መልክ በማድነቅ እንደሚናገር ማወቁ ትኩረት ይስባል።b አልፎ ተርፎም መጽሐፍ ቅዱስ ዳዊትን ትንከባከበው የነበረችው አቢሳ “እጅግ ውብ” እንደነበረች ይናገራል።—1 ነገሥት 1:4
የእውነተኛ ውበት ትርጉም
የሆነ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ በአንደኛ ደረጃ ትኩረት የሚሰጠው አንድ ሰው ላለው ውጫዊ መልክ ወይም የሰውነት ቅርጽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ከፍ አድርጎ ይገልጻል። (1 ጴጥሮስ 3:4) አንድን ሰው በአምላክም ሆነ በሰዎች ዘንድ በእርግጥ ውብ ወይም አስቀያሚ የሚያደርገው ውስጣዊ ማንነቱ ነው።—ምሳሌ 11:20, 22
የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቤሴሎምን እንውሰድ። “በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (2 ሳሙኤል 14:25) ሆኖም ይህ ወጣት አታላይ ነበር። ያደረበት ኩራትና የሥልጣን ጥማት በይሖዋ የተቀባውን ንጉሥ ለመገልበጥ እንዲያሴር ገፋፋው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አቤሴሎም ጥሩ መግለጫ አይሰጥም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እርሱን ዓይን ያወጣ ከሃዲና ነፍሰ ገዳይ አድርጎ ይገልጸዋል።
የአንድ ሰው እውነተኛ ውበት ወይም ቁንጅና ውጪያዊ መልኩ ላይ የተመካ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፣ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትሃለች” የሚለው አለምክንያት አይደለም።—ምሳሌ 4:7, 9
ሆኖም በግልጽ ለመናገር አብዛኛውን ጊዜ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት የሚጀምረው አንድ ሰው በቁመናው ሳይደሰት በመቅረቱ ብቻ አይደለም። አንድ የጥናት ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “የምግብ ጉዳይ ክፉኛ የሚያስጨንቃቸውና እንደ አኖሬክሲያ ነርቮሳ፣ ቡሊሚያና የመብላት ሱስ የመሳሰሉ የአመጋገብ ሥርዓት መዛባት የያዛቸው ሰዎች በአመዛኙ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ ነው። ስለ ራሳቸው ዋጋማነት ከፍ ያለ ግምት የላቸውም፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችም ዋጋ ቢስ አድርገው እንደሚያዩዋቸው ይሰማቸዋል።”
የራስን ዋጋማነት ዝቅ አድርጎ የማየት ስሜት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል ለአቅመ ሔዋን መድረስሽ በራስ ያለመተማመን ስሜት እንዲያድርብሽ ሊያደርግ ይችላል። በተለይ ደግሞ ከእኩዮችሽ ቀድመሽ አካላዊ እድገት ካደረግሽ ይህ ሊከሰት ይችላል። ከዚህም በላይ አንዳንድ ወጣቶች ያደጉት ማቆሚያ የሌለው ጠብ ምናልባትም አካላዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት በሚፈጸምበት ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል። መንስኤው ምንም ይሁን ምን በአብዛኛው ከችግሩ ለመላቀቅ የከንቱነትን ስሜት የሚቀሰቅሰው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ሰው እንደመሆንሽ የተላበስሽውን እውነተኛ ዋጋማነት መገንዘብ ማለት ነው። እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ ቢያንስ አንዳንድ የሚደነቁ ባሕርያት እንዳሉት የተረጋገጠ ነው። (ከ1 ቆሮንቶስ 12:14-18 ጋር አወዳድር።) እርግጥ እነዚህ ባሕርያት ለራስሽ ላይታዩሽ ይችሉ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አንዲት የጎለመሰች እህት ያሉሽን ባሕርያት ልትነግርሽ ትችላለች።
ሆኖም ከጤና ጋር በተያያዙ አግባብ ባላቸው ምክንያቶች የተነሳ በእርግጥ ውፍረት መቀነስ ቢያስፈልግሽስ? መጽሐፍ ቅዱስ ባሉን ልማዶች ረገድ “ልከኞች” እንድንሆን ይመክረናል። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) ስለዚህ ምግብ በመቀነስ ወይም በፍጥነት ውፍረት ለመቀነስ ለሚረዱ ዘዴዎች ተገዥ በመሆን ወደ አንድ ጽንፍ ከማጋደል መቆጠቡ የተሻለ ነው። አላስፈላጊ የሆነ ውፍረት ለማስወገድ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ተመጣጣኝ ምግብ መመገብና በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም። “በሌሎች በርካታ ነገሮች ላይ እንደሚታየው ሁሉ ትክክለኛም ሆነ የተሳሳተ ውፍረት መቀነሻ ዘዴ አለ። በተገቢው ሰዓት አለመመገብ፣ ከዳቦና ከውኃ በቀር አንድም ነገር ላለመብላት መወሰን፣ ውፍረት ለመቀነስ የሚረዱ እንክብሎችን መውሰድ ወይም ምግቡን ማስመለስ የተሳሳቱ ዘዴዎች ናቸው” ሲል ኤፍ ዲ ኤ ከንሲውመር የተባለው መጽሔት ዘግቧል።
ምሥጢር ማካፈል ያለው ጥቅም
የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛ የሆኑት ናንሲ ኮሎድኒ በአመጋገብ ሥርዓት መዛባት መያዝን “ካርታም ሆነ ኮምፓስ ሳይይዙ፣ መውጫ በሮች ያሉበትን ቦታ ሳያውቁና መውጫ መንገዱን ማግኘት አለማግኘታቸውን ወይም መቼ ማግኘት እንደሚችሉ ሳያውቁ በባዶ እጅ ውስብስብ መንገድ ውስጥ ከመግባት” ጋር አመሳስለውታል። “ለረጅም ጊዜ በቆያችሁ መጠን ውስብስብ ከሆነው መንገድ ለመውጣት የምታደርጉት ጥረት ይበልጥ ግራ የሚያጋባና ተስፋ አስቆራጭ ይሆንባችኋል።” ስለዚህ የአኖሬክሲያና የቡሊሚያ ምልክቶች ከተከሰቱብሽ እርዳታ ማግኘት አለብሽ ማለት ነው። ማንም ሳይረዳሽ “ውስብስብ ከሆነው መንገድ” መውጣት አትችይም። ስለዚህ ለወላጅሽ ወይም ለሌላ ለምታምኚያት ጎልማሳ ሴት ምስጢርሽን አካፍዪ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል።”—ምሳሌ 17:17
በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ዓይነት እምነት የሚጣልበት ወዳጅነት መሥርተዋል። እርግጥ፣ ሽማግሌዎች ሐኪሞች አይደሉም፤ እንዲሁም እነርሱ የሚሰጡት እገዛ የሕክምና እርዳታ አስፈላጊነትን ሊተካ አይችልም። ሆኖም ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች “የድሀውን ጩኸት” ችላ አይሉም። እንዲሁም የእነርሱ ምክርና ጸሎት በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘ድውዩን ለማዳን’ ሊረዳ ይችላል።—ምሳሌ 21:13፤ ያዕቆብ 5:13-15
ፊት ለፊት ቀርበሽ ለአንድ ሰው ምሥጢርሽን ማካፈል የሚከብድሽ ከሆነ መልስ እንዲሰጥሽ በመጠየቅ ሐሳብሽን በደብዳቤ ግለጪ። ዋናው ቁም ነገር ጉዳዩ ተዳፍኖ እንዳይቀር ማድረግ ነው። “እንዲህ ማድረግሽ ችግሩን ለብቻሽ ልትወጪው እንደማትችዪ ሐቁን አምነሽ በመቀበል፣ ካሁን በኋላ ሌላ ሰው እንዲረዳሽ ፈቃደኛ ለመሆን ቃል መግባትሽ ነው” በማለት ናንሲ ኮሎድኒ ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “እነዚህን እርምጃዎች ማሰብና በተግባር ማዋል ይከብድሽ ይሆናል፤ ሆኖም ውስብስብ ከሆነው መንገድ መውጣት እንድትችዪ ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚያስይዙሽ ገንቢ እርምጃዎች እነዚህ ናቸው።”
ክርስቲያን ወጣቶች ከፍተኛ ኃይል ያለው ሌላ ድጋፍ አላቸው፤ ይኸውም ጸሎት ነው። ለአምላክ የሚቀርብ ጸሎት የአእምሮ ሰላም ለማግኘት የሚረዳ የሥነ ልቦና ዘዴ አይደለም። ጸሎት አንቺ ስለ ራስሽ ካለሽ ግንዛቤ በተሻለ ስለ አንቺ ከሚያውቅ ፈጣሪ ጋር የሚደረግ እውነተኛና ጠቃሚ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት ነው! (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ያለንበት ጊዜ ይሖዋ በሽታዎችን ሁሉ ለማስወገድ የቀጠረው ጊዜ ባይሆንም እንኳ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን አካሄድሽ የተቃና እንዲሆን ሊመራሽ ይችላል። (መዝሙር 55:22) መዝሙራዊው ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔርን ፈለግሁት መለሰልኝም፣ ከመከራዬም ሁሉ አዳነኝ። ይህ ችግረኛ ጮኸ፣ እግዚአብሔርም ሰማው፣ ከመከራውም ሁሉ አዳነው።”—መዝሙር 34:4, 6
ስለዚህ በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ለይሖዋ አምላክ ውስጣዊ ስሜትሽን ግለጪለት። “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:7) ለይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ያለሽን አድናቆት ለመገንባት መዝሙር 34ን, 77ን, 86ን, 103ን እና 139ን ለምን በጥንቃቄ አታነቢም? በእነዚህ መዝሙሮች ላይ ማሰላሰልሽ ይሖዋ ታማኝ እንደሆነና ችግርሽን በአሸናፊነት እንድትወጪ እንደሚፈልግ ያለሽን ጽኑ እምነት ያጠናክርልሻል። የይሖዋን ቃል በማንበብ መዝሙራዊው “አሳብና ጭንቀት በያዘኝ ጊዜ፤ አንተ ታጽናናኛለህ፤ ደስም ታሰኘኛለህ” ሲል የጻፈው ዓይነት ስሜት እንዲኖርሽ ያደርጋል።—መዝሙር 94:19 የ1980 ትርጉም
ለመዳን ጊዜ ስለሚወስድ ትዕግሥተኛ ሁኚ
የተዛባ የአመጋገብ ልማድ ኖሯቸው እርዳታ የሚደረግላቸው አብዛኞቹ ሰዎች በቅጽበት አይድኑም። መግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ጄይሚን እንውሰድ። እርዳታ ማግኘት ከጀመረች በኋላ እንኳ እንደ በሶ ያለ ቀላል ምግብ መመገብ ይከብዳት ነበር። “ምግቡ እንደሚጠቅመኝና በሕይወት ለመቆየት የግድ መብላት እንዳለብኝ ራሴን ደጋግሜ ማስገንዘብ ነበረብኝ” ስትል ተናግራለች። “እያንዳንዱ ጉርሻ በአፌ ውስጥ ይዞራል።”
በአንድ ወቅት ጄይሚ ሞት አፋፍ ላይ የነበረች ቢሆንም እንኳ ከምግብ ጋር በተያያዘ የተፈጠረባትን ጭንቀት ለማሸነፍ ቆርጣ ተነሳች። “መሞት የለብኝም” ስትል ተናግራለች። “ይህን ችግር ታግዬ ማሸነፍ አለብኝ። አኖሬክሲያን ማስወገድ አለብኝ። አዳጋች እንደሚሆን አውቃለሁ፤ ሆኖም እጅ አልሰጥም።” አንቺም እንዲህ ማድረግ ትችያለሽ!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሐምሌ 1999 ንቁ! ገጽ 27-29ን ተመልከት።
b ዘፍጥረት 12:11፤ 29:17፤ 39:6፤ 1 ሳሙኤል 17:42፤ 25:3ን ተመልከት።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተመጣጣኝ ምግብ መመገብና በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ውፍረትሽን ለመቆጣጠር ሊረዳሽ ይችላል