አሮጌ ወረቀቶችን በሚገዛ ሱቅ ውስጥ ተገኘ
በቼናይ ህንድ የሚኖር አንድ የታሚል ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ወጣት የነሐሴ 8, 1999 የንቁ ! እትም ያገኘው በዚህ ሱቅ ውስጥ ነበር። ይህንንና ሊያገኝ የቻላቸውን ሌሎች እትሞችንም ከመረመረ በኋላ ስለ መጽሔቶቹ ያለውን አስተያየት በህንድ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በደብዳቤ ገለጸ።
እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ንቁ ! ትምህርት ሰጭና በጣም ጠቃሚ የሆነ ግሩም መጽሔት ነው። የሚቀርቡት ርዕሰ ጉዳዮች ትልቅ እርዳታ ያበረክታሉ። ላመሰግናችሁ እወዳለሁ!”
ከዚያም ወጣቱ ይህን ጥያቄ አቀረበ:- “በሁሉም የዓለም ማዕዘናት የሚሰራጨው ይህ እውቀት የሚያስጨብጥ መጽሔት በግል ቤተ መጻሕፍቴ ውስጥ ቢኖር ደስ ይለኛል። እስካሁን የታተሙትን መጽሔቶች ካነበብኩ በኋላ ወደፊት የሚወጡት እትሞችም እንዲደርሱኝ እፈልጋለሁ።”
በእያንዳንዱ እትም ገጽ 4 ላይ እንደተገለጸው ንቁ ! በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቃል። በመጽሔቱ ላይ የተገለጸው ዓላማ እንዲህ ይላል:- “ከሁሉም በላይ ይህ መጽሔት አሁን ያለውን ክፉና ዓመፀኛ ሥርዓት የሚተካ ሰላም የሰፈነበትና አስተማማኝ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ፈጣሪ በሰጠው ተስፋ ላይ ሰዎች ያላቸውን እምነት እንዲያሳድጉ ያደርጋል።”
አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለው ባለ 32 ገጽ ብሮሹር የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን የሚጠቁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በመስጠት ይህን የአምላክ ዓላማ ጎላ አድርጎ ያቀርባል። እርስዎም የዚህን ብሮሹር አንድ ቅጂ ማግኘት ከፈለጉ ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይላኩ።
□ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ላኩልኝ።
□ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።