የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • “ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል”
    ንቁ!—2001 | ታኅሣሥ 8
    • “ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል”

      ሮክሳናa በደቡብ አሜሪካ አንድ የተከበረ ቀዶ ሐኪም አግብታ የምትኖር ደስ የምትልና ፍልቅልቅ የሆነች የአራት ልጆች እናት ነች። “ባለቤቴ የሴቶችን ቀልብ የሚማርክና በብዙ ወንዶች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ሰው ነው” ትላለች። ይሁን እንጂ የሮክሳና ባለቤት የቅርብ ጓደኞቻቸው እንኳ የማያውቁት መጥፎ ጎን አለው። “ቤት ውስጥ አውሬ ነው። በጣም ይቀናል።”

      ሮክሳና ታሪኳን መናገር ስትቀጥል የመረበሽ ስሜት ፊቷ ላይ በግልጽ ይነበብ ነበር። “ችግሩ የተፈጠረው በተጋባን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነው። ወንድሞቼና እናቴ ሊጠይቁን መጥተው ነበር። ከእነሱ ጋር በሳቅ በጨዋታ ደስ የሚል ጊዜ አሳለፍኩ። ይሁን እንጂ እነሱ ተመልሰው ሲሄዱ ባለቤቴ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ሶፋ ላይ በኃይል ወረወረኝ። የሆነውን ነገር ማመን አቃተኝ።”

      ሮክሳና የገጠማት ፈተና በዚህ ቢያበቃ ደግ ነበር። ላለፉት በርካታ ዓመታት በተደጋጋሚ ተደብድባለች። የሚፈጸምባት በደል አንድ ወጥ የሆነ ዑደት ያለው ይመስላል። ባለቤቷ ይደበድባታል፣ ከዚያም ይቅርታ እንድታደርግለት በመወትወት ሁለተኛ እንደማይነካት ቃል ይገባል። ጠባዩ ቢያንስ ለጥቂት ጊዜ ይሻሻላል። ከዚያ በኋላ ግን ሁሉ ነገር እንደ አዲስ ያገረሻል። “ምናልባት አሁን ይለወጥ ይሆናል እያልኩ ሁልጊዜ አስባለሁ” ትላለች ሮክሳና። “ቤቱን ጥዬ ከወጣሁ በኋላ እንኳን ተመልሼ እገባለሁ።”

      ሮክሳና ባሏ የሚፈጽምባት የኃይል ድርጊት አንድ ቀን የከፋ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል ስጋት አለባት። “እኔን፣ ልጆቹንና ራሱን እንደሚገድል ዝቶብኛል” ትላለች። “አንድ ቀን ጉሮሮዬ ላይ መቀስ ሊሰካብኝ ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሽጉጥ ጆሮ ግንዴ ላይ ደግኖ ምላጩን ሳበው! ደግነቱ ጥይት አልነበረውም። ሆኖም በድንጋጤ ልሞት ምንም አልቀረኝም ነበር።”

      የዝምታ ቅርስ

      እንደ ሮክሳና ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ጠበኛ በሆኑ ወንዶች በደል ይፈጸምባቸዋል።b ብዙዎቹ የሚደርስባቸውን መከራና ሥቃይ ከመናገር ዝምታን ይመርጣሉ። ጉዳዩን ማሳወቁ ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ይሰማቸዋል። በሚስቶቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙ ብዙዎቹ ባሎችም ቢሆኑ “ሚስቴ በትንሽ በትልቁ ትሸበራለች” ወይም “ማጋነን ትወዳለች” በማለት የሚቀርብባቸውን ውንጀላ ያስተባብላሉ።

      ብዙ ሴቶች በገዛ ቤታቸው የበለጠ ደህንነት ሊሰማቸው ሲገባ ከአሁን አሁን ጥቃት ይደርስብኛል በሚል ፍርሃት ዘወትር ተሸማቅቀው መኖራቸው በጣም ያሳዝናል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ሲታዘንለት የሚታየው ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው እንጂ ጥቃቱ የሚደርስባት ሴት አይደለችም። እንዲያውም አንዳንዶች ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ይደበድባል ብለው ለማመን በጣም ይቸገራሉ። ለምሳሌ አኒታ የተባለች አንዲት ሴት በሌሎች ዘንድ አክብሮት ያተረፈው ባሏ እያደረሰባት ስላለው በደል በተናገረች ጊዜ የገጠማትን ሁኔታ ተመልከት። “ከሚያውቁን ሰዎች አንዱ ‘እንዴት እንዲህ ያለውን የተከበረ ሰው ትወነጅያለሽ?’ አለኝ። ሌላው ደግሞ ራስሽ እያስቆጣሽው መሆን አለበት አለኝ! ባለቤቴ የሚፈጽመው ድርጊት ከተጋለጠም በኋላ እንኳ አንዳንዶቹ ጓደኞቼ ይሸሹኝ ጀመር። ‘ይህ የተለመደ የወንዶች ባሕርይ’ ስለሆነ ችዬ መኖር እንደነበረብኝ ተሰምቷቸዋል።”

      አኒታ የደረሰባት ሁኔታ እንደሚያሳየው ባለ ትዳሮች በትዳር ጓደኞቻቸው ላይ የሚፈጽሙትን በደል ብዙዎቹ ሰዎች አምነው ለመቀበል ይቸገራሉ። አንድ ሰው እወዳታለሁ በሚላት ሴት ላይ እንዲህ ጨካኝ እንዲሆን የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? የኃይል ድርጊት ሰለባዎችስ እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?

      [የግርጌ ማስታወሻዎች]

      a በዚህ ተከታታይ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

      b ብዙ ወንዶችም የኃይል ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው እናምናለን። ሆኖም ከወንዶቹ ይበልጥ ለጉዳት የተጋለጡት ሴቶቹ እንደሆኑና የሚደርስባቸውም ጉዳት በጣም የከፋ እንደሆነ የተካሄዱት ጥናቶች አመልክተዋል። በመሆኑም እነዚህ ርዕሶች በሴቶች ላይ በሚደርሰው በደል ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።

      [በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

      በቤት ውስጥ የሚፈጸም በደል ብዙ ዓይነት መልክ አለው

      የተባበሩት መንግሥታት በሴቶች ላይ የሚፈጸምን በደል ለማስቀረት ያወጣው ድንጋጌ እንደሚለው ከሆነ “በሴቶች ላይ የሚፈጸም በደል” የሚለው ሀረግ “በይፋም ይሁን በድብቅ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም አእምሯዊ ጉዳት ወይም ሥቃይ የሚያስከትል ወይም ሊያስከትል የሚችል በጾታ ላይ የተመሠረተ በደል” የሚያመለክት ከመሆኑም በላይ “እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች ለመፈጸም መዛትን፣ ያልፈለጉትን ነገር እንዲያደርጉ ማስገደድን ወይም በማን አለብኝነት ነፃነታቸውን መግፈፍን ይጨምራል።” በተጨማሪም ይህ በደል “ድብደባን፣ በሕፃናት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ወሲባዊ በደል፣ ከጥሎሽ ጋር በተያያዘ የሚፈጸም በደልን፣ በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸምን የግዳጅ ወሲብ፣ የሴቶችን ግርዛትና ሌሎች በሴቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ባሕላዊ ልማዶችን ጨምሮ በቤተሰብና በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ አካላዊ፣ ወሲባዊና ሥነ ልቦናዊ በደል መፈጸምን” ያካትታል።

  • ወንዶች ሴቶችን የሚደበድቡት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2001 | ታኅሣሥ 8
    • ወንዶች ሴቶችን የሚደበድቡት ለምንድን ነው?

      አንዳንድ ጠበብት እንደሚሉት ከሆነ በትዳር ጓደኞቻቸው የሚገደሉት ሴቶች ቁጥር በሌሎች ሰዎች ከሚገደሉት ሴቶች ጠቅላላ ቁጥር ሳይበልጥ አይቀርም። በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸመውን በደል ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ ለመሻት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። ሚስቱን የሚደበድበው ምን ዓይነት ወንድ ነው? የልጅነት ሕይወቱ ምን ይመስላል? ይጠናኑ በነበረበት ወቅት የኃይለኛነት ባሕርይ ይንጸባረቅበት ነበር? ለሚሰጠው የሕክምና እርዳታ ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል?

      ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ወንዶች ሁሉ አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ ጠበብት መገንዘብ ችለዋል። በአንደኛው ጽንፍ ያለው ወንድ ለዘብ ያለ ነው። መሣሪያ የማይጠቀም ከመሆኑም በላይ በትዳር ጓደኛው ላይ በደል የመፈጸም ልማድ የለውም። የኃይል ድርጊት ለመፈጸም የሚነሳሳው አልፎ አልፎ ሲሆን ለእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የሚገፋፉት በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙት ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላው ጽንፍ ያለው ወንድ ደግሞ ሚስቱን የመደብደብ ሥር የሰደደ ልማድ የተጠናወተው ሰው ነው። በሚስቱ ላይ የሚያደርሰው በደል ቀጣይነት ያለው ከመሆኑም በላይ እምብዛም የጸጸት ስሜት አያድርበትም።

      ይሁን እንጂ ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ወንዶች ሁኔታ የሚለያይ መሆኑ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አንዳንዱ ድብደባ ብዙም አሳሳቢ አይደለም ሊያሰኝ አይችልም። እንዲያውም የትኛውም ዓይነት አካላዊ በደል ጉዳት ብሎም ሞት ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም አንድ ወንድ ሚስቱን የሚደበድበው አልፎ አልፎ መሆኑና የሌላውን ያህል የከፋ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ ከተጠያቂነት ነፃ ሊያደርገው አይችልም። “ተቀባይነት ያለው” የድብደባ ዓይነት የለም። ይሁንና አንድ ወንድ በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ሊንከባከባት ቃል ገብቶ የወሰዳትን ሚስቱን እንዲደበድብ የሚያነሳሱት ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

      ከቤተሰብ ጋር ያለው ትስስር

      አካላዊ በደል የሚፈጽሙት ብዙዎቹ ወንዶች ራሳቸው በእንዲህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ መሆናቸው ምንም አያስገርምም። በትዳር ጓደኞች ላይ የሚፈጸመውን በደል ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ ሲያጠኑ የቆዩት ማይክል ግሮች “ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ አብዛኞቹ ወንዶች ‘ከጦርነት ቀጣናዎች’ በማይለዩ ቤቶች ውስጥ ያደጉ ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል። “በሕፃንነታቸውና በልጅነታቸው ያደጉበት ቤት ‘ዕለት ተዕለት’ ስሜታዊና አካላዊ በደል የሚፈጸምበትና ጥላቻ የነገሠበት ነበር።” አንዲት ባለሙያ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ እያየ ያደገ ወንድ “አባቱ ለሴቶች ያለው ንቀት ገና በልጅነቱ ሊጋባበት ይችላል። ልጁ አንድ ወንድ ምንጊዜም ሴቶችን በቁጥጥሩ ሥር ማድረግ እንዳለበትና ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በማስፈራራት፣ ጉዳት በማድረስና በማዋረድ እንደሆነ ይማራል። በተጨማሪም በአባቱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የተሻለው መንገድ አባቱ የሚያደርገውን ማድረግ እንደሆነ ይማራል።”

      መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ ወላጅ ጠባይ በልጁ ላይ በጎም ይሁን መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 22:​6፤ ቆላስይስ 3:​21) እርግጥ አንድ ወንድ ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታ ሚስቱን ለመደብደብ ሰበብ ሊሆነው ባይችልም ይህ የጠበኛነት መንፈስ ዘሩ የት እንደተዘራ ለመገንዘብ ሊረዳ ይችላል።

      የባሕል ተጽዕኖ

      በአንዳንድ አገሮች ሴትን መደብደብ ተቀባይነት ያለው አልፎ ተርፎም ያለ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው አንድ ሪፖርት “ብዙዎቹ ኅብረተሰቦች ባል ሚስቱን የመደብደብ ወይም የማስፈራራት መብት አለው የሚል ሥር የሰደደ እምነት አላቸው” ሲል ገልጿል።

      እንዲህ ያለው በደል ተቀባይነት በማያገኝባቸው አገሮችም እንኳን ብዙዎቹ ግለሰቦች የኃይለኛነት ጠባይ ያዳብራሉ። አንዳንድ ወንዶች በዚህ ረገድ ያላቸው ጭፍን አስተሳሰብ እጅግ ያስገርማል። የደቡብ አፍሪካው ዊክሊ ሜይል ኤንድ ጋርዲያን እንደሚለው ከሆነ በኬፕ ባሕረ ገብ መሬት የተካሄደው ጥናት በትዳር ጓደኞቻቸው ላይ በደል እንደማይፈጽሙ ከተናገሩት ወንዶች መካከል አብዛኞቹ ሴትን መምታት ተቀባይነት እንዳለውና ይህ እንደ ኃይል ድርጊት ተደርጎ ሊታይ እንደማይችል መናገራቸውን አመልክቷል።

      እንዲህ ዓይነቱ የተዛባ አስተሳሰብ ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በልጅነት እንደሆነ የታወቀ ነው። ለምሳሌ ያህል በብሪታንያ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ11 እስከ 12 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወንዶች ልጆች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት አንዲት ሴት አንድን ወንድ በምታበሳጨው ጊዜ ቢመታት አግባብ ነው የሚል እምነት አላቸው።

      ለመደብደብ ምክንያት አይሆንም

      ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች በትዳር ጓደኛ ላይ በደል እንዲፈጸም የሚያደርጉ ሁኔታዎችን ግልጽ ለማድረግ ሊረዱ ይችላሉ። ሆኖም ድርጊቱን ለመፈጸም ሰበብ ሊሆኑ አይችሉም። በአጭሩ፣ የትዳር ጓደኛን መደብደብ በአምላክ ፊት ከባድ ኃጢአት ነው። በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚከተለውን እናነባለን:- “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል።”​—⁠ኤፌሶን 5:​28-30

      መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ ብዙዎች “በሌሎች ላይ በደል የሚፈጽሙ፣” “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” እና “ጨካኞች” እንደሚሆኑ ከረጅም ጊዜ በፊት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-3፤ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ) በትዳር ጓደኞች ላይ የሚፈጸመው በደል እየተስፋፋ መሄዱ በዚህ ትንቢት ላይ በተጠቀሰው ዘመን እንደምንኖር የሚያሳይ አንድ ምልክት ነው። ይሁን እንጂ አካላዊ በደል የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል? የትዳር ጓደኛቸውን የሚደበድቡ ሰዎች ይህን ጠባያቸውን ሊለውጡ ይችሉ ይሆን?

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      “ሚስቱን የደበደበ ግለሰብ የማያውቀውን ሰው ከደበደበ ግለሰብ እኩል ወንጀለኛ ነው።”​—⁠ዌን ሜን ባተር ዊሜን

      [በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      የወንድ ትምክህተኝነት ዓለም አቀፋዊ ችግር

      እንግሊዝኛ ተናጋሪው ዓለም “ማቺዝሞ” የሚለውን ቃል ከላቲን አሜሪካ ወርሷል። ይህ ቃል የወንድ እብሪተኝነትን የሚያመለክት ሲሆን ወንዶች ለሴቶች ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ለመግለጽ ይሠራበታል። ይሁንና ቀጥሎ የተገለጹት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የወንድ ትምክህተኝነት በላቲን አሜሪካ ብቻ የሚንጸባረቅ ችግር አይደለም።

      ግብፅ:- በእስክንድርያ ለሦስት ወራት የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በሴቶች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ዋናው ምክንያት በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ነው። የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ወደሚሰጡ ተቋማት ከሚሄዱት ሴቶች መካከል 27.9 በመቶ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚፈጸም ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።​—⁠የአራተኛው የዓለም የሴቶች ጉባኤ 5ኛ ጥናታዊ ዘገባ

      ታይላንድ:- ከባንኮክ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ ትልቅ የመኖሪያ ሰፈር ከሚገኙ ባለትዳር ሴቶች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት በየጊዜው ድብደባ ይደርስባቸዋል።​—⁠የሴቶች ጤና የፓስፊክ ክልል ተቋም

      ሆንግ ኮንግ:- “በትዳር ጓደኞቻቸው ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የሚናገሩ ሴቶች ቁጥር ባለፈው ዓመት ከ40 በመቶ በላይ አሻቅቧል።”​—⁠ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት፣ ሐምሌ 21, 2000

      ጃፓን:- በ1995 መጠለያ የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር 4, 843 የነበረ ሲሆን በ1998 ደግሞ ወደ 6, 340 አሻቅቧል። “ከእነዚህ መካከል አንድ ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑት ራሳቸውን የሚያስጠጉበት መጠለያ የፈለጉት ጠበኛ በሆኑት ባሎቻቸው ሳቢያ እንደሆነ ገልጸዋል።”​—⁠ዘ ጃፓን ታይምስ፣ መስከረም 10, 2000

      ብሪታንያ:- “በብሪታንያ በየስድስት ሴኮንዱ በሆነ ቤት ውስጥ የግዳጅ ወሲብ፣ ድብደባ ወይም በስለት የመውጋት ወንጀል ይፈጸማል።” የለንደን ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው ከሆነ “ፖሊስ በየዕለቱ በቤት ውስጥ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሰዎች 1, 300 የስልክ ጥሪ የሚደርሰው ሲሆን ይህም በዓመት ከ570, 000 በላይ ይሆናል። ከእነዚህ መካከል ሰማንያ አንድ በመቶ የሚሆኑት በወንዶች ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ናቸው።”​—⁠ዘ ታይምስ፣ ጥቅምት 25, 2000

      ፔሩ:- ለፖሊስ ሪፖርት ከሚደረጉት ወንጀሎች መካከል ሰባ በመቶ የሚሆነው በባሎቻቸው በሚደበደቡ ሴቶች ላይ የሚፈጸመውን በደል ይጨምራል።​—⁠የሴቶች ጤና የፓስፊክ ክልል ተቋም

      ሩስያ:- “በአንድ ዓመት ውስጥ 14, 500 ሩስያውያን ሴቶች በባሎቻቸው የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 56, 400 የሚሆኑ ደግሞ በቤት ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል ወይም ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።”​—⁠ዘ ጋርዲያን

      ቻይና:- “ቀደም ሲል ያልነበረ ችግር ነው። አሁን ግን በተለይ በከተሞች ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው” ሲሉ የቺንግሉን የቤተሰብ ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ቸን ዪዩን ተናግረዋል። “ጎረቤቶች ለማከላከል የሚያደርጉት ጥረት በቤት ውስጥ የሚፈጸመውን ጥቃት እንደ ቀድሞ ሊገታው አልቻለም።”​—⁠ዘ ጋርዲያን

      ኒካራጉዋ:- “በኒካራጉዋ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው በደል በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ባለፈው ዓመት ብቻ 52 በመቶ የሚሆኑ ኒካራጓውያን ሴቶች በባሎቻቸው በደል ተፈጽሞባቸዋል።”​—⁠የቢ ቢ ሲ ዜና አገልግሎት

      [ገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      አደጋ ጠቋሚ ምልክቶች

      በዩ ኤስ ኤ የሮድ አይለንድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት ሪቻርድ ጄ ጄልስ መሪነት የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ነገሮች በቤት ውስጥ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ በደል ሊፈጸም እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው:-

      1. ሰውየው ቀደም ሲል በሆነ መንገድ በቤት ውስጥ በሚፈጸም በደል ተሳታፊ ከነበረ።

      2. ሥራ ከሌለው።

      3. የተከለከሉ አደገኛ ዕፆችን ቢያንስ በዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ።

      4. ከወላጆቹ ጋር ይኖር በነበረበት ጊዜ አባቱ እናቱን ሲመታ ይመለከት ከነበረ።

      5. ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩ ከሆነ።

      6. ሥራ ቢኖረውም እንኳ ዝቅተኛ ደሞዝ የሚከፈለው ከሆነ።

      7. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያላጠናቀቀ ከሆነ።

      8. ከ18 እስከ 30 ዓመት ድረስ ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ከሆነ።

      9. ከወላጆቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በልጆቻቸው ላይ ኃይል ይጠቀሙ ከነበረ።

      10. በከባድ ድህነት ውስጥ የሚኖር ከሆነ።

      11. ሰውየውና ሴትየዋ ያደጉበት ባሕል የተለያየ ከሆነ።

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      በቤት ውስጥ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በልጆች ላይ ከባድ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል

  • ድብደባ ለሚፈጸምባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ
    ንቁ!—2001 | ታኅሣሥ 8
    • ድብደባ ለሚፈጸምባቸው ሴቶች የሚሆን እርዳታ

      ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ሴቶች ለመርዳት ምን ሊደረግ ይችላል? በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሰው የሚደርስባቸውን ነገር በሚገባ መረዳት መቻል አለበት። ብዙውን ጊዜ የሚደርስባቸው ጉዳት አካላዊ ብቻ አይደለም። በአብዛኛው ዛቻና ማስፈራሪያም ስለሚደርስባቸው ምንም ዋጋ እንደሌላቸውና ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ሆኖ ይሰማቸዋል።

      በመግቢያው ርዕስ ላይ ታሪኳ የተጠቀሰውን የሮክሳናን ሁኔታ ተመልከት። አንዳንድ ጊዜ ባለቤቷ ቃላትን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። “ያንቋሽሸኛል” ስትል ሮክሳና ተናግራለች። “ ‘ትምህርት እንኳን አልጨረሽም። ያለ እኔ እንዴት ልጆቹን ማሳደግ ትችያለሽ? ለምንም ነገር የማትበቂ ሰነፍ እናት ነሽ። ለመሆኑ ጥለሽኝ ብትሄጂ መንግሥት ልጆቹን እንድትወስጂ የሚፈቅድልሽ ይመስልሻል?’ ይለኛል።”

      የሮክሳና ባል በገንዘብ ወጪም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ይጨቁናታል። መኪናቸውን እንድትነዳ የማይፈቅድላት ከመሆኑም በላይ በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ስልክ እየደወለ ምን እንደምታደርግ ይከታተላል። በአንድ ጉዳይ ላይ የራሷን ምርጫ የሚጠቁም አስተያየት ከሰጠች በቁጣ ይገነፍላል። ስለዚህ ሮክሳና ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደሌለባት ታውቃለች።

      ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም በደል በጣም ውስብስብ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ ነው። እርዳታ መስጠት ትችል ዘንድ በርኅራኄ ለማዳመጥ ሞክር። ብዙውን ጊዜ የእንዲህ ዓይነት ድርጊት ሰለባ የሆነች ሴት የሚደርስባትን ነገር ለመናገር እንደምትቸገር አትዘንጋ። ግብህ አቅሟ በሚፈቅድላት መጠን ሁኔታውን ለመቋቋም በምትወስዳቸው እርምጃዎች ጥንካሬ እንድታገኝ መርዳት መሆን ይኖርበታል።

      ድብደባ የሚፈጸምባቸው አንዳንድ ሴቶች ከባለሥልጣናት እርዳታ መሻት ያስፈልጋቸው ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ችግሩ እንደ ፖሊስ ጣልቃ ገብነት ያለ ሁኔታ እስኪጠይቅ ድረስ ከባድ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ በደሉን የሚፈጽመው ሰው ድርጊቱ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እንዲገነዘብ ሊያደርገው ይችል ይሆናል። ይሁንና በአብዛኛው የተፈጠረው ችግር ካለፈ በኋላ ግለሰቡ ለውጥ ለማድረግ የነበረውን ሐሳብ መልሶ እንደሚተወው አይካድም።

      ድብደባ የተፈጸመባት ሚስት ከባልዋ መለየት ይኖርባታልን? መጽሐፍ ቅዱስ ከትዳር ጓደኛ መለያየትን አቅልሎ አይመለከተውም። ሆኖም ድብደባ የሚፈጸምባት ሚስት ጤናዋን ምናልባትም ሕይወቷን ሳይቀር ለአደጋ ከሚያጋልጥ ሰው ጋር አብራ እንድትኖር አያስገድድም። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:​10-16፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) መጽሐፍ ቅዱስ በጣም አስከፊ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ መለያየትን የማይከለክል በመሆኑ አንዲት ሴት በዚህ ረገድ የምትወስደው ውሳኔ ለራስዋ የተተወ ነው። (ገላትያ 6:​5) ማንም ሰው ቢሆን አንዲት ሚስት ከባልዋ እንድትለይ ለማሳመን መሞከር የለበትም፤ ወይም ደግሞ አንዲት ድብደባ የሚፈጸምባት ሴት ጤናዋ፣ ሕይወቷና መንፈሳዊነቷ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ በደል ከሚፈጽምባት ባልዋ ጋር መኖሯን እንድትቀጥል ማንም ሰው ሊገፋፋት አይገባም።

      ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎች ሊለወጡ ይችላሉን?

      በትዳር ጓደኛ ላይ በደል መፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በቀጥታ የሚጻረር ድርጊት ነው። ኤፌሶን 4:​29, 31 ላይ የሚከተለውን ቃል እናገኛለን:- “ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።”

      የክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ማንኛውም ባል በሚስቱ ላይ በደል የሚፈጽም ከሆነ እወዳታለሁ ሊል አይችልም። ሚስቱን የሚበድል ከሆነ የሚሠራቸው ሌሎች መልካም ነገሮች ሁሉ ምን ዋጋ ይኖራቸዋል? ‘የሚማታ’ ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ልዩ መብቶችን ለማግኘት ብቃት አይኖረውም። (1 ጢሞቴዎስ 3:​3 NW፤ 1 ቆሮንቶስ 13:​1-3) እንዲያውም ምንም ዓይነት የንስሐ ፍሬ ሳያሳይ በተደጋጋሚ በቁጣ የሚገነፍል ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገድ ይችላል።​—⁠ገላትያ 5:​19-21፤ 2 ዮሐንስ 9, 10

      ጠበኛ የሆኑ ወንዶች ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉን? አንዳንዶቹ ተለውጠዋል። ብዙውን ጊዜ ግን የትዳር ጓደኛውን የሚደበድብ ሰው (1) ተግባሩ ስህተት መሆኑን አምኖ ካልተቀበለ፣ (2) ምግባሩን ለመለወጥ ፍላጎት ከሌለውና (3) እርዳታ ካልጠየቀ ለውጥ ያደርጋል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለውጥ ለማድረግ ሊገፋፋ የሚችል ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ተገንዝበዋል። የማወቅ ጉጉት አድሮባቸው ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ በርካታ ሰዎች አምላክን ለማስደሰት የሚገፋፋ ጠንካራ ፍላጎት አዳብረዋል። እነዚህ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋ አምላክን በተመለከተ ‘ዐመፃን የሚወዱትን ነፍሱ እንደምትጠላቸው’ ተምረዋል። (መዝሙር 11:​5 አ.መ.ት ) የትዳር ጓደኛውን የሚደበድብ ሰው የባሕርይ ለውጥ ማድረግ እንዲችል ከመማታት መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ለሚስቱ ያለውን አመለካከትም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ይኖርበታል።

      አንድ ሰው የአምላክን እውቀት ሲያገኝ ሚስቱን እንደ አገልጋይ ሳይሆን እንደ “ረዳት፣” እንደ በታች ሳይሆን ‘አክብሮት’ እንደሚገባት አድርጎ መመልከት እንዳለበት ይማራል። (ዘፍጥረት 2:​18፤ 1 ጴጥሮስ 3:​7) በተጨማሪም ርኅራኄ ማሳየትና የሚስቱን አመለካከት መስማት እንዳለበት ይማራል። (ዘፍጥረት 21:​12፤ መክብብ 4:​1) የይሖዋ ምሥክሮች የዘረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ብዙ ባለትዳሮችን ጠቅሟል። ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም፣ አምባገነን ወይም ጉልበተኛ የሆነ ሰው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም።​—⁠ኤፌሶን 5:​25, 28-30

      “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።” (ዕብራውያን 4:​12 አ.መ.ት ) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ባለ ትዳሮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በሚገባ እንዲያጤኑና እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ቆራጥነት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ከዚህ ይበልጥ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ሰማያዊ ንጉሥ ታዛዥ በሆኑ የሰው ዘሮች ሁሉ ላይ በሚገዛበት ጊዜ የሚመጣውን ከጥቃት ነፃ የሆነ ዓለም የመውረስ አስተማማኝ የሆነና የሚያጽናና ተስፋ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ከግፍና ከጭንቀት ነፍሳቸውን ያድናል።”​—⁠መዝሙር 72:​12, 14

      [በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

      ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም፣ አምባገነን ወይም ጉልበተኛ የሆነ ሰው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቦታ የለውም

      [በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማረም

      • ድብደባ የሚፈጸምባቸው ሴቶች ለባሎቻቸው ድርጊት ተጠያቂ ናቸው።

      ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ብዙ ባሎች ድርጊቱን እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸው ሚስቶቻቸው እንደሆኑ በመግለጽ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ ይሞክራሉ። የቤተሰቡ ወዳጅ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ሳይቀሩ ሚስትየው አስቸጋሪ እንደሆነችና ባልየው አልፎ አልፎ ራሱን መቆጣጠር ቢሳነው ምንም እንደማያስደንቅ አድርገው ሊያስቡ ይችላሉ። ይህ ግን የጥቃቱ ሰለባ በሆነችው ሴት ከማመካኘትና ድርጊቱን የሚፈጽመውን ሰው ከተጠያቂነት ነፃ ከማድረግ ተለይቶ አይታይም። እውነት ለመናገር ከሆነ ድብደባ የሚፈጸምባቸው ሚስቶች ብዙውን ጊዜ የባሎቻቸውን መንፈስ ለማረጋጋት የማያደርጉት ጥረት የለም። ከዚህም በላይ በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን የትዳር ጓደኛን መደብደብ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ዘ ባተረር​—⁠ኤ ሳይኮሎጂካል ፕሮፋይል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው የተነሳ በፍርድ ቤት ትእዛዝ የሥነ ልቦና ሕክምና የሚደረግላቸው ወንዶች የመደብደብ ሱስ የተጠናወታቸው ናቸው። ቁጣቸውን ለማብረድ፣ ካደረባቸው የመንፈስ ጭንቀት ለመገላገል፣ የሚፈጠሩትን ግጭቶች ኃይል ተጠቅመው ለመፍታትና ውጥረትን ለማርገብ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። . . . ብዙውን ጊዜ ተጠያቂነታቸውን አምነው አይቀበሉም ወይም ችግሩን አክብደው አይመለከቱትም።”

      • አንድ ሰው አልኮል መጠጣቱ ሚስቱን እንዲደበድብ ያነሳሳዋል።

      አንዳንድ ወንዶች በሚጠጡበት ጊዜ ይበልጥ ጠበኛ እንደሚሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ አልኮሉን ማመካኛ ማድረግ ምክንያታዊ ነውን? ኬ ጄ ዊልሰን ዌን ቫዮለንስ ቢጊንስ አት ሆም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ሰውየው መስከሩ ራሱን ከመውቀስ ይልቅ ድርጊቱን የሚያመካኝበት ነገር እንዲያገኝ ያደርገዋል” ሲሉ ጽፈዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል:- “ኅብረተሰባችን የሰከረ ሰው በቤት ውስጥ የሚፈጽመውን የኃይል ድርጊት ለመቀበል ብዙም የሚቸገር አይመስልም። ድብደባ የተፈጸመባት ሴት ባልዋን እንደሚበድላት አድርጋ ከመመልከት ይልቅ ከባድ ጠጪ ወይም የአልኮል ሱሰኛ እንደሆነ አድርጋ መመልከት ይቀናታል።” ዊልሰን እንዳመለከቱት እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አንዲት ሴት “ሰውየው መጠጣቱን ካቆመ ድብደባውንም ያቆማል” የሚል የማይሆን ተስፋ እንዲያድርባት ሊያደርግ ይችላል።

      በአሁኑ ጊዜ ብዙ ተመራማሪዎች አልኮል መጠጣትና የትዳር ጓደኛን መደብደብ ሁለት የተለያዩ ችግሮች እንደሆኑ አድርገው መመልከት ጀምረዋል። ደግሞም ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን የሚወስዱ አብዛኞቹ ወንዶች የትዳር ጓደኞቻቸውን አይደበድቡም። ዌን ሜን ባተር ዊሜን የተባለው መጽሐፍ ደራሲዎች እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሰውየው ሚስቱን መደብደቡን እንዲቀጥል የሚያደርገው መሠረታዊው ምክንያት ሚስቱን መቆጣጠር፣ ማስፈራራትና ተገዢ ማድረግ መቻሉ ነው። . . . ይህ ሰው አልኮል ከልክ በላይ የመጠጣትና አደገኛ ዕፆችን የመውሰድ ልማድ የተጠናወተው ነው። ሆኖም የኃይል ድርጊት እንዲፈጽም የሚያነሳሳው ይህ ልማድ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።”

      • የትዳር ጓደኛቸውን የሚደበድቡ ወንዶች ከሁሉም ሰው ጋር ይጋጫሉ።

      ብዙውን ጊዜ የትዳር ጓደኛውን የሚደበድብ ሰው ለሌሎች ጥሩ ጓደኛ መሆን ይችላል። የውጪ አልጋ የቤት ቀጋ ይሆናል። የቤተሰቡ ወዳጅ የሆኑ ሰዎች ሚስቱን እንደሚደበድብ ሲሰሙ ለማመን የሚቸገሩት ለዚህ ሊሆን ይችላል። እውነታው ግን ሰውየው ሚስቱን ተገዢ ለማድረግ ጨካኝ መሆንን መምረጡ ነው።

      • ሴቶች መመታታቸውን አይቃወሙም።

      ይህ አስተሳሰብ መሄጃ የሌላት አንዲት ሴት ልታደርገው የምትችለው ነገር አለመኖሩን ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ይችላል። ድብደባ የሚፈጸምባት ሚስት ለአንድ ለሁለት ሳምንት ሊያስጠጓት የሚችሉ ጓደኞች ይኖሯት ይሆናል፤ ከዚያ በኋላስ እንዴት ትሆናለች? ሥራ መያዝና የቤት ኪራይ እየከፈሉ ልጆችን ማሳደግ የማይቻል ነገር ይሆንባታል። በተጨማሪም ሕጉ ልጆቹን ይዛ እንዳትሄድ ይከለክላት ይሆናል። አንዳንዶች እንዲህ ለማድረግ የሞከሩ ቢሆንም ካሉበት ታድነው በግድ አለዚያም ደግሞ በአንዳንድ ማባበያዎች ተመልሰው እንዲገቡ ተደርጓል። ይህን መረዳት ያልቻሉ ወዳጆች እንዲህ ያሉት ሴቶች የሚፈጸምባቸውን በደል እንደማይቃወሙ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ሊያስቡ ይችላሉ።

  • “አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”
    ንቁ!—2001 | ታኅሣሥ 8
    • “አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”

      ሉርዴስ እየተንቀጠቀጡ ያሉትን ከንፈሮችዋን በጣቶቿ ሸፍና በአፓርታማዋ መስኮት በኩል ውጪውን ትኩር ብላ ትመለከታለች። የላቲን አሜሪካ ሴት ስትሆን ኃይለኛ የሆነው ባሏ አልፍሬዶ ለ20 ዓመታት ሲያሠቃያት ኖሯል። አልፍሬዶ ለውጥ ለማድረግ የተነሳሳ ቢሆንም እንኳ ሉርዴስ ያሳለፈችውን አካላዊና ስሜታዊ ሥቃይ መናገሩ ቀላል ሆኖ አላገኘችውም።

      “ችግር መፈጠር የጀመረው ገና በተጋባን በሁለት ሳምንት ውስጥ ነው” አለች ሉርዴስ ዝግ ባለ አንደበት። “አንድ ጊዜ በቡጢ ሲለኝ ሁለት ጥርሶቼ ረገፉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሰነዘረብኝ ቡጢ ጎንበስ ብዬ ሳመልጥ ቁም ሳጥኑን ጠረመሰው። ይበልጥ የጎዱኝ ግን የሚናገራቸው መጥፎ ቃላት ናቸው። ‘የማትረቢ ቆሻሻ’ ይለኝ ነበር። ምንም የማይገባኝ ደደብ አድርጎ ነበር የሚመለከተኝ። ጥዬው እንዳልሄድ የሦስቱ ልጆቼ ነገር ሐሳብ ሆነብኝ።”

      አልፍሬዶ የሉርዴስን ትከሻ እየደባበሰ “ትልቅ ቦታ ያለኝ ባለሙያ ሆኜ ሳለ የፍርድ ቤት መጥሪያ ሲደርሰኝና ምንም ዓይነት በደል እንዳላደርስባት የሚያስጠነቅቅ ትእዛዝ ሲሰጠኝ በኃፍረት ተሸማቀቅኩ” ሲል ተናገረ። “ለመለወጥ ጥረት ባደርግም ብዙም ሳይቆይ ወደ ወትሮው ልማዴ ተመለስኩ።”

      ሁኔታዎች የተለወጡት እንዴት ነው? “በመንገዱ ዳር የሚገኘው ሱቅ ውስጥ ያለችው ሴት የይሖዋ ምሥክር ነች” ስትል ሉርዴስ ገለጸች፤ አሁን ዘና እንዳለች ፊቷ ላይ በግልጽ ይነበባል። “መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማወቅ እንድችል ልትረዳኝ ፈቃደኛ መሆኗን ገለጸችልኝ። ይሖዋ አምላክ ሴቶችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ተገነዘብኩ። መጀመሪያ ላይ አልፍሬዶን ክፉኛ ቢያስቆጣውም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በመንግሥት አዳራሹ ካሉ ሰዎች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ለእኔ አዲስ ገጠመኝ ነበር። የራሴ የሆነ እምነት ሊኖረኝ እንደሚችል፣ የማምንባቸውን ነገሮች በነፃነት መግለጽና አልፎ ተርፎም ለሌሎች ማስተማር እንደምችል ስገነዘብ በጣም ተገረምኩ። በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለኝ ተረዳሁ። ይህም ብርታት ሰጠኝ።

      “መቼም ልረሳው የማልችል አንድ ትልቅ ለውጥ ተፈጠረ። አልፍሬዶ በየሳምንቱ እሁድ በካቶሊክ የቅዳሴ ሥርዓት ላይ መገኘቱን ቀጥሎ ስለነበር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የጀመርኩትን ግንኙነት አጥብቆ ይቃወም ነበር። ትኩር ብዬ ዓይን ዓይኑን እያየሁ ትምክህት በተሞላበትና በረጋ መንፈስ ‘አልፍሬዶ፣ የአንተ አመለካከትና የእኔ አመለካከት የተለያየ ነው’ አልኩት። የሚገርመው ሊመታኝ አልቃጣም! ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቅኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ላለፉት አምስት ዓመታት ፈጽሞ መትቶኝ አያውቅም።”

      ይሁን እንጂ ከዚህ የላቀ ለውጥ የሚፈጠርበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። አልፍሬዶ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሉርዴስ ከተጠመቀች ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ቤቱ ጋበዘኝና በጣም ደስ የሚሉ ሐሳቦችን ከመጽሐፍ ቅዱስ አካፈለኝ። ለሚስቴ ሳልነግር ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ከሉርዴስ ጋር በስብሰባዎች መገኘት ጀመርኩ። እዚያ የምሰማቸው ብዙዎቹ ንግግሮች ከቤተሰብ ሕይወት ጋር የተያያዙ ስለነበሩ ብዙውን ጊዜ በኀፍረት እሸማቀቅ ነበር።”

      አልፍሬዶ ከስብሰባ በኋላ ወንዶችን ጨምሮ የጉባኤው አባላት ወለሉን ሲያጸዱ በመመልከቱ ልቡ በጣም ተነካ። ወደ ቤታቸው ሲሄድ ደግሞ ባሎች ሚስቶቻቸውን ዕቃ በማጠብ ሲረዷቸው ተመለከተ። እነዚህ እንደ ቀላል የሚታዩ ገጠመኞች አልፍሬዶ እውነተኛ ፍቅር እንዴት በተግባር እንደሚገለጽ እንዲያስተውል አደረጉት።

      ብዙም ሳይቆይ አልፍሬዶ ተጠመቀ። አሁን እሱና ሚስቱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። “ብዙውን ጊዜ ምግብ ከተበላ በኋላ ዕቃዎቹን በማነሳሳትና አልጋ በማንጠፍ ይረዳኛል” አለች ሉርዴስ። “ለሠራሁት ምግብ አድናቆቱን የሚገልጽልኝ ከመሆኑም በላይ ሙዚቃን ወይም ለቤታችን የምንገዛቸውን ነገሮች በመሳሰሉ ጉዳዮች የራሴን ምርጫ እንዳደርግ ይፈቅድልኛል። እነዚህ ነገሮች ቀደም ሲል አልፍሬዶ ፈጽሞ የማያደርጋቸው ነበሩ! በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ እቅፍ አበባ ገዛልኝ። አንዳንዴ ሕልም ይመስለኛል!”

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      “በአምላክ ፊት ዋጋ እንዳለኝ ተረዳሁ። ይህም ብርታት ሰጠኝ”

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ባሎች ሚስቶቻቸውን ዕቃ በማጠብ ሲረዷቸው ተመለከተ

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      አልፍሬዶ ከስብሰባ በኋላ ወንዶችን ጨምሮ የጉባኤው አባላት ወለሉን ሲያጸዱ በመመልከቱ ልቡ በጣም ተነካ

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      “በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ እቅፍ አበባ ገዛልኝ”

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ