-
ጠብ ቤተሰብን ሲያናጋንቁ!—1998 | ሚያዝያ 8
-
-
ጠብ ቤተሰብን ሲያናጋ
“ጥፊም ሆነ መገፍተር፣ በጩቤ መውጋትም ሆነ ተኩሶ መግደል በኅብረተሰባችን ውስጥ ከማንኛውም አካባቢ ይበልጥ ጠብ የሚታይበት ቦታ የቤተሰብ ክልል ነው።”—ቢሃይንድ ክሎዝድ ዶርስ
በአሜሪካ በማንኛውም አካባቢ ከሁለት ቤቶች መካከል በአንዱ ቢያንስ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ጠብ አይጠፋም። ከአራት ቤቶች መካከል በአንዱ ደግሞ በተደጋጋሚ ጠብ ይከሰታል። ከጨለመ በኋላ በጎዳና ላይ መጓዝ የሚፈሩ በርካታ ሰዎች ከጎዳና ላይ ይልቅ የከፋ አደጋ የሚጠብቃቸው እገዛ ቤታቸው ውስጥ መሆኑ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
ይሁን እንጂ በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚነሳ ጠብ በአሜሪካ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በመላው ዓለም ያለ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል በዴንማርክ ከ3 ግድያዎች መካከል ሁለቱ የሚፈጸሙት በቤተሰብ ውስጥ ነው። በአፍሪካ ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው ከጠቅላላ ነፍስ ግድያዎች መካከል፣ መጠኑ ከአገር ወደ አገር የተለያየ ቢሆንም፣ ከ22 እስከ 63 በመቶ የሚሆኑት ግድያዎች የሚፈጸሙት በቤተሰብ ውስጥ ነው። በላቲን አሜሪካም ብዙ ሰዎች፣ በተለይም ሴቶች ትምክህተኛ በሆኑ ወንዶች ዝቅ ተደርገው ይታያሉ፣ ይደበደባሉ እንዲሁም ይገደላሉ።
በካናዳ በየዓመቱ አንድ መቶ የሚያክሉ ሴቶች በባሎቻቸው ወይም አለ ሕጋዊ ጋብቻ አብረዋቸው በሚኖሩ ወንዶች እጅ ሕይወታቸው ያልፋል። ከካናዳ በአሥር እጥፍ የሚበልጥ የሕዝብ ብዛት ባላት ዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ 4,000 የሚያክሉ ሴቶች ጠበኛ በሆኑ ባሎቻቸው ወይም በወንድ ጓደኞቻቸው ይገደላሉ። ከዚህም በላይ በየዓመቱ 2,000 የሚያክሉ ልጆች በወላጆቻቸው የሚገደሉ ሲሆን ያንኑ የሚያክል ቁጥር ያላቸው ወላጆች ደግሞ በልጆቻቸው ይገደላሉ።
አዎን፣ በመላው ዓለም ባሎች ሚስቶቻቸውን ይደበድባሉ፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን ይማታሉ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ይደበድባሉ፣ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ እንዲሁም ልጆች እርስ በርሳቸው ይደባደባሉ። ዌን ፋሚሊስ ፋይት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “ሙሉ ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች በመላ ሕይወታቸው በጣም የሚያናድድ ነገርና አምባጓሮ የገጠማቸው ከሥጋ ዘመዶቻቸው ነው። በዚህ ጊዜ የተሰማቸው ንዴት በማንኛውም ሌላ ግንኙነት ካጋጠሟቸው ሁሉ የከፋ ነው።”
እርስ በርስ የሚፋጅ ቤተሰብ
በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም በደል:- ብዙ ጊዜ ባሎች የጋብቻ የምሥክር ወረቀታቸውን ሚስቶቻቸውን ለመደብደብ እንደሚያስችላቸው የፈቃድ ወረቀት አድርገው ይቆጥሩታል። ወንዶችን የሚማቱ ሴቶች ቢኖሩም በወንዶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ሚስቶቻቸውን በሚደበድቡበት ጊዜ የሚደርሰውን ያህል የከፋ አይሆንም። ፓረንትስ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “በትዳር ጓደኞች ላይ እንደ ደረሱ ሪፖርት ከተደረጉት ከባድ ጥቃቶች መካከል 95 በመቶ የሚሆነው ወንዶች ሴቶችን በመደብደባቸው ምክንያት የደረሰ ነው።”
የኒው ዮርክ ክፍለ ሐገር አቃቤ ሕግ ሹም “በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በአሜሪካውያን ኅብረተሰብ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል። . . . በየዓመቱ 6 ሚልዮን የሚደርሱ ሴቶች እንደሚደበደቡ ኤፍ ቢ አይ ገምቷል” ብለዋል። መጠኑ ከአገር ወደ አገር ይለያይ እንጂ፣ ወንዶች በሴቶች ላይ የሚሰነዝሩት ዱላ፣ በሁሉም አገሮች ለማለት ባይቻልም በአብዛኛዎቹ አገሮች እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ነው።
በዩናይትድ ስቴትስ “ከ10 ሴቶች መካከል አንዷ በጋብቻዋ ዘመን ውስጥ ከባሏ ከባድ ጥቃት (ዱላ፣ ጥፊ፣ እርግጫ ወይም ከዚያ የከፋ) እንደሚደርስባት” ይገመታል። ቀለል ያሉት ጥቃቶች ከታከሉ “በዩናይትድ ስቴትስ ከሁለት ሴቶች መካከል በአንዷ ላይ የኃይል ድርጊት ይፈጸማል” በማለት ፋሚሊ ሪሌሽንስ የተባለው መጽሔት ዘግቧል።
እንዲያውም አንድ የኒው ዮርክ አቃቤ ሕግ ሹም “በባሎቻቸው በመደብደባቸው ምክንያት ሆስፒታል እስከመግባት የሚያደርስ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ቁጥር ተገድደው በመደፈር፣ በዘረፋና በመኪና አደጋ ምክንያት ጉዳት ከሚደርስባቸው እንደሚበልጥ” ተናግረዋል።
ዶክተር ሎይስ ጂ ሊቭዚ “በሴቶችና በቤተሰብ አባሎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በጣም የተስፋፋ ከመሆኑም በላይ ይህን ወንጀል የሚፈጽሙት . . . ተራ የሆኑ ሰዎች ናቸው። . . . መደብና ዘር የማይለይ መላውን ሕዝብ ያጠቃለለ ችግር ነው።”
የኃይል ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ለተፈጸመው ድርጊት ራሳቸው ምክንያት እንደሆኑ ስለሚቆጥሩ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ ይሆናል። ፓረንትስ የተባለው መጽሔት እንደሚያብራራው “በራሷ የማትተማመንና ራሷን ዝቅ አድርጋ የምትመለከት ሴት ራሷን ለጥቃት ዒላማ አድርጋ ታቀርባለች። . . . የጉልበት ጥቃት የሚፈጸምባት ሴት ለራሷ የሚበጅ እቅድ ማውጣትና መሥራት ያስፈራታል።”
በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠር አምባጓሮ በልጆችም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። በኃይል ተጠቅሞ ሌሎችን እንደፈለጉ መቆጣጠር እንደሚቻል ይማራሉ። እንዲያውም ልጆቻቸው እንዲህ ካላደረግሽልኝ “አባዬ እንዲመታሽ አደርጋለሁ” ብለው እንደሚያስፈራሯቸው የሚናገሩ እናቶች አሉ።
በልጆች ላይ የሚፈጸም በደል:- በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች ከባድ ጉዳት፣ የአካል ጉድለት ወይም ሞት የሚያስከትል ኃይለኛ ቅጣት ይፈጸምባቸዋል። ከሚፈጸሙት 200 ጥቃቶች መካከል ሪፖርት የሚደረገው አንድ ብቻ እንደሆነ ይገመታል። ሶሺኦሎጂ ኦቭ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ “ብዙውን ጊዜ ለልጆች ከማንኛውም ቦታ ይበልጥ አደገኛ የሚሆንባቸው የገዛ ቤታቸው ነው።”
የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ኢ ቤትስ አንድ ልጅ በወደፊት ሕይወቱ በሚያሳየው ባሕርይ ላይ ኃይለኛ ተጽእኖ ከሚያሳድሩ የቤተሰብ ሁኔታዎች አንዱ በልጅነቱ የሚፈጸምበት በደል እንደሆነ” ተናግረዋል። ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ ደግሞ “ልጆች አድገው ትልቅ ሰው ሲሆኑ ለራሳቸው በሚኖራቸው ግምት ላይ በቀላሉ የማይሽር ጠባሳ የሚተውና የስሜት ቀውስም የሚያስከትል እንደዚህ የከፋ የሕይወት ገጠመኝ የለም” ብለዋል። ከአራት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ላይ በሚገኙ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያደጉ ልጆች ላይ እንኳን የጠበኝነት ባሕርያት ሊታዩ ችለዋል። እንደነዚህ ያሉት ልጆች ሲያድጉ ዕፅ ወሳጆች፣ ሰካራሞች፣ ወንጀለኞች፣ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ያለባቸው የመሆንና አዝጋሚ እድገት የማሳየት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ይሆናል።
በደል የሚፈጸምባቸው ልጆች በደል በፈጸመባቸው ወላጅ ላይ ቂም መያዛቸው የሚጠበቅ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በደሉ ሲፈጸም ዝም ብሎ በመመልከቱ በደል ባልፈጸመባቸው ወላጅ ላይም ቂም ይይዛሉ። ድርጊቱን በዝምታ የተመለከተው ወላጅ በሕፃኑ አእምሮ ውስጥ የድርጊቱ ተባባሪ ሆኖ ይታያል።
በአረጋውያን ላይ የሚፈጸም በደል:- በካናዳ 15 በመቶ የሚሆኑ አረጋውያን በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ልጆቻቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃት እንደሚፈጽሙባቸው ይገመታል። አንድ ዶክተር እንደተነበዩት “ይህ ሁኔታ የአረጋውያን ቁጥር እየጨመረና በልጆቻቸው ላይ የሚወድቀው የገንዘብና የስሜት ሸክም እየከበደ በሄደ መጠን እየተባባሰ መሄዱ የማይቀር ነው።” ይህ ዓይነቱ ሥጋት በመላው ዓለም እየጨመረ ሄዷል።
ብዙውን ጊዜ አረጋውያን የሚፈጸምባቸውን በደል ለመናገር አይፈልጉም። በደል የሚፈጽምባቸው የሚያስተዳድራቸው ሰው ሊሆን ስለሚችል የሚደርስባቸውን ግፍ ችለው ይኖራሉ። አንዲት አሮጊት ልጅዋንና ምራትዋን ለባለ ሥልጣኖች የምታጋልጠው መቼ እንደሆነ ስትጠየቅ “ሌላ ጊዜ” የሚል መልስ ሰጥታለች። በጣም ስለ ደበደቧት ለአንድ ወር ያህል ሆስፒታል ለመቆየት ተገድዳ ነበር።
በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መካከል የሚፈጸም ጥቃት:- ይህ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኝ በቤተሰብ መሃል የሚከሰት ጠብ ነው። አንዳንዶች “ወንዶች ምንጊዜም ወንዶች ናቸው” በማለት ሁኔታውን ያቃልላሉ። ይሁን እንጂ በአንድ ጥናት በተገኘ መረጃ መሠረት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ልጆች በወንድማቸው ወይም በእህታቸው ላይ የፈጸሙት ወንጀል ከቤተሰባቸው ውጪ በሆነ ሰው ላይ ቢፈጽሙ ኖሮ በወንጀል ሊያስከስሳቸው የሚችል ድርጊት ነበር።
ብዙዎች በወንድም ወይም በእህት ላይ የሚፈጸም በደል ካደጉም በኋላ የማይለቅ ጠባይ እንደሚሆን ያምናሉ። በአንዳንዶች ላይ እንደታየው በትዳር ጓደኛቸው ላይ በደል እንዲፈጽሙ የበለጠ ምክንያት የሆናቸው በወላጆቻቸው መካከል የሚፈጸመውን ጠብ መመልከታቸው ሳይሆን ከወንድማቸው ወይም ከእህታቸው ጋር ሲደባደቡ ያደጉ መሆናቸው ነው።
አደገኛ የሆነ የጦርነት አውድማ
አንድ የሕግ ነክ ጉዳዮች ተመራማሪ የቤተሰብ ግጭት ፖሊሶች ለገላጋይነት ከሚጠሩባቸው ሌሎች የግጭት ዓይነቶች ሁሉ እንደሚበልጥ ገምተዋል። በተጨማሪም ሌላ አይነት ግጭቶችን ሲገላግሉ ከተገደሉት ፖሊሶች ይልቅ በቤተሰብ መካከል የተነሳውን ጠብ ሲገላግሉ የተገደሉት ፖሊሶች እንደሚበልጡ ተናግረዋል። አንድ ፖሊስ “ዘረፋ ከሆነ ቢያንስ ተዘጋጅተህ መሄድህ አይቀርም። አንድ ሰው ቤት ስትገባ ግን ምን ሊያጋጥምህ እንደሚችል ፈጽሞ አታውቅም” ብሏል።
አንድ የምርምር ቡድን በቤተሰብ መሃል ስለሚፈጸም ጠብ ሰፊ ጥናት ካደረገ በኋላ ከውጊያ አውድማ ሌላ የቤተሰብን ያህል የኃይል ድርጊት የሚፈጸምበት የማኅበረሰብ ክልል እንደሌለ ደምድሟል።
በቤተሰብ ውስጥ ጠብ እንዲኖር የሚያደርገው ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ድርጊት የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የኃይል ድርጊት ተገቢ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ይኖር ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት በአሜሪካውያን ኅብረተሰብ ውስጥ እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል።”—የክፍለ ሐገር አቃቤ ሕግ ሹም
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ብዙውን ጊዜ ለልጆች ከማንኛውም ቦታ ይበልጥ አደገኛ የሚሆንባቸው የገዛ ቤታቸው ነው።”—ሶሺኦሎጂ ኦቭ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋምሊ
-
-
በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስኤ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?ንቁ!—1998 | ሚያዝያ 8
-
-
በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስኤ የሚሆነው ነገር ምንድን ነው?
“ቤት የውጭው ኅብረተሰብ ከሚያመጣው ውጥረት፣ ጭንቀትና ምክንያተ ቢስነት መጠለያ ከመሆን ይልቅ እነዚህኑ ውጥረቶች የሚያስተላልፍ እንዲያውም ይበልጥ የሚያባብስ ይመስላል።”
—ዚ ኢንቲሜት ኢንቫይሮንመንት፣ ኤክስፕሎሪንግ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ
በቤተሰብ ውስጥ ስለሚነሳ ጠብ ጥናት ማድረግ ከተጀመረ ገና ብዙም አልቆየም። ሰፋ ያለ ጥናት የተደረገው ባለፉት አሥርተ ዓመታት ነው። ከእነዚህ ጥናቶች የተገኙት ውጤቶች ሁልጊዜ ተመሳሳይ ሆነው ባይገኙም በቤተሰብ ውስጥ ለሚነሱ ጠቦች አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮች ሊታወቁ ችለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
አስተዳደግ ምን አስተዋጽኦ አለው?
በርካታ ተመራማሪዎች ስለደረሱበት ግኝት ሲናገሩ “ቃለ መጠይቅ ያደረግንላቸው ባልና ሚስት ይበልጥ ጠበኛ በሆኑ መጠን ልጆቻቸውም እርስ በርሳቸውም ሆነ ከወላጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ይበልጥ ጠበኞች ሆነው ተገኝተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ወጣት ልጆች በቤት ውስጥ ያለውን ጠብ መመልከታቸው ብቻውን በባሕርያቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያሳድራል። ጆን ብራድሾው የተባሉት ቴራፒስት “እናቱ ስትደበደብ የሚመለከት ልጅ ራሱ እንደተደበደበ ያህል ሆኖ ይሰማዋል” ብለዋል። ኤድ የተባለ አንድ ወጣት አባቱ እናቱን ሲመታት ማየት በጣም ያስጠላው ነበር። ይሁን እንጂ በጊዜው ላይገነዘበው ቢችልም አእምሮው ወንዶች ሴቶችን መቆጣጠር እንደሚኖርባቸውና ይህንንም ለማድረግ ማስፈራራት፣ ማሳመምና ማመናጨቅ እንዳለባቸው እንዲያምን እየተደረገ ነበር። ኤድ ካደገ በኋላ ሚስቱን በተመሳሳይ ሁኔታ መሳደብና መደብደብ ጀመረ።
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ጥልና ድብድብ ያለባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዳይመለከቱ ይከለክላሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ ያየውን ሁሉ አትሞ የሚያስቀር ለጋ አእምሮ ላላቸው ልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን ይኖርባቸዋል።
ውጥረት ምን አስተዋጽኦ አለው?
እርግዝና፣ ሥራ ማጣት፣ የወላጅ ሞት፣ መኖሪያ መለወጥ፣ በሽታ፣ የገንዘብ ችግርና የመሳሰሉት ሌሎች ነገሮች ውጥረት ያመጣሉ። አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ጠብ ሳይደርሱ ውጥረቶችን ይቆጣጠራሉ። አንዳንዶች ግን ውጥረት ካጋጠማቸው፣ በተለይ ሌሎች ችግሮች ከተጨመሩባቸው ወደ ጠብ ያመራቸዋል። ለምሳሌ ያህል በዕድሜ የገፉ ወላጆችን መጦር በተለይ ደግሞ በሽተኛ ከሆነና ጧሪው ደግሞ ሌሎች የቤተሰብ ኃላፊነቶች ከተደራረቡበት የኃይል ድርጊት ለመፈጸም ይገፋፋል።
ልጆችን ማሳደግ ውጥረት ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ነው። በዚህ ምክንያት የልጆች ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ልጆችን ማንገላታትም በዚያው መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በተጨማሪም “በባልና ሚስት መካከል ለዱላ የሚያደርስ ግጭት የሚፈጠረው አብዛኛውን ጊዜ በልጆች ምክንያት ስለሆነ” ልጆች ለጠበኝነት መጨመር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢሃይንድ ክሎዝድ ዶርስ የተባለው መጽሐፍ ዘግቧል።
ስለ ወንድነትና ስለ ሴትነት የተዛባ አመለካከት መያዝ
በካናዳ አንድ የአማካሪዎች ቡድን የሚመሩ ዳን ባጆሬክ የተባሉ ሰው ዱለኛ ወንዶች ስለ ሴቶች የተዛባ አመለካከት እንዳላቸውና “ከየትኛውም ባሕል የመጡ ቢሆኑ ወንዶች ምንጊዜም የተሻሉ እንደሆኑ እንዲያምኑ ተደርገው ያደጉ” መሆናቸውን ተናግረዋል። ለዱለኛ ወንዶች የሚደረግ የተሐድሶ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ሃሚሽ ሲንክሌር ወንዶች የሴቶች የበላይ እንደሆኑና እነርሱን “የመቅጣት፣ የመገሰጽና የማሸማቀቅ” መብት እንዳላቸው እንዲያምኑ ተደርገው ያድጋሉ ብለዋል።
በብዙ አገሮች አንድ ወንድ ሚስቱን በቤቱ ውስጥ ከሚገኙት የመገልገያ ዕቃዎች እንደ አንዱ አድርጎ የመቁጠር መብት እንዳለው ይታመናል። ሚስቱን በኃይል መግዛቱና መቆጣጠሩ የወንድነቱና የክብሩ መለኪያ እንደሆነ ይታሰባል። ሴቶች ብዙ ጊዜ በአሰቃቂ ሁኔታ ይደበደባሉ፣ ወይም በሌላ መንገድ በደል ይፈጸምባቸዋል፣ የአገሮቹም ሕግ ይህንኑ የሚፈቅድ በመሆኑ ከሕጉ ምንም ዓይነት ጥበቃ አያገኙም። ወንዱ የበላይ፣ ሴቷ የበታች በመሆኗ ወንዱ ምንም ያህል ባለጌ፣ ጠበኛ፣ ወራዳ ወይም ራስ ወዳድ ቢሆን ሙሉ በሙሉ ልትታዘዘው ይገባል።
የሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ሪፖርተር የሆነው ሞርሊ ሴፈር ስለ አንድ የደቡብ አሜሪካ አገር የሚከተለውን ሪፖርት አቅርቧል:- “የወንድ ትምክህተኝነት እንደዚህ ገኖ የሚታይበት ሌላ የላቲን አሜሪካ አገር የለም። . . . በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተንሰራፍቶ የሚታይ ባሕርይ ነው። በፍርድ ቤት እንኳን አንድ ወንድ ነፍስ የገደለው ክብሩ ስለተነካበት ከሆነ፣ በተለይም የተገደለችው ሚስቱ ወይም ፍቅረኛው ከሆነች በነጻ ይለቀቃል።” የዚህችን አገር ያህል “ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት አገር በምድር ገጽ ላይ አይገኝም” በማለት በአፅንዖት ተናግረዋል። በዚህ አገር ያለው ሁኔታ የከፋ ይሁን እንጂ የወንድ ትምክህተኝነትም ሆነ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ መመልከት በአንድ አገር ብቻ የተወሰነ አይደለም።
የአንድ በኒው ዮርክ የሚገኝ በቤተሰብ መሃል የሚፈጠር ጠብ አስወጋጅና ሕግ አስከባሪ መሥሪያ ቤት ዲሬክተር የሆኑት ሚና ሹልማን “ዱለኝነት ወንዶች በሴቶች ላይ ያላቸውን የተቆጣጣሪነት ሥልጣን ለማስከበርና ያላቸውን ኃይልና መብት ለማሳየት የሚጠቀሙበት መሣሪያ ነው።” አክለውም “በሥልጣንና በመብት መባለግ በቤተሰብ መሃል ጠብ እንዲነሳ ያደርጋል” ብለዋል።
ሚስታቸውን የሚደበድቡ አንዳንድ ወንዶች የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ሲሆን እንዲህ ያለውን ስሜት በሚስቶቻቸውም ላይ ለማሳደር ይሞክራሉ። ከተሳካላቸው የተመኙትን ስለሚያገኙ በሌላ ሰው ላይ ሥልጣንና የበላይነት እንዳገኙ ይሰማቸዋል። በዚህ መንገድ ወንድነታቸውን ለማረጋገጥ የሚችሉ ይመስላቸዋል። ግን ትክክል ናቸው? ጉልበታቸውን የሚያሳዩት በአቅም በማትተካከላቸው ሴት ላይ በመሆኑ እንዲህ ያለው ድርጊታቸው የሚያረጋግጠው ጠንካራ ሰዎች መሆናቸውን ወይስ ምክንያተ ቢስነታቸውን? ጉልበተኛ የሆነ ወንድ አቅመ ደካማ የሆነችንና ደራሽ የሌላትን ሴት መደብደቡ የወንድነት ምልክት ነው? ጠንካራ ሥነ ምግባር ያለው ሰው ከእሱ ያነሰ አቅም ላላቸውና ረዳት ለሌላቸው ሰዎች አሳቢነትና ርኅራሄ ያሳያል እንጂ በደል አይፈጽምባቸውም።
የዱለኛው ምክንያተ ቢስነት ሌላው ገጽታ ደግሞ እንዲደባደብ የምታደርገው ሚስቱ እንደሆነች መናገሩ ነው። ‘ይህን አጥፍተሻል። የምመታሽ በዚህ ምክንያት ነው።’ ወይም ‘ራት ተዘጋጅቶ ስላልቆየኝ ዋጋሽን ታገኚያለሽ’ ይላታል ወይም ይህንን የመሰለ መልእክት የሚያስተላልፍ ቃል ይናገራታል። በደብዳቢው አእምሮ ስህተቱ የእርሷ ነው። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት ስህተት ብትሠራ እሷን ለመደብደብ ሰበብ ሊሆን አይችልም።
መጠጥ መውሰድ ለውጥ ያመጣ ይሆን?
የአልኮል መጠጥ ራስን የመቆጣጠርን ችሎታ ስለሚቀንስና ለግልፍተኝነት ስለሚያጋልጥ አንዳንዶች ለዱለኝነት እንደሚያነሳሳ መገንዘባቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ምንም መጠጥ ባልወሰደበት ወቅት ለጠብ የመነሳሳት ስሜቱን መቆጣጠር ቢችልም ጥቂት ከጠጣ በኋላ ግን ለጠብ መጋበዝ ይጀምራል። መጠጡ የማመዛዘን ችሎታውን ያደነዝዝበትና ንዴቱን መቆጣጠር ያቅተዋል።
ይሁን እንጂ የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የአልኮል መጠጡ ራሱ ሳይሆን ውጥረት ነው የሚሉ አሉ። ያለባቸውን ውጥረት ለማርገብ ሲሉ የአልኮል መጠጦችን የሚወስዱና ንዴታቸውን ለማብረድ ሲሉ መጣላት የሚቀናቸው ሰዎች በባሕርያቸው አንድ ዓይነት ናቸው በማለት ይናገራሉ። ይህ ማለት ደግሞ ጠጪው ሰው ይስከርም አይስከር የጠበኝነት ዝንባሌ አለው ማለት ነው። ይህ ጉዳይ አከራካሪ ቢሆንም አልኮል ግልፍተኛ ያደርጋል እንጂ አንድ ሰው ስሜቱን እንዲቆጣጠር እንደማያደርግ የተረጋገጠ ነው።
መገናኛ ብዙሐን የሰዎችን ባሕርይ የሚቀርጹበት መንገድ
አንዳንዶች እንደሚሉት የቴሌቪዥንና የሲኒማ ፕሮግራሞች ወንዶች የጉልበተኝነት ባሕርይ እንዲያሳዩ ከማበረታታቸውም በላይ በኃይል ተጠቅሞ ንዴት መወጣት ወይም ግጭቶችን ማስወገድ ተገቢ እንደሆነ ያስተምራሉ። አንድ የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ “እኔ ራሴ ራምቦ የተባለው ፊልም ያሳደረብኝ ስሜት በጣም ይደንቀኛል። ሕግ አክባሪ የሆነው ባሕርዬና [ውስጣዊ] ስሜቴ ራምቦ በፈጸማቸው አሰቃቂ የጅምላ ግድያዎች ሲሰቀቅ ውስጣዊ የሆነው የልጅነት ባሕርዬ ደግሞ ይደሰትበት ነበር” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
ብዙ ልጆች በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዓታት ለሚተላለፉ ቁጥር ሥፍር ለሌላቸው የኃይል፣ አስገድዶ የማስነወር፣ ሌሎች ሰዎችን በተለይም ሴቶችን የሚያዋርዱ ድርጊቶችን ለሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መጋለጣቸው ብዙዎቹ ካደጉ በኋላ እነዚህኑ ፀረ ኅብረተሰብ የሆኑ ድርጊቶች የሚፈጽሙ መሆናቸው አያስደንቅም። በእነዚህ ፕሮግራሞች የሚነኩት ትላልቅ ሰዎችም ጭምር ናቸው እንጂ ልጆች ብቻ አይደሉም።
በተጨማሪም በቴሌቪዥንና በፊልም የሚታዩት የድብደባ፣ የብልግና እና ሴቶችን የሚያዋርዱ ድርጊቶች በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእጅጉ ጨምረዋል። ይህም በቤተሰብ ውስጥ ጠብ እንዲጨምር ማድረጉ የማይቀር ነው። አንድ የምርመራ ቡድን እንዳረጋገጠው “ጠብን በመመልከትና በጠበኝነት ባሕርይ መካከል የቅርብ ዝምድና አለ።”
ራስን ማግለል የሚያስከትለው ተጽእኖ
በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ሕይወት በብቸኝነት የተዋጠ ነው። ሰዎች እንደ ልብ የሚጨዋወቱባቸው ትናንሽ ሱቆች በትላልቅ የገበያ አዳራሾች ተተክተዋል። ብዙ ቤተሰቦች የከተሞች መስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ችግርና ሥራ አጥነት ከለመዷቸው አካባቢዎች እንዲፈናቀሉ ያደርጋቸዋል። ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር በሌለባቸው አካባቢዎች በቤተሰብ ውስጥ ጠብ በዝቶ ተገኝቷል።
ጄምስ ሲ ኮልማን ኢንቲሜት ሪሌሽንሺፕስ፣ ማሬጅ ኤንድ ዘ ፋሚሊ በተባለው መጽሐፋቸው ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማስረዳት ሞክረዋል። አንድ ሰው ብቸኛ ሲሆን ትርጉም ያለው ጭውውት የሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች በጣም አነስተኛ ስለሚሆኑ የጠበኝነት ዝንባሌ ያለው ከሆነ የሚያጋጥመውን ሁኔታ በሚዛናዊነት መመልከትና ምሥጢረኛው ከሆነ ሰው እርዳታ ማግኘት ያቅተዋል። ባሕርዩን የሚያለዝብለት ጓደኛ ወይም የቅርብ ዘመድ የሌለው በመሆኑና በየዕለቱ የተሳሳተ አስተሳሰቡን የሚያርምለት የቅርብ ሰው ባለመኖሩ ስሜቱ ያዘዘውን በቀላሉ እንዲፈጽም ያደርገዋል። ምሳሌ 18:1 እንደሚለው ነው:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።”
ለጠበኛ ቤተሰቦች የሚሆን እርዳታ
በቤተሰብ ውስጥ ለጠብ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች በከፊል ተመልክተናል። ሌሎች መንስዔዎችም አሉ። አንዳንዶቹን ምክንያቶች ለይተን ካወቅን አሁን የሚያስፈልገን መፍትሔዎቹን መመርመር ነው። አንድ ሰው ዘወትር ጠብ ባለበት ቤት ውስጥ የሚኖር ከሆነ ሁኔታው ተባብሶ አምባጓሮ ከመነሳቱ በፊት ግጭቱን እንዴት በአጭር ለመቅጨት ይችላል? የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው? በቤተሰብ መሃል ጠብ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ገጽ 10 ላይ የሚጀምረው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የስሜት ዱላ፣ በቃላት መደባደብ
አካላዊ ምት በእጅ የሚሰነዘር ሲሆን ስሜታዊ ምት ግን በቃላት የሚሰነዘር ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የመሣሪያው አይነት ብቻ ነው። ምሳሌ 12:18 እንደሚለው ነው:- “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ፣ የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።”
ይህ “እንደሚዋጋ ሰይፍ” የሆነው የስሜት ዱላ ምን ያህል አደገኛ ነው? ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ሁለቱም የሚያስከትሉት ውጤት አንድ አይነት ነው። ሁለቱም ያሳምማሉ፣ ያስፈራሉ፣ የመጠቃት ስሜት ያሳድራሉ።”
በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም ስሜታዊ ዱላ:- “በባለ ትዳሮች መካከል የሚከሰተው ጠብ የሚያስከትለው ጉዳት በአካል ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በብዛት፣ ምናልባትም አብዛኛውን ጊዜ በቃልና በስሜት የሚሰነዘር ዱላ ነው” በማለት አንዲት ለረዥም ዓመታት ጥቃት የተሰነዘረባት ሴት ተናግራለች። ጥቃቱ በቅጽል ስም በመጥራት፣ በመጮህ፣ ሁልጊዜ በመተቸት፣ አዋራጅ የስድብ ቃላት በማዥጎድጎድና በዛቻ ሊሰነዘር ይችላል።
የሚያዋርዱ፣ የሚያመናጭቁና የሚያስፈራሩ ቃላት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስክትሉ ይችላሉ። መጥፎ ቃላት በመጀመሪያ ላይ በድንጋይ ላይ እንደሚወርድ የውኃ ጠብታ ምንም ጉዳት የማያስከትሉ ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙ ሳይቆይ ግለሰቡ ለራሱ ያለው ግምት ይናዳል። አንዲት ሴት “ከአካላዊና ከቃላት ዱላ አንዱን ምረጪ ብባል ወዲያው በዱላ መመታቱን እመርጣለሁ” ብላለች። ምክንያቱን ስታስረዳ “ዱላው የተወው ሰንበር ስለሚታይ ሌላው ቢቀር ሌሎች ሰዎች ያዝኑልኛል። የቃላት ዱላ ግን እኔኑ ብቻ ያሳብደኛል። ቁስሉ አይታይም። ማንም ስለ እኔ አይገደውም” ብላለች።
በልጆች ላይ የሚሰነዘር ስሜታዊ ዱላ:- ይህ ደግሞ አንድን ልጅ ቁመናውን፣ ብልህነቱን፣ ችሎታውን ወይም ጠቃሚነቱን በማጥላላት ደጋግሞ መተቸትን ሊጨምር ይችላል። በተለይ ልጅን በሽሙጥ መናገር በጣም ጎጂ ነው። ልጆች ከምር የተነገረውንና ለቀልድ ብቻ የተነገረውን መለየት ስለማይችሉ የሚሰነዘርባቸውን የሽሙጥ አነጋገር እንደ እውነት ይወስዳሉ። ሲን ሆጋን ዳውኒ የተባሉት የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ “ሁሉ ሰው ሲስቅ ልጁ ግን ከልቡ ይከፋል። በዚህም ምክንያት የራሱን ስሜት አለማመንን እየተማረ ይሄዳል” ብለዋል።
ስለዚህ ቶማስ ካርላይል የተባሉት ስኮትላንዳዊ ታሪክ ጸሐፊና ሐያሲ “የሽሙጥ አነጋገር በአጠቃላይ የዲያብሎስ ቋንቋ እንደሆነ ተረድቼአለሁ፣ በዚህም ምክንያት ፈጽሜ ከተውኩት ብዙ ጊዜ ሆኖኛል” ሲሉ የተናገሩት ቃል እውነትነት አለው።
ግፍ በተፈጸመባቸው ልጆች ላይ በርካታ ጥናት ያደረጉት ጆይ ባየርስ “አካላዊ ዱላ አንድን ልጅ ሊገድለው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ መንፈሱንም ጭምር መግደል ይቻላል። ወላጆች በተደጋጋሚ ልጃቸውን በሚተቹበት ጊዜ የሚያደርጉት ይህንኑ ነው” ብለዋል። ፋሚሊ ላይፍ ኤጁኬተር የተባለው መጽሔት “ስሜታዊ ቁስል በግልጽ ከሚታየውና ቀስ በቀስ ሊሽር ከሚችለው አካላዊ ቁስል የተለየ ከመሆኑም በላይ በአንድ ልጅ አእምሮና ስብእና ላይ ሊታይ የማይችል ለውጥ ስለሚያመጣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነትና ገሃዱን ዓለም ያበላሽበታል” ይላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ልጅ በተደጋጋሚ ጊዜ ድብደባ መመልከቱ ወደፊት በሚኖረው ባሕርይ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል
-
-
በቤተሰብ ውስጥ ጠብ የማይኖርበት ጊዜንቁ!—1998 | ሚያዝያ 8
-
-
በቤተሰብ ውስጥ ጠብ የማይኖርበት ጊዜ
“በቤት ውስጥ ጨርሶ ጠብ እንዳይኖር ለማድረግም ሆነ በቤተሰብ ውስጥ የሚነሳውን ጠብ እንዲቀንስ ለማድረግ በኅብረተሰብም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጦች ማድረግን ይጠይቃል።”—ቢሃይንድ ክሎዝድ ዶርስ
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ነፍስ ግድያ የተፈጸመው በሁለት ወንድማማቾች መካከል በተነሣ ጠብ ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 4:8) ከዚያ ወዲህ ባሳለፍናቸው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጅ በቤተሰብ መሃል በሚፈጸም የኃይል ድርጊት ሲታመስ ኖሯል። ለዚህ ችግር መፍትሔ ያስገኛሉ ተብለው የተሰነዘሩ በርካታ ሐሳቦች ቢኖሩም እነዚህ ሐሳቦች የየራሳቸው ድክመት ያለባቸው ናቸው።
ለምሳሌ ያህል ተደባዳቢ ለሆኑ ሰዎች ከሚሰጠው የጠባይ ማረሚያ ፕሮግራም ተጠቃሚ የሚሆኑት ችግር እንዳለባቸው አምነው የተቀበሉት ብቻ ናቸው። ችግሩን በማሸነፍ ላይ የሚገኝ ተደባዳቢ የነበረ አንድ ባል “[ማረሚያ በመቀበል ላይ የምንገኘው] ባሎች አንድ እጅ ስንሆን ‘አሮጊትዋን ልክ ማስገባት ያስፈልጋል’ ብለው የሚደነፉ ምንም አይነት እርዳታ የማይደረግላቸው ከእኛ በሦስት እጅ የሚበልጡ ባሎች አሉ” ብሏል። ስለዚህ ዱለኛ የሆነው ባል የባሕርይ ችግር ያለበት መሆኑን አምኖ መቀበል ይኖርበታል። ዱለኛ የሆነበትን ምክንያት መርምሮ ማወቅ አለበት። ጉድለቶቹን እንዲያርም የሚያስችለው እርዳታ ካገኘ ባሕርዩን ለማረቅ የሚያስችለውን መንገድ መከተል ይችል ይሆናል።
ይሁን እንጂ የማኅበረሰባዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉ ፕሮግራሞች የሠራተኛ እጥረት አለባቸው። በዚህም ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ 90 በመቶ የሚሆኑ በልጆች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች የቤተሰብ ሁኔታ በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ግድያው ከመፈጸሙ በፊት ተጠቁሞ እንደነበር ይገመታል። ስለዚህ የማኅበራዊ ኑሮ ፕሮግራሞችና የፖሊስ ድርጅቶች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር በጣም ውስን ነው። በጣም አስፈላጊ የሆነ ሌላ ነገር አለ።
“አዲሱ ሰው”
አንድ የተመራማሪዎች ቡድን “በቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን ዝምድና ከመለወጥ የተሻለ ምንም ነገር የለም” ብሏል። በቤተሰብ ውስጥ ለጠበኝነት ዋነኛ ምክንያት የሚሆነው የአስተሳሰብ ችግር ስላለ እንጂ ጉልበተኛ መሆንን ለማሳየት የሚደረግ ብቻ አይደለም። ችግሩ የሚመነጨው የቤተሰብ አባሎች ማለትም ባሎች፣ ሚስቶች፣ ልጆች፣ ወላጆች፣ ወንድማማቾችና እህትማማቾች አንዳቸው ለሌላው ካላቸው አመለካከት የተነሳ ነው። በእነዚህ ግንኙነቶች ረገድ መሠረታዊ ለውጥ እንዲኖር ከተፈለገ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አዲስ ሰው’ ብሎ የሚጠራውን አዲስ ስብዕና መልበስ ያስፈልጋል።—ኤፌሶን 4:22-24፤ ቆላስይስ 3:8-10
በቤተሰብ አባሎች መካከል የተሻለ ዝምድና እንዲኖር የሚያስችለውን ክርስቶስ መሰል አዲስ ሰው ለመልበስ የሚረዱንን አንዳንድ ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ዝምድና ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመርምር።—ማቴዎስ 11:28-30ን ተመልከት።
ለልጆች ሊኖር የሚገባ አመለካከት:- ወላጅ የመሆን ኃላፊነት በመውለድ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ በርካታ ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ሸክም ስለሚቆጥሩ የወላጅነት ግዴታቸውን በፍቅር መወጣት ይቸግራቸዋል። በልጆቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙት እንደነዚህ ያሉት ወላጆች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ‘የይሖዋ ስጦታ’ እንደሆኑና ከእርሱ የተገኙ ‘ሽልማቶች’ መሆናቸውን ይናገራል። (መዝሙር 127:3) ወላጆች ለተሰጣቸው ስጦታ ተገቢውን እንክብካቤ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ልጆቻቸውን እንደ ሸክም የሚቆጥሩ ወላጆች በዚህ አመለካከታቸው ረገድ አዲሱን ሰው ማዳበር ይኖርባቸዋል።a
ከልጆች ምክንያታዊ የሆኑ ነገሮችን መጠበቅ:- አንድ ጥናት እንዳመለከተው በልጆቻቸው ላይ በደል የሚፈጽሙ ብዙ እናቶች ሕፃኑ አንድ ዓመት ሲሞላው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንደሚገባው ይጠብቃሉ። ጥናት ከተደረገባቸው እናቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ በስድስት ወር ዕድሜው ትክክልና ስህተት የሆነውን ሊለይ እንደሚችል ይጠብቃሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው ፍጽምና ያለው ሆኖ እንደማይወለድ ያመለክታል። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሕፃን ገና ከተወለደ ጀምሮ ማስተዋል ይኖረዋል አይልም። ከዚህ ይልቅ የአንድ ሰው ‘የማስተዋል ችሎታ’ የሚዳብረው “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት” የሚያስችለውን ስልጠና ካገኘ በኋላ እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 5:14 NW] ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “ልጅነት ጠባይ፣” ስለ ልጅነት “ስንፍና” እንዲሁም ጉርምስና “ከንቱ” ስለመሆኑ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:11፤ ምሳሌ 22:15፤ መክብብ 11:10) ወላጆች የልጆቻቸውን አቅምና ችሎታ በመረዳት ከዕድሜያቸውና ከችሎታቸው ጋር የማይመጣጠን ነገር ከመጠበቅ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።
ለልጆች ዲሲፕሊን መስጠት:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዲሲፕሊን” [NW] ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትርጉም “ማስተማር” ማለት ነው። ስለዚህ ዲሲፕሊን የሚሰጥበት ዋነኛ ዓላማ ለማሰልጠን እንጂ ለማሳመም አይደለም። መማታት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ቢችልም አለ ዱላ ብዙ ዲሲፕሊን መስጠት ይቻላል። (ምሳሌ 13:24) መጽሐፍ ቅዱስ “ተግሳጽን ስማ፣ ጠቢብም ሁን” ይላል። (ምሳሌ 8:33 በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ከዚህም በላይ ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን የሚያናድድ ሁኔታ ሲያጋጥመው ራሱን ‘መግታት’ እንደሚያስፈልገውና ተግሳጽ በሚሰጥበት ጊዜ ‘ትዕግሥት’ ማሳየት እንደሚኖርበት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:24፤ 4:2) ይህም ልጆች በሚቀጡበት ጊዜ እንኳን ከመጠን በላይ መጮህ ወይም ከልክ ያለፈ ኃይል መጠቀም አግባብ አለመሆኑን ያመለክታል።
በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መሠረት እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘የምሰጠው ዲሲፕሊን ያስተምራል ወይስ በማሳመም የሚቆጣጠር ብቻ ነው? የምሰጠው ዲሲፕሊን ትክክለኛ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያሰርጽ ነው ወይስ ፍርሃትን?’
ትልልቅ ሰዎች ሊኖራቸው የሚገባ የባሕርይ ገደብ:- አንድ ተደባዳቢ ባል ሚስቱን የደበደበው “ራሱን መቆጣጠር” ተስኖት እንደሆነ ተናገረ። አንድ አማካሪ ይህን ሰው ሚስትህን በጩቤ ወግተህ ታውቃለህ? ብሎ ጠየቀው። “ይህንንስ በፍጹም አላደርገውም!” ሲል መለሰለት። ሰውዬው ለራሱ ያወጣውና የሚጠብቀው ገደብ እንዳለውና መሠረታዊ ችግሩ ግን እነዚህ ገደቦች ትክክለኛ አለመሆናቸው እንደሆነ እንዲያስተውል ተደረገ።
የአንተስ ገደብ እስከምን ድረስ ነው? አለመግባባቱ ተባብሶ ወደ መደባደብ ከመድረሱ በፊት ታቆማለህ ወይስ በቁጣ ገንፍለህ እስከ መጮህ፣ የስድብ ውርጅብኝ እስከ ማውረድ፣ እስከ መገፍተር፣ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን እስከ መወርወር ወይም እስከ መማታት ትደርሳለህ?
አዲሱ ሰው የአእምሮ ወይም የአካል ዱላ እስከ መሰንዘር የማያደርስ ጥብቅ የሆነ ገደብ አለው። ኤፌሶን 4:29 “ክፉ [“የበሰበሰ፣” NW] ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” ይላል። ቁጥር 31 ደግሞ በመቀጠል “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” ይላል። “ቁጣ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ግልፍተኛ የመሆንን ባሕርይ” ያመለክታል። ቶክሲክ ፓረንትስ የተባለው መጽሐፍ ሕፃናትን የሚደበድቡ ወላጆች የጋራ ባሕርይ “በከፍተኛ ደረጃ ግልፍተኛ መሆን ነው” ማለቱ ትኩረት የሚስብ ነው። አዲሱ ሰው በስሜት ግንፍልነት ላይ ጥብቅ የሆነ የአካልም ሆነ የቃል ገደብ ይጥላል።
እርግጥ አዲሱን ሰው መልበስ የሚኖርበት ባል ብቻ አይደለም። ሚስትም ይህንን ባሕርይ መልበስ ያስፈልጋታል። ባልዋ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ለሚያደርገው ጥረት አድናቆት ማሳየትና ከእርሱ ጋር መተባበር ይኖርባታል እንጂ ቁጣውን የምታነሳሳ መሆን የለባትም። በተጨማሪም ሁለቱም ቢሆኑ አንዳቸው ከሌላው ፍጽምና መጠበቅ አይኖርባቸውም። ከዚህ ይልቅ 1 ጴጥሮስ 4:8ን ሥራ ላይ ለማዋል መጣር ይኖርባቸዋል:- “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”
ለአረጋውያን አክብሮት ማሳየት:- ዘሌዋውያን 19:32 “ሽማግሌውን አክብር” ይላል። አንድ በዕድሜ የገፋ ወላጅ ሕመምተኛ በሚሆንበት ወይም አስቸጋሪ ጠባይ በሚያሳይበት ጊዜ ይህን ትእዛዝ መፈጸም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። አንደኛ ጢሞቴዎስ 5:3, 4 ወላጆችን ስለ ማክበርና ውለታቸውን ስለ መክፈል ይናገራል። ይህም ገንዘብም ሆነ አክብሮት መስጠትን ሊያካትት ይችላል። ወላጆቻችን ራሳችንን ልንረዳ በማንችልበት የጨቅላነት ዕድሜ ብዙ ነገር ስላደረጉልን አሁን እነርሱ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል።
በወንድማማቾችና እህትማማቾች መካከል የሚነሳውን ግጭት ማሸነፍ:- ቃየል ያደረበት ጥላቻ ሥር ሰድዶ ወንድሙን አቤልን ከመግደሉ በፊት “ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፣ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት” የሚል ምክር ተሰጥቶት ነበር። (ዘፍጥረት 4:7) ስሜትን መቆጣጠር ይቻላል። መቻቻልን ተማሩና “እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ።”—ኤፌሶን 4:2
በሌሎች ላይ እምነት መጣልን መማር
በቤታቸው ውስጥ የኃይል ድርጊት ከሚፈጸምባቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ገበናቸውን አይገልጡም። ዶክተር ጆን ራይት “በየጊዜው የሚደበደቡ ሴቶች ስሜታዊና አካላዊ ጥበቃ ለማግኘት ብቃት ያለው ሦስተኛ ሰው መፈለግ ይኖርባቸዋል” በማለት አጥብቀው ይመክራሉ። ይህ ምክር በደል ለሚፈጸምበት ለማንኛውም የቤተሰብ አባል ይሠራል።
አንድ የኃይል ድርጊት የሚፈጸምበት የቤተሰብ አባል እምነቱን በሌላ ሰው ላይ ለመጣል የሚቸገርበት ጊዜ ይኖራል። ምክንያቱም ይህ ሰው በጣም ቅርቡ የሆነው የገዛ ራሱ ቤተሰብ አባል እንኳን ከሥቃይ በስተቀር ያስገኘለት ነገር የለም። ይሁን እንጂ ምሳሌ 18:24 “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” ይላል። እንዲህ ያለውን ወዳጅ ማግኘትና እርሱንም ምሥጢረኛ ለማድረግ መቻል አስፈላጊውን እርዳታ ለማግኘት የሚያስችል ጠቃሚ እርምጃ ነው። እርግጥ ዱለኛውም ግለሰብ ቢሆን እርዳታ ያስፈልገዋል።
በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክር ይሆናሉ። እነዚህ ሰዎች አዲሱን ሰው መልበስ የሚጠይቀውን ጥረት በሙሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በቤተሰባቸው ውስጥ የኃይል ድርጊት ሲፈጽሙ የቆዩ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የቀድሞ ዝንባሌያቸው እንዳያገረሽባቸው መጽሐፍ ቅዱስ “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” እንዲጠቅማቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ለእነዚህ አዳዲስ ምሥክሮች አዲሱን ሰው መልበስ ቀጣይነት ያለው ሂደት እንጂ አንድ ሰሞን ብቻ የሚደረግ ነገር አይደለም። ምክንያቱም ቆላስይስ 3:10 “የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል” ይላል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ስለዚህ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የይሖዋ ምሥክሮች እጅግ ብዙ የሆኑ የመንፈሳዊ ‘ወንድሞችንና እህቶችን፣ እናቶችንና ልጆችን’ እርዳታ ስለሚያገኙ በዚህ ረገድ በጣም አመስጋኞች ናቸው።—ማርቆስ 10:29, 30፤ በተጨማሪም ዕብራውያን 10:24, 25 ተመልከት።
ከዚህም በላይ ከ85,000 በላይ በሆኑት በመላው ዓለም በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ፣ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” የሆኑ አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾች አሉ። ‘ዓይኖቻቸውና ጆሮዎቻቸው የሕዝቡን ችግሮች ለማየትና ለማዳመጥ የተከፈቱ’ ናቸው። (ኢሳይያስ 32:2, 3) ስለዚህ አዲሶችም ሆኑ ቆየት ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አዲሱን ሰው ለመልበስ በሚያደርጉት ጥረት ከክርስቲያን ጉባኤ ብዙ እርዳታ የማግኘት ግሩም አጋጣሚ አላቸው።
ርህሩህ የበላይ ተመልካቾች
እነዚህ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሰዎች ምክር ለማግኘት ወደ እነርሱ ሲመጡ አላንዳች አድልዎ በጥሞና እንዲያዳምጡ የሚያስችላቸውን ስልጠና አግኝተዋል። ሁሉን ሰው፣ በተለይም ከፍተኛ የጭካኔ ድርጊት የተፈጸመባቸውን በታላቅ ርህራሄና ማስተዋል እንዲያዳምጡ ይመከራሉ።—ቆላስይስ 3:12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14
ለምሳሌ ያህል ባልዋ የደበደባት አንዲት ሚስት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊደርስባት ይችላል። በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች በቤተሰብ አባሎች ላይ የሚደርሰው ዱላ ከቤተሰቡ ውጪ ባሉ ሰዎች ላይ ቢፈጸም ኖሮ ተደባዳቢው ሰው ወህኒ መግባቱ አይቀርም ነበር። እንደ ጾታዊ በደል ያሉት ሌሎች ዓይነት በደሎች የተፈጸመባቸው በሚያዙበት መንገድ በደግነት መያዝ አስፈላጊ ነው።
ከዚህም በላይ የአምላክን ሕግ የሚጥሱ ሁሉ ስለ ድርጊታቸው ተጠያቂዎች ናቸው። በዚህ መንገድ የጉባኤው ንጽሕና ይጠበቃል፣ ለንጹሐን ሰዎችም አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ይቻላል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የአምላክ መንፈስ ሳይታገድ በነጻ እንዲፈስ ያስችላል።—1 ቆሮንቶስ 5:1-7፤ ገላትያ 5:9
አምላክ ለጋብቻ ያለው አመለካከት
አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር በሚሆንበት ጊዜ በአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቦ ከሚገኘው የክርስቲያናዊ አኗኗር ሥርዓት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ይስማማል። ወንድ የቤተሰብ ራስ በመሆን በእውነተኛ አምልኮ ረገድ ቤተሰቡን እንደሚመራ ይማራል። (ኤፌሶን 5:22) ይሁን እንጂ ራስ መሆኑ ሚስቱን እንዲደበድብ ወይም ዝቅ አድርጎ እንዲመለከታት ወይም ፍላጎቶችዋን ችላ እንዲል ሥልጣን አይሰጠውም።
እንዲያውም በተቃራኒው የአምላክ ቃል የሚከተለውን ግልጽ ምክር ይሰጣል:- “ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለ ሆንን፣ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፣ ይመግበዋል ይከባከበውማል።” (ኤፌሶን 5:25, 28, 29) የአምላክ ቃል ሚስቶች መከበር እንዳለባቸው በግልጽ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 3:7፤ በተጨማሪም ሮሜ 12:3, 10ንና ፊልጵስዩስ 2:3, 4ን ተመልከት።
ማንኛውም ክርስቲያን ባል ሚስቱን በአንደበቱም ሆነ በአካል እያቆሰለ እወዳታለሁ ወይም አከብራታለሁ ሊል አይችልም። የአምላክ ቃል “ባሎች ሆይ፣ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው” ስለሚል እንዲህ ብሎ ቢናገር ትልቅ ግብዝነት ይሆንበታል። (ቆላስይስ 3:19) በአርማጌዶን የአምላክ ፍርድ በቅርቡ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ሲወርድ ግብዞች ሁሉ የአምላክን አገዛዝ የሚቃወሙ ሰዎች የሚደርስባቸው ዓይነት ዕጣ ይቀበላሉ።—ማቴዎስ 24:51
ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ባል ሚስቱን እንደ ገዛ አካሉ መውደድ ይኖርበታል። የራሱን አካል ይደበድባል፣ ወይስ ፊቱን በቡጢ ይመታል፣ ወይስ የገዛ ራሱን ፀጉር ይነጫል? ራሱን በሌሎች ፊት ያመናጭቃል ወይስ ያሽሟጥጣል? እንዲህ የሚያደርግ ሰው ሌላው ቢቀር አእምሮው ልክ አይደለም መባሉ አይቀርም።
አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን ቢደበድብ ክርስቲያናዊ ሥራዎቹ በሙሉ በአምላክ ፊት ከንቱ ይሆኑበታል። “የሚማታ” ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት ሊሰጠው እንደማይበቃ አስታውሱ። (1 ጢሞቴዎስ 3:3 NW፤ 1 ቆሮንቶስ 13:1-3) በባልዋ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት የምትፈጽም ሚስትም የአምላክን ሕግ ትጥሳለች።
ገላትያ 5:19-21 “ጥል፣ ክርክር . . . ቁጣ” አምላክ የሚያወግዛቸው ባሕርያት መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ “እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ይላል። ስለዚህ የትዳር ጓደኛን ወይም ልጅን መደብደብ ትክክል ሊሆን የሚችልበት አንድም ምክንያት የለም። የአብዛኞቹን አገሮች ሕግም ሆነ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ድርጊት ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳትሙት መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት ክርስቲያን ነን እያሉ የዱለኛነት ጠባይ ስላላቸው ሰዎች ሲናገር “ክርስቲያን ነኝ የሚል ማንኛውም ሰው በተደጋጋሚ በቁጣ እየገነፈለ የኃይል ድርጊት የሚፈጽም ከሆነና ከዚህም ድርጊቱ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ሊወገድ ይችላል” በማለት በዚህ ጉዳይ ላይ ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸውን አመለካከት ግልጽ አድርጓል።—ግንቦት 1, 1975 ገጽ 287 (የእንግሊዝኛ) ከ2 ዮሐንስ 9, 10 ጋር አወዳድር።
የአምላክ ሕግ ምን ይፈቅዳል?
የአምላክን ሕግ በሚጥሱ ሁሉ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የሚሰጠው አምላክ ራሱ ነው። ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ግን ተደባዳቢው የትዳር ጓደኛ የማይለወጥና ከድርጊቱ የማይመለስ በሚሆንበት ጊዜ የአምላክ ቃል ለተበደለው ክርስቲያን ምን የሚፈቅደው ነገር ይኖራል? ንጹሕ የሆነው ወገን የሚደርስበትን አእምሮአዊ፣ መንፈሳዊና አካላዊ ጉዳት ችሎ፣ ሕይወቱን ሳይቀር ለአደጋ አጋልጦ እንዲኖር ይገደዳልን?
መጠበቂያ ግንብ በቤት ውስጥ ስለሚፈጸም የኃይል ድርጊት ካተተ በኋላ የአምላክ ቃል ምን እንደሚፈቅድ ገልጿል። “ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፣ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፣ ባልም ሚስቱን አይተዋት’ ሲል መክሯል።” ጽሑፉ በመቀጠል “የሚፈጸመው በደል ለመሸከም የማይቻል ከሆነ ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ ከሆነ የሚያምነው ወገን ‘ለመለየት’ ሊመርጥ ይችላል። ቢሆንም በተቻለ መጠን እንደገና ‘ታርቆ’ አብሮ ለመኖር ጥረት መደረግ እንደሚኖርበት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:10-16) ይሁን እንጂ ‘መለየት’ ብቻውን ለመፋታትና ሌላ ለማግባት የሚያስችል ምክንያት አይሆንም። ቢሆንም በሕግ መፋታት ወይም በሕግ ተለያይቶ መኖር በሌላ ጊዜ ሊደርስ ከሚችል ዱላ ሊከላከል ይችላል።”—የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መጋቢት 15, 1983፤ ገጽ 28-9፤ በተጨማሪም 21-109 ገጽ 16-17 ተመልከት።
እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች በደል የተፈጸመበት ግለሰብ የሚመርጠው እርምጃ በግሉ የሚወሰን ይሆናል። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።” (ገላትያ 6:5) ማንም ቢሆን ይህን ሊወስንላት አይችልም። በተጨማሪም ማንም ለጤናዋ፣ ለሕይወትዋና ለመንፈሳዊነትዋ አደገኛ ወደሆነባት ዱለኛ ባልዋ እንድትመለስ ሊያስገድዳት ወይም ሊጫናት አይገባም። ይህ በራስዋ ምርጫና ፍላጎት እንጂ ሌሎች በሚጭኑባት ፈቃድ ወይም ተጽእኖ የሚወሰን አይደለም።—ፊልሞና 14ን ተመልከት።
በቤተሰብ መሃል ጠብ የማይኖርበት ጊዜ
የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ሰዎች “ተሳዳቢዎች” “የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው” እንዲሁም “አስፈሪዎች” እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በተነበየው በዚህ የመጨረሻ ቀን በቤተሰብ መሃል ጠብ እንደሚስፋፋ ተምረዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 3 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) አምላክ ከመጨረሻው ቀን በኋላ ሰዎች “ምንም የሚያስደነግጣቸው ሳይኖር በሰላም” የሚኖሩበት ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።—ሕዝቅኤል 34:28 የ1980 ትርጉም
በዚህ አስደናቂ የሆነ አዲስ ዓለም ውስጥ በቤተሰብ መሃል የሚነሳ ጠብ የተረሳ ነገር ይሆናል። “ገሮች ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11
መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስለሚሰጠው ተስፋ ያገኛችሁትን እውቀት የበለጠ እንድትማሩ አጥብቀን እንመክራችኋለን። በአሁኑ ጊዜ እንኳን በቤተሰባችሁ ክልል የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ በማዋል ብዙ ጥቅም ልታገኙ ትችላላችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው በተባለው መጽሐፍ ከምዕራፍ 7 እስከ 9 ላይ “ልጅ መውለድ ኃላፊነትም ስጦታም ነው፣” “በወላጅነታችሁ የምታከናውኗቸው የሥራ ድርሻዎች” እና “ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሰልጠን” የተሰኙት ምዕራፎች የተዋጣ ወላጅ ለመሆን የሚያስችሉ ግሩም የሆኑ በርካታ ምክሮችን ይዘዋል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤተሰብ ውስጥ ለሚፈጠሩ ግጭቶች መፍትሔ እንድታገኙ ይረዱዋችኋል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በደል የተፈጸመባቸው ሰዎች ችግራቸውን ብቃት ላለው ወዳጅ መግለጽ ይኖርባቸዋል
-