የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ባልና ሚስት ሐሳባቸውን በመግለጥ ረገድ ልዩነት አላቸውን?
    ንቁ!—1996 | ሐምሌ 8
    • ባልና ሚስት ሐሳባቸውን በመግለጥ ረገድ ልዩነት አላቸውን?

      ጌታቸው ወደ አበበ ቢሮ ዘው ብሎ ገባ። አንገቱን ስላቀረቀረ የተጨነቀበት ነገር እንዳለ በግልጽ መመልከት ይቻላል። አበበ ወዳጁን በአክብሮት ከተመለከተ በኋላ የሚናገረውን ለመስማት ተዘጋጀ። “ይህን የገባሁትን የሥራ ውል በተሳካ ሁኔታ የምጨርስ አይመስለኝም” በማለት ጌታቸው በረጅሙ ተነፈሰ። “ብዙ ያልጠበቅኳቸው ችግሮች አጋጥመውኛል፣ ዋናው መሥሪያ ቤት ደግሞ በጣም እያጣደፈኝ ነው።” “ለምንድን ነው የምትጨነቀው ጌታቸው?” በማለት አበበ በተረጋጋ መንፈስ ይጠይቀዋል። “ለዚህ ሥራ ከአንተ የተሻለ ሰው እንደማይገኝ ታውቃለህ። እነርሱም ቢሆኑ ይህን ያውቃሉ። እስቲ በቂ ጊዜ ስጠው። የሚሻል አይመስልህም? እኔም እኮ ባለፈው ወር . . .” በማለት የሠራውን ስህተት ይነግረውና አብረው ይስቃሉ። ጌታቸው ጭንቀቱ ቀልሎት ከቢሮው እየሳቀ ይወጣል። አበበም ጓደኛውን ለመርዳት በመቻሉ ደስ ይለዋል።

      አሁን ደግሞ አበበ በዚያው ምሽት ቤቱ እንደገባ ሚስቱ አልማዝ አንድ የተበሳጨችበት ነገር እንዳለ በቀላሉ ተመለከተ። ከወትሮው በተለየ ሞቅ ያለ ስሜት ሰላምታ ከሰጣት በኋላ ያስጨነቃት ነገር ምን እንደሆነ እንድትነግረው መጠበቅ ጀመረ። በዝምታ ተውጠው ከቆዩ በኋላ አልማዝ “አሁንስ ፈጽሞ መቋቋም አልቻልኩም! ይህ አዲስ አለቃ በጣም ጨቋኝ ነው” ትለዋለች። አበበ ቁጭ እንድትል ካደረገ በኋላ እጁን ትከሻዋ ላይ አድርጎ “አትበሳጪ የኔ ቆንጆ። ይህ በሥራ ዓለም ያለ ነገር ነው። አለቆች ሲባሉ እንዲህ ናቸው። የእኔም አለቃ ዛሬ እንዴት እንደጮኸብኝ ልነግርሽ አልችልም። ቢሆንም ይህን ያህል የሚያበሳጭሽ ከሆነ ሥራውን ልትተይ ትችያለሽ” ይላታል።

      አልማዝ “ስለ እኔ ስሜት ፈጽሞ ግድየለህም!” ስትል በቁጣ ትመልስለታለች። “ፈጽሞ አታዳምጠኝም! ሥራውን ልተው አልችልም! አንተ የምታመጣው ገንዘብ አይበቃንም!” ወደ መኝታ ቤት ሮጣ ከገባች በኋላ በሩን ዘግታ ስቅስቅ ብላ ማልቀስ ትጀምራለች። አበበ ደንግጦ ምን እንደሆነች በመገረም ከውጭ ቆሞ ይጠብቃል። አበበ ሊያጽናናት ብሎ የተናገረው ቃል ይህን የመሰለ ያልተጠበቀ ውጤት ያስከተለው ለምን ይሆን?

      በወንድና በሴት መካከል የባሕርይ ልዩነት ስላለ ነውን?

      በእነዚህ ምሳሌዎች ልዩነት የተፈጠረው ጌታቸው ወንድ፣ አልማዝ ሴት ስለሆነች ነው የሚል ቀላል መልስ የሚሰጡ ሰዎች ይኖራሉ። የሥነ ልሳን ተመራማሪዎች በጋብቻ ውስጥ ሐሳብ ለሐሳብ የመግባባት ችግር የሚፈጠረው በጾታ ልዩነት ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ። እንደ ዩ ጀስት ዶንት አንደርስታንድ (ፈጽሞ አይገባህም) እና ሜን አር ፍሮም ማርስ፣ ውመን አር ፍሮም ቬነስ (ወንዶች ከማርስ፣ ሴቶች ደግሞ ከቬነስ የመጡ ናቸው) ያሉት መጻሕፍት ወንዶችና ሴቶች አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ቢሆኑም በግልጽ ሊታይ የሚችል የአነጋገር ስልት ልዩነት አላቸው የሚለውን አስተሳሰብ ያራምዳሉ።

      ይሖዋ ሴትን ከወንድ በፈጠረ ጊዜ በጥቂቱ ብቻ ከወንድ ለየት ያለች እንድትሆን አድርጎ እንዳልፈጠራት የታወቀ ነው። ወንድና ሴት አንዱ የሌላውን አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች እንዲያሟሉ በጥሩ ማስተዋል ውብ ሆነው የተፈጠሩ ናቸው። በእነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑ የባሕርይ ልዩነቶች ላይ የአስተዳደግና የሕይወት ተሞክሮ ልዩነቶች፣ ባሕል፣ የአካባቢ ሁኔታና ማኅበረሰቡ ለወንድነትና ለሴትነት ያለው አመለካከት በባሕርይ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ሲጨመር ሁኔታው በጣም የተወሳሰበ ይሆናል። እነዚህን ተጽእኖዎች በሙሉ ግምት ውስጥ በማስገባት ወንዶችና ሴቶች ሐሳባቸውን በመግለጽ ረገድ ያላቸውን ልዩነት ለይቶ ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል። ይሁን እንጂ “አይነተኛው ወንድ” ወይም “አይነተኛዋ ሴት” የሚገኙት በሥነ ልቦና መጻሕፍት ብቻ ነው።

      ሴቶች ስሜታውያን እንደሆኑ ይነገራል። ይሁን እንጂ ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ርህሩህና ስሜታዊ የሆኑ ብዙ ወንዶች አሉ። በምክንያታዊነት የማሰብ ባሕርይ ያላቸው በአብዛኛው ወንዶች ናቸው ቢባልም ጥሩ የማመዛዘንና የማስተዋል ችሎታ ያላቸው ብዙ ሴቶች አሉ። ስለዚህ ይህ ባሕርይ ሙሉ በሙሉ የሴቶች ወይም የወንዶች ነው ለማለት አይቻል እንጂ አንድ እርግጠኛ የሆነ ነገር አለ። ነገሮችን በሌላው ግለሰብ አመለካከት ለማየት መቻልና አለመቻል በተለይ በትዳር ውስጥ ተስማምቶ በሰላም ለመኖር ወይም ለግጭትና ለጦርነት ምክንያት ሊሆን ይችላል።

      ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ ውስጥ ሐሳብ ለሐሳብ ለመግባባት ባለመቻላቸው ምክንያት በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ችግሮች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ብዙ አስተዋይ የሆኑ ባሎች ሊያረጋግጡ እንደሚችሉት “የፀጉሬ አሠራር እንዴት ነው?” እንደሚሉት ያሉ ቀላል የሚመስሉ ጥያቄዎች አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጥበበኛ የሆኑ ሚስቶች በሚጓዙበት ጊዜ ባላቸው መንገዱ ከጠፋው “ለምን ቆም ብለህ ሰው አትጠይቅም?” እያሉ በተደጋጋሚ መጠየቅ ጥሩ እንዳልሆነ ተምረዋል። አፍቃሪ የሆኑ የትዳር ጓደኞች የባላቸውን ወይም የሚስታቸውን ልዩ ባሕርይ አቃልለው “ጠባዬ ነው፣ ምንም ማድረግ አልችልም” በማለት ከራሳቸው ጠባይ ጋር የሙጥኝ ከማለት ይልቅ የትዳር ጓደኛቸውን ውስጣዊ ባሕርይ ለማስተዋል ይጥራሉ። እንዲህ ሲባል አንዳቸው የሌላውን የሐሳብ አገላለጽ በቀዝቃዛ ስሜት ይመረምራሉ ማለት ሳይሆን አንዳቸው የሌላውን ልብና አእምሮ ለማስተዋል በፍቅር ይገፋፋሉ ማለት ነው።

      አንዱ ሰው ከሌላው የተለየ እንደሆነ ሁሉ እያንዳንዱ የጋብቻ ጥምረትም በዓይነቱና በባሕርዩ የተለየ ነው። እውነተኛ የሆነ የአእምሮና የልብ ስምምነት የሚገኘው በአጋጣሚ አይደለም። ሰብዓዊ ባሕርያችን ፍጽምና የጎደለው በመሆኑ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል ሌሎች ስለ አንድ ነገር ያላቸው አመለካከት ከእኛ አመለካከት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ማሰብ በጣም ቀላል ነው። ብዙ ጊዜ ለእኛ ሊደረግልን የምንፈልገውን ነገር ለሌሎች እናደርጋለን። ምናልባት “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማ ሕግ የፈጸማችሁ ሊመስላችሁ ይችላል። (ማቴዎስ 7:12) ይሁን እንጂ ኢየሱስ እናንተ የምትፈልጉት ነገር ሁሉ ለሌላውም ሰው ጥሩ እንደሚሆን አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ሌሎች እናንተ የሚያስፈልጋችሁን ወይም የምትፈልጉትን ነገር እንዲሰጧችሁ እንደምትመኙ ማመልከቱ ነበር። ስለዚህ እነሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር መስጠት አለባችሁ ማለት ነው። በተለይ በትዳር ውስጥ ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላውን ፍላጎት ለመፈጸም ቃለ መሐላ የፈጸሙ በመሆናቸው ይህን መፈጸም በጣም አስፈላጊ ነው።

      አልማዝና አበበ ይህን መሐላ ፈጽመዋል። ተጋብተው ያሳለፏቸው ሁለት ዓመታት አስደሳች ነበሩ። ይሁን እንጂ እርስ በርሳቸው በሚገባ እንደሚተዋወቁ ቢሰማቸውም በበጎ ፈቃድ ብቻ ሊወገድ የማይችል ሰፊ የመግባባት ክፍተት በመካከላቸው መኖሩን የሚያሳዩ ሁኔታዎች የሚፈነዱባቸው ጊዜያት አሉ። ምሳሌ 16:23 (አዓት) “የጠቢብ ሰው ልብ አፉ አስተዋይ እንዲሆን ያደርጋል” ይላል። አዎን፣ ሐሳብ ለሐሳብ በመግባባት ረገድ አስተዋይ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። አስተዋይነት ለአበበና ለአልማዝ ምን ዓይነት በር ሊከፍትላቸው እንደሚችል እንመልከት።

      የወንድ አመለካከት

      አበበ የሚኖረው እያንዳንዱ ሰው የበታችነትም ሆነ የበላይነት ደረጃ ቢኖረው ድርሻውን ለመፈጸም በሚገደድበት የፉክክር ዓለም ውስጥ ነው። ደረጃውን፣ ብቃቱን፣ ችሎታውንና ጠቃሚነቱን የሚያሳየው በመናገር ነው። ነጻነቱን እንደ ውድ ነገር ይመለከታል። ስለዚህ አበበ እንዲህ አድርግ ተብሎ ከታዘዘ ትእዛዙን ለመቀበል እምቢተኛ ይሆናል። የቀረበለት ጥያቄ ምክንያታዊ ቢሆንም “ሥራህን እንደሚገባ አልፈጸምክም” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ከሆነ እምቢተኛ ለመሆን ይገፋፋል።

      አበበ ከሰዎች ጋር የሚነጋገርበት መሠረታዊ ምክንያት መረጃ ለመለዋወጥ ነው። ስለተማራቸው አዳዲስ ነገሮች፣ ስለ አንዳንድ ሐሳቦችና ተጨባጭ ሁኔታዎች መናገር ይወዳል።

      አበበ በሚያዳምጥበት ጊዜ የሚነገረውን ነገር ከራሱ ጋር ለማዋሃድ ስለሚፈልግ በተናጋሪው ንግግር ጣልቃ ለመግባት “እህ! አዎ!” እንደሚሉት ባሉት ቃላት እንኳን ለማቋረጥ አይፈልግም። የማይስማማበት ነገር ከኖረ ግን በተለይ የቅርብ ወዳጁ ከሆነ ተቃውሞውን ለመግለጽ ወደኋላ አይልም። ወዳጁ የሚነግረውን ነገር ከተለያዩ ገጽታዎች ለማስተዋል ጥረት ያደርጋል፣ ይህም ለሚያዳምጠው ነገር ፍላጎት ያለው መሆኑን ያሳያል።

      አበበ ችግር ካጋጠመው ብቻውን ሆኖ የችግሩን መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግ ይመርጣል። ስለዚህም ከማንኛውም ሰውም ሆነ ነገር ይርቃል። አለበለዚያም ችግሩን የሚያስረሳው ነገር ለማድረግና ለመዝናናት ይፈልጋል። ችግሩን ለሰው የሚያዋየው ምክር ሲፈልግ ብቻ ነው።

      አበበ እንደ ጌታቸው ችግር አጋጥሞት ወደ እርሱ የሚመጣ ሰው ካጋጠመው ወዳጁን ብቃት እንደጎደለው ሳይሰማው የመርዳት ኃላፊነት እንዳለበት ይገነዘባል። በሚሰጠው ምክር ላይ አክሎ ራሱ ያጋጠመውን ችግር በመናገር ችግሩ በወዳጁ ላይ ብቻ የደረሰ እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ያደርጋል።

      አበበ ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ያስደስተዋል። ለእርሱ ጓደኝነት ማለት አንዳንድ ነገሮች አብሮ ማድረግ ነው።

      ለአበበ ቤቱ ማንነቱን ለማሳየት ለመናገር የማይገደድበት፣ በእሱነቱ ብቻ የሚታመንበት፣ የሚወደድበት፣ የሚደነቅበትና ተቀባይነት የሚያገኝበት፣ ከአደባባይ ኑሮ እፎይ የሚልበት ቦታ ነው። ቢሆንም አበበ ብቻውን መሆን የሚፈልግበት ጊዜ ይኖረዋል። አልማዝን ወይም እርስዋ የምታደርጋቸውን ነገሮች ለመሸሽ ብሎ ላይሆን ይችላል። የፈለገው ብቻውን ለመሆን ብቻ ነው። አበበ ስጋቱን፣ ጭንቀቱንና በውስጡ ያለውን ያለመረጋጋት መንፈስ ለሚስቱ መግለጽ ያስቸግረዋል። እንድትጨነቅ አይፈልግም። እርስዋን መንከባከብና መጠበቅ ግዴታው እንደሆነና አልማዝም ይህን ግዴታውን እንደሚወጣ እንድትተማመንበት ይፈልጋል። አበበ ድጋፍ እንዲሰጠው ቢፈልግም የማንንም አዘኔታ አይፈልግም። ሰዎች እንደሚያዝኑለት ሲናገሩ ብቃት እንደሌለውና ዋጋ ቢስ እንደሆነ ይሰማዋል።

      የሴት አመለካከት

      አልማዝ ራስዋን የምትመለከተው ማኅበራዊ ግንኙነቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ እንዳለች አንዲት ግለሰብ ነው። ለእርስዋ እነዚህን ግንኙነቶችና ዝምድናዎች ማጠናከር በጣም አስፈላጊ ነው። ከሌሎች ጋር ቅርርብ ለመፍጠርና የተፈጠረውን ቅርርብ ለማጠንከር መነጋገር ያስፈልጋታል።

      ለአልማዝ የሌሎች ጥገኛ መሆን የተፈጥሮ ባሕርይ ነው። አበበ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት የእርስዋን አስተያየት ቢጠይቅ እንደምትወደድ ይሰማታል። ቢሆንም ባልዋ ነገሮችን በቀዳሚነት እንዲያከናውን ትፈልጋለች። ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ባልዋን ማማከር ትወዳለች። ይህን የምታደርገው ቅርበትዋንና በእርሱ የምትታመን መሆንዋን ለማሳየት እንጂ ምን ማድረግ እንደሚገባት እንዲነግራት ላይሆን ይችላል።

      አልማዝ ይህን እፈልጋለሁ ብላ በቀጥታ መናገር በጣም ያስቸግራታል። አበበን ለመጨቅጨቅ ወይም ደስተኛ እንዳልሆነች እንዲሰማው ለማድረግ አትፈልግም። ከዚህ ይልቅ የሚያስፈልጋትን እንዲያስተውል ትፈልጋለች ወይም ስለሚያስፈልጋት ነገር ፍንጭ የሚሰጥ ነገር ታደርጋለች።

      አልማዝ ከሌሎች ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜ ዝርዝር ነገሮችን ለማወቅ ትፈልጋለች፣ ብዙ ጥያቄዎችም ትጠይቃለች። ይህም ለሰዎችና ከሰዎች ጋር ላላት ግንኙነት በጣም አሳቢ ከመሆን የተፈጥሮ ባሕርይዋ የሚመነጭ ነው።

      አልማዝ በምታዳምጥበት ጊዜ ተናጋሪውን እንደምትከታተል ወይም ስለሚናገረው ወይም ስለምትናገረው ነገር ፍላጎት ያላት መሆኑን ለማሳየት በተደጋጋሚ ጥያቄዎች ትጠይቃለች፣ ወይም ራስዋን ትነቀንቃለች ወይም የቃለ አጋኖ ቃላት ታሰማለች።

      ሰዎች ስለሚፈልጉት ነገር ገና ሳይናገሩ ለማወቅ ትጣጣራለች። ለእርስዋ ሳትጠየቅ እርዳታ መስጠት ፍቅርዋን ለመግለጽ የሚያስችላት ግሩም መንገድ ነው። በተለይ ባልዋ እድገት እንዲያደርግና እንዲሻሻል ለመርዳት ትፈልጋለች።

      አልማዝ ችግር ሲያጋጥማት ትደናገጣለች። መፍትሔ ለማግኘት ባይሆንም ስሜትዋን መግለጽና ለሰው መናገር ትፈልጋለች። ችግርዋን የሚረዳና የሚያስብላት ሰው መኖሩን ለማወቅ ትፈልጋለች። ስሜትዋ በሚረበሽበት ጊዜ ጥፋተኛውንና ጥፋተኛ ያልሆነውን የማይመርጥ ከባድ ንግግር ትናገራለች። “ፈጽሞ አትሰማኝም!” ስትል ቃል በቃል አትሰማኝም ማለትዋ አይደለም።

      አልማዝ ዘወትር የምታስታውሳት የልጅነት ጓደኛዋ አብራት ብዙ ነገር የሠራች ጓደኛዋ ሳትሆን ስለ ብዙ ነገሮች አብራት ያወራችዋ ናት። ስለዚህ በትዳርዋም ስሜትዋን የምታካፍለው ጥሩ አድማጭ የማግኘትን ያህል በውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አያስደስቷትም።

      ለአልማዝ ቤትዋ የሚተቻት ሳይኖር እንደልብዋ ልትናገር የምትችልበት ቦታ ነው። ስጋትዋንና ጭንቀትዋን ለአበበ ለመግለጽ ወደ ኋላ አትልም። እርዳታ የሚያስፈልጋት ከሆነ ምን ጊዜም ባልዋ ከጎንዋ እንደሚሆንና እንደሚያዳምጣት ስለምትተማመንበት እርዳታውን መጠየቅ አያሳፍራትም።

      አልማዝ አብዛኛውን ጊዜ እንደምትወደድ ይሰማታል፣ ስለትዳርዋም አትሰጋም። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ምንም ግልጽ ምክንያት ሳይኖራት ስጋትና ያለመወደድ ስሜት ተሰምቷት በአጣዳፊ ማጽናኛና ባልንጀራ ማግኘት ትፈልጋለች።

      አዎን፣ አበበና አልማዝ አንዳቸው የሌላው ማሟያ ሲሆኑ የተለያየ ባሕርይ አላቸው። ሁለቱም የትዳር ጓደኛቸውን ለመውደድና ለመደገፍ ልባዊ ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑም በመካከላቸው ያለው ልዩነት ከባድ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከላይ በጠቀስነው ሁኔታ እያንዳንዳቸው ከራሳቸው አመለካከት አንጻር የተሰማቸውን ሲናገሩ ለመስማት ብንችል ምን ይሉ ይሆን?

      በራሳቸው ዓይን የተመለከቷቸው ነገሮች

      “ወዲያው በሩን ከፍቼ እንደገባሁ አልማዝ የተበሳጨችበት ነገር እንዳለ ለማየት ችዬአለሁ” ይላል አበበ። “በጊዜው የተበሳጨችበትን ምክንያት የምትነግረኝ መስሎኝ ነበር። ለኔ ይህን ያህል ከባድ ችግር ሆኖ አልታየኝም። ይህን ያህል መበሳጨት እንደማይኖርባትና መፍትሔውም ቀላል እንደሆነ እንድትገነዘብ ከረዳኋት ብስጭቷ ይሻላታል ብዬ አሰብኩ። ሳዳምጣት ከቆየሁ በኋላ ‘ፈጽሞ አትሰማኝም!’ ስትለኝ በጣም አዘንኩ። ለብስጭትዋ ሁሉ እኔን ምክንያት እንዳደረገች ሆኖ ተሰማኝ።”

      አልማዝ የበኩሏን ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “ቀኑን ሁሉ ስበሳጭ ነበር የዋልኩት። ስህተቱ የአበበ እንዳልነበረ አውቃለሁ። በጣም ደስ ብሎት ሲገባ ግን የኔን መበሳጨት ከጉዳይ ያልቆጠረው ሆኖ ተሰማኝ። ምን እንደሆንኩ ለምን አልጠየቀኝም? ችግሬን ስነግረው የሰጠኝ ምላሽ የማልረባና ትንሹን ነገር የማጋንን መሆኔን የሚያሳይ ነበር። መፍትሔ ፈላጊው አበበ ስሜቴን እንደሚረዳልኝ ከመናገር ይልቅ እንዴት ችግሬን መወጣት እንደሚኖርብኝ ነገረኝ። እኔ የፈለግሁት ስሜቴን እንዲረዳልኝና እንዲያዝንልኝ እንጂ መፍትሔ እንዲሰጠኝ አልነበረም!”

      አበበና አልማዝ ይህን የመሰለ ጊዜያዊ አለመግባባት ቢያጋጥማቸውም በጣም ይዋደዳሉ። ይህን ፍቅራቸውን ለመግለጽ የሚችሉት ምን ነገር ቢያስተውሉ ነው?

      ነገሮችን በሌላው ሰው ዓይን ማየት

      አበበ፣ አልማዝ ምን እንደሆነች ቢጠይቃት በግል ጉዳይዋ ውስጥ መግባት የሚሆንበት መስሎ ተሰማው። ስለዚህም ሰዎች ሊያደርጉለት የሚፈልገውን ነገር አደረገላት። ራስዋ አውጥታ እስክትናገር ድረስ ጠበቃት። አልማዝ ግን ካጋጠማት ችግር በተጨማሪ አበበ ሊረዳት ዝግጁ አለመሆኑ አበሳጫት። ዝም ማለቱን አክብሮት እንደሆነ ሳይሆን ግድየለሽነት እንደሆነ ቆጠረች። አልማዝ መናገር ስትጀምር ደግሞ አበበ ምንም ነገር ሳይናገር አዳመጣት። እርስዋ ግን ስሜቷን የማያዳምጣት ሆኖ ታያት። ካዳመጠ በኋላ ደግሞ አዘኔታውን ሳይሆን መፍትሔ ነገራት። ይህም ‘ያንቺ ስሜት ግምት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም፣ ይህን ችግር መፍታት ምን ያህል ቀላል እንደሆነ እይ’ የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነበር።

      ሁለቱም ራሳቸውን በሌላው ቦታ አድርገው ችግሩን ቢያዩት ኖሮ እንዴት ያለ የተለየ ውጤት ይገኝ ነበር! እንደሚከተለው ሊሆን ይችል ነበር።

      አበበ ቤቱ ሲገባ አልማዝን ተበሳጭታ ያገኛታል። ቀስ ብሎ “አልማዝዬ፣ ምን ሆነሻል?” ብሎ ይጠይቃል። እንባዋ እየተናነቃት መናገር ትጀምራለች። አልማዝ “ጥፋቱ ያንተ ነው” ማለትዋ ወይም አበበ የሚገባውን እንደማያደርግ መናገርዋ አይደለም። አበበ እቅፍ ያደርጋትና በትዕግሥት ያዳምጣታል። ስትጨርስ “በጣም ስለተበሳጨሽ አዝናለሁ። ይህን ያህል የተበሳጨሽው ለምን እንደሆነ ገብቶኛል” ይላታል። አልማዝም “ስላዳመጥኸኝ በጣም አመሰግናለሁ። ስሜቴን እንደተረዳኽልኝ በማወቄ በጣም ቀለል ብሎኛል” ትለዋለች።

      ብዙ ባለ ትዳሮች በመካከላቸው የሚነሳውን አለመግባባት ከመፍታት ይልቅ ለመፋታት ይመርጣሉ። ለብዙ ቤቶች መፍረስ ምክንያቱ ሐሳብ ለሐሳብ አለመግባባት ነው። የትዳራቸውን መሠረት የሚያናጋ ጭቅጭቅ ይነሳል። እንዲህ ያለው ጭቅጭቅ የሚነሳው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ጭቅጭቅ የሚነሳው እንዴት እንደሆነና እንዴት ማስወገድ እንደሚቻል ይነግረናል።

  • የጭቅጭቅ መንስኤና ባሕርይ
    ንቁ!—1996 | ሐምሌ 8
    • የጭቅጭቅ መንስኤና ባሕርይ

      እሷ የፈለገችው ስሜቷን ለመግለጽ ነው። እርሱ ግን መፍትሔ ለመስጠት ይፈልጋል። በዘመናት በሙሉ በትዳር ውስጥ የተነሱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ጭቅጭቆች የተለያየ ይዘት ቢኖራቸውም በአብዛኛው በጥቂት መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው። የትዳር ጓደኛችሁ ከእናንተ የተለየ አመለካከት ወይም የሐሳብ አገላለጽ እንዳለው/ላት ከተረዳችሁ እንደ ቋያ እሳት የሚንቀለቀለውን ወላፈን አብርዳችሁ ደስታ የሰፈነበትን ቤት የሚያሞቅ የከሰል ፍም ለማድረግ ትችላላችሁ።

      “ሕይወቴን እንድትቆጣጠሪ አልፈልግም!”

      አንድ ባል ጨቅጫቃና በባልዋ ላይ ለመሠልጠን የምትፈልግ ሚስት ካለችው ከሚስቱ በሚሰነዘሩት ምክሮች፣ ጥያቄዎችና ትችቶች ምክንያት መፈናፈኛ እንዳጣ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠበኛ ሚስት እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት” በማለት ይህ ዓይነቱ ስሜት ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ያመለክታል። (ምሳሌ 19:13) ሚስት ባልዋን አንድ ነገር ስትጠይቅ እርስዋ ባላወቀችው ምክንያት ጥያቄዋን በዝምታ ያልፋል። ያልሰማ ይመስላትና ደግማ እንዲህ አድርግ ትለዋለች። በዚህ ጊዜ ባል የባሰውን ይናደድና ዝም ይላል። ሴቲቱ ነዝናዛ ሚስት፣ ወንዱ ደግሞ በሚስቱ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ የሚሰማው ባል ናቸው? ወይስ እንዲያው ሐሳብ ለሐሳብ ያልተግባቡ ሁለት ግለሰቦች?

      በሚስት አመለካከት ለባልዋ ጠቃሚ ምክር ስትሰጥ ለእርሱ ያላትን ፍቅር ከሁሉ በተሻለ መንገድ መግለጿ እንደሆነ ይሰማታል። በባልዬው አመለካከት ግን አለቃው ለመሆን መፈለግዋና ብቃት የሌለው መሆኑን ማመልከትዋ ነው። ለእርስዋ “ቦርሳህን እንዳትረሳ” ስትል አሳቢነትዋን መግለጽዋና የሚያስፈልገውን ሁሉ መያዙን ማረጋገጥዋ ነው። ለእርሱ ግን ልጅ ሳለ እናቱ “ሹራብህን ለብሰሃል?” ትለው የነበረውን ያስታውሰዋል።

      ሚስት ድካም ተሰምቷት ባሏን “ዛሬ ውጭ መብላት ትፈልጋለህ?” ብላ ትጠይቃለች። እንደ እውነቱ ግን “ዛሬ ስለደከመኝ ምግብ ማብሰል አልችልምና ውጭ ወጥተን እንብላ” ማለቷ ነው። ለሚስቱ ከፍተኛ አክብሮት ያለው ባል ግን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እርስዋ የምትሠራውን ያህል የሚጥመው ምግብ እንደሌለ ያረጋግጥላታል። አለበለዚያም ‘እንደፈለገች ልትጠመዝዘኝ ነው’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። በዚህ ጊዜ ሚስቲቱ ቅር በመሰኘት ‘ቀድሞውንስ ምን አስጠየቀኝ?’ ትላለች።

      “አትወደኝም!”

      የተበሳጨውና ግራ የተጋባው ባል “እንዴት እንዲህ ይሰማታል?” “እሠራለሁ፣ የቤቱን ወጪ በሙሉ እሸፍናለሁ፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አበባ አመጣላታለሁ” ይላል።

      መወደድ የሁሉ ሰው የጋራ ፍላጎት ቢሆንም ሴት የምትወደድ መሆኗ በተደጋጋሚ እንዲረጋገጥላት ትፈልጋለች። አውጥታ በአፍዋ ባትናገርም በውስጧ በተለይ፣ በወርሐዊ ልማድዋ ምክንያት ስሜትዋ በሚነካበት ጊዜ ያልተፈለገች ሸክም እንደሆነች ሊሰማት ይችላል። በእነዚህ ጊዜያት ባልዋ ለብቻዋ መሆን ያስፈልጋታል ብሎ በማሰብ ሊርቃት ይችላል። እርስዋ ግን ይህን የእርሱን መራቅ በጣም የፈራችውን ነገር ማለትም የማይወዳት መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ማስረጃ አድርጋ ትተረጉመዋለች። እንዲወዳትና ድጋፍ እንዲሰጣት ለማስገደድ ፈልጋ በቁጣ ልትናገረው ትችላለች።

      “ምን ሆነሃል ውዴ?”

      ወንድ አሳሳቢ ችግር ሲያጋጥመው ጸጥ ያለ ቦታ ይፈልግና ችግሩን ያሰላስላል። በዚህ ጊዜ ሚስቱ አንድ ውጥረት እንዳለበት በደመ ነፍስ ትገነዘብና ራሱን ከቀበረበት የሐሳብ ጉድጓድ ልታወጣው ትሞክራለች። ይህን ያደረገችው በቅን ልቦና ቢሆንም ባልዬው በግል ጉዳዩ እንደገባችበትና እንዳዋረደችው አድርጎ ይቆጥረዋል። ከሐሳቡ ነቅቶ ወደኋላው ዞር ሲል ታማኝ ሚስቱ በቁርጠኝነት ስትከታተለው ይመለከታል። “እባክህ ምን ሆነሃል? ደህና አይደለህም እንዴ? እስቲ እንነጋገርበት?” የሚለውን የሚስቱን ድምፅ ይሰማል።

      ሚስት ምላሽ ካላገኘች በጣም ይከፋታል። እርሷ ችግር ሲያጋጥማት ከባልዋ ጋር መነጋገር ትፈልጋለች። ይህ የምትወደው ሰው ግን ስሜቱን ሊያካፍላት አይፈልግም። “ባይወደኝ ነው” ከሚል መደምደሚያ ላይ ትደርሳለች። ስለዚህ በሚስቱ አእምሮ ውስጥ የሚጉላላውን ሐሳብ ያላወቀው ባል ባገኘው መፍትሔ ረክቶ ከራሱ ውስጣዊ ዓለም ሲወጣ የሚያገኘው አፍቃሪና አሳቢ የነበረችውን የትዳር ጓደኛ ሳይሆን ቸል ያልከኝ ለምንድን ነው ብላ የምታፋጥጠውን የተቆጣች ሴት ይሆናል።

      “ፈጽሞ አትሰማኝም!”

      መሠረተ ቢስ ክስ ሆኖ ይሰማዋል። ከዚህ የበለጠ እንዴት ሊያዳምጣት እንደሚችል ግራ ይገባዋል። ይሁን እንጂ ሚስቱ በምትናገርበት ጊዜ ቃሎችዋ የሂሣብ ስሌት በሚያደርግ ኮምፒዩተር በመመዘን ላይ ያለ ሆኖ ይሰማታል። ባልዋ በንግግርዋ መካከል ጣልቃ ገብቶ “ታዲያ ለምን . . .” ብሎ የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርብላት ጥርጣሬዋ እውነት መሆኑን ታረጋግጣለች።

      ሚስት ያጋጠማትን ችግር ይዛ ወደ ባልዋ ስትመጣ አብዛኛውን ጊዜ የችግሯ ምክንያት ባልዋ መሆኑን ለመናገር ወይም ለችግርዋ መፍትሔ ለማግኘት አይደለም። ከሁሉ በላይ የምትፈልገው ደረቁን ሐቅ ብቻ ሳይሆን ስሜትዋን ጭምር በአዘኔታ የሚያዳምጣት ሰው ነው። ስለዚህ የምትፈልገው ምክር ሳይሆን ስሜትዋን የሚረዳላት ሰው ነው። አንድ ባል በቀና መንፈስ “ውዴ፣ እንዲህ ሊሰማሽ አይገባም። ነገሩኮ ይህን ያህል ከባድ አይደለም” በማለቱ ብቻ ሚስቱ በቁጣ ትገነፍላለች።

      ብዙ ሰዎች የትዳር ጓደኞቻቸው በአእምሮአቸው ውስጥ ያለውን የማንበብ ችሎታ እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ። አንድ ሰው “ከተጋባን 25 ዓመት አልፎናል” ይላል። “ይህን በሚያህል ጊዜ ውስጥ ምን እንደምፈልግ ለማወቅ ካልቻለች ለማወቅ አትፈልግም ወይም በቂ ትኩረት አላደረገችም ማለት ነው።” አንድ ደራሲ ስለ ጋብቻ ግንኙነት በጻፉት መጽሐፍ እንዲህ ብለዋል:- “የጋብቻ ተጓዳኞች ምን እንደሚፈልጉ ከመናገር ይልቅ እርስ በርስ ከተተቻቹና እንዲህ አላደረግህም፣ እንዲህ አላደረግሽም እየተባባሉ ከተካሰሱ የፍቅርና የትብብር መንፈስ እየጠፋ ይሄዳል። በቦታው . . . እያንዳንዱ ተጓዳኝ ሌላው ፍላጎቱን እንዲፈጽምለት የሚያስገድድበት የትግል መድረክ ይከፈታል።”

      “ፈጽሞ ኃላፊነት አይሰማህም!”

      ሚስት አፍዋን አውጥታ ባልዋን በቀጥታ እንዲህ ባትልም በአነጋገርዋና በድምፅዋ እንዲህ የሚል መልእክት ልታስተላልፍ ትችላለች። “ለምን እስካሁን አመሸህ?” የሚለው ጥያቄ መረጃ ለማግኘት ብቻ የቀረበ ሆኖ ሊታይ ይችል ይሆናል። ፈርጠም ባለ አመለካከት ሽንጧን ይዛ ከተናገረች ግን “ፈጽሞ ኃላፊነት የማይሰማህ ሰው ነህ። በጣም አስጨነቅኸኝ። አትደውልም ነበር? ለሰው አታስብም! ይኸው የሠራሁት ራት ተበላሸ” የሚል መልእክት ያስተላልፋል።

      ስለ ራት መበላሸት የተናገረችው እውነት መሆኑ አይካድም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጭቅጭቅ ከተነሣ ግን በመካከላቸው ያለውም ዝምድና መበላሸቱ ይቀር ይሆን? ዶክተር ጆን ግሬይ እንደሚሉት “አብዛኞቹ ጭቅጭቆች የሚፈጠሩት ሁለት ሰዎች ስላልተስማሙ ሳይሆን ወንድዬው ሚስቱ አስተሳሰቡን እንደማትቀበል ሲሰማው ወይም ሴቲቱ የባልዋን አነጋገር ስላልወደደች ነው።”

      አንድ ሰው በራሱ ቤት ውስጥ ለአፉ ልጓም ሳያደርግ እንደልቡ መናገር አለበት ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ሐሳቡን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጽ ሰው የአድማጩን ስሜት ግምት ውስጥ በማስገባት ስምምነትና ሰላም ማስፈን ይኖርበታል። እንዲህ ያለውን አነጋገር ለትዳር ጓደኛ ቀዝቃዛ ውኃ በማቀበል ወይም ፊት ላይ በመርጨት መመሰል ይቻላል። ልዩነት ያመጣው አቀራረቡ ብቻ ነው።

      የቆላስይስ 3:12-14⁠ን ቃላት ሥራ ላይ ማዋል ጭቅጭቅ አስወግዶ ደስታ የሰፈነበት ቤት እንዲኖር ያስችላል። “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”

      [በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      እሱ የሚሟገተው ስለ ሐቅ ነው፣ እሷ የምትሟገተው ስለ ስሜት ነው

  • ደስታ የሰፈነበት ቤት ሁለቱ አንድ በሚሆኑበት ጊዜ
    ንቁ!—1996 | ሐምሌ 8
    • ደስታ የሰፈነበት ቤት ሁለቱ አንድ በሚሆኑበት ጊዜ

      ጠንካራ፣ አስተማማኝና ምቹ ቤት መሥራት ከፈለግክ እንዴት ባሉ የግንባታ ዕቃዎች ትጠቀማለህ? በእንጨት፣ በጡብ ወይስ በድንጋይ? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል። “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል። በእውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ ጓዳዎች ይሞላሉ።” (ምሳሌ 24:3, 4) አዎን፣ ደስታ የሰፈነበት ቤት ለመገንባት ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት ያስፈልጋል።

      ቤቱን የሚገነባው ማን ነው? “ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፣ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሠዋለች።” (ምሳሌ 14:1) ሁኔታው ለወንዱም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። ትዳሩን ጠንካራና ደስታ የሰፈነበት አለበለዚያም ደካማና ምሬት የሞላበት ሊያደርግ ይችላል። ልዩነት የሚያመጣው ምንድን ነው? አንዳንድ ዘመናዊ የጋብቻ አማካሪዎች የሚሰጡት ምክር በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከተጻፉት ዘመን የማይሽራቸው የአምላክ ቃል ምክሮች ጋር በጣም የሚቀራረብ መሆኑ ያስገርማል።

      ማዳመጥ:- ስለ ጋብቻ ምክር የሚሰጥ አንድ መጽሐፍ “ለአንድ ሰው አክብሮት እንዳላችሁ ከምታሳዩባቸው ትላልቅ መንገዶችና የተቀራረበ ዝምድና ለመመስረት ከሚያስችሏችሁ ወሳኝ ነገሮች አንዱ ማዳመጥ ነው” ይላል። የምሳሌ መጽሐፍ “የጠቢባን ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች” ይላል። (ምሳሌ 18:15) የጆሮ ክፍት መሆን እንደ ዓይንና አፍ በግልጽ ሊታይ ስለማይችል የትዳር ጓደኛችሁን እንደምታዳምጡ እንዴት ማሳየት ትችላላችሁ? አንደኛው መንገድ የምታዳምጡ መሆናችሁን የሚያሳይ አካላዊ ወይም የቃል መግለጫ መስጠት ነው።— በገጽ 11 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

      ግልጽ መሆንና መቀራረብ:- ዋን ቱ ዋን— አንደርስታንዲንግ ፐርሰናል ሪለሽንሽፕስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል። “ባሕላችን ግልጽነትን ይቃወማል። ከልጅነታችን ጀምሮ በሰው ጉዳይ ውስጥ እንዳንገባ፣ ገንዘብን፣ አስተሳሰብንና ስሜትን . . . በጠቅላላው የግል ጉዳዮችን ስለሚመለከቱ ነገሮች ምሥጢረኞች እንድንሆን ይነገረናል። ይህ ትምህርት የምንወደው የትዳር ጓደኛ በምናገኝበት ጊዜም ጥሎን አይሄድም። ግልጽ ለመሆን የማያቋርጥ ጥረት ካልተደረገ የተቀራረበ ዝምድና ሊኖር አይችልም።” የምሳሌ መጽሐፍ “የምሥጢር ውይይት ካልኖረ የታቀደው አይሳካም። በሚመካከሩ ዘንድ ግን ጥበብ ይኖራል” ይላል።— ምሳሌ 13:10፤ 15:22 አዓት

      መተማመን:- ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆን በአምላክ ፊት ምለዋል። የትዳር ጓደኞች አንዳቸው ለሌላው የተወሰኑ እንደሆኑና ታማኝ የመሆን ግዴታ እንዳለባቸው እርግጠኛ ሲሆኑ በመካከላቸው ያለው ፍቅር በጥርጣሬ፣ በኩራት፣ በፉክክር መንፈስ፣ የየበኩል ድርሻ ለማግኘት በሚደረግ ትግል አይቆረቁዝም።

      ማካፈል:- በባልና ሚስት መካከል ያለው ዝምድና ጥልቀት እያገኘ የሚሄደው አብረው በሚያሳልፏቸው ተሞክሮዎች ነው። ከጊዜ በኋላ እያንዳንዳቸው በደስታ የሚያስታውሷቸው በርካታ ትዝታዎች ይኖሯቸዋል። ይህን የመሰለውን ጠንካራ ዝምድና ማፍረስ ሊያስቡት እንኳን የማይችሉት ነገር ይሆናል። “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።”— ምሳሌ 18:24

      ደግነትና ርህራሄ:- ደግነት በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ግጭቶች ከመቀነሱም በላይ የኩራትን መንፈስ ያረግባል። ደግነት የተለመደና ሥር የሰደደ የዘወትር ባሕርይ ከሆነ አለመግባባት ተፈጥሮ የስሜት መጋጋል በሚኖርበት ጊዜ እንኳን ጸንቶ ስለሚኖር በተፈጠረው አለመግባባት የሚከሰተው ጉዳት በጣም አነስተኛ ይሆናል። ርህራሄ ፍቅር ሊያድግ የሚችልበት ሞቅ ያለ ሁኔታ እንዲኖር ያስችላል። የርህራሄና የፍቅር ጠባይ ማሳየት በተለይ ለወንዶች አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ “ከምድራዊ ሰው የሚፈለገው ፍቅራዊ ቸርነት ነው” ይላል። (ምሳሌ 19:22 አዓት) ጥሩ ሚስት ደግሞ “የርህራሄ ሕግ በምላስዋ” ይኖራል።— ምሳሌ 31:26

      ትህትና:- ትህትና የኩራትን መርዝ የሚያረክስ መድኃኒት ሲሆን ይቅርታ ለመጠየቅ ፈጣኖች ለመሆንና አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ያነሳሳናል። ፈጸማችሁ ስለተባላችሁት ጥፋት ፈጽሞ የምታውቁት ነገር ካልኖረስ? ለምን በደግነት “ይህን ያህል ስለ ተሰማህ/ሽ በጣም አዝናለሁ” አትሉም? ስለ ትዳር ጓደኛችሁ ስሜት የምታስቡ መሆናችሁን ከገለጻችሁ በኋላ የተፈጠረውን ችግር እንዴት ልታስወግዱ እንደምትችሉ አብራችሁ ተወያዩ። “ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው።”— ምሳሌ 20:3

      መከባበር:- “ከትዳር ጓደኛችን ጋር ያለንን ልዩነት ለመገንዘብና ችግሮች ሲነሱ አብረን ለመፍታት የሚያስችለን ቁልፍ መከባበር ነው። ለአንደኛው የትዳር ጓደኛ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ለሌላኛው በጣም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ቢሆንም አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሁልጊዜ የሌላውን አመለካከት ማክበር ይኖርበታል።” (ኪፒንግ ዩር ፋምሊ ቱጌዘር ዌን ዘ ወርልድ ኢዝ ፎሊንግ አፓርት) “በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፣ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት።”— ምሳሌ 13:10

      በራስ ስህተት የመሳቅ ችሎታ:- በጣም ከባድ የሆነ የግጭት ጭጋግ ከልብ በመነጨ ስሜት አብሮ በመሳቅ ሊወገድ ይችላል። የፍቅርን ሰንሰለት ከማጠንከሩም በላይ የማሰብ ችሎታችንን የሚያዳክምብንን ውጥረት ያረግብልናል። “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል።”— ምሳሌ 15:13

      መስጠት:- የትዳር ጓደኛችሁን መልካም ጎን ፈልጉና አድናቆታችሁን በለጋስነት መንፈስ ግለጹ። ይህ ዓይነቱ የአድናቆት መግለጫ የክራባት ወይም የአበባ ስጦታ ከመስጠት የበለጠ ልባዊ ስሜት ሊቀሰቅስ ይችላል። እርግጥ አንዳችሁ ለሌላችሁ ስጦታ ልትገዙ ወይም ጥሩ ነገር ልታደርጉ ትችላላችሁ። ላይፍ ስኪልስ ፎር አደልት ችልድረን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ግን “በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች በስጦታ ወረቀት ተጠቅልለው የሚመጡ አይደሉም። ፍቅራችሁንና አድናቆታችሁን ከመግለጽ፣ ማበረታቻና እርዳታ ከመስጠት የበለጠ ስጦታ ሊኖር አይችልም” “በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል በብር ላይ እንደፈሰሰ የወርቅ ጌጥ ውበት ይኖረዋል።”— ምሳሌ 25:11 የ1980 ትርጉም

      እነዚህ የተለያዩ ባሕርያት የትዳር ሕንጻ በሚገነባባቸው ጡቦች ቢመሰሉ ጡቦቹን እርስ በርሳቸው የሚያያይዘው ሲሚንቶ ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት ነው። ስለዚህ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ባልና ሚስት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ጌቲንግ ዘ ላቭ ዩ ዋንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “የትዳር ጓደኛችሁን የአመለካከት ልዩነት የግጭት ምክንያት እንደሆነ ሳይሆን . . . የእውቀት ምንጭ እንደሆነ አድርጋችሁ ቁጠሩ። . . . በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ዝርዝር ሁኔታዎች ተዝቆ የማያልቅ የእውቀት ማዕድን ይሆንላችኋል።”

      እያንዳንዱን ያለመግባባት አጋጣሚ እንደ ጦርነት ጥሪ ሳይሆን ይህን የምትወዱትን/ዷትን ግለሰብ ይበልጥ ለማወቅ የሚያስችላችሁ አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በአንድነት ለሚያጋጥሟችሁ ችግሮች መፍትሔ እየፈለጋችሁ፣ ሰላምና አንድነት እየፈጠራችሁ ሁለት የተለያያችሁ ግለሰቦች የሆናችሁትን አንድ የሚያደርገውን ሰንሰለትና ፍቅር ይበልጥ ጥብቅ እንዲሆን ታደርጋላችሁ።

      ይሖዋ በፍጥረቱ ውስጥ በሚታየው ትብብርና ቅንብር በጣም ይደሰታል። እጽዋትና እንስሳት በመሰጣጠትና በመቀባበል የኦክስጅን ዑደት ያካሂዳሉ፤ የጠፈር አካላት የተወሰነላቸውን ምሕዋር ሳይለቁ ይዞራሉ፤ አበቦችና ጥቃቅን ነፍሳት ተረዳድተውና ተጋግዘው ይኖራሉ። በጋብቻ ጥምረትም ውስጥ ባል በቃልም ሆነ በድርጊት ሚስቱን እንደሚወድ የሚያረጋግጥበትና አፍቃሪ የሆነች ሚስት ደግሞ የባልዋን አመራር በፍቅር የምትከተልበት ሞቅ ያለ ዑደት ሊኖር ይችላል። በዚህ መንገድ ሁለቱ የትዳር ጓደኞች ሁለት ከመሆን ይልቅ አንድ በመሆን አንዳቸው ሌላውንና የጋብቻ መሥራች የሆነውን ይሖዋ አምላክን ያስደስታሉ።

      [በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ‘እንዴት እንደምታዳምጡ ተጠንቀቁ።’— ሉቃስ 8:18

      ንቁ አድማጭ መሆን ተናጋሪና አድማጭ በእርግጥ የተግባቡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል። ንቁ አድማጭ መሆን አንዳንድ ጊዜ በእንግሊዝኛ ሚረሪንግ ይባላል። እንዲህ የሚባለው አድማጩ የሚሰማቸውን ቃላትና ያገኘውን ግንዛቤ ልክ እንደመስተዋት ለማንጸባረቅ ስለሚሞክር ነው። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ መሠረታዊ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው:-

      1. የሚነገረውን በጥሞና መከታተል፤ አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን ማዳመጥ።

      2. ከቃሎቹ በስተጀርባ ያለውን ስሜት ማዳመጥ።

      3. የሰማኸውን ለተናጋሪው መድገም። ተናጋሪውን አትተች፣ አትፍረድ ወይም አትቃወም። መልእክቱን በትክክል እንደተረዳህ ብቻ እንዲያውቅ አድርግ። ስሜቱን እንደምትረዳ ግለጽ።

      4. ተናጋሪው በትክክል እንደተረዳህ ያረጋግጥልሃል ወይም የተናገርኸውን ካስተካከለ በኋላ ተጨማሪ መግለጫ ይሰጥ ይሆናል።

      5. ያንተ ግንዛቤ ትክክል ካልነበረ በድጋሚ ሞክር።

      በተለይ በንቃት ማዳመጥ ትችት መስማት የሚያስከተለውን ሕመም በእጅጉ ይቀንሳል። ትችት የሚሰነዘረው አብዛኛውን ጊዜ በተወሰነ እውነት ላይ ተመሥርቶ መሆኑን መቀበል ያስፈልግሃል። ትችቱ የቀረበው በሚያሳምም መንገድ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ራስን በመከላከል መንፈስ ተቺውን በዚያው መጠን ለማሳመም ከመሞከር ይልቅ በንቃት በማዳመጥ ሁኔታውን ብታረግቡ የተሻለ አይሆንም? ለምንም ዓይነት ሁኔታ ኃላፊ እንደሆናችሁ ቢነገር ነገሩን እንደተረዳችሁ በመግለጽ ለተፈጠረው ሁኔታ መፍትሔ የሚገኝበትን መንገድ አስቡ።

      [በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

      ‘ቅር የተሰኛችሁበት ነገር ቢኖር’— ቆላስይስ 3:13

      ቅር የተሰኛችሁበት ነገር ቢኖር ጦርነት ሳታስነሱ ቅሬታችሁን ማሰማት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ የትዳር ጓደኛችሁ መጥፎ ዓላማ ወይም ፍላጎት እንደሌለው/ላት ተናገሩ። አሳቢነት የጎደለው/ላት፣ ችኩል፣ ጥበብ የሌለው/ላት ሆኖ ወይም ሆና ይታያችሁ/ትታያችሁ ይሆናል። ቢሆንም በአጠቃላይ ሲታይ ታስቦ የተደረገ ወይም ለመጉዳት ታቅዶ የተደረገ አይሆንም። የክስ ቃል ሳትጠቀሙ በእርጋታ ስሜታችሁን መግለጽ ትችላላችሁ። “እንዲህ በማድረግህ/ሽ . . . ተሰማኝ” ቢባል ምንም ክርክር ወይም ጭቅጭቅ የሚያስነሳ ነገር አይኖርም። ይህ አነጋገር የሚገልጸው ስሜታችሁን ብቻ ስለሆነ በትዳር ጓደኛችሁ ላይ የተሰነዘረ ክስ አይሆንም። ግለሰቡ/ቧ ቀድሞውንም ቢሆን እናንተን ለማበሳጨት ሆን ብሎ/ላ ያደረገው/ችው ነገር ስለሌለ እንዲህ አላደረግኩም ሊል/ልትል ወይም ሰበብ ሊያቀርብ/ልታቀርብ ይችላል/ትችላለች። ይሁን እንጂ ትኩረታችሁን ችግሩ ላይ በማድረግ መፍትሔ ለመጠቆም ዝግጁ ሁኑ።

      [በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ለአንድ ሰው አክብሮት እንዳላችሁ ከምታሳዩባቸው ትላልቅ መንገዶች አንዱ ማዳመጥ ነው

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ