-
በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣትራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
ምዕራፍ 35
በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸም የሞት ቅጣት
1. መልአኩ ቀዩን አውሬ የገለጸው እንዴት ነው? የራእይን ምልክቶች ለመረዳት የሚያስፈልገው ምን ዓይነት ጥበብ ነው?
መልአኩ በራእይ 17:3 ላይ ስለተጠቀሰው ቀይ አውሬ ተጨማሪ መግለጫ ሲሰጥ ለዮሐንስ እንዲህ አለው:- “ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፣ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፣ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” (ራእይ 17:9, 10) እዚህ ላይ መልአኩ ያሳወቀው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን ምልክቶች ለማስተዋል የሚያስችለውን ከላይ የሚመጣ ጥበብ ነው። (ያዕቆብ 3:17) ይህ ጥበብ የዮሐንስ ክፍል አባሎችና ባልንጀሮቻቸው ይህ የምንኖርበት ጊዜ ምን ያህል አሳሳቢ ጊዜ መሆኑን እንዲያስተውሉ ያስችላቸዋል። ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ የተወሰኑ ልቦች አሁን ሊፈጸም የተቃረበውን የይሖዋ ፍርድ እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል። ለይሖዋም ጤናማ ፍርሐት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ምሳሌ 9:10 እንደሚለው “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] መፍራት ነው፣ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።” ታዲያ ይህ መለኮታዊ ጥበብ ስለ አውሬው ምን ነገር ይገልጥልናል?
2. የቀዩ አውሬ ሰባት ራሶች ትርጉም ምንድን ነው? ‘አምስቱ የወደቁትና አንዱ የኖረው’ እንዴት ነው?
2 የዚህ አስፈሪ አውሬ ሰባት ራሶች ሰባት “ተራሮችን” ወይም ሰባት “ነገሥታትን” ያመለክታሉ። ሁለቱም ቃሎች በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መንግሥታዊ ሥልጣናትን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። (ኤርምያስ 51:24, 25፤ ዳንኤል 2:34, 35, 44, 45) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ የነበራቸው ስድስት የዓለም ኃያል መንግሥታት እንደነበሩ ተገልጾአል። እነርሱም ግብጽ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ-ፋርስ፣ ግሪክና ሮም ናቸው። ከእነዚህ መካከል ዮሐንስ ራእዩን በተቀበለበት ጊዜ አምስቱ መጥተው ያለፉ ሲሆን ሮም ገና ከዓለም ኃያልነቱ አልወረደም ነበር። ይህም “አምስቱ ወድቀዋል፣ አንዱም አለ” ከሚለው ቃል ጋር ይስማማል። ይሁን እንጂ ገና የሚመጣው “የቀረው” መንግሥትስ?
3. (ሀ) የሮማ ግዛት የተከፈለው እንዴት ነው? (ለ) በምዕራቡ ክፍል ምን ነገሮች ተፈጸሙ? (ሐ) ቅዱሱ የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት እንዴት መታየት ይኖርበታል?
3 የሮማ መንግሥት ከዮሐንስ ዘመን በኋላ እንኳን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ግዛቱን ሲያስፋፋ ቆይቶአል። በ330 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ መናገሻ ከተማውን ከሮማ ወደ ባይዛንቲየም አዛወረና የከተማይቱን ስም ለውጦ ኮንስታንቲኖፕል አላት። በ395 እዘአ የሮማ ግዛት ሁለት ቦታ ላይ በምሥራቅና በምዕራብ ተከፈለ። በ410 እዘአ ራሷ ሮማ አላሪክ በተባለው የቪሲጎቶች (ወደ አርያውያን “ክርስትና” የተለወጡ የጀርመን ጎሣዎች ናቸው) ንጉሥ እጅ ወደቀች። የጀርመን ጎሣዎች (“ክርስቲያን” ነን የሚሉት) ስፓኝንና በሰሜን አፍሪካ የሚገኙትን አብዛኞቹን የሮማ ግዛቶች ወረሩ። በአውሮፓ ለብዙ መቶ ዓመታት አለመረጋጋት፣ የግዛት ሽግሽግና ብጥብጥ ሰፍኖ ቆየ። በምዕራቡ ክፍል ታላላቅ ነገሥታት ተነስተው ነበር። ከእነዚህም መካከል በ9ኛው መቶ ዓመት ከሊቀ ጳጳስ ሊዮ ሣልሳዊ ጋር የትብብር ውል ፈርሞ የነበረው ሻርለማኝና በ13ኛው መቶ ዘመን ተነስቶ የነበረው ዳግማዊ ፍሬደሪክ ይገኙበታል። ይሁን እንጂ ግዛታቸው ቅዱሱ የሮማ ግዛት ተብሎ ቢጠራም በስፋቱ ከቀድሞው የሮማ ግዛት በጣም ያነሰ ነበር። የቀድሞው የሮማ ግዛት ቀጠለ እንጂ አዳዲስ ኃያል መንግሥታት አልሆኑም።
4. የምሥራቁ ግዛት እንዴት ያለ የተሳካ ውጤት አግኝቶ ነበር? ይሁን እንጂ የጥንቱ የሮማ መንግሥት የቀድሞ ግዛቶች የነበሩት የሰሜን አፍሪካ፣ የስፔንና የሶሪያ አብዛኞቹ ክፍሎች ምን ሆነው ነበር?
4 በኮንስታንቲኖፕል የተመሠረተው ምሥራቃዊ የሮማ ግዛት ከምዕራቡ ግዛት ብዙም ሳይጣጣም ኖረ። በስድስተኛው መቶ ዘመን የምሥራቁ ንጉሥ የነበረው ንጉሠ ነገሥት ዩስቲንያን ቀዳማዊ አብዛኛውን የሰሜን አፍሪካ ክፍል እንደገና ወርሮ ለመያዝና እስከ ስፓኝና ኢጣልያ ዘልቆ ለመግባት ችሎ ነበር። በሰባተኛው መቶ ዘመን ዳግማዊ ዩስቲንያን በእስላቭ ጎሣዎች ተወስዶ የነበረውን የመቄዶንያ አካባቢ ወደ ግዛቱ ለመመለስ ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ በስምንተኛው መቶ ዘመን ቀድሞ የሮማ መንግሥት ግዛት የነበረው የሰሜን አፍሪካ፣ የስፓኝ፣ የሶርያ ክፍል በአዲሱ የእስልምና ግዛት ሥር ወድቆ ስለነበረ ከኮንስታንቲኖፕል ሆነ ከሮማ ግዛት ውጭ ሆኖ ነበር።
5. የሮማ ከተማ የወደቀችው በ410 እዘአ ቢሆንም የፖለቲካዊው የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ከዓለም መድረክ ሳይጠፋ ለብዙ ዘመናት የቆየው እንዴት ነው?
5 የኮንስታንቲኖፕል ከተማ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይታ ነበር። በ1203 በእስላሞች እጅ ሳይሆን ከምዕራብ በመጡ የመስቀል ጦረኞች እጅ እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ በፋርሳውያን፣ በአረቦች፣ በቡልጋሮችና በሩሲያውያን ተወርራ ነበር። በ1453 ግን በእስላሙ የኦቶማን ገዥ በዳግማዊ መህመድ እጅ ወደቀችና የኦቶማን ወይም የቱርክ ግዛት ዋና ከተማ ሆነች። ስለዚህ የሮማ ከተማ የወደቀችው በ410 እዘአ ቢሆንም የሮማ መንግሥት ርዝራዥ ከዓለም መድረክ ጨርሶ እስኪጠፋ ድረስ ብዙ መቶ ዘመናት ፈጅቶ ነበር። ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ እንኳን ቢሆን የሮማ መንግሥት በዓለም ጉዳዮች ላይ የነበረው ተጽዕኖ በሮማ መንበረ ጵጵስናና በምሥራቃዊው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተመሠረቱት ሃይማኖታዊ መንግሥታት ውስጥ በጉልህ ይታይ ነበር።
6. የትኞቹ አዳዲስ ግዛቶች ተቋቁመዋል? ከሁሉም በላይ የተሳካለት የትኛው ነበር?
6 ከ15ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ግን አንዳንድ አገሮች ፈጽሞ አዳዲስ የሆኑ መንግሥታትን ማቋቋም ጀምረው ነበር። ከእነዚህ አዲስ ግዛት አስፋፊ ኃይላት አንዳንዶቹ ቀድሞ የሮማ ቅኝ ግዛት በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙ ቢሆኑም ግዛታቸው የሮም ግዛት ቅጥያ አልነበረም። ፖርቱጋል፣ ስፓኝ፣ ፈረንሣይና ሆላንድ የሠፊ ግዛት ባለቤቶች ሆኑ። ከሁሉም በላይ የተሳካላት ግን ‘ፀሐይ አይጠልቅበትም’ የተባለ ሠፊ ግዛት ልትመሠርት የቻለችው የብሪታንያ መንግሥት ነበረች። የብሪታንያ ግዛት በሰሜን አሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በሕንድ፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያና እስከ ፓስፊክ ውቅያኖስ ድረስ የተስፋፋ ነበረ።
7. ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት የተቋቋመው እንዴት ነው? ሰባተኛው ራስ ወይም ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ዮሐንስ ተናገረ?
7 በ19ኛው መቶ ዘመን በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ቅኝ ግዛቶች አንዳንዶቹ ከብሪታንያ ተገንጥለው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የሚባል ነጻ መንግሥት መሠረቱ። በአዲሱ ብሔርና በቀድሞው እናት አገር መካከል የፖለቲካ ግጭት መኖሩ አልቀረም ነበር። ቢሆንም አንደኛው የዓለም ጦርነት ሁለቱም አገሮች የጋራ ጥቅም እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ስላስገደዳቸው በመካከላቸው ልዩ የሆነ ዝምድና ተመሠረተ። በዚህም መንገድ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በብልጽግናው ተወዳዳሪ በሌለው በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካና በዓለም በስፋቱ አንደኛ የሆነ የንጉሠ ነገሥት ግዛት እምብርት በሆነችው በብሪታንያ የተቋቋመ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ተመሠረተ። ስለዚህ እስከ መጨረሻው ጊዜ የሚቆየውና የዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋሙበትን ክልል ጭምር የሚገዛው ሰባተኛው ራስ ወይም የዓለም ኃያል መንግሥት ይህ ነው። ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት የሚቆየው የአምላክ መንግሥት ብሔራዊ ግዛቶችን ሁሉ እስከሚያጠፋበት ጊዜ ድረስ ብቻ ስለሆነ የግዛቱ ዘመን ከስድስተኛው ራስ ጋር ሲወዳደር “ጥቂት ጊዜ” ነው።
ስምንተኛ ንጉሥ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?
8, 9. መልአኩ ምሳሌያዊውን ቀይ አውሬ ምን ብሎ ጠርቶታል? ከሰባቱስ የወጣው በምን መንገድ ነው?
8 መልአኩ ቀጥሎ ለዮሐንስ ያብራራለታል። “የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፣ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።” (ራእይ 17:11) ምሳሌያዊው ቀይ አውሬ የወጣው ከሰባቱ ራሶች ነው። የተገኘው ወይም የተወለደው ‘ከባሕር ከወጣው’ የመጀመሪያና ቀዩ አውሬ ምስል ከሆነለት አውሬ ነው። ለሕልውናው ምክንያት የሆነለት በምን መንገድ ነው? በ1919 ትልቁ ራስ የአንግሎ አሜሪካ መንግሥት ነበር። የቀደሙት ስድስት ራሶች ወድቀዋል። በዓለም ላይ የነበራቸውም የበላይነት ተወስዶባቸው ለዚህ ጥምር መንግሥት ተሰጥቶአል። ለመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር መቋቋም ዋነኛ ኃይል የነበረውና አሁንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነኛ ጠበቃና የገንዘብ ደጋፊ የሆነው ይኸው በጊዜው የዓለም ኃያል መንግሥታት መስመር ተወካይ የሆነው ሰባተኛ ራስ ነው። ስለዚህ በምሳሌያዊ አነጋገር ስምንተኛ ንጉሥ የሆነው ቀይ አውሬ ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ራሶች የወጣ ነው። ነገሩን በዚህ መንገድ ስንመለከት ስምንተኛው አውሬ ከሰባቱ እንደወጣ መነገሩ ቀደም ባለው ራእይ በግ የሚመስል ሁለት ቀንዶች ያሉት አውሬ (የአንግሎ አሜሪካ ኃያል መንግስት፣ የመጀመሪያው አውሬ ሰባተኛ ራስ) ምስል እንዲሠራ እንዳሳሰበና ለምስሉም ሕይወት እንደሰጠው ከተገለጸው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ራእይ 13:1, 11, 14, 15
9 በተጨማሪም የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የመጀመሪያ አባሎች ከሆኑት መንግሥታት መካከል ታላቂቱ ብሪታንያን ጨምሮ የመንግሥት መቀመጫቸውን አንዳንዶቹ የቀድሞ ራሶች ይገዙባቸው በነበሩት ቦታዎች ላይ ያደረጉ መንግሥታት ነበሩ። እነዚህም መንግሥታት ግሪክ፣ ኢራን (ፋርስ) እና ኢጣልያ (ሮም) ናቸው። ቆየት ብሎም የቀደሙት ስድስት የዓለም ኃያል መንግሥታት ይገዙአቸው የነበሩትን አገሮች የሚያስተዳድሩ መንግሥታት የአውሬው ምስል ደጋፊ አባላት ሆኑ። በዚህም ረገድ ይህ ቀይ አውሬ ከሰባቱ የዓለም ኃይላት የወጣ ነው ሊባል ይችላል።
10. (ሀ) ቀዩ አውሬ ራሱ “ስምንተኛው ንጉሥ ነው” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት መሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደግፈው የተናገሩት እንዴት ነው?
10 ቀዩ አውሬ “ራሱ ስምንተኛ ንጉሥ” እንደሆነ መገለጹን አስተውል። በዛሬው ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም መንግሥት እንዲመስል ሆኖ የተዋቀረ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እንደ መንግሥት ሆኖ በኮሪያ፣ በሲና ባሕረ ሰላጤና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች እንዳደረገው በብሔራት መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች የጦር ኃይል ልኮአል። ይሁን እንጂ የንጉሥ ምስል ብቻ ነው። እንደ ሃይማኖታዊ ምስል ሁሉ እርሱም በፈጠሩትና በሚያመልኩት ሰዎች ከተሰጠው በስተቀር የራሱ የሆነ እውነተኛ ኃይልም ሆነ ሥልጣን የለውም። ይህ ምሳሌያዊ አውሬ በጣም ደካማ መስሎ የታየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሁን እንጂ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር አምባገነን አባል መንግሥታት ጨርሶ ጥለውት ወደ ጥልቁ እንደወረደበት እንደ ፊተኛው ጊዜ ፈጽሞ የወደቀበት ጊዜ አልነበረም። (ራእይ 17:8) በ1987 አንድ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ስመ ጥር መሪ በሌሎች የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተጻራሪ አቋም ቢኖራቸውም ከሮማ ጳጳሳት ጋር አንድ ሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚደግፍ መግለጫ አውጥተዋል። እንዲያውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ የተመሠረተ “ሁሉን አቀፍ የኅብረ ብሔራት የፀጥታ ጥበቃ ሥርዓት” እንዲቋቋም ጥሪ አድርገዋል። ዮሐንስ ቀጥሎ እንደሚገለጽለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውነተኛ ሥልጣን ኖሮት እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል። ከዚያ በኋላ እርሱ ራሱ “ወደ ጥፋት ይሄዳል።”
ለአንድ ሰዓት የሚቆዩ አሥር ነገሥታት
11. የይሖዋ መልአክ በምሳሌያዊው ቀይ አውሬ ላይ ስላሉት አሥር ቀንዶች ምን ተናግሮአል?
11 በቀደመው የራእይ መጽሐፍ ምዕራፍ ላይ ስድስተኛውና ሰባተኛው መላእክት የአምላክን የቁጣ ጽዋ አፍስሰው ነበር። የምድር ነገሥታትም በአርማጌዶን ወደሚደረገው የአምላክ ጦርነት በመሰብሰብ ላይ እንደሆኑና ‘ታላቂቱ ባቢሎንም’ በአምላክ ፊት እንደምትታሰብ ተነግሮናል። (ራእይ 16:1, 14, 19) አሁን ደግሞ የአምላክ ፍርድ በእነዚህ ላይ እንዴት እንደሚፈጸም በተብራራ ሁኔታ እንማራለን። የይሖዋ መልአክ ዮሐንስን ሲያነጋግረው እናዳምጥ:- “ያየሃቸውም አሥሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አሥር ነገሥታት ናቸው፣ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ። እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፣ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ። እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፣ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።”—ራእይ 17:12-14
12. (ሀ) አሥሩ ቀንዶች ምን ያመለክታሉ? (ለ) ምሳሌያዊዎቹ አሥር ቀንዶች ‘ገና መንግሥት ያልተቀበሉት’ እንዴት ነው? (ሐ) ምሳሌያዊዎቹ አሥር ቀንዶች አሁን መንግሥት የተቀበሉት እንዴት ነው? የሚቆዩትስ ለምን ያህል ጊዜ ነው?
12 አሥሩ ቀንዶች በአሁኑ ጊዜ የዓለምን መድረክ የሚቆጣጠሩትንና የአውሬውን ምስል የደገፉትን የፖለቲካ ኃይላት በሙሉ ያመለክታሉ። በአሁኑ ጊዜ ካሉት አገሮች ብዙዎቹ በዮሐንስ ዘመን አይታወቁም ነበር። ይታወቁ የነበሩት እንደ ግብፅና ፋርስ (ኢራን) ያሉት አገሮችም ቢሆኑ አሁን ያላቸው ፖለቲካዊ መዋቅር ከቀድሞው ፈጽሞ የተለየ ነው። ስለዚህ አሥሩ ‘ቀንዶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ገና መንግሥት አልተቀበሉም’ ነበር። በዚህ በአሁኑ የጌታ ቀን ግን “መንግሥት” ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ተቀብለዋል። ታላላቆቹ ቅኝ ገዥ መንግሥታት ከወደቁ በኋላ በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አዳዲስ ብሔራት ተወልደዋል። እነዚህ አዳዲስ ብሔራትም ሆኑ ብዙ ዘመን የቆዩት የፖለቲካ ኃይላት ከአውሬው ጋር ይሖዋ ዓለማዊ የፖለቲካ ኃይላትን በሙሉ እስከሚያጠፋበት እስከ አርማጌዶን ድረስ “ለአንድ ሰዓት” ማለትም ለአጭር ጊዜ ብቻ መግዛት ይኖርባቸዋል።
13. አሥሩ ቀንዶች “አንድ አሳብ” የኖራቸው በምን መንገድ ነው? ይህስ በበጉ ላይ ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዲኖር አድርጎአል?
13 በዛሬው ጊዜ እነዚህን አሥር ቀንዶች ከሚያንቀሳቅሱት ጠንካራ ኃይሎች አንዱ ብሔራዊ ስሜት ነው። የአምላክን መንግሥት ከመቀበል ይልቅ ብሔራዊ ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ ስለሚፈልጉ “አንድ አሳብ” አላቸው። የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበርና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት የሆኑትም ለዚህ ዓላማ ነው። የዓለምን ሰላም ለማስጠበቅና በዚያውም ሕልውናቸውን ለማስከበር ነው። ቀንዶቹ እንዲህ ያለ አቋምና ዝንባሌ ስላላቸው “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” የሆነውን በጉን እንደሚቃወሙ የታወቀ ነው። ምክንያቱም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ እነዚህን መንግሥታት በሙሉ አጥፍቶ እርሱ ብቻውን በቦታቸው እንዲቆም የይሖዋ ዓላማ ነው።—ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 24:30፤ 25:31-33, 46
14. የዓለም ገዥዎች ከበጉ ጋር ሊዋጉ የሚችሉት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
14 እርግጥ፣ የዚህ ዓለም ገዥዎች በኢየሱስ ላይ ምንም ለማድረግ አይችሉም። እርሱ የሚኖረው እነርሱ ሊደርሱ በማይችሉበት በሰማይ ነው። ይሁን እንጂ ከሴቲቱ ዘር የቀሩት የኢየሱስ ወንድሞች አሁንም በምድር ላይ ናቸው። ለጥቃትም የተጋለጡ መስለው የሚታዩ ናቸው። (ራእይ 12:17) ከቀንዶቹ መካከል ብዙዎቹ እነዚህን ቀሪዎች አምርረው እንደሚጠሉ አሳይተዋል። ይህንንም በማድረጋቸው በጉን ወግተውታል። (ማቴዎስ 25:40, 45) ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአምላክ መንግሥት ‘እነዚህን ሁሉ መንግሥታት የምትፈጭበትና የምታደቅበት’ ጊዜ ይመጣል። (ዳንኤል 2:44) በቅርቡ እንደምንመለከተው በዚያ ጊዜ የምድር ነገሥታት በሙሉ እስከ መጨረሻው ድረስ ከበጉ ጋር ይዋጋሉ። (ራእይ 19:11-21) ሆኖም ግን ብሔራት በዚህ ጥቃታቸው እንደማይሳካላቸው የሚያስገነዝብ በቂ መረጃ ተሰጥቶናል። እነዚህ ነገሥታትም ሆኑ ቀይ አውሬ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “አንድ አሳብ” ቢኖራቸውም ታላቁን “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ” ሊያሸንፉ አይችሉም። ‘የተመረጡትንና ከእርሱ ጋር በታማኝነት የጸኑትን’ ገና በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓንንም ቢሆን ሊያሸንፉ አይችሉም። እነዚህም ቢሆኑ በፍጹም አቋማቸው ጸንተው የሰይጣንን ክስ ሐሰተኛነት በማረጋገጥ ድል ይነሳሉ።—ሮሜ 8:37-39፤ ራእይ 12:10, 11
ጋለሞታይቱን ማጥፋት
15. መልአኩ ስለ አመንዝራዋ እንዲሁም አሥሩ ቀንዶችና አውሬው ለዚህች አመንዝራ ስላላቸው ዝንባሌና ስለሚወስዱባት እርምጃ ምን ብሎአል?
15 የአሥሩ ቀንዶች ጠላትነት የተቃጣው በአምላክ ሕዝቦች ላይ ብቻ አይደለም። መልአኩ አሁን የዮሐንስን ትኩረት ወደ ጋለሞታይቱ ዞር እንዲል ያደርጋል:- “አለኝም:- ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፣ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው። ያየሃቸውም አሥር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፣ ሥጋዋንም ይበላሉ፣ በእሳትም ያቃጥሉአታል።”—ራእይ 17:15, 16
16. ታላቂቱ ባቢሎን የፖለቲካ መንግሥታት በሚነሱባት ጊዜ መከላከያና ድጋፍ ለማግኘት በውኃዎችዋ ልትተማመን የማትችለው ለምንድን ነው?
16 የጥንትዋ ባቢሎን ለመከላከያዋ ትመካ የነበረው በውኃዎችዋ እንደነበረ ሁሉ ታላቂቱ ባቢሎንም የምትመካው አባሎችዋ በሆኑት “ወገኖችና ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብም ቋንቋዎችም” ነው። መልአኩ ስለሚቀጥለው አስደንጋጭ እርምጃ ከመናገሩ በፊት ስለ እነዚህ ሕዝቦችና ወገኖች መናገሩ ተገቢ ነበር። የምድር ፖለቲካዊ መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ በታላቅ ቁጣ ይነሳሉ። በዚያ ጊዜ እነዚህ “ወገኖችና ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብና ቋንቋዎች” ምን ያደርጋሉ? የአምላክ ሕዝቦች የኤፍራጥስ ወንዝ ውኃ እንደሚደርቅ ታላቂቱ ባቢሎንን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። (ራእይ 16:12) ይህ ውኃ በመጨረሻ ላይ ፈጽሞ ይደርቃል። ይህች አስጸያፊ ባልቴት አመንዝራ ከፍተኛ ችግር በሚያጋጥማት ጊዜ ድጋፍ ሊሆናት አይችልም።—ኢሳይያስ 44:27፤ ኤርምያስ 50:38፤ 51:36, 37
17. (ሀ) የታላቂቱ ባቢሎን ሀብት ሊያድናት የማይችለው ለምንድን ነው? (ለ) የታላቂቱ ባቢሎን ፍጻሜ ክብር ያለው የማይሆነው ለምንድን ነው? (ሐ) አሥሩ ቀንዶች ወይም ብሔራት በተናጠል ከሚወስዱት እርምጃ በተጨማሪ የትኞቹ ሌሎች ኃይሎች ታላቂቱ ባቢሎንን ቦጫጭቆ በማጥፋቱ ድርጊት ተካፋይ ይሆናሉ?
17 የታላቂቱ ባቢሎን ሰፊ ብልጽግና ሊያድናት አይችልም። እንዲያውም ራእዩ እንደሚገልጸው አውሬውና አሥሩ ቀንዶች በጣም ተቆጥተው በሚጣሉአት ጊዜ የማዕረግ ልብስዋንና ጌጦችዋን ሁሉ ስለሚያወልቁባት ጥፋትዋን ሊያፋጥንባት ይችላል። ሀብትዋን ሁሉ ይዘርፉባታል። በአሳፋሪ ሁኔታ እውነተኛ ባሕርይዋ በግልጽ እንዲታይ ስለሚያደርጉ “ራቁትዋን ያደርጉአታል።” እንዴት ያለ ታላቅ ጥፋት ነው! ፍጻሜዋም ቢሆን የውርደት ፍጻሜ ይሆናል። “ሥጋዋንም” ሁሉ በልተው ባዶና ሕይወት የሌለበት አጽም ያደርጓታል። በመጨረሻም “በእሳት ያቀጥሉአታል።” ክብር ያለው ቀብር ሳይደረግላት በሽታ አስተላላፊ እንደሆነ ነገር በእሳት ትቃጠላለች። ታላቂቱን አመንዝራ የሚያጠፉት በአሥሩ ቀንዶች የተወከሉት ብሔራት ብቻ አይደሉም። “አውሬውም” ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በዚህ ከፍተኛ ጥፋት ይተባበራል። የሐሰት ሃይማኖት እንዲጠፋ ፈቃድ ይሰጣል። አሁንም እንኳን ቢሆን ከ190 ከሚበልጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት መካከል ብዙ መንግሥታት በድምፅ አሰጣጣቸው ለሃይማኖት፣ በተለይም ለሕዝበ ክርስትና ጥላቻ እንዳላቸው አሳይተዋል።
18. (ሀ) አሁንም እንኳን ቢሆን ብሔራት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ እንዲነሱ የሚያስችሉ ምን በቂ ምክንያቶች ታይተዋል? (ለ) በታላቂቱ ባቢሎን ላይ አጠቃላይ ጥቃት የሚፈጸምበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?
18 ብሔራቱ በቀድሞ ወዳጃቸው ላይ ይህን በሚያክል ቁጣ የተነሳሱት ለምንድን ነው? በቅርቡ ከተፈጸሙ ሁኔታዎች እንኳን በባቢሎናዊ ሃይማኖቶች ላይ ለመነሳት የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ ተመልክተናል። እንደ ቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረትና ቻይና ባሉት አገሮች የተቋቋሙ መንግሥታት በወሰዱት የተቃውሞ እርምጃ ምክንያት ሃይማኖት ያለው ተጽዕኖና ተደማጭነት በጣም ቀንሶአል። በአውሮፓ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ክፍሎች በጣም የተስፋፋው ሃይማኖታዊ ግድየለሽነትና ጥርጣሬ አብያተ ክርስቲያናትን ባዶ አስቀርቶአቸዋል። ሃይማኖት ጨርሶ በድን ሆኖአል። በጣም ሰፊ የሆነው የካቶሊክ ግዛትም ቢሆን መሪዎቿ ሊገድቡት ባልቻሉት ዓመፅና ብጥብጥ እርስበርሱ ተለያይቶአል። ይሁን እንጂ ይህ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸመው የመጨረሻ አጠቃላይ ጥፋት የሚመጣው አምላክ በዚህች ታላቅ አመንዝራ ላይ በሚያስፈጽመው ሊለወጥ የማይችል ፍርድ ምክንያት እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም።
የአምላክን አሳብ መፈጸም
19. (ሀ) ይሖዋ በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የሚያስፈጽመው ፍርድ በ607 ከዘአበ በከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ላይ ካስፈጸመው ፍርድ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ከዘአበ ከ607 በኋላ የታየው የኢየሩሳሌም የመፈራረስና የባድማነት ሁኔታ ለዘመናችን ጥላ የሚሆነው እንዴት ነው?
19 ይሖዋ ፍርዱን የሚያስፈጽመው እንዴት ነው? ይህን ለመረዳት ይሖዋ በጥንት ዘመን በከዳተኛ ሕዝቦቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ ልንመለከት እንችላለን። ስለነዚህ ሕዝቦቹ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በኢየሩሳሌምም ነቢያት ላይ የሚያስደነግጥን ነገር አይቻለሁ፣ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፣ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፣ ሁሉም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ።” (ኤርምያስ 23:14) በ607 ከዘአበ ይሖዋ በናቡከደናፆር በመጠቀም ይህችን መንፈሳዊ አመንዝራ የሆነች ከተማ ‘ልብስዋ እንዲገፈፍ፣ የክብርዋ ጌጥ እንዲወሰድና ዕራቁትዋንና እርቃንዋን’ እንድትቀር አድርጎ ነበር። (ሕዝቅኤል 23:4, 26, 29) የዚያ ዘመንዋ ኢየሩሳሌም ለዛሬዋ ሕዝበ ክርስትና አምሳያ ነች። ዮሐንስ ቀደም ባሉት ራእዮች እንደተመለከተው ይሖዋ በሕዝበ ክርስትናም ሆነ በሌሎቹ የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ተመሳሳይ ቅጣት ይፈጽማል። ከዘአበ ከ607 በኋላ የነበረው የኢየሩሳሌም ባድማነትና ባዶነት ሃይማኖታዊቷ ሕዝበ ክርስትና ልብስዋን ተገፍፋና ጌጦችዋን ተነጥቃ በአሳፋሪ ሁኔታ ዕርቃንዋን ከቀረች በኋላ ምን እንደምትመስል ያመለክታል። የቀረው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍልም ቢሆን ከዚህ የተሻለ ዕጣ አያጋጥመውም።
20. (ሀ) ይሖዋ አሁንም እንደገና ፍርዱን ለማስፈጸም በሰብዓዊ ገዥዎች እንደሚጠቀም ዮሐንስ ያመለከተው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ “አሳብ” ምንድን ነው? (ሐ) ብሔራት የራሳቸውን “አንድ አሳብ” የሚፈጽሙት በምን መንገድ ነው? ይሁን እንጂ የሚፈጸመው የማን አሳብ ነው?
20 ይሖዋ ዳግመኛ የቅጣት ፍርዱን ለማስፈጸም በሰብዓዊ ገዥዎች ይጠቀማል። “እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና።” (ራእይ 17:17) የአምላክ “አሳብ” ምንድን ነው? የታላቂቱ ባቢሎን አጥፊዎች ሙሉ በሙሉ ሊያጠፉአት እንዲችሉ ተጣምረው አንድ ሠራዊት እንዲሆኑ ነው። እርግጥ ገዢዎቹ እርሷን ለማጥቃት የሚነሳሱበት ምክንያት የራሳቸውን “አንድ አሳብ” ለመፈጸም ነው። በታላቂቱ ባቢሎን ላይ መነሳት ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚያራምድላቸው ይመስላቸዋል። በግዛት ክልሎቻቸው ውስጥ የተደራጀ ሃይማኖት መኖሩ ሉዓላዊነታቸውን ሥጋት ላይ የሚጥል ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እርምጃቸውን ሁሉ የሚቆጣጠረውና የሚመራው ይሖዋ ነው። ለብዙ ዘመናት የቆየችውን አመንዝራ ጠላቱን በአንድ ምት ጨርሶ በመደምሰስ የእርሱን አሳብ ይፈጽማሉ።—ከኤርምያስ 7:8-11, 34 ጋር አወዳድር።
21. ቀዩ አውሬ ታላቂቱ ባቢሎንን ለማጥፋት የሚያገለግል በመሆኑ ብሔራት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምን ያደርጉለታል?
21 አዎ፣ ብሔራት ታላቂቱን ባቢሎን ለማጥፋት ቀዩን አውሬ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መሣሪያ አድርገው ይጠቀማሉ። ይህን እርምጃ የሚወስዱት ግን “አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ . . . መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው” ይሖዋ ስለሚያስገባ ነው እንጂ በራሳቸው ፈቃድ ተነሳስተው አይደለም። ጊዜው ሲደርስ ብሔራቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይገነዘባሉ። ያላቸውን ኃይልና ሥልጣን አውሰውት የሚያኝክና የሚያጠፋ ጥርስ እንዲኖረው በማድረግ በሐሰት ሃይማኖት ላይ ተነስቶ “የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም ድረስ” እንዲዋጋና እንዲያሸንፍ ያስችሉታል። በዚህ መንገድ ይህች ጥንታዊት አመንዝራ ሙሉ በሙሉ ትደመሰሳለች። አዎ፣ ፈጽማ ትጥፋ!
22. (ሀ) መልአኩ በራእይ 17:18 ላይ የተናገረው የመደምደሚያ ምስክርነት ምን ያመለክታል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የምሥጢሩን መገለጥ እንዴት ተቀብለዋል?
22 መልአኩ በሐሰት ሃይማኖት ዓለም አቀፍ ግዛት ላይ የሚፈጸመው የይሖዋ የቅጣት ፍርድ የማይቀርና የተረጋገጠ መሆኑን አበክሮ ሲገልጽ ምስክርነቱን እንዲህ በማለት ያጠቃልላል። “ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።” (ራእይ 17:18) ታላቂቱ ባቢሎንም በብልጣሶር ዘመን እንደነበረችው ባቢሎን ‘በሚዛን ተመዝና ቀልላ ተገኝታለች።’ (ዳንኤል 5:27) የሚመጣባት ጥፋት ፈጣንና የማያዳግም ይሆናል። የይሖዋ ምሥክሮች የታላቂቱ አመንዝራና የቀዩ አውሬ ምሥጢር ስለ መፈታቱ ምን ይሰማቸዋል? የይሖዋን የፍርድ ቀን በቅንዓት ያውጃሉ። ከልባቸው እውነትን ለሚፈልጉ ሰዎችም “በጸጋ” ይመልሳሉ። (ቆላስይስ 4:5, 6፤ ራእይ 17:3, 7) የሚቀጥለው ምዕራፍ እንደሚያብራራልን ታላቂቱ አመንዝራ በምትጠፋበት ጊዜ ከጥፋቱ ለመዳን የሚፈልጉ ሁሉ አሁኑኑ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
[በገጽ 252 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በተከታታይ የተነሱት ሰባት የዓለም ኃያል መንግሥታት
ግብፅ
አሦር
ባቢሎን
ሜዶ-ፋርስ
ግሪክ
ሮማ
አንግሎ-አሜሪካ
[በገጽ 254 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ንጉሥ ነው”
[በገጽ 255 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጀርባቸውን ወደ በጉ አዙረው “ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ይሰጣሉ”
[በገጽ 257 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ሙሉ በሙሉ በመጥፋት የጥንቷን ኢየሩሳሌም እንድትመስል ይደረጋል
-
-
ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!
-
-
ምዕራፍ 36
ታላቂቱ ከተማ ድምጥማጥዋ ጠፋ
ራእይ 12--ራእይ 18:1 እስከ 19:10
ርዕሰ ጉዳይ:- የታላቂቱ ባቢሎን ውድቀትና ጥፋት፤ የበጉ ሰርግ ስለመከናወኑ ማስታወቂያ ተነገረ
ራእዩ የሚፈጸምበት ጊዜ:- ከ1919 ጀምሮ ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ እስካለው ጊዜ ድረስ
1. የታላቁ መከራ መክፈቻ የሚሆነው ምንድን ነው?
የታላቂቱ ባቢሎን አጠፋፍ ድንገተኛ፣ አስደንጋጭና አውዳሚ ይሆናል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከፍተኛ እልቂት ካስከተሉት ታላላቅ ክንውኖች አንዱ በመሆን ‘ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ላልሆነውና ወደ ፊትም ለማይሆነው ታላቅ መከራ’ መክፈቻ ይሆናል።—ማቴዎስ 24:21
2. የፖለቲካ ግዛቶች ሲነሱና ሲወድቁ የቆዩ ቢሆንም እስከ ዛሬ ጸንቶ የቆየው ምን ዓይነት ግዛት ነው?
2 የሐሰት ሃይማኖት ከተቋቋመ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። ይሖዋን ተቃውሞ በመነሳት ሰዎች የባቤልን ግንብ እንዲሠሩ ካደረገው የደም ጥማት ከነበረው፣ ከናምሩድ ዘመን ጀምሮ ያለማቋረጥ ኖሮአል። ይሖዋ የእነዚህን ዓመፀኛ ሰዎች ልሳን ዘባርቆ በምድር ሁሉ እንዲበተኑ ባደረገ ጊዜ የባቢሎንም የሐሰት ሃይማኖት አብሮአቸው በምድር በሙሉ ተሰራጨ። (ዘፍጥረት 10:8-10፤ 11:4-9) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ግዛቶች ሲነሱም ሲወድቁም ኖረዋል። ባቢሎናዊ ሃይማኖት ግን እስከ አሁን ሳይጠፋ እንዳለ ቀጥሏል። ብዙ ዓይነት ቅርጽና መልክ በመያዝ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ወይም ትንቢት የተነገረለት ታላቂቱ ባቢሎን ሆኖአል። የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል የጥንቱ ባቢሎናዊ ትምህርትና የክህደት “ክርስትና” መሠረተ ትምህርት ጥምረት ውጤት የሆነችው ሕዝበ ክርስትና ናት። ታላቂቱ ባቢሎን እጅግ በጣም ረዥም የሆነ ታሪክ ስላላት ብዙ ሰዎች የመጥፋትዋን ሐሳብ ለመቀበል ያዳግታቸዋል።
3. የራእይ መጽሐፍ የሐሰት ሃይማኖትን መጥፋት የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
3 በዚህም ምክንያት የራእይ መጽሐፍ መጀመሪያ ስለ ሐሰት ሃይማኖት ውድቀትና በኋላ ደግሞ ወደ ፍጹም ጥፋት ስለሚያደርሱአት ክንውኖች ሁለት ዝርዝር መግለጫዎችን በመስጠት ስለሚደርስባት ጥፋት አስተማማኝ ማረጋገጫ መስጠቱ ተገቢ ነው። ቀደም ብለን እርስዋ “ታላቂቱ ጋለሞታ” ስለመሆንዋና በፖለቲካው ዓለም ውስጥ የሚገኙ የቀድሞ ወዳጆችዋ ስለሚያደርሱባት ጥፋት ተመልክተን ነበር። (ራእይ 17:1, 15, 16) አሁን ደግሞ በሌላ ራእይ የጥንትዋ ባቢሎን አምሳያ በሆነች በአንዲት ከተማ እንደተመሰለች እንመለከታለን።
ታላቂቱ ባቢሎን ትወድቃለች
4. (ሀ) ዮሐንስ ቀጥሎ የተመለከተው ራእይ ምንድን ነው? (ለ) የመልአኩን ማንነት ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው? እርሱስ የታላቂቱን ባቢሎን መውደቅ ማስታወቁ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ታሪኩን ይገልጽልናል:- “ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፣ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ:- ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች” ብሎ ጮኸ። (ራእይ 18:1, 2ሀ) ዮሐንስ ይህን የመልአኩን ማስታወቂያ ሲሰማ ሁለተኛ ጊዜው ነው። (ራእይ 14:8 ተመልከት።) በዚህ ጊዜ ግን የሰማዩ መልአክ ክብር ምድርን በሙሉ ሲያበራ ስለታየና ግርማው ከፍተኛ እንደሆነ ስለተገለጸ ለማስታወቂያው ከፍተኛ ክብደት ተሰጥቶአል። ታዲያ ይህ መልአክ ማን ሊሆን ይችላል? ነቢዩ ሕዝቅኤል ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ስለ አንድ ሰማያዊ ራእይ ሲጽፍ “ከክብሩም [ከይሖዋ] የተነሣ ምድር ታበራ ነበር” ብሎአል። (ሕዝቅኤል 43:2) ከይሖዋ ክብር ጋር ሊወዳደር በሚችል ክብር ሊያበራ የሚችል መልአክ የይሖዋ “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” የሆነው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው። (ዕብራውያን 1:3) በ1914 ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የይሖዋ ተባባሪ ንጉሥና ፈራጅ በመሆን በምድር ላይ በሥልጣኑ ሲጠቀም ቆይቷል። በዚህ ምክንያት የታላቂቱ ባቢሎንን ውድቀት የሚያሳውቀው መልአክ ኢየሱስ መሆኑ ተገቢ ነበር።
5. (ሀ) መልአኩ የታላቂቱ ባቢሎንን መውደቅ ለማወጅ የሚጠቀመው በማን ነው? (ለ) ‘የአምላክ ቤት’ ነን በሚሉት ላይ ፍርድ በሚጀምርበት ጊዜ ሕዝበ ክርስትና ምን ይደርስባታል?
5 ይህ ታላቅ ሥልጣን የተሰጠው መልአክ እንዲህ ያለውን አስደናቂ ዜና ለሰው ልጆች ለማሰማት የሚጠቀመው በማን ነው? ታላቂቱ ባቢሎን በመውደቅዋ ምክንያት ነፃ በወጡት ቅቡዓን ቀሪዎች ወይም በዮሐንስ ክፍል አባላት እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። እነዚህ ቀሪዎች ከ1914 እስከ 1918 በነበረው ጊዜ ከታላቂቱ ባቢሎን ብዙ መከራ ደርሶባቸው ነበር። በ1918 ግን ጌታ ይሖዋና ‘የአብርሃም ቃል ኪዳን መልእክተኛ’ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “በአምላክ ቤት ላይ” ወይም ክርስቲያን ነን ይሉ በነበሩት ሕዝቦች ላይ ፍርድ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ከዳተኛዋ ሕዝበ ክርስትና ለፍርድ ቀረበች። (ሚልክያስ 3:1፤ 1 ጴጥሮስ 4:17) በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ተጨማልቃ የነበረችበት የደም አፍሳሽነት ወንጀል፣ የይሖዋን ታማኝ ምሥክሮች በማሳደድ ድርጊት መካፈልዋና ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶችዋ በዚህ ፍርድ ቀን ከቅጣት ለመዳን አልረዳትም። ማንኛውም የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አልቻለም።—ከኢሳይያስ 13:1-9 ጋር አወዳድር።
6. ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 ወድቃለች ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
6 ስለዚህ በ1919 ታላቂቱ ባቢሎን ወድቃ ስለነበረ የአምላክ ሕዝቦች ነጻ ወጥተው መንፈሳዊ ብልጽግና በሚያገኙበት መንፈሣዊ ርስታቸው እንደ አንድ ቀን በሚቆጠር አጭር ጊዜ ውስጥ የሚቋቋሙበት መንገድ ተከፍቶላቸው ነበር። (ኢሳይያስ 66:8) በዚህ ዓመት ታላቁ ዳርዮስ ይሖዋ አምላክና ታላቁ ቂሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐሰት ሃይማኖት በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን እንዳይኖረው የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አድርገው ነበር። ከዚያ በኋላ ይሖዋን ከማገልገል፣ አመንዝራይቱ ታላቂቱ ባቢሎን ለጥፋት የተወሰነች መሆንዋንና የይሖዋ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበት ጊዜ በጣም ቅርብ መሆኑን ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ከማሳወቅ ምንም ሊያግዳቸው አልቻለም።—ኢሳይያስ 45:1-4፤ ዳንኤል 5:30, 31
7. (ሀ) ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 ባትጠፋም ይሖዋ እንዴት ተመልክቶአታል? (ለ) ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 በወደቀች ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ምን አገኙ?
7 እርግጥ ነው ታላቂቱ ባቢሎን በ1919 አልጠፋችም። የጥንትዋ የባቢሎን ከተማም ብትሆን በፋርሳዊው ቂሮስ ሠራዊት እጅ በወደቀችበት ዓመት በ539 ከዘአበ አልጠፋችም። በይሖዋ አመለካከት ግን ይህች ድርጅት ወድቃለች። የተፈረደባት ድርጅት ስለሆነች ጥፋትዋን ብቻ ትጠብቃለች። ስለዚህ የሐሰት ሃይማኖት የይሖዋን ሕዝቦች በምርኮ ይዛ ልታቆይ አትችልም። (ከሉቃስ 9:59, 60 ጋር አወዳድር።) እነዚህ የይሖዋ ሕዝቦች ከምርኮ የተለቀቁት መንፈሣዊ ምግብ በጊዜው እያቀረቡ የጌታ ታማኝና ልባም ባሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ነበር። ‘ጥሩ አድርጋችኋል’ የሚል የፍርድ ብይን ስለተሰጣቸው በይሖዋ ሥራ በትጋት የሚካፈሉበት ሹመት ተሰጥቶአቸዋል።—ማቴዎስ 24:45-47፤ 25:21, 23፤ ሥራ 1:8
8. ኢሳይያስ 21:8, 9 ላይ የተጠቀሰው ጉበኛ ወይም ጠባቂ ምን ሁኔታ እንደሚኖር አውጆ ነበር? በዛሬው ጊዜ የዚህ ጉበኛ ጥላ የሆነው ማን ነው?
8 ይሖዋ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ ስለሆነው ስለዚህ ክንውን በሌሎች ነቢያት አማካኝነት ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢሳይያስ እንደ አንበሳ ባለ ድፍረት “ጌታ [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፣ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፣ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክዬአለሁ” በማለት ስለ ተናገረ ጉበኛ ወይም ጠባቂ ገልጾ ነበር። ይህ ጠባቂ ያስተዋለውና እንደ አንበሳ ባለ ድፍረት ያወጀው ክንውን ምን ነበር? “ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች፣ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ።” (ኢሳይያስ 21:8, 9) ይህ ጠባቂ በዘመናችን ዓይኑን በሰፊው ከፍቶ ሁኔታዎችን የሚከታተለውን የዮሐንስ ክፍል ያመለክታል። ይህ ጠባቂ ዛሬ በመጠበቂያ ግንብ እና በሌሎች ቲኦክራቲካዊ ጽሑፎች እየተጠቀመ ባቢሎን ወድቃለች የሚለውን ዜና በሰፊው በማሰራጨት ላይ ላለው ከፍተኛ ሁኔታ ነቅቶ ለሚሠራው የዮሐንስ ክፍል ጥላ ነው።
የታላቂቱ ባቢሎን ማሽቆልቆል
9, 10. (ሀ) ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወዲህ የባቢሎናዊ ሃይማኖት ተጽዕኖ የቀነሰው እንዴት ነው? (ለ) ኃያሉ መልአክ ታላቂቱ ባቢሎን የደረሰባትን ውድቀት የገለጸው እንዴት ነው?
9 በ539 ከዘአበ የደረሰው የጥንትዋ ባቢሎን ውድቀት ለበርካታ ዓመታት ለቀጠለው ማሽቆልቆልና በመጨረሻ ለደረሰባት ፍጹም ባድማነት መጀመሪያ ነበር። በተመሳሳይም የባቢሎናዊው ሃይማኖት ተጽዕኖ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስገራሚ ሁኔታ ሲያሽቆለቁል ቆይቶአል። በጃፓን አገር የሺንቶዎች የንጉሠ ነገሥት አምልኮ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ እየከሰመ መጥቶአል። በቻይና ማንኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴና ሹመት የሚቆጣጠረው መንግሥቱ ነው። በሰሜን አውሮፓ በሚገኙት ፕሮቴስታንት አገሮች አብዛኞቹ ሰዎች ለሃይማኖት ግድየለሾች ሆነዋል። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በውስጥዋ በተነሳው መከፋፈልና መለያየት ምክንያት ምድር አቀፍ ግዛትዋ ተዳክሞአል።—ከማርቆስ 3:24-26 ጋር አወዳድር።
10 እነዚህ አዝማሚያዎች በሙሉ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ለሚመጣው ወታደራዊ ጥቃት መንገድ የሚጠርገው ‘የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ’ ክፍል ናቸው። ሊቀ ጳጳሳቱ በጥቅምት ወር 1986 ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ኪሣራ ስለደረሰባት “ዳግመኛ ለማኝ መሆን ሊኖርባት ነው” ሲሉ ማስታወቃቸው የዚህን ድርቀት መጠን የሚያሳይ ነው። (ራእይ 16:12) በተለይ ከ1919 ወዲህ ታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ባድማ መሆንዋ በገሐድ መታየት ጀምሮአል። ይህም ሁኔታ ኃያሉ መልአክ እንደሚከተለው በማለት በተናገረው መሠረት ተፈጽሞአል። “የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፣ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ፣ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች።” (ራእይ 18:2ለ) በቅርቡ ታላቂቱ ባቢሎን በዘመናዊቷ ኢራቅ ምድር እንደምትገኘው የጥንትዋ ባቢሎን ፍርስራሽና ፍጹም ባድማ ትሆናለች።—በተጨማሪ ኤርምያስ 50:25-28ን ተመልከት።
11. ታላቂቱ ባቢሎን “የአጋንንት ማደሪያ” እና ‘የእርኩስ ትንፋሽና የእርኩሳን ወፎች መዘዋወሪያ’ የሆነችው በምን መንገድ ነው?
11 እዚህ ላይ “አጋንንት” የሚለው ቃል ኢሳይያስ ስለወደቀችው ባቢሎን ሲገልጽ የጠቀሰውን “ፍየል መሰል አጋንንት” [(ሴኢሪም) NW] የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። እንዲህ ይላል:- “በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፣ ጉጉቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፣ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ። በዚያም አጋንንት [“ፍየል መሰል አጋንንት፣” NW] ይዘፍናሉ።” (ኢሳይያስ 13:21) እነዚህ ፍጥረታት ለተመለከታቸው ሰው አጋንንት መስለው የሚታዩ አስቀያሚና ፀጉራም የምድረ በዳ አራዊት ናቸው እንጂ ቃል በቃል አጋንንት ላይሆኑ ይችላሉ። በታላቂቱ ባቢሎን ፍርስራሽ ውስጥ እንደነዚህ ያሉ አራዊትና የሸተተና የገማ አየር (“እርኩስ ትንፋሽ”) እንዲሁም እርኩሳን ወፎች መኖራቸው በመንፈሣዊ በድን የመሆንዋን ሁኔታ ያመለክታል። ለሰው ልጅ ምንም ዓይነት የሕይወት ተስፋ አትሰጥም።—ከኤፌሶን 2:1, 2 ጋር አወዳድር።
12. የታላቂቱ ባቢሎን ሁኔታ በኤርምያስ ምዕራፍ 50 ላይ ከተነገረው ትንቢት ጋር አንድ የሆነው እንዴት ነው?
12 በተጨማሪም የታላቂቱ ባቢሎን ሁኔታ በኤርምያስ ትንቢት ከተገለጸው ጋር ይመሳሰላል። “ሰይፍ በከለዳውያንና በባቢሎን በሚኖሩ ላይ በአለቆችዋና በጥበበኞችዋ ላይ አለ፣ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] . . . እርስዋ የተቀረጹ ምስሎች ምድር ናት፣ እነርሱም በጣዖታት ይመካሉና ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል። እነርሱም ይደርቃሉ። ስለዚህ የምድረ በዳ አራዊት ከተኩላዎች ጋር ይቀመጡባታል። ሰጎኖችም ይቀመጡባታል። ሰውም ከዚያ ወዲያ ለዘላለም አይቀመጥባትም። እስከ ልጅ ልጅም ድረስ የሚኖርባት የለም።” የጣዖት አምልኮትዋና የድግምት ጸሎትዋ ታላቂቱ ባቢሎንን አምላክ ሰዶምንና ገሞራን በገለበጠ ጊዜ ከፈጸመው የቅጣት ፍርድ ጋር ከሚመሳሰለው ቅጣት ሊያድናት አይችልም።—ኤርምያስ 50:35-40
የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይን ጠጅ
13. (ሀ) ኃያሉ መልአክ የታላቂቱ ባቢሎን ግልሙትና በጣም የተስፋፋ መሆኑን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው የትኛው በጥንትዋ ባቢሎን ውስጥ የነበረ የፆታ ብልግና ነው?
13 ኃያሉ መልአክ ከዚህ ቀጥሎ የታላቂቱ ባቢሎን ግልሙትና በጣም የተስፋፋ ስለመሆኑ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋaቁጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋልና፣ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም [“ተጓዥ፣” NW] ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሣ ባለጠጋዎች ሆኑ” (ራእይ 18:3) እርኩስ በሆነው ሃይማኖታዊ አካሄድዋ የምድርን አሕዛብ በሙሉ በክላለች። በጥንትዋ ባቢሎን ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ እንደጻፈው እያንዳንዷ ልጃገረድ በቤተ መቅደሱ ይፈጸም በነበረው የአምልኮ ሥርዓት ድንግልናዋን እንድትሰጥ ይፈለግባት ነበር። በጦርነት በፈራረሰችው በካምፑቺያ አገር በአንጎር ዋት ለማየት የሚያስነውሩ የፆታ ግንኙነቶችን የሚያሳዩ ምስሎች እስከ ዛሬ ድረስ ይታያሉ። በሕንድ አገር በካጁራሆ በሚገኙ ቤተ መቅደሶች ደግሞ ቪሽኑ የተባለው የሂንዱዎች አምላክ አስጸያፊ በሆኑ የፆታ ግንኙነት ስሜት ቀስቃሽ ትርዒቶች ተከቦ የሚያሳዩ ምስሎች አሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በ1987 እና በ1988 የቴሌቪዥን ወንጌላውያንን ዓለምን ያናጋው የፆታ ብልግና መጋለጡና የሃይማኖት መሪዎች በግብረ ሰዶም ልማድ የተበከሉ መሆናቸው መታወቁ ሕዝበ ክርስትናም በጣም አስነዋሪ የሆኑ የዝሙት ድርጊቶችን የምትፈቅድ መሆኑን አረጋግጦአል። ይሁን እንጂ ብሔራት በሙሉ ከዚህ ይበልጥ ከባድ የሆነ የዝሙት ድርጊት የፈጸሙበት መንገድ አለ።
14-16. (ሀ) በፋሽስት ኢጣልያ ውስጥ ምን ዓይነት ሕገወጥ የሃይማኖትና የፖለቲካ ዝምድና ተመስርቶ ነበር? (ለ) ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ምን መግለጫ አውጥተው ነበር?
14 ሂትለርን በናዚ ጀርመን የሥልጣን እርካብ ላይ ስላቆናጠጠው ሕገወጥ የሆነ የሃይማኖትና የፖለቲካ ጥምረት ቀደም ስንል ተመልክተናል። ሌሎች ብሔራትም ቢሆኑ ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባች በመዘባረቅዋ ምክንያት ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። ለምሳሌ ያህል የካቲት 11 ቀን 1929 የቫቲካንን ከተማ ሉዓላዊ መንግሥት ያደረገው የላተራን ውል የተባለው ስምምነት በሙሶሎኒና በካርዲናል ጋስፓሪ ተፈረመ። በዚህ ጊዜ ፓፓ ፓየስ 11ኛ “ኢጣልያን ለአምላክ መልሼ አስረክቤአለሁ፣ አምላክም ወደ ኢጣልያ ተመልሶአል” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነበርን? ከስድስት ዓመት በኋላ የሆነውን ነገር እንመልከት። ጥቅምት 3 ቀን 1935 ኢጣልያ “አሁንም የባሪያ ንግድ የሚፈጸምባት የአረመኔዎች አገር ነች” የሚል ሰበብ በማቅረብ ኢትዮጵያን ወረረች። ይሁን እንጂ የአረመኔ ድርጊት የፈጸመው ማን ነበር? የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሙሶሎኒን አረመኔያዊ ድርጊት አውግዛ ነበርን? ፓፓው ግልጽ አቋም ያልያዘ መግለጫ ቢሰጡም ጳጳሶቻቸው “የአባት አገራቸውን” የኢጣልያን ጦር ኃይል በይፋ ባርከዋል። አንቶኒ ሮድስ ዘ ቫቲካን ኢን ዘ ኤጅ ኦፍ ዘ ዲክታተርስ (ቫቲካን በአምባገነኖች ዘመን) በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ብለው ነበር:-
15 “የኡዲን [ኢጣልያ] ጳጳስ ጥቅምት 19 ቀን [1935] በጻፉት የጵጵስና መልእክታቸው ‘እርምጃው ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎ መናገር ለእኛ ተገቢም ወቅታዊም አይደለም። የኢጣልያዊነትም ሆነ የክርስቲያንነት ግዴታችን ለጦር ኃይላችን ድል ማግኘት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ነው’ ሲሉ ጽፈዋል። የፓዱዋ ጳጳስ ደግሞ ጥቅምት 21 ቀን ‘በዚህ በተደቀነብን አስቸጋሪ ጊዜ በመሪዎቻችንና በጦር ኃይላችን ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራችሁ እንጠይቃለን’ ሲሉ ጽፈዋል። ጥቅምት 24 ቀን የክሬሞና ጳጳስ የበርካታ ክፍለ ጦሮችን የዘመቻ አርማ ከባረኩ በኋላ ‘በአፍሪካ ምድር ለኢጣልያውያን ሊቅ ሕዝቦች ለም መሬት በሚያስገኙትና ለአፍሪካውያኑም የሮማንና የክርስትናን ወግና ባሕል በሚያደርሱት በእነዚህ ወታደሮች ላይ የእግዚአብሔር በረከት ይኑር። ኢጣልያ ለመላው ዓለም የክርስትና ጠባቂና ሞግዚት ሆና እንደገና ትቁም’ ብለዋል።”
16 ኢትዮጵያ በሮማ ካቶሊክ ቀሳውስት ቡራኬ ተወረረች። ከእነዚህ ቀሳውስት መካከል አንዳቸው እንኳን እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹህ ነኝ” ሊሉ ይችላሉን?—ሥራ 20:26
17. ስፓኝ ቀሳውስትዋ “ሰይፋቸውን ማረሻ” አድርገው ባለመቀጥቀጣቸው ምክንያት ምን ዓይነት ችግር ደርሶባታል?
17 ከጀርመን፣ ከኢጣልያና ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የታላቂቱ ባቢሎን ምንዝር ሰለባ የሆነች አንዲት ሌላ አገር እንጨምር። እርስዋም ስፓኝ ናት። በዚያች አገር ከ1936 እስከ 1939 ለተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በአብዛኛው ምክንያት የሆነው ዲሞክራሲያዊው መንግሥት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ሥልጣንና ኃይል ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩ ነበር። ጦርነቱ በተፋፋመበት ጊዜ የአብዮታዊው ሠራዊት ፋሽስታዊ መሪ የነበሩት ካቶሊኩ ፍራንኮ ራሳቸውን “የቅዱስ መስቀል ሠራዊት ክርስቲያን ጄኔራል” ብለው ይጠሩ ነበር። በኋላ ግን ይህን የማዕረግ ስማቸውን ትተውታል። በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስፓኞች በጦርነቱ ሞቱ። በጦርነቱ ከሞቱት ከእነዚህ ሰዎች ሌላ የፍራንኮ ብሔረተኞች በአነስተኛ ግምት 40, 000 የሚያክሉ የሕዝባዊ ግንባር አባሎችን ሲገድሉ ሕዝባዊው ግንባር ደግሞ 8, 000 መነኮሳትን፣ ቀሳውስትንና ደናግሎችን ገድለዋል። ማንኛውም የእርስበርስ ጦርነት ይህን የመሰለ አሳዛኝ ሁኔታና መከራ ያስከትላል። ይህም ኢየሱስ “ሰይፍ የሚያነሱ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ሥፍራው መልስ” ሲል የተናገረው ቃል እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። (ማቴዎስ 26:52) ሕዝበ ክርስትና እንዲህ ባለው ደም መፋሰስ መካፈልዋ በጣም የሚዘገንን ነገር ነው። ቀሳውስትዋ “ሠይፋቸውን ማረሻ” ለማድረግ እንዳልቻሉ ግልጽ ነው።—ኢሳይያስ 2:4
ተጓዥ ነጋዴዎች
18. “የምድር ተጓዥ ነጋዴዎች” የተባሉት እነማን ናቸው?
18 ተጓዥ “የምድር ነጋዴዎች” የተባሉት እነማን ናቸው? በዘመናችን አጠራር ከበርቴ ነጋዴዎች፣ ትልቅ የንግድ ድርጅቶችን የሚያንቀሳቅሱ ከበርቴዎች፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ብለን ልንጠራቸው እንችላለን። ይሁን እንጂ በሕጋዊ የንግድ ሥራ መሰማራት ስህተት ነው ማለታችን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የንግድ ሰዎች ከሸፍጥ፣ ከስግብግብነትና ከመሳሰሉት መጥፎ ድርጊቶች እንዲጠበቁ እያስጠነቀቀ ጥሩ ምክር ይሰጣቸዋል። (ምሳሌ 11:1፤ ዘካርያስ 7:9, 10፤ ያዕቆብ 5:1-5) ከሁሉ የሚበልጠው ትርፍ “ያለኝ ይበቃኛል” እያሉ ለአምላክ ማደር ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:6, 17-19) ይሁን እንጂ የሰይጣን ዓለም በጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች አይገዛም። ምግባረ ብልሹነት በጣም ተስፋፍቶአል። ሃይማኖቶች፣ ፖለቲካዊ ድርጅቶችና ታላላቅ የንግድ ተቋሞች ምግባረ ብልሹዎች ሆነዋል። ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ስለፈጸሙት ምዝበራ፣ በሕገወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ ስለማስተላለፍና ስለመሳሰሉት ቅሌቶች ብዙ ጊዜ ከዜና ማሠራጫዎች እንሰማለን።
19. የምድር ነጋዴዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በመጥፎ የተጠቀሱበትን ምክንያት እንድንረዳ የሚያስችለን የትኛው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ ነው?
19 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የጦር መሣሪያ ንግድ በዓመት ከ1,000,000,000,000 ዶላር በላይ ሆኖአል። ይህን የሚያክል ወጪ ለጦር መሣሪያዎች የሚውለው በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሕይወት ማቆያ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን እየተነጠቁ ነው። በጣም የሚያስከፋ ሁኔታ ቢሆንም የዓለም ኢኮኖሚ ዋነኛ ደጋፊ ሆኖ የተገኘው የጦር መሣሪያ ንግድ የሆነ ይመስላል። ሚያዝያ 11 ቀን 1987 በለንደን ስፔክታተር ጋዜጣ ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ የሚከተለውን ዘገባ አስፍሮ ነበር። “ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ኢንዱስትሪዎች ብቻ ሲቆጠሩ በዩናይትድ ስቴትስ 400, 000 የሚያክሉ ሠራተኞች በአውሮፓ ደግሞ 750, 000 የሚያክሉ ሠራተኞች በጦር መሣሪያ ምርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው። የሚያስገርመው ግን የጦር መሣሪያዎች ግንባታ ሥራ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ያለው ድርሻ እየሰፋ በሄደ መጠን የመሣሪያዎቹ አምራቾች በቂ መከላከያ ያላቸው የመሆኑና ያለመሆኑ ጥያቄ ወደ ጎን ገሸሽ የተደረገ መሆኑ ነው።” ቦምቦችና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በምድር በሙሉ፣ ለጠላት አገሮችም ሳይቀር ሲሸጡ ብዙ ትርፍ ይገኛል። እነዚህ ቦምቦች አንድ ቀን ተመልሰው ሻጮቻቸውን ሊያጠፉ እንደሚችሉ አይታሰብም። ምንኛ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ነው! በዚህ ሁሉ ላይ በጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ አካባቢ የሚታየውን ሸፍጥና አጭበርባሪነት እንመልከት። ስፔክታተር ጋዜጣ እንደገለጸው በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ “የአሜሪካ መንግሥት በየዓመቱ 900 ሚልዮን ዶላር ግምት ያለው የጦር መሣሪያና ትጥቅ ባልታወቀ ምክንያት ይጠፋበታል።” የምድር ነጋዴዎች በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በክፉ አድራጊነት መጠቀሳቸው አያስደንቅም።
20. ሃይማኖት ምግባረ ብልሹ በሆነ የንግድ ሥራ እንደሚካፈል ማስረጃ የሚሆን ምን ምሳሌ አለን?
20 ክብር የተጎናጸፈው መልአክ እንደተናገረው የሃይማኖት ድርጅቶች እንደዚህ ባለው ምግባረ ብልሹ የንግድ እንቅስቃሴዎች በሰፊው ተካፍለዋል። ለምሳሌ ያህል በ1982 የኢጣልያው ባንኮ አምብሮዚያኖ ከስሮ በተዘጋበት ድርጊት ቫቲካን ከፍተኛ ሚና ነበራት። ጉዳዩ በ1980ዎቹ ዓመታት በሙሉ በእንጥልጥል ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ ገንዘቡ የት ደረሰ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊገኝ አልቻለም። በየካቲት ወር 1987 የሚላን ዳኞች ሦስት የቫቲካን ቀሳውስትና አንድ አሜሪካዊ ሊቀ ጳጳስ ታስረው እንዲቀርቡ ማዘዣ አውጥተው ነበር። ባንኩ በተጭበረበረ ሁኔታ ከስሮ እንዲዘጋ በማድረግ ወንጀል ተካፋዮች ነበሩ የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ቫቲካን የሃይማኖት መሪዎቹን አሳልፋ ለመስጠት እምቢተኛ ሆናለች። በ1987 በሐምሌ ወር ከፍተኛው የኢጣልያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በቫቲካንና በኢጣልያ መንግሥት መካከል ተደርጎ የነበረ የቆየ ስምምነት በመጥቀስ ማዘዣው ውድቅ እንዲሆን በይኖአል።
21. ኢየሱስ በዘመኑ ከነበረው አጠያያቂ የንግድ ሥራ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበረው እንዴት እናውቃለን? በዛሬው ጊዜ በባቢሎናዊ ሃይማኖት ውስጥ ምን ነገር እንመለከታለን?
21 ኢየሱስ በዘመኑ በነበረው አጠያያቂ የንግድ እንቅስቃሴ ተካፍሎ ነበርን? በፍጹም አልተካፈለም። እንዲያውም ምንም ዓይነት ንብረት አላበጀም ነበር። “ራሱን የሚያስጠጋበት” አልነበረውም። ኢየሱስ አንዱን ሀብታም ወጣት “ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ፣ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፣ መጥተህም ተከተለኝ” ሲል መክሮት ነበር። ይህ ሰው ኢየሱስ እንደመከረው ቢያደርግ ኖሮ በንግድ ጉዳይ ከመጨነቅ ነፃ ሊሆን ይችል ስለ ነበረ ጥሩ ምክር ነበር። (ሉቃስ 9:58፤ 18:22) ባቢሎናዊው ሃይማኖት ግን ከዚህ በተለየ ሁኔታ ከትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ጋር ተቆራኝቶአል። ለምሳሌ ያህል አልባኒ ታይምስ ዩኒየን በ1987 እንደዘገበው የማያሚ ፍሎሪዳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ የፋይናንስ አስተዳዳሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን በሚያመርቱ፣ የብልግና ፊልሞችን በሚሠሩና ሲጋራ አምራች በሆኑ ኩባንያዎች ውስጥ አክሲዮኖች እንዳሉአት አምነዋል።
“ሕዝቤ ሆይ፣ . . . ከእርስዋ ዘንድ ውጡ”
22. (ሀ) ከሰማይ የመጣው ድምፅ ምን አለ? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች በ537 ከዘአበ እና በ1919 እዘአ በጣም ያስደሰታቸው ሁኔታ ያጋጠማቸው እንዴት ነው?
22 ዮሐንስ ቀጥሎ የሚናገረው ቃል በጥንትዋ ባቢሎን ላይ ከተፈጸመው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ትንቢታዊ ቃል ነው። “ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል:- ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።” (ራእይ 18:4) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት ስለ ጥንትዋ ባቢሎን አወዳደቅ ከሚናገሩት ትንቢቶች መካከል ይሖዋ ለሕዝቦቹ “ከባቢሎን መካከል ሽሹ” ሲል የሰጠው ትዕዛዝ ይገኝበታል። (ኤርምያስ 50:8, 13) ዛሬም በተመሳሳይ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ታላቅ ጥፋት ስለሚመጣ የአምላክ ሕዝቦች ከመካከልዋ እንዲወጡ ተመክረዋል። በ537 ከዘአበ ታማኞቹ እስራኤላውያን ከባቢሎን ለመውጣት መቻላቸው ትልቅ ደስታ አስገኝቶላቸው ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ የአምላክ ሕዝቦች በ1919 ከባቢሎናዊ ምርኮ ለመውጣት መቻላቸው ብዙ ደስታ አስገኝቶላቸዋል። (ራእይ 11:11, 12) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ሽሹ የሚለውን ትዕዛዝ ተቀብለዋል።
23. ከሰማይ የተሰማው ድምፅ ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽቶ መውጣት በጣም አጣዳፊ መሆኑን አጠንክሮ የገለጸው እንዴት ነው?
23 ከዓለማዊ ሃይማኖቶች አባልነት በመውጣትና ፈጽሞ በመለየት ከታላቂቱ ባቢሎን መሸሽ በእርግጥ አጣዳፊ ጉዳይ ነውን? ለዚህች አስቀያሚ አሮጊት፣ ለታላቂቱ ባቢሎን ከአምላክ ጋር የሚመሳሰል አመለካከት ሊኖረን ስለሚገባ በእርግጥም አጣዳፊ ነው። አምላክ ታላቂቱ ጋለሞታ ብሎ ለመጥራት ቅር አልተሰኘም። በዚህም ምክንያት ከሰማይ የመጣው ድምፅ ስለዚህች አመንዝራ ተጨማሪ መግለጫ ለዮሐንስ ሰጥቶታል። “ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፣ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ። እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፣ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኃዘን ስጡአት። በልብዋ፣ ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኃዘንንም ከቶ አላይም ስላለች፣ ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሠፍቶችዋ ይመጣሉ፣ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ብርቱ ነውና።”—ራእይ 18:5-8
24. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን መሸሽ የሚኖርባቸው ከምን ለመዳን ነው? (ለ) ከታላቂቱ ባቢሎን ሳይሸሹ የቀሩ ሁሉ በምን ኃጢአት ተካፋዮች ይሆናሉ?
24 በጣም ከባድ ቃላት ናቸው! ስለዚህ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ኤርምያስ በዘመኑ የነበሩ እስራኤላውያን እርምጃ እንዲወስዱ ሲያሳስብ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ከባቢሎን ውስጥ ሽሹ። . . . የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] በቀል ጊዜ ነውና። እርሱም ብድራትዋን ይከፍላታልና። ሕዝቤ ሆይ፣ ከመካከልዋ ውጡ። እያንዳንዳችሁም ከእግዚአብሔር [“ከይሖዋ፣” NW] ጽኑ ቁጣ ራሳችሁን አድኑ።” (ኤርምያስ 51:6, 45) ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ከሰማይ የመጣው ድምፅ የአምላክ ሕዝቦች ከመቅሰፍትዋ እንዳይቀበሉ ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽተው መውጣት እንደሚኖርባቸው ያስጠነቅቃል። ይሖዋ በዚህ ዓለም ላይ፣ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ጭምር የሚያወርደው መቅሰፍት መሰል ፍርድ በአሁኑ ጊዜ በመታወጅ ላይ ነው። (ራእይ 8:1 እስከ 9:21፤ 16:1-21) የአምላክ ሕዝቦች በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚደርሰው መቅሰፍት እንዳይደርስባቸውና ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር እንዳይሞቱ ከፈለጉ ራሳቸውን ከሐሰት ሃይማኖት መለየት ይኖርባቸዋል። ከዚህም በላይ በዚህች ድርጅት ውስጥ መቆየታቸው በኃጢአትዋ ተካፋዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ልክ እንደርስዋ በመንፈሳዊ ምንዝርና “በምድር የታረዱ ሁሉ ደም” ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል።—ራእይ 18:24፤ ከኤፌሶን 5:11ና ከ1 ጢሞቴዎስ 5:22 ጋር አወዳድር።
25. የአምላክ ሕዝቦች ከጥንትዋ ባቢሎን የወጡት እንዴት ነበር?
25 ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን የሚወጡት እንዴት ነው? በጥንትዋ ባቢሎን የነበሩት አይሁዶች ከባቢሎን ከተማ ወጥተው እስከ ተስፋይቱ ምድር ድረስ የእግር ጉዞ ማድረግ ነበረባቸው። ይሁን እንጂ ከጉዞው የበለጠ ነገር ያስፈልግ ነበር። ኢሳይያስ ለእስራኤላውያን በትንቢታዊ አነጋገር እንዲህ ብሎ ነበር:- “እናንተ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፣ እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ፣ ርኩስን ነገር አትንኩ። ከመካከልዋ ውጡ፣ ንጹሐን ሁኑ።” (ኢሳይያስ 52:11) አዎ፣ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ሊያረክሱባቸው የሚችሉትን ርኩስ የባቢሎን ሃይማኖት ልማዶች መተው ነበረባቸው።
26. የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘ከመካከልዋ ውጡ፣ እርኩስንም አትንኩ’ የሚለውን ቃል የታዘዙት እንዴት ነው?
26 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደሚከተለው በማለት የኢሳይያስን ቃል ጠቅሶ ነበር:- “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ስለዚህም ጌታ [“ይሖዋ፣” NW]:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ፣ ርኩስንም አትንኩ ይላል።” የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ይህንን ትዕዛዝ ለመፈጸም ከቆሮንቶስ ከተማ መውጣት አላስፈለጋቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ከሐሰት ሃይማኖት የረከሱ ቤተ መቅደሶች መራቅና እነዚያ የጥንት ጣዖት አምላኪዎች ይፈጽሙ ከነበረው እርኩስ ተግባራት ራሳቸውን መለየት ነበረባቸው። ንጹሕ ሕዝቦች ሆነው ይሖዋን ሊያገለግሉ የሚችሉት ይህን ቢያደርጉ ብቻ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:14-17፤ 1 ዮሐንስ 3:3
27. በጥንትዋ ባቢሎን ላይ የተፈጸመውና በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጸመው ፍርድ ተመሳሳይነት ያለው እንዴት ነው?
27 የጥንትዋ ባቢሎን የወደቀችውና በመጨረሻም ባድማ የሆነቸው ለኃጢአትዋ መቀጫ እንዲሆናት ነበር። “ፍርድዋ እስከ ሰማይ ደርሶአልና።” (ኤርምያስ 51:9) በተመሳሳይም የታላቂቱ ባቢሎን ኃጢአት ይሖዋ እስኪያየው ድረስ ‘ወደ ሰማይ ደርሶአል።’ የፍትሕ አጉዳይነት፣ የጣዖት አምልኮ፣ የሥነ ምግባራዊ ብልግና፣ የጭቆናና የግድያ ወንጀል ተከምሮባታል። የጥንትዋ ባቢሎን የወደቀችው በከፊል በይሖዋ ቤተ መቅደስና በእውነተኛ አምላኪዎቹ ላይ ላደረሰችው ጉዳት በቀል እንዲሆን ነበር። (ኤርምያስ 50:8, 14፤ 51:11, 35, 36) በተመሳሳይም የታላቂቱ ባቢሎን ውድቀትና የመጨረሻ ጥፋት ባለፉት በርካታ መቶ ዘመናት በአምላክ እውነተኛ አምላኪዎች ላይ ለፈጸመችው በደል የበቀል መግለጫ ነው። በእርግጥም “አምላካችን የሚበቀልበት ቀን” የሚጀምረው በታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ነው።—ኢሳይያስ 34:8-10፤ 61:2፤ ኤርምያስ 50:28
28. ይሖዋ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የሚፈጽመው የትኛውን የፍትሕ ማስፈጸሚያ ደረጃ ነው? ለምንስ?
28 በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ እሥራኤላዊ ከአገሩ ሰዎች የአንዱን ንብረት ቢሰርቅ እጅግ ቢያንስ የሰረቀውን ንብረት እጥፍ አድርጎ መመለስ ነበረበት። (ዘጸአት 22:1, 4, 7, 9) በመጪው የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ጊዜም ይሖዋ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ፍርድ እንዲፈጸም ያደርጋል። እርስዋ ካደረገችው በእጥፍ የሚበልጥ እንድትቀበል ይደረጋል። ታላቂቱ ባቢሎን ለበደለቻቸው ሰዎች ምንም ዓይነት ምህረት ስላላሳየች ለእርሷም ምህረት አይደረግላትም። ‘በአሳፋሪ የቅምጥልነት ኑሮ’ ለመኖር ስትል የምድር ሕዝቦችን ስትቦጠቡጥ ኖራለች። አሁን ግን መከራና ሐዘን ይመጣባታል። የጥንትዋ ባቢሎን ምንም ነገር ሊነካት እንደማይችል ትተማመን ስለነበረ “መበለትም ሆኜ አልኖርም፣ የወላድ መካንነትም አላውቅም” እያለች ትታበይ ነበር። (ኢሳይያስ 47:8, 9, 11) ታላቂቱ ባቢሎንም ልክ እንደርስዋ ምንም ነገር ሊደርስባት እንደማይችል ተማምናለች። ይሁን እንጂ “ብርቱ” የሆነው ፈራጅዋ ይሖዋ የበየነባት ጥፋት “በአንድ ቀን” እንደሆነ ያህል ፈጥኖ ይመጣባታል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በባለ ማጣቀሻው አዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ
[በገጽ 236 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ”
በ18 መቶዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ ነጋዴዎች መጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኦፒየም ወደ ቻይና በድብቅ ያስገቡ ነበር። ቻይናውያን ባለ ሥልጣኖች በመጋቢት ወር 1839 ላይ 20, 000 ሳጥን ዕጽ ከብሪታንያ ነጋዴዎች በመንጠቅ ይህን ሕገወጥ ንግድ ለማቆም ሞክረው ነበር። በዚህም ምክንያት በቻይናና በብሪታንያ መካከል ግጭት ተፈጠረ። በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት እየተበላሸ በሄደበት ጊዜ የፕሮቴስታንት ሚሲዮኖች እንደሚከተሉት ያሉትን መግለጫዎች በማሰማት ብሪታንያ ውጊያ እንድትጀምር ይቀሰቅሱ ነበር:-
“የእንግሊዝ መንግሥት ተቆጥቶ የሚነሳና አምላክም በዚህ በመጠቀም የክርስቶስ ወንጌል ወደ ቻይና እንዳይገባ የከለከሉትን እንቅፋቶች የሚያስወግድ ስለሚመስለኝ እነዚህ ችግሮች መቀስቀሳቸው በጣም ያስደስተኛል።”—ሄንሪየታ ሹክ፣ የደቡብ ባፕቲስት ሚሲዮናዊ።
በመጨረሻም ጦርነቱ ተጀመረ። ይህም ጦርነት በዛሬው ዘመን የኦፒየም ጦርነት ተብሎ የሚጠራው ነው። ሚሲዮናውያን እንደሚከተሉት ያሉትን ቃላት በማሰማት ከብሪታንያ ጎን በሙሉ ልባቸው ተሰልፈው ነበር:-
“በአሁኑ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ እንደ ኦፒየም ወይም እንደ እንግሊዝ ጉዳይ ሳይሆን አምላክ በሰው ልጅ የክፋት ድርጊት በመጠቀም ቻይና የተገለለችበትን ግድግዳ አፍርሶ ምህረቱን ሊያወርድላት ያሰበውን ዓላማ ለማስፈጸም ያደረገው ጉዳይ እንደሆነ አድርጌ ለመመልከት እገደዳለሁ።”—ፒተር ፓርከር፣ ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ።
ሌላው ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ ሳሙኤል ደብልዩ ዊልያምስ ደግሞ በመጨመር “በተደረገው ነገር ሁሉ የአምላክ እጅ እንዳለበት ግልጽ ነው። በምድር ላይ ሠይፍ ይዤ መጥቼአለሁ ያለው [ኢየሱስ] ጠላቶቹን በአፋጣኝ እርምጃ ለማጥፋትና የራሱን መንግሥት ለማቋቋም እንደመጣ የምንጠራጠርበት ምንም ምክንያት የለም። አምላክ የሰላሙን መስፍን በቦታው እስኪያስቀምጥ ድረስ እየደጋገመ ይገለባብጣቸዋል” ብለዋል።
ሚሲዮናዊው ጄ ሉዊስ ሹክ በቻይናውያን ብሔረተኞች ላይ ስለተፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እንዲህ ያለውን ትዕይንት . . . አምላክ መለኮታዊው እውነት እንዳይስፋፋ እንቅፋት የሆኑትን ጥራጊ ቆሻሻዎች ለማስወገድ መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመበት እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ።”
ኤላይጃ ሲ ብሪጅማን የተባሉት ኮንግሪጌሽናሊስት ሚሲዮናዊ ደግሞ እንዲህ በማለት አክለዋል:- “አምላክ ብዙ ጊዜ ጠንካራ ክንድ ያላቸውን የሕዝብ ባለ ሥልጣናት በመጠቀም ለመንግሥቱ ጥርጊያ መንገድ አዘጋጅቶአል። . . . በእነዚህ ታላላቅ ጊዜያት ሁሉ መሣሪያ የሆኑት ሰዎች ሲሆኑ አስፈጻሚው ኃይል ግን መለኮታዊ ነበር። የብሔራት ሁሉ የበላይ ገዥ የሆነው አምላክ እንግሊዝን መሣሪያ በማድረግ ቻይናን ቀጥቶአል፣ አዋርዶአል።” ጥቅሱ የተወሰደው ዘ ሚሽነሪ ኢንተርፕራይዝ ኢን ቻይና ኤንድ አሜሪካ (በጆን ኬ ፌይርባንክ የታተመ የሃርቫርድ ጥናት) በተባለው ጽሑፍ ላይ ከሰፈረው “ኢንድስ ኤንድ ሚንስ” ከተባለው የስትዋርት ክሬይተን ሐተታ ነው።
[በገጽ 264 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ተጓዥ ነጋዴዎችም . . . ባለጠጋዎች ሆኑ”
“ከ1929 እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍንዳታ ድረስ [የቫቲካን የፋይናንስ አስተዳዳሪ የነበሩት] [ቤርናንዲኖ] ኖጋራ የቫቲካን መዋዕለ ንዋይና የቫቲካን ወኪሎች በተለይ በኤሌክትሪክ፣ በቴሌፎን መገናኛ፣ በብድርና በባንክ፣ በትናንሽ የባቡር መስመሮች፣ የእርሻ መሣሪያዎችን በማምረት፣ በሲሚንቶ፣ በሰው ሠራሽ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችና በመሳሰሉት የተለያዩ የኢጣልያ የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሠሩ አድርገው ነበር። አብዛኞቹም ከፍተኛ ትርፍ አስገኝተዋል።
“ኖጋራ ብዙ ኩባንያዎችን ውጠዋል። ከእነዚህም መካከል ላ ሶቺዬታ ኢታልያና ዴላ ቪስኮዛ፣ ላ ሱፐርቴዚሌ፣ ላ ሶቺዬታ ሜሪዲዮናሌ ኢንዱስትርዬ ቴሲሌ እና ላ ቺዛራዮን የተባሉት ኩባንያዎች ይገኛሉ። እነዚህን ኩባንያዎች በሙሉ በአንድ ኩባንያ አጣምረው ሲ አይ ኤስ ኤ ቪስኮዛ ብለው ከሰየሙ በኋላ አዲሱ ኩባንያ በጣም የታመኑ የቫቲካን ተከታይ በነበሩት በባሮን ፍራንቼስኮ ማሪያ ኦዳሶ ሥር እንዲተዳደር አደረጉ። ከዚያም ይህ አዲስ ኩባንያ ኤስ ኤን አይ ኤ ቪስኮዛ ከተባለው በጣም ትልቅ የጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ ጋር እንዲቀላቀል አደረጉ። ቫቲካን በኤስ ኤን አይ ኤ ቪስኮዛ ውስጥ የነበራት ድርሻ በጣም ከፍተኛ ሆነ። በመጨረሻም ሁሉን በቁጥጥሯ ሥር አደረገች። በዚህም ምክንያት ባሮን ኦዳሶ ምክትል ፕሬዚደንት ሆኑ።
“በዚህም መንገድ ኖጋራ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን በቁጥጥራቸው ውስጥ አስገቡ። ኖጋራ በጣም ዘዴኛና መሰሪ ሰው ስለነበሩ በተለያዩ ዘዴዎች ሌሎች ኢንዱስትሪዎችንም ለመቆጣጠር ችለዋል። በኢጣልያ ታሪክ ውስጥ የኢጣልያን ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ረገድ ከእኚህ ታታሪ ሰው የበለጠ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሰው አይገኝም። . . . ቤኒቶ ሙሶሎኒ ያለመውን ሰፊ ግዛት ለማግኘት አልቻለም። ቢሆንም ቫቲካንና ቤርናንዲኖ ኖጋራ ሌላ ዓይነት ሰፊ ግዛት እንዲያቋቁሙ አስችሎአቸዋል።”—ዘ ቫቲካን ኢምፓየር በኒኖ ሎ ቤሎ፣ ገጽ 71–3
ይህ በምድር ነጋዴዎችና በታላቂቱ ባቢሎን መካከል ያለውን የቅርብ ትብብር የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው። እነዚህ ነጋዴዎች የንግድ ሸሪካቸው ስትጠፋ ማዘናቸው የሚያስደንቅ ነገር አይደለም።
[በገጽ 259 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰዎች በመላዋ ምድር ላይ በሚሰራጩበት ጊዜ ባቢሎናዊ ሃይማኖታቸውን ይዘው ሄዱ
[በገጽ 261 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የዮሐንስ ክፍል እንደ አንድ ጠባቂ በመሆን የባቢሎንን መውደቅ ያስታውቃል
[በገጽ 266 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንትዋ ባቢሎን ፍርስራሽ መጪውን የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት ያመለክታል
-