የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ተስፋ በእርግጥ ለውጥ ያመጣል?
    ንቁ!—2004 | ግንቦት 8
    • ተስፋ በእርግጥ ለውጥ ያመጣል?

      ዳንኤል ዕድሜው ገና አሥር ዓመት ብቻ ቢሆንም ከካንሰር በሽታ ጋር አንድ ዓመት ሙሉ ሲታገል ቆይቷል። የቅርብ ጓደኞቹም ሆኑ ሐኪሞቹ እንደማይድን ተረድተው ተስፋ ቆርጠው ነበር። ዳንኤል ግን ተስፋ አልቆረጠም። አድጎ ተመራማሪ በመሆን አንድ ቀን ለካንሰር በሽታ መድኃኒት እንደሚያገኝ ያምን ነበር። በተለይም እሱን የያዘውን ዓይነት የካንሰር በሽታ በማከም ልዩ ችሎታ ያለው ሐኪም ሊያየው እንደሚመጣ ሰምቶ ተስፋ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ሐኪሙ የሚመጣበት ቀን ሲደርስ በመጥፎ የአየር ጠባይ ምክንያት ለመቅረት ተገደደ። ዳንኤል ቅስሙ ተሰበረ። ለመጀመሪያ ጊዜ በትካዜ ተዋጠ። ሐኪሙ በቀረ በሁለት ቀን ውስጥ ሞተ።

      ይህን የዳንኤልን ታሪክ የተናገረው ተስፋ እና ተስፋ መቁረጥ በጤና ረገድ በሚጫወቱት ሚና ላይ ጥናት ያደረገ አንድ የጤና ባለሙያ ነበር። አንተም ተመሳሳይ ታሪኮች ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አረጋዊ ሰው በሞት አፋፍ ላይ ሳሉ አንድ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቁት ሰው ወይም ክንዋኔ ካለ እስከዚያ ቀን ድረስ ለመቆየት ይጓጓሉ። ያ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው ሰው ወይም ቀን ደርሶ ካለፈ በኋላ ግን ወዲያውኑ ይሞታሉ። ይህን ሁኔታ ምን ይሉታል? በእርግጥ ተስፋ አንዳንዶች እንደሚያምኑት በቀላሉ የማይገመት ኃይል አለው?

      ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ የሕክምና ተመራማሪዎች አዎንታዊ አመለካከት፣ ተስፋና ሌሎችም ገንቢ ስሜቶች በአንድ ሰው ሕይወትና ጤንነት ላይ ኃይለኛ ውጤት እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህ አመለካከት ግን ሁሉም ተመራማሪዎች የሚስማሙበት አይደለም። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንዲህ ያለው አመለካከት ሳይንሳዊ መሠረት የሌለው አፈ ታሪክ ነው በማለት ያጣጥሉታል። አካላዊ ሕመም የሚመጣው አካላዊ በሆኑ መንስኤዎች ብቻ ነው ብለው ማሰብ ይቀላቸዋል።

      እርግጥ ነው፣ ተስፋ ጠቃሚ ስለመሆኑ መጠራጠር ዛሬ አልተጀመረም። በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ግሪካዊው ፈላስፋ አርስቶትል ለተስፋ ፍቺ እንዲሰጥ ተጠይቆ መልስ ሲሰጥ “የቁም ቅዠት ነው” ብሏል። በቅርቡ ደግሞ አሜሪካዊው የፖለቲካ ሰው ቤንጃሚን ፍራንክሊን “ተስፋ በሕይወት ያቆየኛል ብሎ የሚያስብ ሰው በረሃብ ይሞታል” ብለዋል።

      ታዲያ ስለ ተስፋ እውነታው ምንድን ነው? ተስፋ ሰዎች ፈጽሞ በማይጨበጥ ነገር ራሳቸውን ለማጽናናት የሚሞክሩበት የሕልም እንጀራ ነው? ወይስ ተስፋ ሁላችንም ጤንነትና ደስታ እንድናገኝ የግድ የሚያስፈልገን እውነተኛ መሠረትና ጥቅም ያለው ነገር? እንዲህስ ብለን ለማመን የሚያስችል ጠንካራ ማስረጃ አለ?

  • ተስፋ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2004 | ግንቦት 8
    • ተስፋ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

      ቀደም ባለው ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ዳንኤል የተባለው የካንሰር ሕመምተኛ ተስፋ ባይቆርጥ ኖሮስ? ሕመሙን ተቋቁሞ እስከዛሬ ድረስ በሕይወት መኖር ይችል ነበር? ተስፋ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚሟገቱ ሰዎች እንኳ እንዲህ ብለው ለመናገር አይደፍሩም። ዋናው ቁም ነገር ያለው እዚህ ላይ ነው። ተስፋ ከመጠን በላይ የተጋነነ ግምት ሊሰጠው አይገባም። ተስፋ ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ አይደለም።

      ዶክተር ናታን ቸርኔ ሲቢኤስ ኒውስ ከተባለ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በጠና በታመሙ በሽተኞች ረገድ ተስፋ የሚጫወተው ሚና ተጋንኖ መቅረብ እንደማይኖርበት ሲያስጠነቅቁ “የሚፈለገውን ያህል አላሰላሰለችም እንዲሁም ብሩሕ አመለካከት አልያዘችም በማለት ሚስቶቻቸውን የሚቆጡ ባሎች አጋጥመውናል” ብለዋል። አክለውም ሲናገሩ “እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አንድ ሰው የዕጢውን ወይም የካንሰሩን እድገት መቆጣጠር ይችላል የሚል የተሳሳተ እምነት ስለፈጠረ ታማሚዎቹ በሽታው ከባሰባቸው የዕጢውን እድገት ለመቆጣጠር ተገቢውን ጥረት አላደረጉም ተብሎ ይታሰባል፤ ይህ ደግሞ ምክንያታዊነት የጎደለው ነው” ብለዋል።

      እንደ እውነቱ ከሆነ ለሞት በሚዳርግ በሽታ የተያዙ ሰዎች እልህ አስጨራሽ በሆነ ከባድ ትግል ላይ ናቸው። ስለሆነም የሚወዷቸው ሰዎች ይህ ከባድ ቀንበር ሳያንስ በእነርሱ ላይ የጥፋተኝነት ስሜት መጨመር እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው። ታዲያ ተስፋ ምንም ዋጋ የለውም ብለን መደምደም ይኖርብናል?

      በጭራሽ። ለምሳሌ ያህል ከላይ የጠቀስናቸው ዶክተር ሕመምንና የሕመም ምልክቶችን ማስታገሥ ስለሚቻልበት መንገድ ልዩ ሥልጠና ወስደዋል። ይህ ዓይነቱ ሕክምና በሽታን በማዳን ወይም ዕድሜን በማራዘም ላይ ሳይሆን በሽተኛው በሕይወት እስከኖረ ድረስ ምቾት እንዲሰማውና ደስተኛ እንዲሆን በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ መስክ ላይ የተሰማሩ ዶክተሮች በጠና የታመሙ በሽተኞችን እንኳ ሳይቀር ደስተኛ የሚደርጉ የሕክምና ዓይነቶች ጠቃሚ መሆናቸውን በጥብቅ ያምናሉ። ተስፋ ይህንና ከዚህም ያለፈ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።

      ተስፋ ያለው ጠቀሜታ

      ዶክተር ጊፎርድ ጆንዝ የተባሉ አንድ የሕክምና መጽሔት አዘጋጅ “ተስፋ ፍቱን መድኃኒት ነው” በማለት ይናገራሉ። እኚህ ሰው በሞት አፋፍ ላይ ለሚገኙ በሽተኞች ስሜታዊ ድጋፍ ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ለማወቅ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶችን መርምረዋል። እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ተስፋን ለማለምለምና አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ይረዳል ተብሎ ይታሰባል። በ1989 የተደረገ አንድ ጥናት እንዲህ ያለውን ድጋፍ ያገኙ በሽተኞች ረዥም ዕድሜ እንደኖሩ የጠቆመ ሲሆን በቅርቡ የተደረገ ሌላ ጥናት ግን ውጤቱን አጠራጣሪ አድርጎታል። የሆነ ሆኖ ስሜታዊ ድጋፍ የሚያገኙ በሽተኞች ከማያገኙት ጋር ሲነጻጸሩ የሚያጋጥማቸው የመንፈስ ጭንቀትና የሕመም ስሜት አነስተኛ እንደሆነ ጥናቶች አረጋግጠዋል።

      አዎንታዊና አፍራሽ አመለካከት በልብ በሽታ ላይ በሚያስከትለው ውጤት ላይ ያተኮረ አንድ ጥናት እንመልከት። ስለ ሕይወት ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ ወይም አፍራሽ መሆኑን ለማየት ከ1,300 በሚበልጡ ሰዎች ላይ ጥንቃቄ የታከለበት ጥናት ተካሂዶ ነበር። ከአሥር ዓመት በኋላ በእነዚህ ሰዎች ላይ በተደረገው ክትትል ከመካከላቸው 12 በመቶ የሚያህሉት የልብ ሕመም እንዳጋጠማቸው ተደርሶበታል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች ውስጥ አፍራሽ አመለካከት ያላቸው አዎንታዊ አመለካከት ካላቸው በ2 እጥፍ ገደማ ይበልጣሉ። በሃርቫርድ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የጤናና ማኅበራዊ ሁኔታ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑ ሎረ ኩብዛንስኪ የተባሉ ሴት እንደሚከተለው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “‘አዎንታዊ አስተሳሰብ’ ለጤንነታችሁ ጥሩ ነው ለሚለው አመለካከት የሚቀርበው ማስረጃ በአብዛኛው በምርምር የተደገፈ አልነበረም። በልብ በሽታ ዙሪያ የተደረገው ይህ ጥናት ግን ይህን አመለካከት የሚደግፍ ተጨባጭ የሕክምና ማስረጃ አስገኝቷል።”

      ጥሩ ጤንነት እንደሌላቸው ከሚሰማቸው ሰዎች ይልቅ ጥሩ ጤንነት እንዳላቸው የሚሰማቸው ሰዎች ከቀዶ ሕክምና በኋላ ቶሎ እንደሚያገግሙ አንዳንድ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ረዥም ዕድሜ በመኖርና በአዎንታዊ አመለካከት መካከል ግንኙነት እንዳለም ታውቋል። አንድ ጥናት አረጋውያን ስለ እርጅና ያላቸው አዎንታዊና አሉታዊ አመለካከት እንዴት እንደሚነካቸው መርምሯል። አረጋውያን እርጅና ከጥበብና ከካበተ ልምድ ጋር ዝምድና እንዳለው የሚያሳዩ ቃላት በፍጥነት የሚያልፉበት የኮምፒውተር ጨዋታ እንዲጫወቱ ከተደረጉ በኋላ ከበፊቱ የበለጠ ብርታትና ጥንካሬ አግኝተው መራመድ እንደጀመሩ ተደርሶበታል። እንዲያውም የታየው መሻሻል ለ12 ሳምንታት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት ከሚያስገኘው ውጤት ጋር ተመጣጣኝ ነበር!

      ተስፋ፣ ብሩሕ አመለካከትና አዎንታዊ አስተሳሰብ የመሳሰሉት ስሜቶች ለጤና ጠቃሚ መስለው የሚታዩት ለምንድን ነው? ምናልባት የሳይንስ ሊቃውንትና ሐኪሞች እርግጠኛ መልስ ለመስጠት በሚያስችላቸው መጠን ስለ ሰው አእምሮና አካል አላወቁም ይሆናል። የሆነ ሆኖ ጉዳዩን የሚያጠኑ ጠበብቶች በተሞክሮና በእውቀት ላይ ተንተርሰው ምሑራዊ ግምት መስጠት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በነርቭ ሥርዓት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ሲሉ ሐሳብ ሰጥተዋል:- “ደስተኛ መሆንና ተስፋን ማለምለም ጥሩ ነው። ደስተኝነት ውጥረትን የሚያስወግድ ደስ የሚል ሁኔታ ስለሆነ ለሰውነትም ይስማማል። ደስተኝነት ሰዎች ምንጊዜም ጤነኞች ሆነው ለመኖር ሊያደርጉት የሚችሉት አንድ ተጨማሪ ነገር ነው።”

      ይህ አስተያየት ለሐኪሞች፣ ለሥነ ልቦና ተመራማሪዎችና ለሳይንስ ሊቃውንት አዲስ ሊመስል ቢችልም ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን አዲስ አይደለም። ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን በመንፈስ አነሳሽነት “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል” የሚለውን ሐሳብ በጽሑፍ አስፍሯል። (ምሳሌ 17:22) እዚህ ላይ የተባለውን ልብ በል። ይህ ጥቅስ ደስተኛ ልብ “ጥሩ መድኀኒት ነው” ይላል እንጂ ማንኛውንም ሕመም ይፈውሳል አይልም።

      እንዲያውም ተስፋ መድኃኒት ቢሆን ኖሮ እሱን የማያዝ ማን ሐኪም ይኖራል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ሊሆን ይችላል። የሆነ ሆኖ ተስፋ ጥሩ ጤንነት ከማስገኘቱም በላይ ሌሎች ጥቅሞች አሉት።

      አዎንታዊም ሆነ አፍራሽ አመለካከት በሕይወትህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

      አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በብዙ መንገዶች እንደሚጠቀሙ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ሌላው ቀርቶ በስፖርቱ መስክ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሴት አትሌቶች ላይ አንድ ጥናት ተካሂዶ ነበር። አሠልጣኞቹ ስለ አትሌቶቹ ችሎታ ጥንቃቄ የተሞላበት ግምገማ አቀረቡ። በሌላ በኩል ደግሞ አትሌቶቹ ራሳቸው ስለሚያገኙት ውጤት ያላቸው ተስፋ ተጠና። ስለሚያገኙት ውጤት በትክክል ለመተንበይ ያስቻለው አሠልጣኞቻቸው አትሌቶቹ ከዚያ በፊት ባስመዘገቡት ችሎታ ላይ ተንተርሰው ያቀረቡት ግምገማ ሳይሆን ሴቶቹ ራሳቸው ስለ ውጤታቸው የነበራቸው ተስፋ ነበር። ተስፋ ይህን ያህል ብርቱ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ያስቻለው ምንድን ነው?

      የአዎንታዊ አመለካከት ተቃራኒ በሆነው አፍራሽ አመለካከት ላይ ጥናት በማድረግ ብዙ እውቀት ለማግኘት ተችሏል። በ1960ዎቹ ዓመታት የተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች የእንስሳትን ባሕርይ በሚመለከት ያልተጠበቁ ውጤቶችን አስገኝተዋል። ተመራማሪዎቹ ከእነዚህ ውጤቶች በመነሳት ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው በሚገጥሟቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ሳቢያ ውለው አድረው “ምንም ነገር ባደርግ አይሳካልኝም” የሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊያዳብሩ እንደሚችሉ ደርሰውበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥናቱ የተካሄደባቸው ሰዎች ደስ የማይል ድምፅ እንዲሰሙ ተደረጉና የተለያዩ የኤሌክትሪክ ቁልፎችን በየተራ በመጫን ጫጫታውን ማስቆም እንደሚችሉ ተነገራቸው። እነሱም እንደተባሉት አድርገው ድምፁን ማስቆም ቻሉ።

      በሁለተኛው ቡድን ውስጥ ላሉትም ይኸው ነገር ተነገራቸው። ሆኖም የኤሌክትሪክ ማጥፊያውን መጫናቸው ምንም ውጤት አላስገኘም። በዚህም ምክንያት በሁለተኛው ቡድን ውስጥ ካሉት መካከል ብዙዎቹ ምንም ማድረግ አንችልም የሚል ስሜት አዳበሩ። በዚያው ዕለት በተደረገ ሌላ ጥናት ላይ እነዚህ ሰዎች ምንም ነገር ቢያደርጉ ልዩነት እንደማያመጣ ስለተሰማቸው ሙከራ ከማድረግ ተቆጠቡ። በዚሁ በሁለተኛው ቡድን ውስጥ ያሉ አዎንታዊ አመለካከት የነበራቸው ሰዎች ግን ምንም ማድረግ አንችልም ብለው ተስፋ አልቆረጡም።

      ከእነዚህ ሙከራዎች መካከል አንዳንዶቹን ያዘጋጁት ዶክተር ማርቲን ሴሊግመን አዎንታዊና አፍራሽ አመለካከትን ማጥናት የዕድሜ ልክ ሥራቸው እንዲሆን ለመወሰን ተገፋፍተዋል። በዚህም ምክንያት ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ማሰብ የሚቀናቸው ሰዎች ስላላቸው አስተሳሰብ በጥንቃቄ አጠኑ። ከዚያም እንዲህ ያለው አፍራሽ አመለካከት ሰዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸው እንቅፋት እንደሚሆንባቸው አልፎ ተርፎም ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳይወስዱ እንደሚያደርጋቸው ተገነዘቡ። ሴሊግመን አፍራሽ አመለካከትንና የሚያስከትላቸውን ውጤቶች በሚመለከት ሲያጠቃልሉ እንዲህ አሉ:- “ለሃያ አምስት ዓመት ካደረግሁት ጥናት እንደተገነዘብኩት አፍራሽ አመለካከት እንዳላቸው ሰዎች ማንኛውም መጥፎ አጋጣሚ የሚደርስብን በራሳችን ጥፋት እንደሆነ አድርገን የማሰብ ልማድ ከተጠናወተንና ይህንንም ለመለወጥ ምንም ማድረግ እንደማንችል ከተሰማን ለምናደርገው ነገር ሁሉ እንቅፋት ስለሚሆንብን የፈራነው ይደርስብናል።”

      ከላይ እንደተጠቀሰው እንዲህ ዓይነቱ መደምደሚያ ለአንዳንዶች አዲስ ቢመስልም ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን እንግዳ ነገር አይደለም። የሚከተለውን ምሳሌ ልብ በል:- “በመከራ ጊዜ ፈራ ተባ ካልህ፣ ዐቅምህ ምንኛ ደካማ ነው!” (ምሳሌ 24:10) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ መቁረጥ አፍራሽ አስተሳሰብ እንዲያድርብህና አስፈላጊውን ነገር እንዳታደርግ አቅም ሊያሳጣህ እንደሚችል ይገልጻል። ታዲያ አፍራሽ አመለካከትን ታግለህ በማሸነፍ አዎንታዊ አመለካከትን ለማዳበርና ተስፋህን ለማለምለም ምን ልታደርግ ትችላለህ?

      [በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ተስፋ ብዙ መልካም ነገሮችን ለማድረግ ያስችላል

  • አፍራሽ አመለካከትን መዋጋት ትችላለህ
    ንቁ!—2004 | ግንቦት 8
    • አፍራሽ አመለካከትን መዋጋት ትችላለህ

      የሚያጋጥሙህን እንቅፋቶች የምትመለከታቸው እንዴት ነው? በርካታ ጠበብቶች እንደሚያምኑት ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አዎንታዊ ወይም አፍራሽ አመለካከት ያለህ ሰው ስለመሆንህ ይናገራል። ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ከባድ ችግሮች የሚደርሱብን ሲሆን በአንዳንዶቻችን ላይ ደግሞ ችግሩ ያይላል። ታዲያ አንዳንድ ሰዎች ከደረሰባቸው ችግር አገግመውና መንፈሳቸውን አድሰው እንደገና ሲሞክሩ ሌሎች ግን በጥቃቅን ችግሮችም እንኳን ተስፋ የሚቆርጡት ለምንድን ነው?

      ለምሳሌ ያህል፣ ሥራ በመፈለግ ላይ ነህ እንበል። ለቃለ መጠይቅ ቀረብህና ተቀባይነት ሳታገኝ ቀረህ። ከዚያ በኋላ ስለዚህ ሁኔታ ምን ይሰማሃል? ምናልባት አንተን በአንተነትህ ሳይቀበሉህ የቀሩ ይመስል ሁኔታውን እንደዘላቂ ችግር ቆጥረህ ‘እንደ እኔ ያለውን ሰው ማንም ስለማይቀጥር ፈጽሞ ሥራ አላገኝም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይባስ ብሎ ደግሞ ይህ አንድ አጋጣሚ ለሁሉም የሕይወትህ ዘርፍ የሚኖርህን አመለካከት አጨልሞብህ ‘እኔ ጨርሶ የማልረባ ሰው ነኝ፤ ለማንም አልጠቅምም’ እንድትል ሊያደርግህ ይችላል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አንድ ሰው አፍራሽ አመለካከት እንዳለው በግልጽ የሚያሳይ ነው።

      አፍራሽ አመለካከትን መዋጋት

      አፍራሽ አመለካከትን መዋጋት የምትችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ እንዲህ ያሉትን አሉታዊ አስተሳሰቦች ለይቶ ማወቅ መቻል ነው። ቀጣዩ እርምጃ ደግሞ እነዚህን አሉታዊ አስተሳሰቦች መዋጋት ይሆናል። ተቀባይነት እንዳታገኝ ያደረጉህን ሌሎች ምክንያቶች ለማወቅ ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ ቃለ መጠይቁን ማለፍ ያልቻልከው በእርግጥ ማንም ሊቀጥርህ ስለማይፈልግ ነው? ወይስ ቀጣሪው ሌሎች መሥፈርቶችን የሚያሟላ ሰው ስለፈለገ?

      በተጨባጭ እውነታዎች ላይ በማተኮር እንዲህ ያለው አፍራሽ አመለካከት መሠረተ ቢስ መሆኑን ልትገነዘብ ትችላለህ። አንድ ጊዜ ተቀባይነት ስላላገኘህ ብቻ በእርግጥ ጨርሶ አትረባም ማለት ነው? መጠነኛ ስኬት ስላገኘህባቸው መስኮች ማለትም ስለ መንፈሳዊ እንቅስቃሴህ፣ ከቤተሰብህ ወይም ከወዳጆችህ ጋር ስላለህ ግንኙነት ለምን አታስብም? ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ ወደ አእምሮህ የሚመጡትን “ክፉ ሐሳቦች” ቶሎ ከአእምሮህ አውጣቸው። ለመሆኑ ወደፊት ፈጽሞ ሥራ እንደማታገኝ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? አሉታዊ አስተሳሰብን ከአእምሮህ ለማውጣት ልታደርገው የምትችለው ሌላም ነገር አለ።

      አዎንታዊና በግብ ላይ ያተኮረ አስተሳሰብ

      በቅርብ ዓመታት ተመራማሪዎች ለተስፋ ጠበብ ያለ ሆኖም ትኩረት የሚስብ ፍቺ ሰጥተውታል። ተስፋ ከግቦችህ ላይ እንደምትደርስ ማመንን ይጨምራል ብለው ይናገራሉ። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ተስፋ በእርግጥ ግብ ላይ ከመድረስ በላይ የሆኑ ነገሮችንም የሚጨምር ቢሆንም ተመራማሪዎቹ የሰጡት ፍቺ በበርካታ መንገዶች ጠቃሚ ይመስላል። እንዲህ ያለው ተስፋ ይበልጥ አዎንታዊና በግብ ላይ ያተኮረ አስተሳሰብ እንድናዳብር ሊረዳን ይችላል።

      ለመጪው ጊዜ ያወጣናቸው ግቦች ላይ እንደርሳለን ብለን ለማመን እንድንችል ግብ የማውጣትና እዚያ ላይ የመድረስ ልምድ ማጎልበት ያስፈልገናል። እንዲህ ዓይነት ልምድ እንደሌለህ ከተሰማህ ለራስህ ስለምታወጣቸው ግቦች በጥሞና ማሰቡ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለመሆኑ ግቦች አሉህ? ብዙውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የምንሰጠው ምን እንደሆነ እንኳ ቆም ብለን ሳናስብ በዕለታዊ የኑሮ ውጣ ውረዶች በቀላሉ ልንጠመድ እንችላለን። ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን በግልጽ ማስቀመጥን በሚመለከት መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ” በማለት ከረዥም ጊዜ በፊት ጥሩ አድርጎ የገለጸውን ምክር እናገኛለን።—ፊልጵስዩስ 1:10

      ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡንን ነገሮች ከወሰንን በኋላ በተለያዩ መስኮች ለምሳሌ ያህል ከመንፈሳዊ ሕይወታችን፣ ከቤተሰብ ሕይወታችን ወይም ከሥጋዊ ሕይወታችን ጋር በተያያዘ ወሳኝ ግቦችን ማውጣት ቀላል ይሆንልናል። ይሁንና መጀመሪያ ላይ ብዙ ግቦችን አለማውጣቱ እንዲሁም እያንዳንዱ ግብ ልንደርስበት የምንችል መሆኑን ማረጋገጡ አስፈላጊ ነው። አንድ ግብ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ከሆነብን ሊያስጨንቀን ብሎም ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። በመሆኑም ብዙውን ጊዜ የረዥም ጊዜ ግቦችን በአጭር ጊዜ ግቦች መከፋፈል የተሻለ ነው።

      “ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም” የሚለው የጥንት ብሂል እውነትነት አለው። ወሳኝ የሆኑ ግቦችን ካወጣን በኋላ ከግቦቻችን ላይ ለመድረስ የሚያስችል ወኔና ቁርጠኝነት ሊኖረን ያስፈልጋል። ባወጣናቸው ግቦች አስፈላጊነትና እነርሱ ላይ መድረስ በሚያስገኘው ጥቅም ላይ በማሰላሰል ቁርጠኝነታችንን ማጠናከር እንችላለን። እንቅፋቶች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ የታወቀ ነው፤ ሆኖም እነዚህን መሰናክሎች መውጫ ቀዳዳ እንደሌላቸው ችግሮች ሳይሆን ልንወጣቸው እንደምንችላቸው ፈተናዎች አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል።

      ሆኖም ግቦቻችን ላይ ለመድረስ ስለሚያስችሉን ተግባራዊ መንገዶችም ማሰብ ያስፈልገናል። ስለ ተስፋ ጠቃሚነት ሰፊ ጥናት ያካሄዱ ሪክ ሲንደር የተባሉ ደራሲ አንድ ሰው ያሰበው ግብ ላይ ለመድረስ የተለያዩ መንገዶችን መፈለግ እንደሚኖርበት ይመክራሉ። በመሆኑም አንዱ መንገድ ውጤታማ ካልሆነ ሌሎች አማራጮችን መሞከር እንችላለን።

      በተጨማሪም ሲንደር አንድን ግብ በሌላ ግብ የመተካት ልማድ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ። አንድ ግብ ላይ እንዳንደርስ መሰናክል ካጋጠመን እርሱን ይዘን መብሰልሰል ተስፋ ከመቁረጥ በቀር ምንም ፋይዳ አይኖረውም። በሌላ በኩል ግን ያንን ግብ ሊደረስበት በሚችል የተሻለ ግብ መተካት ተስፋችንን የምንጥልበት ነገር ያስገኝልናል።

      በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ ምሳሌ ይዞልናል። ንጉሥ ዳዊት ለአምላኩ ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የመሥራት ትልቅ ግብ ነበረው። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን መብት የሚያገኘው ልጁ ሰሎሞን እንደሆነ ነገረው። ዳዊት በሁኔታው ቅር ከመሰኘት ወይም እኔ ካልሠራሁ ብሎ ችክ ከማለት ይልቅ የነበረውን ግብ ቀየረ። መላ ጉልበቱን ልጁ ወደፊት ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ገንዘብና ቁሳቁስ ለማጠራቀም አዋለ።—1 ነገሥት 8:17-19፤ 1 ዜና መዋዕል 29:3-7

      አፍራሽ አመለካከትን በመዋጋት እንዲሁም አዎንታዊና በግብ ላይ ያተኮረ አመለካከት በማዳበር ተስፋችንን ከፍ በማድረግ ረገድ ቢሳካልንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። ለምን? በዚህ ዓለም አብዛኛው ጊዜ የተስፋ ቢስነት ስሜት የሚያጋጥመን ከቁጥጥራችን ውጪ ከሆኑ መንስኤዎች በመሆኑ ነው። የሰውን ልጅ እያሰቃዩ ያሉት እንደ ድህነት፣ ጦርነት፣ የፍትሕ መዛባት እንዲሁም በሽታና ሞት የመሳሰሉ አይቀሬ ችግሮች የሚያስከትሉት ስጋት እያሉ እንዴት አድርገን በተስፋ የተሞላ አመለካከት ይዘን መቀጠል እንችላለን?

      [በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ለቃለ መጠይቅ ቀርበህ ተቀባይነት ባታገኝ ወደፊት ጨርሶ ሥራ እንደማታገኝ ይሰማሃል?

      [በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ንጉሥ ዳዊት በነበሩት ግቦች ረገድ ማስተካከያ አድርጓል

  • እውነተኛ ተስፋ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?
    ንቁ!—2004 | ግንቦት 8
    • እውነተኛ ተስፋ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

      ሰዓትህ ተሰብሮ ሳይሆን አይቀርም፣ መሥራቱን አቁሟል። ለማሠራት ስትፈልግ ደግሞ ብዙ ምርጫዎች እንዳሉ ትገነዘባለህ። ሰዓት አዳሾችን የሚያስተዋውቁ ማስታወቂያዎች ሞልተዋል፤ ሁሉም ስለ ችሎታቸው በእርግጠኝነት የሚናገሩ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ የሚናገሩት ሐሳብ እርስ በርሱ ይጋጫል። ዳሩ ግን ይህን የተበላሸብህን ሰዓት ከዓመታት በፊት የሠራው በአካባቢህ የሚኖር የረቀቀ ችሎታ ያለው ጎረቤትህ መሆኑን ብትደርስበትስ? ከዚህም በላይ በነጻ ሊያድስልህ ፈቃደኛ እንደሆነ ቢነገርህ ምን ታደርጋለህ? ወደ ማን እንደምትሄድ ግልጽ ነው።

      ይህን ሰዓት ተስፋ ከማድረግ ችሎታህ ጋር አወዳድረው። በዚህ በመከራ በተሞላ ዘመን አንተም እንደ ብዙዎች ሁሉ በምንም ነገር ላይ ተስፋ እንዳጣህ ከተሰማህ ለእርዳታ ወደ ማን ዞር ትላለህ? በርካታ ሰዎች ችግሩን ለመፍታት ችሎታ እንዳላቸው ቢናገሩም ማለቂያ የሌለው ምክራቸው አደናጋሪና እርስ በርሱ የሚጋጭ ሊሆን ይችላል። ታዲያ መጀመሪያውኑ የሰውን ልጅ ተስፋ የማድረግ ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ወደሠራው ፈጣሪ ለምን ዞር አትልም? መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” በማለት ይናገራል። እርሱ ሊረዳህ ፈቃደኛ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 17:27፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

      ጥልቀት ያለው የተስፋ ፍቺ

      መጽሐፍ ቅዱስ ለተስፋ የሚሰጠው ፍቺ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሐኪሞች፣ የሳይንስ ሊቃውንትና የሥነ ልቦና ጠበብቶች ከሚሰጡት ፍቺ ይበልጥ ሰፊና ጥልቀት ያለው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተስፋ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በጉጉት መጠበቅና መልካም ነገር እንደሚመጣ ማመን የሚል ፍቺ አላቸው። በመሠረቱ ተስፋ የሁለት ነገሮች ቅንጅት ውጤት ነው። ይኸውም አንድን ጥሩ ነገር የማግኘት ምኞት እና ያ ጥሩ ነገር እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችለውን መሠረት አካትቶ የያዘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው ተስፋ በእውነታ እና በማስረጃ ላይ ጽኑ ሆኑ የተመሠረተ እንጂ እንዲያው ምኞት ብቻ አይደለም።

      በዚህ ረገድ ተስፋ በጭፍን ሳይሆን በማስረጃ ላይ ከተመሠረተ እምነት ጋር ተመሳሳይ ነው። (ዕብራውያን 11:1) ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በእምነትና በተስፋ መካከል ልዩነት እንዳለ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 13:13

      ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ የምትወደው ወዳጅህ አንድ ውለታ እንዲውልልህ ስትጠይቀው የምትፈልገውን እንደሚያደርግልህ ተስፋ አድርገህ ነው። በእርሱ የተማመንከውና ተስፋ ያደረግከው ወዳጅህን አሳምረህ ስለምታውቀውና ከዚያ በፊት ደግነቱንና ልግስናውን ስላየህ እንጂ እንዲያው በከንቱ አይደለም። እምነትህና ተስፋህ እርስ በርስ የተሳሰሩ ቢሆኑም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ታዲያ በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ እምነት ሊኖርህ የሚችለው እንዴት ነው?

      ለተስፋ መሠረቱ

      አምላክ የእውነተኛ ተስፋ ምንጭ ነው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ “የእስራኤል ተስፋ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኤርምያስ 14:8) የጥንት እስራኤላውያን የነበራቸው ማንኛውም አስተማማኝ ተስፋ ከእርሱ የመነጨ ስለሆነ እሱ ተስፋቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ እንዲያው ምኞት ብቻ አልነበረም። አምላክ እስራኤላውያን ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ሰጥቷቸው ነበር። በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከእነርሱ ጋር ባደረገው ግንኙነት ቃል የገባላቸውን ተስፋዎች በመፈጸም ረገድ መልካም ስም አትርፏል። የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ኢያሱ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ . . . ታውቃላችሁ” በማለት ነግሯቸዋል።—ኢያሱ 23:14

      በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም አምላክ የሰጠውን ተስፋ በመፈጸም ረገድ ያተረፈውን ስም እንደያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ቃል በገባቸው አስደናቂ ተስፋዎች እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ በሚዘግቡ ትክክለኛ ታሪኮች የተሞላ ነው። ትንቢታዊ ተስፋዎቹ እጅግ አስተማማኝ ከመሆናቸው የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ተስፋዎቹ በተሰጡበት ወቅት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ተደርጎ ተገልጿል።

      መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋ መጽሐፍ እንደሆነ የምንናገረው ለዚህ ነው። አምላክ ከሰዎች ጋር ስላደረጋቸው ግንኙነቶች የሚናገሩ ታሪኮችን ስታጠና በእሱ ላይ ተስፋ እንድታደርግ የሚገፋፋህ ምክንያት እየተጠናከረ እንደሚሄድ የተረጋገጠ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ሲል አስፍሯል።—ሮሜ 15:4

      አምላክ ምን ተስፋ ይሰጠናል?

      ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ተስፋ የሚያስፈልገን መቼ ነው? ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ነው ብለህ ትመልስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ተስፋ ፈጽሞ የማይጨበጥ መስሎ የሚታያቸው የሚወዱትን ሰው በሞት በሚነጠቁበት ጊዜ ነው። ደግሞስ ከሞት የበለጠ ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን ይኖራል? ሞት እያንዳንዳችንን እግር በእግር ይከታተለናል። ልናመልጠው የማንችል ከመሆኑም በላይ በራሳችን ከሞት ለመነሳት ኃይል የለንም። መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “የመጨረሻው ጠላት” ብሎ መጥራቱ የተገባ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:26

      ታዲያ ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ተስፋ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? ሞትን የመጨረሻው ጠላት ብሎ የጠራው መጽሐፍ ቅዱስ በዚያው ጥቅስ ላይ ይህ ጠላት ‘እንደሚደመሰስ’ ይናገራል። ይሖዋ አምላክ ከሞት ይበልጥ ኃይለኛ ነው። ይህንንም በበርካታ አጋጣሚዎች አረጋግጧል። እንዴት? ሙታንን በማስነሣት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በዘጠኝ የተለያዩ አጋጣሚዎች ኃይሉን ተጠቅሞ የሞቱ ሰዎችን እንደገና እንዳስነሳ የሚዘግቡ ታሪኮችን ይዟል።

      ከእነዚህ መካከል አንዱ ይሖዋ ለልጁ ለኢየሱስ ኃይል ሰጥቶ ለአራት ቀናት ሞቶ የቆየውን ወዳጁን አልዓዛርን እንዲያስነሣ ያደረገበት አጋጣሚ ነው። ኢየሱስ ይህን ያደረገው በምስጢር ሳይሆን በግልጽ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ነው።—ዮሐንስ 11:38-48, 53፤ 12:9, 10

      ‘እነዚያ ሰዎች የተነሡት ለምን ነበር? አርጅተው እንደገና ሞተው የለም?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን ሞተዋል። ሆኖም ከላይ እንደተገለጹት ያሉ ስለ ትንሣኤ የሚናገሩ እምነት የሚጣልባቸው ታሪኮች በመኖራቸው የሞቱብን የምንወዳቸው ሰዎች እንደገና እንዲነሱ ከመመኘት ያለፈ ነገር ሊኖረን ችሏል። ይኸውም እንደገና እንደሚነሱ ለማመን የሚያስችል መሠረት ወይም ማስረጃ አለን። በሌላ አነጋገር እውነተኛ ተስፋ አለን።

      ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሏል። (ዮሐንስ 11:25) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙታንን እንዲያስነሣ ይሖዋ የሚጠቀምበት እሱን ነው። ኢየሱስ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የክርስቶስን] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አዎን፣ በመቃብር የሚገኙ አንቀላፍተው ያሉት ሁሉ በገነት ምድር ላይ እንደገና ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው።

      ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ልብ የሚነካ የትንሣኤ ትዕይንት እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ በድናቸውም ይነሣል። እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ። ጠልህ እንደ ንጋት ጠል ነው፤ ምድር ሙታንን ትወልዳለች።”—ኢሳይያስ 26:19

      ይህ ተስፋ የሚያጽናና አይደለም? አንድ ሕፃን ጥበቃ በሚያገኝበት በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንደሚቆይ ሁሉ ሙታንም ማንም ሊያስበው ከሚችለው በላይ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ሥር ይገኛሉ። በእርግጥም በመቃብር ያረፉ ሁሉ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ወሰን የለሽ የማስታወስ ችሎታ ውስጥ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ። (ሉቃስ 20:37, 38) አዲስ የተወለደ ሕፃን አፍቃሪ ከሆነና በጉጉት ሲጠባበቀው ከቆየው ቤተሰብ ጋር እንደሚቀላቀል ሁሉ ሙታንም በቅርቡ ተነስተው አስደሳች ወደሆነና በደስታ ወደሚቀበላቸው ዓለም ይገባሉ! ስለዚህ ከሞት ጋር በምንጋፈጥበት ጊዜም ተስፋ አለን።

      ተስፋ ምን ጥቅም ሊያስገኝልህ ይችላል?

      ጳውሎስ ስለ ተስፋ ጠቃሚነት ብዙ ያስተምረናል። ተስፋን ከራስ ቁር ጋር በማመሳሰል የመንፈሳዊ ትጥቅ አንዱ አቢይ ክፍል እንደሆነ ተናግሯል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) ተስፋን ከራስ ቁር ጋር ያመሳሰለው ለምን ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ወታደር ወደ ጦርነት በሚዘምትበት ጊዜ በአብዛኛው ከሱፍ ወይም ከቆዳ በሚሠራ ቆብ ላይ የብረት ቁር ይለብስ ነበር። የብረት ቁሩ በወታደሩ ራስ ላይ የሚሰነዘሩት አብዛኞቹ ምቶች የሞት አደጋ ሳያስከትሉ ነጥረው እንዲመለሱ ያደርጋል። ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ቁም ነገር ምንድን ነው? ቁር በራስ ላይ ከሚሰነዘር ምት እንደሚከላከል ሁሉ ተስፋም አእምሮን ይጠብቃል። ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ ጠንካራ ተስፋ ካለህ መከራ በሚደርስብህ ጊዜ የአእምሮህ ሰላም በድንጋጤ አይናጋም ወይም ተስፋ አትቆርጥም። ታዲያ ከመካከላችን እንዲህ ዓይነቱ ቁር የማያስፈልገው ማን ነው?

      ጳውሎስ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተዛማጅ የሆነ ተስፋን ለመግለጽ ሌላም ጉልህ ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን።” (ዕብራውያን 6:19) ከአንድ ጊዜ በላይ የመርከብ አደጋ ደርሶበት በሕይወት የተረፈው ጳውሎስ የመልሕቅን ጥቅም አሳምሮ ያውቃል። መርከበኞች ማዕበል ሲያንገላታቸው የመርከቡን መልሕቅ ወደ ባሕሩ ይጥሉታል። መልሕቁ የባሕሩ ወለል ላይ አርፎ እንደማይነቃነቅ ሆኖ ከተያዘ መርከቡ ወደ ባሕሩ ዳር ተገፍቶ ከዓለት ጋር በመላተም ፋንታ ማዕበሉ ከሚያስከትለው አደጋ ለመትረፍና በሰላም ለመሄድ አጋጣሚ ይኖረዋል።

      በተመሳሳይም አምላክ ቃል የገባልን ነገሮች በሙሉ “ጽኑና አስተማማኝ” ከሆኑልን ይህን በመከራ የተሞላ ዘመን በሰላም እንድናልፈው ይረዱናል። የሰው ልጅ ከእንግዲህ በጦርነት፣ በወንጀል፣ በኀዘን አልፎ ተርፎም በሞት ፍዳውን የማያይበት ዘመን በቅርቡ እንደሚመጣ ይሖዋ ቃል ገብቷል። (በገጽ 20 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት) ይህን ተስፋ የሙጥኝ ብለን ብንይዝ በዚህ ዓለም ተስፋፍቶ በሚገኘው ምስቅልቅሉ የወጣ የብልግና መንፈስ ሳንሸነፍ ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ስለሚሰጠን ከጥፋት ለመዳን ይረዳናል።

      ይሖዋ የሚሰጠው ተስፋ አንተንም በግል ይጨምራል። እሱ ያዘጋጀልህን ሕይወት እንድታጣጥም ይፈልጋል። የእሱ ፍላጎት “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” ነው። ታዲያ ልንድን የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ እያንዳንዳችን ‘ትክክለኛውን እውነት ወደ ማወቅ መድረስ’ አለብን። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የአምላክን ቃል እውነት አስመልክቶ ይህን ሕይወት ሰጪ እውቀት እንድትቀስም ያበረታቱሃል። በዚህም አማካኝነት አምላክ የሚሰጥህ ተስፋ በዚህ ዓለም ልታገኝ ከምትችለው ከማንኛውም ተስፋ እጅግ የላቀ ነው።

      እንዲህ ያለ ተስፋ እስካለህ ድረስ አምላክ ከፈቃዱ ጋር ተስማምተህ የምታወጣቸውን ግቦች ሁሉ እንድትደርስባቸው የሚያስፈልግህን ጥንካሬ ሊሰጥህ ስለሚችል ፈጽሞ ተስፋ አትቆርጥም። (2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:13) የሚያስፈልግህ ይህ ዓይነቱ ተስፋ አይደለም? ስለዚህ ተስፋ የሚያስፈልግህ ከሆነ፣ ስትፈልገው የቆየኸው ይህን ከነበረ፣ አይዞህ። ተስፋው በእጅህ ነው። ልታገኘው ትችላለህ!

      [በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

      ተስፋ እንድናደርግ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች

      የሚከተሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ተስፋህን እንድታለመልም ሊረዱህ ይችላሉ።

      ◼ አምላክ ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።

      የአምላክ ቃል መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆንና አንድነት ባላቸው ደስተኛ ቤተሰቦች እንደምትሞላ ይናገራል።—መዝሙር 37:11, 29፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 21:3, 4

      ◼ አምላክ ሊዋሽ አይችልም።

      እርሱ ማንኛውንም ዓይነት ውሸት ይጠላል። ይሖዋ ከማንኛውም ዓይነት ነውር የጸዳና ቅዱስ ስለሆነ ከቶ ሊዋሽ አይችልም።—ምሳሌ 6:16-19፤ ኢሳይያስ 6:2, 3፤ ቲቶ 1:2፤ ዕብራውያን 6:18

      ◼ አምላክ ገደብ የለሽ ኃይል አለው።

      ይሖዋ ብቻ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ቃል የገባቸውን ነገሮች ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል አንዳችም ነገር የለም።—ዘፀአት 15:11፤ ኢሳይያስ 40:25, 26

      ◼ አምላክ ለዘላለም እንድትኖር ይፈልጋል።

      —ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

      ◼ አምላክ በእኛ ላይ ተስፋ አለው።

      በስህተታችንና በጉድለታችን ላይ ሳይሆን በጥሩ ባሕርይዎቻችንና በምናደርጋቸው ጥረቶች ላይ ማተኮር ይመርጣል። (መዝሙር 103:12-14፤ 130:3፤ ዕብራውያን 6:10) ትክክል የሆነውን እንደምናደርግ ተስፋ የሚያደርግ ሲሆን እንዲህ ማድረጋችን ያስደስተዋል።—ምሳሌ 27:11

      ◼ አምላክ ከዓላማው ጋር የሚስማሙ ግቦች ላይ እንድትደርስ እንደሚረዳህ ቃል ገብቷል።

      አገልጋዮቹ ተስፋ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው አይፈልግም። አምላክ እኛን ለመርዳት ከምንም በላይ ብርቱ የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ይሰጠናል።—ፊልጵስዩስ 4:13

      ◼ በአምላክ ተስፋ ማድረግ ፈጽሞ አያስቆጭም።

      እጅግ አስተማማኝና እምነት የሚጣልበት ስለሆነ አያሳፍራችሁም።—መዝሙር 25:3

      [በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ቁር ራስን ከጉዳት እንደሚጠብቅ ሁሉ ተስፋም አእምሮን ይጠብቃል

      [በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      እንደ መልሕቅ ሁሉ ጽኑ መሠረት ያለው ተስፋም መረጋጋት ያስገኛል

      [ምንጭ]

      Courtesy René Seindal/Su concessione del Museo Archeologico Regionale A. Salinas di Palermo

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ