የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሐምሌ 2017
ከሐምሌ 10-16
w88-E 9/15 17 አን. 8
ይሖዋ ሰይፉን ከሰገባው መዘዘ!
8 ቀጥሎ ደግሞ የባቢሎንና የግብፅ ገዢዎች በታላላቅ ንስሮች ተመስለዋል። አንዱ ንስር፣ ንጉሥ ዮአኪንን ከሥልጣኑ አንስቶ በቦታው ሴዴቅያስን በማስቀመጥ የአርዘ ሊባኖስን ዛፍ ቀንበጥ ሰበረ። ሴዴቅያስ ታማኝ እንደሚሆን ለናቡከደነጾር ቢምልም እንኳ ከሌላው ታላቅ ንስር ከግብፅ ገዢ እርዳታ በመጠየቅ ቃል ኪዳኑን አፈረሰ። ሴዴቅያስ መሐላውን በሚምልበት ጊዜ የአምላክን ስም ጠርቶ ከሆነ መሐላውን ማፍረሱ በይሖዋ ላይ ስድብ አምጥቷል። ቃል ማፍረስ በአምላክ ላይ ስድብ የሚያመጣ መሆኑን ማወቃችን ብቻ እንኳ ቃላችንን ከማፍረስ እንድንቆጠብ ሊያደርገን ይገባል። በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም መጠራት ልዩ መብት ነው!—ሕዝቅኤል 17:1-21
w88-E 9/15 17 አን. 7
ይሖዋ ሰይፉን ከሰገባው መዘዘ!
7 ታማኝ ባልሆኑት ነዋሪዎቿ ምክንያት ይሁዳ ጥሩ ፍሬ ባለማፍራቱ መቃጠል ብቻ በሚገባው የጫካ የወይን ግንድ ተመስላለች። (ሕዝቅኤል 15:1-8) በተጨማሪም ይሖዋ ከግብፅ ታድጎ ባሳደጋት ተወልዳ የተጣለች ልጅ ተመስላለች። ይሖዋ እንደ ሚስቱ አድርጎ ወስዷት ነበር፤ እሷ ግን ወደ ሐሰተኛ አማልክት ዘወር በማለት መንፈሳዊ ምንዝር በመፈጸሟ ጥፋት ደርሶባታል። ሆኖም አምላክ ታማኞች ከሆኑት ጋር ‘ዘላቂ ቃል ኪዳን ያደርጋል’፤ ይህም ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር የገባው አዲሱ ቃል ኪዳን ነው።—ሕዝቅኤል 16:1-63፤ ኤርምያስ 31:31-34፤ ገላትያ 6:16
ከሐምሌ 31–ነሐሴ 6
bsi07 7 አን. 4 [si-E 133 አን. 4]
የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 26—ሕዝቅኤል
4 የመጽሐፉን ትክክለኛነት የሚያረጋግጠው ሌላኛው ማስረጃ ሕዝቅኤል እንደ ጢሮስ፣ ግብፅና ኤዶም ባሉ አጎራባች አገሮች ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች አስገራሚ ፍጻሜ ነው። ለምሳሌ ጢሮስ እንደምትጠፋ ሕዝቅኤል ተንብዮ ነበር፤ ናቡከደነፆር ከተማዋን ለ13 ዓመታት ከከበባት በኋላ ሲይዛት ትንቢቱ በከፊል ተፈጽሟል። (ሕዝ. 26:2-21) ጢሮስ በዚህ ጦርነት ሙሉ በሙሉ አልጠፋችም። ይሖዋ የፈረደው ግን ሙሉ በሙሉ መጥፋት እንደሚገባት ነው። ይሖዋ በሕዝቅኤል አማካኝነት እንዲህ በማለት ተንብዮ ነበር፦ “ዐፈሯን ከላይዋ ጠርጌ የተራቈተ ዐለት አደርጋታለሁ። . . . ድንጋይሽን፣ ዕንጨትሽንና የግንቦች ፍርስራሽ ወደ ባሕር ይጥላሉ።” (26:4, 12) ታላቁ እስክንድር ከ250 ዓመታት በኋላ የደሴት ከተማ በሆነችው በጢሮስ ላይ በዘመተበት ጊዜ ይህ ሁሉ ተፈጽሟል። የእስክንድር ወታደሮች በየብስ ላይ የሚገኘውን የወደመውን ከተማ ፍርስራሽ ጠርገው ባሕሩ ውስጥ በመደልደል በደሴት ላይ ወደምትገኘው ከተማ የሚወስድ 800 ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ሠሩ። ከዚያም ውስብስብ የሆነ ከበባ በማድረግ 46 ሜትር ርዝመት ባለው አጥሯ ላይ ወጥተው ወደ ከተማዋ በመግባት በ332 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተቆጣጠሯት። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ብዛት ያላቸው ደግሞ በባርነት ተሸጡ። ሕዝቅኤል እንደተነበየው ጢሮስ ‘የተራቈተ ዐለት እንዲሁም የመረብ ማስጫ ቦታ’ ሆናለች። (26:14) ከተስፋይቱ ምድር በሌላኛው አቅጣጫ የሚገኙት ከዳተኞቹ ኤዶማውያንም ሕዝቅኤል በተነበየው መሠረት ተደመሰሱ። (25:12, 13፤ 35:2-9) በተጨማሪም ሕዝቅኤል ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋትና ስለ እስራኤል ተመልሶ መቋቋም የተናገራቸው ትንቢቶች ትክክል መሆናቸው ተረጋግጧል።—17:12-21፤ 36:7-14
ce-E 216 አን. 3
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው?
3 ዝነኛ የፊንቄ ወደብ የሆነችው ጢሮስ በስተ ደቡብ በኩል በምታዋስናትና የይሖዋ አምላኪ በሆነችው በእስራኤል ላይ ክህደት ፈጽማለች። ይሖዋ በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት ጢሮስ ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋ ተናግሯል፤ ይህ ትንቢት የተነገረው ከመፈጸሙ ከ250 ዓመታት በፊት ነበር። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ብሔራትን በአንቺ ላይ አስነሳለሁ። እነሱ የጢሮስን ቅጥሮች ያፈርሳሉ፤ ማማዎቿንም ያወድማሉ፤ አፈሯን ከላይዋ ጠርጌ አስወግዳለሁ፤ የሚያንጸባርቅ ገላጣ ዓለትም አደርጋታለሁ። በባሕር መካከል የመረብ ማስጫ ቦታ ትሆናለች።” በተጨማሪም ሕዝቅኤል “እነሆ፣ በጢሮስ ላይ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን ከሰሜን አመጣለሁ” በማለት ጢሮስን መጀመሪያ የሚከበውን አገርና ንጉሥ፣ በስም ጠቅሶ ተናግሯል።—ሕዝቅኤል 26:3-5, 7
it-1-E 70
እስክንድር
እስክንድር በትንሿ እስያ ማለትም አንደኛው በግረናይከስ ወንዝ ላይ፣ ሁለተኛው ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን የሚያህል የፋርስ ሠራዊት ከፍተኛ ሽንፈት በተከናነበበት በኢሰስ ሜዳ በፋርሳውያን ላይ ሁለት ወሳኝ ድሎችን ተቀዳጀ። ከዚያ በኋላ፣ በመሸሽ ላይ ያሉትን ፋርሳውያን ከማሳደድ ይልቅ ትኩረቱን ደሴት ላይ በምትገኘው በጢሮስ ከተማ ላይ አደረገ። ይህ ከመሆኑ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የጢሮስ ቅጥሮች፣ ማማዎች፣ ቤቶችና አፈር ወደ ባሕር እንደሚጣል ትንቢት ተነግሯል። (ሕዝቅኤል 26:4, 12) እስክንድር ናቡከደነጾር ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የደመሰሳትን በየብስ ላይ የምትገኘውን የጢሮስ ከተማ ክፍል ፍርስራሽ በመጠቀም ደሴት ላይ ወደሚገኘው የከተማዋ ክፍል የሚወስድ 800 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ ሠራ። እስክንድር በባሕር ኃይሉና በጦር መሣሪያዎች አማካኝነት ሐምሌ 332 ዓ.ዓ. ላይ ያቺን ኩሩ የባሕር ላይ እመቤት እንዳልነበረች አደረጋት።
w88-E 9/15 21 አን. 24
ይሖዋ ሰይፉን ከሰገባው መዘዘ!
24 ቀጥሎ ሕዝቅኤል አንድ ያልተለመደ ነገር እንዲያደርግ ታዘዘ። (ሕዝቅኤል 24:15-18ን አንብብ።) ነቢዩ ሚስቱ ስትሞት የሐዘን መግለጫ እንዳያሳይ የታዘዘው ለምንድ ነው? አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም፣ በነዋሪዎቿና በቤተ መቅደሱ ላይ በሚደርሰው ጥፋት ምን ያህል እንደሚደናገጡ ለማሳየት ነው። ሕዝቅኤል ጥፋቱን አስመልክቶ በበቂ ሁኔታ ስለተናገረ የኢየሩሳሌምን መጥፋት እስኪሰማ ድረስ ዳግመኛ የአምላክን መልእክት አይናገርም። በተመሳሳይም ሕዝበ ክርስትናም ሆነች ግብዝ የሆኑት ተከታዮቿ ጥፋት በሚደርስባቸው ወቅት ይደናገጣሉ። የጠባቂው ክፍል የሆኑት ቅቡዓን ስለ ሕዝበ ክርስትና ጥፋት የሚበቃቸውን ያህል ስለተናገሩ “ታላቁ መከራ” ከጀመረ በኋላ ምንም መናገር አያስፈልጋቸውም። (ማቴዎስ 24:21) የሕዝበ ክርስትና ተከታዮችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች አምላክ ‘ሰይፉን’ በሕዝበ ክርስትና ላይ በሚመዝበት ወቅት ቢደናገጡም እንኳ ይህን ያደረገው ‘ይሖዋ እንደሆነ ያውቃሉ።’—ሕዝቅኤል 24:19-27