በይሖዋ መታመንን ተምሬአለሁ
ያን ኮርፓ-ኦንዶ እንደተናገረው
ጊዜው በ1942 ሲሆን በሩሲያ፣ ኩርስክ አቅራቢያ በሃንጋሪ ወታደሮች እየተጠበቅኩ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሩስያ ጋር ውጊያ ገጥመው የነበሩት የሦስቱ ጥምር ኃይሎች እስረኞች ነበርን። የምቀበርበት ጉድጓድ ተቆፍሮ ነበር። ከአሁን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች አባል አይደለሁም ብዬ እንድፈርም የአሥር ደቂቃ ጊዜ ተሰጠኝ። ከዚያ በኋላ የሆነውን ነገር ከመተረኬ በፊት እዚህ ደረጃ ላይ የደረስኩት እንዴት እንደሆነ ልግለጽላችሁ።
የተወለድኩት በ1904 በአሁኑ ጊዜ በምሥራቅ ስሎቫኪያ በምትገኘው ዛሆር በምትባለው ትንሽ መንደር ነበር። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዛሆር በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቼኮዝሎቫኪያ አገር አካል ሆነች። በምንኖርበት መንደር 200 ቤቶችና ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ አንዱ የግሪክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የካልቪን ቤተ ክርስቲያን ነበር።
ወደ ካልቪን ቤተ ክርስቲያን እሄድ የነበረ ቢሆንም አኗኗሬ በጣም ልቅ ነበር። እኔ ከምኖርበት ብዙም ሳይርቅ አንድ በባሕርይው ለየት ያለ ሰው ይኖር ነበር። አንድ ቀን ጠጋ ብሎ አነጋገረኝና መጽሐፍ ቅዱስ አዋሰኝ። ይህን መጽሐፍ በእጄ ስነካ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። በዚህ ጊዜ በ1926 አካባቢ ማለት ነው፣ ባርቦራን አገባሁና ብዙም ሳይቆይ ባርቦራ እና ያን የተባሉ ሁለት ልጆችን ወለድን።
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብጀምርም ብዙዎቹ ነገሮች አይገቡኝም ነበር። ስለዚህ ወደማውቀው አንድ ፓስተር ዘንድ ሄድኩኝና እንዲረዳኝ ጠየኩት። “መጽሐፍ ቅዱስ የተዘጋጀው ለተማሩ ሰዎች ነው። በከንቱ ባትደክም ይሻላል” አለኝ። ከዚያም ካርታ እንድንጫወት ጋበዘኝ።
ከዚያ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሱን አውሶኝ ወደነበረው ሰው ዘንድ ሄድኩ። ሰውየው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ነበር። እኔን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁሉም ነገር ግልጥልጥ ብሎ ይታየኝ ጀመር። ከመጠን በላይ መጠጣቴን አቁሜ ጥሩ ሥነ ምግባር መከተል ጀመርኩ። እንዲያውም ለሌሎች ሰዎች ስለ ይሖዋ መናገር ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በዛሆር የተዘራው በ1920ዎቹ መግቢያ ላይ ሲሆን ወዲያው አንድ ንቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ተመሠረተ።
ይህ ሁሉ የሆነው ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ተቃውሞ እያለ ነበር። የአካባቢው ቄስ አብዷል ብሎ በማስነገር አብዛኞቹ የቤተሰቦቼ አባላት በእኔ ላይ እንዲነሱ ቅስቀሳ አደረገ። ይሁን እንጂ ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት በመቻሌ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ለማገልገል ቆርጬ ተነሳሁ። ከዚያም በ1930 ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩና ተጠመቅኩ።
ከባድ ፈተና የጀመረበት ጊዜ
በ1938 አካባቢያችን በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ከጀርመን ጎን ተሰልፋ በነበረችው በሃንጋሪ አገዛዝ ሥር ወደቀ። በዚያን ጊዜ ከአንድ ሺህ ያነሰ ሕዝብ ይኖርባት በነበረው መንደራችን 50 የምንሆን የይሖዋ ምሥክሮች እንኖር ነበር። ሕይወታችንንና ነፃነታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ መስበካችንን አላቋረጥንም።
በ1940 ለሃንጋሪ ጦር እንድሰለፍ በግዴታ ተወሰድኩ። ምን አደርግ ይሆን? የጦር መሣሪያዎቻቸውን ቀጥቅጠው ወደ ሰላም መሣሪያ ስለሚለውጡ ሰዎች የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንብቤአለሁ። እንዲሁም ከጊዜ በኋላ አምላክ ከምድረ ገጽ ጦርነትን ፈጽሞ እንደሚያጠፋ አውቃለሁ። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4) ስለዚህ ምንም ይምጣ ምን ላለመዋጋትና በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ላለመግባት ወሰንኩ።
የ14 ወር እስራት ተፈርዶብኝ በፔክስ፣ ሃንጋሪ እንድቆይ ተወሰነ። ሌሎች አምስት ምሥክሮችም በእስር ቤቱ ነበሩ፤ አንድ ላይ ለመሆን በመቻላችን ደስ አለን። ይሁን እንጂ ለተወሰነ ጊዜ እግሮቼ በሰንሰለት ታስረው ብቻዬን ተገልዬ እንድታሰር ተደርጎ ነበር። ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆናችን እንደበደብ ነበር። በተጨማሪም ሙሉ ቀን ቀጥ ብለን እንድንቆም እንገደድ ነበር፤ ማረፍ የምንችለው እኩለ ቀን ላይ ለሁለት ሰዓታት ብቻ ነበር። በዚህ መልኩ ለበርካታ ወራት ተሰቃይተናል። ሆኖም በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ስለነበረን ደስተኞች ነበርን።
አቋማችንን እንድናላላ የቀረበልን ጥያቄ
ከጦር ሠራዊቱ ጋር ተቀላቅለን ወደ ጦር ግንባር መሄዳችን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳመን አንድ ቀን 15 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ወደ እኛ መጡ። በውይይታችን መካከል “ነፍስ የማትሞት መሆኗንና ጦርነት ላይ እንዳለን ብንሞት ወደ ሰማይ እንደምንሄድ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሳያችሁን ከጦር ሠራዊቱ ጋር እንቀላቀላለን” አልናቸው። ማስረጃ ማቅረብ አልቻሉም፤ በዚህም የተነሳ በውይይቱ ለመቀጠል አልፈለጉም።
በ1941 የእስራት ጊዜዬ ስላለቀ ከቤተሰቦቼ ጋር የምገናኝበትን ጊዜ መናፈቅ ጀመርኩ። ሆኖም በሰንሰለት ታስሬ በሃንጋሪ፣ ሻርሽፓተክ ውስጥ ወደሚገኘው የጦር ሰፈር ተወሰድኩ። እዚያም እንደደረስን ነፃ ለመለቀቅ የሚያስችለኝ አንድ አጋጣሚ ተሰጠኝ። “ማድረግ ያለብህ ነገር ቢኖር እቤት ከተመለስክ በኋላ 200 ፔንጎ እንደምትከፍል በፊርማህ ማረጋገጥ ብቻ ነው” ተብሎ ተነገረኝ።
“ይህማ እንዴት ይሆናል?” ብዬ ጠየኳቸው። “ገንዘቡን የፈለጋችሁት ለምንድን ነው?”
“ገንዘቡን ከከፈልክ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ገብተህ እንድታገለግል የሚያስችል የአካል ብቃት እንደሌለህ የሚያረጋግጥ የጽሑፍ ማስረጃ ይሰጥሃል” ተባልኩ።
ይህ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ ከተተኝ። ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜያት ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት የተፈጸመብኝ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ጉስቁልና ደርሶብኛል። አሁን ጥቂት ገንዘብ እንደምከፍል ከተስማማሁ በነፃ ልለቀቅ ነው። “እስቲ ላስብበት” አልኳቸው።
ምን እንደማደርግ ግራ ተጋባሁ። ሚስቴና ልጆቼ በጣም ያሳስቡኛል። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ አንድ ማበረታቻ የያዘ ደብዳቤ ከአንድ የእምነት ባልደረባዬ ደረሰኝ። “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፣ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም” የሚለውን ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን 10:38 ላይ ያሰፈረውን የይሖዋን ቃላት ጠቅሶ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በጦር ካምፑ ውስጥ ያሉ ሁለት የጦር መኮንኖች አነጋገሩኝ። አንደኛው “የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አጥብቀህ በመያዝህ ምን ያህል እንደምናከብርህ አታውቅም! ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ!” አለኝ።
በቀጣዩ ቀን 200 ፔንጎ ከከፈልክ ትለቀቃለህ ወዳሉኝ ሰዎች ዘንድ ሄድኩና “ይሖዋ አምላክ እንድታሰር እንደፈቀደ ሁሉ የምፈታበትንም መንገድ እርሱ ራሱ ያዘጋጅልኛል። ለመለቀቅ ብዬ ገንዘብ አልከፍልም” አልኳቸው። በዚህም ምክንያት የአሥር ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። ሆኖም እምነቴን ለማስካድ የተደረገብኝ ሙከራ ይህ ብቻ አልነበረም። የጦር መሣሪያ ሳልይዝ ለሁለት ወር ብቻ ጦር ሠራዊቱ ውስጥ ገብቼ ባገለግል ምሕረት እንደሚደረግልኝ በፍርድ ቤቱ ተነገረኝ! ይህንንም ቢሆን እንደማልቀበል አስታወቅኩኝ። ከዚያም ፍርዱ የጸና ሆነ።
ስደቱ ተባባሰ
ፔክስ ወደሚገኘው እስር ቤት ዳግመኛ ተወሰድኩ። በዚህ ጊዜ ይደርስብኝ የነበረው ቅጣት ይበልጥ ጠነከረ። እጆቼን የፊጥኝ አስረው ለሁለት ሰዓታት ያህል በታሰሩት እጆቼ ወደ ላይ አንጠለጠሉኝ። በዚህም የተነሳ በሁለቱ ትከሻዎቼ ላይ ውልቃት ደረሰብኝ። እንደዚህ ያለው ቅጣት ለስድስት ወራት ያክል በተደጋጋሚ ተፈጽሞብኛል። አቋሜን ባለማላላቴ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።
በ1942 የፖለቲካ እስረኞችን፣ አይሁዳውያንንና 26 የይሖዋ ምሥክሮችን አንድ ላይ አድርገው የጀርመን ወታደሮች ይዘውት ወደነበረው ኩርስክ ወደሚባል ከተማ ወሰዱን። ከዚያም ለጀርመናውያን አሳልፈው ሰጡን፤ እነርሱም እስረኞቹ በጦር ግንባር ላይ ለሚገኙ ወታደሮች ምግብ፣ የጦር መሣሪያና ልብስ እንዲያጓጉዙ አደረጉ። እኛ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማችንን የሚጻረር በመሆኑ ይህን ለመሥራት ፈቃደኞች አልሆንም። በዚህም ምክንያት መልሰው ወደ ሃንጋሪዎቹ ላኩን።
በመጨረሻ ኩርስክ ውስጥ በሚገኝ እስር ቤት ተከተትን። ለበርካታ ቀናት በቀን ሦስት ጊዜ በቆመጥ እንደበደብ ነበር። ጭንቅላቴን በጣም ስለተመታሁ መሬት ላይ ተዘረርኩኝ። እየተደበደብኩ ሳለሁ አምርሬ ሞቴን ተመኘሁ። መላው ሰውነቴ ከመደንዘዙ የተነሳ ምንም ነገር አይሰማኝም ነበር። ለሦስት ቀን ያህል አንዲት ቁራሽ ምግብ አልተሰጠንም። ከዚያም ወደ ፍርድ ቤት ተወሰድንና ስድስቱ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ሲገደሉ ሀያዎቻችን ቀረን።
በጥቅምት 1942 በኩርስክ የደረሰብኝ የእምነት ፈተና ከዚህ ቀደም ከደረሱብኝ ፈተናዎች ሁሉ የከፋ ነበር። በጥንት ጊዜ የነበረው ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ሕዝቡ እጅግ አስፈሪ የሆነ ሁኔታ በገጠማቸው ጊዜ የተናገራቸው ቃላት የተሰማንን ስሜት ጥሩ አድርገው የሚገልጹ ነበሩ:- “ይህን የመጣብንን ታላቅ ወገን እንቃወም ዘንድ አንችልም፤ የምናደርገውንም አናውቅም፤ ነገር ግን ዓይኖቻችን ወደ አንተ ናቸው።”—2 ዜና መዋዕል 20:12
የቀረነው 20 እስረኞች በ18 የሃንጋሪ ወታደሮች ታጅበን የራሳችንን የመቃብር ጉድጓድ እንድንቆፍር ተወሰድን። ጉድጓዶቹን ቆፍረን እንደጨረስን በአንድ ሰነድ ላይ እንድንፈርም የአሥር ደቂቃ ጊዜ እንደተሰጠን ተነገረን። ሰነዱ በከፊል እንዲህ ይነበባል:- “የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ትምህርት ሐሰት ነው። ከአሁን በኋላ ትምህርቱን አላምንበትም ወይም አልደግፍም። ለሃንጋሪያውያን አገር እዋጋለሁ። . . . ከአሁን ጀምሮ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆኔን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ።”
አሥሩ ደቂቃ ካለፈ በኋላ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ተሰጠ:- “ወደ ቀኝ ዙር! ወደ መቃብሩ ሂድ!” ከዚያም “የመጀመሪያውና ሦስተኛው እስረኞች ጉድጓዱ ውስጥ ግቡ!” የሚል ትእዛዝ ተከተለ። እነዚህ ሁለት እስረኞች በሰነዱ ላይ እንዲፈርሙ ተጨማሪ አሥር ደቂቃ ተሰጣቸው። ከወታደሮቹ መካከል አንዱ “እምነታችሁን ካዱና ከመቃብሩ ውስጥ ውጡ!” በማለት ተማጸናቸው። አንድም ቃል የተናገረ አልነበረም። ከዚያም መኮንኑ ተኩሶ ገደላቸው።
“ሌሎቹንስ ምን እናርጋቸው?” በማለት አንድ ወታደር መኮንኑን ጠየቀ።
“እሰሯቸው” በማለት መለሰ። “እንደገና እናሠቃያቸውና ጠዋት በአሥራ ሁለት ሰዓት ላይ እንረሽናቸዋለን።”
ወዲያው ፍርሃት ፍርሃት አለኝ። የፈራሁት እሞታለሁ ብዬ ሳይሆን ሥቃዩን መቋቋም ያቅተኝና እምነቴን እክድ ይሆናል የሚል ስጋት አድሮብኝ ነው። ስለዚህም ወደፊት ወጣ አልኩና “ጌታዬ፣ አሁን ከገደላችኋቸው ሰዎች የተለየ የሠራነው ነገር የለም። እኛንም ለምን አትገድሉንም?” አልኩ።
ሆኖም ፈቃደኞች አልነበሩም። እጆቻችንን የፊጥኝ አሰሩን። ከዚያም በታሰሩት እጆቻችን አንጠለጠሉን። ሕሊናችንን ስንስት በላያችን ላይ ውኃ ያፈስሱብናል። የሰውነታችን ክብደት ትከሻችን እንዲወልቅ ስለሚያደርግ ይሰማን የነበረው ሥቃይ በቃላት የሚገለጽ አልነበረም። ይህ ዓይነቱ ሥቃይ ለሦስት ሰዓት ያህል ቀጠለ። ከዚያም ወዲያውኑ ከአሁን በኋላ ማንም የይሖዋ ምሥክር እንዳይገደል የሚል መመሪያ ወጣ።
ወደ ምሥራቅ መጓዝ፤ ከዚያም ማምለጥ
ከሦስት ሳምንታት በኋላ ወደ ዶን ወንዝ ዳርቻ ተጓዝን። ኃላፊዎቹ በሕይወት እንደማንመለስ ነግረውን ነበር። ቀን ቀን ቦይ እንድንቆፍርና መልሰን እንድንደፍን በማድረግ ዓላማ የሌለው ሥራ እንድንሠራ ያደርጉን ነበር። ሲመሽ በአካባቢው እንድንዘዋወር የተወሰነ ነፃነት ይሰጠን ነበር።
ሁኔታውን ስመለከት ሁለት አማራጮች እንዳሉ ተገነዘብኩ። አንደኛው እዚሁ መሞት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከጀርመናውያን አምልጠን እጃችንን ለሩሲያ ጦር መስጠት ነበር። ሦስታችን ብቻ ቀዝቃዛውን የዶን ወንዝ አቋርጠን ለማምለጥ ወሰን። ታኅሣሥ 12, 1942 ወደ ይሖዋ ጸለይንና ጉዞ ጀመርን። ወደ ሩሲያውያን ግንባር ስንደርስ ወዲያውኑ 35,000 ገደማ የሚሆኑ እስረኞች በሚገኙበት ካምፕ ውስጥ ጨመሩን። በጸደይ ወቅት በሕይወት የተረፉት 2,300 እስረኞች ብቻ ነበሩ። የቀሩት በረሃብ አለቁ።
ነፃ ብወጣም የገጠመኝ አሳዛኝ ሁኔታ
በቀሪው የጦርነቱ ወቅትና ጦርነቱ ካበቃ በኋላም ለብዙ ወራት በሩስያ እስር ቤት እንደታሰርኩ ቆየሁ። በመጨረሻም ኅዳር 1945 ወደ ትውልድ መንደሬ ወደ ዛሆር ተመለስኩ። እርሻችን ብልሽትሽቱ ወጥቶ ስለነበር እንደገና አንድ ብዬ መጀመር ነበረብኝ። በጦርነቱ ጊዜያት ባለቤቴና ልጆቼ እርሻው ላይ ይሠሩ ነበር። ሆኖም ጥቅምት 1944 የሩሲያ ጦር እየተቃረበ ሲመጣ ወደ ምሥራቅ ተጋዙ። የነበረን ንብረት አንድም ሳይቀር ተዘርፏል።
ከሁሉም የከፋው ደግሞ ወደ ቤት ስመለስ ባለቤቴ በጠና ታማ አገኘኋት። የካቲት 1946 ሞተች። ዕድሜዋ ገና 38 ዓመት ነበር። ከአምስት የመከራ ዓመታት በኋላ ስንገናኝ አብረን ያሳለፍነው ጊዜ በጣም አጭር ነበር።
ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በመካፈል ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ ማጽናኛ አገኘሁ። በ1947 በበርኖ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ 400 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዤ ለመገኘት ጥቂት ገንዘብ ተበደርኩ። በዚያም የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን ወንድም ናታን ኤች ኖርን ጨምሮ በርካታ ክርስቲያን ወንድሞቼ ከፍተኛ ማጽናኛና ማበረታቻ ሰጡኝ።
ከጦርነቱ በኋላ የነበረው ነፃነት ለረዥም ጊዜ አልዘለቀም። በ1948 የኮሙኒስት አገዛዝ ጭቆና ያደርስብን ጀመር። በቼኮዝሎቫኪያ የነበረውን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት ይመሩ የነበሩት በርካታ ወንድሞች በ1952 ታሰሩ። በዚህም ምክንያት ጉባኤዎችን እንዳገለግል ኃላፊነት ተሰጠኝ። በ1954 ተያዝኩና የአራት ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። ወንዱ ልጄ ያን እና የእርሱ ወንድ ልጅ ዩሪ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው እነርሱም ታሰሩ። በፓንክራትስ ግዛት ፕራግ ውስጥ በሚገኘው ወኅኒ ቤት ሁለት ዓመት አሳለፍኩ። በ1956 ምሕረት ተደረገልኝና ተለቀቅኩ።
በመጨረሻ ነፃነት ተገኘ!
በመጨረሻም በ1989 በቼኮዝሎቫኪያ የነበረው የኮሙኒስት አገዛዝ ተገረሰሰና የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሕጋዊ ዕውቅና አገኘ። በመሆኑም አንድ ላይ ለመሰብሰብና በይፋ ለመስበክ ነፃነት አገኘን። በዚያን ጊዜ በዛሆር አንድ መቶ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን ይህም በመንደሩ ካሉት 10 ሰዎች መካከል አንዱ የይሖዋ ምሥክር ነበር ማለት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በዛሆር 200 ሰዎች ሊያስቀምጥ የሚችል አንድ የሚያምርና ሰፊ የመንግሥት አዳራሽ ገነባን።
ጤንነቴ እየተቃወሰ በመሄዱ ወንድሞች ወደ መንግሥት አዳራሹ በመኪና ያመላልሱኛል። እዚያ ስሆን ደስ ይለኛል እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ሐሳብ ስሰጥ እርካታ ይሰማኛል። በተለይ ደግሞ በርካታ የልጅ ልጆቼን ጨምሮ ሦስት ትውልድ የሚሆኑ ቤተሰቦቼ ይሖዋን ሲያገለግሉ በመመልከቴ ልዩ ደስታ ይሰማኛል። ከእነዚህ መካከል አንደኛው በቤተሰብ ኃላፊነት ምክንያት ሥራውን እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ በቼኮዝሎቫኪያ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል።
በተደጋጋሚ ጊዜያት በርካታ ፈተና ደርሶብኝ በነበረበት ወቅት ጥንካሬ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ጠብቆ ያቆየኝ ‘የማይታየውን እንደማየው’ አድርጌ መላ ትኩረቴን በእርሱ ላይ ማድረጌ ነው። (ዕብራውያን 11:27) አዎን፣ የይሖዋን የማዳን እጅ አይቻለሁ። አሁንም እንኳን ቢሆን አቅሜ የሚፈቅደውን ያህል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ ለመገኘትና ለሕዝብ በሚሰጠው አገልግሎት ስሙን በማወጁ ሥራ ለመካፈል የምጥረው በዚህ የተነሳ ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሆር የሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ሐሳብ የመስጠት መብት በጣም ያስደስተኛል