ፈተናዎች ቢኖሩም በይሖዋ መደሰት
ጆርጅ ስኪፒኦ እንደተናገረው
በታኅሣሥ 1945 ከእጆቼና ከእግሮቼ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኜ በአንድ የሆስፒታል ክፍል ውስጥ ተኝቻለሁ። ለእኔ ሁኔታው ጊዜያዊ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር፤ ሌሎች ግን እንደገና በእግሬ ቆሜ መራመድ እችላለሁ የሚል ግምት አልነበራቸውም። ይህ ለአንድ ብርቱ የ17 ዓመት ልጅ እንዴት ያለ ፈታኝ ነገር ነበር! እንዲህ ያለውን ግምታዊ ሐሳብ ለመቀበል አልፈለግሁም ነበር! በቀጣዩ ዓመት ከአሠሪዬ ጋር ወደ እንግሊዝ መጓዝን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ውጥኖች ነበሩኝ።
በምንኖርባት በሴይንት ሄለና ደሴት በእጅጉ ተስፋፍቶ በነበረው በልምሻ በሽታ (poliomyelitis) ተለክፌ ነበር። ይህ በሽታ አሥራ አንድ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ብዙዎችንም ሽባ አድርጓል። ታምሜ ተኝቼ በነበረበት ወቅት ስላሳለፍኩት አጭር ሕይወትና ስለ ወደፊት ሁኔታዬ የማሰላስልበት ሰፊ ጊዜ አግኝቼ ነበር። ማሰላሰሌ መከራ ቢደርስብኝም ደስተኛ የምሆንበት ምክንያት እንዳለኝ እንድገነዘብ አስችሎኛል።
አነስተኛ ጅምር
በ1933 የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ፖሊስና የባብቲስት ዲያቆን ለነበረው አባቴ ለቶም ጥቂት የተጠረዙ መጽሐፎች ሰጥተውት ነበር። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ለአጭር ጊዜ በደሴቲቱ የቆዩ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ወይም አቅኚዎች ነበሩ።
አንደኛው መጽሐፍ የአምላክ በገና የሚል ርዕስ ነበረው። አባቴ ይህን መጽሐፍ ከቤተሰባችንና ፍላጎት ካላቸው የተወሰኑ ግለሰቦች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይጠቀምበት ነበር። መጽሐፉ የያዘው ትምህርት ከባድ ስለነበር ብዙም አይገባኝም ነበር። ሆኖም የተወያየንበትን እያንዳንዱን ጥቅስ በራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሰምርበት እንደነበር አስታውሳለሁ። አባቴ የምናጠናው ነገር እውነት መሆኑንና በባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚሰብከው ነገር የተለየ መሆኑን ወዲያውኑ ተገነዘበ። ስላወቀው ነገር ለሌሎች መናገርና ሥላሴ፣ እሳታማ ሲኦልና የማትሞት ነፍስ የሚባሉ ነገሮች እንደሌሉ ከመድረክ መስበክ ጀመረ። ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከፍተኛ ጉምጉምታ ፈጠረ።
በመጨረሻ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ቤተ ክርስቲያኑ ስብሰባ ጠራ። በመጀመሪያ የቀረበው ጥያቄ “ባፕቲስቶችን የሚደግፍ ማን ነው?” የሚል ነበር። አብዛኞቹ እንደግፋለን አሉ። ቀጥሎ “ይሖዋን የሚደግፍ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ሲቀርብ በግምት አንድ አሥር ወይም አሥራ ሁለት የሚሆኑ ሰዎች እንደግፋለን አሉ። እነዚህ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቀው እንዲወጡ ተጠየቁ።
በሴይንት ሄለና አዲስ ሃይማኖት ቀስ በቀስ የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። አባቴ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ጋር በመጻጻፍ በቴፕ የተቀዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን ለሕዝብ ለማሰማት የሚያስችል መሣሪያ እንዲልኩለት ጠይቆ ነበር። መሣሪያው ትልቅ ስለሆነ ወደ ሴይንት ሄለና ለመላክ እንደማይቻል ነገሩት። አንድ አነስተኛ የሸክላ ማጫወቻ መሣሪያ የተላከለት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ወንድሞች ተጨማሪ ሁለት ማጫዎቻዎች እንዲላክላቸው አዝዘው ነበር። በደሴቲቱ ውስጥ በእግርና በአህያ በመዘዋወር መልእክቱን ለሰዎች ይናገሩ ነበር።
መልእክቱ እየተስፋፋ ሲሄድ ተቃውሞውም እየጨመረ መጣ። እኔ በምማርበት ትምህርት ቤት ልጆች “ሰዎች ተሰብሰቡ፣ ሰዎች ተሰብሰቡ፣ የቶሚ ስኪፒኦንን የሸክላ ማጫወቻ ባንድ ስሙ!” እያሉ ይዘምሩ ነበር። በጓደኞቼ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የምፈልግ ተማሪ ስለነበርኩ ይህ ለእኔ በጣም ከባድ ፈተና ነበር። ታዲያ እንድጸና የረዳኝ ምንድን ነው?
ስድስት ልጆች የነበሩበት ትልቁ ቤተሰባችን ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነበረው። በተጨማሪም በየዕለቱ ጠዋት ከቁርስ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ እናነብ ነበር። ይህ ቤተሰባችን በእውነት ውስጥ በታማኝነት እንዲቀጥል ትልቅ እርዳታ እንዳበረከተለት ምንም አያጠራጥርም። እኔ በበኩሌ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ያደረብኝ ገና ትንሽ እያለሁ ሲሆን ለብዙ ዓመታት የዘለቀ ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልማድ ነበረኝ። (መዝሙር 1:1–3) ትምህርት ባቆምኩበት ወቅት ማለትም በ14 ዓመቴ በእውነት ላይ በሚገባ ተመሥርቼ የነበረ ሲሆን ይሖዋን መፍራትም በልቤ ውስጥ ነበር። ይህ ደግሞ እነዚያ ፈተናዎች ቢኖሩብኝም በይሖዋ እንድደሰት አስችሎኛል።
ተጨማሪ ፈተናዎችና ደስታዎች
ታምሜ ተኝቼ በነበርኩበት ጊዜ ወደኋላ መለስ ብዬ ስላሳለፍኩት የልጅነት ሕይወትና ወደፊት ስለሚጠብቀኝ ነገር ሳስብ ይህ ሕመም አምላክ ያመጣብኝ ፈተና ወይም ቅጣት አለመሆኑን ቀደም ሲል ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ተገንዝቤ ነበር። (ያዕቆብ 1:12, 13) ያም ሆኖ ግን በልምሻ በሽታ መለከፍ ከባድ ፈተና ነው፤ የሚያስከትለው ውጤት ደግሞ በቀሪው የሕይወት ዘመኔ አብሮኝ ይዘልቃል።
በሽታዬ እየተሻለኝ ሲሄድ እንደገና በእግሮቼ ለመራመድ ቀስ እያልኩ መለማመድ ነበረብኝ። በተጨማሪም አንዳንድ የእጆቼ ጡንቻዎች አይሠሩም ነበር። በየቀኑ በጣም ብዙ ጊዜ እወድቅ ነበር። ቢሆንም ልባዊ በሆነ ጸሎትና በማያቋርጥ ጥረት በ1947 በምርኩዝ እየታገዝኩ በእግሮቼ መራመድ ቻልኩ።
በዚህ ወቅት እንደኔው ዓይነት እምነት ያላት ዶርስ የምትባል አንዲት ወጣት ወደድኩ። ስለ ትዳር ለማሰብ ገና ልጆች ነበርን፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ በደንብ ለመራመድ ጥረት እንዳደርግ አነሳስቶኝ ነበር። የማገኘው ደሞዝ ትዳር ለመመሥረት የሚያስችል ስላልነበረ ሥራዬን ለቀቅኩና የራሴን የጥርስ ሕክምና ክሊኒክ ከፍቼ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ሠራሁ። በ1950 ተጋባን። በዚህ ጊዜ አንድ አነስተኛ መኪና ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ አጠራቅሜ ነበር። አሁን ወንድሞችን ወደ ስብሰባዎችና ወደ መስክ አገልግሎት ለመውሰድ እችላለሁ።
በደሴቲቱ ላይ የታየው ቲኦክራሲያዊ እድገት
በ1951 ማኅበሩ የመጀመሪያውን ተወካይ ወደ እኛ ላከ። ከደቡብ አፍሪካ የመጣ ያኮበስ ቫን ስታደን የሚባል ወጣት ወንድም ነበር። ከጥቂት ጊዜ በፊት ሰፊ ወደ ሆነ ቤት ተዛውረን ስለነበር አንድ ዓመት ሙሉ ከእኛ ጋር ተቀመጠ። የግሌን ሥራ እሠራ ስለነበር አንድ ላይ ሆነን በስብከቱ ሥራ ብዙ ጊዜ አሳልፈናል፤ ከእሱም እጅግ ጠቃሚ የሆነ ሥልጠና አግኝቻለሁ።
ኮስ ብለን የምንጠራው ያኮበስ መደበኛ የጉባኤ ስብሰባዎች የሚካሄዱበትን ሁኔታ አደራጅቶ ስለነበር በእነዚህ ስብሰባዎች ሁላችንም በደስታ እንካፈል ነበር። ፍላጎት ካላቸው ሰዎች መካከል መኪና የነበራቸው ሁለት ብቻ ስለነበሩ የመጓጓዣ ችግር ነበረብን። መሬቱ አባጣ ጎርባጣና ኮረብታማ የነበረ ከመሆኑም በላይ ደህና ናቸው የሚባሉት መንገዶች በጣም ጥቂት ነበሩ። በመሆኑም እያንዳንዱን ሰው ወደ ስብሰባ ቦታ መውሰድ ራሱን የቻለ ሥራ ነበር። አንዳንዶች ማለዳ ተነሥተው በእግራቸው ጉዞ ይጀምራሉ። በትንሿ መኪናዬ ውስጥ ሦስት ሰዎች እጭንና የተወሰነ ርቀት ከወሰድኳቸው በኋላ አወርዳቸዋለሁ። ከዚያም ቀሪውን መንገድ በእግራቸው ይቀጥላሉ። ወደ ኋላ ተመልሼ ሌሎች ሦስት ሰዎች ጭኜ የተወሰነ ርቀት ከወሰድኳቸው በኋላ አወርዳቸውና እመለሳለሁ። በመጨረሻ በዚህ ሁኔታ ሁሉም ወደ ስብሰባው ይደርሳሉ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ሁሉንም ቤታቸው ለማድረስ ደግሞ እንደዚያው እናደርግ ነበር።
በተጨማሪም ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ውጤታማ አቀራረቦችን እንዴት መጠቀም እንደምንችል ኮስ አስተምሮናል። ብዙ ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎች አጋጥመውናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ያን ያህል ጥሩ የሚባሉ አይደሉም። ይሁን እንጂ ከመስክ አገልግሎት የምናገኘው ደስታ የስብከት እንቅስቃሴአችንን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች የሚያደርሱብንን ፈተና የሚያስንቅ ነበር። አንድ ቀን ጠዋት ከኮስ ጋር እያገለገልሁ ነበር። ወደ አንድ በር ስንደርስ ከውስጥ ድምፅ ሰማን። ጮክ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብ ሰው ድምፅ ነበር። በደንብ የምናውቃቸውን የኢሳይያስ ምዕራፍ 2ን ቃላት በግልጽ እየሰማን ነበር። ቁጥር 4 ላይ ሲደርስ በሩን አንኳኳን። አንድ አረጋዊ ሰው ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ወደ ውስጥ እንድንገባ ጋበዙን፤ እኛም ኢሳይያስ 2:4ን ተጠቅመን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች አብራራንላቸው። የሚኖሩበት አካባቢ መኪና የማይገባበት ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላቸው። ቤታቸው ለመድረስ አቀበት ቁልቁለት መውጣትና መውረድ እንዲሁም ከድንጋይ ድንጋይ እየዘለሉ ወንዝ መሻገር ይጠይቅ ነበር። ይሁን እንጂ ልፋታችን ከንቱ ሆኖ አልቀረም። እኚህ ቅን አረጋዊ እውነትን ተቀብለው ተጠመቁ። ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በሁለት ከዘራ በመጠቀም የተወሰነ ርቀት በእግራቸው ከመጡ በኋላ የተቀረውን መንገድ በመኪና እወስዳቸው ነበር። እኚህ ወንድም እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ የታመኑ ምሥክር ነበሩ።
የፖሊስ አዛዡ ሥራችንን ይቃወም የነበረ ሲሆን ኮስን ከአገር ለማባረር በተደጋጋሚ ጊዜ ይዝት ነበር። በወር አንዴ ኮስን ለጥያቄ ይጠራው ነበር። ሁልጊዜ ኮስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ መልስ ይሰጠው ስለነበር ጥላቻው እየጨመረ ሄደ። በጠራው ቁጥር መስበኩን እንዲያቆም ኮስን ያስጠነቅቀው የነበረ ቢሆንም በዚያ ሁሉ ጊዜ እየተመሠከረለት ነበር። ኮስ ሴይንት ሄለናን ለቅቆ ከሄደ በኋላ እንኳ ሳይቀር መቃወሙን ቀጥሎ ነበር። ከዚያም ያ ግዙፍና ጠንካራ የፖሊስ አዛዥ በድንገት ታመመና መንምኖ ሣር አከለ። ሐኪሞች በሽታውን ሊያውቁለት አልቻሉም። በዚህ ምክንያት ደሴቲቱን ለቅቆ ሄደ።
ጥምቀትና የማያቋርጥ ጭማሪ
ኮስ በደሴቲቱ ላይ ሦስት ወር ከቆየ በኋላ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ማከናወኑ ተገቢ ሆኖ ተሰማው። ለጥምቀት የሚያገለግል ተስማሚ የሆነ ገንዳ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። ሰፊ ጉድጓድ ቆፍረን በሲሚንቶ ከለሰንነው በኋላ ውኃ ልንሞላው ወሰንን። ጥምቀቱ ሊከናወን ከታቀደበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ዝናብ በመዝነቡ በሚቀጥለው ቀን ጧት ጉድጓዱ ጢም ብሎ ሞልቶ ስናገኘው ተደሰትን።
በዚያን ዕለት እሁድ ቀን ጧት ኮስ የጥምቀት ንግግር አደረገ። የጥምቀት እጩዎቹ እንዲቆሙ ሲጠይቅ 26 የምንሆን ሰዎች ተጠማቂዎች የሚመልሷቸውን የተለመዱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ብድግ አልን። በደሴቲቱ ላይ ለመጠመቅ የመጀመሪያዎቹ ምሥክሮች የመሆን መብት አግኝተናል። ከመጠመቄ በፊት አርማጌዶን ይመጣል የሚል ስጋት ስለነበረኝ ይህ ቀን በሕይወቴ ውስጥ እጅግ የተደሰትኩበት ቀን ነበር።
ከጊዜ በኋላ ሁለት ጉባኤዎች የተቋቋሙ ሲሆን አንዱ በሌቭልዉድ ሌላኛው ደግሞ በጄምስታውን ይገኙ ነበር። ሦስት ወይም አራት ሆነን በየሳምንቱ 13 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ወደ አንደኛው ጉባኤ እንሄድና ቅዳሜ ማታ የሚካሄደውን የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትና የአገልግሎት ስብሰባ እንመራ ነበር። እሁድ ጠዋት በመስክ አገልግሎት ከተካፈልን በኋላ እንመለስና እነዚህኑ ስብሰባዎች ከመጠበቂያ ግንብ ጥናት ጋር በራሳችን ጉባኤ ውስጥ ከሰዓት በኋላና ማታ ላይ እናደርጋለን። ስለዚህ ቅዳሜና እሁድ አስደሳች በሆኑ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የተሞሉ ነበሩ። ሙሉ ጊዜዬን በስብከቱ ሥራ ማሳለፍ እመኝ የነበረ ቢሆንም የማስተዳድረው ቤተሰብ ነበረኝ። ስለዚህ በ1952 በጥርስ ሐኪምነት እንደገና ቋሚ የመንግሥት ሠራተኛ ሆንኩ።
በ1955 ተጓዥ የማኅበሩ ተወካዮች ማለትም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በየዓመቱ ደሴቲቱን መጎብኘት ጀመሩ፤ በጉብኝታቸውም ወቅት ለተወሰነ ጊዜ እኔ ቤት ያርፉ ነበር። እነዚህ ወንድሞች በቤተሰባችን ላይ ገንቢ ተጽእኖ አሳድረዋል። በዚሁ ጊዜ እኔም በደሴቲቱ በመዘዋወር የማኅበሩን ሦስት ፊልሞች በማሳየቱ ሥራ የመካፈል መብት አገኘሁ።
መለኮታዊ ፈቃድ የተባለው አስደሳች ስብሰባ
በ1958 በኒው ዮርክ በተካሄደው መለኮታዊ ፈቃድ በተሰኘው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ስል እንደገና ከመንግሥት ሥራዬ ለቀቅሁ። ያ ትልቅ ስብሰባ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረና በይሖዋ ለመደሰት ተጨማሪ ምክንያቶችን የሰጠኝ ነበር። ወደ ደሴቲቱ የሚወስድ ቋሚ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ ለአምስት ወራት ተኩል ያክል ቆየን። ስብሰባው ስምንት ቀናት የፈጀ ሲሆን ፕሮግራሞቹም ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምረው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ያበቁ ነበር። ሆኖም አንድም ቀን ደክሞኝ አያውቅም፤ እያንዳንዱን ቀን በጉጉት እጠባበቅ ነበር። በፕሮግራሙ ላይ ሴይንት ሄለናን በመወከል ለሁለት ደቂቃ የመናገር መብት አግኝቼ ነበር። በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ ለተሰበሰበ በጣም ብዙ ሕዝብ ንግግር ማድረግ ከመጠን በላይ የሚያስፈራ ነበር።
ስብሰባው አቅኚ ሆኜ ለማገልገል የነበረኝን ውሳኔ አጠናክሮልኛል። በተለይ “የአምላክ መንግሥት በመግዛት ላይ ነው—የዓለም ፍጻሜ ቀርቧልን?” የሚለው የሕዝብ ንግግር አበረታች ነበር። ከስብሰባው በኋላ በብሩክሊን የሚገኘውን የማኅበሩን ዋና መሥሪያ ቤትና ፋብሪካውን ተዘዋውረን ጎበኘን። በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ከነበረው ከወንድም ኖር ጋር በሴይንት ሄለና ስላለው የሥራ እድገት ተነጋገርን። አንድ ቀን ደሴቲቱን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳለው ነገረኝ። ለቤተሰባችንና ለወዳጆቻችን ለማሰማት ሁሉንም ንግግሮች በቴፕ ቀድተን የነበረ ሲሆን ስብሰባውን የሚያሳዩ በርካታ ተንቀሳቃሽ ፊልሞችንም አምጥተን ነበር።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የነበረኝ ግብ ተሳካ
በደሴቲቱ ላይ ሌላ የጥርስ ሐኪም ስላልነበረ ተመልሼ ስመጣ ወደ ቀድሞ ሥራዬ እንድመለስ ጥያቄ ቀረበልኝ። ሆኖም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን እንደምፈልግ ገለጽኩ። ከብዙ ድርድር በኋላ በሳምንት ስድስት ቀን እሠራ በነበረበት ጊዜ ከማገኘው የሚበልጥ ደሞዝ እየተከፈለኝ በሳምንት ሦስት ቀን ለመሥራት ተስማማሁ። ኢየሱስ የተናገራቸው “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” የሚሉት ቃላት እውነት መሆናቸውን ላረጋግጥ ችያለሁ። (ማቴዎስ 6:33) በሰለሉ እግሮች አቀበት ቁልቁለት መጓዝ ሁልጊዜ ቀላል አልነበረም። ያም ሆኖ ግን አቅኚ በመሆን ለ14 ዓመታት ያክል ያገለገልኩ ሲሆን በደሴቱ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች እውነትን እንዲማሩ መርዳቴ ደስታዬን እጥፍ ድርብ አድርጎታል።
በ1961 ሙያዊ ብቃት ያለው የጥርስ ሐኪም ለመሆን የሚያስችለኝ ሁለት ዓመት የሚፈጅ በነፃ የሚሰጥ ሥልጠና እንድወስድ መንግሥት ወደ ፊጂ ደሴቶች ሊልከኝ ፈልጎ ነበር። ሌላው ቀርቶ ቤተሰቤ ጭምር ከእኔ ጋር አብሮ ሊሄድ እንደሚችል ነግረውኝ ነበር። ይህ የሚያጓጓ ግብዣ ነበር፤ ሆኖም በጥሞና ካሰብኩበት በኋላ ግብዣውን ላለመቀበል ወሰንኩ። ለዚህን ያህል ረዥም ጊዜ ከወንድሞች ለመለየትና ከእነሱ ጋር የማገልገል መብት ለማጣት አልፈለግሁም። በጣም የተናደደው ጉዞውን ያዘጋጀው ከፍተኛው የሕክምና መኮንን ነበር። “መጨረሻው በጣም ቀርቧል ብለህ ብታስብም የምታገኘውን ገንዘብ እስከዚያው ድረስ ልትጠቀምበት ትችላለህ” አለኝ። ሆኖም በአቋሜ ጸናሁ።
በቀጣዩ ዓመት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄጄ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ለጉባኤ የበላይ ተመልካቾች የሚሰጠውን የአንድ ወር ሥልጠና እንድወስድ ተጋበዝኩ። የጉባኤ ኃላፊነቶቻችንን በሚገባ ለመወጣት የሚያስችል እጅግ ጠቃሚ የሆነ መመሪያ አግኝተናል። ከትምህርት ቤቱ በኋላ ከአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጋር አብሬ በመሥራት ተጨማሪ ሥልጠና አግኝቻለሁ። ከዚያም በሴይንት ሄለና የሚገኙትን ሁለት ጉባኤዎች ከአሥር ዓመት በላይ ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን አገልግያለሁ። ከጊዜ በኋላ ሌሎች ብቃት ያላቸው ወንድሞች በመገኘታቸው ተራ በተራ እየተለዋወጥን መሥራት ጀመርን።
በመሀሉ ጄምስታውንን ለቅቀን የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ሌቭልዉድ ተዛወርን፤ እዚያም ለአሥር ዓመታት ያህል ቆየን። በዚህ ጊዜ ውስጥ በአቅኚነት፣ ሦስት ቀን ለመንግሥት በመሥራትና በአንድ አነስተኛ ሱቅ ውስጥ በመነገድ ያለ እረፍት እሠራ ነበር። በተጨማሪም የጉባኤ ጉዳዮችን እከታተል የነበረ ሲሆን እኔና ባለቤቴ አራት ትንንሽ ልጆች ያሉት ቤተሰብ እናስተዳድር ነበር። ትንሽ እፎይታ ለማግኘት ስል የሦስት ቀን ሥራዬን አቁሜና ሱቁን ሸጬ ከቤተሰቤ ጋር ለሦስት ወር እረፍት ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕ ታውን ሄድኩ። ከዚያም ወደ አሴንሺን ደሴት ተዛውረን አንድ ዓመት ቆየን። በዚህ ጊዜ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት ችለን ነበር።
ወደ ሴይንት ሄለና ስንመለስ ቀደም ሲል ወደ ነበርንበት ወደ ጄምስታውን ተዛወርን። አንድ ከመንግሥት አዳራሹ ጋር ተያይዞ የተሠራ ቤት አድሰን ገባን። የገቢ ምንጭ ማግኛ እንዲሆነን እኔና ወንድ ልጄ ጆን አንድ ፎርድ የጭነት መኪና ቀይረን የአይስ ክሬም መሸጫ አደረግነው፤ ከዚያም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አይስ ክሬም ሸጥን። ሥራውን እንደ ጀመርን አካባቢ ይህንኑ መኪና እየነዳሁ ሳለ አደጋ አጋጥሞኝ ነበር። መኪናው ሲገለበጥ እግሮቼን አጣበቃቸው። በዚህ ምክንያት ከጉልበቴ በታች ያሉት ሕዋሳት ሞቱ፤ ለማገገምም ሦስት ወራት ወስዶብኛል።
እስከ አሁን ያገኘኋቸውና ወደፊት የማገኛቸው የተትረፈረፉ በረከቶች
ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ደስታችንን እጥፍ ድርብ የሚያደርጉ በርካታ በረከቶች አግኝተናል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በ1985 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው ብሔራዊ የአውራጃ ስብሰባ መገኘታችንና በወቅቱ በመገንባት ላይ የነበረውን አዲስ የቤቴል ሕንፃ መጎብኘታችን ነበር። ሌላው ደግሞ ከልጄ ከጆን ጋር በመሆን በጄምስታውን አቅራቢያ አንድ ውብ የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ በመገንባቱ ሥራ አነስተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ መቻላችን ነበር። በተጨማሪም ሦስቱ ወንዶች ልጆቻችን በሽምግልና እያገለገሉ በመሆናቸውና አንድ የልጅ ልጄ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ቤቴል እያገለገለ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን። እንዲሁም ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት ከፍተኛ ደስታ ልናጭድ ችለናል።
አገልግሎታችንን የምናከናውንበት መስክ ወደ 5,000 በሚሆኑ ሰዎች ብቻ ላይ የተወሰነ ነበር። ያም ሆኖ ግን በአንድ ክልል ደጋግሞ መሥራቱ ጥሩ ውጤቶችን አስገኝቷል። ለእኛ ጥላቻ ያላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ሴይንት ሄለና ወዳጃዊ በሆነ መንፈስ የምትታወቅ ነች፤ በእግር እየተጓዛችሁም ሆነ መኪና እየነዳችሁ የትም ቦታ ብትሄዱ ይቀበሏችኋል። ካለኝ ተሞክሮ እንደተገነዘብኩት ሰዎችን በቅርብ ማወቅ ለእነሱ መመስከርን ይበልጥ ቀላል ያደርገዋል። ምንም እንኳ ብዙዎቹ ወደ ሌላ አገር የሄዱ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ 150 የሚሆኑ አስፋፊዎች አሉን።
ልጆቻችን አድገው ራሳቸውን ችለው በመውጣታቸው እኔና ባለቤቴ ከተጋባን ከ48 ዓመታት በኋላ እንደገና ለብቻችን መኖር ጀመርን። ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ሁሉ የባለቤቴ ታማኝ ፍቅርና ድጋፍ ስላልተለየኝ ፈተናዎች ቢኖሩም በደስታ ይሖዋን ማገልገሌን እንድቀጥል ረድቶኛል። አካላዊ ጥንካሬያችን እየተዳከመ ቢሆንም መንፈሳዊ ጥንካሬያችን ግን ዕለት ዕለት ይታደሳል። (2 ቆሮንቶስ 4:16) ከቤተሰቤና ከወዳጆቼ ጋር በመሆን ሌላው ቀርቶ በ17 ዓመቴ ከነበረኝ አካላዊ ጤንነት ወደ ተሻለ ሁኔታ የምመለስበትን አስደሳች ጊዜ እጠባበቃለሁ። ልባዊ ምኞቴ በሁሉም መስክ ወደ ፍጽምና መድረስ ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ አፍቃሪውንና አሳቢውን አምላካችንን ይሖዋን እንዲሁም በመግዛት ላይ ያለውን ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን ለዘላለም ማገልገል ነው።—ነህምያ 8:10
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆርጅ ስኪፒኦ እና ሽማግሌ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሦስቱ ልጆቹ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆርጅ ስኪፒኦ ከባለቤቱ ከዶርስ ጋር