ሁከትና ብጥብጥ በበዛበት ዓለም ውስጥ ሰላም አግኝተዋል
በዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ ያለው ፎቶግራፍ በቦስኒያ እና በሄርዚጎቪና የሚካሄደውን የተፋፋመ ውጊያ ያሳያል። እንዲህ ባለው ቦታ ሰላም ሊገኝ ይችላልን? የሚያስገርም ቢሆንም መልሱ አዎን የሚል ነው። በዚያች አሳዛኝ አገር የሮማ ካቶሊክ፣ የምሥራቁ ኦርቶዶክስና ሙስሊም ማኅበረሰቦች ለግዛት ክልላቸው እየተዋጉ ባሉበት ወቅት ብዙ ሰዎች ሰላምን ይናፍቃሉ፤ አንዳንዶቹም ይህንን ሰላም አግኝተዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት የዶርም ቤተሰብ የሳራዬቮ ነዋሪዎች ናቸው። የዶርም ቤተሰብ በጦርነት በምትታመሰው በዚህች ከተማ ውስጥ ሁልጊዜ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ይናገራሉ። (ማቴዎስ 24:14) ለምን? ምክንያቱን የዶርም ቤተሰብ ይህ መንግሥት እውን እንደሆነ፣ በሰማይ እንደተቋቋመና ለሰው ዘር ሰላም የሚያስገኝ ከሁሉ የተሻለና ብቸኛ ተስፋ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ሐዋርያው ጳውሎስ “የሰላም ምሥራች” ብሎ በጠራው ምሥራች ላይ ሙሉ እምነት አላቸው። (ኤፌሶን 2:17 አዓት) እንደ ቦዞ እና ሄና ዶርም በመሳሰሉት ሰዎች አማካኝነት ብዙ ሰዎች በቦስኒያ እና በሄርዚጎቪና ሰላም እያገኙ ነው።
እውነተኛ ሰላም ይመጣል
ስለ ዶርም ቤተሰብ ብዙ ማለት ይቻላል። አስቀድመን ግን በአምላክ መንግሥት ላይ እምነት ስላሳደሩ አንድ ባልና ሚስት እንመልከት። አርቱር እና አሪና ይባላሉ። ከትንንሽ ልጆቻቸው ጋር በመሆን በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ክልል በአንድ ግዛት ውስጥ ይኖሩ ነበር። የእርስ በርስ ጦርነት ሲፈነዳ አርቱር አንዱን ወገን ደግፎ ተዋግቶ ነበር። ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ‘የራሴ ጎረቤቶች ከሆኑት ከእነዚህ ሰዎች ጋር የምዋጋው ለምንድን ነው?’ ብሎ ራሱን ጠየቀ። ከአገሩ በመውጣት ከብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በኋላ ከሚስቱና ከትንንሽ ልጆቹ ጋር ኢስቶኒያ ደረሰ።
አርቱር ለጉብኝት ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሄዶ ሳለ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ፤ ስለ አምላክ መንግሥት የነገሩት ነገር አስገረመው። የይሖዋ ፈቃድ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በሰው ዘር ላይ የምትገዛ ብቸኛ መንግሥት እንድትሆን ነው። (ዳንኤል 2:44) ከዚያ በኋላ ምድር የእርስ በርስ ጦርነት ወይም ዓለም አቀፍ ግጭቶች የሌሉባት ሰላማዊ መኖሪያ ትሆናለች። ኢሳይያስ ያን ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ በማለት ተንብዮአል፦ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”—ኢሳይያስ 11:9
የይሖዋ ምሥክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ከሚያገለግሉ መጽሐፎች ውስጥ በአንዱ ላይ ያለውን የወደፊቱን ሰላማዊ ምድር የሚያሳይ ሥዕል ለአርቱር ሲያሳየው አርቱር ያንን በሚመስል ቦታ ይኖር እንደነበረና አሁን ግን ያ ቦታ በእርስ በርስ ጦርነት እንዳልነበር እንደሆነ ነገረው። አርቱር ወደ ኢስቶኒያ ሲመለስ እርሱና ቤተሰቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ባደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ስለ አምላክ መንግሥት የበለጠ አወቁ።
ሁከትና ብጥብጥ እያለም እንኳ የሚገኝ ሰላም
መዝሙር 37:37 (አዓት) “ነቀፋ የሌለበትን ሰው ተመልከት፤ በቅንነት የሚመላለሰውንም ሰው በደንብ እይ፤ እንዲህ ያለው ሰው ወደፊት ሰላም ያገኛል” ይላል። እንዲያውም በአምላክ ዓይን ነቀፋ የሌለበትና ቅን የሆነ ሰው ሰላም የሚያገኘው ወደፊት ብቻ አይደለም። አሁንም ሰላም አለው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ፖል የተባለውን ሰው ተሞክሮ ተመልከት።
ፖል ከጎረቤት አገር ተሰዶ በደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ራቅ ብሎ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ይኖራል። ትውልድ አገሩ ሳለ በአንድ የነዳጅ ኩባንያ ውስጥ የሚሠራ አንድ የይሖዋ ምሥክር አግኝቶት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዳውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ ሰጠው።a ፖል ያን የይሖዋ ምሥክር እንደገና ባያገኘውም መጽሐፉን ጠለቅ ብሎ ማጥናት ጀመረ። የእርስ በርስ ጦርነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደሚገኘው የስደተኞች ካምፕ እንዲገባ አደረገው፤ እዚያም ያወቀውን ነገር ለሌሎች መናገር ጀመረ። ጥቂት ሰዎች የሚናገረው ነገር እውነት መሆኑን አመኑ። እነዚህ ሰዎች ብዙም ሳይቆይ ያወቁትን በመጠቀም በካምፑ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መስበክ ጀመሩ።
ፖል ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ በመላክ እርዳታ ጠየቀ። ከአዲስ አበባ የተላከው አገልጋይ ስለ አምላክ መንግሥት ይበልጥ ለማወቅ ዝግጁ የሆኑ 35 ሰዎች እርሱን ሲጠባበቁ በማግኘቱ በጣም ተገርሞ ነበር። እነዚህን ሰዎች በቋሚነት ለመርዳት የሚያስችል ዝግጅት ተደረገ።
እንደ ፖል የመሳሰሉ ሰዎች ሰላም አግኝተዋል ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው? ኑሯቸው አስቸጋሪ ቢሆንም በአምላክ ላይ እምነት አላቸው። በዚህ ዓለም ብጥብጥና ሁከት ሲነኩ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይሠሩበታል። በምላሹም በዛሬው ጊዜ እምብዛም የሌለውን እርካታ ያገኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” በማለት ለፊልጵስዩስ ጉባኤ የተናገረው ነገር ለእነርሱም ይሠራል። በእርግጥም ‘የሰላም አምላክ’ ከሆነው ከይሖዋ ጋር እንደተቀራረቡ ይሰማቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 9
በአሁኑ ጊዜ ያለው ሰላም
በመግዛት ላይ ያለው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ “የሰላሙ መስፍን” በማለት ይጠራዋል። (ኢሳይያስ 9:6 አዓት) አንድ የጥንት ነቢይ ስለ እርሱ ሲናገር “ለአሕዛብም ሰላምን ይናገራል፤ ግዛቱም ከባሕር እስከ ባሕር፣ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሆናል” ብሏል። (ዘካርያስ 9:10) እንደዚህ ያሉ በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ቃላት ሆሴ በተባለ ሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትለዋል።
በአንድ ወቅት እስር ቤት ውስጥ ነበር። ሽብር ፈጣሪ የነበረ ሲሆን አንድ የፖሊስ ካምፕ በቦንብ ለማውደም በዝግጅት ላይ ሳለ ተያዘ። መንግሥት ያሉትን ሁኔታዎች እንዲያስተካክል ለማስገደድ ብቸኛው መፍትሄ ዓመፅ እንደሆነ ይሰማው ነበር። እስር ቤት እያለ የይሖዋ ምሥክሮች ሚስቱን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኗት ጀመር።
ሆሴ ከተፈታ በኋላ እርሱም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረ ሲሆን “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ የሚናገረውን እሰማለሁ፤ ለሕዝቡና በታማኝነት ከእርሱ ጎን ለሚቆሙት ሰላምን ይናገራል” የሚሉት የመዝሙር 85:8 (አዓት) ቃላት በእርሱ ላይ ይፈጸሙ ጀመር። ቢሆንም ይህ ጥቅስ “በራሳቸው ችሎታ ወደ መመካት ዞር ማለት የለባቸውም” በሚል ማስጠንቀቂያ ይደመድማል። ስለዚህ ይሖዋ የሚሰጠውን ሰላም የሚሻ ሰው በራሱ አይመካም ወይም ከይሖዋ ፈቃድ ጋር አይጻረርም።
በአሁኑ ጊዜ ሆሴና ባለቤቱ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው። ሆሴ ቤት ውስጥ በተሠሩ ቦምቦች መፍትሄ ያገኛሉ ብሎ ያስባቸው የነበሩትን ችግሮች የሚያስወግደው የአምላክ መንግሥት መሆኑን ለሰዎች በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ። ሆሴና ባለቤቱ “እግዚአብሔር በጎ ነገርን ይሰጣል” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማመን ፈቃደኞች ሆነዋል። (መዝሙር 85:12) ሆሴ ሊያጠፋው አስቦት ወደነበረው ካምፕ በቅርቡ ሄዶ ነበር። የሄደው ለምን ነበር? እዚያ ለሚኖሩት ቤተሰቦች ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር ነው።
ሰላማዊ ሰዎች
መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 37:10, 11 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው!
ቢሆንም የይሖዋን ሰላም የሚያገኙት “ገሮች” ብቻ እንደሆኑ ልብ በል። ሰላምን የሚፈልጉ ሰዎች ሰላማዊነትን መማር አለባቸው። ይህም የኒው ዚላንድ ነዋሪ በሆነው ኬዝ ላይ ታይቷል። ኬዝ “ፈርጣማ ጡንቻና አቋም ያለው፣ ጠበኛ፣ ተጨቃጫቂ” እንደሆነ ይነገርለት ነበር። የአንድ የወንበዴዎች ቡድን አባል የነበረ ሲሆን በግንብ በታጠረ ቤት ውስጥ ይኖራል፤ ማንም ሰው ሰርጎ እንዳይገባ ለመከላከል ግቢው በሦስት ውሾች ይጠበቅ ነበር። ስድስት ልጆች የወለደችለት ሚስቱ ፈትታው ነበር።
ኬዝ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተገናኘ ጊዜ ምሥራቹ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያደርግ አስችሎታል። ብዙም ሳይቆዩ እርሱና ልጆቹ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። እስከ ወገቡ የሚደርሰውን ፀጉሩን ከመቆረጡም በላይ ለቀድሞ ጓደኞቹ ስለ አምላክ መንግሥት ይነግራቸው ጀመር። ከእነርሱም አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል።
ኬዝ በመላው ዓለም እንደሚኖሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ልበ ቅን ሰዎች “ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፣ . . . ከክፉ ፈቀቅ ይበል፣ መልካምንም ያድርግ፣ ሰላምን ይሻ ይከተለውም” የሚሉትን የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት በተግባር ማዋል ጀምሯል። (1 ጴጥሮስ 3:10, 11) የቀድሞ ሚስቱ እንደገና ልታገባው የተስማማች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ‘ሰላምን መሻትና መከተል’ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እየተማረ ነው።
የይሖዋ ሰላም በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ውስጥ የተወለደውን አትሌት ጨምሮ ለብዙ ሰዎች ሕይወት አድን ሆኖላቸዋል። ይህ ሰው በኦሎምፒክ ውድድር ሜዳሊያዎች ያገኘ ቢሆንም ያሰበው ሁሉ ስላልተሳካለት ወደ አደንዛዥ ዕፅና አልኮል ዞረ። ከ19 ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ የሕይወትን ትክክለኛ ዓላማ ለማግኘት እንዲረዳው ወደ አምላክ ጸለየ። በእነዚህ ዓመታት አድካሚ ሥራ በሚሠራበት ሳይቤሪያ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ሦስት ዓመት በእስር አሳልፏል፣ በድብቅ መርከብ ተሳፍሮ ወደ ካናዳ ተጉዟል እንዲሁም በአደንዛዥ ዕፅ አመሉ የተነሳ ሁለት ጊዜ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር። ሩሲያንኛ ከሚናገሩ ምሥክሮች ጋር ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት ረዳው። በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰው እንደሌሎቹ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከአምላክ ጋር ሰላም ከማግኘቱ በላይ ለራሱም ሰላም አለው።
የትንሣኤ ተስፋ
አሁን ደግሞ ሳራዬቮ ውስጥ ወደሚገኙት ቦዞ እና ሄን ዶርም እንመለስ። እነዚህ ባልና ሚስት ማግዳላና የተባለች የአራት ዓመት ልጅ አለቻቸው። ባለፈው ሐምሌ ለአገልግሎት ከቤት ወጥተው ሳለ የመድፍ ጥይት ፈንድቶ ሦስቱም ሞቱ። ለሌሎች እየሰበኩት ስለነበረው ሰላም ምን ለማለት ይቻላል? ሕይወታቸውን የቀጠፈው የመድፍ ጥይት ይህ ሰላም የሕልም እንጀራ እንደሆነ ያሳያልን?
በፍጹም አያሳይም! በዚህ ሥርዓት ውስጥ አሳዛኝ ሁኔታዎች ይከሰታሉ። ሰዎች በቦንብ ወይም በመድፍ ጥይት ይሞታሉ። ሌሎች በበሽታ ወይም በአደጋ ይሞታሉ። ብዙዎች አርጅተው ይሞታሉ። አምላክ የሚሰጠውን ሰላም ያገኙ ሰዎች እነዚህ ነገሮች አይደርሱባቸውም ማለት ባይሆንም እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ተስፋ ቢስ አይሆኑም።
ኢየሱስ ወዳጁ ለነበረችው ማርታ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” በማለት ተስፋ ሰጥቷታል። (ዮሐንስ 11:25) እንደሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ የዶርም ቤተሰብም በዚህ ያምናል። ስለዚህ የዶርም ቤተሰብ አባላት ቢሞቱ ከሞት ተነስተው እውነተኛ ሰላም በሰፈነበት ምድር ላይ እንደሚኖሩ እምነት ነበራቸው። ይሖዋ አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኃዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአል።”—ራእይ 21:4
ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ተከታዮቹን “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ . . . ልባችሁ አይታወክ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:27) አስቀድሞ ይህ ዓይነቱ ሰላም በነበራቸውና ከሞት ከተነሱ በኋላ ይህንን ሰላም ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ በሚያገኙት የዶርም ቤተሰብ ሁኔታ እንደሰታለን። የሰላም አምላክ የሆነውን ይሖዋን በሚያመልኩ ሁሉ እንደሰታለን። እነዚህ ሰዎች የአእምሮ ሰላም አላቸው። ከአምላክ ጋር ሰላም አላቸው። ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ሰላምን ይኮተኩታሉ። ወደፊት ሰላም የሰፈነበት ጊዜ እንደሚመጣ እምነት አላቸው። አዎን፣ ምንም እንኳ ምስቅልቅሉ በወጣ ዓለም ውስጥ ቢኖሩም ሰላም አግኝተዋል። በእርግጥም አምላክን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩ ሁሉ ሰላም አላቸው። አንተም እንዲህ ያለው ሰላም ይኑርህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሁከትና ብጥብጥ በበዛበት ዓለም ውስጥ ቢኖሩም እንኳ ሰላም አግኝተዋል