የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • መረቡና ዓሦቹ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?
    መጠበቂያ ግንብ—1992 | ሰኔ 15
    • መረቡና ዓሦቹ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?

      “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።”—ማቴዎስ 13:11

      1, 2. የኢየሱስን ምሳሌዎች ትርጉም ለማወቅ ፍላጎት የሚያድርብን ለምን ሊሆን ይችላል?

      አንድ ምሥጢራዊ የሆነ ነገር ማወቅ ወይም እንደ እንቆቅልሽ ያለ አስቸጋሪ ነገር መፍታት ያስደስታችኋልን? ምሥጢሩን ወይም እንቆቅልሹን ለመፍታት መቻላችሁ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚኖራችሁን ቦታ በይበልጥ ግልጽ የሚያደርግላችሁ ከሆነስ? ኢየሱስ በተናገረው አንድ አጭር ምሳሌ አማካኝነት ይህን የመሰለ ማስተዋል የማግኘት ትልቅ መብት ሊኖራችሁ ይችላል። የሰሙትን ሁሉ ግራ ያጋባና ከዚያም ጊዜ ወዲህ ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን ሰዎች ያደናገረ ምሳሌ ነው። እናንተ ግን ልትረዱት ትችላላችሁ።

      2 ኢየሱስ በምሳሌዎች ስለሚጠቀምበት ምክንያት በማቴዎስ 13 ላይ የተናገረውን ልብ በሉ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” ብለው ጠየቁት። (ማቴዎስ 13:10) አዎ፣ ኢየሱስ አብዛኞቹ ሰዎች ሊረዱ በማይችሉአቸው ምሳሌዎች ይጠቀም የነበረው ለምንድን ነው? በቁጥር 11 እስከ 13 ላይ መልሱን ሰጥቶአል፦ “ለእናንተ የመንግስተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፣ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። . . . ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ።”

      3. የኢየሱስን ምሳሌዎች መረዳታችን ጥቅም ሊያመጣልን የሚችለው እንዴት ነው?

      3 ከዚያም በኋላ መንፈሣዊ ድንቁርናና ዕውርነት ስለያዘው ሕዝብ የሚናገረው የኢሳይያስ 6:9, 10 ትንቢት በእነርሱ ላይ ተፈጻሚነት እንዳገኘ ጠቀሰላቸው። እኛ ግን እንደነዚህ ሰዎች መሆን አያስፈልገንም። የኢየሱስን ምሳሌ ብንረዳና በተረዳነውም ብንመላለስ አሁንም ሆነ ወደፊት ለዘላለም ደስተኞች ለመሆን እንችላለን። ኢየሱስ ይህንን የሞቀ ማረጋገጫ ሰጥቶናል፦ “የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ [ደስተኞች (አዓት)] ናችሁ።” (ማቴዎስ 13:16) ይህ ማረጋገጫ ሁሉንም የኢየሱስ ምሳሌዎች የሚያካትት ነው። ለአሁኑ ግን በማቴዎስ 13:47-50 ላይ የተመዘገበውን ስለ ዓሣ ማጥመጃ መረብ በተነገረ በአንድ አጭር ምሳሌ ላይ እናተኩር።

      ጥልቅ ትርጉም ያለው ምሳሌ

      4. በማቴዎስ 13:47-50 ላይ እንደተመዘገበው ኢየሱስ በምሳሌ አማካኝነት የገለጸው ነገር ምንድን ነው?

      4 “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፣ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉዎችን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፣ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”

      5. የመረቡን ምሳሌ ትርጉም በሚመለከት ምን ዓይነት ጥያቄዎች ይነሳሉ?

      5 ሰዎች በመረብ ዓሣ ሲያጠምዱ ቢያንስ በፊልም ወይም በቴሌቪዥን ሳታዩ አትቀሩም። ስለዚህ የኢየሱስን ምሳሌ በዓይነ ሕሊና ለመመልከት አስቸጋሪ አይሆንም። ይሁን እንጂ ነገሩን በዓይነ ሕሊና ማየቱ ቀላል ቢሆንም ዝርዝር ሁኔታውና ትርጉሙስ? ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ የመረቡ ምሳሌ ስለ “መንግሥተ ሰማያት” የሚናገር እንደሆነ ተናግሮአል። ቢሆንም “ሁሉም ዓይነት” ሰው ይኸውም መልካሙም ሆነ ክፉው ወደ መንግሥቱ ይሰበሰባል ማለቱ እንዳልነበረ የታወቀ ነው። ዓሦቹን የሚያጠምዱትስ እነማን ናቸው? ይህ ዓሣ የማጥመድና የተጠመዱትን ዓሦች የመለየት ሥራ የተፈጸመው በኢየሱስ ዘመን ነው ወይስ “በነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ” በሆነው በዚህ በዘመናችን አካባቢ ሊሆን ይችላል? አንተስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ቦታ ሊኖርህ እንደሚችል ይሰማሃልን? በመጨረሻ ከሚያለቅሱትና ጥርሳቸውን ከሚያፋጩት መካከል ከመሆን ለመዳን የምትችለው እንዴት ነው?

      6. (ሀ) የመረቡን ምሳሌ ለመረዳት መጓጓት የሚኖርብን ለምንድን ነው? (ለ) የምሳሌውን ትርጉም ለመረዳት የሚያስችለን ቁልፍ ምንድን ነው?

      6 እንደነዚህ የመሳሰሉት ጥያቄዎች ምሳሌው ቀላል እንዳልሆነ ያሳያሉ። ይሁን እንጂ “ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ [ደስተኞች (አዓት)] ናችሁ” የሚለውን አትዘንጉ። ጆሮቻችን ደንቆሮዎች ዓይኖቻችንም የተሸፈኑ እንዳልሆኑና የምሳሌውን ትርጉም ጠልቀን ለመመርመር እንችል እንደሆነ እንመልከት። በእርግጥ የምሳሌውን ትርጉም የምንፈታበት አስፈላጊ ቁልፍ አለን። ኢየሱስ የገሊላን ዓሣ አጥማጆች ሥራቸውን ትተው “ሰዎችን አጥማጆች” የመሆን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠሩ እንዴት እንደጋበዛቸው ባለፈው ትምህርታችን ላይ ተመልክተናል። (ማርቆስ 1:17) ኢየሱስ “ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምዱ ትሆናላችሁ” ብሏቸው ነበር።—ሉቃስ 5:10

      7. ኢየሱስ ዓሦችን የምን ምሳሌ አድርጎ ተናግሮአል?

      7 በዚህ መሠረት የተጠቀሱት ዓሦች ሰዎችን ያመለክታሉ። ስለዚህ ቁጥር 49 ክፉዎችን ከጻድቃን ስለመለየት ሲናገር ጻድቃን ወይም ክፉዎች ስለሆኑ የባሕር ፍጥረታት መናገሩ ሳይሆን ጻድቃን ወይም ክፉ ስለሆኑ ሰዎች መናገሩ ነበር። በተመሳሳይም ማቴ 13 ቁጥር 50ም የባሕር እንስሳት እንደሚያለቅሱ ወይም ጥርሳቸውን እንደሚያፋጩ ያመለክታል ብለን እንድናስብ አያደርገንም። ይህ ምሳሌ የሚናገረው ስለ ሰዎች መሰባሰብና ከተሰባሰቡም በኋላ ስለመለየታቸው ነው። የመለየቱም ሥራ ከውጤቱ መገንዘብ እንደሚቻለው በጣም ከባድ ነገር ነው።

      8. (ሀ) ተስማሚ ባልሆኑ ዓሦች ላይ ከደረሰው ነገር ምን ልንማር እንችላለን? (ለ) ጥሩ ስላልሆኑት ዓሦች ከተነገረው ምሳሌ መንግሥቱን በተመለከተ ምን ብለን መደምደም እንችላለን?

      8 ተስማሚ ያልሆኑት ዓሦች ማለትም ክፉዎች ወደሚያለቅሱበትና ጥርሳቸውን ወደሚያፋጩበት የእቶን እሳት እንደሚጣሉ አስተውሉ። ኢየሱስ በሌሎች ሥፍራዎች ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ከመንግሥቱ ውጭ ከመሆን ጋር የሚዛመድ ነገር እንደሆነ አመልክቶአል። (ማቴዎስ 8:12፤ 13:41, 42) በማቴዎስ 5:22 እና 18:9 ላይ ዘላለማዊ ጥፋትን ለማመልከት “ገሃነመ እሳትን” ጠቅሶአል። ታዲያ ይህ ሁሉ የዚህን ምሳሌ ትርጉም መረዳትና ከምሳሌው ጋር የሚስማማ ድርጊት መፈጸም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያመለክት አይደለምን? በአምላክ መንግሥት ውስጥ ክፉዎች እንደሌሉና ወደ ፊትም እንደማይኖሩ ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ ኢየሱስ በቁጥር 47 ላይ “መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች . . . መረብ ትመስላለች” ሲል የአምላክን መንግሥት በተመለከተ የተለያዩ የዓሣ ዓይነቶችን እንዲሰበስብ ከተጣለ መረብ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ይኖራል ማለቱ ነበር።

      9. በመረቡ ምሳሌ ውስጥ ለመላእክት ምን ዓይነት ቦታ ተሰጥቶአል?

      9 መረቡ ከተጣለና ዓሦቹ ከተሰበሰቡ በኋላ የመለየት ሥራ ይካሄዳል። ኢየሱስ በዚህ ሥራ የሚካፈሉት እነማን እንደሆኑ ተናግሮአል። ማቴዎስ 13:49 ዓሣ የሚያጠምዱትና የሚለዩት መላእክት እንደሆኑ ይገልጻል። ስለዚህ ኢየሱስ በምድር ላይ ለመንግሥተ ሰማያት የሚበቁ መልካም ሰዎችንና ለመንግሥታዊው ጥሪ ተስማሚ ያልሆኑ ሰዎችን በመለየት ሥራ ላይ የሚውለውን መሣሪያ በበላይነት ስለሚቆጣጠሩ መላእክት መናገሩ ነበር።

      የማጥመዱ ሥራ የሚከናወነው መቼ ነው?

      10. ዓሣ የማጥመዱ ሥራ ረዥም ዘመን የሚፈጅ መሆኑን የሚያመለክቱት የትኞቹ ምክንያቶች ናቸው?

      10 በምሳሌው ዙሪያ ያለው ሐሳብ ይህ መቼ እንደሚከናወን ለማወቅ ይረዳናል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከመናገሩ በፊት መልካም ዘር ስለ መዝራቱ፣ በኋላ ግን እርሻው ላይ እንክርዳድ ስለ መዘራቱና እርሻውም የዚህ ዓለም ምሳሌ ስለ መሆኑ የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። በማቴዎስ 13:38 ላይ መልካሙ ዘር “የመንግሥቱን ልጆች እንክርዳዱም የክፉውን ልጆች” እንደሚያመለክት ገልጾአል። እነዚህም እስከ ነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ መከር ድረስ ለብዙ መቶ ዘመናት ጎን ለጎን አድገዋል። ከዚያ በኋላ ግን እንክርዳዱ ተለይቶ ተቃጠለ። ይህንን ከመረቡ ምሳሌ ጋር ስናነጻጽር ፍጥረታቱ ወደ መረቡ የሚሰበሰቡበት ጊዜ ረዥም ዘመን የሚወስድ ነው።—ማቴዎስ 13:36-43

      11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓለም አቀፍ ዓሣ የማጥመድ ሥራ የተጀመረው እንዴት ነው?

      11 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ መሠረት መረቡ ዓሦቹን የሚሰበስበው አለምንም ምርጫ ማለትም ጥሩዎቹንም መጥፎዎቹንም በአንድ ላይ ነው። ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ዓሣ የማጥመዱን ሥራ ይመሩ የነበሩት መላእክት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚሆኑትን “ዓሦች” ለመሰብሰብ የተጠቀሙት በአምላክ ክርስቲያናዊ ድርጅት ነበር። በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ በዓል በፊት የኢየሱስ መረብ 120 ደቀ መዛሙርትን ይዞ ነበር ለማለት ይቻላል። (ሥራ 1:15) የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ግን በመረቡ አማካኝነት የሚከናወነው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ተጀምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ዓሦች ተይዘዋል። ከ36 እዘአ በኋላ ዓሣ የማጥመዱ ሥራ ወደ ዓለም አቀፍ ባሕሮች ተዛመተ። አሕዛብ የሆኑ ሰዎች ወደ ክርስትና እየተሳቡ የክርስቶስ ቅቡዓን ጉባኤ አባሎች ሆኑ።—ሥራ 10:1, 2, 23-48

      12. ከሐዋርያት ሞት በኋላ ምን ነገር በሰፊው ተስፋፋ?

      12 ሐዋርያት ከምድር ገጽ በጠፉባቸው ተከታታይ መቶ ዘመናት መለኮታዊውን እውነት ለማግኘት ያገኙትንም ይዘው ለመቆየት የታገሉ ታማኝ ክርስቲያኖች መኖራቸው አልቀረም። እጅግ ቢያንስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የአምላክን ሞገስ አግኝተው ነበር። እነርሱም በመንፈሱ ቀብቶአቸዋል። ቢሆንም ሐዋርያት ሞተው ባለቁ ጊዜ እነርሱ ገትተውት የነበረው ክህደት በሰፊው አደገ። (2 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ሳይገባው የአምላክ ጉባኤ ነኝ የሚል ድርጅት ተቋቋመ። ይህ ድርጅት ከኢየሱስ ጋር እንድገዛ በአምላክ መንፈስ የተቀባሁ ቅዱስ ሕዝብ ነኝ በማለት በሐሰት የሚናገር ሆነ።

      13. ሕዝበ ክርስትና በመረቡ ሥራ ውስጥ ተሳትፎ ነበራት ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

      13 በሐሰት ክርስቲያን ነን ባዮች በመረቡ ምሳሌ ውስጥ ቦታ ያላቸው ይመስላችኋልን? አዎ፣ አላቸው ብለን የምንመልስበት በቂ ምክንያት አለን። ምሳሌያዊው መረብ ሕዝበ ክርስትናን ይጨምራል። እውነት ነው፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ተራ ሰዎች እንዳይደርስ ለማገድ ሞክራለች። ቢሆንም የሕዝበ ክርስትና አባላት የሆኑ ሰዎች ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ የአምላክን ቃል በመተርጎም፣ በመገልበጥና በማሠራጨት ረገድ ከፍተኛ የሥራ ድርሻ አበርክተዋል። በኋለኞቹ ዘመናትም ሕዝበ ክርስትና መጽሐፍ ቅዱስን በተለያዩ የሩቅ ሐገሮች ቋንቋዎች የተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራትን አቋቁማለች ወይም ደግፋለች። በተጨማሪም አብያተ ክርስቲያናት የዳቦ ክርስቲያኖችን ለማፍራት ሐኪምና አስተማሪዎች ሆነው የሚሠሩ ሚስዮናውያንን ወደ ተለያዩ አገሮች ልካለች። እነርሱም የአምላክ ሞገስ የሌላቸውን ብዙ መጥፎ ዓሦች ቢሰበስቡና የተበላሸውን ክርስትና ቢያስፋፉም ሌላው ቢቀር ክርስቲያን ያልነበሩትን ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አስተዋውቀዋል።

      14. የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት መልካም ዓሦችን የማጥመዱን ሥራ በአንዳንድ መንገዶች የደገፉት እንዴት ነበር?

      14 በዚህ ጊዜ ሁሉ የተበተኑት ታማኞች በተቻላቸው መጠን ከአምላክ ቃል ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በኖሩበት ዘመን ሁሉ በምድር ላይ የሚገኘው የአምላክ እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ክፍል ሆነዋል። እነርሱም በአብዛኛው አምላክ ጥሩ እንደሆኑ የሚቆጥራቸውንና በመንፈሱ የሚቀባቸውን ዓሦች ወይም ሰዎች ሲሰበስቡ እንደቆዩ እርግጠኛ ልንሆን እንችላለን። (ሮሜ 8:14-17) እነዚህ ክርስቲያን ነን ይሉ የነበሩት መልካም ሰዎች የዳቦ ክርስቲያኖች ሊሆኑ ወይም የሕዝበ ክርስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ወደ ቋንቋቸው ከተረጎሙት ቅዱሳን ጽሑፎች መጠነኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ላገኙ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማዳረስ ችለዋል። እውነት ነው በሕዝበ ክርስትና ይሰበሰቡ የነበሩት ሰዎች በአብዛኛው በአምላክ አመለካከት መጥፎዎች ቢሆኑም መልካሞቹም ዓሦች መሰብሰባቸው አላቆመም ነበር።

      15. በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሰው መረብ በቀጥታ የሚያመለክተው ምንን ነው?

      15 ስለዚህ መረቡ የአምላክ ጉባኤ ነኝ የሚለውንና ዓሦችን የሚሰበስበውን ምድራዊ መሣሪያ ያመለክታል። ይህ መረብ ሁለቱንም ማለትም ሕዝበ ክርስትናንም ሆነ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን ጉባኤ ያጠቃልላል። የእውነተኛዎቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በማቴዎስ 13:49 ላይ በተጠቀሱት መላእክት እየተመራ መልካም ዓሦችን መሰብሰቡን ቀጥሎአል።

      የምንኖርበት ዘመን ልዩ የሆነ ዘመን ነው

      16, 17. ኢየሱስ በተናገረው የመረቡ ምሳሌ አፈጻጸም ውስጥ ዘመናችን በጣም ልዩ ቦታ የሚሰጠው ለምንድን ነው?

      16 አሁን ምሳሌው ስለ ተፈጸመበት የጊዜ ሁኔታ እንመልከት። መረቡ ለብዙ መቶ ዘመናት ጥሩዎቹንም ሆነ መጥፎዎቹን ወይም ክፉዎቹን ዓሦች ሲሰበስብ ቆይቶአል። በኋላ ግን መላእክት ወሳኝ የሆነውን የመለያየት ሥራ የሚፈጽሙበት ጊዜ ደረሰ። ይህ የተከናወነው መቼ ነው? ይህ የሆነው “በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ላይ እንደሆነ ማቴ 13 ቁጥር 49 በግልጽ ያመለክታል። ይህም ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች ከተናገረው ምሳሌ ጋር ይመሳሰላል፦ “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል።”—ማቴዎስ 25:31, 32

      17 ስለዚህ ከማቴዎስ 13:47-50 ጋር በሚስማማ መንገድ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከጀመረበት ከ1914 አንስቶ የሰዎችን የወደፊት ዕጣ የሚወስን የመለየት ሥራ በመላእክት መሪነት ሲከናወን ቆይቶአል። ይህ ሥራ በተለይ ግልጽ ሆኖ መታየት የጀመረው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎች ከጊዜያዊ እሥራት ወይም ግዞት ወጥተው ዓሣ የማጥመዱን ሥራ የሚያከናውኑ ጥሩ መሣሪያዎች መሆን ከጀመሩበት ከ1919 ወዲህ ነው።

      18. መልካሞቹ ዓሦች ተሰብስበው በዕቃዎቹ ውስጥ የተጨመሩት እንዴት ነው?

      18 ከመጥፎዎቹ የተለዩት ጥሩ ዓሦች ምን ይሆናሉ? ማቴ 13 ቁጥር 48 እንደሚነግረን ዓሣ አጥማጆቹና የመለያየት ሥራ የሚያከናውኑት መላእክት “መልካሙን [ዓሦች] ለቅመው በዕቃዎቹ ውስጥ አከማቹ፣ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት።” ዕቃዎቹ ጥሩ ጥሩ ዓሦች ተጠብቀው የሚቆዩባቸው መያዣዎች ናቸው። ታዲያ እንዲህ ያለ ነገር በዘመናችን ተፈጽሞአልን? በእርግጥ ተፈጽሞአል። ምሳሌያዊዎቹ ዓሦች እንደተጠመዱ ወደ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጉባኤዎች ተሰብስበዋል። እነዚህ ዕቃ መሰል ጉባኤዎች ምሳሌያዊዎቹን ዓሦች የመጠበቅና ለመለኮታዊው አገልግሎት የማዘጋጀት አገልግሎት ሰጥተዋል። በዚህ አትስማማምን? አሁንም አንድ ሰው ‘ይህ ሁሉ ጥሩ ነው፣ ነገር ግን ከአሁኑና ከወደፊት ሕይወቴ ጋር ምን ግንኙነት አለው?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል።

      19, 20. (ሀ) የዚህን ምሳሌ ትርጉም ማወቃችን በአሁኑ ጊዜ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ከ1919 ጀምሮ ምን አስፈላጊ የሆነ ዓሣ የማጥመድ ሥራ ሲከናወን ቆይቶአል?

      19 እዚህ ላይ የቀረበው የምሳሌው አፈጻጸም ከሐዋርያት ዘመን አንስቶ እስከ 1914 ባለው ዘመን ብቻ የተወሰነ አይደለም። በዚያ ዘመን ውስጥ የመረቡ መሣሪያ ሁለቱንም ሐሰተኛና እውነተኛ ክርስቲያን ነን ባዮች ሲሰበስብ ቆይቶአል። አዎ፣ ሁለቱንም መጥፎ ዓሦችንና መልካም ዓሦችን ሲሰበስብ ነበር። ከዚህም በላይ በመላእክቱ ይከናወን የነበረው የመለያየቱ ሥራም በ1919 አካባቢ አላበቃም። የዚህ የመረቡ ምሳሌ አፈጻጸም በአንዳንድ ሁኔታዎች እስከ ጊዜአችን ድረስ ደርሶአል። እኛንም ሆነ የወደፊት ሕይወታችንን የሚነካ ምሳሌ ነው። “የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ [ደስተኞች (አዓት)] ናችሁ” የሚለው አነጋገር የሚፈጸምልን ሰዎች ለመሆን ከፈለግን ይህ የሆነበትን ምክንያትና መንገድ መረዳት ይኖርብናል።—ማቴዎስ 13:16

      20 ከ1919 በኋላ ቀሪዎች በምሳሌያዊው መረብ እየተጠቀሙ ዓሦችን ከባሕር ያወጡ እንደነበረና ጥሩዎችን ዓሦች ከመጥፎዎቹ ይለዩ ከነበሩት መላእክት ጋር በመተባበር የስብከቱን ሥራ በትጋት ማከናወን እንደ ጀመሩ ሳታውቅ አትቀርም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻዎቹ የ144,000 ክፍሎች በምሳሌው መረብ ተይዘው እስኪያልቁ ድረስ ጥሩዎቹ ዓሦች በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ እንደቆዩ በጊዜው የነበረው እስታትስቲካዊ መረጃ ያረጋግጣል። (ራእይ 7:1-4) በ1930ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ግን በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡትን ጥሩ ዓሦች የመሰብሰቡ ሥራ በመሠረቱ አቆመ። ታዲያ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ መረቡን ጥሎ እጁን አጣምሮ በመቀመጥ ሰማያዊ ውርሻውን ተጠባበቀን? በፍጹም እንዲህ አላደረገም!

      ዓሣ በማጥመዱ ሥራ የሚኖርህ ተሳትፎ

      21. በጊዜያችን ምን ሌላ ዓሣ የማጥመድ ሥራ እየተከናወነ ነው? (ሉቃስ 23:43)

      21 ኢየሱስ ስለ መረቡ የተናገረው ምሳሌ በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ ቦታ ስለሚሰጣቸው ጥሩ ዓሦች ይናገራል። ይሁን እንጂ ባለፈው ጥናት ላይ እንደተብራራው ከዚህ ምሳሌ ውጪ በመከናወን ላይ ያለ ምሳሌያዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ አለ። ይኸኛው ዓሣ የማጥመድ ሥራ የሚከናወነው በገነቲቱ ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ምሳሌያዊ ዓሦች ለመሰብሰብ ነው እንጂ በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሱትን መልካም ቅቡዓን ዓሦች ለመሰብሰብ አይደለም።—ራእይ 7:9, 10፤ ከማቴዎስ 25:31-46 ጋር አወዳድር።

      22. ምን የሚያስደስት ውጤት ልናገኝ እንችላለን? የዚህስ ውጤት አማራጭ ምንድን ነው?

      22 ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ያለህ ከሆንክ ይሖዋ እስከ ዘመናችን ድረስ ሕይወት አድን የሆነ ዓሣ የማጥመድ ሥራ እንዲቀጥል በመፍቀዱ ልትደሰት ትችላለህ። ይህም በጣም አስደናቂ የሆነ አጋጣሚ እንድታገኝ አስችሎሃል። አጋጣሚ የምንለው ለምንድን ነው? የመጨረሻው ውጤት ዓሣ የማጥመዱን ሥራ ለሚመራው አምላክ ታማኝ ሆነን በመኖራችን ላይ የተመካ ስለሆነ አጋጣሚ የሚለውን ቃል መጠቀማችን ተገቢ ነው። (ሶፎንያስ 2:3) በመረቡ የተያዙት ዓሦች በሙሉ ጥሩ ሽልማት እንደማያገኙ በምሳሌው ላይ የተገለጸውን ልብ በሉ። መጥፎዎቹ ወይም ክፉዎቹ ከጻድቆቹ እንደሚለዩ ኢየሱስ ተናግሮአል። መጨረሻውስ ምን ይሆናል? ኢየሱስ በማቴዎስ 13:50 ላይ መጥፎዎቹ ወይም ክፉዎቹ ዓሦች የሚደርስባቸውን አስከፊ ውጤት ገልጾአል። ወደ እቶኑ እሳት ይጣላሉ። ይህም የዘላለም ጥፋት ማለት ነው።—ራእይ 21:8

      23. በጊዜያችን የሚከናወነውን ዓሣ የማጥመድ ሥራ እጅግ አስፈላጊ ያደረገው ምንድን ነው?

      23 ለጥሩዎቹ ቅቡዓን ዓሦችም ይሁን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ምሳሌያዊ ዓሦች በጣም ግሩም የሆነ ጊዜ ይጠብቃቸዋል። ስለዚህ መላእክቱ በአሁኑ ጊዜ በዓለም በሙሉ የሚከናወነውን የተሳካለት ዓሣ የማጥመድ ሥራ በመምራትና በመቆጣጠር ላይ መሆናቸው አለ በቂ ምክንያት አይደለም። የሚያዙትም ዓሦች በጣም ብዙ ናቸው። ሐዋርያት ኢየሱስ እንዳዘዛቸው መረባቸውን በጣሉ ጊዜ በተአምራዊ ሁኔታ ብዙ ዓሦችን ከመያዛቸው ጋር የሚመሳሰል ክንውን ነው ብትሉ ስህተት አይሆንባችሁም።

      24. በመንፈሳዊው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ረገድ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

      24 አንተስ በዚህ ሕይወት አድን በሆነው መንፈሳዊ ዓሣ የማጥመድ ሥራ በተቻለህ መጠን በመካፈል ላይ ነህን? እስከ አሁን ድረስ በየግላችን የሠራነው ሥራ ምንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው ዓሣ የማጥመድና ሕይወት የማዳን ሥራ የተገኘውን ውጤት ብንመለከት እንጠቀማለን። ይህን ማድረጋችን በፊታችን ባሉት ጊዜያት በበለጠ ቅንዓት መረባችንን እንድንጥል ሊያነሳሳን ይገባል።—ከማቴዎስ 13:23፤ 1 ተሰሎንቄ 4:1 ጋር አወዳድር።

      እነዚህን ነጥቦች ታስታውሳለህን?

      ◻ ኢየሱስ በተናገረው የመረብ ምሳሌ ውስጥ የተገለጹት ሁለት ዓይነት ዓሦች ምን ያመለክታሉ?

      ◻ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በመረቡ አሠራር የተካፈሉት በምን መንገድ ነው?

      ◻ በዘመናችን በመፈጸም ላይ የሚገኘው ዓሣ የማጥመድ ሥራ በጣም ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

      ◻ የመረቡ ምሳሌ ራሳችንን ምን ብለን እንድንመረምር ሊያደርገን ይገባል?

      [በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      በገሊላ ባሕር ላይ ለብዙ መቶ ዘመናት ዓሣ የማጥመድ ሥራ ሲከናወን ቆይቶአል

      [ምንጭ]

      Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

  • በዓለም ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን ማጥመድ
    መጠበቂያ ግንብ—1992 | ሰኔ 15
    • በዓለም ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን ማጥመድ

      “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፣ ግድ ደርሶብኝ ነውና፣ ወንጌልን ባልሰብክ ግን ወዮልኝ”—1 ቆሮንቶስ 9:16

      1, 2. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 9:16 ላይ የሠፈሩትን ቃላት ፈጽመው የተገኙት እነማን ብቻ ናቸው? እንዲህ ብለህ የመለስከውስ ለምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የትኛውን ኃላፊነት ተቀብለዋል?

      በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ጳውሎስ በተናገራቸው በእነዚህ ቃላት የተገለጸውን ከባድ ሥራ ፈጽመው የተገኙት እነማን ናቸው? ‘ስለ መንፈሣዊ ፍላጎታቸው የሚያስቡ’ ወንዶችንና ሴቶችን ለማጥመድ በሚሊዮን በሚቆጠር ብዛት በዓለም ላይ የተሠማሩት እነማን ናቸው? (ማቴዎስ 5:3 (አዓት)) በማቴዎስ 24:14 ላይ ያለውን የክርስቶስ ትዕዛዝ ለመፈጸም ሲሉ በብዙ አገሮች እስራት፣ ሞትና የመሳሰሉት ሥቃዮች የደረሱባቸው እነማን ናቸው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ