-
ከእውነት የተሻለ ምንም ነገር የለምመጠበቂያ ግንብ—1998 | ጥር 1
-
-
ከእውነት የተሻለ ምንም ነገር የለም
ጂ ኤን ፋን ደር ቤል እንደተናገረው
በሰኔ 1941 ለጌስታፖዎች አሳልፈው ሰጡኝና በጀርመን በርሊን አቅራቢያ ወደሚገኘው የዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ተወሰድኩ። በዚያም 38190 የሚል የእስረኛ ቁጥር ተሰጥቶኝ አስከፊው የሞት ጉዞ እስከተደረገበት እስከ ሚያዝያ 1945 ድረስ ቆየሁ። ይህንን ከመተረኬ በፊት ግን መጀመሪያ እንዴት እስረኛ ለመሆን እንደበቃሁ ልንገራችሁ።
የተወለድኩት አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ1914 በኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከተማ ነበር። አባቴ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረው በምድር ባቡር መሥሪያ ቤት ውስጥ ሲሆን ትንሿ የመኖሪያ ሕንጻችንም የምትገኘው ከባቡር ሀዲድ አጠገብ ነበር። በ1918 ወደ ጦርነቱ ማብቂያ ገደማ የጦር ጉዳተኞችን የሚያመላልሱ በርካታ ባቡሮች በቤታችን በኩል እያስገመገሙ ሲያልፉ እመለከት ነበር። እነዚህ ባቡሮች ከጦር ግንባር ወደ ቤታቸው በሚመለሱ ቁስለኛ ወታደሮች የታጨቁ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም።
ዕድሜዬ 12 ዓመት ሲሆን ሥራ ለመያዝ ትምህርቴን አቋረጥኩ። ከስምንት ዓመታት በኋላ በሰዎች ማመላለሻ መርከብ ላይ ተሳፋሪዎችን በማስተናገድ ሥራ ተቀጥሬ ለአራት ዓመታት ያክል ከኔዘርላንድስ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እየተመላለስኩ ስሠራ ቆየሁ።
በ1939 በጋ ላይ ኒው ዮርክ ከተማ ወደብ በደረስንበት ወቅት ሌላ የዓለም ጦርነት ስጋት አጥልቶ ነበር። በመሆኑም እኛ በነበርንበት መርከብ ላይ የተሳፈረ አንድ ሰው ጽድቅ ስለሚሰፍንበት መንግሥት የሚናገር መንግሥት (የእንግሊዝኛ) የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ ሲሰጠኝ በደስታ ተቀበልሁት። የባሕር ላይ ሕይወት አስጊ እየሆነ በመምጣቱ ወደ ሮተርዳም ተመልሼ ሌላ ሥራ መፈለግ ጀመርኩ። መስከረም 1 ቀን ጀርመን ፖላንድን ስትወርር መንግሥታት ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገቡ።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር
በመጋቢት 1940 አንድ እሁድ ዕለት ጠዋት ባለ ትዳር የሆነውን ወንድሜን ልጠይቅ ቤቱ ሄጄ ሳለ አንድ የይሖዋ ምሥክር የበሩን ደወል ደወለ። ከአሁን ቀደም መንግሥት የሚለውን መጽሐፍ እንዳገኘሁ ከገለጽሁለት በኋላ ስለ ሰማይ እንዲሁም ወደዚያ የሚሄዱት እነማን እንደሆኑ ጠየቅሁት። የሰጠኝ መልስ ግልጽና ምክንያታዊ ስለነበር ‘እውነት ይህ ነው’ ብዬ ደመደምኩ። አድራሻዬን ሰጠሁትና እቤቴ መጥቶ እንዲያነጋግረኝ ጋበዝኩት።
ሦስት ጊዜ ያህል ብቻ ተገናኝተን ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንዳደረግን ከምሥክሮቹ ጋር ከቤት ወደ ቤት አብሬ መሄድ ጀመርኩ። ወደ አገልግሎት ክልሉ ስንደርስ ከየት እንደምጀምር አሳየኝና ብቻዬን መመሥከሩን ተያያዝኩት። በዚያን ጊዜ ብዙ አዲሶች አገልግሎት የሚጀምሩት በዚህ መንገድ ነበር። ጽሑፎችን ማስተዋወቅ ያለብኝ ሁልጊዜ ወደ ውስጥ ገባ ብዬ እንደሆነና መንገድ ላይ መታየት እንደሌለብኝ ተነግሮኝ ነበር። በጦርነቱ የመጀመሪያ ዓመታት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገን ነበር።
ከሦስት ሣምንታት በኋላ ማለትም ግንቦት 10, 1940 የጀርመን ሠራዊት ኔዘርላንድስን በመውረሩ የራይኩ ኮሚሽነር ዛይሲክቫርት የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት ታግዷል ሲል ግንቦት 29 አዋጅ አስነገረ። ስብሰባዎችን እናደርግ የነበረው በትናንሽ ቡድኖች ሆነን ነበር፤ ለዚያውም የስብሰባ ቦታዎቻችን እንዳይታወቁ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። በጊዜው በተለይ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉብኝት ትልቅ ማበረታቻ ሆኖልናል።
ሲጋራ በጣም አጨስ ነበር፤ አንድ ጊዜ የሚያስጠናኝን የይሖዋ ምሥክር ጋብዤው እንደማያጨስ ስረዳ “እኔ ፈጽሞ ሲጋራ መተው አልችልም!” ብዬ አሰብኩ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ብቻዬን መንገድ ላይ እየተጓዝኩ ‘የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ ከልቤ የይሖዋ ምሥክር መሆን አለብኝ’ ብዬ አሰብኩ። ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አጭሼ አላውቅም።
ከእውነት ጎን መሰለፍ
በሰኔ 1940 ማለትም ያንን የይሖዋ ምሥክር ወንድሜ ቤት ካገኘሁት ከሦስት ወር በኋላ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በማሳየት ተጠመቅሁ። ከዚያም ከጥቂት ወራት በኋላ በጥቅምት 1940 አቅኚ በመሆን ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባሁ። በወቅቱ የአቅኚነት ጃኬት በመባል የሚታወቀው ጃኬት ተሰጠኝ። የመጻሕፍትና የቡክሌቶች መያዣ የሚሆን ብዙ ኪስ ያለው ሲሆን ከኮት ሥርም ሊለበስ የሚችል ነበር።
ጀርመን አገሪቱን ከተቆጣጠረችበት ጊዜ ጀምሮ ለማለት ይቻላል የይሖዋ ምሥክሮች በዘዴ እየታደኑ ይታሰሩ ነበር። በየካቲት 1941 ጠዋት ከሌሎች ጥቂት ወንድሞች ጋር ወደ አገልግሎት ወጥቼ ነበር። እነርሱ በአንድ ወገን ያሉትን ቤቶች ሲያንኳኩ እኔ ደግሞ ዞሬ ወደ እነርሱ ለመሄድ በሌላኛው ወገን እያገለገልኩ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን እንዳዘገያቸው ለማየት ስሄድ አንድ ሰው አገኘሁና “አንተም እነዚህን ትንንሽ መጻሕፍት ይዘሃል?” ሲል ጠየቀኝ።
“አዎን” በማለት መለስኩለት። ከዚያ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞኝ ሄደ። ለአራት ሳምንታት ያህል በማረፊያ ቤት ቆየሁ። አብዛኞቹ መኮንኖች ተግባቢዎች ነበሩ። አንድ እስረኛ ወደ ጌስታፖዎች እስካልተላለፈ ድረስ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አላሠራጭም ብሎ ፈርሞ ሊለቀቅ ይችል ነበር። ሁለተኛ አላሠራጭም ብዬ እንድፈርም ሲጠይቁኝ “በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ብትሰጡኝ እንኳን ይህን ውል አልፈርምም” ስል መለስኩላቸው።
ትንሽ ጊዜ ካቆዩኝ በኋላ ለጌስታፖዎች አሳልፈው ሰጡኝ። ከዚያም ጀርመን ውስጥ ወደሚገኘው የዛክሰንሃውዘን ማጎሪያ ካምፕ ተወሰድኩ።
የዛክሰንሃውዘን ሕይወት
ሰኔ 1941 ዛክሰንሃውዘን ስደርስ በዚያ 150 የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ ጀርመናውያን ነበሩ። አዳዲሶቹ እስረኞች እዚያ እንደደረስን አይሶሌሽን ወደሚባለው የካምፑ ክፍል ተወሰድን። በዚያ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ተቀብለው ከፊታችን ለሚጠብቀን ነገር ያዘጋጁን ጀመር። ከአንድ ሳምንት በኋላ ሌሎች ምሥክሮች ከኔዘርላንድስ ወደ ካምፑ ተጨመሩ። በመጀመሪያ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ ከአንዱ ማደሪያ ሕንጻ ፊት ለፊት አንድ ቦታ ላይ እንድንቆም ይደረግ ነበር። አንዳንድ ጊዜም እስረኞች ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ በየዕለቱ እንደዚህ እንዲቆሙ ይደረግ ነበር።
ወንድሞች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው የነበረ ቢሆንም በተደራጀ መልክ መንፈሳዊ ነገሮችን የመመገብን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር። በየዕለቱ አንድ ሰው በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ሐሳብ ተዘጋጅቶ እንዲመጣ ይመደብ ነበር። ከዚያም በመሰብሰቢያው ሜዳ ላይ እያንዳንዳቸው በግለሰብ ደረጃ ወደ እርሱ እየሄዱ የተዘጋጀውን ነገር ያዳምጡ ነበር። በዚህም ሆነ በዚያ ጽሑፎች በድብቅ ወደ ካምፑ ይገቡ የነበረ ሲሆን እሁድ እሁድ አንድ ላይ እየተገናኘን እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እናጠና ነበር።
በዩናይትድ ስቴትስ በ1941 በጋ ወር በሴንት ሉዊስ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የወጣው ልጆች (የእንግሊዝኛ) የተባለው አዲስ መጽሐፍ አንድ ቅጂ ወደ ዛክሰንሃውዘን በድብቅ ገብቶ ነበር። መጽሐፉ ተገኝቶ እንዳይቃጠል ሲባል ገነጣጥለን ሁሉም ለማንበብ እንዲችል የመጽሐፉን ክፍሎች ተራ በተራ እንቀባበል ነበር።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ የካምፑ አስተዳደር ስብሰባዎችን እንደምናካሂድ ደረሰብን። ከዚያም ምሥክሮቹ በተለያዩ ማደሪያ ክፍሎች ውስጥ እንዲበታተኑ ተደረገ። ይህም ለሌሎች እስረኞች ለመመሥከር የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ከፈተልን፤ ከዚህ የተነሣ ከፖላንድና ከዩክሬይን እንዲሁም ከሌሎች ቦታዎች የመጡ ብዙ ሰዎች እውነትን ተቀበሉ።
ናዚዎች በዚያን ጊዜ ቢቤልፎርሸር ተብለው ይጠሩ የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች አቋም ለማስለወጥ ወይም ደግሞ ጨርሶ ለመደምሰስ የነበራቸው ዕቅድ ከማንም የተሰወረ አልነበረም። ከዚህ የተነሣ ከፍተኛ ጫና ይደረግብን ነበር። እምነታችንን ክደን ከፈረምን ነፃ ልንለቀቅ እንደምንችል ይነገረን ነበር። አንዳንድ ወንድሞች “ነፃ ብለቀቅ እኮ ይሖዋን ይበልጥ ላገለግለው እችላለሁ” ብለው ማሰብ ጀመሩ። ጥቂቶች ፈርመው ቢወጡም አብዛኞቹ ወንድሞቻችን የነበረባቸውን የምግብና የልብስ ችግር እንዲሁም ይደርስባቸው የነበረውን ሰብዓዊ ክብር የሚያዋርድ ነገርና ከባድ እንግልት ተቋቁመው በታማኝነት ጸንተዋል። አቋማቸውን ካላሉት መካከል አንዳንዶቹ ከዚያ በኋላ ጨርሶ ደብዛቸው ጠፍቶ ቀርቷል። ይሁን እንጂ ሌሎቹ ቆይተው በመመለስ እስካሁንም በትጋት ሲያገለግሉ ማየት ደስ የሚል ነው።
በእስረኞች ላይ ጭካኔ የሞላበት ድርጊት ሲፈጸም ቆመን እንድናይ ዘወትር ያስገድዱን ነበር። ለምሳሌ ያህል 25 ጊዜ በዱላ ይደበደቡ ነበር። አንድ ጊዜ አራት ሰዎች በስቅላት ሲገደሉ እንድናይ ተደርገናል። እንዲህ ያሉትን ነገሮች መመልከቱ ራሱ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም። እኔ በነበርኩበት ማደሪያ ውስጥ የነበረ አንድ ረጅምና መልከ መልካም ወንድም እንዲህ አለኝ:- “እዚህ ከመምጣቴ በፊት ደም ሳይ ወዲያው ራሴን ስቼ እወድቅ ነበር። አሁን ግን ለምጄዋለሁ።” እንዲህ ሲባል ግን ስሜታችን ጨርሶ ጠፍቷል ማለት አልነበረም። እውነቱን ለመናገር ያሰቃዩን የነበሩትን ሰዎች በክፉ ዓይኔ አይቻቸው ወይም ለእነርሱ ጥላቻ አድሮብኝ አያውቅም።
ለተወሰነ ጊዜ ከአንድ ኮማንዶ (የሥራ ጓድ) ጋር ከሠራሁ በኋላ ከባድ ትኩሳት ስለያዘኝ ሆስፒታል እንድተኛ ተደረገ። አንድ የኖርዌይ ተወላጅ የሆነ ሐኪምና አንድ ቼኮዝሎቫኪያዊ ነርስ በደግነት ረዱኝ፤ ምናልባትም ሕይወቴ የተረፈው በእነርሱ ደግነት ነው ማለት እችላለሁ።
የሞት ጉዞ
በሚያዝያ 1945 ጀርመን በጦርነቱ ድል እየተነሳች መምጣቷ ግልጽ ነበር። የምዕራባውያኑ ጥምር ኃይሎች ከምዕራብ የሶቪየት ሠራዊት ደግሞ ከምሥራቅ በፍጥነት እየገሰገሱ ነበር። ናዚዎች ባለቻቸው ጥቂት ቀን ውስጥ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ያሉትን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሙሉ ፈጅተው አንዳችም ምልክት ሳይተው ያንን ሁሉ ሬሳ ማስወገድ ፈጽሞ ከአቅማቸው በላይ ነበር። ስለዚህ የታመሙትን ለመግደልና የቀረውን እስረኛ በቅርብ ወደሚገኘው የባሕር ወደብ ለመውሰድ ወሰኑ። ዕቅዳቸው መርከብ ላይ ጭነው መርከቡን ማስጠም ነበር።
ሚያዝያ 20 ምሽት የ26,000ዎቹ እስረኞች ጉዞ ከዛክሰንሃውዘን ተጀመረ። ካምፑን ለቀን ከመውጣታችን በፊት የታመሙት ወንድሞቻችን ከክሊኒክ ወጡ። እነርሱ የሚጓዙበት ጋሪ ተዘጋጀ። ከስድስት የተለያዩ አገሮች በጠቅላላ 230 የይሖዋ ምሥክሮች ነበርን። ከታመሙት ወንድሞች መካከል አንዱ ሥራው በኔዘርላንድስ እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው አርቱር ቪንክለር ይገኝበት ነበር። ምሥክሮቹ እንጓዝ የነበረው ከኋላ ሆነን ነበር፤ በጉዞውም እንድንቀጥል እርስ በርሳችን እንበረታታ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ምንም እረፍት 36 ሰዓት ያህል ተጓዝን። በጣም ከመንገላታቴና ሰውነቴ ከመዛሉ የተነሣ እየሄድኩ እንቅልፍ ይወስደኝ ነበር። ወደኋላ መቅረት ወይም ለማረፍ ብሎ ትንሽ ቁጭ ማለት ግን የማይታሰብ ነገር ነበር፤ ምክንያቱን አንድ ሰው እንደዚያ ቢያደርግ ወታደሮቹ ይገድሉታል። ሌሊት ሌሊት ሜዳ ላይ ወይም ጫካ ውስጥ እናድር ነበር። ምግብ የለም፤ ቢኖርም ደግሞ በጣም ጥቂት ነው። ረሃቡ ሲጠናብኝ የስዊድን ቀይ መስቀል ሰጥቶን የነበረውን የጥርስ ሳሙና መላስ ጀመርኩ።
አንድ ቦታ ስንደርስ የጀርመን ጠባቂዎቻችን የሩሲያና የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በየት በየት በኩል እንዳለ ግራ ስለተጋቡ ጫካ ውስጥ ለአራት ቀናት ያህል ቆየን። ይህ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነበር፤ ምክንያቱም ይዛን እንድትሰጥም ወደተዘጋጀችው በሉቤክ ባሕረ ሰላጤ ወደነበረችው መርከብ በታቀደው ጊዜ ሳንደርስ ቀረን። በመጨረሻ ከ12 ቀናት በኋላና 200 የሚያክል ኪሎ ሜትር ተጉዘን ክሪቪትስ ጫካ ደረስን። ይህ ቦታ ከሽዌሪን ብዙም አይርቅም፤ ይህች ከተማ ከሉቤክ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት።
ሶቪየቶች በቀኛችን አሜሪካውያኖቹ ደግሞ በግራችን ነበሩ። ከሚያስተጋባው የከባድ መሣሪያ ድምፅና ከማያቋርጠው የጥይት ተኩስ ወደ ውጊያው ግንባር መጠጋታችንን ተረዳን። የጀርመን ወታደሮች ስለተሸበሩ አንዳንዶቹ ሸሹ ሌሎቹም እንዳይታወቁ በመፍራት ዩኒፎርማቸውን እያወለቁ ከአስከሬኖች ላይ የገፈፉትን የእስረኞች ልብስ ለበሱ። በዚህ ሁሉ ግር ግር መሐል እኛ መመሪያ ለማግኘት አንድ ላይ ተሰብስበን ጸለይን።
ኃላፊነት የነበራቸው ወንድሞች በሚቀጥለው ቀን በጠዋት ተነሥተን የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ወዳሉበት አቅጣጫ እንድንሄድ ወሰኑ። ይህን የሞት ጉዞ ከጀመሩት እስረኞች መካከል ግማሽ የሚያክሉት በመንገድ ላይ የሞቱ ወይም ደግሞ በወታደሮች የተገደሉ ቢሆንም ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንድም የሞተ አልነበረም።
አንድ የካናዳውያን የጦር ጓድ በመኪና ጭኖ እህቴ ትኖር ወደ ነበረችበት ወደ ናይሜገን ከተማ ወሰደኝ። እዚያ እንደደረስኩ ግን እህቴ ከዚያ እንደሄደች አወቅሁ። ከዚያ ወደ ሮተርዳም በእግሬ ለመሄድ ተነሣሁ። ከዚያም እንዳጋጣሚ ሆኖ በአንድ የቤት መኪና የምፈልግበት ቦታ የሚያደርሰኝ ሰው አገኘሁ።
እውነት ሕይወቴ ሆኗል
ሮተርዳም እንደደረስኩ እንደገና አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። ከሦስት ሣምንታት በኋላ ወደ ምድብ ቦታዬ ወደ ዛትፈን ሄድኩ፤ በዚያም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል አገልግያለሁ። በዚህ ጊዜ ሰውነቴ በመጠኑም ቢሆን ወደ ቀድሞው ቦታ ተመለሰ። ከዚያም የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ በተጓዥ አገልጋይነት እንድሠራ ተመደብኩ። ከጥቂት ወራት በኋላም በኒው ዮርክ ሳውዝ ላንሲንግ በሚገኘው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ። የካቲት 1949 ከ12ኛው የትምህርት ቤቱ ክፍል ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ በቤልጅየም እንዳገለግል ተመደብኩ።
በቤልጅየም በተለያየ የአገልግሎት ዘርፍ ሠርቻለሁ። ስምንት ዓመት ለሚያክል ጊዜ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንዲሁም ለአሥርተ ዓመታት በወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ። በ1958 የጉዞ ጓደኛ የሆነችኝን ጀስቲንን አገባሁ። ዛሬ ዕድሜዬ እየገፋ ቢሄድም በተወሰነ መጠን ተተኪ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ በማገልገል እየተደሰትኩ ነው።
ያሳለፍኩትን አገልግሎት ወደኋላ መለስ ብዬ ስመለከተው በእርግጥም “ከእውነት የተሻለ ምንም ነገር የለም” ማለት እችላለሁ። እርግጥ ነው፣ ሁልጊዜ ሁኔታው ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ከስህተቶቼና ከድክመቶቼ የመማርን አስፈላጊነት ተገንዝቤአለሁ። በመሆኑም ከወጣቶች ጋር ስወያይ ብዙውን ጊዜ የምነግራቸው ነገር አለ:- “እናንተም ስህተት ትሠራላችሁ ምናልባትም ከባድ ኃጢአት ልትሠሩ ትችላላችሁ። ነገር ግን አትዋሹ። ጉዳዩን ከወላጆቻችሁና ከሽማግሌዎቻችሁ ጋር ተወያዩበትና አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርጉ።”
በቤልጂየም ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው ወደ 50 በሚጠጉ ዓመታት ውስጥ ልጅ ሆነው የማውቃቸው ወንድሞች ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሆነው ሲያገለግሉ የማየት መብት አግኝቻለሁ። በመላው አገሪቱ የነበሩት 1,700 አስፋፊዎች ቁጥር ወደ 27,000 አድጎ ለማየት ችያለሁ።
“ይሖዋን ከማገልገል የበለጠ በረከት የሚያስገኝ ሕይወት ሊኖር ይችላልን?” እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። እስካሁን አልነበረም፣ አሁንም የለም፣ ወደፊትም ሊኖር አይችልም። ባለቤቴና እኔ ይሖዋን እስከ ዘላለም ማገልገላችንን እንቀጥል ዘንድ ይሖዋ እኛን መምራቱንና መባረኩን እንዲቀጥል ጸሎቴ ነው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1958 ከባለቤቴ ጋር እንደተገባን
-
-
“ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ”መጠበቂያ ግንብ—1998 | ጥር 1
-
-
“ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ”
“እንግዲህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” በማቴዎስ 28:19 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስን ትእዛዝ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በዚህ መልክ ተርጉሞታል። ሆኖም ይህ አተረጓጎም ትችት ተሰንዝሮበታል። ለምሳሌ ያህል አንድ አነስተኛ ሃይማኖታዊ መጽሔት “የግሪክኛው ጥቅስ ‘አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ብለን እንድንተረጉም ብቻ ነው የሚያስችለን!” የሚል ሐሳብ ሰጥቷል። ይህ አባባል ትክክል ነውን?
“አሕዛብን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለው አተረጓጎም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከግሪክኛው ጥቅስ ቃል በቃል የተተረጎመ ነው። ታዲያ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን እያጠመቃችሁ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ብሎ ለመተርጎም የሚያስችል ምን መሠረት አለ? አገባቡ ትርጉሙን ይወስናል። “እያጠመቃችሁ” የሚለው አገላለጽ በግልጽ የሚያመለክተው ብሔራትን ሳይሆን ሰዎችን ነው። ጀርመናዊው ምሁር ሃንስ ብሩንስ እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “‘እያጠመቃችሁ’ የሚለው [ቃል] ብሔራትን የሚያመለክት አይደለም (ግሪክኛው ልዩነቱን ግልጽ ያደርገዋል) ከዚህ ይልቅ በየብሔራቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ያመለክታል።”
ከዚህም በተጨማሪ የኢየሱስ መመሪያ ሥራ ላይ የዋለበትንም መንገድ መመልከት ያስፈልጋል። ጳውሎስና በርናባስ በትንሹ እስያ በምትገኘው በደርቤን ከተማ ስላከናወኑት አገልግሎት እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፣ . . . ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ።” (ሥራ 14:21) ጳውሎስና በርናባስ በደርቤ ከተማ ያሉትን ሰዎች ባጠቃላይ ሳይሆን በዚያች ከተማ የሚኖሩ የተወሰኑ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዳደረጉ ማስተዋል ያስፈልጋል።
በተመሳሳይ መንገድ የራእይ መጽሐፍ ስለ መጨረሻው ዘመን አስቀድሞ ሲናገር የአምላክ አገልጋዮች የሚሆኑት በየብሔራቱ ያሉ ሰዎች ባጠቃላይ ሳይሆኑ “ከሕዝብና [“ከብሔራትና፣” NW] ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ [“የተውጣጡ፣” NW] እጅግ ብዙ ሰዎች” እንደሆኑ ተናግሯል። (ራእይ 7:9፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) ይህም በመሆኑ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ‘በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች’ ትክክለኛ ትርጉም መሆኑ ተረጋግጧል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
-