የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 3/15 ገጽ 28-30
  • የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ ማን ነበር?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ ማን ነበር?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሕይወት ታሪኩ
  • በጽሑፎቹ ላይ የተደረገ ምርምር
  • ጥሩ ምሥክርነት
  • ሉቃስ—የተወደደው የሥራ ባልደረባ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • “ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ”
    ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ስደት በአንጾኪያ እድገት እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ታስታውሳለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 3/15 ገጽ 28-30

የአንጾኪያው ቴዎፍሎስ ማን ነበር?

“እንዲያው የተኮነነ ስም የሰጠኸኝ ይመስል ክርስቲያን ብለህ ትጠራኛለህ። እኔ ግን ክርስቲያን ተብዬ መጠራቴን በፍጹም አላፍርበትም፤ እንዲያውም እኔ ይህን ስም የተቀበልኩት በአምላክ ዘንድ የተወደድኩ ለመሆንና ለአምላክ ጠቃሚ አገልግሎት ለማበርከት በማሰብ ነው።”

ቴዎፍሎስ ሦስት ክፍሎች ያሉትን የቴዎፍሎስ መልእክት ወደ አውቶሊከስ በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን መጽሐፉን የሚጀምረው ከላይ እንደተጠቀሰው በማለት ነው። ይህ ጽሑፍ በሁለተኛው መቶ ዘመን ለነበረው ሃይማኖታዊ ክህደት ያቀረበው የመጀመሪያ መከላከያ ነበር። ቴዎፍሎስ የክርስቶስ ተከታይ እንደሆነ በድፍረት ይናገር ነበር። ስሙ በግሪክኛ ቋንቋ ከያዘው ትርጉም ጋር በመስማማት “በአምላክ ዘንድ የተወደደ” ለመሆን የቆረጠ ይመስላል። ቴዎፍሎስ ማን ነበር? የኖረው መቼ ነው? ምን አከናውኗል?

የሕይወት ታሪኩ

ስለ ቴዎፍሎስ የሕይወት ታሪክ ብዙም አይታወቅም። ያሳደጉት ክርስቲያን ያልሆኑ ወላጆች ናቸው። ቴዎፍሎስ ቅዱ­ሳን ጽሑፎችን በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ ክርስቲያን ሆነ። ከዚያም በሶሪያ አንጾኪያ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ ጳጳስ ሆነ። ይህ ቦታ በአሁኑ ጊዜ ቱርክ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን አንታክያ ተብሎ ይጠራል።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የኢየሱስን ትእዛዝ በማክበር ለአንጾኪያ ነዋሪዎች ሰብከው ነበር። ሉቃስ “የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቊጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ” በማለት ስብከታቸው ጥሩ ውጤት እንዳስገኘ ጽፏል። (ሥራ 11:20, 21) የኢየሱስ ተከታዮች በመለኮታዊ መሪነት ክርስቲያን ተብለው ተሰየሙ። ይህን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኙት በሶሪያ አንጾኪያ ነበር። (ሥራ 11:26) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሶሪያ አንጾኪያ የተጓዘ ሲሆን ይህ ቦታ ወደተለያዩ አካባቢዎች ለሚያደርገው ጉዞ መነሻ ሆኖለት ነበር። በርናባስና ጳውሎስ ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር በመሆን የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዟቸውን የጀመሩት ከአንጾኪያ ነበር።

በአንጾኪያ የሚኖሩ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ወደሚኖሩበት ከተማ መጥተው ሐዋርያት ስለጎበኟቸው በጣም ተበረታትተው መሆን አለበት። በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው እውነት ሞቅ ያለ ምላሽ የሰጡት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የአስተዳደር አካል ወኪሎች ባደረጉላቸው እምነት የሚያጠነክሩ ጉብኝቶች እንደሆነ አያጠራጥርም። (ሥራ 11:22, 23) በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው የአንጾኪያ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ አምላክ ሲወስኑ በማየታቸው ምንኛ ተበረታትተው መሆን አለበት! ሆኖም ቴዎፍሎስ አንጾኪያ ውስጥ የኖረው ይህ ከተፈጸመ ከ100 ዓመታት በኋላ ነበር።

ቴዎፍሎስ ከክርስቶስ ሐዋርያት ጀምሮ ሲቆጠር ስድስተኛው የአንጾኪያ ጳጳስ እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊው ዩሴቢየስ ተናግሯል። ቴዎፍሎስ ብዛት ያላቸው በቃል የተላለፉ ዝርዝር ነገሮችንና መናፍቅነት ትክክል እንዳልሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች በጽሑፍ አስፍሯል። በጊዜው ከነበሩ ክርስትናን ደግፈው ከጻፉ 12 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሰዎች አንዱ ነበር።

በጽሑፎቹ ላይ የተደረገ ምርምር

ቴዎፍሎስ አረማዊ ለሆነው አውቶሊከስ መልስ ሲጽፍ “አእምሯቸው የተበላሸባቸው ምስኪን ሰዎች ቀልጣፋና ውብ አነጋገር እንዲሁም ባዶ ምስጋና ያስደስታቸዋል” በማለት ይጀምራል። ቴዎፍሎስ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎች ለተዋቡ ቃላት ጆሯቸውን ከመስጠት ይልቅ የጉዳዩን ፍሬ ነገር ይመረምራሉ። . . . ቀልጠውና ተቀጥቅጠው፣ ተቆርጠውና ተቀርጸው ስለተሠሩት የሰው እጅ ሥራ የሆኑ ማየትም ሆነ መስማት የማይችሉ ጣዖታት ስለሆኑት የእንጨትና የድንጋይ አማልክትህ የሚናገሩ ጉራ የተሞላባቸው ባዶ ቃላት ጽፈህልኛል።”—ከመዝሙር 115:4-8 ጋር አወዳድር።

ቴዎፍሎስ የጣዖት አምልኮ ስህተት መሆኑን አጋልጧል። ምንም እንኳ ቃላትን የመደጋገም የአጻጻፍ ዘይቤ ያለው ቢሆንም እውነተኛው አምላክ ምን እንደሚመስል ውብ በሆነ መንገድ ለመግለጽ ሞክሯል። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ይህን ይመስላል ብሎ በቃላት መግለጽ አይቻልም፤ በሰው ዓይን ሊታይ አይችልም። ክብሩ ይህ ነው አይባልም፣ ታላቅነቱ አይለካም፣ ከፍታው ከአእምሮ በላይ ነው፣ በኃይሉ የሚወዳደረው የለም፣ በጥበቡ አቻ የለውም፣ በደግነቱ ተፎካካሪ የለውም፣ በቸርነቱ ማንም የሚደርስበት የለም።”

ቴዎፍሎስ ስለ አምላክ የጀመረውን ገለጻ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “እርሱ ጽንፈ ዓለምን ስለሚገዛ ጌታ ነው፣ ከሁሉ ነገር አስቀድሞ ስለነበረ አባት ነው፣ ጽንፈ ዓለሙን አስውቦ የሠራ እርሱ ስለሆነ እርሱ ፈጣሪና ሠሪ ነው፣ ከሁሉ በላይ ስለሆነ ከፍ ከፍ ያለ ነው፣ በሁሉም ነገር ላይ ስለሚገዛና ሁሉ በሥሩ ስለሆነ ሁሉን ቻይ ነው።”

ቴዎፍሎስ በመቀጠል በተለመደው የአጻጻፍ ዘይቤው ይኸውም አንድ በአንድ በመዘርዘርና አንዳንዶቹን በመደጋገም እንዲህ ይላል፦ “ሰማያት የእርሱ ሥራ ናቸው፣ ምድር የእርሱ ፍጥረት ናት፣ ባሕር የእጁ ሥራ ነው፤ ሰው የእርሱ ንድፍና አምሳያ ነው፤ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የእርሱ ፍጥረታት ሲሆኑ ወቅቶችን፣ ቀናትንና ዓመታትን እንዲያመለክቱ እንዲሁም የሰው ባሪያ እንዲሆኑ ሠርቷቸዋል፤ አምላክ ሁሉንም ነገሮች ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቷል። ይህንንም ያደረገው በሥራዎቹ አማካኝነት ታላቅነቱ እንዲታወቅና እንዲታይ ነው።”

ቴዎፍሎስ በጊዜው የነበሩትን የሐሰት አማልክት ይቃወም እንደነበረ ለአውቶሊከስ ከጻፈው ከሚከተለው መልእክት መረዳት ይቻላል፦ “የምታመልካቸው አማልክት የተሰየሙባቸው ስሞች የሞቱ ሰዎች ስሞች ናቸው። . . . ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ? ሳተርን የሰው ሥጋ የሚበላ፣ የገዛ ልጆቹን ሳይቀር እየገደለ የሚበላ አልነበረምን? አንዲት ፍየል ጠብቶ ያደገው . . . ልጁ ጁፒተርስ ቢሆን . . . ከቅርብ ዘመዶቹ ጋር ሳይቀር የጾታ ግንኙነት የሚፈጽም አመንዝራና ሴሰኛ ነበር።”

ቴዎፍሎስ ሐሳቡን በመቀጠል በአረማዊ የጣዖት አምልኮ ላይ የሚያቀርበውን ተቃውሞ ያጠናክራል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ግብፃውያን ያመለኳቸውን በደረታቸው የሚሳቡ ፍጥረታት፣ ከብቶች፣ አራዊት፣ ወፎችና የባሕር ዓሦች የመሳሰሉ አያሌ እንስሳትን መዘርዘር አለብኝን? . . . ግሪኮችና ሌሎች ሕዝቦች ድንጋይ፣ እንጨትና ሌሎች ቁሳቁሶችን አምልከዋል።” ቴዎፍሎስ “እኔ ግን ሕያው አምላክን አመልካለሁ” በማለት ተናግሯል።—ከ2 ሳሙኤል 22:47፤ ከሥራ 14:15 እና ከሮሜ 1:22, 23 ጋር አወዳድር።

ጥሩ ምሥክርነት

የአውቶሊከስን ሐሳብ ለማፍረስ በተጻፉት በሦስቱ የቴዎፍሎስ ጽሑፎች ውስጥ ያሉት ጥብቅ ማሳሰቢያዎችና ምክሮች ብዙ ገጽታ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ በዝርዝር የቀረቡ ናቸው። ሌሎቹ የቴዎፍሎስ ጽሑፎች ደግሞ ሄርሞጄኔዝና ማርሲዮን በተባሉ ሰዎች ላይ ያተኩራሉ። በተጨማሪም በወንጌሎች ላይ ማብራሪያ በማከል የመመሪያ ወይም ማስተማሪያ መጻሕፍት ጽፏል። ሆኖም እስካሁን የቆየው ለአውቶሊከስ የላካቸውን ሦስት መጻሕፍት የያዘ አንድ በእጅ የተጻፈ ጽሑፍ ብቻ ነው።

የመጀመሪያው መጽሐፍ የክርስትናን ሃይማኖት በመደገፍ ለአውቶሊከስ የተጻፈ ነው። ለአውቶሊከስ የተጻፈው ሁለተኛው መጽሐፍ የታወቀውን አረመኔያዊ ሃይማኖት፣ ግምታዊ አስተሳሰብን፣ ፈላስፋዎችንና ባለቅኔዎችን የሚነቅፍ ነበር። ቴዎፍሎስ በሦስተኛ መጽሐፉ ላይ አረመኔያዊ ጽሑፎችን ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር አነጻጽሯል።

ቴዎፍሎስ ሦስተኛ መጽሐፉን መጻፍ ሲጀምር አውቶሊከስ የእውነት ቃል የፈጠራ ታሪክ ነው ብሎ ያስብ ነበር። ቴዎፍሎስ እንዲህ በማለት አውቶሊከስን ነቅፎታል፦ “ሞኞችን ታግሠሃል። እንዲህ ባይሆን ኖሮ አእምሮ የጎደላቸው ሰዎች በባዶ ቃላት አይማርኩህም ነበር፤ እንዲሁም በሰፊው የሚናፈሰውን መሠረት የሌለው ወሬ አታምንም ነበር።”

ይህ “በሰፊው የሚናፈስ መሠረት የሌለው ወሬ” ምን ነበር? ቴዎፍሎስ የዚህን ወሬ ምንጭ ጠቅሷል። ስም አጥፊዎች “[እኛ] አምላክን የምናመልክ ክርስቲያኖች ሚስቶቻችን የጋራ እንደሆኑና አንዳችን ከሌላው ሚስት ጋር የጾታ ብልግና እንደምንፈጽም በመናገር አረመኔያዊ በሆነ አፋቸው በሐሰት ይከሱናል። ሌላው ቀርቶ ከአንድ ወላጅ ከተወልድነው እህቶቻችን ጋር የጾታ ግንኙነት እንደምንፈጽም የሚናገሩ ሲሆን ከሁሉ ይልቅ የሚያዋርደውና ጭካኔ የተሞላበት አነጋገራቸው ደግሞ የሰው ሥጋ እንደምንበላ የሚያናፍሱት የሐሰት ወሬ ነው።” ቴዎፍሎስ አረማውያን በሁለተኛው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩት ክርስቲያን እንደሆኑ በግልጽ በሚናገሩ ሰዎች ላይ ያላቸውን ፈጽሞ የተሳሳተ አመለካከት ለመዋጋት ጥረት አድርጓል። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው የእውነት ብርሃን ተጠቅሟል።—ማቴዎስ 5:11, 12

ቴዎፍሎስ በዕብራይስጡና በግሪኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በተደጋጋሚ መጠቀሙና ከእነዚህ ጽሑፎች መጥቀሱ የአምላክን ቃል ጥሩ አድርጎ ያውቅ እንደነበረ ያሳያል። ከጥንቶቹ የወንጌል ተንታኞች አንዱ ነበር። ቴዎፍሎስ ለቅዱሳን ጽሑፎች የሰጣቸው የተለያዩ ትርጉሞች በጊዜው የነበረውን የአብዛኛውን ሰው አመለካከት በጥልቀት ለማስተዋል ያስችላል። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉ ጽሑፎች ላይ በነበረው ጥሩ እውቀት ተጠቅሞ እነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ከአረማውያን ፍልስፍናዎች ያላቸውን ከፍተኛ ብልጫ አሳይቷል።

የቴዎፍሎስ አጻጻፍ ይኸውም ለማስተማር ያለው ኃይለኛ ጉጉትና ደጋግሞ የመጻፍ ዘይቤው አንዳንድ ሰዎችን ላያስደስት ይችላል። አስቀድሞ ተነግሮ የነበረው ክህደት የቴዎፍሎስን ትክክለኛ አመለካከት ምን ያህል እንደነካው አናውቅም። (2 ተሰሎንቄ 2:3-12) ሆኖም ቴዎፍሎስ በ182 እዘአ እስከሞተ ድረስ ክርስትናን ደግፎ የሚጽፍ ጠንካራ ሰው ነበር። በዘመናችን የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ቴዎፍሎስ ስለጻፋቸው ጽሑፎች ይበልጥ ለማወቅ ይፈልጋሉ።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አውቶሊከስ ያቀረባቸው የመከራከሪያ ነጥቦች የተሳሳቱ መሆናቸውን ቴዎፍሎስ አረጋግጧል

[ምንጭ]

በገጽ 28 እና 30 ላይ ያሉት ሥዕሎች ምንጭ፦Illustrirte Pracht - Bibel/Heilige Schrift des Alten und Neuen Testaments, nach der deutschen Uebersetzung D. Martin Luther’s

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ