የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 10/15 ገጽ 17-22
  • ወንድምህን ገንዘብ ልታደርገው ትችላለህ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወንድምህን ገንዘብ ልታደርገው ትችላለህ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?
  • ወንድምህን ገንዘብ ለማድረግ ጣር
  • የጎለመሰ ሰው እርዳታ ማግኘት
  • ገንዘብ ለማድረግ የሚወሰድ የመጨረሻ እርምጃ
  • አለመግባባትን የምትፈቱት እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • የጉባኤውን ሰላምና ንጽሕና መጠበቅ
    የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ
  • በዛሬው ጊዜ አምላክን በመሐሪነቱ ምሰሉት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • አለመግባባቶችን በፍቅር መፍታት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 10/15 ገጽ 17-22

ወንድምህን ገንዘብ ልታደርገው ትችላለህ

“ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው [“በደሉን ንገረው፣” 1980 ትርጉም ]። ቢሰማህ፣ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው።”​—⁠ማቴዎስ 18:15

1, 2. አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ኢየሱስ ምን ተግባራዊ ምክር ሰጥቷል?

ኢየሱስ አገልግሎቱን ሊያጠናቅቅ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ሲቀረው ለደቀ መዛሙርቱ ወሳኝ የሆኑ ትምህርቶች አስተማራቸው። እነዚህን ትምህርቶች ማቴዎስ ምዕራፍ 18 ላይ ማንበብ ትችላለህ። አንደኛው እንደ ሕፃናት ትሑት የመሆንን አስፈላጊነት የሚገልጽ ነበር። በመቀጠልም “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን” እንዳናሰናክል መጠንቀቅና የባዘኑትን ‘ታናናሾች’ ፈልገን ለመመለስ መጣር እንዳለብን አሳስቦ ነበር። ከዚያም ኢየሱስ በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ጠቃሚ ምክር ጨምሮ ተናገረ።

2 ኢየሱስ የተናገራቸውን እነዚህን ቃላት ታስታውስ ይሆናል:- “ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው ባይሰማህ ግን፣ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፣ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፣ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፣ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” (ማቴዎስ 18:15-17) ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብን መቼ ነው? ይህንንስ ስናደርግ ዝንባሌያችን ምን መሆን አለበት?

3. በጥቅሉ ሲታይ ሌሎች የሚፈጽሙትን ስህተት በተመለከተ ማድረግ የሚገባን ምንድን ነው?

3 ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንንና ስህተት ልንሠራ ስለምንችል ይቅር ባይ ለመሆን መጣር እንዳለብን በቀደመው ርዕስ ላይ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። በተለይ አንድ ክርስቲያን በተናገረው ወይም በፈጸመው ድርጊት ብንጎዳ ይህን ማድረጉ የግድ አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥሮስ 4:​8) ብዙውን ጊዜ የተፈጸመብንን በደል ችላ ብሎ ማለፉ ማለትም ይቅር ማለትና መርሳቱ ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። እንዲህ በማድረጋችን የክርስቲያን ጉባኤን ሰላም ለመጠበቅ አንድ ዓይነት አስተዋጽኦ እንዳበረከትን አድርገን ልንመለከተው እንችላለን። (መዝሙር 133:​1፤ ምሳሌ 19:​11) ሆኖም ከበደለህ ወንድም ወይም እህት ጋር ተወያይተህ ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት እንዳለብህ የሚሰማህ ጊዜ ሊኖር ይችላል። ከላይ የሰፈሩት የኢየሱስ ቃላት በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብህ መመሪያ ይሆኑሃል።

4. ሌሎች ሲሳሳቱ ማቴዎስ 18:​15ን በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በሥራ ላይ ልናውል የምንችለው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ‘አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው’ በማለት ምክር ሰጥቷል። ይህ ጥበብ ነው። አንዳንድ የጀርመንኛ ትርጉሞች ግለሰቡ የሠራውን ስህተት “በአራት ዓይኖች ፊት” ማለትም በአንተና በእርሱ ዓይኖች ፊት አቅርበው በማለት ገልጸውታል። ስለ ጉዳዩ ‘ለብቻ ሆኖ’ በደግነት መነጋገሩ ብዙውን ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ይበልጥ ቀላል ያደርገዋል። ቅር የሚያሰኝ ወይም ደግነት የጎደለው ነገር የፈጸመ ወይም የተናገረ ወንድም ለብቻህ ሆነህ በምታነጋግረው ጊዜ ጥፋቱን ለማመን ይበልጥ ቀላል ይሆንለታል። ሌሎች ባሉበት ከሆነ ግን ሰብዓዊ የኃጢአተኝነት ዝንባሌ ስህተት መፈጸሙን እንዲክድ ወይም ለሠራው ስህተት ሰበብ ለማቅረብ እንዲሞክር ሊያደርገው ይችላል። ሆኖም ጉዳዩን “በአራት ዓይኖች ፊት” አቅርበህ ከተነጋገራችሁ ጉዳዩ ኃጢአት ወይም ሆነ ተብሎ የተፈጸመ በደል ሳይሆን አለመግባባት ብቻ ሆኖ ታገኘዋለህ። ሁለታችሁም ጉዳዩ በመካከላችሁ የተፈጠረ አለመግባባት መሆኑን አንዴ ከተረዳችሁ በማይረባ ነገር ግንኙነታችሁ እንዲሻክር ከመፍቀድ ይልቅ ወዲያው ልትፈቱት ትችላላችሁ። ስለዚህ በማቴዎስ 18:​15 ላይ የሰፈረው መሠረታዊ ሥርዓት በዕለታዊ ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ቀላል አለመግባባቶች ለመፍታት ጭምር ሊሠራ ይችላል።

ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?

5, 6. ከጥቅሱ አገባብ አንጻር ማቴዎስ 18:​15 የሚያመለክተው ምን ዓይነት ኃጢአትን ነው? ይህንን እንደሚያመለክትስ የሚያሳየው ምንድን ነው?

5 እንደ እውነቱ ከሆነ ኢየሱስ የሰጠው ምክር ከበድ ላሉ ጉዳዮች የሚሠራ ነው። ኢየሱስ “ወንድምህም ቢበድልህ [“ኃጢአት ቢሠራ፣” NW]” በማለት ተናግሯል። ሰፋ አድርገን ከተመለከትነው “ኃጢአት” የሚለው አነጋገር ማንኛውንም ዓይነት ስህተት ወይም ጥፋት ሊያመለክት ይችላል። (ኢዮብ 2:​10፤ ምሳሌ 21:​4፤ ያዕቆብ 4:​17) ይሁን እንጂ ከጥቅሱ ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች እንደሚያመለክቱት ኢየሱስ ኃጢአት በማለት የጠቀሰው ከበድ ያለ ኃጢአትን የሚያመለክት መሆን አለበት። ግለሰቡን “እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ” ሊያስቆጥር የሚችል ክብደት ያለው ስህተት ነው። ታዲያ ይህ ሐረግ ምን ነገርን የሚያመለክት ነው?

6 እነዚህን የኢየሱስ ቃላት ያዳምጡ የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአገራቸው ሰዎች ከአሕዛብ ጋር ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ግንኙነት እንደማያደርጉ ያውቁ ነበር። (ዮሐንስ 4:​9፤ 18:​28፤ ሥራ 10:​28) እንዲሁም የአይሁድ ተወላጅ ቢሆኑም እንኳ ሕዝቡን የሚጨቁኑትን ቀረጥ ሰብሳቢዎች ሙሉ በሙሉ ይርቋቸው ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ማቴዎስ 18:​15-17 ላይ የሠፈረው መግለጫ የሚያመለክተው በቀላሉ ይቅር ብለህ ልትረሳው የምትችለውን ቅሬታ ወይም ቅያሜ ሳይሆን ከበድ ያሉ ኃጢአቶችን ነው።​—⁠ማቴዎስ 18:​21, 22a

7, 8. (ሀ) በሽማግሌዎች እልባት ማግኘት የሚኖርባቸው እንዴት ያሉ ኃጢአቶች ናቸው? (ለ) በማቴዎስ 18:​15-17 መሠረት በሁለት ክርስቲያኖች መካከል መፍትሔ ማግኘት የሚኖርባቸው ምን ዓይነት ኃጢአቶች ናቸው?

7 በሕጉ ሥር፣ የተበደለው ወገን ይቅር በማለቱ ብቻ የማያበቁ አንዳንድ ኃጢአቶች ነበሩ። አምላክን መሳደብ፣ ክህደት፣ የጣዖት አምልኮና እንደ ዝሙት፣ ምንዝርና ግብረ ሰዶም የመሰሉ የጾታ ብልግናዎች ለሽማግሌዎች (ወይም ለካህናት) መነገርና በእነርሱ በኩል እልባት ማግኘት ነበረበት። በክርስቲያን ጉባኤም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ዘሌዋውያን 5:​1፤ 20:​10-13፤ ዘኁልቁ 5:​30፤ 35:​12፤ ዘዳግም 17:​9፤ 19:​16-19፤ ምሳሌ 29:​24) ሆኖም ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረለት ኃጢአት በሁለት ሰዎች መካከል ሊያልቅ የሚችል መሆኑን ልብ በል። ለምሳሌ ያህል:- አንድ ሰው በንዴት ወይም በቅናት ተነሳስቶ የሌላውን ስም ቢያጠፋ። አንድ ክርስቲያን በተወሰኑ የሕንፃ መሣሪያዎች ተጠቅሞ አንድ የግንባታ ሥራ ለመሥራትና ይህንን ሥራ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ጨርሶ እንደሚያስረክብ ቢስማማ። ሌላ ክርስቲያን ደግሞ በአንድ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ወይም ዕለት እንደሚከፍል በመስማማት ገንዘብ ቢበደር። አንድ ግለሰብ አሠሪው ሥልጠና ቢሰጠው (ሥራውን ለቆ ቢወጣ እንኳ) በዚያ አካባቢ አሠሪውን እንደማይፎካከር ወይም የአሠሪውን ደንበኞች ወደ ራሱ እንደማይወስድ ቃል ቢገባ።b አንድ ወንድም እነዚህን በመሰሉ ተግባሮች የገባውን ቃል ቢጥስና ንሥሐ ባይገባ ይህ በእርግጥም ከባድ ኃጢአት ነው። (ራእይ 21:​8) ሆኖም እንደዚህ ያሉት ስህተቶች ጉዳዩ በሚመለከታቸው በሁለቱ ግለሰቦች መካከል መፍትሔ ሊያገኙ ይችላሉ።

8 ታዲያ ለችግሩ እልባት ለመስጠት የኢየሱስን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ብዙውን ጊዜ ሦስት ደረጃ እንዳላቸው ተደርገው ይታያሉ። እስቲ እያንዳንዱን ደረጃ በየተራ እንመልከት። ኢየሱስ የተናገራቸውን እነዚህን ቃላት ድርቅ ያለ ሕግ አድርገህ ከመመልከት ይልቅ የተነሣህበትን ፍቅራዊ ዓላማ ሳትዘነጋ የቃላቱን አጠቃላይ መንፈስ ለመረዳት ሞክር።

ወንድምህን ገንዘብ ለማድረግ ጣር

9. ማቴዎስ 18:​15ን በሥራ ላይ ማዋልን በተመለከተ ምን ነገር በአእምሯችን መያዝ ይኖርብናል?

9 ኢየሱስ ንግግሩን እንዲህ በማለት ጀመረ:- “ወንድምህም ቢበድልህ፣ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፣ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው።” በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ እንዲያው በጥርጣሬ የሚወሰድ እርምጃ አይደለም። ወንድምህ ስህተት መሥራቱ እንዲታየውና ስህተቱን ማስተካከል እንደሚያስፈልገው ለማስገንዘብ የሚረዳህ የተጨበጠ ማስረጃ ሊኖርህ ይገባል። ችግሩ እንዳይባባስ ወይም ግለሰቡ ይበልጥ ግትር እየሆነ እንዳይሄድ ቶሎ እርምጃ መውሰዱ ጥሩ ነው። ደግሞም ጉዳዩን በሆድህ ይዘህ ማብሰልሰልህ ሊጎዳህ እንደሚችል አትዘንጋ። ጉዳዩ በአንተና በእርሱ መካከል የሚያልቅ እንደመሆኑ መጠን የሌሎችን ድጋፍ ለማግኘት ወይም ሌሎች ስለ አንተ መጥፎ አመለካከት እንዳይኖራቸው ስትል ቀድመህ ለሌሎች ማውራት አይኖርብህም። (ምሳሌ 12:​25፤ 17:​9) ለምን? ምክንያቱም የተነሳህበትን ዓላማ መሳት ስለማትፈልግ ነው።

10. ወንድማችንን ገንዘብ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?

10 ዋነኛው ዓላማህ ወንድምህን ገንዘብ ማድረግ እንጂ እርሱን መቅጣት፣ ማዋረድ ወይም መጉዳት አይደለም። በትክክል ስህተት ፈጽሞ ከሆነ ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ዝምድናም አደጋ ላይ ወድቋል። ክርስቲያን ወንድምህ እንደሆነ እንዲቀጥል እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ለብቻችሁ ሆናችሁ በምትነጋገሩበት ጊዜ የረጋ መንፈስ መያዝህና ኃይለኛ ቃላት ከመሰንዘር ወይም በክስ መልክ ከመናገር መቆጠብህ ውይይታችሁ ጥሩ ውጤት የማስገኘቱ አጋጣሚ ከፍ ያለ ይሆናል። ፊት ለፊት ተገናኝታችሁ በችግሩ ላይ በምታደርጉት በዚህ ፍቅራዊ ውይይት ወቅት ሁለታችሁም ፍጹማን አለመሆናችሁን አዎን፣ ኃጢአተኞች መሆናችሁን አስታውሱ። (ሮሜ 3:​23, 24) ስህተቱን ለሌሎች በመንገር እንዳላማኸው ሲገነዘብና ከልብህ ልትረዳው የምትፈልግ መሆኑን ሲያይ በቀላሉ መፍትሔ ላይ ልትደርሱ ትችላላችሁ። እንዲህ ዓይነቱ ደግነት ያለበት ግልጽ ውይይት በተለይ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው ለማለት የሚቻለው ሁለታችሁም በተወሰነ መጠን ጥፋተኞች መሆናችሁን ወይም ደግሞ ለችግሩ መንስኤ የሆነው አለመግባባት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ከሆነ ነው።​—⁠ምሳሌ 25:​9, 10፤ 26:​20፤ ያዕቆብ 3:​5, 6

11. በደል የፈጸመብን ግለሰብ ባይሰማን እንኳ ምን ልናደርግ እንችላለን?

11 በትክክል አንድ ዓይነት ስህተት እንደተፈጸመና ይህም ቀላል እንዳልሆነ እንዲገነዘብ ከረዳኸው ንሥሐ ለመግባት ሊገፋፋ ይችል ይሆናል። ሆኖም ኩራት እንዲህ እንዳያደርግ እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል። (ምሳሌ 16:​18፤ 17:​19) ስለዚህ መጀመሪያ ላይ ስትነጋገሩ ስህተቱን ባያምንና ንሥሐ ባይገባ እንኳ የሚቀጥለውን እርምጃ ከመውሰድህ በፊት ተጨማሪ አጋጣሚ ትሰጠዋለህ። ኢየሱስ ‘አንድ ጊዜ ብቻ ሄደህ ውቀሰው’ አላለም። አንተ በግልህ ልትጨርሰው የምትችለው ኃጢአት እስከሆነ ድረስ የገላትያ 6:​1ን መንፈስ በመያዝ “በአራት ዓይኖች ፊት” ዳግመኛ ለማነጋገር አስብ። ሊሳካልህ ይችል ይሆናል። (ከይሁዳ 22, 23 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ኃጢአት እንደተፈጸመ ብታውቅና ግለሰቡ ምንም ዓይነት ጥሩ ምላሽ ባይሰጥህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

የጎለመሰ ሰው እርዳታ ማግኘት

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ በጠቀሰው መሠረት ስህተትን ለማስተካከል በሁለተኛ ደረጃ የሚወሰደው እርምጃ ምንድን ነው? (ለ) ይህን እርምጃ በሥራ ላይ ለማዋል ምን ተገቢ የሆነ ምክር ተሰጥቷል?

12 አንተ ከበድ ያለ ስህተት ብትፈጽምና ሌሎች አንተን ለመርዳት በሚያደርጉት ጥረት በአንዴ ተስፋ ቆርጠው ቢተዉህ ደስ ይልሃል? ደስ እንደማይልህ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ወንድምህን ገንዘብ ለማድረግና ከአንተና ከሌሎች ጋር አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ ይችል ዘንድ ለመርዳት በመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ጥረትህን ማቆም እንደሌለብህ ኢየሱስ አመልክቷል። ኢየሱስ መወሰድ ያለበትን ሁለተኛ እርምጃ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል:- “ባይሰማህ ግን፣ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፣ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ።”

13 ኢየሱስ “አንድ ወይም ሁለት” ሰው ይዘህ ሂድ ብሏል። ኢየሱስ የመጀመሪያውን እርምጃ ከወሰድክ በኋላ ችግሩን ለሌሎች ሰዎች ለማውራት፣ ለተጓዥ የበላይ ተመልካች ለመንገር ወይም ለሌሎች በደብዳቤ ለማሳወቅ ነፃ ትሆናለህ አላለም። አንተ ስህተት እንደተሠራ ብታምንም ጉዳዩ ገና ሙሉ በሙሉ አልተረጋገጠም። የተሳሳተ ወሬ በማውራት በኋላ እንደ ስም አጥፊ መቆጠር እንደማትፈልግ ግልጽ ነው። (ምሳሌ 16:​28፤ 18:​8) ሆኖም ኢየሱስ አንድ ወይም ሁለት ሰዎችን ይዘህ መሄድ እንደምትችል ተናግሯል። ለምን? እነዚህስ ሰዎች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ?

14. ሁለተኛውን እርምጃ በምንወስድበት ወቅት እነማንን ይዘን ልንሄድ እንችላለን?

14 ወንድምህ ኃጢአት መፈጸሙን እንዲያምንና ከአንተም ሆነ ከአምላክ ጋር ያለውን ሰላም ጠብቆ ማቆየት ይችል ዘንድ ንስሐ እንዲገባ በመቀስቀስ ወንድምህን ገንዘብ ለማድረግ እየጣርክ ነው። ይህንንም ዳር ማድረስ ይቻል ዘንድ ከአንተ ጋር የሚሄዱት “አንድ ወይም ሁለት” ሰዎች ስህተቱ ሲፈጸም የተመለከቱ ቢሆኑ ይመረጣል። ምናልባት ችግሩ ሲደርስ በአካል የነበሩ ወይም በንግድ ጉዳይ ምን ነገር እንደተፈጸመ (ወይም ምን ነገር ሳይደረግ እንደቀረ) በቂ መረጃ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ምሥክሮችን ማግኘት የማይቻል ከሆነ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን በመፍታት ረገድ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውና የተፈጸመው ነገር በትክክል ስህተት መሆን አለመሆኑን በሚገባ መለየት የሚችሉ ሰዎች ሊሆኑ ይገባል። ከዚህም በላይ በሌላ ወቅት መገኘት የሚያስፈልጋቸው ቢሆን እንኳ የተባለውን ነገር በትክክል አስታውሰው መመሥከር የሚችሉ፣ የቀረቡትን እውነታዎችና የተደረጉትን ጥረቶች በእርግጠኝነት መናገር የሚችሉ መሆን አለባቸው። (ዘኁልቁ 35:​30፤ ዘዳግም 17:​6) ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ያልሆኑ ገለልተኛ ሰዎች ወይም ዳኞች አይደሉም፤ ከዚያ ይልቅ እዚያ የተገኙበት ምክንያት የአንተንም ሆነ የእነርሱን ወንድም ገንዘብ ለማድረግ ነው።

15. ሁለተኛውን እርምጃ የምንወስድ ከሆነ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጠቃሚ እርዳታ ሊሰጡ የሚችሉት ለምንድን ነው?

15 የምትወስዳቸው ሰዎች የግድ የጉባኤ ሽማግሌዎች መሆን አለባቸው ብለህ ማሰብ የለብህም። ሆኖም ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው የጎለመሱ ሰዎች በመሆናቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ። እነዚህ ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆና[ሉ]።” (ኢሳይያስ 32:​1, 2) ወንድሞችንና እህቶችን በምክንያታዊነት በማወያየትና በማስተካከል ረገድ ተሞክሮ አላቸው። እንዲሁም ስህተት የፈጸመው ግለሰብ ‘ስጦታ በሆኑት በእነዚህ ወንዶች’ ላይ ትምክህቱን ለመጣል አይቸገርም።c (ኤፌሶን 4:​8, 11, 12) እነዚህ የጎለመሱ ሰዎች በተገኙበት ጉዳዩን በግልጥ መነጋገርና ከእነርሱ ጋር በጸሎት መካፈል ጉዳዩን በአዲስ መልክ ለማየትና ፈጽሞ መፍትሔ የሌለው የመሰለውን ጉዳይ መቋጫ እንዲገኝለት ለማድረግ ይችላል።​—⁠ከያዕቆብ 5:​14, 15 ጋር አወዳድር።

ገንዘብ ለማድረግ የሚወሰድ የመጨረሻ እርምጃ

16. ኢየሱስ የገለጸው ሦስተኛው እርምጃ ምንድን ነው?

16 ሁለተኛው እርምጃ ለተፈጠረው ችግር ምንም ዓይነት መፍትሔ ካላስገኘ ሦስተኛው እርምጃ በሚወሰድበት ወቅት የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች የግድ በጉዳዩ ይገባሉ። “እነርሱንም [አንዱን ወይም ሁለቱን] ባይሰማ፣ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፣ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” ይህ ምን ማለት ነው?

17, 18. (ሀ) ‘ለጉባኤ የመናገርን’ አስፈላጊነት እንድንረዳ የሚያስችለን ምሳሌ የትኛው ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይህን እርምጃ የምንሠራበት እንዴት ነው?

17 ይህ አባባል የተፈጸመውን ኃጢአት ወይም በደል በተለመደው የጉባኤ ስብሰባ ወይም ልዩ ስብሰባ ላይ እንድናቀርበው ፈቃድ እንደሚሰጠን አድርገን መመልከት አይኖርብንም። ተገቢውን የአሠራር ሂደት የሚነግረን የአምላክ ቃል ነው። በጥንቷ እስራኤል የሚኖር አንድ ሰው ዓመፀኛ፣ ሆዳም ወይም ሰካራም ቢሆን ምን እንደሚደረግ ተመልከት:- “ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ ቢቀጡትም የማይሰማቸው እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፣ አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማው ሽማግሌዎች ወደሚኖርበትም ስፍራ በር ያምጡት፤ የከተማውንም ሽማግሌዎች:- ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፣ ለቃላችንም አይታዘዝም ስስታምና ሰካራም ነው ይበሉአቸው። የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት።”​—⁠ዘዳግም 21:​18-21፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

18 ግለሰቡ የሠራውን ኃጢአት አዳምጦ ፍርድ የሚሰጠው መላው ብሔር ወይም የተወለደበት ነገድ አይደለም። ከዚያ ይልቅ “ሽማግሌዎች” የተባሉት ጉባኤውን ወክለው ጉዳዩን ይመለከታሉ። (‘ካህናቱና በዚያ ዘመን የሚፈርዱ ፈራጆች’ ስለሚይዙት ጉዳይ ከሚናገረው ከዘዳግም 19:​16, 17 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ዛሬ ሦስተኛውን እርምጃ መውሰድ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሽማግሌዎች ጉባኤውን በመወከል ጉዳዩን ይይዙታል። እነርሱም ቢሆኑ ዓላማቸው በተቻለ መጠን ክርስቲያን ወንድማቸውን ገንዘብ ማድረግ ነው። ይህንንም ከወገናዊነትና ከአድሎአዊነት በመራቅ ፍትሕን በማስፈጸም ያሳያሉ።

19. ጉዳዩን ለመስማት የተሰየሙት ሽማግሌዎች ምን ለማድረግ ይጥራሉ?

19 እነሱም ኃጢአት በትክክል መፈጸሙን (ወይም እየተፈጸመ እንዳለ) ለማረጋገጥ ማስረጃዎችን ይመረምራሉ እንዲሁም ምሥክሮችን ያዳምጣሉ። ጉባኤውን ከብክለትና ከዓለም መንፈስ ለመጠበቅ ይፈልጋሉ። (1 ቆሮንቶስ 2:​12፤ 5:​7) ‘ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ይመክራሉ ተቃዋሚዎችንም ይወቅሳሉ።’ ይህም ከቅዱስ ጽሑፋዊው ብቃታቸው ጋር የሚስማማ ነው። (ቲቶ 1:​9) መቼም መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ አንድ የይሖዋ ነቢይ እንደሚከተለው ብሎ የጻፈላቸውን እስራኤላውያን ዓይነት አቋም እንደማይዝ ተስፋ ይደረጋል። “በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፣ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፣ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።”​—⁠ኢሳይያስ 65:​12

20. ኃጢአተኛው ለመስማትና ንስሐ ለመግባት እምቢተኛ ከሆነ ኢየሱስ የተናገረው የትኛው መመሪያ ተግባራዊ ይሆናል?

20 ሆኖም ከላይ የተገለጹት ሰዎች የነበራቸውን ዓይነት ዝንባሌ የሚያሳይ ኃጢአተኛ አይኖርም ብለን ለመናገር አንደፍርም። ሆኖም እንደዚያ ዓይነት ዝንባሌ ያለው ኃጢአተኛ ኢየሱስ “እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ” በማለት የሰጠው ግልጽ መመሪያ ይሠራበታል። ሰብዓዊነት በጎደለው መንገድ እንዲታይ ወይም ጉዳት እንዲደርስበት ጌታ መመሪያ አልሰጠም። ሐዋርያው ጳውሎስ ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛ ከጉባኤ እንዲወገድ የሰጠው መመሪያ ምንም የሚያሻማ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 5:​11-13) ይህም ቢሆን ከጊዜ በኋላ ኃጢአተኛውን ገንዘብ ለማድረግ ሊረዳ ይችል ይሆናል።

21. ከጉባኤ የተወገደ አንድ ግለሰብ አሁንም ቢሆን ምን የማድረግ አጋጣሚው አልተዘጋበትም?

21 ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ ከተናገረው ምሳሌ ይህ ሁኔታ ሊደርስ እንደሚችል ማየት እንችላለን። በምሳሌው ላይ የተገለጸው ኃጢአተኛ ፍቅር የሞላበትን የአባቱን ቤት ጥሎ ወጥቶ ለተወሰነ ጊዜ ለብቻው ከኖረ በኋላ ‘ወደ ልቡ ተመለሰ።’ (ሉቃስ 15:​11-18) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ አንዳንድ ኃጢአተኞች ከጊዜ በኋላ ንስሐ ይገቡና ‘ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ እንደሚወጡ’ ገልጾለታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:​24-26) ንሥሐ ለመግባት እምቢተኛ በመሆን ከጉባኤ የግድ መወገድ የሚኖርበት ማንኛውም ኃጢአተኛ የአምላክን ሞገስና ታማኝ በሆኑ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ሞቅ ያለ የወዳጅነት ሕብረት እንዳጣ ሲገነዘብ ወደ አእምሮው ይመለሳል።

22. አሁንም ቢሆን ወንድማችንን ገንዘብ ልናደርገው የምንችለው እንዴት ሊሆን ይችላል?

22 ኢየሱስ አሕዛብንና ቀራጮችን ጨርሶ ሊቤዡ የማይችሉ ሰዎች አድርጎ አልተመለከታቸውም። ቀራጭ የነበረው ማቴዎስ ሌዊ ንስሐ ገብቶ በቅንነት ‘ኢየሱስን ከመከተሉም’ በላይ ለሐዋርያነት ተመርጧል። (ማርቆስ 2:​15፤ ሉቃስ 15:​1) በመሆኑም በጊዜያችን የሚኖር አንድ ኃጢአተኛ ‘ቤተ ክርስቲያንን ሳይሰማት’ ቀርቶ ከጉባኤ ቢወገድ አንድ ቀን ንስሐ ገብቶ አካሄዱን ያስተካክላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህ ግለሰብ ንስሐ ገብቶ እንደገና የጉባኤው አባል በሚሆንበት ጊዜ ወንድማችን ወደ እውነተኛው አምልኮ ተመልሶ ስናይ ደስ ይለናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በማክሊንቶክ እና ስትሮንግስ የተዘጋጀው ሳይክለፒዲያ እንዲህ ይላል:- “በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱት ቀራጮች [ቀረጥ ሰብሳቢዎች] ከአረመኔዎች ጋር በመቀራረብ የረከሱ፣ ለጨቋኞች ቀኝ እጅ ሆነው ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ከዳተኞችና ከሃዲዎች እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። ከኃጢአተኞች ጋር በአንድ ዓይን ይታዩ ነበር። . . . በዚህ መንገድ የተገለሉ ሰዎች በመሆናቸው ጨዋ የሆኑ ሰዎች ጨርሶ ወደ እነርሱ አይቀርቡም ነበር። እነርሱን ወዳጅ ወይም ጓደኛ በማድረግ የሚቀርቧቸው ልክ እንደ እነርሱ ኅብረተሰቡ ያገለላቸው ሰዎች ብቻ ነበሩ።”

b በንግድ ወይም ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች በተወሰነ ደረጃ የማታለል ወይም የማጭበርበር ሁኔታ የሚታይባቸው ድርጊቶች ኢየሱስ በገለጸው የኃጢአት ዓይነት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ። ኢየሱስ በማቴዎስ 18:​15-17 ላይ የተመዘገበውን መመሪያ ከሰጠ በኋላ ሁኔታውን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ገንዘብ ተበድሮ መክፈል ስላቃታቸው ባሪያዎች (ሠራተኞች) የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል።

c አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል:- “አንዳንድ ጊዜ ስህተት የፈጸመ አንድ ግለሰብ አንድ ሰው በተለይ ደግሞ ከእርሱ የተለየ አመለካከት ያለው ሰው ከሚሰጠው ምክር ይልቅ ሁለት ወይም ሦስት (በተለይ በሌሎች ዘንድ አክብሮትን ያተረፉ) ሰዎች የሚሰጡትን ምክር ለመቀበል ይበልጥ ፈቃደኛ ሆኖ ይገኛል።”

ታስታውሳለህን?

◻ ማቴዎስ 18:​15-17 በቅድሚያ የሚሠራው ለምን ዓይነት ኃጢአት ነው?

◻ የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ የሚኖርብን ከሆነ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

◻ ሁለተኛውን እርምጃ የምንወስድ ከሆነ የእነማንን እርዳታ ልናገኝ እንችላለን?

◻ ሦስተኛው እርምጃ በሚወሰድበት ወቅት የግድ መገኘት የሚኖርባቸው እነማን ናቸው? ወንድማችንን ገንዘብ ማድረግ የምንችለው እንዴት ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይሁዳውያን ቀራጮችን ያገልሏቸው ነበር። ማቴዎስ አካሄዱን ለውጦ የኢየሱስ ተከታይ ሆኗል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ አንድን ጉዳይ “በአራት ዓይኖች ፊት” ልንፈታ እንችላለን

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ