-
ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችመጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 1
-
-
ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች
“አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ . . . አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።”—ኢያሱ 23:14
መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? በጥንት ዘመን የነበሩ ጠቢባን የሚናገሯቸው ትንቢቶች የተድበሰበሱና አስተማማኝ ያልሆኑ እንደነበሩ የታወቀ ነው፤ ዘመናዊው ኮኮብ ቆጠራም ቢሆን ከዚህ የተሻለ አይደለም። ፊውቸሮሎጂ ማለትም ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተንተርሶ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ ሙከራ የሚደረግበት መስክም ቢሆን ከዘመናት በኋላ ስለሚፈጸሙ ነገሮች በዝርዝር አይናገርም። ከዚህ በተቃራኒ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ‘ገና የሚመጣውን ከጥንቱ’ የሚናገሩ ቢሆንም እንኳ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚገልጹ ከመሆኑም ሌላ ሁልጊዜ ትክክለኛ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።—ኢሳይያስ 46:10
ምሳሌ፦ በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ዳንኤል የሜዶ ፋርስ መንግሥት በአጭር ጊዜ ውስጥ በግሪክ እጅ እንደሚወድቅ በራእይ ተመልክቶ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ድል አድራጊው የግሪክ ንጉሥ “በኀይሉ በበረታ ጊዜ” መንግሥቱ ‘እንደሚሰበር’ ወይም እንደሚበታተን ተንብዮ ነበር። ታዲያ ማን ይተካዋል? ዳንኤል ‘ከመንግሥቱ አራት መንግሥታት ይወጣሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም’ በማለት ጽፏል።—ዳንኤል 8:5-8, 20-22
የታሪክ ምሁራን ምን ይላሉ? ዳንኤል ከኖረበት ዘመን ከ200 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ታላቁ እስክንድር የግሪክ ንጉሥ ሆነ። እስክንድር በአሥር ዓመታት ውስጥ የሜዶ ፋርስን መንግሥት ድል በመንሳት የግሪክ ግዛት እስከ ኢንደስ ወንዝ (በዘመናችን ፓኪስታን ውስጥ ይገኛል) ድረስ እንዲስፋፋ አደረገ። ይሁንና እስክንድር በ32 ዓመቱ በድንገት ሞተ። በትንሿ እስያ በምትገኘው በኢፕሰስ አቅራቢያ በተደረገ ጦርነት ደግሞ ግዛቱ ተበታተነ። በዚህ ውጊያ ላይ ያሸነፉት አራቱ ድል አድራጊዎች ከጊዜ በኋላ የግሪክን ግዛት ተከፋፈሉት። ይሁንና አንዳቸውም ቢሆኑ የእስክንድርን ያህል ኃያል መሆን አልቻሉም።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የያዛቸው ትንቢቶች ሁልጊዜ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ሊነገርለት የሚችል ሌላ መጽሐፍ አለ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው?
“የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች . . . እጅግ በጣም ብዙ በመሆናቸው ፍጻሜያቸውን ያገኙት በአጋጣሚ ነው ማለት ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው።”—ኤ ሎየር ኤግዛምንስ ዘ ባይብል፣ በኧርወን ሊንተን
-
-
እውነተኛ ታሪክ እንጂ አፈታሪክ አይደለምመጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 1
-
-
እውነተኛ ታሪክ እንጂ አፈታሪክ አይደለም
“ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ [መረመርኩ።]”—ሉቃስ 1:3
መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? አስገራሚ የሆኑ ታሪኮችን የሚያወሱ ተረቶችና አፈታሪኮች ጉዳዩ የተፈጸመበትን ትክክለኛ ቦታና ቀን እንዲሁም በወቅቱ የነበሩ በታሪክ ውስጥ የታወቁ ሰዎችን አይጠቅሱም። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ አኳያ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ ዘገባው “በሙሉ እውነት” እንደሆነ አንባቢዎች እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።—መዝሙር 119:160
ምሳሌ፦ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የባቢሎን ንጉሥ የሆነው “ናቡከደነፆር [የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን] ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው” ይላል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የባቢሎን ንጉሥ የሆነው “ዮርማሮዴቅ [ኤዊልሜሮዳክ] በባቢሎን በነገሠ በዓመቱ ዮአኪንን ከእስራቱ ፈታው።” ዘገባው አክሎም “ንጉሡም ለዮአኪን እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የዕለት ቀለቡን ይሰጠው ነበር” ይላል።—2 ነገሥት 24:11, 15፤ 25:27-30
የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ምን አግኝተዋል? የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በጥንቷ ባቢሎን ፍርስራሾች ውስጥ በዳግማዊ ናቡከደነፆር ዘመን የተዘጋጁ ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ሰነዶችን አግኝተዋል። እነዚህ ሰነዶች በባቢሎን ለሚኖሩ ሠራተኞችና ምርኮኞች ስለሚሰጣቸው ድርሻ የሚገልጹ ዝርዝሮችን ይዘዋል። በዝርዝሩ ውስጥ “የያሁድ (የይሁዳ) ምድር ንጉሥ” የሆነው “ያውኪን [ዮአኪን]” እና ቤተሰቡ ተካትተዋል። ናቡከደነፆርን የተካው ኤዊልሜሮዳክ የሚባል ሰው መኖሩን በተመለከተስ የተገኘ መረጃ አለ? በሱሳ ከተማ አቅራቢያ በተገኘ የአበባ ማስቀመጫ ላይ “የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ልጅ የሆነው የባቢሎን ንጉሥ የአሚል ማርዱክ [የኤዊልሜሮዳክ] ቤተ መንግሥት” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ተገኝቷል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ዝርዝር ጉዳዮችን የሚጠቅሱና ትክክለኛ የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎችን የያዘ ሌላ ጥንታዊ የሃይማኖት መጽሐፍ አለ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ጊዜንና ቦታን የሚጠቅሱት ዘገባዎች ከየትኞቹም ጥንታዊ ጽሑፎች የበለጠ ትክክለኛና እምነት የሚጣልባቸው ናቸው።”—ኤ ሳይንቲፊክ ኢንቨስቲጌሽን ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ በሮበርት ዊልሰን
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን ዮአኪንን የሚጠቅስ የባቢሎናውያን ሰነድ
[ምንጭ]
© bpk, Berlin/Vorderasiatisches Museum, SMB/Olaf M. Tessmer/Art Resource, NY
-
-
ትክክለኛ ሳይንሳዊ ሐሳቦችመጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 1
-
-
ትክክለኛ ሳይንሳዊ ሐሳቦች
“የምክርና የዕውቀት ቃል የሆኑ፣ መልካም ትምህርቶችን አልጻፍሁልህምን? . . . ተገቢውን መልስ ትሰጥ ዘንድ፣ እውነተኛውና የታመኑ ቃሎችን [አላስተማርኩህምን?]”—ምሳሌ 22:20, 21
መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ በጥንታዊ መጻሕፍት ላይ የሚገኙት ሐሳቦች አስተማማኝ ያልሆኑና አደገኛ ናቸው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በጣም የተሳሳቱ መሆናቸው በዘመናዊ ሳይንስ ተረጋግጧል። በዛሬው ጊዜም እንኳ የመማሪያ መጻሕፍትን የሚያዘጋጁ ሰዎች መጻሕፍቱን በቅርቡ ከተገኘ እውቀት ጋር ለማስማማት ሲሉ በየጊዜው ማረም ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ፈጣሪ ሲሆን ቃሉም “ለዘላለም ጸንቶ [እንደሚኖር]” ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—1 ጴጥሮስ 1:25
ምሳሌ፦ የሙሴ ሕግ፣ እስራኤላውያን “ከሰፈር ውጭ” ጉድጓድ ቆፍረው እንዲጸዳዱና በኋላም አፈር እንዲመልሱበት ያዝዝ ነበር። (ዘዳግም 23:12, 13) እስራኤላውያን የእንስሳም ሆነ የሰው በድን ከነኩ በውኃ መታጠብ ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 11:27, 28፤ ዘኍልቍ 19:14-16) የሥጋ ደዌ በሽታ ያለባቸው ሰዎች በሽታቸው ተላላፊ እንዳልሆነ እስኪረጋገጥ ድረስ ተገልለው እንዲቀመጡ ይደረግ ነበር።—ዘሌዋውያን 13:1-8
ዘመናዊው የሕክምና ሳይንስ ምን ያሳያል? ዛሬም ቢሆን ቆሻሻን በተገቢው መንገድ ማስወገድ፣ እጅን መታጠብና የታመሙ ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግ በሽታን ለመከላከል የሚረዱ ውጤታማ ዘዴዎች ናቸው። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ)፣ መጸዳጃ ቤት ወይም ሌላ ቆሻሻ ማስወገጃ መንገድ በሌለበት አካባቢ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ ሲገልጽ “ከማንኛውም የውኃ አካል ቢያንስ 30 ሜትር ርቃችሁ ተጸዳዱ፤ እንዲሁም ዓይነ ምድራችሁን ቅበሩ” ይላል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ ማኅበረሰቦች ዓይነ ምድርን በአግባቡ የሚያስወግዱ ከሆነ በተቅማጥ በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው በ36 በመቶ ይቀንሳል። ሐኪሞች በድን ከነኩ በኋላ እጃቸውን ካልታጠቡ ብዙ ታካሚዎች በበሽታ እንዲጠቁ እንደሚያደርጉ ከተገነዘቡ 200 ዓመት እንኳ አይሞላም። ዛሬም ቢሆን እጅን መታጠብ “በሽታዎች እንዳይዛመቱ ለመከላከል የሚረዳ ከሁሉ የበለጠ ውጤታማ ዘዴ እንደሆነ” ሲዲሲ ይገልጻል። የሥጋ ደዌ ወይም ሌላ ዓይነት በሽታ ያለባቸው ሰዎች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ሳውዲ ሜዲካል ጆርናል የተባለው መጽሔት በቅርቡ እንደገለጸው “ወረርሽኝ እንደጀመረ አካባቢ፣ ይበልጥ እንዳይዛመት ለመቆጣጠር የሚረዳው ብቸኛው ውጤታማ መንገድ የታመሙ ግለሰቦች ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም።”
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ማንኛውም ጥንታዊ የሃይማኖት መጽሐፍ ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ይስማማል ብለህ ትጠብቃለህ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው ትላለህ?
“ማንም ቢሆን በሙሴ ዘመን ንጽሕናን ስለ መጠበቅ የተሰጡትን መመሪያዎች ሲያነብ መደነቁ አይቀርም።”—ማንዋል ኦቭ ትሮፒካል ሜዲሲን፣ በዶክተር አልዶ ካስቴላኒ እና ዶክተር አልበርት ቻልመርዝ
-
-
እርስ በርስ የሚስማሙ መጻሕፍትመጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 1
-
-
እርስ በርስ የሚስማሙ መጻሕፍት
“መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣም፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ።”—2 ጴጥሮስ 1:21
መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? በጥንት ዘመን የተዘጋጁ ጽሑፎች የተጻፉት በተመሳሳይ ወቅት ቢሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ ይጋጫሉ። በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ወቅትና ቦታ የተጻፉ መጻሕፍት ደግሞ እርስ በርስ የመስማማታቸው አጋጣሚ እጅግ ጠባብ ነው። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የሚገኙትን 66 መጻሕፍት ያስጻፋቸው አንድ አካል እንደሆነ ይገልጻል፤ በመሆኑም እነዚህ መጻሕፍት እርስ በርስ የሚስማሙ ከመሆናቸውም ሌላ ስለ አንድ ዓይነት መልእክት ይናገራሉ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ምሳሌ፦ በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የኖረ ሙሴ የተባለ እረኛ፣ የሰው ልጆችን የሚያድን “ዘር” እንደሚመጣ በመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ መጽሐፍ ላይ ጽፎ ነበር። ይህ ዘር ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ የትውልድ ሐረግ እንደሚመጣ ቆየት ብሎ በዚሁ መጽሐፍ ላይ ተተንብዮ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:17, 18፤ 26:24፤ 28:14) ከ500 ዓመታት በኋላ ነቢዩ ናታን፣ ዘሩ ከንጉሥ ዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ ገለጸ። (2 ሳሙኤል 7:12) ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ዘሩ ኢየሱስንና የተመረጡ ተከታዮቹን ያቀፈ እንደሚሆን አብራራ። (ሮም 1:1-4፤ ገላትያ 3:16, 29) በመጨረሻም የዚህ ዘር አባላት ስለ ኢየሱስ በምድር ላይ እንደሚመሠክሩ፣ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ እንዲሁም ከእሱ ጋር ለ1,000 ዓመት እንደሚገዙ የሚናገር ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ላይ ተጻፈ፤ ይህ ትንቢት የተነገረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ነበር። ኢየሱስንና የተመረጡ ተከታዮቹን ያቀፈው ይህ ዘር ዲያብሎስን ያጠፋል፤ እንዲሁም የሰው ልጆችን ያድናል።—ራእይ 12:17፤ 20:6-10
የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ምን ይላሉ? ልዊ ጎሴን የተባሉ ምሁር 66ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሚገባ ከመረመሩ በኋላ “በአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ውስጥ በበርካታ ሰዎች የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ያለው የሚያስገርም ስምምነት” በጣም እንዳስደነቃቸው ጽፈዋል፤ አክለውም ‘ጸሐፊዎቹ የአምላክ ልጅ ዓለምን እንዴት እንደሚቤዥ የሚገልጸውን ታሪክ ሙሉ በሙሉ ባይረዱትም ተመሳሳይ ዓላማ ለማሳካት ያለማሰለስ ጥረት አድርገዋል’ ብለዋል።—ቴአፕኑስቲ—ዘ ፕሌናሪ ኢንስፓይሬሽን ኦቭ ዘ ሆሊ ስክሪፕቸርስ
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከ1,500 በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ 40 በሚያህሉ ሰዎች የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እርስ በርሱ ይስማማል ብለህ ትጠብቃለህ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው ትላለህ?
“ይህ መጽሐፍ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ድረስ እርስ በርስ ስምምነት ያለው እንደሆነ ይሰማናል። . . . ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ይህን መጽሐፍ ሊወዳደር ቀርቶ ሊጠጋ እንኳ የሚችል ጽሑፍ የለም።”—ዘ ፕሮብሌም ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ በጄምስ ኦር
-
-
ለዘመናችንም የሚጠቅምመጠበቂያ ግንብ—2012 | ሰኔ 1
-
-
ለዘመናችንም የሚጠቅም
“ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።”—መዝሙር 119:105
መጽሐፍ ቅዱስን የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? አንዳንድ ጽሑፎች ግሩም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ይሆናል፤ ሕይወታችንን ለመምራት የሚረዳ አስተማማኝ መመሪያ ግን ሊሰጡን አይችሉም። በዘመናችን የሚዘጋጁ ስለ አንድ ነገር አሠራር የሚገልጹ መመሪያዎችም በየጊዜው መታረም ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ በውስጡ ስለያዘው ሐሳብ ሲናገር “ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል” ይላል።—ሮም 15:4
ምሳሌ፦ መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ጤንነታችንን ለመጠበቅ የሚያስችሉን ጠቃሚ ሐሳቦች ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ይላል። (ምሳሌ 14:30) እንዲሁም “ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 18:1) በሌላ በኩል ደግሞ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ይናገራል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
የምርምር ውጤቶች ምን ያሳያሉ? ውስጣዊ ሰላም፣ ጠንካራ ወዳጅነት እንዲሁም ለጋስነት የተሻለ ጤንነት እንዲኖርህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን እንዲህ ይላል፦ “ቁጣቸውን ከሚቆጣጠሩ ወንዶች ጋር ሲነጻጸሩ በቁጣ የመገንፈል ችግር ያለባቸው ወንዶች በአንጎላቸው ውስጥ ደም በመፍሰሱ ለሕመም የመጋለጣቸው አጋጣሚ በሁለት እጥፍ ከፍ ያለ ነው።” በአውስትራሊያ ለአሥር ዓመት የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው “ከወዳጆቻቸውና ሚስጥራቸውን ከሚያካፍሏቸው ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው” አረጋውያን ረዘም ያለ ዕድሜ ይኖራሉ። በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ተመራማሪዎች ደግሞ በ2008 ባካሄዱት ጥናት “ገንዘብን ራስን ለማስደሰት ከማዋል ይልቅ ሌሎችን ለመጥቀም ማዋሉ የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ” አረጋግጠዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ተጽፎ ካለቀ ወደ 2,000 የሚጠጉ ዓመታት ያለፉት ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ በጤና ጉዳይ ላይ የሚሰጠውን ምክር እምነት ልትጥልበት ትችላለህ? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው ትላለህ?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“መጽሐፍ ቅዱስ በጣም ይማርከኛል፤ . . . ምክንያቱም ከጤና ጋር የተያያዙ ግሩም ምክሮችን ይሰጣል።”—ሃዋርድ ኬሊ፣ የሕክምና ዶክተር፣ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ክፍል መሥራች አባል
-