-
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት እምነት ልትጥልባቸው ትችላለህ?መጠበቂያ ግንብ—2012 | ነሐሴ 1
-
-
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት እምነት ልትጥልባቸው ትችላለህ?
አንድ ሰው አስደናቂ የሆነ ታሪክ ቢነግርህ ግለሰቡ እምነት የሚጣልበት መሆን አለመሆኑ ታሪኩን በማመንህ ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም? ግለሰቡ፣ ታሪኩን የተረከበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ከዚያ ቀደም እውነት በመናገር ረገድ ያተረፈው ስምም እሱን እንድታምነው ወይም እንዳታምነው ሊያደርግህ ይችላል። ይህ ግለሰብ እስከ ዛሬ እውነት ብቻ ይነግርህ ከነበረና ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃ ሰጥቶህ የማያውቅ ከሆነ አሁን የነገረህን ታሪክ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለህ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተአምራት በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ተአምራት በተፈጸሙበት ወቅት ማናችንም በሕይወት አልነበርንም። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እምነት የሚጣልባቸውና እውነተኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንችላለን። እንዴት? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ስለ ተአምራት የሚናገሩ ዘገባዎች እምነት እንድንጥልባቸው የሚያደርጉ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት።
ብዙዎቹ ተአምራት የተፈጸሙት በርካታ እማኞች ባሉበት ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ተአምራት ሲፈጸሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተመልክተዋል። (ዘፀአት 14:21-31፤ 19:16-19) እነዚህ ተአምራት የተፈጸሙት ከሕዝብ እይታ ተሰውረው ወይም በድብቅ አልነበረም።
ተአምራቱ የተፈጸሙት በማያደናግርና ግልጽ በሆነ መንገድ ነበር። ተአምራቱን ለመፈጸም ለየት ያሉ ቁሳቁሶችን ወይም ማታለያዎችን መጠቀም አላስፈለገም፤ አሊያም ትኩረት ለመሳብ የሚደረጉ የተጋነኑ ነገሮች አልነበሩም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት አብዛኞቹ ተአምራት የተፈጸሙት ግለሰቦቹ ተአምሩን ከፈጸመው ሰው ጋር በአጋጣሚ በመገናኘታቸውና እርዳታ እንዲደረግላቸው በመጠየቃቸው ነው። (ማርቆስ 5:25-29፤ ሉቃስ 7:11-16) በእነዚህ ወቅቶች ተአምራቱን የፈጸመው ሰው አስቀድሞ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ሊሆን አይችልም።
ተአምራቱን የፈጸሙት ግለሰቦች ዓላማቸው ዝና፣ ክብር እንዲሁም ሀብት ማግኘት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህን ያደረጉት ለአምላክ ክብር ለማምጣት ነበር። (ዮሐንስ 11:1-4, 15, 40) እንዲያውም በተአምራዊ ክንውኖች አሳብበው ለራሳቸው ሀብት ለማካበት የሞከሩ ግለሰቦች ተወግዘዋል።—2 ነገሥት 5:15, 16, 20, 25-27፤ የሐዋርያት ሥራ 8:18-23
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ተአምራት ዓይነታቸው ብዙ መሆኑ በሰው ኃይል ብቻ ሊከናወኑ እንደማይችሉ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ በማዕበል የሚናወጥ ባሕር ጸጥ ብሏል፤ ውኃ ወደ ወይን ተቀይሯል፤ ዝናብ እንዲጠፋና መዝነብ እንዲጀምር ተደርጓል፤ በሽተኞች ተፈውሰዋል እንዲሁም ዓይነ ስውር የሆኑ ሰዎች ማየት ችለዋል።—1 ነገሥት 17:1-7፤ 18:41-45፤ ማቴዎስ 8:24-27፤ ሉቃስ 17:11-19፤ ዮሐንስ 2:1-11፤ 9:1-7
ተአምራቱ በተፈጸሙበት ወቅት የነበሩ ተቃዋሚዎች እንኳ ተአምራቱን አልካዱም። ኢየሱስ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት ወቅት ተቃዋሚዎቹ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች አልዓዛር ሞቶ የነበረ መሆኑን አላስተባበሉም። ደግሞስ እንዴት ይህን ማድረግ ይችላሉ? አልዓዛር አራት ቀናት በመቃብር ውስጥ ቆይቷል። (ዮሐንስ 11:45-48፤ 12:9-11) ኢየሱስ ከሞተ ከበርካታ ዘመናት በኋላ እንኳ የአይሁድ ታልሙድ ጸሐፊዎች ኢየሱስ ተአምር የመፈጸም ችሎታ እንደነበረው ያምኑ ነበር። የእነሱ ጥያቄ ‘ይህን ችሎታ ያገኘው ከየት ነው?’ የሚል ነበር። በተመሳሳይም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ ሸንጎ ፊት በቀረቡበት ወቅት “ተአምር ፈጽማችኋል?” የሚል ጥያቄ አልቀረበላቸውም። ከዚህ ይልቅ የተጠየቁት “ይህን ያደረጋችሁት በምን ሥልጣን ወይም በማን ስም ነው?” ተብለው ነው።—የሐዋርያት ሥራ 4:1-13
ታዲያ ስለ ተአምራት በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ? እስካሁን ከተመለከትነው አንጻር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ስለ ተአምራት የሚገልጹ ዘገባዎች እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህን ዘገባዎች እንድናምንባቸው የሚያደርጉን ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ተአምር እንደተፈጸመ ሲናገር ጊዜውን፣ ቦታውንና የግለሰቦቹን ስም መጥቀሱ የተለመደ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች እንኳ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር የሆኑ ታሪካዊ መረጃዎች ትክክለኝነት ያስደንቃቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንድም ሳይቀር በትክክል ተፈጽመዋል። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከሰዎች ጋር አስደሳች ግንኙነት ለመመሥረት የሚያስችሉን በርካታ ምክሮችን የያዘ ሲሆን ይህም በየትኛውም የዕድሜ ክልልና በማንኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ጠቅሟቸዋል። ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ተወዳዳሪ የለውም።
አሁንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንደማትችል ከተሰማህ ይህን መጽሐፍ ይበልጥ ለመመርመር ለምን ጊዜ አትመድብም? ይበልጥ ባወቅኸው መጠን ይበልጥ እምነት እየጣልክበት ትሄዳለህ። (ዮሐንስ 17:17) ባለፉት ዘመናት ስለተፈጸሙት ተአምራት በሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እምነት ልትጥል እንደምትችልም ትገነዘባለህ። በእነዚህ ዘገባዎች ላይ እምነት ስታዳብር ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ እንደሚፈጸሙ በሚናገራቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል በቂ ምክንያት ይኖርሃል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ተቃዋሚዎች አልዓዛር ሞቶ የነበረ መሆኑን አላስተባበሉም
-
-
በቅርቡ የሚፈጸሙ ተአምራትመጠበቂያ ግንብ—2012 | ነሐሴ 1
-
-
በቅርቡ የሚፈጸሙ ተአምራት
አንድ ሐኪም ከባድ ቀዶ ሕክምና ሊያደርግልህ ቀጠሮ ይዘሃል እንበል፤ ይህ ሐኪም ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ቀዶ ሕክምና አድርጎ እንደማያውቅ ብትገነዘብ ምን ይሰማሃል? ሁኔታው እንደሚያሳስብህ ጥያቄ የለውም። በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ሐኪም በሙያው አንቱ የተባለ ሰው እንደሆነና ለአንተ ከሚያደርግልህ ጋር የሚመሳሰሉ በርካታ ቀዶ ጥገናዎችን በተሳካ ሁኔታ እንዳከናወነ ብታውቅ ምን ይሰማሃል? ይህ ሐኪም ሊረዳህ እንደሚችል ይበልጥ አትተማመንም?
የምንኖርበት ዓለም እንደታመመ ሰው ስለሆነ ከባድ “ቀዶ ጥገና” ያስፈልገዋል። በመሆኑም ይሖዋ አምላክ፣ ምድርን እንደገና ገነት እንደሚያደርጋት በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተስፋ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ይህ እንዲሆን ግን ክፋት ሙሉ በሙሉ መወገድ አለበት። (መዝሙር 37:9-11፤ ምሳሌ 2:21, 22) ምድር እንደገና ገነት ከመሆኗ በፊት በዙሪያችን የምናያቸው መጥፎ ነገሮች በሙሉ መጥፋት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቃል በቃል ተአምር ያስፈልጋል ማለት ይቻላል!—ራእይ 21:4, 5
የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለው መጠነ ሰፊ ለውጥ በቅርቡ እንደሚከናወን ያምናሉ። እንዲህ ያለ እምነት ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው? ይሖዋ አምላክ ከዚህ በፊት የፈጸማቸው ተአምራት ስለ ወደፊቱ ጊዜ የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል እንዳለው ስለሚያረጋግጡ ነው። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት ተአምራት መካከል ስድስቱን ወደፊት እንደሚፈጸሙ ከተነገሩ ተስፋዎች ጋር እናወዳድር።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊት ሕይወታችን የሚሰጣቸውን ተስፋዎች መማርህን እንድትቀጥል እናበረታታሃለን። እምነትህ እያደገ በሄደ መጠን ይሖዋ ከሚፈጽማቸው ተአምራት በግለሰብ ደረጃ ጥቅም የምታገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ያለህ ተስፋም ይጠናከራል።
[በገጽ 9 እና 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተአምር፦
ኢየሱስ በጥቂት ዳቦና ዓሣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መግቧል።—ማቴዎስ 14:13-21፤ ማርቆስ 8:1-9፤ ዮሐንስ 6:1-14
ተስፋ፦
“ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤ እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል።”—መዝሙር 67:6
ለእኛ ያለው ትርጉም፦
ማንም ሰው በረሃብ አይጠቃም።
ተአምር፦
ኢየሱስ ዓይነ ስውራንን ፈውሷል።—ማቴዎስ 9:27-31፤ ማርቆስ 8:22-26
ተስፋ፦
“የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ።”—ኢሳይያስ 35:5
ለእኛ ያለው ትርጉም፦
ዓይነ ስውራን ሁሉ ማየት ይችላሉ።
ተአምር፦
ኢየሱስ የአካል ጉዳተኞችን ፈውሷል።—ማቴዎስ 11:5, 6፤ ዮሐንስ 5:3-9
ተስፋ፦
“አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል።”—ኢሳይያስ 35:6
ለእኛ ያለው ትርጉም፦
የአካል ጉዳተኞች በሙሉ ይፈወሳሉ።
ተአምር፦
ኢየሱስ የተለያየ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ፈውሷል።—ማርቆስ 1:32-34፤ ሉቃስ 4:40
ተስፋ፦
“‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24
ለእኛ ያለው ትርጉም፦
ማንኛውም ዓይነት በሽታ ይወገዳል። ፍጹም ጤንነት ይኖረናል።
ተአምር፦
ኢየሱስ የተፈጥሮ ኃይሎችን ተቆጣጥሯል።—ማቴዎስ 8:23-27፤ ሉቃስ 8:22-25
ተስፋ፦
“ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ድካማቸው በከንቱ አይቀርም።”—ኢሳይያስ 65:21, 23
“ሕዝቤ ሰላማዊ በሆነ መኖሪያ፣ በሚያስተማምን ቤት፣ ጸጥ ባለም ስፍራ ዐርፎ ይኖራል።”—ኢሳይያስ 32:18
ለእኛ ያለው ትርጉም፦
የተፈጥሮ አደጋዎች አይኖሩም።
ተአምር፦
ኢየሱስ ሙታንን አስነስቷል።—ማቴዎስ 9:18-26፤ ሉቃስ 7:11-17
ተስፋ፦
“በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ።”—ዮሐንስ 5:28, 29
“ባሕርም በውስጡ ያሉትን ሙታን ሰጠ፤ ሞትና ሔዲስም በውስጣቸው ያሉትን ሙታን ሰጡ።”—ራእይ 20:13
ለእኛ ያለው ትርጉም፦
በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ይነሳሉ።
-