-
አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
-
-
ምዕራፍ ሦስት
አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
አምላክ ለሰው ዘር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
አምላክ ተቃውሞ የደረሰበት እንዴት ነው?
በምድር ላይ ያለው ሕይወት ወደፊት ምን መልክ ይኖረዋል?
1. አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ በጣም አስደሳች ነው። ይሖዋ ምድር ደስተኛና ጤናማ በሆኑ ሰዎች እንድትሞላ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ በዔድን የአትክልት ስፍራ እንዳዘጋጀ’ እና “ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ” እንዳበቀለ ይናገራል። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ በዚያች ውብ መኖሪያ ውስጥ በማስቀመጥ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” አላቸው። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 9, 15) ስለዚህ የአምላክ ዓላማ ሰዎች ልጆችን እንዲወልዱ፣ መኖሪያቸው የሆነችውን ገነት በመላዋ ምድር ላይ እንዲያስፋፉና እንስሳትን እንዲንከባከቡ ነበር።
2. (ሀ) አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም እንዴት እናውቃለን? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ለዘላለም የሚኖሩት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?
2 ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ እንዲኖሩ ያለው ዓላማ ይፈጸማል የሚል እምነት አለህ? አምላክ “የተናገርሁትን . . . እፈጽማለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:9-11፤ 55:11) አዎን፣ አምላክ ዓላማውን እንደሚፈጽም የተረጋገጠ ነው! ‘ምድርን የፈጠራት መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ እንዳልሆነ’ ገልጿል። (ኢሳይያስ 45:18 የ1954 ትርጉም) አምላክ በምድር ላይ እንዲኖሩ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? ለምን ያህል ጊዜስ እንዲኖሩ ይፈልጋል? መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል መልስ ይሰጣል።—መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4
3. በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ምን አሳዛኝ ሁኔታ ይታያል? ይህስ ምን ጥያቄዎች ያስነሳል?
3 እርግጥ ነው፣ ይህ ገና አልተፈጸመም። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ይታመማሉ እንዲሁም ይሞታሉ፤ አልፎ ተርፎም እርስ በርስ ይጋጫሉ ብሎም ይገዳደላሉ። በመሆኑም አንድ የተፈጠረ ችግር አለ። ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማ አሁን በምድር ላይ ከሚታየው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው! ታዲያ የተፈጠረው ችግር ምንድን ነው? የአምላክ ዓላማ ያልተፈጸመው ለምንድን ነው? ችግሩ የተጠነሰሰው በሰማይ በመሆኑ የትኛውም በሰው ልጆች የተጻፈ የታሪክ መጽሐፍ መልሱን ሊሰጠን አይችልም።
አንድ ጠላት ተነሳ
4, 5. (ሀ) በእባብ አማካኝነት ሔዋንን ያነጋገራት ማን ነው? (ለ) ቀደም ሲል ጨዋና ሐቀኛ የነበረ ሰው ሌባ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያው መጽሐፍ በኤደን የአትክልት ሥፍራ አንድ ተቃዋሚ ብቅ እንዳለ ይገልጽልናል። ይህ ተቃዋሚ “እባብ” ተብሎ የተገለጸ ቢሆንም እንስሳ አይደለም። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ “ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው” ሲል ይገልጸዋል። “የጥንቱ እባብ” ተብሎም ተጠርቷል። (ዘፍጥረት 3:1፤ ራእይ 12:9) ጥሩ ችሎታ ያለው አንድ ሰው አሻንጉሊት እየተናገረ እንዳለ በማስመሰል መናገር እንደሚችል ሁሉ ይህ ኃይለኛ መልአክ ወይም የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡርም ሔዋንን ለማነጋገር አንድን እባብ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሟል። ይህ መንፈሳዊ ፍጡር፣ አምላክ ምድርን ለሰው ልጆች ባዘጋጀበት ወቅት እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢዮብ 38:4, 7
5 ይሁን እንጂ የይሖዋ ፍጥረታት በሙሉ ፍጹማን በመሆናቸው ‘ዲያብሎስን’ ወይም ‘ሰይጣንን’ የፈጠረው ማን ነው? በአጭር አነጋገር ከአምላክ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ ራሱን ለውጦ ዲያብሎስ ሆነ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በአንድ ወቅት ጨዋና ሐቀኛ የነበረ ሰው ተለውጦ ሌባ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይኖርብናል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ግለሰቡ በልቡ ውስጥ መጥፎ ምኞት እንዲጸነስ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚያ ነገር ማሰቡን ከቀጠለ መጥፎው ምኞት እያየለ ይሄዳል። ከዚያም ሁኔታው ከተመቻቸለት ሲያስበው የቆየውን መጥፎ ምኞት ወደ ተግባር ሊለውጠው ይችላል።—ያዕቆብ 1:13-15
6. አንድ ኃያል የሆነ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ሰይጣን ዲያብሎስ የሆነው እንዴት ነው?
6 በሰይጣን ዲያብሎስ ላይም የደረሰው ሁኔታ ይኸው ነው። አምላክ አዳምና ሔዋንን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን በዘሮቻቸው እንዲሞሉ ሲነግራቸው ሰይጣን ሳይሰማ አልቀረም። (ዘፍጥረት 1:27, 28) ‘እነዚህ ሁሉ ሰዎች እኮ አምላክን በማምለክ ፋንታ እኔን ሊያመልኩ ይችላሉ’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መጥፎ ምኞት በውስጡ ተጸነሰ። በመጨረሻም ይህን ምኞቱን ወደ ተግባር በመለወጥ ስለ አምላክ ውሸት ተናግሮ ሔዋንን አታለላት። (ዘፍጥረት 3:1-5) በዚህ መንገድ “ዲያብሎስ” ይኸውም “ስም አጥፊ” እንዲሁም “ሰይጣን” ማለትም “ተቃዋሚ” ሆነ።
7. (ሀ) አዳምና ሔዋን የሞቱት ለምንድን ነው? (ለ) የአዳም ዘሮች በሙሉ የሚያረጁትና የሚሞቱት ለምንድን ነው?
7 ሰይጣን ዲያብሎስ በመዋሸትና በማታለል አዳምና ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ አደረጋቸው። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:6) በዚህም ምክንያት አምላክ ትእዛዙን ከጣሱ ሞት እንደሚጠብቃቸው በነገራቸው መሠረት ከጊዜ በኋላ ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:17-19) አዳም ኃጢአት በሠራበት ጊዜ ፍጽምና ስለጎደለው ለዘሮቹ በሙሉ ኃጢአትን አውርሷል። (ሮሜ 5:12) ይህን ሁኔታ ለማስረዳት እንጀራ ለመጋገር የሚያገለግል ምጣድ እንደ ምሳሌ መጠቀም ይቻላል። ምጣዱ ስንጥቅ ካለው በምጣዱ ላይ የሚጋገረው እንጀራ ሁሉ ምን ይኖረዋል? እያንዳንዱ እንጀራ በምጣዱ ላይ ያለውን ስንጥቅ ወይም እንከን ይዞ ይወጣል። በተመሳሳይም እያንዳንዱ ሰው ከአዳም አለፍጽምናን ወርሷል። ሁሉም ሰው የሚያረጀውና የሚሞተው በዚህ ምክንያት ነው።—ሮሜ 3:23
8, 9. (ሀ) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሰይጣን ምን የሚል ተቃውሞ አስነስቷል? (ለ) አምላክ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ያላጠፋቸው ለምንድን ነው?
8 ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት እንዲሠሩ በገፋፋቸው ጊዜ ዓመጽ እያነሳሳ ነበር። ይሖዋ የሚገዛበትን መንገድ መቃወሙ ነበር። በመሆኑም ሰይጣን በተዘዋዋሪ መንገድ ‘አምላክ ክፉ ገዥ ነው። ውሸት የሚናገር ከመሆኑም በላይ ተገዥዎቹን ጥሩ ነገር ይከለክላቸዋል። ሰዎች ለአምላክ መገዛት አያስፈልጋቸውም። ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር በራሳቸው መወሰን ይችላሉ። በእኔ አገዛዝ ሥር ቢሆኑ ደግሞ የተሻለ ጥቅም ያገኛሉ’ ማለቱ ነበር። አምላክ እንዲህ ላለው ስድብ ያዘለ ውንጀላ ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? አንዳንዶች፣ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ማጥፋት ነበረበት ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ ሰይጣን ላስነሳው ተቃውሞ ጥሩ ምላሽ ይሆናል? የአምላክ አገዛዝ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል?
9 ይሖዋ ፍጹም የሆነ የፍትሕ ባሕርይ ያለው አምላክ በመሆኑ ዓመጸኞቹን ወዲያውኑ ሊያጠፋቸው አይችልም። ሰይጣን ላስነሳው ተቃውሞ አጥጋቢ የሆነ ምላሽ ለመስጠትና ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ተሰምቶታል። ስለሆነም አምላክ የሰው ልጆች ለተወሰነ ጊዜ በሰይጣን ተጽዕኖ ሥር ሆነው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ፈቀደላቸው። ይሖዋ ይህን ያደረገበት ምክንያትና ለእነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት ሳይሰጥ ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያልፍ የፈቀደበት ምክንያት በዚህ መጽሐፍ 11ኛ ምዕራፍ ላይ ይብራራል። ይሁን እንጂ አሁን እንደሚከተለው ብለን ማሰባችን ተገቢ ነው:- አዳምና ሔዋን ምንም ዓይነት መልካም ነገር አድርጎላቸው የማያውቀውን ሰይጣንን ማመናቸው ትክክል ነው? ሁሉን ነገር የሰጣቸው ፈጣሪያቸው ይሖዋ ጨካኝና ውሸታም ነው ብለው ማመናቸው ትክክል ነው? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?
10. ለሰይጣን ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ከይሖዋ ጎን መቆም የምትችለው እንዴት ነው?
10 በዛሬው ጊዜ በእያንዳንዳችን ፊት ተመሳሳይ የሆኑ አከራካሪ ጉዳዮች ስለሚደቀኑ እነዚህን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል። አዎን፣ ለሰይጣን ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ከይሖዋ ጎን መቆምህን ማሳየት የምትችልበት አጋጣሚ አለህ። ይሖዋን ገዥህ አድርገህ መቀበልና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ማሳየት ትችላለህ። (መዝሙር 73:28፤ ምሳሌ 27:11) የሚያሳዝነው ግን በዚህ ዓለም ላይ ካሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል እንዲህ ያለውን ምርጫ የሚያደርጉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ እንደሆነ ያስተምራል? የሚል አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ ያስነሳል።
ይህን ዓለም የሚገዛው ማን ነው?
ሰይጣን የዓለም መንግሥታት በሙሉ የእሱ ባይሆኑ ኖሮ ለኢየሱስ ለመስጠት እንዴት ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል?
11, 12. (ሀ) በኢየሱስ ላይ የደረሰው ፈተና ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑን የሚያሳይ ምን ሌላ ማስረጃ አለ?
11 ኢየሱስ የዚህ ዓለም ገዥ ሰይጣን መሆኑን ተጠራጥሮ አያውቅም። በአንድ ወቅት ሰይጣን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለኢየሱስ ‘የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው’ አሳይቶት ነበር። ከዚያም ሰይጣን “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” ሲል ቃል ገባለት። (ማቴዎስ 4:8, 9፤ ሉቃስ 4:5, 6) እስቲ አስበው። ሰይጣን የእነዚህ መንግሥታት ገዥ ባይሆን ኖሮ ይህ ግብዣ ለኢየሱስ ፈተና ይሆንበት ነበር? ኢየሱስ እነዚህ ሁሉ የዓለም መንግሥታት የሰይጣን መሆናቸውን አልካደም። ገዥያቸው ሰይጣን ባይሆን ኖሮ ኢየሱስ ይህን ከመናገር ወደኋላ አይልም ነበር።
12 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክና ዕጹብ ድንቅ የሆነው ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ ነው። (ራእይ 4:11) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ ላይ ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ዓለም ገዥ እንደሆኑ አይናገርም። እንዲያውም ኢየሱስ በቀጥታ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11) አልፎ ተርፎም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስን “የዚህ ዓለም አምላክ” ሲል ይጠራዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4) ይህን ተቃዋሚ ወይም ሰይጣንን በተመለከተ ክርስቲያኑ ሐዋርያ ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር ነው’ ሲል ጽፏል።—1 ዮሐንስ 5:19
የሰይጣን ዓለም የሚወገደው እንዴት ነው?
13. አዲስ ዓለም መምጣቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ዓመት አልፎ ዓመት በተተካ ቁጥር ይህ ዓለም ለሕይወት ይበልጥ አስጊ እየሆነ መጥቷል። በጦርነት በሚፋጁ ሠራዊቶች፣ አጭበርባሪ በሆኑ ፖለቲከኞች፣ ግብዝ በሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ርኅራኄ በሌላቸው ወንጀለኞች ተሞልቷል። ዓለም በአጠቃላይ ሊለወጥና ሊስተካከል ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፉውን ዓለም በአርማጌዶን ጦርነት የሚያጠፋበት ጊዜ እንደተቃረበ ይገልጻል። በዚያን ጊዜ ይህ ዓለም ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ይተካል።—ራእይ 16:14-16
14. አምላክ የመንግሥቱ ገዥ እንዲሆን የመረጠው ማንን ነው? ይህስ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነው?
14 ይሖዋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን የሰማያዊ መንግሥቱ ወይም መስተዳድሩ ገዥ እንዲሆን መርጦታል። መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዓመታት በፊት “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም . . . የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም” ሲል ተንብዮ ነበር። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ይህን መንግሥት በተመለከተ ኢየሱስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:10) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት እንደምንመለከተው የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የዚህን ዓለም መንግሥታት በሙሉ በማጥፋት በእነሱ ቦታ ይተካል። (ዳንኤል 2:44) ከዚያም ምድርን ገነት ያደርጋል።
አዲስ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!
15. ‘አዲሱ ምድር’ ምንድን ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን” ሲል ዋስትና ይሰጠናል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ኢሳይያስ 65:17) አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር” የሚለውን ቃል የሚጠቀመው በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ለማመልከት ነው። (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም) ስለዚህ ጻድቁ “አዲስ ምድር” የአምላክን ሞገስ የሚያገኘውን ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ያመለክታል።
16. አምላክ በእሱ ፊት ተቀባይነት ለሚያገኙ ሰዎች የሚሰጠው እጅግ ውድ የሆነ ስጦታ ምንድን ነው? ይህን ስጦታ ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 ኢየሱስ በመጪው አዲስ ዓለም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሁሉ “የዘላለም ሕይወት” ስጦታን እንደሚቀበሉ ቃል ገብቷል። (ማርቆስ 10:30) እባክህ ዮሐንስ 3:16ንና 17:3ን አውጣና ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን የተናገረውን ሐሳብ አንብብ። አሁን ደግሞ በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ ይህን አስደሳች የሆነ የአምላክ ስጦታ ለመቀበል ብቁ የሆኑ ሰዎች የሚያገኟቸውን በረከቶች በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት።
17, 18. በየትኛውም የምድር ክፍል ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ እንደሚሰፍን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
17 ክፋት፣ ጦርነት፣ ወንጀልና ዓመጽ ይወገዳሉ። “ክፉ ሰው አይዘልቅም . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ።” (መዝሙር 37:10, 11) አምላክ ‘ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ስለሚያስወግድ’ ሰላም ይሰፍናል። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 2:4) ከዚያም “ጽድቅ ይሰፍናል፤ ጨረቃ ከስፍራዋ እስከምትታጣ ድረስም [ለዘላለም] ሰላም ይበዛል።”—መዝሙር 72:7
18 የይሖዋ አምላኪዎች በተረጋጋ ሁኔታ ይኖራሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት እስራኤላውያን አምላክን እስከታዘዙ ድረስ በተረጋጋ ሁኔታ ይኖሩ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:18, 19) በገነት ውስጥም ተመሳሳይ በሆነ የተረጋጋ ሁኔታ መኖር መቻል ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ኢሳይያስ 32:18፤ ሚክያስ 4:4
19. በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ምግብ እንደሚትረፈረፍ እንዴት እናውቃለን?
19 የምግብ እጥረት አይኖርም። መዝሙራዊው “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 72:16) ይሖዋ አምላክ የእርሱ የሆኑትን ጻድቃን ይባርካል፤ ‘ምድርም ፍሬዋን ትሰጣለች።’—መዝሙር 67:6
20. መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
20 መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። በአንድ ወቅት ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ያበላሿት ምድር ውብ በሆኑ አዳዲስ ቤቶችና የአትክልት ሥፍራዎች ትሞላለች። (ኢሳይያስ 65:21-24፤ ራእይ 11:18) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሰዎች የሚኖሩባቸው የምድር ክፍሎች እየተስፋፉ ስለሚሄዱ መላዋ ምድር እንደ ኤደን ገነት ውብና ፍሬያማ ትሆናለች። በተጨማሪም አምላክ ‘እጁን በመዘርጋት የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት ያረካል።’—መዝሙር 145:16
21. በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም እንደሚሰፍን የሚያሳየው ምንድን ነው?
21 በሰዎችና በእንስሳት መካከል ሰላም ይሰፍናል። የዱርና የቤት እንስሳት በአንድነት ይመገባሉ። በአሁኑ ጊዜ አደገኛ የሆኑትን እንስሳት በዚያን ጊዜ ሕፃን ልጅ እንኳ አይፈራቸውም።—ኢሳይያስ 11:6-9፤ 65:25
22. በሽታ ምን ይሆናል?
22 በሽታ ይጠፋል። ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ገዥ ሆኖ የሚያከናውነው ፈውስ ምድር ሳለ ካከናወነው ፈውስ ይበልጥ መጠነ ሰፊ ይሆናል። (ማቴዎስ 9:35፤ ማርቆስ 1:40-42፤ ዮሐንስ 5:5-9) በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6
23. ትንሣኤ ልባችን በሐሴት እንዲሞላ የሚያደርገው ለምንድን ነው?
23 በሞት ያጣናቸው ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይዘው ከሞት ይነሳሉ። በሞት አንቀላፍተው የሚገኙና አምላክ የሚያስባቸው ሰዎች ሁሉ ዳግም ሕያው ይሆናሉ። እንዲያውም ‘ጻድቃንም ኀጥአንም ከሙታን ይነሣሉ።’—የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ ዮሐንስ 5:28, 29
24. በምድር ላይ በገነት ስለ መኖር ስታስብ ምን ይሰማሃል?
24 ስለ ታላቁ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ አምላክ ለመማርና እሱን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ የሚያደርጉ ሁሉ አስደሳች ጊዜ ይጠብቃቸዋል! ኢየሱስ ከጎኑ ለተሰቀለው ክፉ አድራጊ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎ ቃል በገባለት ጊዜ የተናገረው ስለመጪዋ ምድራዊ ገነት ነበር። (ሉቃስ 23:43) እነዚህን ሁሉ በረከቶች ማግኘት የምንችልበትን በር ስለከፈተልን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይበልጥ መማራችን በጣም አስፈላጊ ነው።
-
-
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
-
-
ምዕራፍ ስምንት
የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት ምን ያስተምረናል?
የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?
ይህ መንግሥት የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርገው መቼ ነው?
1. አሁን የምንመረምረው የትኛውን የታወቀ ጸሎት ነው?
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ብዙዎች የጌታ ጸሎት ወይም አቡነ ዘበሰማያት ብለው የሚጠሩትን ጸሎት በሚገባ ያውቁታል። ሁለቱም መጠሪያዎች ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ናሙና አድርጎ የሰጠውን የታወቀ ጸሎት የሚያመለክቱ ናቸው። ይህ ጸሎት ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሐሳቦችን የያዘ ሲሆን በዚህ ጸሎት ውስጥ የተገለጹትን የመጀመሪያዎቹን ሦስት ልመናዎች መመርመርህ ትክክለኛ የሆነ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንድታገኝ ይረዳሃል።
2. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በጸሎታቸው ውስጥ እንዲጠቅሷቸው ካስተማራቸው ነገሮች መካከል ሦስቱ ምንድን ናቸው?
2 ኢየሱስ በዚህ የናሙና ጸሎት መግቢያ ላይ አድማጮቹን “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፤ እንዲሁ በምድር ትሁን’” ሲል አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9-13) እነዚህ ሦስት ልመናዎች ምን ትርጉም አላቸው?
3. ስለ አምላክ መንግሥት ልናውቀው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
3 ይሖዋ ስለተባለው የአምላክ ስም ቀደም ሲል ብዙ ተምረናል። በተጨማሪም ስለ አምላክ ፈቃድ ማለትም ለሰው ዘር እስካሁን ስላከናወናቸውና ወደፊት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች በተወሰነ ደረጃ ተምረናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን እንድንጸልይ ሲያስተምረን ምንን ማመልከቱ ነው? የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ይህ መንግሥት መምጣቱ የአምላክን ስም የሚያስቀድሰው እንዴት ነው? የዚህ መንግሥት መምጣት ከአምላክ ፈቃድ መፈጸም ጋር የሚያያዘውስ እንዴት ነው?
የአምላክ መንግሥት ምንነት
4. የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ንጉሡስ ማን ነው?
4 የአምላክ መንግሥት በይሖዋ አምላክ የተቋቋመ መስተዳድር ሲሆን በአምላክ የተሾመ ንጉሥ አለው። የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ንጉሡ ኢየሱስ ከሰብዓዊ ገዥዎች ሁሉ የሚበልጥ ሲሆን “የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶችም ጌታ” ተብሎ ተጠርቷል። (1 ጢሞቴዎስ 6:15) ከየትኛውም ሰብዓዊ ገዥ፣ ሌላው ቀርቶ በጣም የተሻለ ነው ከሚባለው ሰብዓዊ ገዥም እንኳ የላቀ መልካም ነገር ማከናወን የሚያስችል ኃይል አለው።
5. የአምላክ መንግሥት የሚገዛው የት ሆኖ ነው? የሚገዛውስ ምንን ነው?
5 የአምላክ መንግሥት የሚገዛው የት ሆኖ ነው? ለዚህ መልስ ለማግኘት በቅድሚያ ኢየሱስ የት ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ እንደተሰቀለና በኋላም ከሞት እንደተነሳ ቀደም ሲል ተምረሃል። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሰማይ አረገ። (የሐዋርያት ሥራ 2:33) በመሆኑም የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በዚያ ማለትም በሰማይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰማያዊ መንግሥት’ በማለት የሚጠራው ለዚህ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 4:18) የአምላክ መንግሥት ያለው በሰማይ ቢሆንም ምድርን ይገዛል።—ራእይ 11:15
6, 7. ኢየሱስን ከሁሉ የላቀ ንጉሥ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
6 ኢየሱስን ከሁሉ የላቀ ንጉሥ የሚያደርገው ምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት የማይሞት መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ከሰብዓዊ ነገሥታት ጋር በማወዳደር “እርሱ ብቻ ኢመዋቲ [የማይሞት] ነው፤ ሊቀረብ በማይቻል ብርሃን ውስጥ ይኖራል” ሲል ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 6:16) በመሆኑም ኢየሱስ የሚያከናውናቸው ጠቃሚ ነገሮች ሁሉ ዘላቂነት ይኖራቸዋል ማለት ነው። ለሕዝቡ በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን እንደሚያከናውን ደግሞ የተረጋገጠ ነው።
7 ስለ ኢየሱስ የተነገረውን የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተመልከት:- “የእግዚአብሔር መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፣ የምክርና የኀይል መንፈስ፣ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስ ይለዋል፤ ዐይኑ እንዳየ አይፈርድም፤ ጆሮውም እንደ ሰማ አይበይንም። ነገር ግን ለድኾች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድር ምስኪኖችም ፍትሕን ይበይናል።” (ኢሳይያስ 11:2-4) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ጻድቅና ርኅሩኅ ንጉሥ ሆኖ የምድርን ሕዝብ እንደሚገዛ ቃል የተገባ መሆኑን ያሳያሉ። እንዲህ ያለ ገዥ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ?
8. ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት እነማን ናቸው?
8 የአምላክን መንግሥት በተመለከተ ያለው ሌላው እውነታ ደግሞ ኢየሱስ የሚገዛው ብቻውን አለመሆኑ ነው። ከኢየሱስ ጋር የሚገዙ ሌሎች ነገሥታት ይኖራሉ። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ብንጸና፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:12) አዎን፣ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስና በአምላክ የተመረጡ ሌሎች ታማኝ አገልጋዮች በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ። እንዲህ ያለ ልዩ መብት የሚያገኙት ሰዎች ስንት ናቸው?
9. ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት ስንት ናቸው? አምላክ እነዚህን ሰዎች መምረጥ የጀመረውስ መቼ ነው?
9 በዚህ መጽሐፍ ሰባተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው ሐዋርያው ዮሐንስ ባየው አንድ ራእይ ላይ “በጉ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በጽዮን ተራራ [በሰማይ ባለው ንጉሣዊ ቦታው] ላይ ቆሞ” የተመለከተ ሲሆን “ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግምባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች ነበሩ።” እነዚህ 144,000 ሰዎች እነማን ናቸው? ዮሐንስ ራሱ “በጉ ወደ ሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኩራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ራእይ 14:1, 4) አዎን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማይ እንዲገዙ ተለይተው የተመረጡ ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ናቸው። ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት ካገኙ በኋላ ከኢየሱስ ጋር “በምድር ላይ ይነግሣሉ።” (ራእይ 5:10) አምላክ የ144,000ዎቹን ቁጥር ለማሟላት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ታማኝ ክርስቲያኖችን ሲመርጥ ቆይቷል።
10. ኢየሱስና 144,000ዎቹ የሰውን ዘር እንዲገዙ መደረጉ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
10 ኢየሱስና 144,000ዎቹ የሰውን ዘር እንዲገዙ መደረጉ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። አንደኛ ነገር፣ ኢየሱስ ሰው መሆንና መሠቃየት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር ‘በድካማችን የማይራራልን አይደለም፤ ነገር ግን እንደ እኛ የተፈተነ ነው፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም’ ብሏል። (ዕብራውያን 4:15፤ 5:8) ተባባሪ ገዥዎቹም ሰው ሆነው ባሳለፉት የሕይወት ዘመናቸው ሥቃይና መከራ ደርሶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የነበሩ ሲሆን የተለያዩ ዓይነት በሽታዎችን ለመቋቋም ተገድደዋል። በእርግጥም የሰው ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በሚገባ ይረዳሉ!
የአምላክ መንግሥት ምን ያከናውናል?
11. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ፈቃድ በተመለከተ ምን ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል?
11 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩ ባስተማረበት ወቅት የአምላክ ፈቃድ ‘በምድርም እንዲሆን’ መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። አምላክ ያለው በሰማይ ሲሆን ታማኝ የሆኑት መላእክት ምንጊዜም ፈቃዱን በሰማይ ሲፈጽሙ ኖረዋል። ይሁን እንጂ በዚህ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው አንድ ክፉ መልአክ የአምላክን ፈቃድ ማድረጉን በመተው አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንዲሠሩ አደረጋቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ዲያብሎስ በመባል ስለሚታወቀው ስለዚህ ክፉ መልአክ የሚያስተምረውን ትምህርት በተመለከተ ምዕራፍ 10 ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ እናገኛለን። ሰይጣንና እሱን ለመከተል የመረጡ መላእክት የነበሩ መንፈሳዊ ፍጡራን ማለትም አጋንንት ለተወሰነ ጊዜ በሰማይ እንዲቆዩ ተፈቅዶላቸው ነበር። በመሆኑም በዚያን ጊዜ በሰማይ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ የነበሩት ሁሉም አይደሉም። የአምላክ መንግሥት መግዛት ሲጀምር ግን ይህ ሁኔታ ይለወጣል። የተሾመው አዲሱ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ጦርነት ይከፍታል።—ራእይ 12:7-9
12. በራእይ 12:10 ላይ ምን ሁለት ዋና ዋና ክንውኖች ተገልጸዋል?
12 የሚከተሉት ትንቢታዊ ቃላት የሚፈጸመውን ሁኔታ ይገልጻሉ:- “ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኀይልና መንግሥት፣ የእርሱ ክርስቶስ ሥልጣንም መጥቶአል። ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት ሲከሳቸው የነበረው፣ የወንድሞቻችን ከሳሽ [ሰይጣን] ተጥሎአልና።” (ራእይ 12:10) በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ክንውኖች እንደተገለጹ አስተውለሃል? አንደኛ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት መግዛት ይጀምራል። ሁለተኛ ደግሞ ሰይጣን ከሰማይ ወደ ምድር ይጣላል።
13. ሰይጣን ከሰማይ መባረሩ ምን ውጤት አስገኝቷል?
13 ወደፊት እንደምንመለከተው እነዚህ ሁለት ክንውኖች ተፈጽመዋል። ታዲያ ምን ውጤት አስከተለ? መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ የተፈጸመውን ሁኔታ ሲገልጽ “ስለዚህ ሰማያት ሆይ፣ በውስጣቸውም የምትኖሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ” ይላል። (ራእይ 12:12) አዎን፣ ታማኝ የሆኑት መላእክት ሰይጣንና አጋንንቱ በመባረራቸውና በሰማይ ያለው ፍጡር ሁሉ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ በመሆኑ ይደሰታሉ። በሰማይ የተሟላና የማይደፈርስ ሰላምና ስምምነት ሰፍኗል። የአምላክ ፈቃድ በሰማይ ተፈጽሟል።
ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ መባረራቸው በምድር ላይ ወዮታ አስከትሏል። እነዚህ ችግሮች በቅርቡ ይወገዳሉ
14. ሰይጣን ወደ ምድር መጣሉ ምን ሁኔታ አስከትሏል?
14 ስለ ምድርስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል” ሲል ይገልጻል። (ራእይ 12:12) ሰይጣን ከሰማይ ስለተባረረና የቀረው ጊዜ ጥቂት እንደሆነ ስላወቀ ተቆጥቷል። በቁጣ ተሞልቶ በምድር ላይ መከራ ወይም ‘ወዮታ’ አምጥቷል። ይህን ‘ወዮታ’ በተመለከተ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን። ይሁንና ይህ ሁኔታ እያለ የአምላክ መንግሥት የይሖዋን ፈቃድ በምድር ላይ መፈጸም የሚችለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን።
15. አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ ምንድን ነው?
15 አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ አስታውስ። ምዕራፍ 3 ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተምረህ ነበር። አምላክ በኤደን ውስጥ እንደገለጸው ለዚህች ምድር ያለው ፈቃድ ገነት እንድትሆን እንዲሁም በማይሞቱና ጻድቃን በሆኑ የሰው ዘሮች እንድትሞላ ነው። ሰይጣን፣ አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንዲሠሩ ስላደረገ አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድ የሚፈጸምበት ጊዜ ሊዘገይ ችሏል፤ ሆኖም የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። ይሖዋ አሁንም ‘ጻድቃን ምድርን እንዲወርሱና በእርሷም ለዘላለም እንዲኖሩ’ ለማድረግ ዓላማ አለው። (መዝሙር 37:29) የአምላክ መንግሥት ደግሞ ይህን ዓላማ ዳር ያደርሳል። በምን መንገድ?
16, 17. ዳንኤል 2:44 ስለ አምላክ መንግሥት ምን ያስተምረናል?
16 ዳንኤል 2:44 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ተመልከት። እንዲህ ይላል:- “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” ይህ ትንቢት ስለ አምላክ መንግሥት ምን ያስተምረናል?
17 በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ መንግሥት “በነዚያ ነገሥታት ዘመን” ወይም ሌሎቹ ሰብዓዊ መንግሥታት ባሉበት ዘመን እንደሚቋቋም ይገልጽልናል። በሁለተኛ ደረጃ መንግሥቱ ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ያስገነዝበናል። በሌላ መንግሥት ድል የማይነሳና የማይተካ ይሆናል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል ውጊያ እንደሚኖር ይጠቁመናል። የአምላክ መንግሥት በውጊያው ድል ይቀዳጃል። በመጨረሻም የሰውን ዘር የሚገዛ ብቸኛ መስተዳድር ይሆናል። ከዚያ በኋላ የሰው ልጆች አይተውት በማያውቁት ከሁሉ የተሻለ አገዛዝ ሥር ይኖራሉ።
18. በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ውጊያ ምን በመባል ይታወቃል?
18 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንግሥትና በዚህ ዓለም መንግሥታት መካከል ስለሚደረገው የመጨረሻ ጦርነት ብዙ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል መጨረሻው እየቀረበ ሲመጣ ክፉ መናፍስት ‘የዓለምን ነገሥታት’ ለማሳት የውሸት ወሬ እንደሚያሰራጩ ያስተምራል። ዓላማቸው ምንድን ነው? ‘ነገሥታቱን ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚሆነው ጦርነት ለመሰብሰብ’ ነው። የምድር ነገሥታት “በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ” ይሰበሰባሉ። (ራእይ 16:14, 16) በእነዚህ ሁለት ቁጥሮች ላይ በተገለጸው ሐሳብ መሠረት በሰብዓዊ መንግሥታትና በአምላክ መንግሥት መካከል የሚካሄደው የመጨረሻው ውጊያ የሐርማጌዶን ወይም የአርማጌዶን ጦርነት በመባል ይታወቃል።
19, 20. የአምላክ ፈቃድ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ እንዳይፈጸም ያገደው ነገር ምንድን ነው?
19 የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን አማካኝነት ምን ነገር ያከናውናል? አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ በድጋሚ አስታውስ። ይሖዋ አምላክ ምድር በገነት ውስጥ ሆነው በሚያገለግሉት ጻድቃንና ፍጹማን የሆኑ የሰው ዘሮች እንድትሞላ ለማድረግ ዓላማ አለው። ይህ ዓላማ አሁን እንዳይፈጸም ያገደው ነገር ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ኃጢአተኞች በመሆናችን እንታመማለን እንዲሁም እንሞታለን። ይሁን እንጂ ለዘላለም መኖር እንድንችል ኢየሱስ እንደሞተልን ምዕራፍ 5 ላይ ተምረናል። በዮሐንስ ወንጌል ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል” የሚሉትን ቃላት ሳታስታውስ አትቀርም።—ዮሐንስ 3:16
20 ሌላው ችግር ደግሞ ብዙ ሰዎች ክፉ ነገሮች የሚፈጽሙ መሆናቸው ነው። ይዋሻሉ፣ ያጭበረብራሉ እንዲሁም የጾታ ብልግና ይፈጽማሉ። የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አይፈልጉም። ክፉ ነገሮችን የሚፈጽሙ ሰዎች በአምላክ የአርማጌዶን ጦርነት ይጠፋሉ። (መዝሙር 37:10) የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ያልተፈጸመበት ሌላው ምክንያት መንግሥታት ይህን የአምላክ ፈቃድ እንዲያደርጉ ሰዎችን የሚያበረታቱ አለመሆናቸው ነው። ብዙዎቹ መንግሥታት በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር የተሳናቸው ከመሆኑም በላይ ጨካኞች አሊያም ብልሹ ሥነ ምግባር ያላቸው ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው ሰውን መግዛቱ ጉዳት’ እንዳስከተለ በግልጽ ይናገራል።—መክብብ 8:9
21. መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርገው እንዴት ነው?
21 ከአርማጌዶን በኋላ የሰው ዘር በአንድ መስተዳድር ይኸውም በአምላክ መንግሥት ሥር ብቻ ይሆናል። ይህ መንግሥት የአምላክን ፈቃድ የሚፈጽም ከመሆኑም በላይ አስደሳች በረከቶች ያመጣል። ለምሳሌ ያህል ሰይጣንንና አጋንንቱን ያስወግዳል። (ራእይ 20:1-3) የኢየሱስ መሥዋዕት ያለው ኃይል ጥቅም ላይ ስለሚውል ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከሕመምና ከሞት ነፃ ይሆናሉ። ከዚህ ይልቅ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለዘላለም ይኖራሉ። (ራእይ 22:1-3) ምድር ገነት ትሆናለች። በዚህ መንገድ መንግሥቱ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸምና የአምላክ ስም እንዲቀደስ ያደርጋል። ይህ ምን ማለት ነው? በመጨረሻ በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር በሕይወት ያለ ሁሉ የይሖዋን ስም ያከብራል ማለት ነው።
የአምላክ መንግሥት እርምጃ የሚወስደው መቼ ነው?
22. የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜም ሆነ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ እንዳልመጣ እንዴት እናውቃለን?
22 ኢየሱስ ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ሲያስተምራቸው መንግሥቱ በዚያን ጊዜ እንዳልመጣ ግልጽ ነበር። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግስ መንግሥቱ መጥቷል? አልመጣም፤ ምክንያቱም ጴጥሮስም ሆነ ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “እግዚአብሔር ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው” የሚለው በመዝሙር 110:1 ላይ የሚገኘው ትንቢት በእሱ ላይ እንደተፈጸመ ተናግረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:32-35፤ ዕብራውያን 10:12, 13) ስለዚህ ኢየሱስ የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ አስፈልጎት ነበር።
በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ላይ ይሆናል
23. (ሀ) የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
23 ኢየሱስ ሲጠባበቅ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ዘመን ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህ ጊዜ የሚያበቃው በ1914 እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ማስተዋል ችለው ነበር። (ይህን ጊዜ በተመለከተ ከገጽ 215-218 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።) በ1914 በዓለም ላይ መታየት የጀመሩት ክስተቶች እነዚህ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የደረሱበት መደምደሚያ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ክርስቶስ በ1914 ንጉሥ እንደሆነና የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መግዛት እንደጀመረ ያመለክታል። በመሆኑም አሁን የምንኖረው ሰይጣን በቀረው “ጥቂት ዘመን” ውስጥ ነው። (ራእይ 12:12፤ መዝሙር 110:2) በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት በቅርቡ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም ለማድረግ እርምጃ ይወስዳል ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ይህ ትልቅ የምሥራች እንደሆነ ይሰማሃል? እውነት ነው ብለህስ ታምናለህ? የሚቀጥለው ምዕራፍ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል እነዚህን ነገሮች እንደሚያስተምር እንድታስተውል ይረዳሃል።
-