-
ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱመጠበቂያ ግንብ—2013 | ጥር 15
-
-
ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ
“የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ።”—ኢያሱ 24:15
1-3. (ሀ) ትክክለኛ ምርጫ በማድረግ ረገድ ኢያሱ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ሲያጋጥሙን ምን ነገር ማሰብ ይኖርብናል?
በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ምርጫዎች ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ። አንድ ሰው ምርጫ የሚያደርገው አማራጮች ሲኖሩት ነው፤ እንዲህ ያለው ሰው ሕይወቱን የሚመራበትን አቅጣጫ ለመወሰን በተወሰነ መጠን ነፃነት አለው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በጉዞ ላይ ያለ አንድ ሰው መንታ መንገድ ላይ ደረሰ እንበል። ይህ ሰው የትኛውን መንገድ ይመርጣል? ግለሰቡ መድረሻውን የሚያውቅ ከሆነ አንደኛው መንገድ ወደሚፈልገው ቦታ እንደሚያደርሰው ሌላኛው ጎዳና ደግሞ ካሰበው ቦታ እንደሚያርቀው የታወቀ ነው።
2 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የመሰለ ሁኔታ ስላጋጠማቸው በርካታ ሰዎች የሚናገር ታሪክ ይዟል። ለምሳሌ ቃየን ቁጣው እንዲቆጣጠረው የመፍቀድ አሊያም ቁጣውን የመቆጣጠር ምርጫ ነበረው። (ዘፍ. 4:6, 7) በሌላ በኩል ኢያሱ ከእውነተኛው አምላክና ከሐሰት አማልክት አንዱን መምረጥ ነበረበት። (ኢያሱ 24:15) የኢያሱ ግብ ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ መኖር ነበር፤ በመሆኑም ወደዚያ አቅጣጫ የሚመራውን መንገድ መርጧል። ቃየን ግን እንዲህ ያለ ግብ ስላልነበረው ከይሖዋ የሚያርቀውን የሕይወት ጎዳና ተከትሏል።
3 አንዳንድ ጊዜ እኛም በሕይወት ጎዳና ላይ ስንጓዝ መንታ መንገድ ያጋጥመናል። በዚህ ጊዜ መድረሻችንን ማለትም ግባችንን ማሰብ ይኖርብናል፤ ግባችን፣ በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋን ማስከበርና ምንም ነገር ከእሱ እንዲያርቀን አለመፍቀድ ነው። (ዕብራውያን 3:12ን አንብብ።) በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በሕይወታችን ውስጥ ከሚያጋጥሙን ከይሖዋ ሊያርቁን ከሚችሉ ነገሮች መካከል ሰባቱን እንመረምራለን።
ሥራ
4. ሰብዓዊ ሥራ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
4 ክርስቲያኖች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰባቸውን የማስተዳደር ግዴታ አለባቸው። አንድ ሰው ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማቅረብ የማይፈልግ ከሆነ እምነት ከሌለው ሰው የከፋ ወይም ይሖዋን የካደ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። (2 ተሰ. 3:10፤ 1 ጢሞ. 5:8) ሰብዓዊ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ከምንሰጣቸው ነገሮች አንዱ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ይሁንና ጥንቃቄ ካላደረግን ሥራችን ከይሖዋ ሊያርቀን ይችላል። እንዴት?
5. ሥራ ስንመርጥ የትኞቹን ጉዳዮች ማጤናችን አስፈላጊ ነው?
5 ሥራ እየፈለግህ ነው እንበል። የምትኖረው ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት አገር ውስጥ ከሆነ መጀመሪያ የምታገኘውን ማንኛውንም ሥራ ዓይንህን ሳታሽ ለመቀበል ትፈተናለህ? የሥራው ዓይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ቢሆንስ? የሥራው ጸባይ ብዙ ሰዓት እንድትሠራ ወይም እንድትጓዝ የሚጠይቅ በመሆኑ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎችህን የሚያስተጓጉልብህ ወይም ከቤተሰብህ የሚያርቅህ ቢሆንስ? ሥራ አጥቶ ከመቀመጥ ይሻላል በሚል የማይሆን ሥራ ትይዛለህ? የተሳሳተ ጎዳና መከተል ከይሖዋ እንደሚያርቅህ አትዘንጋ። (ዕብ. 2:1) ሥራ ለመቀጠርም ሆነ ሥራ ለመቀየር እያሰብክ ከሆነ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
6, 7. (ሀ) አንድ ሰው ከሰብዓዊ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ግቦች ሊኖሩት ይችላሉ? (ለ) ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ የሚያስችልህ የትኛው ግብ ነው? ለምንስ?
6 ቀደም ሲል እንደተገለጸው መድረሻህን በአእምሮህ መያዝህ ጠቃሚ ነው። ‘ይህ ሥራ እንዲያደርሰኝ የምፈልገው የት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሰብዓዊ ሥራን የምትመለከተው ግብህ ላይ ለመድረስ ይኸውም ራስህንና ቤተሰብህን እያስተዳደርክ ይሖዋን ለማገልገል እንደሚያስችል ነገር አድርገህ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን ይባርከዋል። (ማቴ. 6:33) ሥራህን ብታጣ ወይም ድንገተኛ የገንዘብ ችግር ቢያጋጥምህ ይሖዋ ዝም ብሎ እንደማይመለከትህ አስታውስ። (ኢሳ. 59:1) ይሖዋ ለእሱ “ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን” ያውቃል።—2 ጴጥ. 2:9
7 በሌላ በኩል ደግሞ የምትፈልገው በቁሳዊ መበልጸግ ብቻ ከሆነስ? ሊሳካልህ ይችላል። ያም ሆኖ እንዲህ ያለው “ስኬት” ልትመልሰው የማትችል ዋጋ እንደሚያስከፍልህ አትዘንጋ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) ለሀብትና ለሥራ ከልክ ያለፈ ቦታ መስጠት አንተን ከይሖዋ ከማራቅ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።
8, 9. ወላጆች ለሰብዓዊ ሥራ ከሚኖራቸው አመለካከት ጋር በተያያዘ ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? አብራራ።
8 ወላጅ ከሆንክ የአንተ ምሳሌነት በልጆችህ ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስብ። ልጆችህ የሚያስተውሉት ምንድን ነው? ከፍተኛ ቦታ የምትሰጠው ለሥራህ እንደሆነ ነው ወይስ ከይሖዋ ጋር ላለህ ዝምድና? ለዝና፣ ለክብር ወይም ለሀብት ትልቅ ቦታ የምትሰጥ ከሆነ እነሱም እንዲህ ያለውን የጥፋት ጎዳና ሊከተሉ ይችላሉ። እንደ ወላጅ መጠን ለአንተ የሚሰጡት አክብሮት ይቀንስ ይሆን? አንዲት ክርስቲያን ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እኔ እስከማስታውሰው ድረስ አባቴ በሥራ በጣም የተወጠረ ሰው ነበር። መጀመሪያ ላይ እንዲህ ጠንክሮ የሚሠራው ለቤተሰቡ የተሻለ ነገር ለማቅረብና እኛን በእንክብካቤ ለማሳደግ ስለሚፈልግ ይመስለኝ ነበር። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነገሮች ግልጽ ሆኑ። ይሠራል፣ ይሠራል፤ እንዲህ የሚያደርገው ግን ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሳይሆን የቅንጦት ዕቃዎችን ለመግዛት ነው። በዚህ ምክንያት ቤተሰባችን የሚታወቀው ሌሎችን በመንፈሳዊ በማበረታታት ሳይሆን በሀብት ነው። እኔ ግን ሀብቱ ቀርቶብኝ በመንፈሳዊ ቢረዳን ይሻለኝ ነበር።”
9 ወላጆች፣ ለሥራችሁ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ራሳችሁን ከይሖዋ እንዳታርቁ ተጠንቀቁ። ትልቁ ሀብት ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ መሆኑን ከልባችሁ እንደምታምኑ ለልጆቻችሁ በአኗኗራችሁ አሳዩአቸው።—ማቴ. 5:3
10. አንድ ወጣት የሥራ መስክ በሚመርጥበት ጊዜ ምን ነገር ማሰብ ይኖርበታል?
10 የሥራ መስክ በመምረጥ ላይ ያለህ ወጣት ከሆንክ ትክክለኛውን ጎዳና መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው? ይህ የተመካው ቀደም ሲል እንደተወያየነው ሕይወትህን መጠቀም በምትፈልግበት መንገድ ላይ ነው። ሥልጠና ለመውሰድ ወይም ለመቀጠር ያሰብከው የሥራ መስክ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይበልጥ ለማስቀደም ይረዳሃል ወይስ ከይሖዋ ያርቅሃል? (2 ጢሞ. 4:10) ግብህ ደስታቸው በኪሳቸው ላይ የተመካ ሰዎችን የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ ነው? ወይስ ምርጫህ “ጐልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም” በማለት በትምክህት የጻፈውን የዳዊትን ስሜት እንደምትጋራ ያሳያል? (መዝ. 37:25) አንደኛው መንገድ ከይሖዋ እንደሚያርቅህ ሌላኛው ደግሞ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንደሚያስገኝልህ አትዘንጋ። (ምሳሌ 10:22ን እና ሚልክያስ 3:10ን አንብብ።) ታዲያ የትኛውን መንገድ ትመርጣለህ?a
መዝናኛ
11. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መዝናኛ ምን ይናገራል? ይሁንና ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?
11 መጽሐፍ ቅዱስ መዝናናትን አያወግዝም፤ እንዲሁም ጊዜን እንደማባከን አድርጎ አይመለከተውም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጥቂቱ ይጠቅማል” በማለት ጽፎለታል። (1 ጢሞ. 4:8) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለሳቅና ለጭፈራ ጊዜ እንዳለው’ ይናገራል፤ በተጨማሪም መጠነኛ እረፍት ማድረግን ያበረታታል። (መክ. 3:4፤ 4:6) ይሁንና ጠንቃቃ ካልሆንን መዝናኛ ከይሖዋ ሊያርቀን ይችላል። እንዴት? ብዙ ጊዜ አደጋው የሚከሰተው ከሁለት አቅጣጫ ነው፤ አንደኛው የመዝናኛው ዓይነት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በመዝናናት የሚጠፋው ጊዜ ነው።
ተገቢ ዓይነት መዝናኛ በተገቢው መጠን መንፈስን ያድሳል
12. በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?
12 እስቲ በመጀመሪያ፣ ስለምንመርጠው የመዝናኛ ዓይነት እንመልከት። ጤናማና ጥሩ የሆነ መዝናኛ እንዳለ ግልጽ ነው። ይሁንና አብዛኛው መዝናኛ ዓመፅን፣ መናፍስታዊ ድርጊትንና የፆታ ብልግናን ጨምሮ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቅ እንደሆነ አይካድም። በመሆኑም የምንመርጠውን መዝናኛ በጥንቃቄ መመርመር ይኖርብናል። መዝናኛው በአንተ ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል? የዓመፀኝነት፣ የፉክክር ወይም የብሔራዊ ስሜት እንዲኖርህ የሚያበረታታ ነው? (ምሳሌ 3:31) ገንዘብህን እንድታባክን ያደርግሃል? ሌሎችንስ ያሰናክላል? (ሮም 14:21) የምትመርጠው የመዝናኛ ዓይነት ከማን ጋር እንድትውል ያደርግሃል? (ምሳሌ 13:20) መጥፎ ነገር የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርብህ ያደርጋል?—ያዕ. 1:14, 15
13, 14. ለመዝናናት ከምታውለው ጊዜ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል?
13 በመዝናኛ የምታሳልፈው ጊዜም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል። ‘ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ጊዜ እስካጣ ድረስ በመዝናናት ብዙ ጊዜ አጠፋለሁ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። በመዝናኛ የምታጠፋው ጊዜ ከልክ ያለፈ ከሆነ የእረፍት ጊዜህ የምታስበውን ያህል መንፈስህን አያድስልህም። እንዲያውም በእረፍት ጊዜያቸው ይበልጥ የሚደሰቱት ለመዝናኛ ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” በማስቀደማቸው፣ ሲዝናኑ የሕሊና ወቀሳ አይሰማቸውም።—ፊልጵስዩስ 1:10, 11ን አንብብ።
14 በመዝናናት ረጅም ጊዜ ማሳለፍ አስደሳች ቢመስልም ይህን መንገድ መከተል አንድን ሰው ከይሖዋ ሊያርቀው ይችላል። ኪም የተባለች የ20 ዓመት ወጣት ይህን ሁኔታ ከራሷ ሕይወት ተምራለች። ይህች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንድም ግብዣ አያመልጠኝም ነበር። ሁልጊዜ ዓርብ፣ ቅዳሜና እሁድ አንድ ትልቅ ግብዣ አይጠፋም ነበር። አሁን ግን ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ማስተዋል ችያለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ አቅኚ እንደመሆኔ መጠን ለአገልግሎት ጠዋት 12 ሰዓት ላይ እነሳለሁ፤ በመሆኑም እስከ ሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት ድረስ ግብዣ ላይ መቆየት አልችልም። ሁሉም ማኅበራዊ ግብዣዎች መጥፎ እንዳልሆኑ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ትልቅ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ልክ እንደ ሌሎቹ ነገሮች ለግብዣዎችም ተገቢውን ቦታ መስጠት ይኖርብናል።”
15. ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈስን የሚያድስ መዝናኛ እንዲመርጡ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
15 ወላጆች የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት የማሟላት ግዴታ አለባቸው። ይህ ደግሞ መዝናኛን ይጨምራል። ወላጅ ከሆንክ ሁሉም የመዝናኛ ዓይነቶች መጥፎ እንደሆኑ በመፈረጅ ቤተሰብህ ደስታ የራቀው ሕይወት እንዲመራ አታድርግ። በሌላ በኩል ደግሞ የመዝናኛ ምርጫችሁ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንዳይሆን ጥንቃቄ አድርግ። (1 ቆሮ. 5:6) አስቀድመህ በጉዳዩ ላይ በሚገባ ካሰብክበት ለቤተሰብህ የሚሆን መንፈስን የሚያድስ መዝናኛ ማግኘት ትችላለህ።b እንዲህ የምታደርግ ከሆነ አንተንም ሆንክ ልጆችህ የመረጣችሁት ጎዳና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርቡ የሚያስችላችሁ ይሆናል።
ቤተሰብ
16, 17. በርካታ ወላጆች ምን ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል? ይሖዋ ሥቃያቸውን እንደሚረዳ እንዴት እናውቃለን?
16 በወላጅና በልጅ መካከል ያለው ዝምድና በጣም ጠንካራ በመሆኑ ይሖዋ ራሱ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ይህን ዝምድና እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (ኢሳ. 49:15) በመሆኑም አንድ የቤተሰባችን አባል ይሖዋን ሲተው በጥልቅ ማዘናችን የሚጠበቅ ነገር ነው። አንዲት እህት ልጇ ስትወገድ የተሰማትን ስሜት እንዲህ በማለት ገልጻለች፦ “ቅስሜ ተሰብሮ ነበር። ‘ይሖዋን የተወችው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ያስጨንቀኝ ነበር። የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ራሴን እወቅስ ነበር።”
17 ይሖዋ ሥቃያችሁን ይረዳል። የምድራዊው ቤተሰብ የመጀመሪያ አባላትም ሆኑ ከጥፋት ውኃው በፊት የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ባመፁ ጊዜ ‘ልቡ እጅግ አዝኖ’ ነበር። (ዘፍ. 6:5, 6) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው የማያውቁ ሰዎች ሁኔታው ምን ያህል ሥቃይ እንደሚያስከትል መረዳት ሊከብዳቸው ይችላል። ያም ቢሆን የተወገደው የቤተሰብ አባል የተከተለው ተገቢ ያልሆነ ጎዳና እናንተን ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ መፍቀድ ጥበብ አይደለም። ታዲያ አንድ የቤተሰብ አባል ይሖዋን ሲተው የሚፈጠረውን ከባድ ሐዘን መቋቋም የምትችሉት እንዴት ነው?
18. ወላጆች፣ ልጃቸው ይሖዋን ሲተው ራሳቸውን መውቀስ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
18 ለተፈጠረው ነገር ራሳችሁን አትውቀሱ። ይሖዋ በሰዎች ፊት ምርጫ አስቀምጧል፤ ራሱን ወስኖ የተጠመቀ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል “የራሱን የኃላፊነት ሸክም” መሸከም ይኖርበታል። (ገላ. 6:5) ይሖዋ፣ ኃጢአት የሠራው ሰው በወሰደው ምርጫ የሚጠይቀው እሱን እንጂ እናንተን አይደለም። (ሕዝ. 18:20) በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎችን መውቀስ አይኖርባችሁም። ይሖዋ ተግሣጽ ለመስጠት ያደረገውን ዝግጅት አክብሩ። ጉባኤውን ለመጠበቅ የተሾሙትን እረኞች መደገፍ እንጂ ከዲያብሎስ ጎን መቆም አይገባችሁም።—1 ጴጥ. 5:8, 9
ይሖዋን የተወው የቤተሰባችሁ አባል እንደሚመለስ ተስፋ ማድረጋችሁ ስህተት አይደለም
19, 20. (ሀ) ልጆቻቸው የተወገዱ ወላጆች ሐዘናቸውን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይችላሉ? (ለ) ልጆቻቸው የተወገዱባቸው ወላጆች ምን ነገር ተስፋ ማድረጋቸው ስህተት አይደለም?
19 በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ ላይ የምትቆጡ ከሆነ ከእሱ እየራቃችሁ ትሄዳላችሁ። ይሖዋን የተወው የቤተሰባችሁ አባል፣ እንዲያስተውል ማድረግ ያለባችሁ የቤተሰብ ዝምድናን ጨምሮ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ይሖዋን ለማስቀደም ያላችሁን ቁርጠኝነት ነው። በመሆኑም ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የራሳችሁን መንፈሳዊነት አጠናክሩ። ታማኝ ከሆኑ ወንድሞችና እህቶች ራሳችሁን አታግልሉ። (ምሳሌ 18:1) በጸሎት አማካኝነት ስሜታችሁን ለይሖዋ ንገሩት። (መዝ. 62:7, 8) በስልክ፣ በኢ-ሜይል ወይም በሌላ መንገድ ከተወገደው የቤተሰብ አባል ጋር ለመገናኘት ሰበብ አስባብ አትፈላልጉ። (1 ቆሮ. 5:11) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ተጠመዱ። (1 ቆሮ. 15:58) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው እህት እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ወደ ይሖዋ ስትመለስ እሷን በደንብ መርዳት እንድችል ራሴን በይሖዋ አገልግሎት ማስጠመድና መንፈሳዊነቴን መገንባት እንዳለብኝ ይሰማኛል።”
20 መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ሁሉን ተስፋ ያደርጋል” ይላል። (1 ቆሮ. 13:4, 7) በመሆኑም ይሖዋን የተወው የቤተሰባችሁ አባል እንደሚመለስ ተስፋ ማድረጋችሁ ስህተት አይደለም። በየዓመቱ በርካታ ሰዎች ንስሐ ገብተው ወደ ይሖዋ ድርጅት ይመለሳሉ። ይሖዋ ንስሐ ስለገቡ አይናደድም። ከዚህ ይልቅ “ይቅር” ለማለት ዝግጁ ነው።—መዝ. 86:5
ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ አድርጉ
21, 22. ነፃ ምርጫህን ከምትጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
21 ይሖዋ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ነፃ ምርጫ ሰጥቷቸዋል። (ዘዳግም 30:19, 20ን አንብብ።) ይሁንና ይህ መብት ከባድ ኃላፊነት ያስከትላል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ራሱን እንደሚከተለው በማለት መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘የትኛውን መንገድ እየተከተልኩ ነው? ሥራ፣ መዝናኛ ወይም ቤተሰብ ከይሖዋ እንዲያርቀኝ እየፈቀድኩ ነው?’
22 ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር መቼም ቢሆን አይቀንስም። ከይሖዋ ልንርቅ የምንችለው እኛ ራሳችን የተሳሳተ ጎዳና ለመከተል ከመረጥን ብቻ ነው። (ሮም 8:38, 39) ይህ ደግሞ እንዲደርስብን አንፈልግም። እንግዲያው ምንም ነገር ከይሖዋ እንዳያርቀን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ቁርጥ ውሳኔያችንን ልናሳይ የምንችልባቸውን ሌሎች አራት አቅጣጫዎች ያብራራል።
a የሥራ መስክ ስለመምረጥ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 38 ተመልከት።
b በዚህ ረገድ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የኅዳር 2011 ንቁ! መጽሔትን ከገጽ 17-19 ተመልከት።
-
-
ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ቅረቡመጠበቂያ ግንብ—2013 | ጥር 15
-
-
ምንጊዜም ወደ ይሖዋ ቅረቡ
“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።”—ያዕ. 4:8
1, 2. (ሀ) የሰይጣን “ዕቅድ” ምንድን ነው? (ለ) ወደ አምላክ ለመቅረብ ምን ሊረዳን ይችላል?
ይሖዋ አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ወደ እሱ የመቅረብ ፍላጎት እንዲኖራቸው አድርጎ ነው። የሰይጣን ፍላጎት ግን የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን ማለትም ይሖዋ እንደማያስፈልገን ሆኖ እንዲሰማን ማድረግ ነው። ሰይጣን በኤደን የአትክልት ስፍራ ሔዋንን ካሳሳተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ውሸት ሲያስፋፋ ቆይቷል። (ዘፍ. 3:4-6) አብዛኛው የሰው ዘርም ባለፉት ዘመናት ሁሉ ይህን ስህተት ሲደግም ቆይቷል።
2 እኛ ግን በሰይጣን ወጥመድ ላለመግባት መጠንቀቅ እንችላለን። ምክንያቱም “የእሱን ዕቅድ እናውቀዋለን።” (2 ቆሮ. 2:11) ሰይጣን፣ የተሳሳቱ ምርጫዎችን እንድናደርግ በመገፋፋት ከይሖዋ ሊያርቀን ይሞክራል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው በሥራ፣ በመዝናኛና በቤተሰብ ጉዳዮች ረገድ ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እንችላለን። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ ለቴክኖሎጂ፣ ለጤና፣ ለገንዘብ እንዲሁም ለኩራት ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ‘ወደ አምላክ እንድንቀርብ’ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።—ያዕ. 4:8
ቴክኖሎጂ
3. ቴክኖሎጂ ጥሩም መጥፎም ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
3 በዛሬው ጊዜ በየትኛውም የዓለም ክፍል የተራቀቁ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። እነዚህን መሣሪያዎች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። በአግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ግን ከሰማዩ አባታችን ሊያርቁን ይችላሉ። እስቲ ኮምፒውተርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አሁን እያነበብክ ያለኸው መጽሔት የተዘጋጀው በኮምፒውተር እገዛ ነው። ኮምፒውተር ለምርምርና ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ዓይነተኛ መሣሪያ ከመሆኑም በላይ አልፎ አልፎ ዘና ለማለትም ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ለኮምፒውተር ከልክ ያለፈ ፍቅር ሊኖረን ይችላል። የንግዱ ዓለም አዲስ የወጡ ምርቶች የግድ እንደሚያስፈልጉን በዘዴ ሊያሳምነን ይሞክራል። አንድ ወጣት ታብሌት የሚባል ዘመናዊ ኮምፒውተር እንዲኖረው በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ ይህን ዕቃ ለመግዛት ሲል አንዱን ኩላሊቱን በድብቅ ሸጧል። እንዴት የሚያሳዝን ውሳኔ ነው!
4. አንድ ክርስቲያን በኮምፒውተር ከመጠን በላይ የመጠቀም ልማዱን ያሸነፈው እንዴት ነው?
4 አንድ ሰው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አላግባብ ወይም ከመጠን በላይ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና መሥዋዕት ቢያደርግ ደግሞ ይበልጥ አሳዛኝ ይሆናል። ጆንa የተባለ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ‘አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ’ በማለት እንደሚናገር አውቃለሁ። ያም ቢሆን በኮምፒውተር አጠቃቀም ረገድ ዋነኛው ጠላቴ እኔው ራሴ ነበርኩ።” አብዛኛውን ጊዜ ጆን በጣም መሽቶ እንኳ ከኢንተርኔት ላይ አይነሳም። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም በደከመኝ መጠን ከሰዎች ጋር በኢንተርኔት የጽሑፍ መልእክት መለዋወጤን ወይም ጤናማ ባይሆኑም እንኳ አጫጭር ቪዲዮዎችን መመልከቴን ማቆም እየከበደኝ ይሄዳል።” ይህን መጥፎ ልማዱን ለማቆም ሲል የመኝታ ሰዓቱ ሲደርስ ኮምፒውተሩ ራሱን በራሱ እንዲዘጋ አደረገው።—ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እርዷቸው
5, 6. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው ከሌሎች ጋር የሚያንጽ ጊዜ እንዲያሳልፉ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ወላጆች እያንዳንዱን የልጆቻችሁን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ባይኖርባችሁም የኮምፒውተር አጠቃቀማቸውን ግን መከታተል ይገባችኋል። ከፊታችሁ ዘወር እንዲሉ ወይም እንዳያስቸግሯችሁ ስትሉ ብቻ በኢንተርኔት ብልግናንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንዲመለከቱ፣ የጭካኔ ድርጊት የሚንጸባረቅባቸውን የኮምፒውተር ጨዋታዎች እንዲጫወቱ ወይም ከመጥፎ ጓደኞች ጋር እንዲገጥሙ አትፍቀዱላቸው። አለበለዚያ ልጆቻችሁ ‘አባትና እናቴ ዝም ካሉኝ ምንም ችግር የለውም ማለት ነው’ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ወላጆች እንደመሆናችሁ መጠን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ ልጆቻችሁን ከይሖዋ ከሚያርቃቸው ከማንኛውም ነገር የመጠበቅ ኃላፊነት አለባችሁ። እንስሳት እንኳ ልጆቻቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ። አንዲት ድብ፣ ጠላት ግልገሎቿን ሊያጠቃ ቢመጣ ምን እንደምታደርግ ለማሰብ ሞክሩ!—ከሆሴዕ 13:8 ጋር አወዳድር።
6 ልጆቻችሁ፣ በማንኛውም ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ምሳሌ ከሚሆኑ ክርስቲያኖች ጋር የሚያንጽ ጊዜ እንዲያሳልፉ ዝግጅት አድርጉ። እንዲሁም ልጆቻችሁ ከእናንተ ጋር አብረው መዋል እንደሚፈልጉ አትዘንጉ! እንግዲያው ከልጆቻችሁ ጋር ለመሳቅ፣ ለመጫወት፣ ለመሥራት እንዲሁም ‘ወደ አምላክ ለመቅረብ’ ጊዜ መድቡ።b
ጤና
7. ሁላችንም ጤነኛ መሆን የምንፈልገው ለምንድን ነው?
7 “ጤንነትህ እንዴት ነው?” ይህ የተለመደ አባባል በተዘዋዋሪ አንድን አሳዛኝ እውነታ መቀበላችንን ያሳያል። የመጀመሪያ ወላጆቻችን፣ ሰይጣን ከይሖዋ እንዲያርቃቸው ስለፈቀዱ ሁላችንም እንታመማለን። ሕመም የሰይጣንን ዓላማ ለማሳካት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤ ምክንያቱም ከታመምን ይሖዋን ማገልገል ከባድ ይሆንብናል። ከሞትን ደግሞ ከነአካቴው ይሖዋን ማገልገላችንን እናቆማለን። (መዝ. 115:17) በመሆኑም ሁላችንም ጤነኛ ለመሆን መፈለጋችን የሚጠበቅ ነገር ነው።c ስለ ወንድሞቻችን ጤንነትና ደኅንነት ማሰባችንም ተገቢ ነው።
8, 9. (ሀ) ስለ ጤንነታችን ከመጠን በላይ ከመጨነቅ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ደስታችንን መጠበቃችን ምን ጥቅም አለው?
8 ያም ሆኖ ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ ከመጨነቅ መራቅ ይኖርብናል። አንድን ዓይነት የአመጋገብ ሥርዓት፣ የሕክምና ዓይነት ወይም ምርት በትጋት የሚያስተዋውቁ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማወጅ እንኳ የዚህን ያህል አይተጉ ይሆናል። እንዲያውም ሌሎችን እየረዱ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ያም ሆኖ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በትላልቅ የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ከስብሰባ በፊትም ሆነ በኋላ፣ ጤናን ወይም ውበትን ለመጠበቅ የሚረዱ ምርቶችን ማስተዋወቅ ተገቢ አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
9 በስብሰባዎች ላይ የምንገኘው፣ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመጨዋወትና የአምላክ መንፈስ ውጤት የሆነውን ደስታን ለማግኘት ነው። (ገላ. 5:22) እንዲህ ባሉ ወቅቶች፣ ተጠይቀንም ሆነ ሳንጠየቅ ጤናን አስመልክቶ ምክር መስጠት ወይም አንድን ዓይነት ምርት ማስተዋወቅ የመጣንበትን ዓላማ እንድንስት የሚያደርገን ከመሆኑም በላይ የሌሎችን ደስታ ሊሰርቅ ይችላል። (ሮም 14:17) ደግሞም አንድ ሰው ጤናውን በተመለከተ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። በተጨማሪም ለሁሉም በሽታዎች መፍትሔ ማግኘት የሚችል ሰው የለም። በጣም ጎበዝ የሚባል ሐኪምም እንኳ ያረጃል፣ ይታመማል ውሎ አድሮም ይሞታል። በመሆኑም ስለ ጤንነታችን ከልክ በላይ መጨነቃችን ሕይወታችንን አያራዝምልንም። (ሉቃስ 12:25) በሌላ በኩል ግን “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው።”—ምሳሌ 17:22
10. (ሀ) አንድን ሰው በይሖዋ ዘንድ ውብ የሚያሰኘው ምንድን ነው? (ለ) የተሟላ ጤንነት የሚኖረን መቼ ነው?
10 ስለ መልካችን ማሰባችንም የተገባ ነው። ይሁንና የእርጅና ምልክቶችን ሁሉ ለማጥፋት መሞከሩ አስፈላጊ አይደለም። እንዲያውም እነዚህ ምልክቶች የጉልምስና፣ የክብርና የውስጣዊ ውበት መገለጫዎች ናቸው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) ይሖዋ የሚመለከተን እንደዚህ ነው፤ እኛም ራሳችንን በይሖዋ ዓይን ማየት አለብን። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4ን አንብብ።) ታዲያ መልካችንን ለማሳመር ብለን ጤናችንን አልፎ ተርፎም ሕይወታችንን አደጋ ላይ የሚጥል ቀዶ ሕክምና (ፕላስቲክ ሰርጀሪ) ወይም ሌሎች ሕክምናዎችን ማድረጋችን ጥበብ ነው? የዕድሜያችንና የጤንነታችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እውነተኛ የሆነውና ከውስጣችን የሚወጣው ውበት ምንጭ ‘የይሖዋ ደስታ’ ነው። (ነህ. 8:10) የተሟላ ጤንነትና የወጣትነት ውበት የምናገኘው በአዲሱ ዓለም ብቻ ነው። (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳ. 33:24) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጥበበኞች መሆናችንና እምነት ማዳበራችን አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከሁሉ በተሻለ መንገድ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር ይረዳናል።—1 ጢሞ. 4:8
ገንዘብ
11. ገንዘብ ወጥመድ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
11 ገንዘብ በራሱ መጥፎ አይደለም፤ መነገድም ቢሆን ስህተት አይደለም። (መክ. 7:12፤ ሉቃስ 19:12, 13) “የገንዘብ ፍቅር” ማዳበር ግን ከይሖዋ እንደሚያርቀን ምንም አያጠያይቅም። (1 ጢሞ. 6:9, 10) “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” ማለትም ለሕይወታችን ስለሚያስፈልጉ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ በመንፈሳዊ እንዳናድግ ሊያንቀን ይችላል። ‘ሀብት ያለው የማታለል ኃይልም’ ይኸውም ሀብት ዘላቂ ደስታና ደኅንነት ያስገኛል የሚለው የተሳሳተ እምነትም ቢሆን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። (ማቴ. 13:22) ኢየሱስ አምላክንም ሆነ ሀብትን በአንድነት ማገልገል የሚችል ማንም ሰው እንደሌለ በግልጽ ተናግሯል።—ማቴ. 6:24
12. በአሁኑ ጊዜ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የትኞቹ ወጥመዶች የተለመዱ ሆነዋል? ከእነዚህስ ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ለገንዘብ የተሳሳተ አመለካከት ማዳበር ወደ ስህተት ጎዳና ሊመራ ይችላል። (ምሳሌ 28:20) በአቋራጭ ለመክበር ካላቸው ጉጉት የተነሳ ሎተሪ የቆረጡ ወይም ደግሞ እንደ ሠንሰለት ተያይዘው በመሄድ ብዙ ሰዎችን በሚያነካኩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የገቡ ክርስቲያኖች አሉ፤ እንዲያውም አንዳንዶች በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችን በዚህ ንግድ ውስጥ ለማስገባት ጥረት አድርገዋል። ሌሎች ደግሞ ሊታመን የማይችል ትርፍ ያስገኛሉ በሚባሉ የንግድ ዘርፎች ላይ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱ በቀረበላቸው ሐሳብ ተታልለዋል። አንተም ስግብግብነት የአጭበርባሪዎች ሰለባ እንዳያደርግህ ተጠንቀቅ! ስለዚህ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ አዳብር። አንድ ግብዣ የማይታመን እስኪመስል ድረስ ጥሩ ከሆነ እውነትም የማይታመን ሊሆን ይችላል።
13. ይሖዋ ለገንዘብ ያለው አመለካከት ዓለም ካለው አመለካከት የሚለየው እንዴት ነው?
13 ‘መንግሥቱንና ጽድቁን’ የምናስቀድም ከሆነ ይሖዋ ሚዛናችንን ሳንስት መሠረታዊ ነገሮችን ለማሟላት የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። (ማቴ. 6:33፤ ኤፌ. 4:28) ይሖዋ ከመጠን በላይ በመሥራታችን ምክንያት ጉባኤ ውስጥ እንድናንቀላፋ ወይም መንግሥት አዳራሽ ቁጭ ብለን ስለ ገንዘብ እንድንጨነቅ አይፈልግም። ይሁን እንጂ በዙሪያችን ያሉ ብዙ ሰዎች የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ማድረግና በኋላ ላይ ዘና ያለ ሕይወት መኖር የሚችሉት አሁን ገንዘብ ለማግኘት ከተሯሯጡ ብቻ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በአብዛኛው ልጆቻቸውም ለቁሳዊ ነገሮች ተመሳሳይ ግብ እንዲኖራቸው ይጫኗቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ማስተዋል የጎደለው እንደሆነ ገልጿል። (ሉቃስ 12:15-21ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነት ሰው በአንድ በኩል የስግብግብነት ፍላጎቱን እያሟላ በሌላ በኩል ደግሞ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና መጠበቅ እንደሚችል አድርጎ ያስብ የነበረውን ግያዝን ያስታውሰናል።—2 ነገ. 5:20-27
14, 15. ገንዘብ አስተማማኝ የሆነ ሕይወት ለመምራት እንደሚያስችል ማሰብ ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።
14 አንዳንድ ንስሮች በጥፍሮቻቸው ሊያነሷቸው ከሚችሉት በላይ ክብደት ያላቸውን ዓሣዎች ከያዙ በኋላ ዓሣውን መልሰው ባለመልቀቃቸው እንደሰጠሙ ታይቷል። አንድ ክርስቲያንስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል? አሌክስ የተባለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በባሕርዬ በጣም ቆጣቢ ነኝ። ሻምፖ ስጠቀም እንኳ ብዙ እንዳወጣሁ ከተሰማኝ ትርፉን መልሼ ዕቃ ውስጥ እጨምረዋለሁ።” ይሁንና አሌክስ ሥራውን ለቅቆ አቅኚ ለመሆን ሲል የአክስዮን ንግድ ውስጥ መግባት ፈለገ። ከዚያም የአክሲዮኖችን ዋጋና የገበያውን ሁኔታ በማጥናቱ ሥራ ተጠመደ። በመጨረሻም አንድ አክሲዮን በፍጥነት ዋጋው እንደሚጨምር የገበያ ጥናት ተንታኞች የተናገሩትን በማመን፣ ባጠራቀመው ገንዘብ ላይ ብድር ጨምሮ አክሲዮኑን ገዛ። የአክሲዮኑ ዋጋ ግን እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ በፍጥነት አሽቆለቆለ። አሌክስ እንዲህ ብሏል፦ “ገንዘቤን መልሼ ማግኘት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ትንሽ ብቆይ የአክሲዮኑ ዋጋ ከፍ ሊል ይችላል ብዬ አሰብኩ።”
15 አሌክስ ለብዙ ወራት ከአክሲዮኑ ውጪ የሚያስበው ነገር አልነበረም። በዚህም የተነሳ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር አቃተው፤ እንዲሁም እንቅልፍ እንቢ አለው። ይሁንና የአክሲዮኑ ዋጋ እንደወረደ ቀረ። አሌክስ ያጠራቀመውን ገንዘብ ያጣ ከመሆኑም በላይ ቤቱን መሸጥ ነበረበት። “ቤተሰቤን ለከባድ ሥቃይ ዳረግኩት” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ይሁንና ከደረሰበት ነገር ጥሩ ትምህርት አግኝቷል። “በሰይጣን ሥርዓት የሚታመን ሁሉ ለከፋ ሐዘን እንደሚዳረግ አሁን ተገንዝቤያለሁ” ብሏል። (ምሳሌ 11:28) በእርግጥም በዚህ ሥርዓት ውስጥ ባጠራቀምነው ገንዘብ ወይም በንግዳችን አሊያም ገንዘብ ለማግኘት ባለን ችሎታ ላይ ተስፋ መጣል “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በሆነው በሰይጣን ላይ ተስፋ ከማድረግ ተለይቶ አይታይም። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ጢሞ. 6:17) አሌክስ “ስለ ምሥራቹ ሲል” ቀላል ሕይወት መኖር ጀምሯል። እንዲህ ማድረጉ እሱም ሆነ ቤተሰቡ ይበልጥ ደስተኞች እንዲሆኑና ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ እንደረዳቸው ይናገራል።—ማርቆስ 10:29, 30ን አንብብ።
ኩራት
16. መኩራት ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው? ተገቢ የማይሆነውስ?
16 በአንዳንድ ነገሮች መኩራት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ የይሖዋ ምሥክር በመሆናችን ምንጊዜም ኩራት ሊሰማን ይገባል። (ኤር. 9:24) በተወሰነ መጠን ለራሳችን አክብሮት ካለን ጥሩ ውሳኔ እናደርጋለን፤ እንዲሁም የሥነ ምግባር አቋማችንን አናላላም። ይሁንና ቦታችንን የማንጠብቅ ወይም ለራሳችን ያለን ግምት ከልክ ያለፈ ከሆነ ይህ ሁኔታ ከይሖዋ ሊያርቀን ይችላል።—መዝ. 138:6፤ ሮም 12:3
በጉባኤ ውስጥ መብት ለማግኘት ከመጓጓት ይልቅ ትኩረታችሁን በአገልግሎታችሁ ላይ አድርጉ!
17, 18. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትሑት በመሆናቸው አሊያም በኩራታቸው የተጠቀሱ ሰዎችን ተናገር። (ለ) አንድ ወንድም ኩራት ከይሖዋ እንዳያርቀው ያደረገው እንዴት ነው?
17 መጽሐፍ ቅዱስ ኩሩ ስለነበሩና ትሑት ስለነበሩ ሰዎች የሚናገሩ ታሪኮችን ይዟል። ንጉሥ ዳዊት ትሑት በመሆን የይሖዋን መመሪያ ይጠይቅ ስለነበር ይሖዋ ባርኮታል። (መዝ. 131:1-3) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ትዕቢተኛ የነበሩት ንጉሥ ናቡከደነፆርና ቤልሻዛር ልካቸውን እንዲያውቁ አድርጓል። (ዳን. 4:30-37፤ 5:22-30) በዛሬው ጊዜም ትሕትናችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። ዕድሜው 32 ዓመት የሆነ ራየን የተባለ አንድ የጉባኤ አገልጋይ ጉባኤ በቀየረበት ወቅት ያጋጠመውን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ወዲያው ሽማግሌ ሆኜ እንደምሾም ጠብቄ ነበር። ሆኖም ያሰብኩት ሳይሆን አንድ ዓመት አለፈ።” ታዲያ ራየን ሽማግሌዎቹ ተገቢውን አክብሮት እንዳላሳዩት ተሰምቶት ይናደድ ወይም ይበሳጭ ይሆን? ኩራት ከይሖዋና ከሕዝቡ እንዲያርቀው በመፍቀድ ጉባኤ መሄዱን ያቆም ይሆን? አንተ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር?
18 ራየን “ስለሚዘገይ ተስፋ የሚናገሩ ጽሑፎችን በሙሉ አነበብኩ” ብሏል። (ምሳሌ 13:12 የ1954 ትርጉም) አክሎም “ትዕግሥትንና ትሕትናን ማዳበር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይሖዋ እንዲያሠለጥነኝ መፍቀድ ነበረብኝ” ብሏል። ራየን በራሱ ላይ ከማተኮር ይልቅ በጉባኤ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ የሚያገኛቸውን ሰዎች በመርዳት ላይ ትኩረት ማድረግ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ እድገት የሚያደርጉ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ጀመረ። ራየን እንዲህ ብሏል፦ “ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ሽማግሌ ሆኜ ስሾም ያልጠበቅኩት ነገር ሆነብኝ። ምክንያቱም ትኩረቴ ሁሉ አገልግሎቴ ላይ ስለነበር ስለ መብት ማሰቤን ትቼ ነበር።”—መዝሙር 37:3, 4ን አንብብ።
ከይሖዋ ጋር ተቀራርባችሁ ኑሩ!
19, 20. (ሀ) የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን ከይሖዋ እንዳያርቁን ምን ማድረግ እንችላለን? (ለ) ምንጊዜም ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ለመኖር የእነማንን ምሳሌ መከተል እንችላለን?
19 በዚህና ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ላይ የተወያየንባቸው ነገሮች በሙሉ በሕይወታችን ውስጥ ተገቢውን ቦታ እስከሰጠናቸው ድረስ በራሳቸው ስህተት አይደሉም። የይሖዋ አገልጋይ በመሆናችን ልንኮራ ይገባል። ይሖዋ ከሰጠን ውድ ስጦታዎች መካከል ደስተኛ ቤተሰብና ጥሩ ጤንነት ይገኙበታል። ሥራና ገንዘብም ቢሆን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማሟላት እንደሚረዱን እንገነዘባለን። በተጨማሪም መዝናኛ መንፈሳችንን እንደሚያድስ፣ ቴክኖሎጂም ጠቃሚ አገልግሎት ሊሰጠን እንደሚችል እናውቃለን። ሆኖም እነዚህን ነገሮች ተገቢ ባልሆነ ጊዜ ወይም ከመጠን በላይ አሊያም አምልኳችንን በሚነካ መንገድ የምንጠቀምባቸው ከሆነ ከይሖዋ ሊያርቁን ይችላሉ።
ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ!
20 የሰይጣን ፍላጎት እኛን ከይሖዋ ማራቅ እንደሆነ የታወቀ ነው። ያም ቢሆን እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ በእናንተም ሆነ በቤተሰባችሁ ላይ እንዳይደርስ ማድረግ ትችላላችሁ! (ምሳሌ 22:3) ወደ ይሖዋ ለመቅረብና ከእሱ ጋር ምንጊዜም ተቀራርባችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ። በዚህ ረገድ ትምህርት የሚሰጡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹ በርካታ ምሳሌዎች አሉ። ሄኖክና ኖኅ ‘አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አድርገዋል።’ (ዘፍ. 5:22፤ 6:9) ሙሴ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል።” (ዕብ. 11:27) ኢየሱስ ሁልጊዜ በሰማይ የሚገኘው አባቱን የሚያስደስት ነገር ያደርግ ስለነበረ የአምላክ ድጋፍ አልተለየውም። (ዮሐ. 8:29) እንዲህ ያሉ ሰዎችን ምሳሌ ለመከተል ጥረት አድርጉ። “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ። ያለማቋረጥ ጸልዩ። ስለ ሁሉም ነገር አመስግኑ።” (1 ተሰ. 5:16-18) እንዲሁም ምንም ነገር ከይሖዋ እንዲያርቃችሁ አትፍቀዱ!
a ስሞቹ ተቀይረዋል።
b “ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ” የሚለውን የጥቅምት 2011 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።
c “ጤናን ለማሻሻል የሚረዱ አምስት ቁልፍ ነገሮች” የሚለውን የመጋቢት 2011 ንቁ! መጽሔት ተመልከት።
-