-
ከዲያብሎስ ወጥመዶች ተጠንቀቁ!መጠበቂያ ግንብ—2012 | ነሐሴ 15
-
-
ከዲያብሎስ ወጥመዶች ተጠንቀቁ!
‘ከዲያብሎስ ወጥመድ ውጡ።’—2 ጢሞ. 2:26
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ሌሎችን መተቸት የሚቀናን ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
በሰው ፍርሃትና ተጽዕኖ ላለመሸነፍ የጲላጦስና የጴጥሮስ ታሪክ ትምህርት የሚሆነን እንዴት ነው?
ከመጠን ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳንደቆስ ምን ሊረዳን ይችላል?
1, 2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመረምረው የትኞቹን የዲያብሎስ ወጥመዶች ነው?
ዲያብሎስ የይሖዋ አገልጋዮችን ለመያዝ አድፍጦ ይጠብቃል። የእሱ ዋነኛ ዓላማ አዳኞች እንደሚያደርጉት ሰለባዎቹን መግደል አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዲያብሎስ ፍላጎት የአምላክ አገልጋዮችን ከነሕይወታቸው ከያዘ በኋላ የእሱን ጥቅም እንዲያራምዱ ማድረግ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 2:24-26ን አንብብ።
2 አዳኞች አንድን እንስሳ ለመያዝ የተለያዩ ወጥመዶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ለምሳሌ እንስሳው ከተደበቀበት እንዲወጣና እነሱ ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረግ ሸምቀቆ ውስጥ ያስገቡታል። አሊያም ስውር የሆኑና ሲነኩ እንስሳውን በቁጥጥር ሥር የሚያደርጉ የወጥመድ ዓይነቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። ዲያብሎስም የአምላክን አገልጋዮች ከነሕይወታቸው ለመያዝ ተመሳሳይ ዘዴዎችን ይጠቀማል። በሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ የእሱ ወጥመዶች በአቅራቢያችን እንዳሉ የሚጠቁሙ የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ማስተዋልና ከዚያ መራቅ ይኖርብናል። ይህ ርዕስ ዲያብሎስ በተወሰነ መጠን ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው ሦስት ወጥመዶች ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንደምንችል ያብራራል። እነዚህም (1) ያልተገራ አንደበት፣ (2) የሰው ፍርሃትና የእኩዮች ተጽዕኖ እንዲሁም (3) ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ናቸው። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ደግሞ ሌሎች ሁለት የሰይጣን ወጥመዶችን እንመለከታለን።
ያልተገራ አንደበት የሚያስነሳውን እሳት ማጥፋት
3, 4. አንደበትን አለመቆጣጠር ምን ሊያስከትል ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
3 አንዳንድ አዳኞች አንድን እንስሳ ከተደበቀበት እንዲወጣ ለማድረግ የአካባቢውን የተወሰነ ክፍል እሳት ይለቁበታል፤ ከዚያም እንስሳው ለማምለጥ ሲሞክር ይይዙታል። ዲያብሎስ በምሳሌያዊ ሁኔታ በጉባኤው ውስጥ እሳት ማስነሳት ይፈልጋል። ከተሳካለት ደግሞ የጉባኤውን አባላት ካሉበት ሰላማዊ ስፍራ እንዲወጡ በማድረግ እጁ ውስጥ ያስገባቸዋል። ታዲያ ሳይታወቀን የሰይጣን ተባባሪዎች ልንሆን ወይም በእሱ መዳፍ ውስጥ ልንገባ የምንችለው እንዴት ነው?
4 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ምላስን ከእሳት ጋር አመሳስሎታል። (ያዕቆብ 3:6-8ን አንብብ።) አንደበታችንን መቆጣጠር ካልቻልን በጉባኤ ውስጥ እሳት ልንለኩስ እንችላለን። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንመልከት፦ በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንዲት እህት የዘወትር አቅኚ እንደሆነች ማስታወቂያ ተነግሯል። ከስብሰባው በኋላ ሁለት እህቶች ስለዚህ ማስታወቂያ እያወሩ ነው። አንደኛዋ እህት በሰማችው ማስታወቂያ እንደተደሰተችና አቅኚ ለሆነችው እህት ያላትን መልካም ምኞት ትገልጻለች። ሌላኛዋ ግን ይህች እህት አቅኚ ለመሆን የተነሳሳችበት ምክንያት ጥሩ እንዳልሆነና የሰዎችን ትኩረት መሳብ እንደምትፈልግ ትናገራለች። ከሁለቱ እህቶች ለጓደኝነት የምትመርጡት የትኛዋን ነው? ከእነዚህ ሁለት እህቶች በንግግሯ በጉባኤ ውስጥ እሳት የምትጭረው የትኛዋ እንደሆነች መለየት አዳጋች አይደለም።
5. ያልተገራ አንደበት የሚያስነሳውን እሳት ለማጥፋት ምን ማድረግ ይኖርብናል?
5 ያልተገራ አንደበት የሚያስነሳውን እሳት ማጥፋት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴ 12:34) በመሆኑም አንደበታችንን ለመግራት የመጀመሪያው እርምጃ ልባችንን መመርመር ነው። የማያንጽ ንግግር እንድንናገር የሚገፋፋንን መጥፎ ስሜት ለማስወገድ ጥረት እናደርጋለን? ለምሳሌ አንድ ወንድም አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ላይ ለመድረስ እየተጣጣረ እንደሆነ ስንሰማ ቶሎ የምናስበው ይህ ወንድም እንዲህ ለማድረግ የተነሳሳው በቅን ልቦና እንደሆነ ነው? ወይስ የራሱን ጥቅም ፍለጋ እንደሆነ ይሰማናል? ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር የመጠራጠር ዝንባሌ ካለን ዲያብሎስም ቢሆን ታማኝ የአምላክ አገልጋይ በሆነው በኢዮብ ውስጣዊ ግፊት ላይ ጥያቄ እንዳስነሳ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ኢዮብ 1:9-11) ወንድማችንን ከመጠራጠር ይልቅ እሱን ለመንቀፍ ያነሳሳንን ምክንያት መመርመራችን ተገቢ ነው። ስለ ወንድማችን እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖረን ያደረገን በእርግጥ በቂ ምክንያት አለን? ወይስ ልባችን በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ተስፋፍተው በሚገኙት ፍቅር የጎደላቸው ባሕርያት ተመርዟል?—2 ጢሞ. 3:1-4
6, 7. (ሀ) ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር በመጥፎ እንድንተረጉም የሚገፋፉን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ሌሎች ሲሰድቡን ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
6 ሌሎች የሚያደርጉትን ነገር በመጥፎ እንድንተረጉም ሊያነሳሱን የሚችሉ ተጨማሪ ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት። አንዱ ምክንያት እኛ የምናከናውነው ነገር ከሌሎች ጎልቶ እንዲታይ ስለምንፈልግ ሊሆን ይችላል። በሌላ አባባል ሌሎችን ወደታች በመጫን ራሳችንን ከፍ ለማድረግ እየሞከርን ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ማድረግ የሚገባንን ነገር ሳናከናውን በመቅረታችን ከተጠያቂነት ለማምለጥ መንገድ እየፈለግን ይሆናል። ሌሎችን የሚያጥላላ ነገር እንድንናገር የሚያነሳሳን ኩራትም ይሁን ቅናት አሊያም በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት ውጤቱ አስከፊ ነው።
7 አንድን ሰው ለመንቀፍ በቂ ምክንያት እንዳለን ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ምናልባትም ያ ሰው አንደበቱን ባለመቆጣጠሩ የተነሳ ተጎድተን ይሆናል። ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ አጸፋውን መመለስ መፍትሔ አይሆንም። እንዲህ ማድረግ በእሳቱ ላይ ጭድ እንደመጨመር ነው፤ አልፎ ተርፎም የአምላክን ሳይሆን የዲያብሎስን ዓላማ ማራመድ ነው። (2 ጢሞ. 2:26) በዚህ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ተገቢ ነው። ኢየሱስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። . . . ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥ. 2:21-23) ኢየሱስ ይሖዋ ነገሮችን በራሱ መንገድ እንደሚይዝና ጊዜውን ጠብቆ መፍትሔ እንደሚሰጥ እርግጠኛ ነበር። እኛም ብንሆን በአምላክ ላይ ተመሳሳይ እምነት ሊኖረን ይገባል። አንደበታችንን ፈዋሽ በሆነ መንገድ የምንጠቀምበት ከሆነ በጉባኤ ውስጥ “የመንፈስን አንድነት” መጠበቅ እንችላለን።—ኤፌሶን 4:1-3ን አንብብ።
እንደ ሸምቀቆ ከሆኑት የሰው ፍርሃትና የእኩዮች ተጽዕኖ ተጠንቀቁ
8, 9. ጲላጦስ በኢየሱስ ላይ የፈረደው ለምንድን ነው?
8 በሸምቀቆ የተያዘ እንስሳ እንደፈለገ መሆን አይችልም። በተመሳሳይም በሰው ፍርሃትና በእኩዮች ተጽዕኖ የተሸነፈ ሰው በተወሰነ መጠን ሕይወቱን የሚቆጣጠሩት ሌሎች ናቸው። (ምሳሌ 29:25ን አንብብ።) ከዚህ በመቀጠል በሰው ፍርሃትና በሌሎች ተጽዕኖ የተሸነፉ የሁለት ሰዎችን ምሳሌ እንመለከታለን፤ እንዲሁም ከእነሱ ተሞክሮ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመረምራለን።
9 የሮማ ገዥ የሆነው ጳንጥዮስ ጲላጦስ፣ ኢየሱስ ንጹሕ ሰው መሆኑን ስለሚያውቅ ሊጎዳው አልፈለገም ነበር። እንዲያውም “ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር” እንዳልፈጸመ ተናግሯል። ያም ሆኖ ኢየሱስ እንዲገደል ፈረደበት። ለምን? ይህን ያደረገው ሕዝቡ ባሳደረበት ተጽዕኖ ስለተሸነፈ ነው። (ሉቃስ 23:15, 21-25) ሕዝቡ “ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም” በማለት ሲጮኽ የእነሱን ፍላጎት ለማርካት ተገደደ። (ዮሐ. 19:12) ጲላጦስ ለክርስቶስ ቢፈርድ ሥልጣኑን ምናልባትም ሕይወቱን ሊያሳጣው እንደሚችል በማሰብ ፈርቶ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የዲያብሎስን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።
10. ጴጥሮስ ክርስቶስን እንዲክድ ያደረገው ምንድን ነው?
10 ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ነበር። ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ በሕዝብ ፊት መሥክሯል። (ማቴ. 16:16) ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በአንድ ወቅት ኢየሱስ የተናገረው ነገር ስላልገባቸው ትተውት ቢሄዱም ጴጥሮስ ግን ለኢየሱስ ታማኝ ሆኗል። (ዮሐ. 6:66-69) ጠላቶች ኢየሱስን ለማሰር በመጡ ጊዜም ጴጥሮስ ሰይፉን በመምዘዝ ጌታውን ተከላክሏል። (ዮሐ. 18:10, 11) ብዙም ሳይቆይ ግን ጴጥሮስ በሰው ፍርሃት ስለተሸነፈ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ እንደማያውቀው በመናገር ካደው። ይህ ሐዋርያ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በሰው ፍርሃት ወጥመድ በመያዙ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንዳይወስድ ተሽመድምዷል።—ማቴ. 26:74, 75
11. የትኞቹን መጥፎ ተጽዕኖዎች መቋቋም ይኖርብናል?
11 ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን አምላክን የሚያሳዝኑ ነገሮች እንድናደርግ የሚደርስብንን ጫና መቋቋም ይኖርብናል። አሠሪዎቻችን ወይም ሌሎች ሰዎች ሐቀኝነት የጎደለው ነገር እንድናደርግ አሊያም የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም ጫና ሊያሳድሩብን ይችላሉ። ተማሪዎች ደግሞ እኩዮቻቸው ፈተና ላይ እንዲያጭበረብሩ፣ የብልግና ምስሎችን እንዲመለከቱ፣ እንዲያጨሱ፣ ዕፅ እንዲወስዱ፣ ከልክ በላይ እንዲጠጡ ወይም የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽሙ የሚያደርሱባቸውን ጫና መቋቋም ሊኖርባቸው ይችላል። ታዲያ በሰው ፍርሃትና ተጽዕኖ ተሸንፈን ይሖዋን የሚያሳዝኑ ነገሮች ከማድረግ እንድንቆጠብ ምን ሊረዳን ይችላል?
12. ከጲላጦስና ከጴጥሮስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
12 ከጲላጦስና ከጴጥሮስ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት። ጲላጦስ ስለ ክርስቶስ የነበረው እውቀት ውስን ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ ንጹሕ እንደነበረና ተራ ሰው እንዳልነበረ ያውቃል። ይሁንና ጲላጦስ ትሕትና ይጎድለው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለእውነተኛው አምላክ ፍቅር አልነበረውም። በመሆኑም ዲያብሎስ ከነሕይወቱ በቀላሉ መዳፉ ውስጥ አስገባው። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ጴጥሮስ ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት የነበረው ከመሆኑም በላይ ይወደው ነበር። ይሁን እንጂ ልኩን ማወቅ የተሳነው ብሎም በፍርሃት የተሸነፈበትና ለተጽዕኖ እጁን የሰጠበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስ ከመያዙ ቀደም ብሎ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ግን አልሰናከልም” በማለት በጉራ ተናግሮ ነበር። (ማር. 14:29) ይህ ሐዋርያ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ አልፈራም፤ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” በማለት እንደተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት አቋም ቢኖረው ኖሮ ፈተናውን ለመቋቋም የተሻለ ብቃት ይኖረው ነበር። (መዝ. 118:6) ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወቱን ከማጠናቀቁ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ ጴጥሮስንና ሌሎች ሁለት ሐዋርያቱን ወደ ውስጠኛው የጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ይዟቸው ገብቶ ነበር። ይሁንና ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ነቅተው ከመጠበቅ ይልቅ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ኢየሱስ ከቀሰቀሳቸው በኋላ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ጸልዩም” አላቸው። (ማር. 14:38) ጴጥሮስ ግን ተመልሶ ተኛ፤ በመሆኑም በኋላ ላይ በሰው ፍርሃትና ተጽዕኖ ተሸነፈ።
13. መጥፎ ነገር እንድንፈጽም የሚደረግብንን ጫና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
13 ከጲላጦስና ከጴጥሮስ፣ ሌላም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፦ ተጽዕኖን በመቋቋም ረገድ ስኬታማ መሆን ከፈለግን ትክክለኛ እውቀት፣ ትሕትና፣ ልክን ማወቅ፣ ለአምላክ ፍቅር ማዳበር እንዲሁም ሰውን ሳይሆን ይሖዋን መፍራት ያስፈልገናል። እምነታችን የተመሠረተው በትክክለኛ እውቀት ላይ ከሆነ ስለምናምንበት ነገር በድፍረትና በቆራጥነት መናገር እንችላለን። ይህ ደግሞ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋምና የሰውን ፍርሃት ለማሸነፍ ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ ከልክ በላይ በራሳችን መመካት የለብንም። ከዚህ ይልቅ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን መቀበል ይኖርብናል። መንፈሱን እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ መጸለይ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ለስሙ ጥብቅና ለመቆምና መመሪያዎቹን ከፍ አድርገን ለመመልከት እንድንችል ለእሱ ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል። በተጨማሪም ፈተና ከመድረሱ በፊት ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆቻችንን በጸሎት ታግዘን የምናዘጋጃቸው ከሆነ እኩዮቻቸው መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ ጫና በሚያሳድሩባቸው ጊዜ ጥሩ ምላሽ መስጠት ይችላሉ።—2 ቆሮ. 13:7a
ከሚያደቅቀው ወጥመድ ተጠንቀቁ —ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት
14. ከዚህ በፊት ከሠራነው ስህተት ጋር በተያያዘ ዲያብሎስ ምን ብለን እንድንደመድም ይፈልጋል?
14 ሌላኛው የወጥመድ ዓይነት እንስሳው አዘውትሮ በሚያልፍበት መንገድ ላይ ትልቅ ግንድ ወይም ድንጋይ ከፍ አድርጎ ማንጠልጠል ነው። ከዚያም ምንም ያልጠረጠረው እንስሳ የወጥመዱን ገመድ ሲነካው ድንጋዩ ወይም ግንዱ እንስሳው ላይ በመውደቅ ያደቅቀዋል። ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከሚያደቅቅ ወጥመድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ከዚህ በፊት ስለሠራነው ስህተት ስናስብ ‘ፈጽሞ እንደደቀቅን’ ሊሰማን ይችላል። (መዝሙር 38:3-5, 8ን አንብብ።) ሰይጣን፣ የይሖዋ ምሕረት የማይገባን ሰዎች እንደሆንን ወይም አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር እንደማንችል አድርገን እንድንደመድም ይፈልጋል።
15, 16. ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?
15 የሚያደቅቀው ወጥመድ ሰለባ እንዳትሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ ጊዜ ሳታጠፋ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ለማደስ የሚያስችልህን እርምጃ ውሰድ። ወደ ሽማግሌዎች በመሄድ የእነሱን እርዳታ ጠይቅ። (ያዕ. 5:14-16) ስህተትህን ለማስተካከል የተቻለህን ሁሉ አድርግ። (2 ቆሮ. 7:11) ተግሣጽ በሚሰጥህ ጊዜ ከልክ በላይ አትዘን። ምክንያቱም ተግሣጽ ይሖዋ እንደሚወድህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ዕብ. 12:6) ወደ ኃጢአት የመራህን ድርጊት ላለመድገም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ፤ እንዲሁም ይህን ውሳኔህን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርግ። ንስሐ ከገባህና መጥፎ ድርጊት መፈጸምህን እርግፍ አድርገህ ከተውክ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሠራኸውን ኃጢአት ሊሸፍን እንደሚችል እምነት ይኑርህ።—1 ዮሐ. 4:9, 14
16 አንዳንዶች ይቅር የተባለላቸውን ኃጢአት እያሰቡ በጥፋተኝነት ስሜት ይዋጣሉ። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ ኢየሱስ በጣም ተጨንቆ በነበረበት ሰዓት ላይ ጥለውት ቢሄዱም ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት ይቅር እንዳላቸው አስታውስ። በተጨማሪም አስጸያፊ የሆነ የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸሙ ምክንያት ከቆሮንቶስ ጉባኤ ተወግዶ የነበረ አንድ ሰው ንስሐ በመግባቱ ይሖዋ ይቅር ብሎታል። (1 ቆሮ. 5:1-5፤ 2 ቆሮ. 2:6-8) መጽሐፍ ቅዱስ ከባድ ኃጢአት ይፈጽሙ የነበሩ ሆኖም ንስሐ በመግባታቸው አምላክ ይቅር ስላላቸው ሌሎች ሰዎችም ይናገራል።—2 ዜና 33:2, 10-13፤ 1 ቆሮ. 6:9-11
17. ቤዛው ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
17 እውነተኛ ንስሐ ከገባህና ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግልህ አምነህ የምትቀበል ከሆነ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ቀደም ሲል የሠራሃቸውን ኃጢአቶች ሊሸፍን እንደማይችል ሆኖ ፈጽሞ ሊሰማህ አይገባም። አለበለዚያ በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ ትገባለህ። ዲያብሎስ፣ ቤዛው የሁሉንም ሰዎች ኃጢአት ሊሸፍን አይችልም ብለህ እንድታምን ይፈልጋል። ይሁንና ሰዎች ንስሐ እስከገቡ ድረስ ኃጢአታቸው ሙሉ በሙሉ ይቅር ይባልላቸዋል። (ምሳሌ 24:16) በቤዛው ላይ ያለህ እምነት ሸክም የሆነብህ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከላይህ ላይ እንዲወርድ ብሎም አምላክን በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህና አእምሮህ እንድታገለግለው ያስችልሃል።—ማቴ. 22:37
የሰይጣንን ዕቅዶች እናውቃቸዋለን
18. ከዲያብሎስ ወጥመዶች መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ሰይጣን በእጁ እንግባለት እንጂ እኛን ለማጥመድ የሚጠቀምበት የወጥመድ ዓይነት አያሳስበውም። የሰይጣንን ዕቅዶች ስለምናውቃቸው ዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ማድረግ እንችላለን። (2 ቆሮ. 2:10, 11) የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ለመወጣት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን ወደ አምላክ የምንጸልይ ከሆነ በዲያብሎስ ወጥመድ አንያዝም። ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ ምክንያቱም አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣል፤ ለእሱም ይሰጠዋል” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:5) አዘውትረን የግል ጥናት በማድረግ እንዲሁም ከአምላክ ቃል ያገኘነውን ትምህርት በሥራ ላይ በማዋል ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት የሚዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎች፣ የዲያብሎስ ወጥመዶች ፍንትው ብለው እንዲታዩን በማድረግ ከእነሱ መራቅ እንድንችል ይረዱናል።
19, 20. ክፉ የሆኑ ነገሮችን መጥላት ያለብን ለምንድን ነው?
19 ጸሎትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመልካም ነገሮች ፍቅር እንድናዳብር ይረዱናል። ያም ሆኖ ክፉ የሆኑ ነገሮችን መጥላታችን የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። (መዝ. 97:10) የራስ ወዳድነት ምኞቶች በሚያስከትሏቸው ጎጂ ውጤቶች ላይ ማሰላሰላችን ከእነሱ ለመራቅ ያስችለናል። (ያዕ. 1:14, 15) ለመጥፎ ነገሮች ጥላቻ እንዲሁም ለመልካም ነገሮች እውነተኛ ፍቅር ስናዳብር ሰይጣን በወጥመዶቹ ላይ የሚያስቀምጣቸው ማባበያዎች አያጓጉንም፤ ከዚህ ይልቅ እንሸሻቸዋለን።
20 ሰይጣን እኛን ለማጥቃት መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ አምላክ ስለሚረዳን በጣም አመስጋኞች ነን! ይሖዋ በመንፈሱ፣ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት “ከክፉው” ያድነናል። (ማቴ. 6:13) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ዲያብሎስ የአምላክን አገልጋዮች ከነሕይወታቸው ለመያዝ ውጤታማ ሆኖ ያገኛቸውን ሁለት ተጨማሪ ወጥመዶች እንመረምራለን፤ እንዲሁም ከእነዚህ ወጥመዶች እንዴት መራቅ እንደምንችል እንመለከታለን።
-
-
ጸንታችሁ በመቆም የሰይጣንን ወጥመዶች ተቋቋሙ!መጠበቂያ ግንብ—2012 | ነሐሴ 15
-
-
ጸንታችሁ በመቆም የሰይጣንን ወጥመዶች ተቋቋሙ!
“የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች [ተቋቋሙ]።”—ኤፌ. 6:11
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
አንድ የይሖዋ አገልጋይ ከፍቅረ ንዋይ ወጥመድ መራቅ የሚችለው እንዴት ነው?
አንድ ያገባ ክርስቲያን በምንዝር ጉድጓድ ውስጥ እንዳይወድቅ ምን ሊረዳው ይችላል?
ከፍቅረ ንዋይና ከሥነ ምግባር ብልግና ጋር በተያያዘ የሚቀርብልንን ፈተና መቋቋማችን ጥቅሞች አሉት ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?
1, 2. (ሀ) ሰይጣን ለቅቡዓኑም ሆነ ‘ለሌሎች በጎች’ የርኅራኄ ስሜት የሌለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን የሰይጣን ወጥመዶች እንመረምራለን?
ሰይጣን ዲያብሎስ ለሰው ልጆች በተለይም ለይሖዋ አገልጋዮች ምንም ዓይነት የርኅራኄ ስሜት የለውም። እንዲያውም በቅቡዓን ቀሪዎች ላይ ጦርነት አውጇል። (ራእይ 12:17) እነዚህ ቀናተኛ ክርስቲያኖች በዘመናችን የሚካሄደውን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በግንባር ቀደምትነት እየሠሩ ሲሆን ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑንም እያጋለጡ ነው። ዲያብሎስ፣ ቅቡዓንን ለሚያግዙትና ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ለሚያደርጉት ‘ለሌሎች በጎችም’ ፍቅር የለውም፤ ሰይጣን ለዘላለም የመኖር ተስፋውን አጥቷል። (ዮሐ. 10:16) በመሆኑም መቆጣቱ የሚያስገርም አይደለም! ተስፋችን ሰማይም ይሁን ምድር ሰይጣን የእኛ ደኅንነት እንደማያሳስበው የተረጋገጠ ነው። ዓላማው እኛን ማጥቃት ነው።—1 ጴጥ. 5:8
2 ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት የተለያዩ ወጥመዶችን ይዘረጋል። ዲያብሎስ የማያምኑትን ሰዎች ‘አእምሮ በማሳወሩ’ ብዙዎች ምሥራቹን አይቀበሉም፤ እንዲሁም የእሱን ወጥመዶች ማስተዋል አይችሉም። ዲያብሎስ የመንግሥቱን መልእክት የተቀበሉ ሰዎችንም ለመያዝ ወጥመድ ያዘጋጃል። (2 ቆሮ. 4:3, 4) ቀደም ሲል በተመለከትነው ርዕስ ላይ ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ሦስት ወጥመዶች ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንደምንችል አይተናል። እነዚህም (1) ያልተገራ አንደበት፣ (2) የሰው ፍርሃትና የእኩዮች ተጽዕኖ እንዲሁም (3) ከመጠን ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ናቸው። አሁን ደግሞ ሌሎች ሁለት የሰይጣን ወጥመዶችን እንዴት መቋቋም እንደምንችል እንመረምራለን፤ የመጀመሪያው ፍቅረ ንዋይ ሲሆን ሁለተኛው ምንዝር የመፈጸም ፈተና ነው።
ፍቅረ ንዋይ—አንቆ የሚይዝ ወጥመድ
3, 4. የዚህ ሥርዓት ጭንቀት አንዳንዶች ቁሳዊ ነገር እንዲያሳድዱ ያደረጋቸው እንዴት ነው?
3 ኢየሱስ በሰጠው አንድ ምሳሌ ላይ በእሾህ መካከል ስለተዘራ ዘር ተናግሮ ነበር። አንድ ሰው ቃሉን ሊሰማ ቢችልም ‘የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ቃሉን እንደሚያንቀውና የማያፈራ እንደሚያደርገው’ ተናግሯል። (ማቴ. 13:22) በእርግጥም ፍቅረ ንዋይ፣ ጠላታችን ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው ወጥመዶች አንዱ ነው።
4 ቃሉን የሚያንቁት፣ ሁለት ነገሮች በአንድነት ተጣምረው ነው። አንደኛው “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” ነው። የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ’ ዘመን ውስጥ በመሆኑ በርካታ የሚያስጨንቁ ነገሮች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:1) ኑሮ እየተወደደ በመምጣቱና የሥራ አጦች ቁጥር በመጨመሩ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ተቸግረህ ይሆናል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ በማሰብም ተጨንቀህ ሊሆን ይችላል፤ ለምሳሌ ‘ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ሕይወቴን ለመምራት በቂ ገንዘብ ይኖረኝ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስብህ ይሆናል። አንዳንዶች ገንዘብ አስተማማኝ የሆነ ሕይወት ለመምራት ዋስትና እንደሚሆን ስለተሰማቸው ጭንቀታቸውን ለማስወገድ ሲሉ ሀብትን ማሳደድ ጀምረዋል።
5. ‘ሀብት የማታለል ኃይል’ ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?
5 ኢየሱስ፣ ቃሉን የሚያንቀው ሌላኛው ነገር “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” እንደሆነ ተናግሯል። ይህ ነገር ከጭንቀት ጋር ተዳምሮ ቃሉን ሊያንቀው ይችላል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ” እንደሆነ ይናገራል። (መክ. 7:12) ሆኖም ሀብትን ማሳደድ የጥበብ እርምጃ አይደለም። ብዙዎች ሀብታም ለመሆን ጥረት ባደረጉ መጠን ፍቅረ ንዋይ ወጥመድ እንደሆነባቸው አስተውለዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ለሀብት ባሪያ ሆነዋል።—ማቴ. 6:24
6, 7. (ሀ) አንድ ሰው በሥራ ቦታው በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ የመያዝ አደጋ ሊያጋጥመው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ትርፍ ሰዓት እንዲሠራ ግብዣ ሲቀርብለት ምን ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል?
6 አንድ ሰው ሀብታም የመሆን ምኞት የሚያዳብረው ሳይታወቀው ሊሆን ይችላል። እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። አሠሪህ ወደ አንተ መጥቶ እንዲህ አለህ እንበል፦ “ዛሬ የምሥራች ይዤልህ መጥቻለሁ! ድርጅታችን አንድ ትልቅ ጨረታ አሸንፏል። ይህ ማለት እንግዲህ፣ ለተወሰኑ ወራት ምሽት ላይ ሥራ መግባት አለብህ ማለት ነው። ነገር ግን ጠቀም ያለ ክፍያ ስለምታገኝ ተጨማሪ ሰዓት ብትሠራም የሚያስቆጭ አይሆንም።” እንዲህ ያለ ግብዣ ቢቀርብልህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? እውነት ነው፣ ለቤተሰብህ ቁሳዊ ነገር የማቅረቡን ጉዳይ በቁም ነገር መመልከትህ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሆኖም ያለብህ ኃላፊነት ይህ ብቻ አይደለም። (1 ጢሞ. 5:8) ግምት ውስጥ ልታስገባቸው የሚገቡ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችም አሉ። ትርፍ ጊዜ በመሥራት የምታሳልፈው ሰዓት ምን ያህል ነው? ሰብዓዊ ሥራህ የጉባኤ ስብሰባንና የቤተሰብ አምልኮን ጨምሮ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህን ይነካብሃል?
7 ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ በዋነኝነት የሚያሳስብህ ምንድን ነው? ትርፍ ሰዓት መሥራትህ ከገንዘብ አኳያ የሚያስገኝልህ ጥቅም ነው ወይስ በመንፈሳዊነትህ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ? ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ያለህ ጉጉት በሕይወትህ ውስጥ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ እንዳትሰጥ እንቅፋት ይሆንብህ ይሆን? የራስህንም ሆነ የቤተሰብህን መንፈሳዊነት ችላ የምትል ከሆነ ፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ሊሆንብህ እንደሚችል ተገንዝበሃል? ገንዘብ ለማግኘት ስትል መንፈሳዊነትህ አደጋ ላይ ወድቆ ከሆነ የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋምና ፍቅረ ንዋይ አንቆ እንዳይዝህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።
8. ያለንበትን ሁኔታ ለመገምገም የሚረዱን የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ናቸው?
8 ፍቅረ ንዋይ አንቆ እንዳይዝህ በየጊዜው ያለህበትን ሁኔታ ገምግም። ለመንፈሳዊ ነገሮች አክብሮት የጎደለው መሆኑን በተግባሩ እንዳስመሠከረው እንደ ዔሳው መሆን እንደማትፈልግ ግልጽ ነው። (ዘፍ. 25:34፤ ዕብ. 12:16) እንዲሁም ኢየሱስ ያለውን ሁሉ ሸጦ ለድሆች በመስጠት እሱን እንዲከተል ግብዣ እንዳቀረበለት ሰው መሆን እንደማትፈልግ የተረጋገጠ ነው። ይህ ሰው የተባለውን ከማድረግ ይልቅ “ብዙ ንብረት ስለነበረው እያዘነ ሄደ።” (ማቴ. 19:21, 22) ሀብት ወጥመድ ስለሆነበት፣ በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ ታላቅ ሰው የሆነው የኢየሱስ ተከታይ የመሆን ውድ መብት አጣ! አንተም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የመሆን መብትህን እንዳታጣ ተጠንቀቅ።
9, 10. ቅዱሳን መጻሕፍት ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተ ከሚሰጡት ምክር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ትችላለህ?
9 ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ ከፈለግን ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ይኖርብናል፦ “‘ምን እንበላለን?’ ወይም ‘ምን እንጠጣለን?’ ወይም ደግሞ ‘ምን እንለብሳለን?’ ብላችሁ ፈጽሞ አትጨነቁ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ አሕዛብ አጥብቀው የሚፈልጓቸው ናቸው። በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”—ማቴ. 6:31, 32፤ ሉቃስ 21:34, 35
10 ሀብት ያለው የማታለል ኃይል ወጥመድ እንዳይሆንብህ ከፈለግክ “የሚያስፈልገኝን ያህል . . . ስጠኝ እንጂ ሀብታም ወይም ድኻ አታድርገኝ” በማለት የተናገረው የአጉር ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 30:8 የ1980 ትርጉም) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው አጉር ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሚሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሀብት የማታለል ኃይል እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። የዚህ ሥርዓት ጭንቀትና ሀብት ያለው የማታለል ኃይል መንፈሳዊነትህን ሊያሳጡህ እንደሚችሉ ፈጽሞ አትዘንጋ። ስለ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ ጊዜህን ሊያባክንብህ፣ ኃይልህን ሊያሟጥጥብህ እንዲሁም ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም ያለህን ፍላጎት ቀስ በቀስ ሊያጠፋብህ ይችላል። በመሆኑም የሰይጣን ወጥመድ የሆነው ፍቅረ ንዋይ አንቆ እንዳይዝህ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ!—ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።
ምንዝር—ስውር ጉድጓድ
11, 12. አንድ ክርስቲያን ከሥራ ባልደረባው ጋር ምንዝር ለመፈጸም የሚፈተነው እንዴት ሊሆን ይችላል?
11 አዳኞች፣ አንድ ትልቅ እንስሳ ለመያዝ ሲፈልጉ እንስሳው አዘውትሮ በሚመላለስበት መንገድ ላይ ጉድጓድ ይቆፍራሉ፤ አብዛኛውን ጊዜ ጉድጓዱ ላይ ቀጫጭን እንጨት ከረበረቡ በኋላ አፈር ያለብሱታል። ሰይጣን በጣም ውጤታማ ሆኖ ካገኛቸው ፈተናዎች አንዱ ከዚህ ወጥመድ ጋር ይመሳሰላል፤ ይህም የሥነ ምግባር ብልግና ነው። (ምሳሌ 22:14፤ 23:27) በርካታ ክርስቲያኖች በቀላሉ እጃቸውን እንዲሰጡ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን በማስገባታቸው እዚህ ጉድጓድ ውስጥ ገብተዋል። አንዳንድ ያገቡ ክርስቲያኖች ከተቃራኒ ፆታ ጋር አላስፈላጊ የሆነ ቅርርብ በመፍጠራቸው ምንዝር እስከመፈጸም ደርሰዋል።
12 በሥራ ቦታችሁ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት እንድትጀምሩ ትፈተኑ ይሆናል። አንድ ዓለማዊ ጥናት እንደጠቆመው ምንዝር ከፈጸሙት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች እንዲሁም ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ወንዶች ይህን ያደረጉት አብረዋቸው ከሚሠሩ ሰዎች ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ በመፍጠራቸው ነው። የሥራህ ዓይነት፣ ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ሰዎች ጋር እንድትቀራረብ ያስገድድሃል? ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከሥራ ያለፈ ግንኙነት እንዳይፈጠር ገደብ አበጅተሃል? ለምሳሌ፣ አንዲት እህት አብሯት ከሚሠራ አንድ ሰው ጋር ከሥራ ውጪ ስለሆኑ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ የምታወራ ከሆነ ሚስጥረኛዋ ልታደርገው አልፎ ተርፎም በትዳሯ ውስጥ ስለሚያጋጥማት ችግር ልታጫውተው ትችላለች። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ወንድም አብራው ከምትሠራ ሴት ጋር ስለተግባባ እንዲህ ብሎ ሊያስብ ይችላል፦ “የእኔን አመለካከት ታከብርልኛለች፤ ደግሞም የምናገረውን በጥሞና ታዳምጣለች። እንዲሁም ለእኔ አድናቆት አላት። ምናለ ሚስቴ እንዲህ ብትሆንልኝ!” እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምንዝር ለመፈጸም ምን ያህል እንደተጋለጡ አስተዋላችሁ?
13. በጉባኤ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ሊመሠረት የሚችለው እንዴት ነው?
13 ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት በጉባኤ ውስጥም ሊጀመር ይችላል። እስቲ የሚከተለውን አንድ እውነተኛ ታሪክ እንመልከት፦ ዳንኤልና ባለቤቱ ሣራa የዘወትር አቅኚዎች ነበሩ። ዳንኤል “እምቢ የሚል ቃል ከአፉ የማይወጣ ሽማግሌ” እንደነበር ይናገራል። የሚሰጠውን ኃላፊነት በሙሉ በደስታ የሚቀበል ሰው ነበር። ዳንኤል አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የነበሩት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሦስቱ ተጠምቀውለታል። እነዚህ አዲስ የተጠመቁ ወንድሞች በተወሰነ መጠን እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። በመሆኑም ዳንኤል በተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶች በሚወጣጠርበት ጊዜ ሣራ እነዚህን ወንድሞች ትረዳቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ይህ ነገር ልማድ እየሆነ መጣ፤ የዳንኤል የቀድሞ ጥናቶች ስሜታዊ እርዳታ ባስፈለጋቸው ቁጥር ወደ ሣራ ይመጣሉ። እሷ ደግሞ ትኩረት በሚያስፈልጋት ጊዜ ወደ ዳንኤል ጥናቶች ዘወር ትላለች። በዚህ መንገድ አንድ አደገኛ ወጥመድ ተዘረጋ። ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ከወር እስከ ወር ያላትን ኃይል ሁሉ ተጠቅማ ሌሎችን ለመርዳት ትጥር ስለነበር መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ እርዳታ ያስፈልጋት ነበር። ይህ ሁኔታ እሷን ችላ ከማለቴ ጋር ተዳምሮ በጣም አሳዛኝ ነገር እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል። ባለቤቴ ከቀድሞ ጥናቶቼ ከአንዱ ጋር ምንዝር ፈጸመች። አፍንጫዬ ሥር ሆና በመንፈሳዊ ስትደክም ምንም አላስተዋልኩም፤ ምክንያቱም ትኩረት ያደረግኩት ኃላፊነቶቼን በመወጣት ላይ ብቻ ነበር።” ይህ ሁኔታ በአንተ ላይ እንዳይደርስ ምን ማድረግ ትችላለህ?
14, 15. አንድ ያገባ ክርስቲያን በምንዝር ጉድጓድ ውስጥ ከመግባት ምን ሊጠብቀው ይችላል?
14 በምንዝር ጉድጓድ ውስጥ እንዳትወድቅ ከፈለግክ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ማሰላሰልህ ጠቃሚ ነው። ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏል። (ማቴ. 19:6) ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነትህ ከትዳር ጓደኛህ እንደሚበልጥ አድርገህ በፍጹም ማሰብ የለብህም። በተጨማሪም እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን ለማከናወን ስትል ብዙ ጊዜ ከትዳር ጓደኛህ ተለይተህ ጊዜ ማሳለፍህ በትዳርህ ውስጥ ችግር እንዳለ ይጠቁማል፤ ይህ ደግሞ ወደ ፈተና አልፎ ተርፎም ከባድ ኃጢአት ወደ መሥራት ሊመራህ ይችላል።
15 ምናልባት ሽማግሌ ከሆንክ መንጋውን የመንከባከቡ ኃላፊነትህ ያሳስብህ ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ፤ በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት [ጠብቁ]።” (1 ጴጥ. 5:2) በአደራ የተሰጡህን የጉባኤ አባላት ችላ ማለት እንደሌለብህ የታወቀ ነው። ሆኖም በጉባኤ ውስጥ እረኛ የመሆን ኃላፊነትህን የምትወጣው የባልነት ኃላፊነትህን አደጋ ላይ ጥለህ መሆን የለበትም። የትዳር ጓደኛህ “እየተራበች” መንጋውን ለመመገብ መሯሯጥህ ምንም ፋይዳ የለውም፤ እንዲያውም እንዲህ ማድረጉ አደገኛ ነው። ዳንኤል ‘ቤተሰብህ እስኪጎዳ ድረስ በጉባኤ ኃላፊነት መወጠር የለብህም’ ብሏል።
16, 17. (ሀ) ያገቡ ክርስቲያኖች በሥራ ቦታቸው የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር ሐሳቡም እንኳ እንደሌላቸው በግልጽ ለማሳወቅ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ? (ለ) ክርስቲያኖች ምንዝር እንዳይፈጽሙ ሊረዷቸው የሚችሉ አንዳንድ ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?
16 ያገቡ ክርስቲያኖች በምንዝር ወጥመድ ውስጥ ከመግባት እንዲጠበቁ ሊረዷቸው የሚችሉ በርካታ ምክሮች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የመስከረም 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ምክር ይዟል፦ “በሥራ ቦታም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የፍቅር ግንኙነት ወደ መመሥረት ሊያደርሱ በሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቁ። ለምሳሌ፣ ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ከሥራ ሰዓት ውጭ ተቀራርቦ መሥራት ለፈተና ሊዳርግ ይችላል። ያገባችሁ እንደመሆናችሁ መጠን ከትዳር ጓደኛችሁ ውጭ ከማንም ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ፈቃደኛ አለመሆናችሁን በንግግራችሁም ሆነ በአኳኋናችሁ በግልጽ ማሳየት ይኖርባችኋል። ለአምላክ ያደራችሁ ሰዎች ስለሆናችሁ ሌሎችን በማሽኮርመምም ሆነ ተገቢ ባልሆነ አለባበስና አጋጌጥ አላስፈላጊ ትኩረት መሳብ እንደማትፈልጉ ጥያቄ የለውም። . . . የትዳር ጓደኛችሁንና የልጆቻችሁን ፎቶግራፍ በሥራ ቦታችሁ ማስቀመጣችሁ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጧቸው ሰዎች መኖራቸውን እናንተም ሆናችሁ ሌሎች እንድታስታውሱ ይረዳችኋል። ሌሎች ሰዎች እናንተን በፍቅር ለመማረክ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉበት የሚያበረታታ አዝማሚያ ላለማሳየትና ሌላው ቀርቶ ድርጊታቸውን በዝምታ ላለማለፍም ጭምር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።”
17 የሚያዝያ 2009 ንቁ! “ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?” በሚለው ርዕስ ላይ የትዳር ጓደኛ ካልሆነ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት ስለ መፈጸም ማውጠንጠን አደጋ እንዳለው አስጠንቅቆ ነበር። ይህ መጽሔት አንድ ሰው ስለ ፆታ ግንኙነት ማውጠንጠኑ ምንዝር የመፈጸሙ አጋጣሚ ሰፊ እንዲሆን ሊያደርግ እንደሚችል ጠቁሟል። (ያዕ. 1:14, 15) ያገባህ ከሆንክ ከትዳር ጓደኛህ ጋር እንዲህ ያሉ ትምህርቶችን በየጊዜው መከለስህ ጥበብ ነው። የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው ይሖዋ ከመሆኑም በላይ ጋብቻ ቅዱስ ነገር ነው። ከባለቤትህ ጋር ስለ ትዳራችሁ ለመወያየት ጊዜ መመደብህ ቅዱስ ነገሮችን እንደምታደንቅ ከምታሳይባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ ነው።—ዘፍ. 2:21-24
18, 19. (ሀ) ምንዝር መፈጸም ምን መዘዝ ያስከትላል? (ለ) ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን ምን ጥቅሞችን ያስገኛል?
18 ተገቢ ያልሆነ የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ከተፈተንክ ዝሙትም ሆነ ምንዝር መፈጸም በሚያስከትለው ጎጂ ውጤት ላይ አሰላስል። (ምሳሌ 7:22, 23፤ ገላ. 6:7) የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ይሖዋን የሚያሳዝኑ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውንም ሆነ የትዳር ጓደኛቸውን ይጎዳሉ። (ሚልክያስ 2:13, 14ን አንብብ።) ከዚህ ይልቅ ንጹሕ ሥነ ምግባር መያዝ በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ማሰላሰሉ ጠቃሚ ነው። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ንጹሕ ሕሊና ይዘው የተሻለ ሕይወት መምራት ይችላሉ።—ምሳሌ 3:1, 2ን አንብብ።
19 መዝሙራዊው “ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ዕንቅፋትም የለባቸውም” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 119:165) እንግዲያው ለእውነት ፍቅር ሊኖረን ይገባል፤ እንዲሁም በእነዚህ ክፉ ቀኖች ‘የምንመላለሰው ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ ማስተዋል አለብን።’ (ኤፌ. 5:15, 16) የምንጓዝበት የሕይወት መንገድ ሰይጣን እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን ለማጥመድ በዘረጋቸው ወጥመዶች የተሞላ ነው። ሆኖም ራሳችንን ከእነዚህ ወጥመዶች ለመጠበቅ በቂ መሣሪያዎች አሉን። ይሖዋ “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም” እንዲሁም “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን” እንድንችል የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል።—ኤፌ. 6:11, 16
-