የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ምን ጥቅም አለው?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ታኅሣሥ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ

      መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ምን ጥቅም አለው?

      “መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው የሚታወቅ የሃይማኖት መጽሐፍ ነው። ይሁንና የሌላ አገር መጽሐፍ ስለሆነ ለቻይናውያን ምንም አይጠቅምም።”—ሊን፣ ቻይና

      “የራሴን የሂንዱ ሃይማኖት ቅዱስ መጻሕፍት እንኳ መረዳት አቅቶኛል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊገባኝ ይችላል?”—ኧሚት፣ ሕንድ

      “መጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ መጽሐፍ ስለሆነ ለመጽሐፉ አክብሮት አለኝ፤ ደግሞም በብዛት በመሸጥ ረገድ ተወዳዳሪ እንደሌለው ሰምቻለሁ። ይሁንና መጽሐፉን በዓይኔ እንኳ አይቼው አላውቅም።”—ዩሚኮ፣ ጃፓን

      በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍ ያለ ግምት አላቸው። ሆኖም ስለ መጽሐፉ ይዘት የሚያውቁት ነገር የለም፤ አወቁ ቢባል እንኳ እውቀታቸው ቁንጽል ነው። ይህ አባባል በእስያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሁኔታ በትክክል ይገልጻል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በብዛት በሚሰራጭበት ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም።

      አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበች

      ያም ሆኖ ‘መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ማድረግ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ልትጠይቅ ትችላለህ። ይህን ቅዱስ መጽሐፍ መረዳትህ የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስገኝልሃል፦

      • እውነተኛ እርካታና ደስታ

      • የቤተሰብ ችግሮችን መቋቋም የሚቻልበት ጥበብ

      • ጭንቀትን የምትቋቋምበት ጥንካሬ

      • ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት

      • ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም መቻል

      ለምሳሌ ያህል፣ በጃፓን የምትኖረውን የዮሺኮን ሁኔታ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ለማወቅ ስለፈለገች መጽሐፉን በግሏ ለማንበብ ወሰነች። ይህስ ምን አስገኘላት? እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ እንድገነዘብ እና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ተስፋ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። አሁን የባዶነት ስሜት አይሰማኝም።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኧሚት መጽሐፍ ቅዱስን በግሉ ለመመርመር ወሰነ። ከዚያም “በጣም የገረመኝ ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ሁሉ የሚጠቅም መረጃ የያዘ መሆኑ ነው” ብሏል።

      መጽሐፍ ቅዱስ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። አንተስ መጽሐፉን በመመርመር እንዴት ሊጠቅምህ እንደሚችል ለምን አታይም?

      መጽሐፍ ቅዱስ ስላለው ጥቅም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል! የሚለውን ብሮሹር ተመልከት። ጽሑፉ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።

  • ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባ መጽሐፍ
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ታኅሣሥ 1
    • በመጽሐፍ መልክ ከተዘጋጀውም ሆነ ከሞባይል ስልክ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ

      ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባ መጽሐፍ

      መጽሐፍ ቅዱስ ዕድሜ ጠገብ መጽሐፍ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ለመሆኑ ምን ያህል ዘመን አስቆጥሯል? መጽሐፍ ቅዱስን መጻፍ የተጀመረው ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ነበር። ይህም ማለት በቻይና ኃያሉ የሻንግ ሥርወ መንግሥት ይገዛ በነበረበት ዘመን እንዲሁም በሕንድ የቡድሃ ሃይማኖት ከመቋቋሙ ከአሥር መቶ ዓመታት ገደማ በፊት መሆኑ ነው።—“መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱ መረጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል

      አንድ መጽሐፍ ለሰዎች ሕይወት የሚጠቅምና መመሪያ የያዘ እንዲሆን ከተፈለገ ሊረዱት የሚችሉትና እነሱን የሚመለከት ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

      ለምሳሌ ያህል ‘የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ አሳስቦህ ያውቃል? ይህ ጥያቄ የሰው ልጆችን ለበርካታ ሺህ ዓመታት ግራ ሲያጋባ ቆይቷል፤ ዛሬም እውነታው ይኸው ነው። ሆኖም የዚህ ጥያቄ መልስ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ አንድ እና ሁለት ላይ ይገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ወደኋላ መልሶን የከዋክብት ረጨቶችን፣ ከዋክብትንና ምድርን የያዘው ግዑዙ ጽንፈ ዓለም እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጣ ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 1:1) ከዚያም ምድር ለሰው ልጆች መኖሪያነት እንዴት ምቹ እንደተደረገች፣ ሕይወት ያላቸው የተለያዩ ነገሮች እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጡ፣ ሰዎች እንዴት እንደተፈጠሩ እንዲሁም እነዚህ ሁሉ ነገሮች የተፈጠሩበት ዓላማ ምን እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ይገልጻል።

      ሰዎች ሊረዱት በሚችል መንገድ የተጻፈ

      መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንወጣ የሚያስችል ተግባራዊ ምክር ይዟል። ምክሩ ደግሞ ለመረዳት አያዳግትም። ይህንን ከሁለት አቅጣጫ ማየት እንችላለን።

      በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ግልጽ፣ ቀጥተኛ እና ማራኪ በሆነ መንገድ ነው። ለመረዳት የሚከብዱ ወይም ሚስጥራዊ የሆኑ አገላለጾችን ብዙ ቦታዎች ላይ አናገኝም፤ ከዚህ ይልቅ ተጨባጭ የሆኑና ሊገቡን የሚችሉ መግለጫዎችን ይጠቀማል። ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑት ሐሳቦች እንኳ የተገለጹት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በምንጠቀምባቸው ቃላት ነው።

      ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ ለማስተማር በየዕለቱ በሚያዩአቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ በርካታ ቀላል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ፣ በተለምዶ የተራራው ስብከት ተብሎ በሚጠራው ላይ የተጠቀሱ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። አንድ ተንታኝ ይህን ስብከት “ጠቃሚ ሐሳቦችን የያዘ ንግግር” በማለት የገለጸ ከመሆኑም ሌላ ዓላማውን በተመለከተ ያስተዋለውን ሲናገር “ጭንቅላታችንን በእውቀት መሙላት ሳይሆን ድርጊታችንን መምራትና መቆጣጠር ነው” ብሏል። እነዚህን ምዕራፎች በ15 ወይም በ20 ደቂቃ ውስጥ አንብበህ መጨረስ ትችላለህ፤ ደግሞም ኢየሱስ ያስተማረው ትምህርት ቀላል ሆኖም አሳማኝ በመሆኑ መገረምህ አይቀርም።

      መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ቀላል እንዲሆን የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ ይዘቱ ነው። የአፈ ታሪክ ወይም የተረት መጽሐፍ አይደለም። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛው “ስለ ታላላቅ ሰዎችም ሆነ ስለ ተራ ሰዎች” እንዲሁም “ስላሳለፉት ውጣ ውረድና ተስፋ ስላደረጉት ነገር ብሎም ስላጋጠማቸው ሽንፈትና ስለተቀዳጁት ድል” እንደሚገልጽ ዘግቧል። በእውን ስለነበሩ ስለ እነዚህ ሰዎችና ክንውኖች የሚገልጹትን ዘገባዎች ከራሳችን ሕይወት ጋር ማያያዝና በውስጣቸው የያዟቸውን ትምህርቶች መረዳት አይከብደንም።—ሮም 15:4

      ሁሉም ሰው ሊያገኘው የሚችል

      አንድን መጽሐፍ አንብበህ መረዳት እንድትችል በምታውቀው ቋንቋ መጻፍ ይኖርበታል። የምትኖረው የትም ሆነ የት ወይም ዜግነትህ ምንም ይሁን ምን በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አንተ መረዳት በምትችለው ቋንቋ የማግኘት አጋጣሚ አለህ። ይህን ለማመን የሚያዳግት ክንውን ዳር ለማድረስ ምን ጥረት እንደጠየቀ ተመልከት።

      ትርጉም። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ፣ በአረማይክና በግሪክ ነው። ይህ በራሱ የአንባቢዎቹን ቁጥር እንደሚገድበው የታወቀ ነው። በመሆኑም በቅን ልቦና የተነሳሱ ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ቋንቋዎችም እንዲገኝ ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይግባውና፣ በዛሬው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል በ2,700 ገደማ ቋንቋዎች ይገኛል። ይህ ሲባል ከዓለም ሕዝብ መካከል 90 ከመቶ በላይ የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋው ማንበብ ይችላል ማለት ነው።

      ሕትመት። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው እንደ ፓፒረስና ብራና ባሉ ሊበላሹ በሚችሉ ቁሶች ላይ ነበር። መልእክቱን በቀጣይነት ለማስተላለፍ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ደግሞ ደጋግሞ በእጅ መገልበጥ አስፈልጓል። የእነዚህ ቅጂዎች ዋጋ ውድ በመሆኑ ብዙ ሰዎች መግዛት አይችሉም ነበር። ሆኖም ጉተንበርግ ከ550 ዓመታት በፊት የሠራው የማተሚያ ማሽን መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው እንዲሰራጭ አስችሏል። አንድ ግምታዊ አኃዝ እንደሚያሳየው መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉም ሆነ በከፊል ከአምስት ቢሊዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች ተሰራጭቷል።

      በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስን ሊተካከል የሚችል ሌላ ሃይማኖታዊ ጽሑፍ የለም። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሊረዱት የሚገባ መጽሐፍ ነው። ሆኖም መጽሐፉን መረዳት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። ግን ከየት? ጥቅም ማግኘት የምትችለውስ እንዴት ነው? ቀጣዩ ርዕስ መልሱን ይዟል።

      መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱ መረጃዎች

      • መጽሐፍ ቅዱስ 66 መጻሕፍትን ይዟል።

      • መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፣ ሕግ፣ ትንቢት፣ ግጥም፣ ምሳሌ፣ መዝሙርና ደብዳቤ የያዘ መጽሐፍ ነው።

      • መጻፍ የተጀመረው በ1513 ዓ.ዓ. ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ በ98 ዓ.ም. ነው፤ በመሆኑም ከ1,600 የሚበልጡ ዓመታት ፈጅቷል።

      • መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት 40 በሚያህሉ ሰዎች ነው።

      ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?

      ሕይወት እንዴት እንደተገኘ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት። ጽሑፉ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።

      መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው?

      ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት። ጽሑፉ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።

  • መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እገዛ ማግኘት
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ታኅሣሥ 1
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ

      መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እገዛ ማግኘት

      አንድን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ እየጎበኘህ ነው እንበል። በዚያ ሕዝቡም ሆነ ባሕሉ እንዲሁም ምግቡ ለአንተ እንግዳ ነው፤ ገንዘባቸውንም ቢሆን ከዚህ በፊት አይተኸው አታውቅም። ሁኔታው ግራ ሊያጋባህ እንደሚችል ግልጽ ነው።

      አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነብ ተመሳሳይ ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። በዚህ ጊዜ ወደማታውቀው አንድ ጥንታዊ ዓለም የሄድክ ያህል ነው። በዚያም ፍልስጤማውያን የሚባሉ ሕዝቦች ታገኛለህ፣ ‘ከልብስ መቅደድ’ ጋር የተያያዘ ያልተለመደ ባሕል ትመለከታለህ ወይም መና የሚባል ምግብና ድራክማ የሚባል ሳንቲም መኖሩን ታያለህ። (ዘፀአት 16:31፤ ኢያሱ 13:2፤ 2 ሳሙኤል 3:31፤ ሉቃስ 15:9) ይህ ሁሉ ግራ ሊያጋባህ ይችላል። በመሆኑም የማታውቀውን አገር ስትጎበኝ የሚመራህ ሰው እንደሚያስፈልግ ሁሉ በዚህ ረገድም ነገሮችን የሚያብራራልህ ሰው ብታገኝ ደስ አይልህም?

      በጥንት ጊዜ የቀረበ እርዳታ

      ቅዱሳን መጻሕፍትን በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጻፍ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች መልእክቱን መረዳት እንዲችሉ እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤል ብሔር የመጀመሪያ መሪ የነበረው ሙሴ በሕጉ ላይ የተጻፈውን ነገር ለሕዝቡ “ያብራራ” ነበር።—ዘዳግም 1:5

      ከዚያ ከአሥር መቶ ዓመታት ገደማ በኋላም ብቃት ያላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት አስተማሪዎች ይገኙ ነበር። በ455 ዓ.ዓ. በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ አደባባይ ላይ በርካታ ሕፃናትን ጨምሮ ብዛት ያላቸው አይሁዳውያን ተሰብስበው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎቹ ከቅዱስ ‘መጽሐፉ ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አነበቡላቸው።’ ይሁንና በዚህ ብቻ አልተወሰኑም። “የተነበበውን ነገር ማስተዋል እንዲችል ሕዝቡን ይረዱት ነበር።”—ነህምያ 8:1-8

      ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመሳሳይ የሆነ የማስተማር ሥራ አከናውኗል። እንዲያውም በሕዝቡ ዘንድ በዋነኝነት የሚታወቀው በአስተማሪነቱ ነበር። (ዮሐንስ 13:13) ብዛት ያላቸው ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችንም አስተምሯል። አንድ ወቅት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕዝብ በሰፊው የሚታወቀውን የተራራ ስብከቱን የሰጠ ሲሆን እነሱም “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።” (ማቴዎስ 5:1, 2፤ 7:28) በ33 ዓ.ም. የጸደይ ወራት ኢየሱስ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወዳለች አንዲት መንደር ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እየተነጋገረ በተጓዘበት ወቅት ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ገልጦላቸዋል [‘በግልጽ አብራርቶላቸዋል፣’ የግርጌ ማስታወሻ]።’—ሉቃስ 24:13-15, 27, 32

      የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ነበሩ። አንድ ወቅት ላይ ከኢትዮጵያ የሄደ ባለሥልጣን ቅዱሳን መጻሕፍትን እያነበበ ሳለ ፊልጶስ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ወደ እሱ ቀርቦ “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኢትዮጵያዊውም “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” በማለት መለሰለት። ከዚያም ፊልጶስ ያነብ የነበረው ክፍል ምን ትርጉም እንዳለው አብራራለት።—የሐዋርያት ሥራ 8:27-35

      በዛሬው ጊዜ የሚገኝ እርዳታ

      በጥንት ዘመን እንደነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በ239 አገሮች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራ ይካፈላሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ቀደም ሲል የክርስትና እምነት ተከታዮች አልነበሩም። ለጥናቱ ምንም ዓይነት ክፍያ አይጠየቅም፤ እንዲሁም በሚያጠናው ግለሰብም ቤት ሆነ በሌላ አመቺ ቦታ ሊካሄድ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ኮምፒውተር ወይም ተንቀሳቃሽ መሣሪያ በመጠቀም በስልክ ወይም በቪዲዮ መጽሐፍ ቅዱስ ይማራሉ።

      በዚህ ዝግጅት እንዴት መጠቀም እንደምትችል በዝርዝር ለማወቅ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን እንድታነጋግር እናበረታታሃለን። እንዲህ ካደረግክ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሊገባው የማይችል መጽሐፍ ከመሆን ይልቅ “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ” የሚጠቅም እንደሆነ ትገነዘባለህ። በመሆኑም ‘ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ መታጠቅና ሙሉ በሙሉ ብቁ መሆን’ ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

      www.jw.org/am ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት

      www.jw.org/am ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው እንዴት ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት

      ድረ ገጽ ላይ የቀረበ እርዳታ

      አንዲት ሴት ካፌ ውስጥ ቁጭ ብላ jw.org የተባለውን ድረ ገጽ ስትጎበኝ

      መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ማንም እርዳታ መመርመር ትፈልጋለህ? ይህን ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ jw.org/am የተባለውን ድረ ገጽ ጎብኝ። ድረ ገጹ ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከቱ መረጃዎች በነፃ ያቀርባል። በሚከተሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መረጃ ማግኘት ትፈልግ ይሆናል፦

      ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች

      • የሕይወት ትርጉሙ ምንድን ነው?

      • ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?

      • ስንሞት ምን እንሆናለን?

      (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በሚለው ሥር ይገኛል)

      የግል ጉዳዮች

      • የመንፈስ ጭንቀት ቢያጋጥምህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

      • ከከባድ በሽታ ጋር መኖር

      • የገንዘብ ችግርና ዕዳ

      (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በሚለው ሥር ይገኛል)

      ለቤተሰብ

      • መጨቃጨቅ ማቆም የምትችሉት እንዴት ነው?

      • ልጆችን ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ አድርጎ ማሳደግ

      • በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ የሥነ ምግባር እሴቶችን ትከሉ

      (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ባለትዳሮች እና ወላጆች በሚለው ሥር ይገኛል)

      ለወጣቶች የተሰጡ ምክሮች

      • ፆታዊ ትንኮሳ ቢያጋጥመኝ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

      • ጉልበተኞች ቢያስቸግሩኝ ምን ላድርግ?

      • ብቸኝነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

      (የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ወጣቶች በሚለው ሥር ይገኛል)

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ