የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሳይንስ በሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሰኔ 1
    • መኪናን፣ ጂፒኤስን፣ ሳተላይትን፣ አውሮፕላንን እና የአንጎል ምስልን ጨምሮ በሳይንስ መስክ የተገኘ እድገት

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ ተተክቷል?

      ሳይንስ በሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?

      አንድ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው ሳይንስ “አስተውሎ በማየት፣ በሙከራና የአንድን ነገር መጠን በመለካት ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ሥርዓት ባለው መንገድ ለማወቅ የሚደረግ ጥናት” ነው። ይህን ሁሉ ማድረግ ደግሞ አዳጋች ከመሆኑም ሌላ ብዙውን ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት ለሳምንታት፣ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት ሙከራዎችን ያደርጋሉ፤ ይመራመራሉ። አንዳንድ ጊዜ ልፋታቸው መና ሊቀር ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ግን የሰው ልጆችን የሚጠቅሙ ሥራዎችን አከናውነዋል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

      አንድ የአውሮፓ ኩባንያ ጠንካራ ፕላስቲክንና ዘመናዊ ማጣሪያን በመጠቀም ሰዎች የተበከለ ውኃ በመጠጣት ምክንያት ከሚመጣ በሽታ እንዲጠበቁ የሚረዳ አንድ መሣሪያ ሠርቷል። እንደነዚህ ያሉ መሣሪያዎች በ2010 በሄይቲ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ በመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት ጥቅም ላይ ውለዋል።

      ከመሬት በላይ ደግሞ አቅጣጫ ለመጠቆም የሚረዳ የሳተላይቶች አውታር አለ፤ ይህም ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተም ተብሎ ይጠራል። ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተም መጀመሪያ የተሠራው ለወታደራዊ አገልግሎት ቢሆንም መኪና አሽከርካሪዎች፣ የአውሮፕላን አብራሪዎች፣ መርከበኞች አልፎ ተርፎም አዳኞችና ተራራ ወጪዎች የሚጓዙበትን አቅጣጫ ለማወቅ ይጠቀሙበታል። ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተምን ለፈለሰፉት የሳይንስ ሊቃውንት ምስጋና ይግባቸውና የምትፈልግበት ቦታ በቀላሉ መድረስ ትችላለህ።

      ሞባይል ስልክ፣ ኮምፒውተር ወይም ኢንተርኔት ትጠቀማለህ? ዘመናዊ ሕክምና ጤንነትህ እንዲሻሻል ወይም ከነበረብህ በሽታ እንድትድን አድርጓል? በአውሮፕላን ትጓዛለህ? እንዲህ ከሆነ ሳይንስ ለሰው ዘር ካበረከታቸው ነገሮች በአንዳንዶቹ እየተጠቀምክ ነው ማለት ነው። እንግዲያው ሳይንስ በሕይወትህ ላይ በብዙ መንገዶች ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ሊባል ይችላል።

      ሳይንስ ያሉበት የአቅም ገደቦች

      በዘመናችን ያሉ የሳይንስ ሊቃውንት የእውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት ሲሉ በተፈጥሮ ላይ ጥልቅ ምርምር እያደረጉ ነው። የኑክሌር የፊዚክስ ሊቃውንት፣ የአተምን ውስጣዊ አሠራሮች በጥልቀት የሚመረምሩ ሲሆን የአስትሮፊዚክስ ጠበብት ደግሞ የጽንፈ ዓለምን አመጣጥ ለማወቅ በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተከናወኑትን ነገሮች ያጠናሉ። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት በዓይን በማይታየውና ሊደረስበት በማይችለው ዓለም ላይ ይበልጥ ምርምር ባደረጉ መጠን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው አምላክ ቢኖር ኖሮ ሊያገኙት ይገባ እንደነበር ይናገራሉ።

      አንዳንድ ስመ ጥር የሳይንስ ሊቃውንትና ፈላስፎች ከዚህም አልፈው ሄደዋል። እነዚህ ሰዎች፣ የሳይንሳዊ ጽሑፎች አዘጋጅ የሆኑት አሚር አክዜል “የአምላክን መኖር በመቃወም የቀረበ ሳይንሳዊ መከራከሪያ” በማለት የገለጹትን ሐሳብ ያራምዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም የታወቁ አንድ የፊዚክስ ሊቅ “በጽንፈ ዓለም ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክት አምላክ ለመኖሩ ማስረጃ ያልተገኘ መሆኑ እንዲህ ዓይነት አምላክ እንደሌለ በማያሻማ መልኩ ያረጋግጣል” በማለት ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው አምላክ እንደሠራቸው የተገለጹት ነገሮች “አስማታዊ ጥበብ” እና “ከሰብዓዊ ችሎታ በላይ የሆኑ ማታለያዎች” እንደሆኑ ይናገራሉ።a

      አሁን የሚነሳው ጥያቄ ግን ሳይንስ እንዲህ ያለ ድምዳሜ ላይ መድረስ የቻለው ስለ ተፈጥሮ ሁሉንም ነገር አውቆ ነው? የሚል ነው። የዚህ ጥያቄ መልስ በአጭሩ አይደለም የሚል ነው። ሳይንስ አስገራሚ እድገት እንዳስመዘገበ ባይካድም ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት አሁንም ገና ብዙ ያልታወቁና ምናልባትም ሊታወቁ የማይችሉ ነገሮች እንዳሉ ይገነዘባሉ። “እያንዳንዱን ነገር አበጥረን ማወቅ አንችልም” በማለት በተፈጥሮ ጥናት መስክ የፊዚክስ ሊቅና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ስቲቨን ዋይንበርግ ተናግረዋል። የታላቋ ብሪታንያ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የሆኑት የተከበሩት ፕሮፌሰር ማርቲን ሪስ “ሰዎች ፈጽሞ ሊረዷቸው የማይችሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ” በማለት ጽፈዋል። በጣም ትንሽ ከሆነችው ሴል አንስቶ እስከ ግዙፉ ጽንፈ ዓለም ድረስ ካሉት ፍጥረታት መካከል አብዛኞቹን ሳይንስ እስካሁን ድረስ ሊረዳቸው አለመቻሉ የተረጋገጠ ሐቅ ነው። የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፦

      • ዲኤንኤ

        የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ሕይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ የሚካሄዱትን ሂደቶች ሙሉ በሙሉ አልተረዱም። ሴሎች ኃይል የሚጠቀሙት፣ ፕሮቲን የሚያመርቱትና እየተባዙ የሚሄዱት እንዴት እንደሆነ ሳይንስ ገና ሙሉ በሙሉ መረዳት አልቻለም።

      • አንድ ልጅ ኳስ ሲያንጠባጥብ

        የስበት ኃይል በቀኑ ውስጥ በእያንዳንዷ ሴኮንድ በእኛ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ሆኖም ይህ ለፊዚክስ ሊቃውንት ሚስጥር ነው። የስበት ኃይል፣ ወደ ላይ በምትዘልበት ጊዜ ወደ ታች የሚስብህ እንዴት እንደሆነ ወይም ጨረቃ ምህዋሯን ጠብቃ በመሬት ዙሪያ እንድትዞር የሚያደርጋት እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አያውቁም።

      • ጽንፈ ዓለም

        የኮስሞሎጂ ባለሙያዎች በግምት 95 በመቶ የሚሆነው የጽንፈ ዓለም ክፍል ለሳይንሳዊ ጥናት በሚያገለግሉ መሣሪያዎች የማይታይ እንደሆነና ምንነቱ ተለይቶ ሊታወቅ እንደማይችል ይናገራሉ። ይህን እንግዳ የሆነ የጽንፈ ዓለም ክፍል፣ ሚስጥራዊ ቁስ አካል እና ሚስጥራዊ ኃይል በማለት ለሁለት ይከፍሉታል። የእነዚህ ነገሮች ምንነት አይታወቅም።

      የሳይንስ ሊቃውንትን የሚያስገርሙ ሌሎች የማይታወቁ ነገሮችም አሉ። ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ? አንድ ታዋቂ የሳይንስ ጸሐፊ “ከምናውቀው ነገር ይልቅ የማናውቀው ነገር በጣም ይበልጣል። ሳይንስ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት እንድንዋጥ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ አእምሯችንን በማስፋት ይበልጥ ምርምር ለማድረግ የሚያነሳሳ እንደሆነ ይሰማኛል” በማለት ጽፈዋል።

      በመሆኑም ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስን ይተካ ይሆን እንዲሁም በአምላክ ማመንን ያስቀር ይሆን ብለህ የምታስብ ከሆነ የሚከተለውን ነጥብ ተመልከት፦ ጥሩ ችሎታ ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ዘመናዊ በሆኑት መሣሪያዎቻቸው በመታገዝ ስለ ተፈጥሮ ማወቅ የቻሉት ነገር በጣም ውስን ከሆነ ሳይንስ ተመራምሮ ሊደርስበት ያልቻለውን ነገር የለም ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ከዚህ ነጥብ ጋር በመስማማት ስለ ሥነ ፈለክ ጥናት አጀማመርና እድገት ረጅም ሐሳብ ካቀረበ በኋላ “የሥነ ፈለክ ጥናት ከተጀመረ 4,000 ዓመት ገደማ ቢያልፍም ጽንፈ ዓለም የጥንቶቹን ባቢሎናውያን ግራ ያጋባ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ግራ እያጋባ ነው” በማለት ደምድሟል።

      ሁሉም ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ የራሱን ውሳኔ የማድረግ መብት አለው፤ የይሖዋ ምሥክሮችም የእያንዳንዱን ሰው መብት ያከብራሉ። “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። (ፊልጵስዩስ 4:5) በመሆኑም ሳይንስና መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ የሚስማሙትና የሚደጋገፉት እንዴት እንደሆነ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

      a አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማይቀበሉት፣ ምድር የጽንፈ ዓለም እምብርት ናት የሚለውንና አምላክ ዓለምን የፈጠረው ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ ነው የሚለውን በመሳሰሉት ቤተ ክርስቲያን በምታስተምራቸው ትምህርቶች ምክንያት ነው።—“መጽሐፍ ቅዱስ እና የተረጋገጡ ሳይንሳዊ እውነቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

      መጽሐፍ ቅዱስ እና የተረጋገጡ ሳይንሳዊ እውነቶች

      መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ይሁን እንጂ ጸሐፊዎቹ በዛሬው ጊዜ ያሉትን የሳይንስ ሊቃውንት ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ ሐሳቦችን ጽፈዋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

      • ጽንፈ ዓለም

        የምድርና የጽንፈ ዓለም ዕድሜ

        የሳይንስ ሊቃውንት ምድር የ4 ቢሊዮን ዓመታት ዕድሜ እንዳላትና ጽንፈ ዓለም ደግሞ ወደ ሕልውና የመጣው ከ13 እስከ 14 ቢሊዮን ዓመታት በፊት እንደሆነ ይገምታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ጽንፈ ዓለም የተፈጠረበትን ጊዜ አይናገርም። እንዲሁም ምድር የተፈጠረችው ከጥቂት ሺህ ዓመታት በፊት እንደሆነ አይናገርም። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ራሱ “በመጀመሪያ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። (ዘፍጥረት 1:1) ይህ ጠቅለል ያለ አነጋገር የሳይንስ ሊቃውንት በትክክለኛ ሳይንሳዊ ሕግጋት ላይ ተመርኩዘው የግዑዙን ዓለም ዕድሜ ማስላት የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል።

      • ተራሮች፣ ዕፀዋትና ውኃ

        ምድርን ለሰው መኖሪያነት ማዘጋጀት

        ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ምድርን ሕይወት ላላቸው ነገሮች መኖሪያነት ለማዘጋጀት ደረጃ በደረጃ የተከናወኑት ነገሮች የወሰዱትን የጊዜ ርዝማኔ ለመግለጽ “ቀን” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። ቀለል ባለ መንገድ የተዘጋጀው ይህ ዘገባ የሚደመደመው የሰዎችን ወደ ሕልውና መምጣት በመግለጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የስድስቱን የፍጥረት “ቀናት” ርዝማኔ አይገልጽም። ይህም በዘመናችን የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት የእነዚህን “ቀናት” ትክክለኛ ርዝማኔ ለማወቅ ጥናት እንዲያካሂዱ በር ከፍቶላቸዋል። የሆነ ሆኖ የፍጥረት “ቀናት” የ24 ሰዓት ርዝማኔ ካላቸው ቀናት በጣም ይበልጣሉ።

      • ምድር

        ምድር የተንጠለጠለችበት መንገድ

        መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድር “በባዶ ስፍራ ላይ” እንደተንጠለጠለች ይገልጻል። (ኢዮብ 26:7) የጥንት ዘመን አፈ ታሪኮች እንደሚገልጹት ፕላኔታችን በአንድ ግዙፍ ፍጥረት ትከሻ ላይ ወይም በዔሊ ላይ በቆሙ ዝሆኖች ጀርባ ላይ እንደተቀመጠች ተደርጋ አልተጠቀሰችም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ የሳይንስ ሊቃውንት በጉዳዩ ላይ እንዲመራመሩ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ኒኮላውስ ኮፐርኒከስ እና ዮሐንስ ኬፕለር፣ ፕላኔቶች በዓይን በማይታይ ኃይል እየተሳቡ በፀሐይ ዙሪያ እንዴት እንደሚሽከረከሩ ገለጹ። ከዚያ ቆየት ብሎ ደግሞ አይዛክ ኒውተን፣ የስበት ኃይል በሕዋ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ የሚንቀሳቀሱበትን መንገድ እንዴት እንደሚቆጣጠር ገለጸ።

      • የዘንግ ቅርጽ ያለው ባክቴሪያ

        በሽታን ስለ መከላከልና ስለ ንጽሕና የተሰጡ መመሪያዎች

        የዘሌዋውያን መጽሐፍ በሽተኞች እንዲገለሉ ማድረግን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዱ ለእስራኤላውያን የተሰጡ መመሪያዎችን ይዟል። ከንጽሕና ጋር በተያያዘ ደግሞ በዘዳግም 23:12, 13 ላይ እስራኤላውያን ከሰፈር ውጭ ገለል ወዳለ ቦታ ሄደው እንዲጸዳዱ የሚያዝዝ ሕግ ይገኛል። እንዲሁም ‘በዓይነ ምድራቸው ላይ አፈር መመለስ’ ነበረባቸው። የሳይንስ ሊቃውንትና ሐኪሞች እንዲህ ዓይነቱን መመሪያ የመጠበቅን አስፈላጊነት የተገነዘቡት ባለፉት 200 ዓመታት ውስጥ ነው።

      አሁን ያነበብከው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መረጃ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፈ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በዘመናቸው የነበሩት በጣም የተማሩ ሰዎች እንኳ ስላልተረዷቸው እንደነዚህ ስላሉ ነገሮች ትክክለኛ መረጃዎችን መጻፍ የቻሉት እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት “ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” በማለት መልስ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 55:9

  • ሳይንስ የደረሰባቸው ነገሮች ውስን ናቸው
    መጠበቂያ ግንብ—2015 | ሰኔ 1
    • አንዲት የሳይንስ ሊቅ በላብራቶሪ ውስጥ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ ተተክቷል?

      ሳይንስ የደረሰባቸው ነገሮች ውስን ናቸው

      ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አምላክ የለሾች ተብለው የሚጠሩትን ሰዎች አመለካከት የሚገልጹ በርካታ መጻሕፍት በሰፊው ተሰራጭተዋል። እነዚህ የኅትመት ውጤቶች የብዙዎችን ቀልብ የሳቡ ሲሆን ለብዙ ውይይትና ክርክር መነሻ ሆነዋል። ይህን በተመለከተ የነርቭ ሳይንስ ሊቅ የሆኑት ዴቪድ ኢግልማን “አንዳንድ አንባቢዎች . . . የሳይንስ ሊቃውንት ሁሉንም ነገር የሚያውቁ ይመስላቸዋል” በማለት ጽፈዋል። አክለውም “ጥሩ አመለካከት ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ግን ምንጊዜም የሌሎችን ሐሳብ የሚቀበሉ ሲሆን ያስመዘገቡት ታሪክም ቢሆን አዳዲስና ያልተጠበቁ ግኝቶች የሞሉበት ነው” ብለዋል።

      አንድ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ በቴሌስኮፕ ሲመለከት

      ባለፉት ዘመናት ሁሉ ተሰጥኦ ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት ተፈጥሮን በተመለከተ ግራ ለሚያጋቡ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት አስገራሚ የሆኑ እመርታዎችን አስመዝግበዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ከባድ ስህተቶችን ፈጽመዋል። አይዛክ ኒውተን ታላላቅ ከሚባሉት የሳይንስ ሊቃውንት አንዱ ነበር። ይህ የሳይንስ ሊቅ የስበት ኃይል ፕላኔቶችን፣ ከዋክብትንና የከዋክብት ረጨቶችን በጽንፈ ዓለም ውስጥ አንድ ላይ ተሳስረው እንዲቀመጡ የሚያደርጋቸው እንዴት እንደሆነ አሳይቷል። ለኮምፒውተር ንድፍ አወጣጥ፣ ለሕዋ ጉዞ እንዲሁም ለኑክሌር ፊዚክስ የሚያገለግል ካልኩለስ የሚባል የሒሳብ ዘርፍ ፈልስፏል። ይሁን እንጂ ኒውተን ኮከብ ቆጠራንና ምትሃታዊ ፎርሙላዎችን ተጠቅሞ የእርሳስ ማዕድንንና ሌሎች ብረቶችን ወደ ወርቅ ለመለወጥ ጥረት አድርጓል።

      ከኒውተን በፊት ከ1,500 ከሚበልጡ ዓመታት ቀደም ብሎ ቶለሚ የሚባል የግሪክ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ሰማያትን በዓይኖቹ ብቻ በመቃኘት ምርምር ያደርግ ነበር። ምሽት ላይ በሰማይ የሚታዩት ፕላኔቶች የሚጓዙበትን መስመር ያጠና ሲሆን በካርታ ሥራም የተካነ ነበር። ይሁን እንጂ ምድር የሁሉም ነገር እምብርት ናት ብሎ ያምን ነበር። በከዋክብት ጥናት ምሁር የሆኑት ካርል ሳጋን ስለ ቶለሚ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “ምድርን ማዕከል ያደረገው [የቶለሚ] ጽንፈ ዓለም ከ1,500 ዓመታት በኋላ ተቀባይነት ማጣቱ አንድ ሰው ከፍተኛ እውቀት ያለው መሆኑ ምንም ስህተት እንዳይፈጽም ዋስትና እንደማይሆን የሚያስገነዝብ ነው።”

      አንዲት የሳይንስ ሊቅ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ

      በዛሬው ጊዜም የሳይንስ ሊቃውንት ምርምር ሲያደርጉ ተመሳሳይ የሆነ ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። ጽንፈ ዓለምን በተመለከተ የተሟላ ማብራሪያ የማግኘታቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው። ሳይንስ እድገት እያደረገ እንደመጣና ጥቅም እንዳስገኘልን ባይካድም የደረሰባቸው ነገሮች ውስን መሆናቸውን ማስታወሳችን ተገቢ ነው። የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ፖል ዴቪስ የሚከተለውን ታዝበዋል፦ “ለሁሉም ነገር የተሟላና የማይለዋወጥ ማብራሪያ ለማግኘት መጣር ከንቱ ልፋት ነው።” ይህ አባባል አንድ የማይካድ ሐቅ ይኸውም ሰዎች ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማይችሉ ያስገነዝባሉ። በመሆኑም ሳይንስ ወደ ሕልውና ስለመጣው ስለ እያንዳንዱ ነገር ማብራሪያ መስጠት ይችላል ተብሎ የሚነገረውን ነገር ከመቀበላችን በፊት በጥንቃቄ ማጤናችን ብልህነት ነው።

      በግልጽ ማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ልናገኝ የማንችለውን መመሪያ ይሰጠናል

      መጽሐፍ ቅዱስ በተፈጥሮ ላይ ስለሚታዩት ድንቅ ነገሮች ሲናገር “እነሆ፣ እነዚህ የመንገዱ ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!” ይላል። (ኢዮብ 26:14) ከሰው የማሰብም ሆነ የመረዳት ችሎታ በላይ የሆነ ብዙ የእውቀት ክምችት አለ። በእርግጥም ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፉት የሚከተሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ዛሬም እውነት ናቸው፦ “የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!”—ሮም 11:33

      ከሳይንስ ልናገኝ የማንችለው መመሪያ

      ሳይንስ ስለ ግዑዙ ዓለም እንድናውቅ የሚያደርግ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆንና አርኪ የሆነ አስደሳች ሕይወት እንድንመራ የሚያስችሉ መመሪያዎችን ይሰጣል። ቀጥሎ የቀረቡትን ምሳሌዎች እንመልከት።

      • ቁም የሚል ምልክት

        ወንጀልን መከላከል

        ለሕይወት አክብሮት ይኑርህ

        “አትግደል።”—ዘፀአት 20:13

        “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው።”—1 ዮሐንስ 3:15

        ሰላምን መፍጠርና ጠብቆ ማቆየት

        “ክፉ ከሆነ ነገር ራቅ፤ መልካም የሆነውንም አድርግ፤ ሰላምን ፈልግ፤ ተከተለውም።”—መዝሙር 34:14

        “የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ይዘራል።”—ያዕቆብ 3:18

        ከዓመፅ ራቅ

        “ይሖዋ ጻድቁንም ሆነ ክፉውን ይመረምራል፤ ክፋትን የሚወዱ ሰዎችን ይጠላል።”—መዝሙር 11:5

        “በዓመፀኛ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤ ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋል።”—ምሳሌ 3:31, 32

      • አንድ ቤተሰብ

        የቤተሰብ ደስታ

        ወላጆችህን ታዘዝ

        “ልጆች ሆይ፣ ከጌታ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ የጽድቅ ተግባር ነውና። ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለው የመጀመሪያው ትእዛዝ እንዲህ የሚል የተስፋ ቃል ይዟል፦ ‘ይህም መልካም እንዲሆንልህና ዕድሜህ በምድር ላይ እንዲረዝም ነው።’”—ኤፌሶን 6:1-3

        ልጆቻችሁን በሚገባ አስተምሩ

        “ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።” —ኤፌሶን 6:4

        “ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው።”—ቆላስይስ 3:21

        የትዳር ጓደኛህን ውደድ እንዲሁም አክብር

        “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”—ኤፌሶን 5:33

      • ዛፍ

        ተፈጥሮን መንከባከብ

        በጥንቷ እስራኤል የተለያየ ዓይነት ብክለት የሚያደርሱ ሰዎችን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድሪቱ በገዛ ነዋሪዎቿ ተበክላለች። . . . በላይዋም የሚኖሩ ሰዎች በደለኞች ሆነው ተገኝተዋል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 24:5, 6) አምላክ ሆን ብለው ምድርን የሚያበላሹ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋል]።” (ራእይ 11:18) እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ ከቅጣት አያመልጡም።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ