-
ልናውቀው የሚገባ ታሪክመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
ልናውቀው የሚገባ ታሪክ
መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች የተለየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል የብዙ የሰዎችን እምነት ለረጅም ጊዜ ሲቀርጽ የኖረ መጽሐፍ የለም። በሌላ በኩል ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ብዙ ትችት የተሰነዘረበት መጽሐፍ የለም።
ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ምሁራን በዘመናችን ያሉት መጽሐፍ ቅዱሶች ከመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች በትክክል የተገለበጡ መሆናቸውን ይጠራጠራሉ። አንድ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “አሁን ያሉን ቅጂዎች ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር አንድ መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን አንችልም። በእጃችን ያሉት ቅጂዎች በስህተት የተሞሉ ናቸው፤ እንዲሁም ከእነዚህ ቅጂዎች ውስጥ አብዛኞቹ የተጻፉት የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ከተዘጋጁ ከዘመናት በኋላ ከመሆኑም ሌላ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በሁለቱ መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩነቶች አሉ።”
ሌሎች ደግሞ በሃይማኖታቸው የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ይጠራጠራሉ። ለምሳሌ ክርስቲያን ያልሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገው ፋይዘል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱስ ቢሆንም እንደተለወጠ ተምሯል። “በዚህም የተነሳ ሰዎች ከእኔ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መነጋገር ሲፈልጉ የማነጋግራቸው በጥርጣሬ መንፈስ ነው። ምክንያቱም የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ የላቸውም። የያዙት የተለወጠውን መጽሐፍ ነው!” በማለት ተናግሯል።
መጽሐፍ ቅዱስ የተለወጠ መሆን አለመሆኑ ለውጥ ያመጣል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚገልጻቸው የሚያጽናኑ ተስፋዎች በመጀመሪያው ጽሑፍ ውስጥ መኖራቸውን እርግጠኛ መሆን ካልቻልክ ልትተማመንባቸው ትችላለህ? (ሮም 15:4) በዘመናችን ያሉት መጽሐፍ ቅዱሶች በሰዎች የተጻፉ የተሳሳቱ ቅጂዎች ከሆኑ ከሥራ፣ ከቤተሰብ ወይም ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ከባድ ውሳኔዎችን ለማድረግ በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ትጠቀማለህ?
የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በአሁኑ ጊዜ ባይገኙም በእጅ የተገለበጡትን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅጂዎችን ማግኘት እንችላለን። እነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች በዘመናት ብዛት በስብሰው ከመጥፋት የተረፉት እንዲሁም የደረሰባቸውን ተቃውሞና የያዙትን መልእክት ለመቀየር የተደረጉ ሙከራዎችን የተቋቋሙት እንዴት ነው? እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁመው ማለፋቸው አሁን በእጅህ የሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ መሆኑን እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ፈተናዎችን እንዴት እንዳለፈ የሚገልጹትን ርዕሶች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ በስብሶ ከመጥፋት ተርፏልመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
መጽሐፍ ቅዱስ በስብሶ ከመጥፋት ተርፏል
ፈተናው፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችና ገልባጮች መልእክቱን በዋነኝነት የጻፉት በፓፒረስና በብራና ላይ ነበር።a (2 ጢሞቴዎስ 4:13) መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ነገሮች ላይ መጻፉ ምን አደጋ ነበረው?
ፓፒረስ በቀላሉ የሚቀደድ ከመሆኑም ሌላ ቶሎ ቀለሙ ይለቃል እንዲሁም ይበላሻል። “ከፓፒረስ የተዘጋጀ ወረቀት ውሎ አድሮ ስለሚበሰብስ የሚቀረው ቃጫና አቧራ ነው” በማለት ስለ ጥንታዊ ግብፅ የሚያጠኑት ሪቻርድ ፓርኪንሰንና ስቲቨን ክወርኪ ይናገራሉ። “ጥቅልሉ ተቀብሮ ከቆየ ሊሻግት ወይም በእርጥበት ሊበሰብስና በአይጦች ወይም በነፍሳት በተለይም በነጭ ምስጦች ሊበላ ይችላል።” አንዳንድ ፓፒረሶች ደግሞ ከተገኙ በኋላ ለኃይለኛ ብርሃን ወይም ለእርጥበት ስለተጋለጡ በፍጥነት ሊበላሹ ችለዋል።
ብራና ከፓፒረስ ለበለጠ ጊዜ የሚያገለግል ቢሆንም አላግባብ ከተያዘ ወይም ለከፍተኛ ሙቀት፣ እርጥበት፣ ወይም ብርሃን ከተጋለጠ እየተበላሸ ይሄዳል።b በነፍሳት ሊበላም ይችላል። በዚህም ምክንያት ኤቭሪዴይ ራይቲንግ ኢን ዘ ግሪኮ ሮማን ኢስት የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው ጥንታዊ መዛግብት “ለረጅም ዘመን ሳይጠፉ መቆየታቸው እምብዛም የተለመደ አይደለም።” መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሁኔታ ቢበሰብስ ኖሮ የያዘው መልእክትም ይጠፋ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፈተና ያለፈው እንዴት ነው? ለአይሁዳውያን የተሰጠው ሕግ እያንዳንዱ ንጉሥ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት “ቅጂ ለራሱ በመጽሐፍ ላይ [መጻፍ]” እንዳለበት ያዛል። (ዘዳግም 17:18) ከዚህም በላይ በሙያቸው የሠለጠኑ ገልባጮች በእጅ የተገለበጡ በርካታ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን በማዘጋጀታቸው ቅዱሳን መጻሕፍት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በመላው እስራኤል አልፎ ተርፎም ርቃ በምትገኘው መቄዶንያ ሊገኙ ችለው ነበር! (ሉቃስ 4:16, 17፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11) በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎች እስከ ዘመናችን ሊቆዩ የቻሉት እንዴት ነው?
የሙት ባሕር ጥቅልሎች በመባል የሚታወቁት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ቅጂዎች ደረቅ የአየር ጠባይ ባለው አካባቢ በሸክላ ማሰሮዎች ውስጥ በመቀመጣቸው ለብዙ ዘመናት ሳይበሰብሱ ቆይተዋል
“አይሁዳውያን ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፈባቸውን ጥቅልሎች ከብልሽትና ከመበስበስ ጠብቀው ለማቆየት ሲሉ ጽሑፎቹን በእንስራ ወይም በማሰሮ ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ ነበራቸው” በማለት የአዲስ ኪዳን ምሁር የሆኑት ፊሊፕ ኮምፎርት ይናገራሉ። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያኖችም ይህንኑ ልማድ ተከትለዋል። በዚህም ምክንያት በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በማሰሮዎች፣ በጨለማ ክፍሎችና በዋሻዎች ውስጥ እንዲሁም ደረቅ በሆኑ ቦታዎች ተገኝተዋል።
ውጤቱ፦ ከ2,000 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸውን ጨምሮ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እስከ ዘመናችን ድረስ ሳይበሰብሱ መቆየት ችለዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በርካታ ጥንታዊ ቅጂዎች ያሉት ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ የለም።
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ በተቃዋሚዎች ከመጥፋት ተርፏልመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
መጽሐፍ ቅዱስ በተቃዋሚዎች ከመጥፋት ተርፏል
ፈተናው፦ ብዙ የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚቃወም አቋም ይዘው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይኖራቸው እንዲሁም መጽሐፉን እንዳያሳትሙ ወይም እንዳይተረጉሙ ከልክለዋል። ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፦
በ167 ዓ.ዓ. ገደማ፦ አይሁዳውያን የግሪክን ሃይማኖት እንዲቀበሉ ለማስገደድ ይጥር የነበረው ሰሉሲዳዊው ንጉሥ አንታይከስ ኤፒፋነስ ሁሉም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች እንዲቃጠሉ አዋጅ አውጥቶ ነበር። የታሪክ ምሁር የሆኑት ሃይንሪክ ግሬትስ እንደጻፉት የንጉሡ ባለሥልጣናት “የሕጉን ጥቅልሎች ባገኙበት ቦታ ሁሉ ያቃጥሉ ነበር፤ እንዲሁም ጥቅልሎቹን በማንበብ ብርታትና መጽናኛ ለማግኘት ይሞክሩ የነበሩ ሰዎችን ገድለዋል።”
መካከለኛው ዘመን፦ አንዳንድ የካቶሊክ መሪዎች ምዕመናኑ የካቶሊክን ቀኖና ትተው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር በመስበካቸው ስለተበሳጩ በላቲን ከተዘጋጀው የመዝሙር መጽሐፍ በቀር ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ይዘው የተገኙ ሰዎችን መናፍቃን በማለት ይፈርጇቸው ነበር። አንድ የቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት “መናፍቃን እንዳሉባቸው የሚጠረጠሩ ቤቶችንና የምድር ቤት ክፍሎችን ሁሉ በመፈተሽ መናፍቃንን በትጋት፣ በታማኝነትና ያለማሰለስ ፈልገው እንዲያመጡ” የሚያዝዝ መመሪያ ለሠራተኞቹ ሰጥቶ ነበር። “መናፍቃን የተገኙባቸው ቤቶች በሙሉ መቃጠል ነበረባቸው።”
የመጽሐፍ ቅዱስ ጠላቶች መጽሐፉን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ቢሳካላቸው ኖሮ የያዘው መልእክትም ይጠፋ ነበር።
በዊሊያም ቲንደል የተተረጎመው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ እገዳ ተጥሎበት የነበረ ከመሆኑም ባሻገር እንዲቃጠል ተደርጓል፤ በ1536 ደግሞ ቲንደል ራሱ ተገድሏል፤ ሆኖም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ እስካሁን ድረስ ሳይጠፋ ቆይቷል
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፈተና ያለፈው እንዴት ነው? የንጉሥ አንታይከስ ዘመቻ ያነጣጠረው በእስራኤል ላይ ነበር፤ ሆኖም በወቅቱ የአይሁድ ማኅበረሰብ በሌሎች አገሮች ውስጥም ይኖር ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን እንደገመቱት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ላይ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት አይሁዳውያን የሚኖሩት ከእስራኤል ውጭ ነበር። አይሁዳውያን በየምኩራቦቻቸው ውስጥ የቅዱሳን መጻሕፍትን ቅጂዎች ያስቀምጡ የነበረ ሲሆን ክርስቲያኖችን ጨምሮ ቀጣዮቹ ትውልዶች ሁሉ የተጠቀሙት በእነዚህ ቅጂዎች ነው።—የሐዋርያት ሥራ 15:21
በመካከለኛው ዘመን የኖሩ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ስደትን በድፍረት የተቋቋሙ ከመሆኑም ሌላ ቅዱሳን መጻሕፍትን መተርጎማቸውንና መገልበጣቸውን ቀጥለው ነበር። በ15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ የማተሚያ መሣሪያ ከመፈልሰፉ በፊትም እንኳ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በ33 ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ነበር። ከዚያ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስገርም ፍጥነት መተርጎምና መታተም ጀመረ።
ውጤቱ፦ ኃያል ነገሥታትና የተሳሳተ አካሄድ የተከተሉ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የሞከሩ ቢሆንም በስፋት በመተርጎምና በመሰራጨት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ ሆኗል። መጽሐፉ የአንዳንድ አገሮችን ሕግና ቋንቋ የቀረጸ ከመሆኑም ሌላ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።
-
-
የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች ከሽፈዋልመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 4
-
-
ማሶሬቶች ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥንቃቄ ገልብጠዋል
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጠብቆ ቆይቷል
ፈተናው፦ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት የተደረጉት ጥረቶች ቢከሽፉም አንዳንድ ገልባጮችና ተርጓሚዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመቀየር ሙከራ አድርገው ነበር። እነዚህ ሰዎች የሚያምኑበትን ነገር በማስተካከል መሠረተ ትምህርታቸውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከማስማማት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን መልእክት ለመቀየር ጥረት አድርገዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
የአምልኮ ቦታዎች፦ በአራተኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መካከል የሳምራውያንን ፔንታቱክa ያዘጋጁት ሰዎች ከዘፀአት 20:17 በኋላ “በገሪዛን ተራራ ላይ። በዚያም መሠዊያ ትሠራለህ” የሚለውን ሐሳብ ጨምረዋል። ሳምራውያን በዚህ ጥቅስ አማካኝነት “በገሪዛን ተራራ” ላይ ቤተ መቅደስ መሥራታቸው የቅዱሳን መጻሕፍት ድጋፍ ያለው እንዲመስል ለማድረግ ሞክረው ነበር።
የሥላሴ መሠረተ ትምህርት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ካለቀ በኋላ 300 ዓመታት እንኳ ሳይሞላ፣ የሥላሴ አማኝ የሆነ አንድ ጸሐፊ በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ‘አብ፣ ቃልና መንፈስ ቅዱስ ሦስትም አንድም ናቸው’ የሚሉትን ቃላት ጨምሮ ነበር። ይህ ሐሳብ በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ብሩስ ሜጽገር እንደገለጹት “ከስድስተኛው መቶ ዘመን ወዲህ ይህ ሐሳብ በጥንታዊው ላቲን እና [በላቲን] ቩልጌት በእጅ በተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ውስጥ በተደጋጋሚ መገኘት ጀመረ።”
የአምላክ ስም፦ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአይሁዳውያንን አጉል እምነት መሠረት በማድረግ የአምላክን ስም ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለማውጣት ወሰኑ። በአምላክ ስም ምትክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፈጣሪን ብቻ ሳይሆን ሰዎችን፣ ጣዖታትን፣ አልፎ ተርፎም ዲያብሎስን ለማመልከት የተሠራባቸውን እንደ “አምላክ” እና “ጌታ” ያሉትን የማዕረግ ስሞች ተጠቀሙ።—ዮሐንስ 10:34, 35፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4b
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፈተና ያለፈው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች ግድየለሾች አልፎ ተርፎም አታላዮች ቢሆኑም እንኳ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውና ጠንቃቃ የሆኑ በርካታ ገልባጮች ነበሩ። ከስድስተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ማሶሬቶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመገልበጥ የማሶሬቶች ጽሑፍ ተብለው የሚጠሩትን ቅጂዎች አዘጋጁ። ማሶሬቶች ምንም ዓይነት ስህተት ላለመሥራት ሲሉ ቃላትንና ፊደላትን ይቆጥሩ እንደነበር ይነገራል። ለመገልበጥ በሚጠቀሙበት ቅጂ ላይ ስህተት እንዳለ ከተሰማቸው ይህን በኅዳጉ ላይ ይገልጹ ነበር። ማሶሬቶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የሚቀይር ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም። ፕሮፌሰር ሞሼ ጎሸን ጎትጺን “ማሶሬቶች ቅዱስ ጽሑፉን የሚቀይር ነገር ሆን ብሎ ማድረግን የሚመለከቱት እንደ ከባድ ወንጀል ነበር” በማለት ጽፈዋል።
በሁለተኛ ደረጃ፣ በዛሬው ጊዜ ብዛት ያላቸው በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች መገኘታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ስህተት የሆኑ ሐሳቦችን ማስተያየት እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሚጠቀሙበት የላቲን ትርጉም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደሆነ ለብዙ መቶ ዓመታት ሲያስተምሩ ኖረዋል። ሆኖም በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የተሳሳተ ሐሳብ አስገብተው ነበር። ይህ ስህተት ከፍተኛ ተቀባይነት ባለው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን ውስጥም ጭምር ገብቷል! ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የተገኙት በእጅ የተገለበጡ ሌሎች ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ምን ነገር አሳይተዋል? ብሩስ ሜጽገር “[በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ] የገባው ሐሳብ ከላቲኑ በስተቀር በሁሉም ጥንታዊ ቅጂዎች (ሲሪያክ፣ ኮፕቲክ፣ አርመንኛ፣ ግዕዝ፣ አረብኛ፣ ስላቮኒክ) ውስጥ አይገኝም” በማለት ጽፈዋል። በዚህም የተነሳ ተሻሽለው የወጡ የኪንግ ጄምስ ቨርዥን እትሞችና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች ይህን የተሳሳተ ሐሳብ አውጥተውታል።
ቼስተር ቢቲ P46—በ200 ዓ.ም. ገደማ በፓፒረስ ላይ የተጻፈ አንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ
በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጠብቆ እንደቆየ ያረጋግጣሉ? የሙት ባሕር ጥቅልሎች በ1947 በተገኙ ጊዜ ምሁራን የዕብራይስጡን የማሶሬቶች ጽሑፍ ከእነሱ አንድ ሺህ ዓመታት ቀደም ብለው ከተጻፉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅልሎች ጋር ማስተያየት ቻሉ። ስለ ሙት ባሕር ጥቅልሎች የሚዘግበው ቡድን አባል የሆነ አንድ ሰው እንደገለጸው አንዱ ጥቅልል እንኳ “ቅዱስ ጽሑፉ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዓመታት በአይሁድ ገልባጮች አማካኝነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲገለበጥ መቆየቱን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።”
በደብሊን፣ አየርላንድ የሚገኘው የቼስተር ቢቲ ቤተ መጻሕፍት እያንዳንዱን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሚወክል የፓፒረስ ስብስብ አለው፤ ከዚህ ስብስብ መካከል በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀ ከ100 ዓመት በኋላ ብቻ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ይገኙበታል። ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ እንደገለጸው “ፓፒረሶቹ ከጽሑፎቹ ጋር በተያያዘ አዳዲስ ዝርዝር መረጃዎችን ይዘዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተገለበጠው ጽሑፍ በሚያስገርም ሁኔታ ከመጀመሪያው ጽሑፍ ጋር እንደሚመሳሰል አሳይተዋል።”
“የዚህን ያህል በትክክል የተላለፈ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም”
ውጤቱ፦ በእጅ የተገለበጡ በርካታ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች መገኘታቸው በጽሑፉ ጥራት ላይ ጥያቄ ከማስነሳት ይልቅ የጽሑፉን ጥራት አረጋግጠዋል። ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክተው ሲጽፉ እንደገለጹት “ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር ለመልእክቱ እንዲህ ያለ በርካታ ጥንታዊ ማስረጃ የተገኘለት ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ የለም፤ እንዲሁም ጽሑፉ ይዘቱ ሳይለወጥ ወደ እኛ እንደደረሰ ማንኛውም ከአድሎ ነፃ የሆነ ምሁር አይክድም።” ዊሊያም ሄንሪ ግሪን የተባሉ ምሁር ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተመለከተ ሲናገሩ “የዚህን ያህል በትክክል የተላለፈ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል።
-
-
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መሰናክሎችን ሊያልፍ የቻለው ለምንድን ነውመጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 4
-
-
የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ የቆየበት ምክንያት
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መሰናክሎችን ማለፍ ችሏል። በዚህም የተነሳ አንተም ይህን መጽሐፍ ማግኘትና ማንበብ ትችላለህ። ደግሞም ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ከመረጥክ እያነበብክ ያለኸው በመጀመሪያው ጽሑፍ ላይ የነበረውን ሐሳብ እንደሆነ መተማመን ትችላለህ።a ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ሳይበሰብስ የቆየው፣ ኃይለኛ ተቃውሞ የተቋቋመውና መልእክቱን ለመለወጥ ሆን ተብሎ የተደረገውን ጥረት ማለፍ የቻለው ለምንድን ነው? መጽሐፉን ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?
“አሁን፣ በእጄ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ”
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው” በማለት ከጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መሰናክሎችን ሊያልፍ የቻለው የአምላክ ቃል ስለሆነና አምላክ ጥበቃ ስላደረገለት እንደሆነ ያምናሉ። በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ፋይዘል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሰማቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን በራሱ ለማረጋገጥ ሲል ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመር ወሰነ። ምርምር ሲያደርግ ያገኘው ነገር አስገረመው። ብዙም ሳይቆይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ተስፋፍተው የሚገኙት አብዛኞቹ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሌሉ ተገነዘበ። ከዚህም በላይ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ በቃሉ ውስጥ ሲያነብ ልቡ ተነካ።
“አሁን፣ በእጄ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ” ይላል። “ደግሞስ አጽናፈ ዓለምን መፍጠር የቻለ አምላክ፣ የምንመራበት መጽሐፍ የመስጠትና ይህን መጽሐፍ የመጠበቅ ኃይል አይኖረውም? ይህ ካልሆነ ደግሞ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ኃይል ገደብ አለው እያልኩ ነው! ለመሆኑ እኔ ማን ሆኜ ነው እንዲህ የምለው?”—ኢሳይያስ 40:8
a በግንቦት 1, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መምረጥ የምትችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
-