የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሐቀኝነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ነው?
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 1
    • አንድ አሠሪ ሠራተኛው ላይ ሲዝት

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?

      ሐቀኝነት ጊዜ ያለፈበት ነገር ነው?

      ሂቶሺ በጃፓን በሚገኝ አንድ ሥራ አስቀጣሪ ድርጅት ውስጥ በሒሳብ ክፍል ውስጥ ይሠራ ነበር። ከአለቃው ጋር ሆኖ የሒሳብ መዝገብ በሚመረምሩበት ጊዜ አለቃው የሐሰት ሪፖርት እንዲያዘጋጅ አዘዘው። ሂቶሺ እንደዚህ ዓይነት ሐቀኝነት የጎደለው ሥራ ለመሥራት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ለአለቃው ነገረው። በመሆኑም አለቃው ከሥራ እንደሚያባርረው አስጠነቀቀው፤ በመጨረሻም ሂቶሺ ሥራውን አጣ።

      በቀጣዮቹ ወራት ሂቶሺ ሥራ ለመቀጠር ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ተስፋ ቆረጠ። ለምሳሌ ያህል፣ ለአንድ የሥራ ቃለ መጠይቅ በቀረበበት ወቅት ሐቀኝነት የጎደለው ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ተናገረ። ቃለ መጠይቅ ያደርግለት የነበረው ሰው “የምታስብበት መንገድ ግራ ይገባል!” አለው። ምንም እንኳ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ሐቀኛ ለመሆን ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ ደግፈው በአቋሙ እንዲጸና ቢያበረታቱትም ሂቶሺ የያዘውን አቋም በተመለከተ ጥርጣሬ አድሮበት ነበር። ሂቶሺ “በእምነቴ ምክንያት እንዲህ ያለ አቋም መያዜ ትክክል ነው የሚለውን ነገር መጠራጠር ጀምሬ ነበር” በማለት ተናግሯል።

      በሂቶሺ ላይ የደረሰው ነገር ሐቀኝነትን ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ሁሉም ሰው እንዳልሆነ የሚያሳይ አሳዛኝ እውነታ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች በንግዱ ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን የሚያዋጣ ነገር እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። በደቡብ አፍሪካ የምትኖር አንዲት ሴት በሥራ ቦታዋ ስለሚያጋጥማት ነገር ስትናገር “ብዙ ሰዎች ሐቀኛ አይደሉም፤ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ የእነሱ ዓይነት አካሄድ እንድከተል ጫና ይደረግብኛል” ብላለች።

      በአሁኑ ጊዜ ከምናያቸው ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች መካከል በተለየ ሁኔታ ተስፋፍቶ የሚገኘው ውሸት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት በማሳቹሴትስ ኤምኸርስት ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሞያ የሆኑት ሮበርት ፌልድማን ያደረጉት አንድ ጥናት እንዳሳየው 60 በመቶ የሚሆኑት አዋቂዎች በ10 ደቂቃ ውስጥ ቢያንስ አንዴ ይዋሻሉ። ፌልድማን እንዲህ ብለዋል፦ “ጥናቱ ያሳየው ውጤት በጣም የሚገርም ነው። ውሸት የሕይወታችን አንዱ ክፍል እስኪመስል ድረስ እንደዚህ ተስፋፍቷል ብለን አልጠበቅንም ነበር።” ብዙ ሰዎች፣ ሌሎች ሲዋሿቸው ደስ ባይላቸውም እነሱ ራሳቸው የሚዋሹ መሆናቸው የሚገርም ነው።

      ውሸት፣ ስርቆት እና ሌሎች ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች ይህን ያህል የተስፋፉት ለምንድን ነው? ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት በማኅበረሰቡ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ከሁሉ በላይ ደግሞ እንዲህ ባሉ ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶች ከመካፈል ለመቆጠብ ምን ማድረግ እንችላለን?

  • ሐቀኛ አለመሆን ምን ጉዳት አለው?
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 1
    • ሁለት ሴቶች ሲያወሩ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?

      ሐቀኛ አለመሆን ምን ጉዳት አለው?

      “በመጠኑም ቢሆን ሐቀኝነትን በማጉደል ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ሁልጊዜ ያጋጥሙናል።”—ሳማንታ፣ ደቡብ አፍሪካ

      በዚህ አባባል ትስማማለህ? ልክ እንደ ሳማንታ፣ ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ በሕይወታችን ውስጥ ከፍ አድርገን የምናያቸው ነገሮች የትኞቹ እንደሆኑ ያሳያል። ለምሳሌ፣ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበን ሰዎች ለእኛ ያላቸው አክብሮት ከሆነ ከኃፍረት ለመዳን ስንል ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸምን እንደ አንድ አማራጭ ልናየው እንችላለን። ይሁንና እውነቱ ሲወጣ ሐቀኛ አለመሆናችን ብዙ መዘዝ ያስከትልብናል። እስቲ አንዳንድ መዘዞቹን እንመልከት።

      ሐቀኝነትን ማጉደል መተማመንን ያጠፋል

      ለማንኛውም ዝምድና መሠረቱ መተማመን ነው። ሁለት ሰዎች እርስ በርስ የሚተማመኑ ከሆነ የደኅንነትና የመረጋጋት ስሜት ይሰማቸዋል። ሆኖም መተማመን በአንድ ጀምበር የሚመጣ ነገር አይደለም። ሰዎች አብረው ጊዜ ሲያሳልፉ እርስ በርሳቸው እውነትን የሚነጋገሩ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ራስ ወዳድነት የማይንጸባረቅበት ነገር የሚያደርጉ ከሆነ በመካከላቸው ያለው መተማመን እያደገ ይሄዳል። ይሁንና ሐቀኝነት የጎደለው አንድ ድርጊት መፈጸም ይህ መተማመን በአንዴ እንዲጠፋ ሊያደርግ ይችላል። አንዴ መተማመን ከጠፋ ደግሞ እንደገና መገንባት በጣም ከባድ ነው።

      ወዳጄ ነው ብለህ ባሰብከው ሰው ተታልለህ ታውቃለህ? ከሆነ ምን ተሰማህ? ምናልባት ስሜትህ ተጎድቶ፣ ሌላው ቀርቶ እንደተከዳህ ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። እንዲህ የተሰማህ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ሐቀኝነትን ማጉደል ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጣቸውን ዝምድናዎች መሠረት ሊያናጋ እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

      ሐቀኝነት ማጉደል ይጋባል

      በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮበርት ኢነስ ባደረጉት ጥናት ላይ “ሐቀኝነትን ማጉደል የሚጋባ ነገር እንደሆነ” ጠቁመዋል። በመሆኑም ሐቀኛ አለመሆንን ከቫይረስ ጋር ልናመሳስለው እንችላለን፤ አጭበርባሪ ከሆነ ሰው ጋር በተቀራረብክ መጠን በእምነት አጉዳይነት “የመጠቃት” አጋጣሚህ የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል።

      ታዲያ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መመሪያዎችን ተመልከት።

      ሰዎች ሐቀኝነት የሚያጎድሉባቸው የተለያዩ መንገዶች

      መዋሸት

      አንድ ሰው የጋብቻ ቀለበቱን ሲያወልቅ

      ምን ማለት ነው? እውነቱን የማወቅ መብት ላለው ሰው ሐሰት መናገር ማለት ነው። አንድን ሰው በተሳሳተ መንገድ እንዲያስብ ለማድረግ እውነቱን ማዛባት ወይም ማጣመም፣ አንድን ጉዳይ የሚመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎችን በማስቀረት ግለሰቡን ማታለል እንዲሁም እውነቱን አጋንኖ በማቅረብ ግለሰቡ ስለ ጉዳዩ የተሳሳተ ግምት እንዲኖረው ማድረግ መዋሸት ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋልና፤ ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።” (ምሳሌ 3:32) “አሁን አታላይነትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”—ኤፌሶን 4:25

      ስም ማጥፋት

      ሁለት ሰዎች፣ ወደ ክፍሉ ስለሚገባው ሰው ሲያንሾካሹኩ

      ምን ማለት ነው? አንድ ሰው በሰዎች ዘንድ ያለው ስም እንዲጎድፍ ለማድረግ የሐሰት እና የተንኮል ወሬ መናገር ማለት ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ነገረኛ ሰው ጭቅጭቅ ያስነሳል፤ ስም አጥፊም የልብ ጓደኛሞችን ይለያያል።” (ምሳሌ 16:28) “እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ ስም አጥፊ ከሌለ ደግሞ ጭቅጭቅ ይበርዳል።”—ምሳሌ 26:20

      ማጭበርበር

      አንድ ሰው ኮቱ ውስጥ ወደደበቃቸው ሰዓቶች ሲጠቁም

      ምን ማለት ነው? አንድን ሰው ገንዘቡን ወይም ንብረቱን እንዲሰጥ ለማድረግ ማታለል ወይም ማወናበድ ማለት ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የተቸገረውንና ድሃ የሆነውን ቅጥር ሠራተኛ አታታል።” (ዘዳግም 24:14, 15) “ችግረኛን የሚያጭበረብር ፈጣሪውን ይሰድባል፤ ለድሃ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል።”—ምሳሌ 14:31

      መስረቅ

      አንድ ሰው ዋሌት ሲሰርቅ

      ምን ማለት ነው? የአንድን ሰው ንብረት ሳያስፈቅዱ መውሰድ ማለት ነው።

      መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ።” (ኤፌሶን 4:28) “አትታለሉ፤ . . . ሌቦች ወይም ስግብግቦች ወይም ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ቀማኞች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

  • ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም ያስገኛል?
    መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016 | ቁጥር 1
    • አንድ ሰው የሰረቀውን ዋሌት ለባለቤቱ ሲመልስ

      የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም አለው?

      ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም ያስገኛል?

      “ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እናምናለን፤ ደግሞም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

      በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንዳንድ ጊዜ “ሐቀኝነት” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል ቀጥተኛ ፍቺው “በተፈጥሮው ጥሩ የሆነን ነገር” ያመለክታል። ይህ ቃል ከሥነ ምግባር አንጻር ውብ መሆን ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።

      ክርስቲያኖች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን” በማለት የተናገረውን ሐሳብ በቁም ነገር ይመለከቱታል። ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል?

      በውስጣችን ያለ ትግል

      አብዛኞቹ ሰዎች ከቤት ከመውጣታቸው በፊት ጠዋት ጠዋት በመስተዋት ራሳቸውን ይመለከታሉ። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ማራኪ ሆነው መታየት ስለሚፈልጉ ነው። ሆኖም ፀጉርን ከማሳመር ወይም ጥሩ ልብስ ከመልበስ የበለጠ አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። በእርግጥም፣ ውስጣዊ ማንነታችን በውጫዊው መልካችን ላይ ውበት ሊጨምርልን ወይም ሊቀንስብን ይችላል።

      የአምላክ ቃል፣ መጥፎ የሆነውን ነገር የማድረግ ዝንባሌ እንዳለን በግልጽ ይናገራል። ዘፍጥረት 8:21 “የሰው የልብ ዝንባሌ ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ ነው” ይላል። በመሆኑም ሐቀኛ ለመሆን በውስጣችን ካለው ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌ ጋር መታገል ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከኃጢአት ጋር የሚያደርገውን ትግል እንደሚከተለው በማለት ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፦ “በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በሰውነቴ ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።”—ሮም 7:22, 23

      ለምሳሌ ያህል፣ ልባችን መጥፎ የሆነውን ነገር እንድናደርግ በሚገፋፋን ወቅት ወይም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ለመፈጸም በምንፈተንበት ጊዜ ልባችን የሚለንን ከመፈጸም ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም ማለት አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን መምረጥ እንችላለን። በውስጣችን ያለውን መጥፎ አስተሳሰብ ለማስወገድ የምንመርጥ ከሆነ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሐቀኝነት የጎደላቸው ቢሆኑም እንኳ ሐቀኛ ሆነን መኖር እንችላለን።

      በትግሉ አሸናፊ መሆን ይቻላል

      ሐቀኛ መሆን ከፈለግን ከሥነ ምግባር አንፃር በጥብቅ የምንከተለው አቋም ሊኖረን ይገባል። የሚያሳዝነው ነገር፣ ሰዎች ከሥነ ምግባር አቋማቸው ይልቅ ስለ አለባበሳቸውና ስለ መልካቸው ስለሚጨነቁ ለዚህ ብዙ ጊዜ ሲያጠፉ ይታያል። እነዚህ ሰዎች ሐቀኝነትን የሚለኩት ባሉበት ሁኔታ ላይ ተመሥርተው ነው። ዚ (ኦነስት) ትሩዝ አባውት ዲስኦነስቲ የተባለው መጽሐፍ ይህን ሁኔታ በዚህ መንገድ አስቀምጦታል፦ “እኛ ለራሳችን ባወጣነው መሥፈርት መሠረት ሐቀኛ እንደሆንን እስከተሰማን ድረስ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ብንፈጽምም ምንም አይመስለንም።” ታዲያ ምን ያህል ሐቀኛ መሆን አለብን በሚለው ጉዳይ ረገድ ልንተማመንበት የምንችል መሥፈርት አለ? ደስ የሚለው ነገር፣ ሊረዳን የሚችል ነገር አለ።

      በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ጠቃሚ እርዳታ እንደሚያበረክት አስተውለዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙት የሥነ ምግባር ደንቦች ተወዳዳሪ የላቸውም። (መዝሙር 19:7) ከቤተሰብ ሕይወት፣ ከሥራ፣ ከሥነ ምግባር፣ ከመንፈሳዊነት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ልንተማመንበት የምንችል መመሪያ ይሰጠናል። ጠቃሚነቱ ደግሞ ጊዜ የማይሽረው እንደሆነ ታይቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሕጎች እና መመሪያዎች ለሁሉም ብሔር፣ ዘር፣ ጎሣና ሕዝብ ይጠቅማሉ። ይህን መጽሐፍ በመመርመር፣ በሚናገረው ሐሳብ ላይ በማሰላሰል እንዲሁም ምክሩን ተግባራዊ በማድረግ ልባችን ሐቀኛ እንዲሆን ማሠልጠን እንችላለን።

      ይሁን እንጂ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ብቻውን ሐቀኛ ለመሆን በምናደርገው ትግል እንድናሸንፍ አይረዳንም። ምክንያቱም የምንኖረው ጥሩ ሥነ ምግባር የሌላቸው ሰዎች በሞሉበት ዓለም በመሆኑ የእነሱን አካሄድ እንድንከተል ተጽዕኖ ይደርስብናል። ስለዚህ አምላክ እንዲረዳንና እንዲያግዘን ወደ እሱ መጸለይ ይኖርብናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13) ይህንን በማድረግ እውነት ለሆነው ነገር ለመቆምና በሁሉም ነገር ሐቀኛ ለመሆን ድፍረት እናገኛለን።

      ሐቀኝነት ወሮታ አለው

      መግቢያችን ላይ የጠቀስነው ሂቶሺ ሐቀኛ በመሆን ረገድ ያተረፈው ጥሩ ስም ጠቅሞታል። የአሁኑ አለቃው ሐቀኛ መሆኑን ያደንቅለታል። ሂቶሺ “በንጹሕ ሕሊና የምሠራው ሥራ በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ” በማለት ተናግሯል።

      ሌሎች ሰዎችም ሐቀኝነት ወሮታ የሚያስገኝ ነገር እንደሆነ በሕይወታቸው አይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሁሉም ነገር በሐቀኝነት እንድንኖር’ የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው የተጠቀሙ አንዳንድ ሰዎችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

      • ንጹሕ ሕሊና

        ሼረል

        “በ13 ዓመቴ ትምህርት አቁሜ ከሌቦች ጋር መሥራት ጀመርኩ። በመሆኑም ከገቢዬ 95 በመቶ የሚሆነው በማጭበርበር የሚገኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ትዳር የመሠረትኩ ሲሆን እኔና ባሌ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። ይሖዋa አምላክ ሐቀኝነት የጎደላቸው ድርጊቶችን እንደሚጠላ ተማርን፤ በመሆኑም በሕይወታችን ለውጥ ለማድረግ ወሰንን። በ1990 ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።—ምሳሌ 6:16-19

        “ቀደም ሲል ቤታችን በተሰረቁ ዕቃዎች ተሞልቶ ነበር፤ አሁን ግን ምንም የተሰረቀ ዕቃ የለንም፤ በመሆኑም ንጹሕ ሕሊና አለኝ። ሐቀኝነት የጎደለው ሕይወት በመምራት ያሳለፍኳቸውን በርካታ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ ታላቅ ምሕረት ስላሳየኝ አመስጋኝ ነኝ። አሁን ይሖዋ በእኔ እንደሚደሰት ስለማውቅ ማታ ማታ ደስ ብሎኝ ወደ መኝታዬ እሄዳለሁ።”—ሼረል፣ አየርላንድ

        ሶኒ

        “አለቃዬ፣ ከደንበኞቻችን አንዱ ጉቦ ሊሰጠኝ ሲል ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ሲሰማ ‘አምላክህ ታማኝ ሰው እንድትሆን አድርጎሃል! ለመሥሪያ ቤታችን ትልቅ ሀብት ነህ’ አለኝ። በሁሉም ነገር ሐቀኛ መሆኔ በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝ አድርጓል። በተጨማሪም ቤተሰቤም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ አቋም እንዲኖራቸው ለመርዳት አስችሎኛል።”—ሶኒ፣ ሆንግ ኮንግ

      • የአእምሮ ሰላም

        ቶም

        “በአንድ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ የሥራ አስኪያጁ ረዳት ሆኜ እሠራለሁ። በዚህ ሥራ ላይ ሀብት ለማካበት ሲባል ሐቀኝነትን ማጉደል የተለመደ ነገር ነው። ብዙዎች ‘ሀብት የሚያስገኝና ኢኮኖሚውን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ በትንሹም ቢሆን ሐቀኝነት ማጉደል ችግሩ ምንድን ነው?’ የሚል አመለካከት አላቸው። እኔ ግን ሐቀኛ በመሆኔ የአእምሮ ሰላም አለኝ። በአቋሜ ምክንያት ምንም ነገር ቢያጋጥመኝ እንኳ ሐቀኛ ሆኜ ለመኖር ቆርጫለሁ። አሠሪዎቼ እንደማልዋሻቸውም ሆነ እንደማልዋሽላቸው ያውቃሉ።”—ቶም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

      • ለራስህ አክብሮት ይኖርሃል

        ካዎሪ

        “አለቃዬ በሥራ ቦታችን ስለጠፉ አንዳንድ ዕቃዎች እንድዋሽ ጠየቀኝ፤ እኔ ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆንኩም። ዕቃውን የሰረቁት ሰዎች ሲጋለጡ ግን አለቃዬ ሐቀኛ በመሆኔ አመሰገነኝ። ሐቀኝነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን ድፍረት ይጠይቃል። የኋላ ኋላ ግን የሌሎችን እምነትና አክብሮት ያስገኝልናል።”—ካዎሪ፣ ጃፓን

      ሐቀኛ መሆን ንጹሕ ሕሊናና የአእምሮ ሰላም እንዲሁም ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ስለሚያደርግ በእርግጥም ይክሳል። በዚህ ሐሳብ አትስማማም?

      a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ