የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w16 ጥቅምት ገጽ 8-12
  • “ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ ለእንግዶች ምን አመለካከት አለው?
  • ለእንግዶች ባለን አመለካከት ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገን ይሆን?
  • ለእንግዶች ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
  • እንግድነት እንዳይሰማቸው እርዷቸው
  • የቦዔዝና የሩት ያልተጠበቀ ጋብቻ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • “ምግባረ መልካም ሴት”
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • “ምግባረ መልካም ሴት”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • የሩት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
w16 ጥቅምት ገጽ 8-12

“ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ”

“ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ።”—ዕብ. 13:2 ግርጌ

መዝሙሮች፦ 124, 79

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ለእንግዶች ባለን አመለካከት ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምን ሊሆን ይችላል?

  • ቦዔዝ ሩትን የያዘበት መንገድ ለእንግዶች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?

  • ለእንግዶች ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

1, 2. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ እንግዶች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

ኦሴ[1] ከጋና ወደ አውሮፓ የመጣው ከ30 ዓመታት ገደማ በፊት ነው፤ በወቅቱ የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ኦሴ ያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ እንዲህ ብሏል፦ “አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እኔ ግድ እንደሌላቸው ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብኩ። የአየሩ ሁኔታም ጨርሶ ያልጠበቅኩት ነበር። ከአውሮፕላን ማረፊያው ስወጣ በሕይወቴ ገጥሞኝ የማያውቅ ዓይነት ብርድ ስለተሰማኝ ማልቀስ ጀመርኩ።” ኦሴ የሄደበትን አገር ቋንቋ በደንብ ባለመቻሉ ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ጥሩ ሥራ ማግኘት አልቻለም። በዚያ ላይ ደግሞ ከቤተሰቡ በመለየቱ ብቸኝነትና ናፍቆት አስቸግሮት ነበር።

2 አንተ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብትሆን ሌሎች ምን እንዲያደርጉልህ እንደምትፈልግ እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ዜግነትህም ሆነ የቆዳህ ቀለም ምንም ይሁን ምን፣ ወደ መንግሥት አዳራሽ ስትገባ ሌሎች ሞቅ አድርገው ቢቀበሉህ ደስ አይልህም? መጽሐፍ ቅዱስ “ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ” የሚል ማሳሰቢያ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ይሰጣል። (ዕብ. 13:2 ግርጌ) እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመርምር፦ ይሖዋ ለእንግዶች ምን አመለካከት አለው? ለእንግዶች ባለን አመለካከት ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምን ሊሆን ይችላል? የውጭ አገር ዜጎች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ እንግድነት እንዳይሰማቸው ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

ይሖዋ ለእንግዶች ምን አመለካከት አለው?

3, 4. በዘፀአት 23:9 መሠረት የአምላክ የጥንት ሕዝቦች የባዕድ አገር ሰዎችን እንዴት እንዲይዙ ይጠበቅባቸው ነበር? ለምንስ?

3 ይሖዋ ሕዝቡን ከግብፅ ነፃ ካወጣቸው በኋላ የሰጣቸው ሕጎች፣ አብረዋቸው ላሉት እስራኤላዊ ያልሆኑ ብዙ ሰዎች ደግነት እንዲያሳዩ የሚያበረታቱ ነበሩ። (ዘፀ. 12:38, 49፤ 22:21) ብዙውን ጊዜ ለባዕድ አገር ሰዎች፣ ሕይወት ከባድ ሊሆንባቸው ስለሚችል ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ አንዳንድ ዝግጅቶችን አድርጎላቸው ነበር። የቃርሚያ ዝግጅትን ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።—ዘሌ. 19:9, 10

4 ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ለባዕድ አገር ሰው አክብሮት እንዲያሳዩ ከማዘዝ ይልቅ ራሳቸውን በእነሱ ቦታ አድርገው እንዲያስቡ አበረታቷቸዋል። (ዘፀአት 23:9⁠ን አንብብ።) እስራኤላውያን “የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር” ያውቃሉ። ዕብራውያኑ፣ ባሪያ ከመሆናቸው በፊትም እንኳ በዘራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት ግብፃውያኑ ያገልሏቸው ነበር። (ዘፍ. 43:32፤ 46:34፤ ዘፀ. 1:11-14) እስራኤላውያን በግብፅ የባዕድ አገር ሰው እያሉ ሕይወት መራራ ሆኖባቸው ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ የባዕድ አገር ሰዎችን ‘እንደ አገራቸው ተወላጅ’ አድርገው እንዲመለከቱ ነግሯቸዋል።—ዘሌ. 19:33, 34

5. ይሖዋ ለባዕድ አገር ሰዎች ያለው ዓይነት አሳቢነት ለማሳየት ምን ሊረዳን ይችላል?

5 ዛሬም ቢሆን ይሖዋ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ለሚገኙ የሌላ አገር ሰዎች በጥንት ጊዜ ያሳየው ዓይነት አሳቢነት እንደሚያሳያቸው መተማመን እንችላለን። (ዘዳ. 10:17-19፤ ሚል. 3:5, 6) እነዚህ ሰዎች መድልዎ ሊደርስባቸው እንደሚችል ወይም የአገሩን ቋንቋ ባለመቻላቸው እንደሚቸገሩ አሊያም ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ካሰብን ለእነሱ ደግነት ለማሳየትና ስሜታቸውን ለመረዳት እንጥራለን።—1 ጴጥ. 3:8

ለእንግዶች ባለን አመለካከት ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገን ይሆን?

6, 7. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በወቅቱ ተስፋፍቶ የነበረውን የወገናዊነት መንፈስ ለማስወገድ ምን ጥረት አድርገዋል?

6 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖች በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ ተስፋፍቶ የነበረውን የወገናዊነት መንፈስ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ነበረባቸው። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ወቅት፣ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከተለያዩ አገሮች የመጡና በቅርቡ ክርስቲያን የሆኑ ሰዎችን በእንግድነት ተቀብለዋል። (ሥራ 2:5, 44-47) እነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከተለያዩ አገሮች ለመጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ያሳዩት ፍቅራዊ አሳቢነት “እንግዳ መቀበል” ሲባል “ለእንግዶች ደግነት ማሳየት” ማለት እንደሆነ መገንዘባቸውን ያሳያል።

7 የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ እያደገ ሲሄድ ግን መድልዎ እንዳለ የሚጠቁም ሁኔታ መታየት ጀመረ። ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ አይሁዳውያን መበለቶቻቸው ቸል ስለተባሉባቸው ቅሬታ አሰሙ። (ሥራ 6:1) ሐዋርያት ይህን ችግር ለመፍታትና ማንም ቸል እንዳይባል ለማድረግ ሲሉ ሰባት ወንዶች ሾሙ። ሰባቱም ወንዶች የግሪክኛ ስም ያላቸው መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምናልባትም ሐዋርያት ይህን ያደረጉት በዜግነት ምክንያት በጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ለማብረድ አስበው ሊሆን ይችላል።—ሥራ 6:2-6

8, 9. (ሀ) ለሌሎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዳለን ወይም በዘራችን የመኩራት ዝንባሌ በውስጣችን እያቆጠቆጠ እንደሆነ የሚያሳየው ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የትኛውን አመለካከት ከውስጣችን ነቅለን ማውጣት ይኖርብናል? (1 ጴጥ. 1:22)

8 ሁላችንም፣ አናስተውለው ይሆናል እንጂ ያደግንበት ባሕል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርግብናል። (ሮም 12:2) በተጨማሪም ጎረቤቶቻችን አሊያም አብረውን የሚሠሩ ወይም የሚማሩ ሰዎች ከእኛ የተለየ ዜግነት፣ ዘርና የቆዳ ቀለም ያላቸውን ሰዎች የሚያንቋሽሽ ነገር ሲናገሩ እንሰማ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያለው የተዛባ አመለካከት ተጽዕኖ እያደረገብን ይሆን? አንድ ሰው በባሕላችን ውስጥ ያለን አንድ ነገር አጋንኖ በማቅረብ በትውልድ አገራችን ላይ ቢቀልድ ምን ይሰማናል?

9 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አይሁዳዊ ላልሆኑ ሰዎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ ነበረው፤ ውሎ አድሮ ግን እንዲህ ያለውን አሉታዊ አመለካከት ማስወገድ ችሏል። (ሥራ 10:28, 34, 35፤ ገላ. 2:11-14) እኛም በተመሳሳይ ለሌሎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዳለን ወይም በዘራችን የመኩራት ዝንባሌ በውስጣችን እያቆጠቆጠ እንደሆነ ካስተዋልን፣ ይህን አመለካከት ከሥሩ ነቅለን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። (1 ጴጥሮስ 1:22⁠ን አንብብ።) ሁላችንም ለመዳን የማንበቃ ሰዎች መሆናችንን እንዲሁም ዜግነታችን ምንም ይሁን ምን ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደሆንን ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 3:9, 10, 21-24) ታዲያ ከሌሎች እንደምንበልጥ እንዲሰማን የሚያደርግ ምን ምክንያት አለን? (1 ቆሮ. 4:7) ይልቁንም ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረው ዓይነት አመለካከት ልናዳብር ይገባል፤ ጳውሎስ እንደ እሱ ቅቡዓን የሆኑትን የእምነት ባልንጀሮቹን “ከዚህ በኋላ እንግዶችና ባዕዳን አይደላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ . . . የአምላክ ቤተሰብ አባላት ናችሁ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ኤፌ. 2:19) ለሌላ አገር ሰዎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ እንዳይኖረን ልባዊ ጥረት ማድረጋችን አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ይረዳናል።—ቆላ. 3:10, 11

ለእንግዶች ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10, 11. ቦዔዝ ከሞዓባዊቷ ሩት ጋር በተያያዘ ያደረገው ነገር ለባዕድ አገር ሰዎች እንደ ይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?

10 ቦዔዝ ከሞዓባዊቷ ሩት ጋር በተያያዘ ያደረገው ነገር ለባዕድ አገር ሰዎች እንደ ይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዳለው ያሳያል። ቦዔዝ በማሳው ላይ የሚካሄደውን የአጨዳ ሥራ ለመቃኘት ሲሄድ፣ አንዲት የባዕድ አገር ሴት ከአጫጆቹ ኋላ እየተከተለች ስትቃርም አየ። ቦዔዝ ይህች ሴት የመቃረም መብት ቢኖራትም እንኳ ይህን ለማድረግ ፈቃድ እንደጠየቀች ሲሰማ፣ ከታጨዱት ነዶዎች ላይ እንኳ ሳይቀር እንድትቃርም በመፍቀድ ደግነት አሳያት።—ሩት 2:5-7, 15, 16⁠ን አንብብ።

11 ከዚያ በኋላ ካደረጉት ውይይት መረዳት እንደሚቻለው ቦዔዝ የሩት ሁኔታ እንዲሁም የባዕድ አገር ሰው በመሆኗ ሊያጋጥማት የሚችለው ችግር አሳስቦት ነበር። ይህን ከሚጠቁሙት ነገሮች አንዱ፣ ማሳ ውስጥ የሚሠሩት ወንዶች እንዳያስቸግሯት ከወጣት ሴት ሠራተኞቹ ሳትርቅ እንድትሠራ የነገራት መሆኑ ነው። ሌላው ቀርቶ እንደ ቅጥር ሠራተኞቹ ሁሉ እሷም በቂ ምግብና ውኃ ማግኘት እንድትችል አድርጎ ነበር። በተጨማሪም ቦዔዝ ሩትን ያነጋገረበት መንገድ ይህችን ድሃ የባዕድ አገር ሴት ዝቅ አድርጎ እንደማይመለከታት የሚያሳይ ነው፤ እንዲያውም አበረታቷታል።—ሩት 2:8-10, 13, 14

12. ከሌላ አገር በቅርቡ ለመጡ ሰዎች ደግነት ማሳየታችን ምን ጥሩ ውጤት ሊኖረው ይችላል?

12 ቦዔዝ፣ ሩትን እንዲያደንቃት ያደረገው ለአማቷ ለናኦሚ የነበራት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የይሖዋ አምላኪ ለመሆን መወሰኗም ጭምር ነው። ቦዔዝ፣ ‘በክንፎቹ ሥር ለመጠለል ብላ ወደ እስራኤል አምላክ’ ለመጣችው ለሩት ደግነት ማሳየቱ እንደ ይሖዋ ዓይነት ታማኝ ፍቅር እንደነበረው ይጠቁማል። (ሩት 2:12, 20፤ ምሳሌ 19:17) እኛም በተመሳሳይ ደግነት ማሳየታችን “ሁሉም ዓይነት ሰዎች” እውነትን እንዲያውቁ እንዲሁም ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወዳቸው እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል።—1 ጢሞ. 2:3, 4

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሌላ አገር ሰዎች ወደ መንግሥት አዳራሻችን ሲመጡ ሞቅ አድርገን እንቀበላቸዋለን? (አንቀጽ 13, 14ን ተመልከት)

13, 14. (ሀ) የውጭ አገር ሰዎች ወደ መንግሥት አዳራሻችን ሲመጡ ሞቅ አድርገን ለመቀበል ልባዊ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ከአንተ የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር መጨዋወት የሚከብድህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

13 የውጭ አገር ሰዎች ወደ መንግሥት አዳራሻችን መጀመሪያ ሲመጡ ሞቅ አድርገን በመቀበል ደግነት ልናሳያቸው እንችላለን። እኛ ወደምንኖርበት አገር በቅርቡ የመጡ የሌላ አገር ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ዓይናፋርነት እንደሚታይባቸውና ከሌሎች ጋር መቀላቀል እንደሚከብዳቸው አስተውለን ይሆናል። በአስተዳደጋቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ቦታ የተነሳ ሌላ ዘር ወይም ዜግነት ካላቸው ሰዎች እንደሚያንሱ ሊሰማቸው ይችላል። በመሆኑም ቅድሚያውን ወስደን ሞቅ አድርገን ልንቀበላቸውና ልባዊ አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል። JW Language (ጄ ደብልዩ ላንግዌጅ) የተባለው አፕሊኬሽን በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነ ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሰላምታ ለመስጠት ይረዳሃል።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4⁠ን አንብብ።

14 ከአንተ የተለየ ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር መጨዋወት ይከብድህ ይሆናል። እንዲህ ያለውን ስሜት ለማሸነፍ ስለ ራስህ አንዳንድ ነገሮች ልትነግራቸው ትችላለህ። ይህን ስታደርግ ከልዩነቶቻችሁ ይልቅ የሚያመሳስሏችሁ ነገሮች እንደሚበዙ ትገነዘብ ይሆናል፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ ባሕል የራሱ የሆነ ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን እንዳለው ትረዳለህ።

እንግድነት እንዳይሰማቸው እርዷቸው

15. ከሌላ አገር መጥተው ከአዲስ ባሕል ጋር ለመላመድ ለሚጥሩ ሰዎች አሳቢነት ለማሳየት ምን ይረዳናል?

15 ሌሎች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ እንግድነት እንዳይሰማቸው መርዳት እንድንችል ‘እኔ ወደ ሌላ አገር ብሄድ ሰዎች ምን እንዲያደርጉልኝ እፈልጋለሁ?’ ብለን ራሳችንን በሐቀኝነት መጠየቃችን ጠቃሚ ነው። (ማቴ. 7:12) ከሌላ አገር መጥተው ከአዲስ ባሕል ጋር ለመላመድ ለሚጥሩ ሰዎች ትዕግሥት አሳዩ። መጀመሪያ ላይ፣ የሚያስቡበትን ወይም አንዳንድ ነገሮችን የሚያደርጉበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይከብደን ይሆናል። ይሁን እንጂ እነሱ አመለካከታቸውን ቀይረው የእኛን ባሕል እንዲቀበሉ ከመጠበቅ ይልቅ እነሱንም ሆነ ባሕላቸውን ለመቀበል ለምን ጥረት አናደርግም?—ሮም 15:7⁠ን አንብብ።

16, 17. (ሀ) ከሌላ አገር ከመጡ ሰዎች ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ምን ማድረግ እንችላለን? (ለ) በጉባኤያችን ያሉ የውጭ አገር ዜጎችን በየትኞቹ መንገዶች ልንረዳቸው እንችላለን?

16 ከሌላ አገር ስለመጡ ሰዎች ባሕልና ስለ አገራቸው ለማወቅ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ከእነሱ ጋር መነጋገር ቀላል ይሆንልናል። በጉባኤያችን ወይም በክልላችን ውስጥ ስለሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ብዙም የማናውቅ ከሆነ በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ስለ እነዚህ ሰዎች ባሕል ምርምር ለማድረግ ጊዜ መመደብ እንችላለን። ከባዕድ አገር ከመጡ ሰዎች ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ የሚረዳን ሌላው ነገር ደግሞ ቤታችን መጋበዝ ነው። ይሖዋ “ለአሕዛብ የእምነትን በር [ከከፈተላቸው]” እኛስ “በእምነት ለሚዛመዱን” የውጭ አገር ሰዎች ቤታችንን ክፍት ልናደርግላቸው አይገባም?—ሥራ 14:27፤ ገላ. 6:10፤ ኢዮብ 31:32

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሌላ አገር የመጡ ሰዎችን ቤታችን እንጋብዛቸዋለን? (አንቀጽ 16, 17ን ተመልከት)

17 ከሌላ አገር ከመጡ ቤተሰቦች ጋር ጊዜ ማሳለፋችን እነዚህ ሰዎች የእኛን ባሕል ለመላመድ ምን ያህል ጥረት እያደረጉ እንዳሉ ለማስተዋል ያስችለናል። እነዚህ ሰዎች ቋንቋውን ለመማር እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እንገነዘብ ይሆናል። በተጨማሪም ተስማሚ መኖሪያ ወይም ሥራ ማግኘት እንዲችሉ ልንረዳቸው እንችል ይሆን? እንዲህ ማድረጋችን በእምነት ባልንጀሮቻችን ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።—ምሳሌ 3:27

18. በዛሬው ጊዜ በሌላ አገር የሚኖሩ ሰዎች አክብሮትና አድናቆት በማሳየት ረገድ የማንን ምሳሌ መከተል ይችላሉ?

18 እርግጥ ነው፣ ከሌላ አገር የመጡ ሰዎችም ከሄዱበት አገር ባሕል ጋር ለመላመድ የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ግልጽ ነው። በዚህ ረገድ ሩት ግሩም ምሳሌ ትሆናለች። አንደኛ ለመቃረም ፈቃድ በመጠየቅ፣ ለሄደችበት አገር ባሕል አክብሮት እንዳላት አሳይታለች። (ሩት 2:7) መቃረም መብቷ እንደሆነ ወይም ደግሞ ሌሎች እሷን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለባቸው አልተሰማትም። ሁለተኛ፣ ለተደረገላት ደግነት አድናቆቷን ገልጻለች። (ሩት 2:13) የሌላ አገር ዜጎች እንዲህ ያለ መልካም ባሕርይ ካላቸው፣ የአገሩ ነዋሪዎችም ሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸው አክብሮት ያሳዩዋቸዋል።

19. በመካከላችን ያሉ እንግዶችን ለመቀበል የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?

19 ይሖዋ የተለያየ ባሕልና ዜግነት ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ አጋጣሚ በመክፈት ጸጋውን ስላሳየን በጣም ደስተኞች ነን። አንዳንዶች በትውልድ አገራቸው መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ወይም ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር በነፃነት የመሰብሰብ አጋጣሚ አላገኙ ይሆናል። አሁን ግን ከእኛ ጋር የመሰብሰብ አጋጣሚ አግኝተዋል፤ ታዲያ በእኛ መሃል ሲሆኑ እንግድነት እንዳይሰማቸው ልንረዳቸው አይገባም? በቁሳዊ ነገሮች ወይም በሌላ መንገድ ልንሰጣቸው የምንችለው እርዳታ ውስን ቢሆንም እንኳ ለእነሱ ደግነት ማሳየታችን እንደ ይሖዋ እንደምንወዳቸው ያረጋግጣል። እንግዲያው በመካከላችን ያሉ እንግዶችን ለመቀበል የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ‘አምላክን እንምሰል።’—ኤፌ. 5:1, 2

^ [1] (አንቀጽ 1) ስሙ ተቀይሯል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ