ጥናት 29
የድምፅ ጥራት
ሰዎችን የሚማርካቸው የሚነገረው መልእክት ብቻ ሳይሆን የሚነገርበትም መንገድ ነው። አንድ ሰው ሲያነጋግርህ ደስ ብሎህ የምትሰማው የድምፁ ቃና አሳቢነት የጎደለውና የቁጣ ከሚሆን ይልቅ ፍቅር፣ ርኅራኄና ደግነት የተንጸባረቀበት ቢሆን አይደለምን?
የድምፃችን ጥራት ከድምፅ አወጣጥ ሂደት ጋር ብቻ የተያያዘ ጉዳይ አይደለም። የግለሰቡም ባሕርይ በዚህ ረገድ የራሱ ድርሻ ሊኖረው ይችላል። አንድ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለው እውቀት እያደገ ሲሄድና ያንንም በሕይወቱ ሲሠራበት በአነጋገሩ የሚያደርገው ለውጥ በግልጽ ይታያል። የድምፁ ቃና እንደ ፍቅር፣ ደስታና ደግነት ያሉትን አምላክ የሚደሰትባቸው ባሕርያት የሚያንጸባርቅ ይሆናል። (ገላ. 5:22, 23) ለሌሎች ያለውን ልባዊ አሳቢነት ከድምፁ ቃና ማስተዋል ይቻላል። የማጉረምረምንና የማማረርን ዝንባሌ አስወግዶ በምትኩ የአመስጋኝነትን ባሕርይ ሲያዳብር ይህ ለውጥ ከአፉ በሚወጣው ቃልና በድምፁ ቃና ግልጽ ሆኖ ይታያል። (ሰቆ. 3:39-42፤ 1 ጢሞ. 1:12፤ ይሁዳ 16) አንድ ሰው እየተናገረ ያለውን ቋንቋ ባትረዳው እንኳ አነጋገሩ የቁጣ፣ የእብሪትና የትችት ይሁን ወይም ደግሞ የትሕትና፣ የደግነትና የፍቅር ከድምፁ ቃና በቀላሉ መረዳት ትችላለህ።
አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ድምፁ ጥሩ የማይሆነው በሕመም ምክንያት ማንቁርቱ ሲጎዳ ወይም ደግሞ አብሮት በሚወለድ እንከን ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያሉት ችግሮች ከባድ ከመሆናቸው የተነሣ በዚህ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መፍትሔ አያገኙ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የአንደበት ክፍሎችን በሚገባ መጠቀም የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማር ድምፅን ለማሻሻል ይረዳል።
በመጀመሪያ ደረጃ የድምፅ ሁኔታ ከሰው ሰው እንደሚለያይ መገንዘብ ያስፈልጋል። ግብህ የሌሎችን ሰዎች ድምፅ መኮረጅ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ የራሱ ልዩ ባሕርይ ያለውን ድምፅህን በተሻለ መንገድ መጠቀምን ተማር። ይህን ለማድረግ ሊረዳህ የሚችለው ምንድን ነው? ሁለት ዓበይት ነገሮች አሉ።
አተነፋፈስህን መቆጣጠር። ድምፅህን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም በቂ አየር መሳብና አተነፋፈስህን በተገቢው መንገድ መቆጣጠር ያስፈልግሃል። አለዚያ ግን ድምፅህ ሊደክምና ንግግርህ ሊቆራረጥ ይችላል።
ሰፋ ያለው የሳንባህ አካል የሚገኘው በደረትህ የላይኛው ክፍል አይደለም። ይህ አካባቢ ትልቅ መስሎ የሚታየው በትከሻ አጥንቶች ምክንያት ነው። ከዚህ ይልቅ ሳንባችን ሰፋ የሚለው ከወደታች ከድልሺ አካባቢ ነው። ድልሺ የሚባለው ጡንቻ ከታችኞቹ የጎድን አጥንቶች ጋር የተያያዘና ደረትንና የሆድ ዕቃን የሚከፍል ነው።
አየር ወደ ውስጥ በማስገባት የሞላኸው የሳንባህን የላይኛውን ክፍል ብቻ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ትንፋሽ ያጥርሃል። ድምፅህ ኃይል አይኖረውም፤ አንተም ቶሎ ትደክማለህ። ጥሩ አተነፋፈስ እንዲኖርህ ትከሻዎችህን ወደኋላ ለጠጥ አድርገህ ቀጥ ብለህ መቀመጥ ወይም መቆም ያስፈልግሃል። ከመናገርህ በፊት አየር ወደ ውስጥ በምትስብበት ጊዜ የሚለጠጠው የደረትህ የላይኛው ክፍል ብቻ መሆን የለበትም። በቅድሚያ የታችኛውን የሳንባህን ክፍል አየር መሙላት ይኖርብሃል። የታችኛው የሳንባህ ክፍል አየር ሲሞላ የጎድን አጥንቶችህ ወደ ጎንና ወደ ጎን ይለጠጣሉ። በዚህ ጊዜ ድልሺ ሆድ ዕቃህን ቀስ ብሎ ወደታች ሲጫነው ቀበቶህ አካባቢ ግፊቱ ይሰማሃል። ይሁንና ሳንባህ ያለው ሆድ ዕቃህ መካከል ሳይሆን ሳንባ አቃፊህ ውስጥ ነው። ይህን ሂደት ራስህ ማየት እንድትችል ሳንባ አቃፊህን ከግራና ከቀኝ በእጆችህ በመያዝ አየር በደንብ ወደ ውስጥ አስገባ። አተነፋፈስህ ትክክለኛ ከሆነ ሆድህ ወደ ውስጥ ተሰልቦ ደረትህ አይነፋም። ከዚህ ይልቅ የጎድን አጥንቶችህ ወደ ውጭ ወጣ ይላሉ።
ቀጥሎ ደግሞ እንዴት አየር እንደምታስወጣ ተለማመድ። ያስገባኸውን አየር ቀስ በቀስ ልታስወጣ ይገባል እንጂ በአንድ ጊዜ በማስወጣት ማባከን የለብህም። ጉሮሮህን በማስጨነቅ አየሩ እንዳይወጣ ለመቆጣጠር አትሞክር። ይህ ደግሞ ድምፅህ እንዲሻክር ወይም እንዲሰልል ያደርጋል። የሆድ ጡንቻዎችና በጎድን አጥንቶች መካከል ያሉት ጡንቻዎች አየር እንዲወጣ የሚያደርጉ ሲሆኑ ድልሺ ግን አየሩ የሚወጣበትን ፍጥነት ይቆጣጠራል።
አንድ ሯጭ ትንፋሹን መቆጣጠር እንደሚለማመድ ሁሉ አንድ ተናጋሪም አተነፋፈሱን በመለማመድ ትንፋሹን መቆጣጠርን ሊማር ይችላል። ቀጥ ብለህና ትከሻዎችህን ወደኋላ ለጠጥ አድርገህ በመቆም የሳንባህን የታችኛውን ክፍል አየር ሙላ። ከዚያም ቀስ በቀስ ትንፋሽህን እየለቀቅህ ረጋ ብለህ በዚያው አንድ ትንፋሽ የቻልከውን ያህል ቁጠር። ከዚያም በተመሳሳይ መንገድ እየተነፈስህ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማንበብን ተለማመድ።
የተወጠሩ ጡንቻዎችን ማዝናናት። የድምፅን ጥራት ለማሻሻል ሌላው በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ዘና ማለት ነው! በምትናገርበት ጊዜ ዘና ማለት በድምፅህ አወጣጥ ላይ ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ ስታይ ትገረማለህ። ጭንቀት ጡንቻዎች እንዲወጠሩ ስለሚያደርግ አእምሮህም ሆነ ሰውነትህ ዘና ማለት ይኖርበታል።
ስለ አድማጮችህ ተገቢውን አመለካከት መያዝ ጭንቀትህን ይቀንስልሃል። በአገልግሎት የምታገኛቸውን ሰዎች በተመለከተ ምናልባት አንተ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናኸው ለጥቂት ወራት ብቻም እንኳ ቢሆን ስለ ይሖዋ ዓላማ ልትነግራቸው የምትችለው ጠቃሚ መልእክት እንደያዝህ አስታውስ። ደግሞም እነርሱ ተገነዘቡትም አልተገነዘቡት ልታነጋግራቸው የሄድከው እርዳታ ስለሚያስፈልጋቸው መሆኑን አትርሳ። በመንግሥት አዳራሽ ንግግር የምትሰጥም ከሆነ በዚያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ አድማጮችህ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው። አንተ ሲሳካልህ ማየት የሚመኙ ወዳጆችህ ናቸው። እንዲህ ዓይነት አፍቃሪ አድማጮች የትም ልታገኝ አትችልም።
የጉሮሮ ጡንቻዎችህን ሥራዬ ብለህ ዘና ለማድረግ መጣር ይኖርብሃል። ሐብለ ድምፅህ አየር በውስጡ በሚያልፍበት ጊዜ እንደሚርገበገብ አስታውስ። የክራር ወይም የመሰንቆ ክር ሲወጠር ወይም ሲላላ ድምፁ እንደሚለወጥ ሁሉ የጉሮሮ ጡንቻዎችም ሲጨነቁ ወይም ዘና ሲሉ የድምፃችን ቃና ይለዋወጣል። ሐብለ ድምፁ ዘና ሲል ድምፅ ወፈር ያለ ይሆናል። የጉሮሮ ጡንቻዎችን ማዝናናት አየር በሰርን በኩል እንደልብ እንዲወጣ ስለሚያደርግ ጥሩ ድምፅ ለማውጣት ይረዳል።
መላ ሰውነትህ ማለትም ጉልበትህ፣ እጅህ፣ ትከሻህና አንገትህ ዘና እንዲል አድርግ። ይህም ሰውነት ድምፅ ጥርት ብሎ እንዲሰማ የሚረዳ የማስተጋባት ባሕርይ እንዲኖረው ያደርጋል። ሰውነታችን በደንብ ድምፅ የማስተጋባት ባሕርይ የሚኖረው ዘና ሲል ስለሆነ ውጥረት ካለበት ይህን ተግባሩን ሊያከናውን አይችልም። ማንቁርት ውስጥ የተፈጠረው ድምፅ የሚያስተጋባው በሰርን ዋሻ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በደረታችን የአጥንት ክፍሎች፣ በጥርስ፣ በላንቃና በሳይነስ አማካኝነት ጭምር ነው። እነዚህ ሁሉ ድምፁ በጥሩ ሁኔታ እንዲስተጋባ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በክራሩ የድምፅ ሣጥን ላይ አንድ ነገር ብትጭንበት ድምፁ ይታፈናል። ድምፅ በደንብ እንዲያስተጋባ ካስፈለገ እንዳይነዝር የሚያግድ ነገር መኖር የለበትም። ጡንቻዎቻችን በመወጠራቸው ምክንያት የሰውነታችን አጥንቶችም መንዘር ካልቻሉ ድምፃችን ይታፈናል። ድምፅህ በደንብ የሚያስተጋባ ከሆነ ግን ድምፅህን መለዋወጥም ሆነ የተለያዩ ስሜቶችን ማንጸባረቅ ትችላለህ። አድማጮችህ ብዙ ቁጥር ያላቸው ቢሆኑም እንኳ በጣም መጨነቅ ሳያስፈልግህ በቂ ድምፅ ማውጣት ትችላለህ።