-
የክፍል ትምህርትትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች
-
-
ሐሳቦች ወይም ሥዕላዊ ትምህርቶች በመታጠብ ላይ እንዳለ ከተሰማቸው የጾታ ትምህርት በሚሰጥባቸው ክፍሎች እንዳይገቡ ሊጠይቁ ይችላሉ።
ሳይንስና ዝግመተ ለውጥ:- የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሳይንስ ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። በዙሪያችን ስላለው ዓለም ያለን ግንዛቤ በጣም እንዲጨምር ላስቻሉን ትጉህ ሳይንቲስቶች አክብሮት አላቸው። ወጣቶቻችን የተለያዩትን የሳይንስ ዘርፎች እንዲማሩ እናበረታታቸዋለን። ምክንያቱም ከዚህ የሚያገኙት እውቀት ለፈጣሪያችን ጥበብና ኃይል ያላቸውን አድናቆት ይጨምርላቸዋል።
ይሁን እንጂ ሳይንስ ነው የሚባለው ሁሉ እውነት ላይሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ እንደ ሳይንሳዊ ሐቅ ተደርገው የሚተላለፉ እንደ ዝግመተ ለውጥ የመሳሰሉ ንድፈ ሐሳቦችም አሉ። ዝግመተ ለውጥ የመጀመሪያው ሕይወት ያለው ነገር የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገር ነው፤ ከዚያም ይህ ሕይወት ያለው ነገር ሲዋለድ ዘሮቹ እየተለወጡ በምድር ላይ የሚኖሩትን ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ሕይወት ያላቸውን ነገሮች አስገኘ ይላል።
የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ንድፈ ሐሳብ እውነት ነው ብለው አያምኑም። ወይም ደግሞ መላው ፍጥረት ቃል በቃል በሰባት ቀናት ብቻ ተፈጥሮ አለቀ የሚል እምነት የለንም። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት እንዲሁም ሌሎቹ ሕያው ፍጥረታት በሙሉ በአምላክ እንደተፈጠሩ እናምናለን። ስለዚህ ሕይወት ስላላቸው ነገሮች አመጣጥ ስለሚገልጹ ንድፈ ሐሳቦች ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ መምህራን የምሥክር ወጣቶቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ቢያከብሩላቸው በጣም ደስ ይለናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ እምነታቸው ከሳይንሳዊ ጭብጦች ጋር እንደሚስማማ እናምናለን። ይህን ለማወቅ ከፈለጋችሁ ምሥክር ወጣቶቻችን ስለ እምነታቸው በደስታ ያስረዷችኋል።
ሙዚቃና የኪነ ጥበብ ትምህርት:- የይሖዋ ምሥክሮች የሙዚቃ ወይም የሥነ ጥበብ ትምህርት ራሱ ስህተት ነው ብለው አያምኑም። ይሁን እንጂ ምሥክር ወጣቶች ከሃይማኖታዊ ወይም የአርበኝነት ስሜት ከሚቀሰቅሱ በዓሎች ጋር ግንኙነት ባለው ማንኛውም ዓይነት ሙዚቃና ኪነ ጥበብ አይሳተፉም። በትምህርት ቤት በሚሰጥ የሙዚቃ ትምህርት በመካፈል ረገድ ግን ምሥክር ወጣቶችና ወላጆቻቸው ከግምት ሊያስገቧቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ።
ለምሳሌ ያህል ትምህርቱ የት፣ በምን ሁኔታ እንደሚሰጥና የሚጫወቱት ሙዚቃ ምን ዓይነት ባሕርይ እንዳለው ያጤናሉ። ትምህርቱ በፖለቲካዊ ወይም በሃይማኖታዊ በዓሎች ላይ በሚጫወት የሙዚቃ ጓድ ውስጥ ማገልገልን የሚጨምር ከሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር ሊሳተፍበት አይችልም። ምሥክሮች የሆኑ ተማሪዎች በልምምድ ክፍለ ጊዜም እንኳን ቢሆን ብሔራዊ መዝሙር ወይም ከሃይማኖት ወይም ከብሔራዊ በዓላት ጋር ግንኙነት ያላቸውን መዝሙሮች አይጫወቱም። ሊታሰብበት የሚገባው ሌላ ጉዳይ የሚወስደው ጊዜና ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለቤተሰብ እንቅስቃሴዎች መሰናክል መሆንና አለመሆኑ ነው።
የጦር ትምህርት:- በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ወታደራዊ ትምህርት ይሰጣቸል። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ። ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም። ከእንግዲህ ወዲህ ሰልፍ [ጦርነት አዓት] አይማሩም” ብሎ ከሚናገርላቸው ሰዎች መካከል ለመሆን ይፈልጋሉ። (ኢሳይያስ 2:4) ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በትምህርት ቤት ወታደራዊ ሥልጠና ከሚሰጥባቸው ትምህርቶች ነፃ እንዲሆኑ ይጠይቃሉ።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “በተቻላችሁ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ይላል። (ሮሜ 12:18) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ሥራ ላይ ማዋላችን ስለ ሌላ ዓይነት የውትድርና ጥበቦች ያለንን አመለካከትም ይነካል። እነዚህም እንደ ጁዶ፣ ካራቴና ኬንዶ እንዲሁም እንደ ቦክስና ነፃ ትግል የመሳሰሉት ወታደራዊ ጥበቦች ናቸው። እነዚህ ወታደራዊ ልምምዶች ተራ ስፖርት ናቸው ቢባሉም እንደነዚህ ያሉትን ወታደራዊ ጥበቦች መለማመድ ለውጊያ ወይም በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ መሠልጠን እንደሆነ አድርገን እንመለከታለን። በዚህ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ባሉት የውትድርና እንቅስቃሴዎች አይካፈሉም። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ወጣቶች በእነዚህ ከመካፈል ነፃ እንዲሆኑ ቢጠይቁም በሌሎች መደበኛ የትምህርት ጊዜያት በሚሰጡ የአካል ማሠልጠኛ ፕሮግራሞች በተቻለ መጠን በደስታ ይተባበራሉ።
-
-
በምርጫ የሚሰጡ ሹመቶችትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች
-
-
በምርጫ የሚሰጡ ሹመቶች
በብዙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በድምጽ ብልጫ ተመርጠው እንደ ክፍል አለቃ ወይም ፕሬዘዳንት የመሰለ ሹመት ይሰጣቸዋል። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች አነስተኛ የፖለቲካ ዘመቻ ያካሂዳሉ። በተጨማሪም ዕጩዎችን የሚያስተዋውቁባቸው ፖስተሮችና ተለጣፊ ወረቀቶች ያዘጋጃሉ። ዓላማውም ወጣቶችን ከፖለቲካ አሠራር ጋር ለማስተዋወቅ ነው። ይሁን እንጂ ምሥክር ወጣቶች ራሳቸውን ለምርጫ በማቅረብም ሆነ ሌሎችን በመምረጥ በትምህርት ቤት በሚከናወነው ፖለቲካ አይካፈሉም። ስለዚህ ለተወዳዳሪነት ቢሰየሙ ወይም ለሥልጣን ቢመረጡ ጥበብ በተሞላበት መንገድ እንደማይቀበሉ ያስታውቃሉ። በዚህ መንገድ ሊያነግሡት ሲፈልጉ የሸሸውን የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ።—ዮሐንስ 6:15
ይሁን እንጂ መምህሩ ራሱ ሲመድብ ሁኔታው የተለየ ይሆናል። ስለዚህ ምሥክሮች ለትራፊክ አመራር ወይም ይህን ለሚመስል ሥራ እንዲረዱ በመምህራቸው ቢመረጡ በተቻላቸው ሁሉ እንዲተባበሩ ይበረታታሉ።
በእርግጥ ወጣቶቻችን ሁሉም ዓይነት ምርጫ ፖለቲካዊ አለመሆኑን ይገነዘባሉ። አንዳንዴ ተማሪዎች በተወሰነ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ መምህሩ ሊጠይቃቸው ይችላል። ስለ አንዳንድ ሥራዎች ወይም እንቅስቃሴዎች የሚሰማቸውን እንዲናገሩ ወይም ለአንድ ንግግር ወይም ድርሰት ያላቸውን አስተያየት እንዲገልጹ ቢጠየቁ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጣስ ላይሆንባቸው ይችላል። ስለ አንዳንድ ነገሮች ጥሩነት ያላቸውን አስተያየት ለመግለጽ እጅ ማውጣትና አንድን ሰው ለፖለቲካዊ ሥልጣን ለመምረጥ እጅ ማውጣት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምሥክር ወጣቶች በትምህርት ቤት በሚከናወነው ፖለቲካ አይካፈሉም
-
-
ከትምህርት ቤቱ ሥርዓት ጋር መተባበርትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች
-
-
ከትምህርት ቤቱ ሥርዓት ጋር መተባበር
የይሖዋ ምሥክሮች ለልጆቻቸው ሊያስተላልፏቸው ከሚችሉት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ቅርሶች አንዱ ጥሩ ትምህርት እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ልጆቹ ለሚያገኙት ትምህርት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው እነማን ናቸው? በትምህርት ቤት የሚያስተምሯቸው መምህራን ብቻ ናቸውን?
የመጀመሪያ ደረጃ ኃላፊነት የሚወድቀው በመምህራን ላይ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ልጆች የተገኙት ከወላጆች እንደመሆኑ መጠን የቤተሰብ ክፍል ናቸው። የመንግሥት ወይም የማንኛውም አስተዳደራዊ ተቋም ንብረቶች አይደሉም። ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ሊማሩ እንደሚገባ የመወሰን ከአምላክ የተሰጠ ኃላፊነት አለባቸው።
ሆኖም የትምህርት ቤት መምህራን በጣም የሚደነቅና ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ያበረክታሉ። በዚህ ሥርዓት በተጓደለበት ዘመን የሚያከናውኑት ሥራ በጣም ከባድ እንደሚሆንባቸው እንገነዘባለን። ወላጆች ከመምህራን ጋር ለመተባበር ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
የወላጆች ትብብር
በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆች ከልጆቻቸው መምህራን ጋር መተዋወቃቸው፣ ከእነርሱ ጋር ለመገናኘትና ለመነጋገር ዝግጅት ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው። ከመምህራኑ ጋር የሚገናኙት ፊት ለፊት ለመፋጠጥ ሳይሆን በልጁ እድገት ረገድ ወላጆችና መምህራን እንዴት ሊተባበሩ እንደሚችሉ ለመነጋገር ነው። ወላጆች መምህሩ የሚናገረውን ለመስማትና ልጆቻቸው እንዲደረግላቸው ስለሚፈልጉት ነገር በግልጽ ለመናገር ደስተኞች ናቸው።
ምሥክር የሆነው አባት ወይም እናት ከመምህሩ ጋር ተገናኝቶ በሚነጋገርበት ጊዜ ልጆቹ ተገቢ የሆነ ክርስቲያናዊ ጠባይ እንዲያሳዩ እንደሚጠብቁባቸውና መጥፎ ነገር አድርገው ቢገኙ እንዲነገረው እንደሚፈልግ ለመምህሩ ማሳወቅ ይኖርበታል። መምህሩ ምክንያታዊ ቅጣት በሚሰጥበት ጊዜም ወላጆች እንደሚደግፉት እንዲያውም ቅጣቱን በቤትም ጭምር እንደሚያጠናክሩለት ሊያረጋግጡለት ይገባል።
ወላጆች ሊረዱ ከሚችሉባቸው ሌሎች መንገዶች አንዱ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ጥሩ ቁርስ መብላታቸውን ማረጋገጥ ነው። የቤት ሥራቸውን አሟልተው መሥራታቸውንና መጽሐፎቻቸውን በሙሉ መያዛቸውን አረጋግጡ። ሁልጊዜ ለትምህርት ቤቱ ደንቦች አክብሮት አሳዩ። ልጆቹም እንዲያከብሩ አሳስቡአቸው። ልጆቹ ስለ ትምህርት ቤትና በትምህርት ቤት ስላጋጠማቸው ማንኛውም ዓይነት ችግር እንዲናገሩ አድርጓቸው።
የዩናይትድ ስቴትስ የጤና፣ የትምህርትና የበጐ አድራጎት ክፍል ኸልፒንግ ችልድረን ሜክ ካርየር ፕላንስ: ቲፕስ ፎር ፓረንትስ በተባለው ጽሑፉ ላይ ልጆቻቸው እንዴት በጥሩ ሁኔታ እንዲማሩ ሊያነሳሷቸው እንደሚችሉ ለወላጆች እንዲህ በማለት ይነግራቸዋል:- “ልጃችሁ በትምህርት ቤት የሚማረውና የሚያጠናው ነገር ወደፊት ሥራ በሚይዝበት ጊዜ ምን ያህል እንደሚጠቅመው እንዲገነዘብ እርዱት። እንደ ንባብ፣ እንደ ሒሳብና እንደ ንግግር ችሎታ ያሉት ትምህርቶች ለማንኛውም የሥራ ዓይነቶች በጣም የሚያገለግሉ መሆናቸውን አስረዱት። በአጭሩ ትምህርት ቤት የሚሄዱት እንዲሁ መሄድ ስላለባቸው ብቻ ሳይሆን በጣም አስፈላጊ ምክንያት ስላለ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዷቸው።”
በዚህ ብሮሹር ላይ የተገለጸው ሁሉ በትምህርት ቤት ባለ ሥልጣኖችና በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች መካከል አስደሳች መተባበር እንዲኖር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ እናደርጋለን።
-