-
ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ማደራጀት የሚቻለው እንዴት ነው?መጠበቂያ ግንብ—1994 | ኅዳር 1
-
-
ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ማደራጀት የሚቻለው እንዴት ነው?
ሽሬሳደ በስፔን ውስጥ የምትኖር አስተዋይ የሆነች ትንሽ ልጅ ነች። አስተማሪዋ የክፍሉ ተማሪዎች “የገና አባት” (“ክሪስማስ ፋዘር”) የሚባለውን ሥዕል በቀለም እንዲቀቡ ስትነግራቸው ሽሬሳደ ገና የአራት ዓመት ልጅ ነበረች። ሽሬሳደ ወዲያው በዚህ ሥራ ላለመሳተፍ ጠየቀች። ይህን ለማድረግም ሕሊናዋ እንደማይፈቅድላት ገለጸች።
ሽሬሳደ ይህን ለማድረግ እምቢ ማለቷ አስተማሪዋን በጣም አስገረማት። ከዚያም አስተማሪዋ ይህን ማድረግ የአንድን አሻንጉሊት ሥዕል ቀለም ከመቀባት የተለየ ነገር እንዳልሆነና ይህም ምንም ስህተት እንደሌለበት ገለጸችላት። ሽሬሳደም “የአንድን አሻንጉሊት ሥዕል ቀለም ከመቀባት የተለየ ነገር ካልሆነ እኔ ራሴ የሣልኩትን አሻንጉሊት እንድቀባ ቢፈቀድልኝ እመርጣለሁ” ስትል መለሰች።
በሌላ ጊዜ ደግሞ የክፍሉ ተማሪዎች የብሔራዊውን ሰንደቅ ዓላማ ሥዕል ቀለም እንዲቀቡ ተነገራቸው። ሽሬሳደ አሁንም ሌላ ነገር መሥራት እንዲፈቀድላት ጠየቀች። ሁኔታውን ለማስረዳት ስትል ለአስተማሪዋ የሲድራቅን፣ የሚሳቅንና የአብደናጎምን ታሪክ ነገረቻት።—ዳንኤል 3:1–28
ከዚያም አስተማሪዋ ብዙም ሳትቆይ አድናቆቷን ለመግለጽ ለሽሬሳደ እናት ስልክ ደወለች። “ልጅሽ ስለ ሕሊናዋ በተደጋጋሚ አነጋግራኛለች። አይገርምሽም? በእሷ ዕድሜ ያለች አንዲት ልጅ ሕሊናዋ ለምን እንደሚረብሻት ማስረዳት መቻሏ በጣም የሚያስገርም ነው! እርግጥ፣ እኔ እያስተማራችኋት ባለው ነገር አልስማማም፤ ሆኖም እየተሳካላችሁ እንዳለ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ልጃችሁን እንደማደንቃትና እንደማከብራት እንድታውቁ እፈልጋለሁ” ስትል ተናገረች።
አንዲት የአራት ዓመት ልጅ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ለማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ማሪና የምትባለው እናቷ ሽሬሳደ መኝታ ቤቷ ውስጥ የራሷ ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት እንዳላት ገልጻለች። ቤተ መጻሕፍቱ እያሰመረች የምትዘጋጅባቸውን የራሷን የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎች፣ ለስብከት የምትጠቀምባቸውን ጽሑፎችና እሷ ከተወለደችበት ጊዜ ጀምሮ የታተሙ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን በሙሉ ያካተተ ነው። በቤተ መጻሕፍቷ ውስጥ ካሉት ጽሑፎች መካከል በጣም የምትወደው በካሴት የተቀዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን ነው። ሁልጊዜ ማታ ማታ በመጽሐፏ እየተከታተለች ይህን ካሴት ታዳምጣለች። ከላይ የተገለጹትን ውሳኔዎች ለማድረግ ያስቻሏት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ናቸው።
በሚገባ የተደራጀ ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት እናንተንም ሆነ ልጆቻችሁን ሊረዳ ይችላልን? በቤት ውስጥ ቤተ መጻሕፍት ማዘጋጀት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
“ቤተ መጻሕፍት ቅንጦት አይደለም”
ሄንሪ ዎርድ ቢቸር የተባሉ ሰው “ቤተ መጻሕፍት ቅንጦት ሳይሆን ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው” ብለዋል። ምንም እንኳን ባናውቀውም ሁላችንም ከእነዚህ “ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች” አንዱ አለን ማለት ይቻላል። እንዴት? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንኳ ካለን ይህ ራሱ እንደ አንድ ቤተ መጻሕፍት ሊቆጠር ስለሚችል ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም ከሁሉ የላቀ የቲኦክራሲያዊ መጻሕፍት ስብስብ ነው። በአራተኛው መቶ ዘመን ዤሮም እኛ መጽሐፍ ቅዱስ ብለን የምንጠራውን በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉትን መጻሕፍት የተሟላ ስብስብ ለመግለጽ ቢብሊዮቴካ ዲቫይና (የመለኮታዊ ጽሑፎች ስብስብ) በሚለው የላቲን ሐረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅሟል። ይሖዋ ተግባራዊ እርዳታ፣ ትምህርትና መመሪያ እንድናገኝ ይህን ቅዱስ የሆነ የጽሑፎች ስብስብ አዘጋጅቶልናል። በፍጹም እንደ ቀላል ልናየው የማይገባን ነገር ነው። መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘታችን በጥንት የነበሩ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች ከነበራቸው የበለጠ ብዙ መጻሕፍትን ያካተተ ቤተ መጻሕፍት አለን ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ በእጅ በተጻፉ ውድ የብራና ጽሑፎች ብቻ በሚገኝበት ወቅት ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ሰዎች አልነበሩም ማለት ይቻላል። ቢኖሩም በጣም ጥቂት ነበሩ። ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ በሮም ውስጥ በእስር ላይ ሳለ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማጥናት በፈለገበት ጊዜ ጢሞቴዎስ ከትንሿ እስያ አንዳንድ ጥቅልሎችን እንዲያመጣለት መጠየቅ ግድ ሆኖበት ነበር። ምናልባትም እነዚህ ጥቅልሎች አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ሊሆኑ ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:13) ሆኖም አንዳንድ ምኩራቦች ብዙ ጥቅልሎች ይቀመጡባቸው ስለነበረ ኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ በስብከት ሥራቸው በእነዚህ የጽሑፍ ስብስቦች ተጠቅመዋል። (ሉቃስ 4:15–17፤ ሥራ 17:1–3) ቅዱሳን ጽሑፎች ከመጀመሪያ መቶ ዘመን ይልቅ በአሁኑ ጊዜ እንደ ልብ ይገኛሉ።
ትልልቅ የማተሚያ መሣሪያዎች በመፈልሰፋቸው በዛሬው ጊዜ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የሚናገሩት ቋንቋ ምንም ይሁን ምን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠነኛ ዋጋ ሊያገኙ ይችላሉ። እኛም ከዚህ የቅዱስ “መጻሕፍት ስብስብ” በተጨማሪ ሌሎች ጽሑፎችን የማሰባሰብ ልዩ አጋጣሚ አለን። “ታማኝና ልባም ባሪያ” መንፈሳዊ ምግብ በወቅቱ ለማቅረብ ከመቶ ዓመት በላይ ያለምንም ፋታ ሲሠራ ቆይቷል።—ማቴዎስ 24:45–47
ነገር ግን የግል ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ካላደራጀን በዚህ ተወዳዳሪ በሌለው ትምህርት ሙሉ በሙሉ ልንጠቀም አንችልም። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ ለዚህ ቤተ መጻሕፍት የሚያስፈልጉትን መጻሕፍት ማሰባሰብ ነው። ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስፈልገንን ትክክለኛ ሐሳብ በቀላሉ ለማግኘት ስለሚያስችለን ይህን ቤተ መጻሕፍት የማደራጀቱ ጉዳይ በእርግጥ ጥረት ሊደረግለት ይገባል።
የትኞቹ መጻሕፍት ያስፈልጉኛል?
በጋብቻህ ውስጥ ያጋጠመህን የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችግር እንዴት መፍታት እንደምትችል ወይም ልጆችህ አደንዛዥ ዕፅ “አንወስድም!” የሚል አቋም እንዲይዙ እንዴት ልትረዳቸው እንደምትችል ግራ ገብቶህ ያውቃልን? በመንፈስ ጭንቀት እየተሠቃየ ያለ ጓደኛህን ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው? አምላክ በእርግጥ እንዳለና ለምን ክፋትን እንደ ፈቀደ የሚገልጹትን ማስረጃዎች በግልጽ ማብራራት ትችላለህን? በራእይ ምዕራፍ 17 ላይ የተገለጸው ቀይ አውሬ ምንን ይወክላል?
የተሟላ ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ካለህ እነዚህና ሌሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይችላሉ። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ መጻሕፍትን፣ ብሮሹሮችንና መጽሔቶችን አትሟል። ከዚህም በላይ እነዚህ ጽሑፎች የቤተሰብ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ሐሳቦችን ያቀርባሉ፣ በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ይገነቡልናል፣ የስብከት ችሎታችንን እንድናሻሽል ያስችሉናል እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንድናስተውል ይረዱናል።
ባለፉት 20 ዓመታት በማኅበሩ የታተሙትን ጽሑፎች አሁንም ማግኘት ይቻላል። ወደ እውነት የመጣኸው በቅርብ ጊዜ ከሆነ ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል በቋንቋህ የተዘጋጁትን በሙሉ ማግኘቱ ጥሩ ይሆናል። ምናልባትም ያለፉ ዓመታት የመጠበቂያ ግንብ ጥራዞች በቋንቋህ ይገኙ ይሆናል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል እና ኮንኮርዳንስ የተባሉትን መጻሕፍት የመሳሰሉ ምርምር ለማድርግ የሚረዱ ተወዳዳሪ የሌላቸው ጽሑፎችም በተለያዩ ቋንቋዎች ታትመዋል። ሆኖም እነዚህን መጻሕፍት ማግኘት የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው።
ቤተ መጻሕፍትህን አደራጅ!
መጽሐፉን የሆነ ቦታ እንዳስቀመጥከው ማወቅ አንድ ነገር ነው፤ የምትፈልገውን መጽሐፍ ማግኘት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ምርምር ለማድረግ የሚረዳንን መጽሐፍ በመፈለግ ብዙ ሰዓት የምናባክን ከሆነ ምርምር ለማድረግ ያለንን ፍላጎት እንደምናጣ የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፎቻችንን አመቺ በሆነ ቦታ በሚገባ አደራጅተን ካስቀመጥናቸው የግል ምርምር ለማድረግ የበለጠ ትኩረት ይኖረናል።
የሚቻል ከሆነ ዋና ዋናዎቹን ቲኦክራሲያዊ መጽሐፎች በአንድ ቦታ ማስቀመጥ ጠቃሚ ነው። በገበያ ላይ የምናገኛቸውን የመጻሕፍት መደርደሪያዎች መግዛት የማንችል ከሆነ ቀለል ባለ ዋጋ መሥራት ይቻላል። የግድ ትልቅ መሆን የለባቸውም። በተጨማሪም ቤተ መጻሕፍቱ አመቺ ቦታ ላይ የሚገኝ መሆን ይኖርበታል። ጣሪያ ጥግ የተቀመጡ መጻሕፍት አቧራ ከመጠጣት በስተቀር የሚሰጡት ጥቅም አይኖርም።
የሚቀጥለው ተግባር መጻሕፍቱን በቦታ በቦታቸው ማስቀመጥ ይሆናል። መጻሕፍቱን ምክንያታዊ በሆነ ቅደም ተከተል በማስተካከል የሚጠፋው አጭር ሰዓት በጣም ብዙ ጥቅም ያመጣል።
አብዛኞቹ የቤተሰብህ አባሎች የይሖዋ ምሥክሮች ካልሆኑ እንዴት ታደርጋለህ? ምንም እንኳን የምትፈልገውን ዓይነት ቤተ መጻሕፍት ማደራጀት ባትችል ቢያንስ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ ጽሑፎችን የያዘ መደርደሪያ በራስህ ክፍል ውስጥ ሊኖርህ ይችል ይሆናል።
ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት መንፈሳዊነትን ለመገንባት ሊረዳ ይችላል
አንዴ መጽሐፎቻችንን ካስተካከልን የምንፈልገውን ሐሳብ ለማውጣት የሚረዳን አንድ ዘዴ ደግሞ ያስፈልገናል። አእምሮአችን ሁሉንም ማስታወስ አይችል ይሆናል፤ እንዲሁም በቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍታችን ውስጥ ያሉትን መጻሕፍት በሙሉ አላነበብናቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ያለው ሐሳብ ሁሉ በቀላሉ ሊገኝ የሚቻል ነው። የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ በቋንቋችን የሚገኝ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማንኛውንም ርዕሰ ጉዳይ የሚመለከተውን ሐሳብ በቀጥታ እንድናገኝ ያስችለናል።
ለብዙ ዓመታት ልዩ አቅኚና ሽማግሌ ሆኖ ያገለገለው ኩሊያን የመጨረሻ ልጁን የግል ጥናት እንዲያደርግ ለማስተማር ኢንዴክስ (ማውጫ) ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳበረከተለት ይገልጻል። “የሰባት ዓመት ልጅ የሆነው ኪሮ በቅርቡ አንድ ቀን ከትምህርት ቤት መጣና ‘አባባ፣ ማኅበር ስለ ዳይኖሰርስ ምን ሐሳብ ሰጥታለች?’ ሲል ጠየቀኝ። በቀጥታ ወደ ኢንዴክስ ሄድንና ‘ዳይኖሰርስ’ የሚለውን ቃል ፈለግን። ወዲያው ርዕሰ ጉዳዩን በዝርዝር የሚያብራራ አንድ ንቁ! መጽሔት አገኘን። ኪሮ የዚያኑ ዕለት መጽሔቱን ማንበብ ጀመረ። አሁን ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍታችን እያንዳንዱን ርዕሰ ጉዳይ የሚዳስስ ጠቃሚ የሆነ ሐሳብ እንደያዘ ያውቃል። ልጆቻችን በቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት በጥሩ ሁኔታ መጠቀምን ከተማሩ በመንፈሳዊ እንዲያድጉ እንደሚረዳቸው አጥብቄ አምናለሁ። ምክንያታዊ ሐሳብ ማቅረብን ይማራሉ፤ ከዚህም በላይ የግል ጥናት አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ይገነዘባሉ።”
በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው የሽሬሳደ አባት ፋስቶ ልጆች በቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት እንዲጠቀሙ ማስተማር በተቻለ መጠን ቀደም ተብሎ መጀመር ይኖርበታል የሚል እምነት አለው። እንዲህ በማለት ገልጿል፦ “አሁን የስድስት ዓመት ልጅ ለሆነችው ሽሬሳደ በኢንዴክስ እንዴት እንደምትጠቀም እያሳየናት ነው። ገነት ስለምትሆነው ምድር በተሰጠው ተስፋ በጣም ስለተማረከች በመጀመሪያ ‘ገነት’ የሚለውን ቃል ከኢንዴክስ ላይ አሳየናት። ከዚያም የተጠቀሱትን የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች እንዴት ፈልጎ ማግኘት እንደሚቻል አስረዳናት። ብዙውን ጊዜ ሥዕሉን ብቻ እናሳያታለን። ሆኖም ይህን ዘዴ በመጠቀማችን ቤታችን ውስጥ ባሉት ጽሑፎች ላይ አንድ ዓይነት ማብራሪያ ለማግኘት ኢንዴክስ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ተምራለች። አንድ ቀን የፋሲካን በዓል በተመለከተ ከትምህርት ቤት ጥያቄ ይዛ ስትመጣ ይህንን ነጥብ እንደተገነዘበች አወቅን። ‘ለምን ከኢንዴክሱ (ከማውጫው) ውስጥ አንፈልግም’ ስትል እናቷን ጠየቀቻት።”
በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉን ነገር ፈትነን መልካም የሆነውን እንድንይዝ’ ያበረታታናል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) ይህም ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሉትን መመርመርን ይጠይቅብናል። (ሥራ 17:11) በሚገባ የተደራጀ ቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት ካለን እንዲህ ዓይነቱ ምርምር አስደሳች ሊሆንልን ይችላል። ንግግር ስንዘጋጅ፣ አንድን ችግር ለመፍታት የሚረዳንን ተግባራዊ ምክር ለማግኘት ስንጥር ወይም ትኩረትን የሚማርክ ሐሳብ ለማግኘት ስንፈልግ በቤተ መጻሕፍታችን በተሳካ ሁኔታ ከተጠቀምንበት ቤተ መጻሕፍታችን ምን ያህል ትልቅ ጥቅም እንዳለው በአእምሮአችን ውስጥ ይቀረጻል።
የሽሬሳደ ወላጆች “በአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ቤተ መጻሕፍት መኖሩ እንዲያው ቅንጦት አይደለም” ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጽሐፎችህን እንዴት መደርደር ትችላለህ?
መጽሐፎችህን በዚህ መንገድ መደርደር አለብህ የሚል ሕግ የለም። ሆኖም ምክንያታዊ በሆነው በሚከተለው መንገድ ከፋፍሎ መደርደሩ መጽሐፎችህን እንደ ይዘታቸው አደራጅተህ ልታስቀምጥ የምትችልበትን አንዱን መንገድ ያሳያል።
1. የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ጥቅስ በጥቅስ የሚያብራሩ ሐሳቦችን የያዙ መጻሕፍት
(ለምሳሌ፦ እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው፣ ራእይ ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!፣ “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”—እንዴት? ፣ “ፈቃድህ በምድር ይሁን”)
2. ከቤተሰብ ኑሮ ጋር ግንኙነት ያላቸው መጻሕፍት
(ለምሳሌ፦ የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው፣ የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ)
3. መጽሐፍ ቅዱስና ምርምር ለማድረግ የሚረዱ መጻሕፍት
(ለምሳሌ፦ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም—ባለማጣቀሻው፣ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች፣ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ (ኢንዴክስ)፣ ኮንኮርዳንስ፣ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል፣ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የኪንግደም ኢንተርሊነር ትርጉም፣ አንድ ጥሩ መዝገበ ቃላት)
4. በወቅቱ ለጉባኤ መጽሐፍ ጥናትና ለቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት የምንጠቀምባቸው መጻሕፍት
5. የቴፕ ካሴቶችና የቪዲዮ ካሴቶች
6. የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ጥራዞች
7. የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ
(ለምሳሌ፦ የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጻሕፍት፣ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች)
8. ዘወትር በአገልግሎታችን የምንጠቀምባቸው መጻሕፍትና ብሮሹሮች
(ለምሳሌ፦ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመርና ማስረዳት፣ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት?፣ ሰዎች አምላክን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ፣ እውነተኛው አንድ አምላክ ያስገኘው የአምልኮ አንድነት)
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽሬሳደ አሁን ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሆናለች
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ ልጅ ምንም እንኳን ትንሽ ቢሆንም በቲኦክራሲያዊ ቤተ መጻሕፍት እየተጠቀመ ነው
-
-
የአስተዳደር አካል ጭማሪመጠበቂያ ግንብ—1994 | ኅዳር 1
-
-
የአስተዳደር አካል ጭማሪ
የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ሠራተኞችን ብዛት ለመጨመር ሲባል በአሁኑ ጊዜ እያገለገሉ ባሉት 11 ሽማግሌዎች ላይ ከሐምሌ 1, 1994 ጀምሮ አንድ አባል ተጨምሯል። አዲሱ አባል ገሪት ሎይሽ ነው።
ወንድም ሎይሽ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቱን የጀመረው ኅዳር 1, 1961 ሲሆን ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 41ኛ ክፍል የተመረቀ ነው። ከ1963 እስከ 1976 ድረስ በኦስትሪያ ውስጥ በክልልና በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ አገልግሏል። በ1967 ካገባ በኋላ እሱና ባለቤቱ መሪት ቪየና በሚገኘው የኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆነው ለ14 ዓመታት አገልግለዋል። ከአራት ዓመታት በፊት በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ከተዛወሩ በኋላ ወንድም ሎይሽ በአስተዳደር ቢሮ ውስጥ እንዲሁም የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት በመሆን ሲያገለግል ነበር። በአውሮፓ መስክ ብዙ ተሞክሮ ያካበተና ጀርመንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ የሩማኒያ ቋንቋና ጣሊያንኛ የሚያውቅ በመሆኑ ለአስተዳደር አካሉ ሥራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
-