ከሲሞናዊነት ተጠበቁ!
የሰማሪያው ሲሞን በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሰው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የኖረ ሲሆን ሰዎች በጥንቆላ ሥራዎቹ በጣም ከመማረካቸው የተነሳ ስለእሱ በሚናገሩበት ጊዜ “ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው” ይሉ ነበር።—ሥራ 8:9-11
ይሁን እንጂ ሲሞን የተጠመቀ ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ቀድሞ እሱ ያሳይ ከነበረው እጅግ የሚልቅ ኃይል መኖሩን ተገነዘበ። ይህ ኃይል ለኢየሱስ ሐዋርያት የተሰጠ ሲሆን ለሌሎች ሰዎች አስደናቂ የሆኑትን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ለመስጠት አስችሏቸው ነበር። ሲሞን በነገሩ እጅግ ከመደነቁ የተነሳ ለሐዋርያት ገንዘብ በመስጠት “እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ” ብሎ ጠየቃቸው።—ሥራ 8:13-19
ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲሞንን እንዲህ ሲል ገሰጸው:- “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም።”—ሥራ 8:20, 21
“ሲሞናዊነት” የሚለው ቃል የተገኘው ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሲሆን ቃሉ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሹመት ወይም እድገት የመግዛት አሊያም የመሸጥ ኃጢአት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ዘ ኒው ካተሊክ ኢንሳክለፒዲያ በተለይ ከ9ኛው እስከ 11ኛው መቶ ዘመን ባለው ጊዜ ውስጥ “ሲሞናዊነት በገዳማት፣ በተራው የቀሳውስት ክፍል፣ በሲኖዶሱና አልፎ ተርፎም በሊቃነ ጳጳሳቱ ደረጃ ተንሰራፍቶ ነበር” ሲል ገልጿል። ዘጠነኛው ዚ ኢንሳክለፒዲያ ብሪታኒካ (1878) እትም የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- “ሊቃነ ጳጳሳቱን ለመምረጥ ይደረግ ስለነበረው ዝግ ስብሰባ የሚያጠና የታሪክ ተማሪ፣ ሲሞናዊነት ያልታከለበት አንድም ምርጫ አለመኖሩን የሚያሳምን በቂ ማስረጃ ያገኛል። እንዲያውም በዝግ ስብሰባው ላይ የሚፈጸመው ሲሞናዊነት በአብዛኞቹ አጋጣሚዎች በዓይነቱ እጅግ የከፋ፣ ዓይን ያወጣና ያልተሰወረ ነበር።”
በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሲሞናዊነት መጠበቅ አለባቸው። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ተጨማሪ መብቶች ሊሰጧቸው የሚችሉ ሰዎችን ከመጠን በላይ ያወድሷቸው ወይም ስጦታዎችን ያጎርፉላቸው ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን መብቶች መስጠት የሚችሉ ሰዎች ስጦታዎችን ለማምጣት አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ ላላቸው ሰዎች አድልዎ ያደርጉ ይሆናል። ሁለቱም ሁኔታዎች ሲሞናዊነት ሲሆኑ ቅዱሳን ጽሑፎች ደግሞ ይህ ዓይነቱን ተግባር በግልጽ ያወግዛሉ። ጴጥሮስ ሲሞንን እንዲህ ሲል አሳስቦታል:- “እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፣ ምናልባትም የልብህን አሳብ [“ይህ ስውር ዘዴህን፣” ኒው ጀሩሳሌም ባይብል] ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና።”—ሥራ 8:22, 23
ደግነቱ ሲሞን ክፉ ምኞቱ ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ተገንዝቧል። ሐዋርያቱን እንዲህ ሲል ተማጽኗቸዋል:- “ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ።” (ሥራ 8:24) እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ዘገባ ውስጥ የሚገኘውን ጠቃሚ ትምህርት በመጠበቅ ማንኛውንም የሲሞናዊነት ጉድፍ ለማስወገድ ይጥራሉ።