የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አመስጋኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 15
    • ስጦታዎች የምስጋና ደብዳቤዎችን ለመጻፍ የሚያስችል ጊዜ የምታጣው ለምንድን ነው?” ብዙውን ጊዜ ሰዎች “አመሰግናለሁ” የሚለውን ምንም ወጪ የማይጠይቅ ቃል እንኳን አይናገሩም። አመስጋኝነት ለእኔ ብቻ በሚለው አመለካከት በከፍተኛ መጠን እየተተካ ነው። ይህ ሁኔታ የመጨረሻውን ዘመን ለይተው ከሚያሳውቁ ምልክቶች ውስጥ አንዱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል:- “የመጨረሻዎቹ ቀናት በአደገኛ ሁኔታዎች የተሞሉ እንደሚሆኑ ማወቅ ይኖርብሃል። ሰዎች ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ ይሆናሉ። . . . ፈጽሞ ምስጋና ቢስ ይሆናሉ።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1, 2 ፊሊፕስ

      በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አመስጋኝነት በሽንገላ ቃላት ይተካል። የአመስጋኝነት መግለጫዎች አንድ ሰው ስለ ግል ጥቅሙ ሳያስብ የሚናገራቸው ከልብ የሚፈልቁ ቃላት ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ከልብ ያልመነጩና የተጋነኑ የሽንገላ ቃላት ወደፊት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመድረስ ወይም የግል ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በስውር ዓላማ የሚሰነዘሩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ይሁዳ 16) ይህን የመሰለው ለስላሳ አነጋገር ተሸንጋዩን ሰው የሚያታልል ከመሆኑም በላይ የኩራትና ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ውጤት ነው። ታዲያ ልባዊ ባልሆኑ የሽንገላ ቃላት መታለል የሚፈልግ ማን ነው? ይሁን እንጂ እውነተኛ የምስጋና ቃላት መንፈስን እንደሚያድሱ የተረጋገጠ ነው።

      አመስጋኝነቱን የሚገልጽ ሰው ይህን በማድረጉ ይጠቀማል። ምስጋና በማቅረቡ የሚሰማው ሞቅ ያለ ስሜት ለደስታውና ለሰላሙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (ከምሳሌ 15:​13, 15 ጋር አወዳድር።) አመስጋኝነት አዎንታዊ ባህርይ ስለሆነ እንደ ቁጣ፣ ቅናትና ብስጭት ከመሳሰሉት አፍራሽ አስተሳሰቦች ይጠብቀዋል።

      “የምታመሰግኑ ሁኑ”

      መጽሐፍ ቅዱስ የአመስጋኝነትን መንፈስ እንድናዳብር አጥብቆ ይመክረናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” (1 ተሰሎንቄ 5:​18) እንዲሁም ጳውሎስ የቆላስይስ ሰዎችን ሲመክር “የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ” ብሏል። (ቆላስይስ 3:​15) የምስጋና መግለጫዎችን የያዙ በርካታ መዝሙራት የሚገኙ ሲሆን ይህ ደግሞ ከልብ የመነጨ ምስጋና ማቅረብ አምላካዊ ባህርይ መሆኑን ያመለክታል። (መዝሙር 27:​4፤ 75:​1) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ አምላክ በዕለት ተለት የሕይወት ጉዳዮች ውስጥ አመስጋኝነታችንን ስናሳይ ይደሰታል።

      ሆኖም በዚህ ውለታ ቢስ ዓለም ውስጥ የአመስጋኝነት መንፈስ እንዳናዳብር ጋሬጣ የሚሆኑብን ነገሮች ምንድን ናቸው? በዕለት ተለት የሕይወት ሂደት ውስጥ አመስጋኝ መሆናችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራሉ።

  • የአመስጋኝነትን መንፈስ አዳብሩ
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | የካቲት 15
    • የአመስጋኝነትን መንፈስ አዳብሩ

      በኒው ዮርክ ግዛት የሚገኝ አንድ ሐኪም በአደገኛ ሁኔታ ላይ የምትገኘውን የማሪን ሕይወት ከሞት ያድናል። ይሁን እንጂ የ50 ዓመቷ ማሪ ሐኪሙን ማመስገን ቀርቶ የታከመችበትን ሒሳብ እንኳ አልከፈለችም። እንዴት ያለ ውለታቢስነት ነው!

      አንድ ጊዜ ኢየሱስ ወደ አንድ መንደር ሲገባ አስከፊው የሥጋ ደዌ በሽታ የያዛቸው አሥር ሰዎችን እንዳገኘ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰዎቹ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ “ኢየሱስ ሆይ፣ አቤቱ፣ ማረን አሉ።” ኢየሱስ “ሂዱ፣ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” ሲል አዘዛቸው። ለምጻሞቹ መመሪያውን ተቀብለው በመሄድ ላይ እያሉ ጤንነታቸው ሲመለስላቸው ይመለከቱና ይሰማቸው ጀመር።

      ከተፈወሱት ለምጻሞች ውስጥ ዘጠኙ በዚያው መንገዳቸውን ቀጠሉ። ነገር ግን ሳምራዊ የሆነው ሌላኛው ለምጻም ኢየሱስን ፍለጋ ተመለሰ። ቀደም ሲል ለምጻም የነበረው ይህ ሰው ኢየሱስን ሲያገኘው በእግሩ ሥር ተደፍቶ አመሰገነው። ኢየሱስም መልሶ:- “አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ።”​—⁠ሉቃስ 17:​11-19

      “ዘጠኙስ ወዴት አሉ?” በሚለው ጥያቄ ውስጥ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ተጠቅሷል። ልክ ማሪ እንዳደረገችው ዘጠኙ ለምጻሞች አመስጋኝነታቸውን ስላልገለጹ ስህተት ሠርተዋል። በዛሬው ጊዜ እንዲህ የመሰለው ውለታቢስነት በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?

      አመስጋኝነት የጠፋበት ምክንያት

      በመሠረቱ ውለታቢስነት የሚመነጨው ከራስ ወዳድነት ነው። የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ወላጆች አዳምንና ሔዋንን ተመልከት። ይሖዋ መለኮታዊ ስጦታዎችን የሰጣቸው ከመሆኑም በላይ ውብ የሆነ የአትክልት ስፍራ፣ ፍጹም አካባቢ እንዲሁም ትርጉም ያለውና የሚያረካ ሥራን ጨምሮ ለደስታቸው የሚሆን ማንኛውንም ነገር ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:​26-29፤ 2:​16, 17) ይሁንና በሰይጣን ተጽእኖ ምክንያት የገዛ ጥቅማቸውን ወደ ማሳደዱ አዘነበሉ። ስለዚህም ባልና ሚስቱ ታዛዥ ባለመሆን ለይሖዋ ልግስና አድናቆት ሳያሳዩ ቀርተዋል።​—⁠ዘፍጥረት 3:​1-5፤ ራእይ 12:​9

      በተጨማሪም አምላክ ልዩ ንብረቱ እንዲሆኑ የመረጣቸውን የጥንት እስራኤላውያንን ተመልከቱ። ኒሳን 14, 1513 ከዘአበ ምሽት በተፈጸመው ሁኔታ እስራኤላውያን ወላጆች ይሖዋን ምንኛ አመስግነው ይሆን! በዚያ ቅጽበታዊ ምሽት የአምላክ መልአክ ‘በግብጽ አገር ያሉትን በኩራት’ በሙሉ ሲገድል በትክክል ምልክት የተደረገባቸውን የእስራኤል ቤቶች ግን አልፎ ሄደ። (ዘጸአት 12:​12, 21-24, 30) እንዲሁም በቀይ ባሕር የፈርዖን ሠራዊት ሊያደርስባቸው ከነበረው ጥቃት ሲያመልጡ ልባቸው በምስጋና ተሞልቶ ‘ሙሴና የእስራኤል ልጆች ለይሖዋ ዘምረዋል።’​—⁠ዘጸአት 14:​19-28፤ 15:​1-21

      ይሁንና ግብጽን ለቀው ከወጡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ “የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ . . . አንጎራጎሩ።” ትንሽ እንኳ ሳይቆዩ ውለታቢስ ሆኑ! በግብጽ አገር በባርነት በነበሩበት ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው ‘በሥጋ ምንቸት አጠገብ መቀመጥንና እንጀራን እስኪጠግቡ ድረስ መብላትን’ ናፈቁ። (ዘጸአት 16:​1-3) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ራስ ወዳድነት አመስጋኝነትን እንዳናዳብርና እንዳናሳይ እንቅፋት የሚሆንብን ነገር ነው።

      የኃጢአተኛው አዳም ዝርያዎች እንደመሆናቸው መጠን የሰው ልጆች በሙሉ ራስ ወዳዶችና ወደ ውለታቢስነት ያደሉ ሆነው ይወለዳሉ። (ሮሜ 5:​12) ምስጋና ቢስ መሆንም በዚህ ዓለም በሚገኙ ሰዎች ላይ ጎልቶ የሚታይ የራስ ወዳድነት መንፈስ አንዱ ገጽታ ነው። ልክ እንደምንተነፍሰው አየር ይህ መንፈስ በየትም ቦታ የሚገኝ ሲሆን እኛንም ሊነካን ይችላል። (ኤፌሶን 2:​1, 2) ስለዚህ የአመስጋኝነትን ባሕርይ ማዳበር ይኖርብናል። ይህን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?

      ማሰላሰል የግድ አስፈላጊ ነው!

      ዌብስተርስ ሰርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ፣ ግራቲቲዩድ የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል “አመስጋኝ መሆን:- ውለታ ለዋለልን ሰው ውለታ መላሽ በመሆን የምናሳየው ሞቅ ያለ ወዳጃዊ ስሜት” በማለት ተርጉሞታል። ስሜት እንዲያው በዘፈቀደ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከውስጥ ፈንቅሎ የሚወጣ ነገር መሆን አለበት። አመስጋኝነት የጥሩ ሥነ ምግባር ወይም የግብረ ገብነት መግለጫ ብቻ ሳይሆን ከልብ የሚመነጭም ነገር ነው።

      ከልብ አመስጋኝ መሆንን ልንማር የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰማንን ስሜት በአብዛኛው ለማሰብ ከምንመርጠው ነገር ጋር ያዛምደዋል። (ኤፌሶን 4:​22-24) የአመስጋኝነትን ስሜት ማዳበር የምንማረው ስለ ተደረገልን ደግነት በአድናቆት ስናሰላስል ነው። ይህን አስመልክተው በአእምሮ ሕክምና ዘርፍ የሚሠሩት ዶክተር ዌን ደብልዩ ዳየር “አስቀድመህ ስላላሰላሰልክበት ነገር ምንም (ስሜት) ሊሰማህ አይችልም” ብለዋል።

      ለምሳሌ ያህል በዙሪያችን ስለሚገኘው ፍጥረት አመስጋኞች የመሆንን ጉዳይ ውሰድ። በከዋክብት የተሞላ ጥርት ያለ ሰማይ ስትመለከት ምን ይሰማሃል? ንጉሥ ዳዊት “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጎበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?” ሲል በአድናቆት ስሜት ተናግሯል። እንዲሁም ፀጥ ባለ ሌሊት ከዋክብቱ ለዳዊት በመናገር እንዲህ ብሎ እንዲጽፍ ገፋፍተውታል:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።” በከዋክብት የተሸፈኑ ሰማያት ዳዊትን በጥልቅ የነኩት ለምንድን ነው? እርሱ ራሱ መልሱን ሲመልስ “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህን ሁሉ አሰላሰልሁ፣ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ” ብሏል።​—⁠መዝሙር 8:​3, 4፤ 19:​1፤ 143:​5

      የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም በታላላቅ የፍጥረት ሥራዎች ላይ የማሰላሰልን ጥቅም ተገንዝቧል። ለምሳሌ ያህል ዝናብ ያዘሉ ደመናዎች ምድራችንን ስለ ማጠጣታቸው ሲጽፍ “ፈሳሾች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ፣ ባሕሩ ግን አይሞላም፤ ፈሳሾች ወደሚሄዱበት ስፍራ እንደ ገና ወደዚያ ይመለሳሉ።” (መክብብ 1:​7) ስለዚህ ዝናብና ወንዞች ምድርን ካራሱ በኋላ ውኃው ወደ ውቅያኖስ ይገባና በትነት እንደገና ተመልሶ ደመና ይሆናል። ይህን የመሰለው የውኃ ዑደት ባይኖር ኖሮ ምድር ምን ትመስል ነበር? ሰሎሞን በእነዚህ ነገሮች ላይ ሲያሰላስል ምን ያህል በምስጋና ስሜት ተሞልቶ ይሆን!

      አመስጋኝ የሆነ ሰው ከቤተሰቡ አባላት፣ ከወዳጆቹና ከጓደኞቹ ጋር ያለውን ዝምድናም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። በደግነት ተነሳስተው የሚያደርጓቸው ነገሮች ትኩረቱን ይስባሉ። ስላደረጉለት ነገር በአድናቆት ሲያሰላስል ልቡ በአመስጋኝነት ይሞላል።

      ምስጋናን መግለጽ

      “አመስግናለሁ” የሚለው ቃል ምንኛ ቀላል ነው! ይህን የመሰለውን መግለጫ መናገር ምንም አያስቸግርም። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችም ሞልተዋል። በር ለከፈተልን ወይም የወደቀብንን እቃ ላነሳልን ሰው ሞቅ ያለ ልባዊ ምስጋና ማቅረብ ምንኛ መንፈስን የሚያነቃቃ ነው! ሱቅ ውስጥ ያለን ሻጭ ወይም የቡና ቤት አስተናጋጅን ወይም ደግሞ ፖስታ የሚያመላልስልንን ሰው ብናመሰግን ሥራቸውን ከማቅለሉም በላይ ደስ ይላቸዋል።

      አመሰግናለሁ የሚል ቃል የተጻፈበት ካርድ መላክ ለተደረገልን ደግነት አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ የሚያስችለን ሌላው ቀላል መንገድ ነው። ከሱቅ የምንገዛቸው ብዙዎቹ ካርዶች ውስጣዊ ስሜትን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጹ ናቸው። ይሁን እንጂ በራስህ የእጅ ጽሑፍ አድናቆትህን የሚገልጹ ቃላት ጽፈህ ብትልክ ይበልጥ ፍቅራዊ ስሜትን የሚያንጸባርቅ አይሆንምን? እንዲያውም አንዳንዶች ምንም ያልተጻፈባቸውን ካርዶች በመግዛት የራሳቸውን ሐሳብ ጽፈው መስጠት ይመርጣሉ።​—⁠ከምሳሌ 25:​11 ጋር አወዳድር።

      በተለይ በአንድ ቤት ውስጥ አብረውን ለሚኖሩ ሰዎች አመስጋኝነታችንን መግለጽ ይገባናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ባለሙያ ሴት ሲናገር “ባልዋም ያመሰግናታል” ይላል። (ምሳሌ 31:​28 የ1980 ትርጉም) አንድ ባል ለሚስቱ ልባዊ የሆኑ የምስጋና ቃላትን መናገሩ ቤታቸውን ሰላምና ደስታ የሰፈነበት አያደርገውምን? በተጨማሪም ባል ውጭ ውሎ ሲመጣ ሚስቱ ሞቅ ያለ አቀባበል ብታደርግለት ደስ አይለውምን? በአሁኑ ጊዜ በትዳር ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ በርካታ ነገሮች አሉ፤ የተጽእኖዎች ማየል በቀላሉ በቁጣ እንድንገነፍል ሊያደርገን ይችላል። አመስጋኝ የሆነ ሰው ነገሮችን ግምት ውስጥ ለማስገባትና ይቅርታ ለመጠየቅ እንዲሁም ይቅር ለማለት ፈጣን ነው።

      ወጣቶችም ከልብ የመነጨ አድናቆታቸውን ለወላጆቻቸው ለመግለጽ ንቁ ሊሆኑ ይገባቸዋል። እርግጥ ወላጆች ፍጹማን አይደሉም። ይሁን እንጂ የእነሱ አለፍጽምና ላደረጉላችሁ ነገር ውለታቢስ እንድትሆኑ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ከተወለዳችሁበት ጊዜ አንስቶ ያሳዩአችሁ ፍቅርና ያደረጉላችሁ እንክብካቤ በፍጹም በገንዘብ ልትገዙት የምትችሉት ነገር አይደለም። የአምላክን እውቀት ካስተማሯችሁ ደግሞ አመስጋኞች የምትሆኑበት ተጨማሪ ምክንያት አላችሁ።

      መዝሙር 127:​3 “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” ይላል። ስለዚህ ወላጆች በረባ ባልረባው ከመጨቃጨቅ ይልቅ ልጆቻቸውን ለማመስገን የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች መፈለግ ይገባቸዋል። (ኤፌሶን 6:​4) እንዲሁም በትናንሽ ልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ የአመስጋኝነት መንፈስ እንዲኮተኮት የማድረግ ትልቅ መብት አላቸው!​—⁠ከምሳሌ 29:​21 ጋር አወዳድር።

      ለአምላክ አመስጋኝ መሆን

      ይሖዋ አምላክ ‘የበጎ ስጦታና የፍጹም በረከት ሁሉ’ ምንጭ ነው። (ያዕቆብ 1:​17) በተለይ የሕይወት ስጦታ ከሁሉ የላቀ ነው። ምክንያቱም አሁን ያሉን ነገሮችም ሆኑ ለወደፊት የምናወጣቸው እቅዶች በሕይወት መመላለሳችንን እስካልቀጠልን ድረስ ከንቱ ናቸው። ቅዱሳን ጽሑፎች ‘የሕይወት ምንጭ [ይሖዋ አምላክ] መሆኑን’ እንድናስታውስ አጥብቀው ይመክሩናል። (መዝሙር 36:​5, 7, 9፤ ሥራ 17:​28) አምላክን ከልብ የማመስገንን ልማድ ለማዳበር ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወታችንን ጠብቀው በሚያቆዩልን ዝግጅቶቹ ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። (መዝሙር 1:​1-3፤ 77:⁠11, 12) ይህን የመሰለው ልብ አድናቆታችንን በቃልም ሆነ በተግባር እንድናሳይ ይገፋፋናል።

      ለአምላክ አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት አንዱና ግልጽ የሆነው መንገድ ጸሎት ነው። መዝሙራዊው ዳዊት “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቁጥር ሁሉ በዛ” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 40:​5) እኛም በተመሳሳይ እንዲህ ብለን ለመናገር ልንገፋፋ ይገባል።

      በተጨማሪም ዳዊት ለሌሎች በሚናገረው ቃል አማካኝነት ለአምላክ አድናቆቱን ለመግለጽ ቆርጦ ተነሥቶ ነበር። “አቤቱ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ” ብሏል። (መዝሙር 9:​1) ለሌሎች ስለ አምላክ መናገርና በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ማካፈል አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው። ይህ በሌሎች የሕይወት ዘርፎችም አመስጋኞች እንድንሆን ይረዳናል።

      ይሖዋ “ምስጋናን እንደ መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብልኝ ያከብረኛል፤ እኔን የሚታዘዙትን ሁሉ አድናቸዋለሁ” ብሏል። ልባዊ ምስጋናን ለይሖዋ ከማቅረብ የሚገኘውን ደስታ የምታጭዱ ያድርጋችሁ።​—⁠መዝሙር 50:​23 የ1980 ትርጉም፤ 100:​2

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው። ውስጣዊ ስሜታችሁን የሚገልጽ ነገር አድርጉ

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ