የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 2/15 ገጽ 8-11
  • ወላጆች ልጆቻችሁን ከአደጋ ጠብቁ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወላጆች ልጆቻችሁን ከአደጋ ጠብቁ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስለ ጾታ ትምህርት በአፍሪካ ያለው አመለካከት
  • ማስተማር ለምን አስፈለገ?
  • ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት
  • ጥበቃ ያገኙና ደስተኛ የሆኑ ልጆች
  • ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ አውሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም የሚደረግብኝን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ቤተሰባችሁን ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎች ጠብቁ
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?—ክፍል 2
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 2/15 ገጽ 8-11

ወላጆች ልጆቻችሁን ከአደጋ ጠብቁ!

ናይጄርያ በሚገኝ በአንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትማር አንዲት ወጣት በጾታ ብልግና የታወቀች ስትሆን ጾታን በሚመለከቱ ጉዳዮች አብረዋት ለሚማሩት ሴት ተማሪዎች ምክር መስጠት ያስደስታት ነበር። ጽንስ ለማስወረድ ይጠቅማሉ ከምትላቸው ነገሮች መካከል አንዱ ትንባሆ የተቀላቀለበት በአካባቢው የሚጠመቅ ቢራ መጠጣት ነው። ከወሲባዊ ጽሑፎች እየወሰደች የምትናገራቸው ነገሮች አብረዋት የሚማሩትን አብዛኞቹን ጓደኞችዋን በጣም ይማርኳቸው ነበር። አንዳንዶች የጾታ ግንኙነት መፈጸም ጀመሩ፤ ከእነርሱም አንዷ ጸነሰች። ጽንሱን ለማስወረድ ብላ ከትምባሆ ጋር የተቀላቀለውን ቢራ ጠጣች። ወዲያው ደም ትተፋ ጀመር። ሆስፒታል ከገባች ከጥቂት ቀናት በኋላ ሞተች።

በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች ነጋ ጠባ ስለ ጾታ ያወራሉ፤ በቀላሉ የሚታለሉ አድማጮቻቸውንም ለውድቀት ይዳርጓቸዋል። ወጣቶች ከአደጋ የሚጠብቃቸውን ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ወደ ማን ዞር ማለት አለባቸው? ልጆቻቸውን ‘በጌታ ምክርና በተግሣጽ’ እንዲያሳድጉ ኃላፊነት ወደተሰጣቸው አምላካዊ ወላጆቻቸው ዞር ማለት ቢችሉ እንዴት ጥሩ ይሆናል።​—⁠ኤፌሶን 6:​4

ስለ ጾታ ትምህርት በአፍሪካ ያለው አመለካከት

በዓለም ዙሪያ ብዙ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ ጾታ ጉዳዮች መወያየት ይከብዳቸዋል። ይህ ችግር በተለይ በአፍሪካ ውስጥ ይብሳል። በሴራ ሊዮን የሚገኝ ዳኖልድ የተባለ አንድ ወላጅ “ስለ ጾታ ጉዳዮች ከልጆች ጋር መነጋገር ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። እንዲህ ማድረግ የአፍሪካ ባሕል አይደለም” ብሏል። ኮንፊደንት የተባለች ናይጄርያዊት ሴት ከዚህ አባባል ጋር መስማማቷን ስትገልጽ:- “ወላጆቼ የጾታ ጉዳይ በግልጽ መነገር እንደሌለበት አድርገው ይቆጥሩታል፤ በባሕላችን ስለዚህ ጉዳይ ማውራት ነውር ነው” ብላለች።

በአንዳንድ የአፍሪካ ባሕሎች ከጾታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን እንደ ቁላ፣ የወንድ ዘር ወይም የወር አበባ የመሳሰሉትን ቃላት መናገር እንደ ጸያፍ ይቆጠራል። እንዲያውም አንዲት ክርስቲያን እናት ሴት ልጅዋ “ዝሙት” የሚለውን ቃል መጠቀም እንደምትችል ብትናገርም “የጾታ ግንኙነት” የሚለውን ቃል ፈጽሞ እንዳታነሳ ከልክላታለች። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ግን ስለ ጾታና ስለ ጾታ ብልቶች በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 17:​11፤ 18:​11፤ 30:​16, 17፤ ዘሌዋውያን 15:​2 የ1980 ትርጉም) ዓላማው ሰዎችን ለማሳፈር ወይም ለማሳቅ ሳይሆን የአምላክን ሕዝቦች ለመጠበቅና ለማስተማር ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16

ከባሕልም ሌላ አንዳንድ ወላጆች ከጾታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ከማንሳት የሚቆጠቡበትን ምክንያት አንድ ናይጄርያዊ ወላጅ “ከልጆቼ ጋር ስለ ጾታ ከተወያየሁ የጾታ ብልግና እንዲፈጽሙ ሊያነሳሳቸው ይችላል” በማለት ገልጿል። ሆኖም ስለ ጾታ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተና ክብር ባለው መንገድ የተሰጠ ማብራሪያ ልጆች ወዲያውኑ እንዲሞክሩት ያበረታታልን? በጭራሽ አያበረታታም። እንደ እውነቱ ከሆነ ወጣቶች ስለ ጉዳዩ ያላቸው እውቀት ጠባብ በሆነ መጠን የጾታ ብልግና የመፈጸማቸው አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “[በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ] ጥበብ ለጥበቃ ያገለግላል” በማለት ይናገራል።​—⁠መክብብ 7:​12 NW

ኢየሱስ በሰጠው ምሳሌ ውስጥ አንድ አስተዋይ ሰው ኃይለኛ ዝናብ ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ቤቱን በአለት ላይ የሠራ ሲሆን ሞኙ ሰው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ በመሥራቱ ኪሳራ ደርሶበታል። (ማቴዎስ 7:​24-27) በተመሳሳይ አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው የዓለምን ልል የጾታ አቋም እንዲከተሉ ማዕበል መሰል ተጽእኖዎች እንደሚያጋጥሟቸው በማወቅ ጸንተው እንዲቆሙ የሚረዳቸውን ትክክለኛ እውቀትና ማስተዋል በመስጠት ልጆቻቸውን ያጠናክሯቸዋል።

ብዙ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ስለ ጾታ ጉዳዮች የማይነጋገሩበትን ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ስትገልጽ አንዲት አፍሪካዊት ሴት እንዲህ ብላለች:- “ወጣት በነበርኩበት ጊዜ ምሥክር የሆኑት ወላጆቼ ከእኔ ጋር ስለ ጾታ ጉዳዮች ተወያይተው አያውቁም፤ ከዚህ የተነሳ ከልጆቼ ጋር ስለ እነዚህ ጉዳዮች የመወያየቱ ሐሳብ ወደ አእምሮዬ መጥቶ አያውቅም።” ሆኖም በዛሬው ጊዜ ባሉት ወጣት ልጆች ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ ከ10 ወይም ከ20 ዓመታት በፊት በነበሩት ወጣቶች ላይ ይደርስ ከነበረው በጣም አይሏል። ይህ ምንም አያስደንቅም። ምክንያቱም የአምላክ ቃል አስቀድሞ እንደተናገረው “በመጨረሻው ቀን . . . ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1, 13

ችግሩን ያባባሰው ብዙዎቹ ልጆች ምሥጢራቸውን ለወላጆቻቸው ለማካፈል አለመፈለጋቸው ወይም አለመቻላቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ተራ በሆኑ ጉዳዮች እንኳ ከሁለቱም አቅጣጫ ያለው የሐሳብ ግንኙነት ደካማ ነው። አንድ የ19 ዓመት ወጣት “ከወላጆቼ ጋር ተወያይቼ አላውቅም። በእኔና በአባቴ መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት የለም። ትኩረት ሰጥቶ አያዳምጠኝም” ሲል አማሯል።

ወጣቶች ስለ ጾታ ጉዳዮች ጥያቄ ማንሳት መጥፎ መዘዝ ያስከትላል ብለውም ሊፈሩ ይችላሉ። አንዲት የ16 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ስለ ጾታ ባነሳ ወላጆቼ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ስለማውቅ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከእነርሱ ጋር አልወያይም። ከጥቂት ጊዜያት በፊት ታላቅ እህቴ እናቴን ከጾታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠይቃት ነበር። እናቴ ለችግሯ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄውን ያነሳችበትን ዓላማ መጠራጠር ጀመረች። እናቴ ብዙ ጊዜ እኔን እየጠራች ስለ እህቴ ትጠይቀኛለች አንዳንድ ጊዜም ስለ ሥነ ምግባር አቋሟ የተሳሳተ ትርጉም ትሰጥ ነበር። እናቴ ለእኔ ያላትን ፍቅር ማጣት ስለማልፈልግ ችግሮቼን ከእርስዋ ደብቄ እይዛለሁ።”

ማስተማር ለምን አስፈለገ?

ልጆቻችንን ስለ ጾታ ጉዳዮች በሚገባ ማስተማሩ ተገቢ ነገር ብቻ ሳይሆን የደግነት ተግባርም ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ጾታ ጉዳዮች ካላስተማሩ እነርሱ ጨርሶ ባልጠበቁት ጊዜ አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ፈጽሞ ባልተከተለ መንገድ ሌሎች ያስተምሯቸዋል። አንዲት የ13 ዓመት ልጅ ድንግልናዋን እንደጠበቀች ብትቆይ ወደፊት ከባድ ሥቃይ እንደሚደርስባት የክፍል ጓደኛዋ ስለነገረቻት ዝሙት ፈጸመች። “ክብረ ንጽሕናሽን በመቀስ ይቆርጡታል” ተብሎ ተነግሯት ነበር። የተነገራትን ነገር ለምን ለክርስቲያን እናቷ እንዳልተናገረች በተጠየቀች ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን ከአዋቂዎች ጋር መወያየት በጭራሽ አይቻልም ብላ መልሳለች።

አንዲት ናይጄርያዊት ልጃገረድ እንዲህ ብላለች:- “የትምህርት ቤት ጓደኞቼ የጾታ ግንኙነት ማንኛውም ጤናማ ሰው ሊፈጽመው የሚገባ ነገር እንደሆነ ሊያሳምኑኝ ሞክረዋል። አሁን የጾታ ግንኙነት መፈጸም ካልጀመርኩ 21 ዓመት ሲሞላኝ በቀሪው ሕይወቴ ላይ መጥፎ ተጽእኖ የሚያስከትል ሕመም እንደሚጀምረኝ ነግረውኛል። ስለዚህ ይህን የመሰለውን አስከፊ ችግር ለማስቀረት ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ጥሩ እንደሆነ ነግረውኛል።”

ይህች ልጅ ከወላጆችዋ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ስለነበራት እቤት ከተማረችው ነገር ጋር እንደሚጋጭ ወዲያውኑ ትዝ አላት። “እንደተለመደው ትምህርት ቤት የነገሩኝን ነገር እቤት ሄጄ ለእናቴ ነገርኳት።” እናቷም ይህ ፈጽሞ ውሸት መሆኑን አሳመነቻት።​—⁠ከምሳሌ 14:​15 ጋር አወዳድር።

ልጆች ጾታን በተመለከተ አምላካዊ ጥበብ እንዲያገኙ የሚረዳውን አስፈላጊ የሆነ እውቀት በመስጠት ወላጆች ልጆቻቸው አደገኛ የሆኑ ሁኔታዎችንና በጾታ ሊደፍሯቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ለይተው እንዲያውቁ ያሰለጥኗቸዋል። በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና ያልተፈለገ እርግዝና ከሚያስከትሉት የልብ ሐዘን እንዲጠበቁ ይረዳቸዋል። ለራሳቸው አክብሮት እንዲኖራቸውና ሌሎች በአክብሮት እንዲመለከቷቸው አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከተሳሳቱ ሐሳቦችና ከጭንቀቶች ነፃ ያደርጋቸዋል። ተገቢ ለሆነ የጾታ ግንኙነት ጤናማና አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ከማድረጉም በላይ ወደ ፊት ትዳር ከመሰረቱ ለደስታ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቋም እንዲይዙ ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም ልጆች ፍቅራዊ አሳቢነት እንደተደረገላቸው ሲገነዘቡ ለወላጆቻቸው ከበፊቱ የበለጠ አክብሮትና ፍቅር እንዲኖራቸው ሊገፋፋቸው ይችላል።

ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት

ወላጆች ከልጆቻቸው ሁኔታ ጋር የሚስማማ ምክር ለመስጠት እንዲችሉ የሐሳብ ግንኙነቱ በሁለቱም አቅጣጫ ክፍት መሆን አለበት። ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮና ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ ካልጣሩ የሚሰጡት ምክር ጥሩ ቢሆንም እንኳ ምንም ጥቅም አይኖረውም። ሁኔታው አንድ ዶክተር የበሽተኛውን ችግር ሳይረዳ መድኃኒት ለማዘዝ ከመሞከሩ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጥሩ መካሪዎች ለመሆን ወላጆች ልጆቻቸው በእርግጥ ምን እንደሚያስቡና እንደሚሰማቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ልጆቻቸው የሚገጥሟቸውን ተጽእኖዎችና ችግሮች እንዲሁም የሚረብሿቸውን ጥያቄዎች መረዳት ይኖርባቸዋል። ልጆችን በጥሞና ማዳመጥ ማለትም ‘ለመስማት የፈጠኑ ለመናገርም የዘገዩ’ መሆን አስፈላጊ ነው።​—⁠ያዕቆብ 1:​19፤ ምሳሌ 12:​18፤ መክብብ 7:​8

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የጠበቀ ዝምድና ማለትም ልጆች ውስጣዊ ስሜታቸውን ገልጸው መናገር የሚያስችላቸው ዝምድና ለመመሥረትና ጠብቆ ለማቆየት ጊዜ፣ ትዕግሥትና ጥረት ይጠይቅባቸዋል። ሆኖም ይህን ዓይነቱን ዝምድና መመሥረት በጣም አስደሳች ነው! አንድ በምዕራብ አፍሪካ የሚኖር የአምስት ልጆች አባት እንዲህ ይላል:- “ለልጆቼ አባታቸው ብቻ ሳይሆን የምሥጢር ጓደኛቸውም ነኝ። ልጆቼ ጾታን ጨምሮ ማንኛውንም ጉዳይ ከእኔ ጋር በነፃነት ይወያያሉ። ሌላው ቀርቶ ሴት ልጆቼም ምሥጢራቸውን ይነግሩኛል። የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመወያየት ጊዜ እንመድባለን። ደስታቸውንም ከእኔ ጋር ይካፈላሉ።”

ከሴት ልጆቹ አንዷ የሆነችው ቦላ እንዲህ ትላለች:- “ከአባቴ የምደብቀው ምንም ምሥጢር የለም። አባቴ አሳቢና የሰውን ስሜት የሚረዳ ነው። ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ጭምር እንኳ አይጮህብንም ወይም አያመናጭቀንም። ከመናደድ ይልቅ ጉዳዩን በጥሞና ካጤነ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብን ወይም ምን ማድረግ እንዳልነበረብን ያስረዳናል። አብዛኛውን ጊዜ ማብራሪያ ለማግኘት ወጣትነትህ እና ቤተሰብ የተባሉትን መጻሕፍት ያነባል።”a

የሚቻል ሆኖ ሲገኝ ወላጆች ለልጆቻቸው ስለ ጾታ ጉዳይ ገና ሕፃን እያሉ ጀምሮ መንገር ቢጀምሩ ጥሩ ይሆናል። እንዲህ ከተደረገ አብዛኛውን ጊዜ አስቸጋሪ በሆኑት በአሥራዎቹ እድሜ ጭምር ለሚዘልቅ ቀጣይ የሆነ ውይይት መሠረት ይጥላል። ውይይቱ ልጆቹ ገና ትንንሽ ሳሉ ካልተጀመረ አንዳንድ ጊዜ ከጊዜ በኋላ መጀመር አስቸጋሪ ይሆናል፤ ሆኖም መጀመር የማይቻል ነገር አይደለም። አምስት ልጆች ያሏት አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- “እኔም ሆንኩ ልጄ ስለ ጾታ ጉዳይ መናገር የሚያሳፍረን መሆኑ እስኪቀር ድረስ ነገሩን ለማንሳት ራሴን አስገድድ ነበር።” የልጃችሁ ደኅንነት አደጋ ላይ ስለሆነ ይህን የመሰለው ጥረት ጊዜና ጉልበት ቢጠፋለት በእርግጥ የማይቆጭ ነው።

ጥበቃ ያገኙና ደስተኛ የሆኑ ልጆች

ልጆች ከአደጋ የሚጠብቃቸውን እውቀት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚያስታጥቋቸውን ወላጆች ያደንቃሉ። በአፍሪካ የሚገኙ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሰጡትን ሐሳብ ቀጥሎ ተመልከት:-

ሃያ አራት ዓመት የሆናት ሞጂሶላ እንዲህ ትላለች:- “ሁልጊዜ እናቴን አመሰግናታለሁ። በተገቢው ጊዜ ስለ ጾታ አስፈላጊውን ትምህርት ሰጥታኛለች። ምንም እንኳ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ስታስረዳኝ አፍር የነበረ ቢሆንም አሁን ግን እናቴ ያደረገችልኝን ጥሩ ነገሮች መመልከት ችያለሁ።”

ኢንኦቦም በማከል እንዲህ ትላለች:- “እናቴ ጾታን በተመለከተ በቂ ስልጠና በመስጠት ያደረገችልኝን ነገር ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከትና ሳስታውስ ሁልጊዜ እደሰታለሁ። ስልጠናው ትልቅ ሴት እስክሆን ድረስ በጣም ጠቅሞኛል። ወደፊት ልጆች ስወልድ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ወስኛለሁ።”

የአሥራ ዘጠኝ ዓመቱ ኩንሌ እንዲህ ብሏል:- “ልቅ የሆነ የጾታ ግንኙነት እንድፈጽም ከዓለማዊ ሴቶች የሚደርስብኝን ተጽእኖ መቋቋም እንድችል ወላጆቼ ረድተውኛል። እነርሱ ስልጠና ባይሰጡኝ ኖሮ ብልግና እፈጽም ነበር። እነርሱ ያደረጉልኝን ምንጊዜም አደንቃለሁ።”

ክርስቲያና እንዲህ ብላለች:- “ስለ ጾታ ጉዳዮች ከእናቴ ጋር የሐሳብ ልውውጥ በማድረጌ ብዙ ጥቅሞች አግኝቻለሁ። ቀሳፊ ከሆኑ በሽታዎችና ካልተፈለገ እርግዝና ልጠበቅ ችያለሁ። በተጨማሪም ለታናናሽ ወንድሞቼና እህቶቼ ሊከተሉት የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ለመተው ችያለሁ። በሌሎች ሰዎች ዘንድ አክብሮት አትርፌአለሁ እንዲሁም ወደ ፊት የማገባው የትዳር ጓደኛዬም ያከብረኛል። ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ ትእዛዛቱን ስለምጠብቅ ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና አለኝ።”

ከላይ የተጠቀሰችው ቦላ እንደሚከተለው ብላለች:- “ያለ አንዳች የጋብቻ ትስስር በጾታ ግንኙነት መደሰት ይቻላል ብላ የምትነግረኝ አንድ የክፍል ጓደኛ ነበረችኝ። የጾታ ግንኙነት መፈጸምን እንደ ቀልድ ትቆጥረው ነበር። ሆኖም በማርገዝዋ ምክንያት ከእኛ ጋር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰድ ሳትችል ስትቀር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ቀልድ አለመሆኑን ተገነዘበች። አመራር የሚሰጠኝ ጥሩ አባት ባይኖረኝ ኖሮ እኔም እንደርሷ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ቀልድ አለመሆኑን ከሚድርስብኝ ችግር ለመማር እገደድ ነበር።”

በወሲባዊ ጉዳዮች ባበደ በዚህ ዓለም ውስጥ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው “መዳን የሚገኝበትን ጥበብ” እንዲያገኙ መርዳታቸው በጣም ያስደስታል! (2 ጢሞቴዎስ 3:​15) ወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው ለልጆቻቸው የሚሰጡት ማሰልጠኛ በአምላክ ዓይን ከሚያስጌጣቸውና ከሚያስውባቸው ውድ ሐብል ጋር ተመሳሳይ ነው። (ምሳሌ 1:​8, 9) ልጆች ያለ ስጋት ይኖራሉ፤ ወላጆች ደግሞ ጥልቅ እርካታ ያገኛሉ። ከወጣት ልጆቹ ጋር ያለውን የንግግር መስመር ሁልጊዜ ክፍት ለማድረግ የሚጥር አንድ አፍሪካዊ አባት እንዲህ ብሏል:- “የአእምሮ ሰላም አለን። ልጆቻችን ይሖዋን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ እንደሚያቁና ዓለማዊ ሰዎች ሊያታልሏቸው እንደማይችሉ እርግጠኞች ነን። በቤተሰቡ ላይ ሐዘን የሚያስከትሉ ነገሮች እንደማያደርጉ እርግጠኞች ነን። በእነርሱ ላይ ያለንን ትምክሕት መና ስላላስቀሩብን ይሖዋን አመሰግናለሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ያስተማሯቸው ክርስቲያን ወጣቶች ሌሎች ወጣቶች ስለ ጾታ ጉዳዮች የሚነግሯቸውን የተዛባ መረጃ አንፈልግም ሊሉ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ