የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ‘እንደኛው ዓይነት ስሜት የነበራቸው’ ሰዎች
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | መጋቢት 1
    • ‘እንደኛው ዓይነት ስሜት የነበራቸው’ ሰዎች

      ንጉሥና ነቢይ ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ አባትም ነበር። ከወንዶች ልጆቹ መካከል አንዱ ካደገ በኋላ ትዕቢተኛና ኩሩ ሆነ። የአባቱን ዙፋን ለመቀማት ቆርጦ በመነሳት የእርስ በርስ ጦርነት እንዲጀመር አደረገ፤ ዓላማው አባቱ እንዲገደል ነበር። ሆኖም በተካሄደው ጦርነት የተገደለው ልጅየው ነበር። አባትየው የልጁን መሞት ሲሰማ ለብቻው ወደ ሰገነት ወጥቶ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፣ ልጄ፣ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፣ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፣ ልጄ አቤሴሎም፣ ልጄ ሆይ” ብሎ አለቀሰ። (2 ሳሙኤል 18:​33) አባትየው ንጉሥ ዳዊት ነው። እንደ ሌሎቹ የይሖዋ ነቢያት ሁሉ እርሱም ‘እንደኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው’ ነበር።​—⁠ያዕቆብ 5:​17

      በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የይሖዋ መልእክተኞች ሆነው ያገለገሉት ወንዶችና ሴቶች የተለያየ የኑሮ ደረጃ የነበራቸው ተራ ሰዎች ነበሩ። ልክ እንደኛ ችግሮች የነበሩባቸው ሲሆኑ ከአለፍጽምና ጋር ብዙ ትግል ያደርጉ ነበር። ከእነዚህ ነቢያት መካከል አንዳንዶቹ እነማን ናቸው? እንደኛው ዓይነት ስሜቶች የነበሯቸውስ እንዴት ነው?

      በራሱ ይመካ የነበረው በኋላ ግን ትሑት የሆነው ሙሴ

      ሙሴ በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖረ አንጋፋ ነቢይ ነበር። ሆኖም 40 ዓመት ቢሆነውም እንኳ የይሖዋ ቃል አቀባይ ሆኖ ለማገልገል ብቁ አልነበረም። ለምን? ወንድሞቹ በግብፁ ፈርዖን ይጨቆኑ በነበሩበት ጊዜ ሙሴ በፈርዖን ቤት ውስጥ ከማደጉም በላይ “በቃሉና በሥራውም የበረታ” ሆኖ ነበር። ታሪኩ “ወንድሞቹም እግዚአብሔር በእጁ መዳንን እንዲሰጣቸው የሚያስተውሉ ይመስለው ነበር” በማለት ይነግረናል። በራሱ ከልክ በላይ በመመካት አንድን ዕብራዊ ባሪያ ለማስጣል የኃይል እርምጃ በመውሰድ አንድ ግብፃዊ ሰው ገደለ።​—⁠ሥራ 7:​22-25፤ ዘጸአት 2:​11-14

      ከዚህ የተነሳ ሙሴ ሸሽቶ ለመሄድ ተገደደ። በዚህ ምክንያት ቀጣዮቹን አራት አሥርተ ዓመታት ራቅ ባለው በምድያም አገር እረኛ ሆኖ አሳለፈ። (ዘጸአት 2:​15) አርባው ዓመት ሲያበቃ፣ አሁን 80 ዓመት የሆነው ሙሴ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል በይሖዋ ታዘዘ። ሆኖም ሙሴ እንደ በፊቱ በራሱ ከልክ በላይ የሚመካ አልነበረም። ብቁ እንዳልሆነ ስለተሰማው “ወደ ፈርዖን የምሄድ . . . እኔ ማን ነኝ?” እና “ምን እላቸዋለሁ?” የሚሉ አገላለጾችን በመጠቀም ይሖዋ እርሱን ነቢይ አድርጎ መላኩ ትክክል መሆኑን አጠያያቂ አደረገ። (ዘጸአት 3:​11, 13) ሙሴ በይሖዋ ፍቅራዊ ማጽናኛና እርዳታ አመርቂ ውጤቶች እያገኘ የተመደበለትን ሥራ ማከናወኑን ቀጠለ።

      አንተም እንደ ሙሴ ያለ ልክ በራስህ ላይ ተመክተህ ጥበብ የጎደላቸውን ነገሮች አድርገህ ወይም ተናግረህ ታውቃለህን? ከሆነ ተጨማሪ ስልጠና ሲሰጥህ በትሕትና ተቀበል። ወይም አንዳንድ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ብቃቱ እንደሌለህ ተሰምቶህ ያውቃል? ወደ ኋላ ከማፈግፈግ ይልቅ በይሖዋና በድርጅቱ አማካኝነት የሚቀርብልህን እርዳታ ተቀበል። ለሙሴ እርዳታ የሰጠው አንተንም ሊረዳህ ይችላል።

      ኤልያስ ተግሳጽ በተሰጠው ጊዜ እንደኛው ዓይነት ስሜቶች ነበሩት

      “ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ [“እንደኛው ዓይነት ስሜቶች የነበሩት፣” NW] ሰው ነበረ፣ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፣ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም።” (ያዕቆብ 5:​17) የኤልያስ ጸሎት ይሖዋ ከእርሱ የራቀውን ሕዝብ ለመቅጣት ከነበረው ፍላጎት ጋር የሚስማማ ነበር። ሆኖም ኤልያስ በጸሎቱ እንዲመጣ የጠየቀው ድርቅ በሰው ልጆች ላይ ሰቆቃ እንደሚያስከትል ያውቅ ነበር። እስራኤል በአመዛኙ የምትተዳደረው በግብርና ሲሆን የሕዝቡ ሕይወት የተመካው በጠልና በዝናብ ላይ ነበር። ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ድርቅ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል። ሣር ቅጠሉ ይደርቃል፣ ሰብል አይኖርም። ለሥራና ለምግብነት የሚያገለግሉ የቤት እንስሳት ይሞታሉ። አንዳንድ ቤተሰቦችም በረሃብ የመሞት አደጋ ይደቀንባቸዋል። ክፉኛ የሚጎዳው ማን ነው? ተራው ሕዝብ ነው። ቆየት ብሎ አንዲት መበለት እፍኝ ዱቄትና ጥቂት ዘይት ብቻ እንደቀራት ለኤልያስ ነግራዋለች። እርሷና ወንድ ልጅዋ ብዙም ሳይቆዩ በረሃብ እንደሚሞቱ እርግጠኛ ነበረች። (1 ነገሥት 17:​12) ኤልያስ ከዚህ በፊት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ለመጸለይ ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ ላልተዉ ሃብታምም ሆኑ ድሃ አገልጋዮቹ እንደሚያስብላቸው በጽኑ ማመን አስፈልጎት ነበር። ታሪኩ እንደሚያሳየው ኤልያስ የጠበቀው ነገር ሳይፈጸም አልቀረም።​—⁠1 ነገሥት 17:​13-16፤ 18:​3-5

      ከሦስት ዓመታት በኋላ ይሖዋ በቅርቡ ዝናብ እንደሚያዘንብ በተናገረ ጊዜ ኤልያስ ድርቁ እንዲቆም የነበረው ልባዊ ፍላጎት ‘ፊቱን በጉልበቱ መካከል በማድረግ በግምባሩ ተደፍቶ’ በጋለ ስሜት ደጋግሞ ባቀረበው ጸሎት ታይቷል። (1 ነገሥት 18:​42) ይሖዋ ጸሎቱን እንደሰማለት የሚያሳይ ምልክት ለማየት በመፈለግ አገልጋዩን “ወጥተህ ወደ ባሕሩ ተመልከት” በማለት ደጋግሞ አሳስቦታል። (1 ነገሥት 18:​43) በመጨረሻም ላቀረበው ጸሎት ምላሽ ‘ሰማዩ ዝናብ ሲሰጥና ምድሪቱም ፍሬዋን ስታበቅል’ ምን ያህል ደስታ ተሰምቶት ይሆን!​—⁠ያዕቆብ 5:​18

      አንተም ወላጅ ወይም የክርስቲያን ጉባኤ ሽማግሌ ከሆንክ ተግሳጽ በምትሰጥበት ጊዜ ከውስጣዊ ስሜቶችህ ጋር በሐሳብ ትፋጭ ይሆናል። ሆኖም አልፎ አልፎ ተግሳጽ አስፈላጊ መሆኑንና በፍቅር ከተሰጠ ደግሞ ‘የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን እንደሚያፈራ’ በጽኑ በማመን እንዲህ ዓይነቶቹን ሰብዓዊ ስሜቶች ማስተካከል ያስፈልጋል። (ዕብራውያን 12:​11) የይሖዋን ሕጎች መታዘዝ የሚያስገኛቸው ውጤቶች ምንጊዜም ጥሩ ናቸው። ልክ እንደ ኤልያስ ሕጎቹ በተግባር እንዲውሉ ከልባችን እንጸልያለን።

      ኤርምያስ ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ ሥር ድፍረት አሳይቷል

      ከሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ይበልጥ ስለ ግል ስሜቶቹ ብዙ የጻፈው ኤርምያስ ሳይሆን አይቀርም። ወጣት በነበረበት ጊዜ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመቀበል አቅማምቶ ነበር። (ኤርምያስ 1:​6) ሆኖም በከፍተኛ ድፍረት የአምላክን ቃል ማወጁን ቀጥሏል። ያገኘው ውጤት ቢኖር ከንጉሡ ጀምሮ እስከ ተራው ሕዝብ ድረስ የእስራኤላውያን ወገኖቹን የከረረ ተቃውሞ ነው። የደረሰበት ተቃውሞ አንዳንድ ጊዜ እንዲናደድና እንዲያለቅስ አድርጎታል። (ኤርምያስ 9:​3፤ 18:​20-23፤ 20:​7-18) በተለያዩ ጊዜያት ሕዝባዊ ዓመፅ ተነስቶበታል፣ ተደብድቧል፣ በእግር ግንድ ታስሯል፣ እስር ቤት ተጥሏል፣ የግድያ ዛቻ ደርሶበታል እንዲሁም ጭቃ ውስጥ ሰጥሞ እንዲሞት ባዶ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሏል። አንዳንድ ጊዜም ደግሞ የይሖዋ መልእክት ራሱ እንዲጨነቅ አድርጎታል። ቀጥሎ የተናገራቸው ቃላት ይህንን ያሳያሉ:- “አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል።”​—⁠ኤርምያስ 4:​19

      አሁንም ቢሆን የይሖዋን ቃል እንደሚወድ ሲገልጽ “ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ” ብሎ ተናግሯል። (ኤርምያስ 15:​16) የዚያኑ ያህል ደግሞ ያደረበት ስጋት ‘በውኑ እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፣ እንዳልታመነች ውኃ ሆንህብኝ’ ብሎ ወደ ይሖዋ በመጮህ በቀላሉ ከሚደርቅ ጅረት ጋር እንዲያመሳስለው ገፋፍቶታል። (ኤርምያስ 15:​18) የሆነ ሆኖ ይሖዋ እርስ በርስ የሚጋጩበትን ስሜቶቹን ስለተረዳለት ተልዕኮውን መወጣት እንዲችል እርሱን መደገፉን ቀጥሏል።​—⁠ኤርምያስ 15:​20፤ በተጨማሪም 20:​7-9ን ተመልከት።

      አንተም አገልግሎትህን ስታከናውን እንደ ኤርምያስ ተስፋ መቁረጥ ወይም ተቃውሞ ይገጥምሃልን? በይሖዋ ታመን። የእርሱን መመሪያ መከተልህን ቀጥል፤ ይሖዋም ጥረትህን ይባርካል።

      ኢየሱስ እንደኛው ዓይነት ስሜቶች ነበሩት

      በታሪክ ዘመናት ሁሉ ከነበሩት ነቢያት የሚበልጠው ታላቁ ነቢይ የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምንም እንኳ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም ስሜቶቹን አምቆ አልያዘም። ስለ ውስጣዊ ስሜቶቹ ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ስሜቶቹ በፊቱ ላይና ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት በግልጽ ታይተው መሆን አለበት። ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ለሰዎች ‘አዘኔታ አሳይቷል’፤ እንዲሁም በምሳሌዎቹ ውስጥ የሰዎቹን ባሕርያት ለመግለጽ ይህንኑ መግለጫ ተጠቅሟል።​—⁠ማርቆስ 1:​41፤ 6:​34፤ ሉቃስ 10:​33

      ገንዘብ ለዋጮችንና እንስሳትን ከቤተ መቅደሱ ሲያባርር “ይህን ከዚህ ውሰዱ” ባለ ጊዜ ጮክ ብሎ ተናግሮ መሆን አለበት። (ዮሐንስ 2:​14-16) “አይሁንብህ ጌታ ሆይ” ሲል ጴጥሮስ ያቀረበው ሐሳብ “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን” የሚል ኃይለኛ ምላሽ አስከትሎበታል።​—⁠ማቴዎስ 16:​22, 23

      ኢየሱስ ለእርሱ በጣም ቅርብ ለነበሩት ለአንዳንድ ሰዎች ልዩ ፍቅር ነበረው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” እንደነበረ ተገልጿል። (ዮሐንስ 21:​7, 20) በተጨማሪም “ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር” የሚል እናነባለን።​—⁠ዮሐንስ 11:​5

      ኢየሱስ የሐዘን ስሜትም ይሰማው ነበር። የአልዓዛር ድንገተኛ ሞት ስላሳዘነው ‘ኢየሱስ እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:​32-36) ኢየሱስ በአስቆሮቱ ይሁዳ ክህደት የተነሳ የተሰማውን የልብ ሐዘን ሲገልጽ “እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ” የሚለውን መዝሙር መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን አንጀት የሚበላ አገላለጽ ጠቅሷል።​—⁠ዮሐንስ 13:​18፤ መዝሙር 41:​9

      ኢየሱስ ተሰቅሎ ከባድ ስቃይ በተሰማው ጊዜ እንኳ ውስጣዊ ስሜቱን በግልጽ አውጥቷል። ‘ይወደው ለነበረው ደቀ መዝሙር’ እናቱን እንዲንከባከብ በአደራ ሰጠው። (ዮሐንስ 19:​26, 27) ኢየሱስ ከጎኑ ከተሰቀሉት ወንጀለኞች መካከል አንደኛው ንስሐ እንደገባ የሚያሳይ ማስረጃ ባየ ጊዜ በርኅራሄ መንፈስ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። (ሉቃስ 23:​43) “አምላኬ አምላኬ፣ ስለ ምን ተውኸኝ?” ብሎ በጮኸ ጊዜ ስሜቱ በጥልቅ ሲነካ ሊታየን ይችላል። (ማቴዎስ 27:​46) በተጨማሪም “አባት ሆይ፣ ነፍሴን [“መንፈሴን፣” NW] በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” በማለት እያቃሰተ የተናገራቸው ቃላት ያለውን ልባዊ ፍቅርና ትምክህት በግልጽ ያሳያሉ።​—⁠ሉቃስ 23:​46

      ይህ ሁሉ እንዴት ያለ ማጽናኛ ይሰጠናል! “[ኢየሱስ] ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፣ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም።”​—⁠ዕብራውያን 4:​15

      የይሖዋ ትምክህት

      ይሖዋ መልእክተኞቹን ሲመርጥ ባደረገው ምርጫ በፍጹም ተጸጽቶ አያውቅም። ለእርሱ ታማኝ መሆናቸውን ያውቃል። በመሆኑም ፍጹም ያልነበሩ አገልጋዮቹ ያላቸውን ጉድለት በርኅራሄ ችላ ብሎ አልፏል። ሆኖም ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ ይጠብቅባቸው ነበር። በእርሱ እርዳታ ተልዕኳቸውን መፈጸም ችለዋል።

      እኛም ታማኝ በሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ትምክህት ማሳየታችንን እንቀጥል። በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ፍጹማን እንደማንሆን ሁሉ እነሱም ፍጹማን አይደሉም። ቢሆንም ፍቅርና ትኩረት ልናሳያቸው አይገባም ብለን በወንድሞቻችን ላይ መፍረድ የለብንም። ጳውሎስ “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል” በማለት ጽፏል።​—⁠ሮሜ 15:​1፤ ቆላስይስ 3:​13, 14

      የይሖዋ ነቢያት እኛ የሚሰማን ዓይነት ስሜቶች ሁሉ ተሰምቷቸዋል። የሆነ ሆኖ በይሖዋ ተመክተዋል፤ ይሖዋም ደግፏቸዋል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ለደስታ ምክንያት የሆናቸውን በጎ ሕሊና፣ የሱን ሞገስ፣ ድጋፍ የሚሰጧቸው ታማኝ ጓደኞችና እርግጠኛ የወደፊት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 12:​1-3) ‘እንደኛው ዓይነት ስሜት የነበራቸውን’ የጥንቶቹን ነቢያት እምነት በመከተል እኛም በሙሉ ትምክህት ይሖዋን የሙጥኝ ብለን እንያዝ።

  • ዶክተሮች፣ ዳኞችና የይሖዋ ምሥክሮች
    መጠበቂያ ግንብ—1998 | መጋቢት 1
    • ዶክተሮች፣ ዳኞችና የይሖዋ ምሥክሮች

      በመጋቢት 1995 የይሖዋ ምሥክሮች በብራዚል ሁለት ትምህርታዊ ሴሚናሮችን አድርገው ነበር። የሴሚናሮቹ ዓላማ ምን ነበር? ሆስፒታል የገባው ታካሚ የይሖዋ ምሥክር በሚሆንበት ጊዜ ደም ስለማይወስድ የሕክምናና የሕግ ባለሙያዎችን ትብብር ለማግኘት ሲባል ነው።​—⁠ሥራ 15:​29

      በአንዳንድ አጋጣሚዎች ዶክተሮች ምሥክር የሆኑ ታካሚዎችን ፍላጎት ችላ በማለት አስገድደው ደም ለመስጠት የሚያስችላቸውን የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት መሞከራቸው የሚያሳዝን ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ምሥክሮቹ ራሳቸውን ለመጠበቅ ያለውን ሕጋዊ መንገድ ሁሉ ተጠቅመዋል። የሆነ ሆኖ ከግጭት ይልቅ ትብብር ይመርጣሉ። በመሆኑም ተመሳሳይ ዓይነት ደም በመስጠት ከማከም ይልቅ ብዙ ዓይነት አማራጮች እንዳሉና የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን አማራጮች በደስታ እንደሚቀበሉ ትምህርታዊ ሴሚናሮቹ አጉልተዋል።a

      የሳኦ ፓውሎ የሕክምና ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ላይ ድሮውንም የምሥክሮቹን አቋም ደግፎ ነበር። በጥር 1995 ምክር ቤቱ፣ ዶክተሩ ባዘዘው ሕክምና ላይ ተቃውሞ ካለ ታካሚው ሕክምናውን ላለመቀበልና ሌላ ዶክተር ለመምረጥ ነፃነት አለው በማለት ወስኖ ነበር።

      በአሁኑ ወቅት በታካሚው ፍላጎት መሠረት ያለ ደም ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕክምና ባለሙያዎች በብራዚል የሕክምና ማኅበረሰብ ውስጥ መኖራቸው የሚያስመሰግን ነው። በመጋቢት 1995 ከተካሄዱት ትምህርታዊ ሴሚናሮች ወዲህ በብራዚል ውስጥ በዶክተሮች፣ በዳኞችና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል። በብራዚል የሚታተመው አምቢቱ ኦስፒታላር የተባለው የሕክምና መጽሔት የይሖዋ ምሥክሮች ደምን በተመለከተ ያላቸው አቋም እንዲከበርላቸው በጽኑ የሚደግፍ ርዕስ በ1997 አሳትሟል። የሪዮ ዲ ጄኔሮና ሳኦ ፓውሎ ግዛቶች የክልሉ የሕክምና ምክር ቤት ባሰፈረው መሠረት “ዶክተሩ የበሽተኛውን ሕይወት ለማትረፍ ያለበት ኃላፊነት የታካሚውን የሕክምና ምርጫ ለማስከበር ካለበት ኃላፊነት የበለጠ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም።” በአሁኑ ጊዜ ይህ በሰፊው የታወቀ ሆኗል።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ