የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ኤልያስ እውነተኛውን አምላክ አስከበረ
በእስራኤል ውስጥ በጥብቅ ይፈለግ የነበረ ሰው ነው። በንጉሡ እጅ ከወደቀ ያለአንዳች ጥርጥር ይገደላል። ይህ እየታደነ የነበረው ሰው ማን ነው? የይሖዋ ነቢይ ኤልያስ ነው።
ንጉሡ አክዓብና አረማዊ የሆነችው ሚስቱ ኤልዛቤል በእስራኤል ውስጥ የበኣል አምልኮ እንዲስፋፋ አድርገው ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ምድሪቱ በድርቅ እንድትመታ ካደረገ እነሆ አራተኛ ዓመቱን ይዟል። በጉዳዩ ክፉኛ ተናድዳ የነበረችው ኤልዛቤል የይሖዋን ነቢያት ለማስገደል የቆረጠች ሲሆን ባልዋ አክዓብ ደግሞ ይበልጥ ትኩረት ያደረገው ኤልያስን ለማስገደል ነው። ከሦስት ዓመታት በፊት፣ ለአክዓብ ‘በእኔ ትእዛዝ ካልሆነ በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም!’ ብሎ የተናገረው ኤልያስ ነበር። (1 ነገሥት 17:1) በተናገረው መሠረት ድርቁ ቀጥሎ ነበር።
በዚህ አደገኛ ሁኔታ ሥር እያለ ይሖዋ ኤልያስን “ሂድ፣ ለአክዓብ ተገለጥ፣ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ” ብሎት ነበር። ለሕይወቱ በጣም አስጊ ቢሆንም ኤልያስ የይሖዋን ትእዛዝ አክብሯል።—1 ነገሥት 18:1, 2
ሁለት ባላንጣዎች ተገናኙ
አክዓብ ኤልያስን ባገኘው ጊዜ “እስራኤልን የምትገለባብጥ [“በእስራኤል ላይ ይህን ከባድ ችግር የፈጠርህ፣” የ1980 ትርጉም ] አንተ ነህን?” ብሎ ጠየቀው። “እስራኤልን የምትገለባብጡ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፣ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም” በማለት ኤልያስ በድፍረት መለሰ። በመቀጠልም “አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፣ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት” ጨምሮ የእስራኤል ሕዝብ በአጠቃላይ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበሰቡ ኤልያስ ጥሪ አስተላለፈ። ከዚያም ሕዝቡን እንዲህ በማለት ተናገራቸው:- “እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ?a እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ።”—1 ነገሥት 18:17-21
ሕዝቡ ምንም መልስ አልሰጠም። ምናልባትም ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ አለማቅረባቸውን በማሰብ ጥፋተኝነት ተሰምቷቸው ይሆናል። (ዘጸአት 20:4, 5) ወይም ሕሊናቸው ከመደንዘዙ የተነሳ ለሁለቱም ማለትም ለይሖዋም ለበኣልም ታማኝነት ለማሳየት መሞከራቸው ምንም ኃጢአት እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ኤልያስ የተሰበሰበውን ሕዝብ ሁለት ወይፈኖች፣ አንደኛውን ለበኣል ነቢያት ሁለተኛውን ደግሞ ለእርሱ እንዲያመጡ አዘዘ። ሁለቱም ወይፈኖች መሥዋዕት ሆነው ሊቀርቡ የተዘጋጁ ሲሆን በእሳት መጠቀም ግን አልተፈቀደም ነበር። ስለዚህ ኤልያስ እንዲህ አላቸው:- “እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፣ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፣ እርሱ አምላክ ይሁን።”—1 ነገሥት 18:23, 24
ይሖዋ ተከበረ
የበኣል ነቢያት “በሠሩት መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ” ጀመር። ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ “በኣል ሆይ፣ ስማን” እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። በኣል ግን ምንም መልስ አልሰጠም። (1 ነገሥት 18:26) በዚህን ጊዜ ኤልያስ “አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ” በማለት ያላግጥባቸው ጀመር። (1 ነገሥት 18:27) የበኣል አምላኪዎች ሰውነታቸውን በቢላዋና በጩቤ እንኳ ሳይቀር ይተለትሉ ጀመር። ይህ ልማድ የአማልክቶቻቸውን ርኅራሄ ለማነሳሳት አብዛኛውን ጊዜ አረማውያን የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው።b—1 ነገሥት 18:28
አሁን የቀትሩ ጊዜ አልፎአል፤ ሆኖም የበኣል አምላኪዎች ‘ትንቢት መናገራቸውን’ እንደቀጠሉ ነው። ይህ ስንኝ በዚህ አገባቡ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ስሜት ማሸብሸባቸውን እንደቀጠሉ የሚያሳይ ነው። የቀትሩ ጊዜ ከተገባደደ በኋላ ኤልያስ ሕዝቡን ሁሉ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። ኤልያስ የይሖዋን መሠዊያ መልሶ ሲሠራ፣ በመሠዊያው ዙሪያ ጉድጓድ ሲቆፍር፣ ወይፈኑን በየብልቱ ሲቆራርጥና በመሠዊያው ላይ እንዲቃጠል እንጨት ረብርቦ የወይፈኑን ብልቶች ሲያስቀምጥ ሁሉም በትኩረት ተመለከቱት። ከዚህ በኋላ ወይፈኑ፣ መሠዊያውና እንጨቱ ሙሉ በሙሉ በውኃ ከመረስረሱም በላይ ምንም እንኳ በጊዜው ድርቅ የነበረ ቢሆንም ዙሪያውን ያለው ጉድጓድ ከሌላ ቦታ በተገኘ ውኃ ተሞላ (ከሜድትራኒያን ባሕር የተገኘ ውኃ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም)። ቀጥሎም ኤልያስ ወደ ይሖዋ እንዲህ ብሎ ጸለየ:- “አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፣ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አንተ፣ አቤቱ፣ አምላክ እንደ ሆንህ፣ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፣ አቤቱ፣ ስማኝ አለ።”—1 ነገሥት 18:29-37
በቅጽበት እሳት ከሰማይ ወርዶ “የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፣ በጉድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።” ይህን ይመለከቱ የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ በግንባራቸው ተደፍተው “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው፣ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው” አሉ። በኤልያስ ትእዛዝ አማካኝነት የበኣል ነቢያት ተይዘው ወደ ቂሶን ወንዝ ከተወሰዱ በኋላ ተገደሉ።—1 ነገሥት 18:38-40
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ኤልያስ ከሰው የተለየ ድፍረት ያሳየ ሊመስል ይችላል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ “ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ” በማለት ያረጋግጥልናል። (ያዕቆብ 5:17) ሙሉ በሙሉ ከፍርሃትና ከጭንቀት ነፃ የሆነ ሰው አልነበረም። ለምሳሌ ያህል የበኣል ነቢያት በመገደላቸው ምክንያት ኤልዛቤል እንደምትበቀለው በዛተችበት ጊዜ ኤልያስ ሸሽቶ ከመሄዱም በላይ ወደ ይሖዋ በመጸለይ “ይበቃኛል አሁንም፣ አቤቱ . . . ነፍሴን ውሰድ” በማለት ተማጽኗል።—1 ነገሥት 19:4
ይሖዋ የኤልያስን ነፍስ በሞት አልወሰደም። ከዚህ ይልቅ በአዘኔታ ተገፋፍቶ ድጋፍ ሰጥቶታል። (1 ነገሥት 19:5-8) በአሁኑ ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ምናልባት በተቃውሞ ምክንያት ሊሆን ይችላል፣ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ይሖዋ ተመሳሳይ የሆነ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ። በእርግጥም የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ከጸለዩ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል ስለሚሰጣቸው” ‘በሁሉም አቅጣጫ ቢገፉም’ እንኳ ‘መፈናፈኛ እስከማጣት አይደርሱም’። በዚህ መንገድ ልክ እንደ ኤልያስ ጸንተው እንዲቆሙ ድጋፍ ያገኛሉ።—2 ቆሮንቶስ 4:7, 8 NW
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንድ ምሁራን ኤልያስ በተዘዋዋሪ እየተናገረ የነበረው የበኣል አምላኪዎች ስለሚያከናውኑት ሃይማኖታዊ ጭፈራ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ። “ማንከስ” የሚለው ቃል በ1 ነገሥት 18:26 ላይ የበኣል ነቢያትን ጭፈራ ለመግለጽ በተመሳሳይ መንገድ ተሠርቶበታል።
b አንዳንዶች የራስን ሰውነት ሆን ብሎ መጉዳት ሰውን መሥዋዕት አድርጎ ከማቅረብ ልማድ ጋር ዝምድና እንዳለው ይገልጻሉ። እነዚህን ተግባሮች የሚፈጽሙት አካላዊ ሥቃይ ወይም ደምን ማፍሰስ የአንድን አምላክ ሞገስ ለማስገኘት ያስችላሉ ተብሎ ይታሰብ ስለነበር ነው።