የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርት ላከ
ወቅቱ 32 እዘአ የፀደይ ወራት ነበር። ኢየሱስ ሊገደል የቀረው ስድስት ወር ብቻ ነበር። ስለዚህ የስብከቱን ሥራ ለማፋጠንና ለአንዳንድ ተከታዮቹ ተጨማሪ ስልጠና ለመስጠት ኢየሱስ 70 ደቀ መዛሙርት መረጠና “ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው።”—ሉቃስ 10:1a
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘በፊቱ የላካቸው’ በኋላ እርሱ ራሱ ወደዚያ በሚሄድበት ጊዜ ሰዎቹ መሲሑን መደገፋቸውን ወይም መቃወማቸውን በተመለከተ በፍጥነት እንዲወስኑ ለማስቻል ነው። ሆኖም “ሁለት ሁለት” አድርጎ የላካቸው ለምንድን ነው? ተቃውሞ በሚያጋጥማቸው ጊዜ አንዱ ለሌላው የብርታት ምንጭ መሆን እንዲችሉ እንደሆነ ግልጽ ነው።
የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ አጣዳፊ መሆኑን ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሲገልጽ “መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 10:2) መከር በሚሰበሰብበት ወቅት ጊዜ ማባከን ጠቃሚ የሆነ ሰብል እንዲባክን ስለሚያደርግ ከመከር ጋር ማመሳሰሉ ተገቢ ነበር። በተመሳሳይም ደቀ መዛሙርቱ የስብከት ሥራቸውን ችላ ቢሉ ውድ የሆነው የሰው ሕይወት ሊጠፋ ይችላል!—ሕዝቅኤል 33:6
ትኩረታቸው ያልተከፋፈለ አገልጋዮች
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተጨማሪ መመሪያ ሲሰጥ “ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 10:4) አንድ መንገደኛ ከረጢትና ምግብ ብቻ ሳይሆን የጫማው ሶል ሊያልቅና ማሰሪያውም ሊበጠስ ስለሚችል አንድ ትርፍ ጫማም መያዙ የተለመደ ነበር። ሆኖም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለእነዚህ ዓይነት ነገሮች መጨነቅ አልነበረባቸውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል ባላቸው መሰል እስራኤላውያን ተጠቅሞ እንደሚንከባከባቸው ማመን ነበረባቸው።
ታዲያ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሰላምታ ለመስጠት ማንንም ማቀፍ እንደሌለባቸው የነገራቸው ለምንድን ነው? የወዳጅነት መንፈስ የሌላቸው እንዲያውም ክፉ መሆን ሊኖርባቸው ነውን? በጭራሽ! ሰላምታ ለመስጠት ማቀፍ የሚል ትርጉም ያለው ኤስፓዞማይ የሚለው የግሪክኛ ቃል አክብሮት ባለው መንገድ “እንደምን አደርክ” ወይም “እንደምን ዋልክ” ከማለት የበለጠ ሊሆን ይችላል። ባሕላዊ የሆነውን መሳሳም፣ መተቃቀፍና ሁለት ጓደኛሞች ሲገናኙ የሚከተለውን ረዥም ጭውውት ሊያጠቃልልም ይችላል። አንድ ተንታኝ ስለዚህ ሲገልጹ “በሩቅ ምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች ሰላምታ የሚለዋወጡት እኛ እንደምናደርገው በትንሹ አንገት ሰበር በማድረግ ወይም በመጨባበጥ ሳይሆን ደጋግሞ በመተቃቀፍና በመስገድ እንዲሁም መሬት ላይ በመደፋት ጭምር የሚደረግ ነበር። ይህ ሁሉ ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ ነበር” ብለዋል። (ከ2 ነገሥት 4:29 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም እነዚህ ድርጊቶች ምንም እንኳ ባሕላዊ ቢሆኑም አላስፈላጊ የሆኑ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን እንዲያስወግዱ ኢየሱስ ተከታዮቹን ረድቷቸዋል።
በመጨረሻም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ስትገቡ ጥሩ አቀባበል ከተደረገላችሁ “በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ” ብሏቸው ነበር። ሆኖም ወደ አንድ ከተማ በሚገቡበት ጊዜ ጥሩ አቀባበል ካልተደረገላቸው ‘ወደ አደባባይዋ ወጥተው ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን’ ማለት ነበረባቸው። (ሉቃስ 10:7, 10, 11) በእግራቸው ላይ ያለውን ትቢያ ማራገፋቸው ወይም መጥረጋቸው ደቀ መዛሙርቱ መልእክቱን ያልተቀበለውን ቤት ወይም ከተማ በሰላም ትተው መሄዳቸውንና በመጨረሻ ላይ ከአምላክ ለሚደርስባቸው ነገር አሳልፈው መስጠታቸውን የሚያመለክት ነው። ሆኖም የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት በደግነት ተቀብለው ያስተናገዱ በረከት ለማግኘት ሊጠባበቁ ይችላሉ። በሌላ ጊዜ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል:- “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፣ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋው አይጠፋበትም።”—ማቴዎስ 10:40, 42
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
በአሁኑ ጊዜ የአምላክን መንግሥት ምስራች የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማፍራት ተልዕኮው ከ5,000,000 በሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ እየተሠራ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የሚያሰራጩት መልእክት አጣዳፊ መሆኑን ተገንዝበዋል። ስለዚህ ጊዜያቸውን በአግባቡ ይጠቀሙበታል። በጣም አስፈላጊ ለሆነው ሥራቸው ሙሉ ትኩረት እንዳይሰጡ የሚከለክሏቸውን ማዘናጊያዎች ያስወግዳሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ ልባዊ ስሜት ለማሳየት ይጥራሉ። የሆነ ሆኖ በማያስፈልግ ወሬ ራሳቸውን አያስጠምዱም፣ ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመከራከር ወይም ዓለም ፍትሕ ለማስፈን በሚያደርገው ከንቱ ጥረት ራሳቸውን አያስገቡም። (ዮሐንስ 17:16) ከዚህ ይልቅ ውይይታቸው የሚያተኩረው ለዘለቄታው የሰው ልጆችን ችግር በሚያስወግደው ብቸኛው የአምላክ መንግሥት ላይ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ጥንድ ጥንድ ሆነው ሲያገለግሉ ይታያሉ። እያንዳንዳቸው ለየብቻቸው ሆነው ቢያገለግሉ ኖሮ የበለጠ ማከናወን አይቻልም ነበር? ምናልባት ይቻል ይሆናል። የሆነ ሆኖ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ከእምነት ጓደኞቻቸው ጋር ጎን ለጎን ሆነው የማገልገላቸውን ጥቅም ይገነዘባሉ። እንዲህ ማድረጋቸው አደገኛ በሆኑ አካባቢዎች በሚመሰክሩበት ጊዜ ጥበቃ ያስገኝላቸዋል። ከአገልግሎት ጓደኛ ጋር ሆኖ ማገልገል ይበልጥ ተሞክሮ ያላቸው የምሥራቹ አስፋፊዎች ካካበቱት ችሎታ አዳዲሶች ጥቅም እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። በእርግጥ አንዳቸው ለሌላው የማበረታቻ ምንጭ መሆን ይችላሉ።—ምሳሌ 27:17
በዚህ “የመጨረሻው ቀን” እየተከናወነ ካለው ከማንኛውም ሥራ ይበልጥ አጣዳፊው የስብከቱ ሥራ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) የይሖዋ ምሥክሮች ‘በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብረው’ የሚሠሩበት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ድጋፍ በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው።—ፊልጵስዩስ 1:27
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችና ጥንታዊ የግሪክኛ ጽሑፎች ኢየሱስ “ሰባ ሁለት” ደቀ መዛሙርት እንደላከ ይናገራሉ። ሆኖም “ሰባ” ልኳል ብሎ ለመናገር የሚያበቃ በርካታ የብራና ጽሑፎች ማስረጃ አለ። ይህ ልዩነት ከዋናው ቁምነገር ማለትም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹን ለስብከት መላኩን ከሚናገረው ትኩረታችንን ሊያዞር አይገባም።