የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 5/1 ገጽ 5-7
  • ይሖዋ ማን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ማን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የስሙ አስፈላጊነት
  • የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት
  • የሁሉም ብሔራት አምላክ
  • ይሖዋን ከማወቅ የሚገኙ ጥቅሞች
  • ይሖዋ ማን ነው?
    ይሖዋ ማን ነው?
  • እውነተኛው አምላክ ማን ነው?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • ብቸኛውን እውነተኛ አምላክ ይሖዋን ከፍ ከፍ አድርገው
    እውነተኛውን አንድ አምላክ አምልክ
  • የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 5/1 ገጽ 5-7

ይሖዋ ማን ነው?

ይሖዋ ከታማኝ አገልጋዮቹ ለአንዱ “ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም” ብሎት ነበር። (ዘጸአት 33:​20) ‘አምላክ መንፈስ’ በመሆኑ ሰዎች በሰብዓዊ ዓይኖቻቸው ሊያዩት አይችሉም። (ዮሐንስ 4:​24) ቀትር ላይ ፀሐይን በቀጥታ ለማየት መሞከር ዓይናችንን እንደሚጎዳው ሁሉ፣ አስደናቂዋን ፀሐያችንን ብቻ ሳይሆን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሌሎች ፀሐያማ አካላትን የፈጠረውንና ከፍተኛ የኃይል አመንጪ የሆነውን አምላክ ለማየት መሞከራችን አስከፊ ጥፋት ያስከትልብናል።

ደግነቱ ስለ አምላክ ለማወቅ የግድ እሱን ማየት አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ ያንን አስደናቂ ጥቅል ማለትም ምድርን ያዘጋጀው ማን እንደሆነ ይነግረናል፤ ባሕርያቱንም ይገልጽልናል። ስለዚህ ሕይወት ስለ ሰጠንና በሰጠን ሕይወት እንድንደሰት ውብ መኖሪያ ስላዘጋጀልን አባት ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመራችን ተገቢ ነው።

የስሙ አስፈላጊነት

ዛሬ ብዙዎች የተለያዩ ስሞች ምን ትርጉም እንዳላቸው አያውቁ ይሆናል፤ ሆኖም ሁሉም ስሞች ትርጉም አላቸው። ለምሳሌ ያህል በእንግሊዝኛ በብዛት የሚታወቀው ዴቪድ (ዳዊት) የሚለው ስም “የተወደደ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ነው። ይሖዋ የሚለው የፈጣሪ ስምም ትርጉም አለው። ትርጉሙ ምንድን ነው? በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ በዕብራይስጥ መለኮታዊው ስም የ-ሐ-ወ-ሐ (YHWH) በሚሉት አራት ፊደላት የተጻፈ ሲሆን በዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ወደ 7,000 ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ይህ መለኮታዊ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ ዓላማዎቹን ለማሳካት ሲል ጥበብ ባለበት መንገድ የፈለገውን እንደሚሆን የሚያመለክት ሐሳብ አለው። እሱ ፈጣሪ፣ ፈራጅ፣ አዳኝ፣ የሕይወት ጠባቂ ስለሆነ የገባውን ቃል ለመፈጸም ይችላል። ከዚህም በላይ በዕብራይስጥ ይሖዋ የሚለው ስም በሂደት ላይ ያለን አንድ ድርጊት ለማመልከትም ተሠርቶበታል። አዎን፣ አሁንም ቢሆን ይሖዋ ዓላማዎቹን ለማሳካት ሲል ማንኛውንም ነገር ያደርጋል። እሱ ሕያው አምላክ ነው!

የይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት

መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪን “እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል” በማለት ይገልጸዋል። (ዘጸአት 34:​6, 7) “ቸርነት” [“ፍቅራዊ ደግነት፣” NW] ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ልዩ ትርጉም አለው። ቃሉ የአንድ ነገር ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ከዚያ ነገር ጋር ራሱን በፍቅር የሚያጣብቅን ደግነት ያመለክታል። “ታማኝ ፍቅር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። የይሖዋ ደግነት ራሱን ከፍጥረቶቹ ጋር በፍቅር ያጣብቃል እንዲሁም አስደናቂ ዓለማዎቹን ከግብ ያደርሳል። ሕይወት ከሰጠህ አምላክ የሚመጣውን እንዲህ ያለውን ፍቅር በአድናቆት አትመለከትምን?

ይሖዋ ለቁጣ የዘገየና ስህተቶቻችንን ይቅር ለማለት የፈጠነ ነው። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ካለው አካል ጋር መቀራረብ ያስደስታል። ያ ማለት ግን ጥፋትን ችላ ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም። “እኔ እግዚአብሔር ፍርድን የምወድድ ስርቆትንና በደልን የምጠላ ነኝ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 61:​8) የፍትሕ አምላክ እንደመሆኑ መጠን በክፋታቸው የሚቀጥሉ እምቢተኛ ኃጢአተኞችን ለዘላለም አይታገሥም። ስለዚህ ይሖዋ በራሱ ጊዜ በዓለማችን ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እንደሚያስወግደው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ስቃይና መከራ የሚደርስባቸውን ሰዎች ችላ አይልም።

በፍቅርና በፍትሕ መካከል ፍጹም የሆነ ሚዛን እንዲኖር ማድረግ ቀላል አይደለም። ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ በሚያጠፉበት ጊዜ መቼ፣ እንዴትና እስከ ምን ድረስ ማረም እንደሚገባህ መወሰኑ አስቸጋሪ ሆኖብህ ያውቃል? በፍትሕና በፍቅራዊ ርኅራኄ መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥበብ ይጠይቃል። ይሖዋ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ይህንን ባሕርይ በከፍተኛ መጠን ያሳያል። (ሮሜ 11:​33-36) በእርግጥም የፈጣሪን ጥበብ በማንኛውም ቦታ ለማየት ይቻላል፤ ለምሳሌ ያህል በዙሪያችን ባሉት ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች ጥበቡ ይታያል።​—⁠መዝሙር 104:​24፤ ምሳሌ 3:​19

ይሁን እንጂ ጥበብ ያለው መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም። ፈጣሪ ፈቃዱን ለመፈጸም ኃይልም ያስፈልገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንስታችሁ ተመልከቱ፣ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።” (ኢሳይያስ 40:​26) ይሖዋ “በኃይሉ ብዛት” አማካኝነት ነገሮችን ያስፈጽማል። እንዲህ ያለው ባሕሪው ወደ እሱ አይስብህም?

የሁሉም ብሔራት አምላክ

‘ይሁን እንጂ ይሖዋ “የብሉይ ኪዳን” አምላክ ማለትም የጥንት እስራኤላውያን አምላክ አይደለምን?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን ራሱን መግለጡ እውነት ነው። ይሁንና የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ጥንድ በመፍጠሩ ምክንያት ይሖዋ ‘በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ . . . ስሙን የሚያገኝበት’ አምላክ ሆኗል። (ኤፌሶን 3:​15 የ1980 ትርጉም) የቀድሞ አባቶችህን ማክበር ተገቢ ነው ብለህ የምታስብ ከሆነ ዛሬ በምድር ላይ ለሚገኙ የዘር ግንዶች ሁሉ ሥረ መሠረትና ለሁላችንም የቀድሞ አባት ለሆነው ለመጀመሪያው ሰው ሕይወትን ለሰጠው መታዘዝ ተገቢ አይሆንምን?

የሰው ልጅ ፈጣሪ አርቆ የማያስብ አይደለም። እርግጥ በአንድ ወቅት ከእስራኤል ብሔር ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና ነበረው። ይሁን እንጂ ያኔም እንኳ ቢሆን ስሙን የጠሩትን ሁሉ እጁን ዘርግቶ ተቀብሏቸዋል። አንድ ጠቢብ የእስራኤል ንጉሥ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል:- “ከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ታላቁን ስምህን፣ . . . ሰምቶ ስለ ስምህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፣ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፣ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፣ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፣ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።” (1 ነገሥት 8:​41-43) አሁንም ቢሆን ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች ይሖዋን ሊያውቁና ከእርሱም ጋር ትርጉም ያለው ዝምድና ሊመሠርቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ አንተን የሚነካህ እንዴት ነው?

ይሖዋን ከማወቅ የሚገኙ ጥቅሞች

ቀደም ሲል በነበረው ርዕስ ሥር ወደ ተጠቀሰው ምሳሌ ስንመለስ በሚያምር መጠቅለያ የተጠቀለለ ስጦታ ቢደርስህ ምንን አስመልክቶ እንደተሰጠህ ለማወቅ እንደምትፈልግ የተረጋገጠ ነው። አጠቃቀሙና ሊደረግለት የሚገባው ጥንቃቄ ምንድን ነው? በተመሳሳይም አምላክ ምድርን ሲያዘጋጅልን በአእምሮው ይዞት የነበረውን ነገር ለማወቅ እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣” ለሰዎች ‘መኖሪያ ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን እንዳልፈጠራት’ ይናገራል።​—⁠ኢሳይያስ 45:​18

ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ለፈጣሪ ስጦታ ቅንጣት ታህል እንኳ አሳቢነት አያሳዩም። ምድርን በማበላሸት ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ ይሖዋን ያሳዝነዋል። ቢሆንም ይሖዋ ከስሙ ጋር በሚስማማ መንገድ ለሰውና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ወደ ኋላ አይልም። (መዝሙር 115:​16፤ ራእይ 11:​18) ምድርን በማደስ የእሱ ታዛዥ ልጆች ለመሆን ለሚፈልጉ እንደ ርስት አድርጎ ይሰጣቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 5:​5

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ይህ እንዴት እንደሚፈጸም ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:​3, 4) ከዚያ በኋላ ማንም ሰው የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ ምክንያት የሐዘን እንባ አያፈስም። ማንም ሰው ተስፋ በመቁረጡ ምክንያት ለእርዳታ አይጮኽም ወይም ገዳይ በሆኑ በሽታዎች አይሰቃይም። ሌላው ቀርቶ ‘ሞት ይሻራል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:​26፤ ኢሳይያስ 25:​8፤ 33:​24) ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ሲፈጥር ምን ዓይነት ሕይወት እንድናገኝ ይፈልግ እንደነበር ይህ መግለጫ ያስረዳል።

በአሁኑ ጊዜም እነዚህ ገነታዊ ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ በይሖዋ አምላኪዎች ዘንድ ማየት ትችላለህ። እንዲህ ይላቸዋል:- “ታዳጊህ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።” (ኢሳይያስ 48:​17) ይሖዋ እኛን ልጆቹን ከሁሉ በተሻለው መንገድ እንድንኖር የሚያስተምር ደግ አባት ነው። መመሪያዎቹ ለሰዎች አላስፈላጊ የሆኑ ገደቦች ሳይሆኑ ፍቅራዊ ጥበቃን የሚሰጡ ናቸው። “ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ተብሎ በተጻፈው መሠረት የእሱን መመሪያዎች መከተል እውነተኛ ነፃነትና ደስታ ያስገኛል። (2 ቆሮንቶስ 3:​17) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍረው የሚገኙትን መመሪያዎች በመከተል ገዥነቱን የሚቀበሉ ሰዎች ወደፊት መላው የሰው ዘር ዓለም የሚኖረውን የአእምሮ ሰላም በአሁኑ ጊዜ አግኝተዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​7

ይሖዋ እንዴት ያለ ደግ አባት ነው! ከእነዚህ ሁሉ ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች በስተጀርባ ስላለው አካል የበለጠ ለማወቅ ፈቃደኛ ነህን? ለማወቅ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች አሁን እንኳ የሚያገኙት ጥቅም በዋጋ የማይተመን ነው። ወደፊት ደግሞ ዘላለማዊ በረከቶች ያገኛሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥንታዊ በሆኑ በርካታ ቤተ ክርስቲያኖች ግድግዳዎች ላይ መለኮታዊው ስም በአራት የዕብራይስጥ ፊደላት ተጽፎ ይታያል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ