ለምናፈቅራቸው ሰዎች ቅድመ ዝግጅት ማድረግ
አሳዛኝ የሆነው የአኒ ታሪክ በቅርቡ በአንድ የአፍሪካ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል። የአኒ ባል ነጋዴ ነበር። 15 መኪናዎች፣ በባንክ የተቀመጠ በጣም ብዙ ገንዘብ፣ ወደ 4,000 የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ጥሬ ገንዘብ፣ አንድ ሱቅ፣ አንድ ቡና ቤትና ሦስት መኝታ ክፍል ያለው ቤት ትቶ በ1995 ሞተ። ሆኖም የሞተው ሳይናዘዝ ነበር።
የባልዋ ወንድም ንብረቱንና ገንዘቡን ከመውረሱም በላይ እርስዋንና ስድስት ልጆችዋን ከቤታቸው አባረራቸው። ከፍተኛ ችግር ላይ የወደቀችው አኒ ስድስት ልጆችዋን ይዛ ከወንድሟ ጋር መኖር ጀመረች። የትምህርት ቤት ክፍያና የደንብ ልብስ መግዣ ገንዘብ ስላልነበረ አራቱ ልጆች ከትምህርት ቤት ለመውጣት ተገደዋል።
አኒ ለአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤት አለች። ፍርድ ቤቱም አንድ መኪና ጨምሮ አንዳንድ ንብረቶች እንዲመለስላት ወሰነ። ሆኖም ምንም ነገር አልተመለሰላትም። የባልዋ ወንድም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዲያከብር ለማስገደድ እንደገና ፍርድ ቤት ሄዳ ትእዛዝ ማምጣት ነበረባት።
ስለ ሞት ማሰብ ለምን አስፈለገ?
አንድ የቤተሰብ ራስ በድንገት ልሞት እችል ይሆናል ብሎ በማሰብ ቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ ሲቀር ምን ነገር ሊከሰት እንደሚችል የአኒ ታሪክ ያሳያል። ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ‘ገንዘባቸውን ለሌሎች ትተው’ ይሄዳሉ። (መዝሙር 49:10) ከዚህም በተጨማሪ የሞቱ ሰዎች በንብረታቸው ላይ የሚደረገውን ነገር መቆጣጠር አይችሉም። (መክብብ 9:5, 10) አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በንብረቱ ላይ የመወሰን መብት እንዲኖረው ከፈለገ ከመሞቱ በፊት ነገሮችን ማስተካከል አለበት።
ምንም እንኳ ባልተጠበቀ ሁኔታ ልንሞት እንደምንችል ሁላችንም ብናውቅም ብዙ ሰዎች በሕይወት ለሚቀሩት የሚያፈቅሩዋቸው ሰዎች ቅድመ ዝግጅት ሳያደርጉ ይቀራሉ። በዚህ ርዕስ ስር ትኩረት የምናደርገው በአፍሪካ ውስጥ አንዳንድ ጎሳዎች በሚከተሉት ባሕል ላይ ቢሆንም ተመሳሳይ ችግሮች በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ይኖራሉ።
ድንገት ልሞት እችላለሁ ብሎ በማሰብ ንብረት አስቀድሞ መናዘዝ ወይም አንዳንድ ሕጋዊ ጉዳዮችን ማስተካከል በግል የሚወሰን ጉዳይ ነው። (ገላትያ 6:5) ሆኖም አንድ ሰው ‘በሕይወት እያለ ሚስቱንና ልጆቹን የሚንከባከብና በጥሩ ሁኔታ የሚይዝ ሰው ምናልባት ብሞት በሚል የሆነ ዝግጅት የማያደርገው ለምንድን ነው?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። ለዚህ ዋናው ምክንያት አብዛኞቻችን እንኳንስ እሞት ይሆናል ብለን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይቅርና እሞታለሁ የሚለው ሐሳቡ ራሱ ወደ አእምሮአችን እንዲመጣ አለመፈለጋችን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁምና። ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና’ ብሎ ስለሚናገር የምንሞትበትን ቀን አስቀድመን ማወቅ አንችልም።—ያዕቆብ 4:14
ድንገተኛ ሞት ሊከሰት ይችላል ብሎ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው። በሕይወት ለቀሩት ፍቅራዊ አሳቢነትንም ያሳያል። ጉዳዮቻችንን እኛው ራሳችን ካላመቻቸን ሌሎች ጣልቃ ይገቡብናል። ምናልባትም ከዚህ በፊት በጭራሽ የማናውቃቸው ሰዎች ስለ ንብረቶቻችንና የቀብር ሥነ ሥርዓት ዝግጅቶቻችን ውሳኔ ያደርጉልን ይሆናል። በአንዳንድ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ገንዘባችንንና ንብረታችንን ማን መውረስ እንዳለበት መንግሥት ይወስናል። በሌሎች አገሮች ቤተዘመድ ይወስናል። እነዚህ ውሳኔዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በቤተዘመድ መካከል ወደ ቂም በቀል የሚመሩ ቅራኔዎችን ይፈጥራሉ። ከዚህም በላይ ሌሎች የወሰኑት ውሳኔ እኛ ከምንመኘው ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል።
አግባብ ባልሆነ መንገድ ንብረት መውሰድ
ባልዋ በሚሞትበት ጊዜ በጣም የምትቸገረው ሚስትየዋ ነች። የትዳር ጓደኛዋን በማጣትዋ የደረሰባት ሐዘን ሳያንሳት ብዙውን ጊዜ አግባብ ባልሆነ መንገድ ንብረቷንም ትቀማለች። ይህ ጉዳይ ቀደም ሲል በተጠቀሰው በአኒ ሁኔታ ተገልጿል። ለንብረት ዝርፊያው አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ በባሕሉ ውስጥ ለሚስቶች የሚሰጠው ቦታ ነው። በአንዳንድ ባሕሎች የሰውየው ሚስት የእርሱ ቤተሰብ ክፍል ተደርጋ አትታይም። በሆነ ጊዜ ወደ ቤቷ እንደምትመለስ ወይም ከሌላ ቤተሰብ ባል እንደምታገባ ስለሚታሰብ እንደ ባዕድ ትቆጠራለች። ከዚህ በተቃራኒ በአንዳንድ ባሕሎች የሰውየው ወንድሞች፣ እህቶችና ወላጆች ምን ጊዜም ከእርሱ ጋር ናቸው የሚል አመለካከት አላቸው። ቤተሰቦቹ እርሱ ከሞተ የእርሱ ንብረት የሚስቱ ወይም የልጆቹ ሳይሆን የእኛ ነው ብለው ያምናሉ።
የሚያደርጉትን ነገር ለሚስቶቻቸው የማያማክሩ ባሎች ይህን ዓይነት አስተሳሰብ ያበረታታሉ። ማይክ ስለ ንግድ ሥራው የሚወያየው ከወንድሞቹ ጋር ብቻ ነበር። ወንድሞቹ ያለውን ንብረት ሁሉ የሚያውቁ ሲሆን ሚስቱ ግን ምንም አታውቅም። ባልየው በሞተበት ጊዜ ወንድሞቹ መጥተው ባልዋ ከአንድ ተበዳሪ ሊቀበል ሲጠብቅ የነበረውን ገንዘብ እንድትሰጣቸው አስገደድዋት። እሷ ግን ስለ ጉዳዩ በፍጹም የምታውቀው ነገር አልነበረም። ቀጥሎም ባሏ የገዛላትን የፎቶ ኮፒ መሣሪያዎችና የጽሕፈት መኪናዎች ወሰዱባት። በመጨረሻም የእርሱ ወንድሞች ቤቱንና በውስጡ ያለውን ሁሉ በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ። ይህች ባሏ የሞተባት ሴትና ትንሿ ልጅዋ ጨርቃቸውን ብቻ ጠቅልለው ከቤት እንዲወጡ አስገደዷቸው።
“ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ”
ክርስቲያን ባሎች ሚስቶቻቸውን ከማፍቀራቸውም በላይ እምነት የሚጣልባቸው አድርገው ይመለከቷቸዋል። እነዚህ ወንዶች “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዷቸው ይገባቸዋል” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይከተላሉ። ከዚህም በተጨማሪ “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ከሚለው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ።—ኤፌሶን 5:28, 31
አምላክን የሚታዘዙ ባሎች “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” ሲል ከጻፈው ከሐዋርያው ጳውሎስ ሐሳብም ጋር ይስማማሉ። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በመስማማት አንድ ክርስቲያን ባል ለረዥም ጊዜ ከቤት ርቆ ለመሄድ ካሰበ እርሱ በሌለበት ጊዜ ቤተሰቡ የሚያስፈልጉትን ነገሮች የሚያገኝበትን ዝግጅት ያደርጋል። በተመሳሳይም፣ ድንገት ቢሞት ለሚስቱና ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን አስቀድሞ ማዘጋጀቱ ምክንያታዊ አይደለምን? ለድንገተኛ አደጋ አስቀድሞ መዘጋጀት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ፍቅራዊ አሳቢነትም ነው።
የቀብር ሥነ ሥርዓት ልማዶች
ክርስቲያን ባሎች ሌላም ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ባልዋ የሞተባት ሴት የትዳር ጓደኛዋን፣ ንብረትዋንና ምናልባትም ልጆችዋን ጭምር ማጣቷ ሳያንሳት አንዳንድ ብሔረሰቦች ባሕላዊ የልቅሶ ሥነ ሥርዓቶችን እንድትከተል ያስገድዷታል። በናይጄሪያ የሚታተመው ዘ ጋርዲያን የተባለው ጋዜጣ በአንዳንድ ቦታዎች ባልዋ የሞተባት ሴት ከሬሳው ጋር ጨለማ ክፍል ውስጥ እንድትተኛ ባሕሉ ያስገድዳታል በማለት በምሬት ተናግሯል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ባል የሞተባቸው ሚስቶች ስድስት ወር ለሚያህል ጊዜ ከቤት ሳይወጡ እዝን እንዲቀመጡ ይገደዳሉ። በእነዚህ ጊዜያት ገላቸውን መታጠብ የማይፈቀድላቸው ሲሆን ይባስ ብሎም ከምግብ በፊትና በኋላ እጅ መታጠብ የተከለከለ ነው።
እነዚህን የመሰሉ ባሕሎች ችግር ይፈጥራሉ፤ በተለይ ደግሞ ባላቸው ለሞተባቸው ክርስቲያን ሴቶች። አምላክን ለማስደሰት ያላቸው ፍላጎት ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር የማይስማሙ ልማዶችን እንዲያስወግዱ ግድ ይላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14, 17) ሆኖም አንድ ባልዋ የሞተባት ሴት ከእነዚህ ልማዶች ጋር ተስማምታ ባለመሄዷ ስደት ሊገጥማት ይችላል። እንዲያውም ሕይወቷን ለማትረፍ ስትል ሸሽታ ለመሄድ ትገደድ ይሆናል።
ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ
መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉህ ሰው እቅድ ውጤቱ ያማረ ነው” በማለት ጥሩ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 21:5 NW) አንድ የቤተሰብ ራስ ምን ቅድመ ዝግጅቶች ሊያደርግ ይችላል? በብዙ ኅብረተሰቦች ውስጥ አንድ ሰው ሲሞት ንብረቱ ለእነማን መሰጠት እንዳለበት የሚገልጽ ሰነድ አስቀድሞ ሊያዘጋጅ ወይም ሊናዘዝ ይችላል። በሰነዱ ላይ ስለ ቀብር ሥነ ሥርዓት ዝግጅትም በዝርዝር ሊያሰፍር ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ከቀብር ሥርዓቱና ከለቅሶ ልማዶች ጋር በተያያዘ የትዳር ጓደኛው ምን ማድረግ እንዳለባት (እንደሌለባት) ሰነዱ በግልጽ ሊያሰፍር ይችላል።
ሊያ የተባለች አንዲት ሴት በ1992 ባልዋን በሞት አጣች። እንዲህ ትላለች:- “አምስት ልጆች አሉኝ፤ አራቱ ሴቶች ሲሆኑ አንዱ ወንድ ነው። ባሌ ከመሞቱ በፊት ለተወሰነ ጊዜ ታሞ ነበር። ሆኖም ከመታመሙ በፊት እንኳ ንብረቱ ሁሉ ለእኔና ለልጆቻችን እንዲሰጥ እንደሚፈልግ የሚገልጽ ኑዛዜ አዘጋጀ። ኑዛዜው የዋስትና ገንዘብ፣ የእርሻ መሬት፣ የእርሻ ከብቶችና ቤት ይጨምር ነበር። ኑዛዜውን ከፈረመበት በኋላ ለእኔ ሰጠኝ። . . . ባለቤቴ ከሞተ በኋላ ዘመዶቹ ውርስ ለመካፈል ፈለጉ። ባለቤቴ የእርሻውን መሬት በራሱ ገንዘብ እንደገዛውና አንዳችም ነገር ይሰጠን ብለው የመጠየቅ መብት እንደሌላቸው ገለጽኩላቸው። በጽሑፍ የሰፈረውን ኑዛዜ ባዩ ጊዜ ነገሩን አምነው ተቀበሉ።”
ከቤተዘመድ ጋር መወያየት
አንድ ሰው ስለሚያምንባቸው ነገሮችና ስለፍላጎቶቹ ለቤተዘመዶቹ ካልነገረ ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ዘመዶቹ ቀብሩ መከናወን ያለበት በመንደሩ ውስጥ ከአካባቢው ልማድ ጋር በሚስማማ መንገድ መሆን አለበት ብለው ድርቅ ያሉትን የአንድ ሰው ሁኔታ እንመልከት። ሚስትየዋና ልጆቿ ሕይወታቸው አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ አስከሬኑን ለዘመዶቹ ትተው ለመሄድ ተገደዱ። “ባለቤቴ ከአጎቶቹ ወይም ከአክስቶቹ ለአንዱ እንኳ እንዴት መቀበር እንደሚፈልግ ቀደም ብሎ ተናግሮ ቢሆን ኖሮ ባሕላዊ በሆኑት የቀብር ሥርዓት ልማዶች መሠረት ይቀበር ብለው ባልተሟገቱ ነበር” በማለት ሚስቱ በምሬት ገልጻለች።
በአንዳንድ ኅብረተሰቦች በቃል የሚገለጽ ኑዛዜ በጽሑፍ የተዘጋጀ ሰነድ ያህል ተቀባይነት አለው። ብዙዎች ባሕላዊ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችንና የለቅሶ ልማዶችን የሚያበረታታ እምነት ባላቸው በአንዳንድ የስዋዚላንድ አካባቢዎች ሁኔታው እንደዚህ ነው። አይዛክ የተባለ አንድ ክርስቲያን ወንድም ይህንን ስለሚያውቅ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ዘመዶቹን ሁሉ ሰብስቦ እርሱ ከሞተ በኋላ ምን እንዲደረግ እንደሚፈልግ ገለጸላቸው። አንዳንድ ንብረቶቹን ማን ማግኘት እንዳለበት ከመናገሩም በላይ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንዴት መከናወን እንዳለበት በግልጽ አስረዳቸው። እርሱ ከሞተ በኋላ ነገሮቹ እርሱ በፈለገው መንገድ ተከናወኑ። አይዛክ በክርስቲያናዊ ሥርዓት የተቀበረ ሲሆን ሚስቱም ጥሩ አያያዝ ተደርጎላታል።
የቤተሰባችሁን ደህንነት ጠብቁ
አንተ ስትሞት የቤተሰቦችህን ደህንነት እንዲጠበቅ አሁን የምታደርገው ነገር የግል ምርጫህ ነው። ሆኖም ክርስቲያን የሆነው ኤድዋርድ እንዲህ ይላል:- “ስምንት አባላት ያሉትን ቤተሰቤን የሚጠቅም የሕይወት ዋስትና ገብቻለሁ። ሚስቴ በባንክ ላለኝ ሒሳብ አብራኝ ፈርማለች። ስለዚህ ብሞት እንኳ ፈርማ ከሒሳቤ ገንዘብ ማውጣት ትችላለች። . . . ቤተሰቦቼን ለመጥቀም ስል ኑዛዜ አዘጋጅቻለሁ። ብሞት ትቼ የማልፈው ነገር ሁሉ ለሚስቴና ለልጆቼ ይሆናል። ኑዛዜዬን የጻፍኩት ከአምስት ዓመት በፊት ነው። ኑዛዜው የተዘጋጀው በአንድ የሕግ ዐዋቂ ሲሆን ሚስቴና ወንድ ልጄ አንድ ቅጂ አላቸው። በኑዛዜዬ ላይ በእኔ የቀብር ሥነ ሥርዓት ዘመዶቼ በማንኛውም ውሳኔ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ በግልጽ አመልክቻለሁ። የይሖዋ ድርጅት አባል ነኝ። ስለዚህ የእኔን የቀብር ሥርዓት ለማከናወን አንድ ወይም ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከተገኙ በቂ ነው። ይህንን ነገር ከዘመዶቼ ጋር ተወያይቼበታለሁ።”
ይህን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ለቤተሰባችሁ ስጦታ ነው ለማለት ይቻላል። እርግጥ ነው ሊከሰት ስለሚችል ሞት አስቀድሞ ማሰብ የቸኮላት ወይም የአበባ እቅፍ ስጦታ ከመስጠት ጋር አንድ አይደለም። ሆኖም ለቤተሰባችሁ ያላችሁን ፍቅር ያሳያል። ከቤተሰባችሁ ጋር አንድ ላይ በሕይወት ያላችሁ እንኳ ባይሆን ‘ስለ ቤተሰባችሁ እንደምታስቡ’ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኢየሱስ ለእናቱ ዝግጅት አድርጓል
“በኢየሱስ መስቀል [“የመከራ እንጨት፣” NW] አጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እኅት፣ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፣ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን:- አንቺ ሴት፣ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን:- እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ [ዮሐንስ] ወደ ቤቱ ወሰዳት።”—ዮሐንስ 19:25-27
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ክርስቲያኖች የቤተሰቦቻቸውን ሕጋዊ መብት የሚያስጠብቁ ዝግጅቶችን በማድረግ አሳቢነታቸውን ያሳያሉ