-
አንድ ክርስቲያን ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር ለተያያዙ ልማዶች የሚኖረው አመለካከትመጠበቂያ ግንብ—1998 | ሐምሌ 15
-
-
አንድ ክርስቲያን ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር ለተያያዙ ልማዶች የሚኖረው አመለካከት
አንድ የሚወዱት ሰው ሳይጠበቅ በድንገት ሲሞት የሚያስከትለው ሐዘን በጣም ከባድ ነው። የአእምሮ መረበሽና ከባድ የስሜት ሥቃይ ያስከትላል። አንድ የሚወዱት ሰው ባደረበት ጽኑ ሕመም ተሠቃይቶ መሞቱ ዱብ ዕዳ ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሞቱ የሚያስከትለው ሐዘንና ቅስም የሚሰብር ስሜት ለረዥም ጊዜ ይቆያል።
ሟቹ የሞተበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሐዘንተኛው ድጋፍና ማጽናኛ ያስፈልገዋል። በተጨማሪም ሐዘን የደረሰበት አንድ ክርስቲያን ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶችን እንዲከተል ተጽዕኖ ከሚያሳድሩበት ሰዎች የሚደርስበትን ስደት መቋቋም ሊያስፈልገው ይችላል። ይህ በአፍሪካ በሚገኙ ብዙ አገሮችና በሌሎች የምድር ክፍል ባሉ አንዳንድ አገሮች ዘንድ የተለመደ ነገር ነው።
አንድ ሐዘን የደረሰበት ክርስቲያን ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ልማዶች እንዳይካፈል ምን ሊረዳው ይችላል? እንዲህ የመሰለ መከራ በሚደርስበት ጊዜ የእምነት አጋሮች ድጋፍ መስጠት የሚችሉት እንዴት ነው? ‘በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፣ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነትን መጠበቅ’ ስለሆነ ይሖዋን ለማስደሰት የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ይፈልጋል።—ያዕቆብ 1:27
በአንድ እምነት የተሳሰሩ
ብዙዎቹን የቀብር ሥነ ሥርዓት ልማዶች የሚያዛምዳቸው አንዱ ነገር የሞቱ ሰዎች በአንድ በማይታይ የቀድሞ አባቶች ዓለም ውስጥ ይኖራሉ የሚለው እምነት ነው። ብዙዎቹ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች የሟቾቹን ፍላጎት ለማሟላት አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የመፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ወይም ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ካልተፈጸመ በማኅበረሰቡ ላይ አንድ ዓይነት ጉዳት ይደርሳል ብለው የሚያምኑ ጎረቤቶቻቸውን እንዳያስከፉ ይፈራሉ።
አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሰውን በመፍራት አምላክን በማያስደስት ልማድ ውስጥ እጁን ማስገባት የለበትም። (ምሳሌ 29:25፤ ማቴዎስ 10:28) መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ምንም የማያውቁ መሆናቸውን እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና።” (መክብብ 9:5, 10) በዚህም የተነሳ ይሖዋ አምላክ በጥንት ጊዜ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦቹ ሙታን የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ወይም ከእነርሱ ጋር ለመገናኘት ብለው ምንም ዓይነት ሙከራ እንዳያደርጉ አዟቸዋል። (ዘዳግም 14:1፤ 18:10-12፤ ኢሳይያስ 8:19, 20) እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት እውነታዎች በሰፊው ተሰራጭተው ከሚገኙት ከብዙዎቹ የቀብር ሥነ ሥርዓት ልማዶች ጋር የሚጋጩ ናቸው።
“በጾታ ግንኙነት ስለ መንጻትስ” ምን ለማለት ይቻላል?
በአንዳንድ የመካከለኛው አፍሪካ አገሮች የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣ ግለሰብ ከሟች የቅርብ ዘመድ ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽም ይጠበቅበታል። ይህ ካልተፈጸመ ሟቹ በሕይወት ባሉት ቤተሰቦቹ ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ ይታመናል። ይህ ሃይማኖታዊ ልማድ “በጾታ ግንኙነት መንጻት” ተብሎ ይጠራል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የጾታ ግንኙነት “ዝሙት” እንደሆነ ይናገራል። ክርስቲያኖች ‘ከዝሙት መራቅ’ ስላለባቸው ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ልማድ በድፍረት ይቋቋማሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:18
መርሲ የተባለች የአንዲት መበለትን ምሳሌ እንውሰድ።a በ1989 ባሏ ሲሞት ዘመዶቿ ከአንድ የባሏ ዘመድ ጋር የጾታ ግንኙነት በማድረግ የመንጻት ሥነ ሥርዓቱን እንድትፈጽም ፈለጉ። እንዲህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የአምላክን ሕግ የሚጻረር መሆኑን በመግለጽ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። በንዴት የጦፉት ዘመዶቿ የስድብ ናዳ ካወረዱባት በኋላ ጥለዋት ሄዱ። ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ “እስቲ ሃይማኖትሽ የሚያደርግልሽን እናያለን” ብለው የቤቷን ጣሪያ በመነቃቀል ቤቷን አፈራረሱባት።
ጉባኤው መርሲን በማጽናናት ሌላ አዲስ ቤት ሠራላት። በአካባቢው ያሉት ጎረቤቶቿ በጣም በመነካታቸው አንዳንዶቹ ቤቱ ሲሠራ ለማገዝ መጡ። የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነችው የመንደሩ አለቃ ሚስት ለቤቱ ክዳን የሚሆን ሳር በማምጣት ቀዳሚ ሆናለች። መርሲ ጽኑ የታማኝነት አቋም ማሳየቷ ልጆቿ እንዲበረታቱ አድርጓል። አራቱ ልጆቿ ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ ወሰኑ። አንደኛው ደግሞ በቅርቡ በተደረገው የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተካፍሏል።
በዚህ በጾታ ግንኙነት የመንጻት ልማድ ሳቢያ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለደረሰባቸው ተጽዕኖ እጃቸውን በመስጠት አማኝ ያልሆነ ሰው አግብተዋል። ለምሳሌ ያህል በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንድ ሚስታቸው የሞተችባቸው አረጋዊ የሟች ሚስታቸው ዘመድ የሆነችውን አንዲት ወጣት ልጃገረድ ተቻኩለው አግብተዋል። ይህን ያደረጉት በጾታ ግንኙነት የመንጻት ሥርዓቱን ፈጽሜያለሁ ለማለት ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ክርስቲያኖች “በጌታ” ብቻ እንዲያገቡ ከሚያዘው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር የሚጋጭ ነው።—1 ቆሮንቶስ 7:39
ሌሊቱን ሙሉ አስከሬን ሲጠብቁ ማደር
በብዙ አገሮች ሐዘንተኞች በሟች ቤት ይሰባሰቡና ሌሊቱን ሙሉ አስከሬኑን ሲጠብቁ ያድራሉ። በዚህ ወቅት ብዙውን ጊዜ ድግስ ይደገሳል እንዲሁም ጆሮ የሚያደነቁር ሙዚቃ ይከፈታል። እንዲህ የሚደረገው የሟችን መንፈስ ጸጥ ያሰኛል እንዲሁም በሕይወት ያሉትን ቤተሰቦች ከርኩስ መንፈስ ይጠብቃል ተብሎ ስለሚታመን ነው። የሟቹን ሰው ሞገስ ለማግኘት ሲባል የውዳሴ ንግግሮች ሊቀርቡ ይችላሉ። አንድ ሰው ከተናገረ በኋላ ሌላ ሰው ንግግር እስኪሰጥ ድረስ ሐዘንተኞቹ ሃይማኖታዊ መዝሙር ይዘምራሉ። ጎህ እስኪቀድ ድረስ እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል።b
ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን መርዳትም ሆነ መጉዳት እንደማይችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚናገር አንድ እውነተኛ ክርስቲያን በእንዲህ ዓይነቶቹ አስከሬን የመጠበቅ ሥነ ሥርዓቶች ላይ አይካፈልም። (ዘፍጥረት 3:19፤ መዝሙር 146:3, 4፤ ዮሐንስ 11:11-14) ቅዱሳን ጽሑፎች መናፍስታዊ እምነቶችን ያወግዛሉ። (ራእይ 9:21፤ 22:15) ሆኖም ባሏ የሞተባት አንዲት ክርስቲያን ሴት ሌሎች ሰዎች መናፍስታዊ ድርጊቶችን እቤቷ እንዳይፈጽሙ መከላከሉ አስቸጋሪ ሊሆንባት ይችላል። ሌሊቱን በሙሉ የሚፈጸመው ሃይማኖታዊ ሥርዓት በቤቷ እንዲከናወን ያስገድዷት ይሆናል። ታዲያ የእምነት ባልደረቦች እንዲህ ያለ ተጨማሪ መከራ ለገጠማቸው በሐዘን ላይ የሚገኙ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት እርዳታ ሊያበረክቱ ይችላሉ?
ብዙውን ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎች የሐዘንተኛውን ዘመዶችና ጎረቤቶች በማነጋገር በሐዘን ላይ ለወደቀው ክርስቲያን ድጋፍ መስጠት ችለዋል። እንዲህ የመሰለው ውይይት ከተደረገ በኋላ ሰዎቹ ቤቱን በሰላም ለቀው ለመሄድና በሌላ ቀን በሚደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት ይስማሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ አምባጓሮ ቢያስነሱስ? በዚህ ጊዜም ጉዳዩን ለማስረዳት መሞከሩ ጠብ ከመፍጠር በቀር ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖር ይሆናል። ‘የጌታም ባሪያ ትዕግሥተኛ ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም።’ (2 ጢሞቴዎስ 2:24) ስለዚህ ለመተባበር አሻፈረኝ ያሉት ዘመዶች በኃይል ለመጠቀም ሲሞክሩ ባሏን በሞት ያጣችው ክርስቲያን ሴትና ልጆቿ ሁኔታው ከቁጥጥራቸው ውጪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ በጥብቅ ስለሚከተሉ በቤታቸው ውስጥ በሚከናወነው የሐሰት ሃይማኖት ሥነ ሥርዓት ላይ ተካፋይ አይሆኑም።—2 ቆሮንቶስ 6:14
ይህ መሠረታዊ ሥርዓት የቀብር ሥነ ሥርዓት በሚፈጸምበትም ጊዜ ይሠራል። የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ የሐሰት ሃይማኖት አገልጋይ አማካኝነት በሚካሄድ መዝሙር፣ ጸሎትና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ተካፋይ አይሆኑም። ከቤተሰቡ አባላት ጋር የቀረበ ዝምድና ያላቸው ክርስቲያኖች እንዲህ በመሰለው ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ቢገኙ እንኳ በእነዚህ ነገሮች አይካፈሉም።—2 ቆሮንቶስ 6:17፤ ራእይ 18:4
ክብር ባለው መንገድ የሚፈጸም የቀብር ሥነ ሥርዓት
የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ሟቹን ላለማስቆጣት ሲባል የሚፈጸም ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት የለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር በመንግሥት አዳራሹ ወይም በሟቹ ቤት አለዚያም ደግሞ በመቃብሩ ቦታ ይሰጣል። የንግግሩ ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታንና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ምን እንደሚል በማብራራት ሐዘን ላይ የሚገኙትን ሰዎች ማጽናናት ነው። (ዮሐንስ 11:25፤ ሮሜ 5:12፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መዝሙር ሊዘመር ይችላል፤ ከዚያም ሥርዓቱ በሚያጽናና ጸሎት ይደመደማል።
በቅርቡ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የኔልሰን ማንዴላ ታናሽ እህት የሆኑ አንዲት የይሖዋ ምሥክር በሞቱ ጊዜ እንዲህ የመሰለው የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጽሞ ነበር። ሥነ ሥርዓቱ ከተፈጸመ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ተናጋሪውን ከልባቸው አመስግነውታል። በርካታ ሹማምንቶችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በቦታው ተገኝተው ነበር። አንዲት የካቢኔ ሚኒስትር “እስካሁን ከተገኘሁባቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ሁሉ ይበልጥ ክብር የተላበሰ ነበር” በማለት ተናግረዋል።
የሐዘን ልብሶች መልበስ ተገቢ ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ ጥልቅ ሐዘን ያድርባቸዋል። ልክ እንደ ኢየሱስ እንባቸውን ያፈስሳሉ። (ዮሐንስ 11:35, 36) ይሁን እንጂ የደረሰባቸውን ሐዘን ውጫዊ በሆነ መግለጫ ለሕዝብ ማሳወቁ አስፈላጊ ሆኖ አይታያቸውም። (ከማቴዎስ 6:16-18 ጋር አወዳድር።) በብዙ አገሮች ባል የሞተባቸው ሴቶች ሟቹን ላለማስቆጣት ሲባል የተለየ የሐዘን ልብስ እንዲለብሱ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ ልብሶች ሟቹ ከተቀበረ በኋላ ለበርካታ ወራት ወይም ለአንድ ዓመት ያህል መለበስ አለባቸው። ልብሶቹን መልበሳቸውን የሚያቆሙት ሌላ ድግስ በሚደገስበት ጊዜ ነው።
የሐዘን ምልክት የሆነውን ይህን ልብስ አለመልበስ ሟቹን ሰው እንደ ማስቀየም ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህ ምክንያት በስዋዚላንድ የሚገኙ አንዳንድ የጎሳ አለቆች የይሖዋ ምሥክሮችን ከገዛ ቤታቸውና ከቄያቸው አባርረዋቸዋል። ሆኖም እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች በሌላ ቦታ በሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎላቸዋል።
የስዋዚላንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተባረሩት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታቸውና ወደ መንደራቸው መመለስ እንዲችሉ ፈርዶላቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ባሏ የሞተባት አንዲት ክርስቲያን ሴት የሞተው ባሏ የሐዘን ልብስ መልበስ እንደሌለባት የገለጸበትን ደብዳቤና የቴፕ ክር ካቀረበች በኋላ ከቤቷ ሳትፈናቀል እንድትኖር ተፈቅዶላታል። በዚህ መንገድ ለባሏ አክብሮት ያላት መሆኑን ማሳየት ችላለች።
አንድ ሰው በተለይ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች በሚዘወተሩበት አካባቢ የሚኖር ከሆነ ከመሞቱ በፊት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እንዴት መከናወን እንዳለበት የሚገልጽ ግልጽ መመሪያ መስጠቱ ትልቅ ጥቅም አለው። ቪክቶር የተባለውን ካሜሩናዊ ምሳሌ ተመልከት። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚፈጸምበትን መንገድ ግልጽ አድርጎ በጽሑፍ አሰፈረ። የሰውን ራስ ቅል ማምለክን ጨምሮ ከሙታን ጋር በተያያዘ የተለያዩ ልማዶችን አጥብቀው የሚከተሉ ተደማጭነት ያላቸው በርካታ ዘመዶች ነበሩት። ቪክቶር በዘመዶቹ የተከበረ ሰው እንደመሆኑ መጠን የእሱንም የራስ ቅል ለዚህ ዓላማ ሊያውሉት እንደሚችሉ ተገነዘበ። በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች የእርሱን የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዴት ሊያከናውኑ እንደሚገባ የሚገልጽ ግልጽ የሆነ መመሪያ አዘጋጀ። ይህም ለሚስቱና ለልጆቹ ሁኔታውን አቀለለላቸው። ለማኅበረሰቡም ጥሩ ምሥክርነት ሊሰጥ ችሏል።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶችን ከመከተል ራቁ
የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች የተለዩ ሆነው መታየት ይፈራሉ። ስደት እንዳይደርስባቸው ሲሉ ሌሊቱን ሙሉ አስከሬን ሲጠብቁ የማደርን ልማድ የሚከተሉ መስለው በመታየት ጎረቤቶቻቸውን ለማስደሰት ይጥራሉ። በግል ማጽናኛ ለመስጠት ተብሎ በሐዘን ላይ የሚገኙ ሰዎችን መጠየቁ የሚያስመሰግን ቢሆንም አስከሬኑ ከመቀበሩ በፊት ባሉት ቀናት ሌሊት ሌሊት በሟቹ ቤት ከቀብር ጋር የተያያዘ ልዩ ሥርዓት ማከናወን ተገቢ አይደለም። እንዲህ ማድረጉ ሌሎች ተመልካቾች መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ የሚናገረውን ነገር አያምኑበትም የሚል ስሜት አድሮባቸው እንዲደናቀፉ ሊያደርግ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 10:32
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ለአምላክ የሚያቀርቡትን አምልኮ በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ እንዲሰጡትና ጊዜያቸውን በጥበብ እንዲጠቀሙበት አጥብቆ ያሳስባቸዋል። (ማቴዎስ 6:33፤ ኤፌሶን 5:15, 16) ሆኖም በአንዳንድ ቦታዎች በቀብር ሥነ ሥርዓት ምክንያት የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ይቋረጣሉ። ይህ በአፍሪካ ብቻ ያለ ችግር አይደለም። አንድን የቀብር ሥነ ሥርዓት በማስመልከት ከደቡብ አሜሪካ የተላከ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ሦስት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የነበራቸው የተሰብሳቢ ቁጥር በጣም አነስተኛ ነበር። የመስክ አገልግሎት ለአሥር ቀናት ገደማ ተቋርጦ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንኳ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በአንዳንድ ሥርዓቶች ላይ ያደርጉት በነበረው ተሳትፎ ከመገረማቸውም በላይ ቅር ተሰኝተዋል።”
በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ሐዘን የደረሰበት ቤተሰብ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከተፈጸመ በኋላ የቅርብ ወዳጆችን በመጥራት ቀለል ያለ ምግብ ይጋብዛል። ይሁን እንጂ በብዙ የአፍሪካ አገሮች በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከብት በሚታረድበት ድል ያለ ድግስ ላይ ለመገኘት ወደ ሟቹ ቤት ይጎርፋሉ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ይህንኑ ልማድ ኮርጀዋል፤ እንዲህ ማድረጋቸው ደግሞ ሟቹን ላለማስቆጣት ሲባል በሚደገሱት ልማዳዊ ድግሶች ያምናሉ የሚል አመለካከት በሌሎች ዘንድ አሳድሯል።
የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የቀብር ሥነ ሥርዓት ሐዘን በደረሰባቸው ሰዎች ላይ ተጨማሪ ሸክም የሚጭን አይደለም። ስለዚህ ለተንዛዛ የቀብር ሥነ ሥርዓት የሚወጣውን ወጪ ለመሸፈን ለቅሶ ከሚደርሱ ሰዎች ገንዘብ መሰብሰብ አግባብ አይደለም። በሐዘን ላይ የወደቁ ድሃ መበለቶች የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል አቅም በማይኖራቸው ጊዜ በጉባኤ ያሉት ሌሎች ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኞች እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። በዚህ መንገድ የሚደረገው እርዳታ በቂ ካልሆነ ሽማግሌዎች ችግር ላይ ለወደቁት ቁሳዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 5:3, 4
ሁሉም የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይጋጫሉ ማለት አይደለም። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚሉት ጋር ተስማምተው ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ ያደርጋሉ።c (ሥራ 5:29) እንዲህ ማድረጉ ተጨማሪ መከራ ሊያስከትል ቢችልም ብዙ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ያሉትን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ መወጣት ችለዋል። “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ባገኙት ብርታትና በመከራቸው ባጽናኗቸው የእምነት ባልደረቦቻቸው ባገኙት ፍቅራዊ እርዳታ ፈተናዎቹን በድል አድራጊነት ተወጥተዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ስሞች ቀይረናቸዋል።
b መጠበቅ ተብሎ የተተረጎመው “ዌክ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአንዳንድ ቋንቋዎችና ባሕሎች ሐዘንተኛውን ለማጽናናት ጥቂት ጊዜ አብሮ ማሳለፍን ያመለክታል። ከቅዱስ ጽሑፉ ጋር የሚጋጭ ምንም ነገር አይደረግ ይሆናል። የግንቦት 22, 1979 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 27-8 ተመልከት።
c ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ልማዶች በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ፈተና በሚያስከትሉባቸው አገሮች፣ ሽማግሌዎች የጥምቀት እጩዎችን ወደፊት ሊገጥማቸው ለሚችለው ፈተና አስቀድመው ሊያዘጋጁአቸው ይችላሉ። አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ላይ ባሉት ጥያቄዎች አማካኝነት ከጥምቀት እጩዎች ጋር ውይይት በሚያደርጉበት ጊዜ “ነፍስ፣ ኃጢአትና ሞት” እንዲሁም “ልዩ ልዩ ሃይማኖትን መቀላቀል” በሚሉት ክፍሎች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ አለባቸው። ሁለቱም ክፍሎች ለውይይት የሚሆኑ ተጨማሪ ጥያቄዎች አሏቸው። የጥምቀት እጩው እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በሚገጥሙት ጊዜ ሊያደርገው የሚገባውን ነገር በተመለከተ የአምላክ ቃል ምን እንደሚል እንዲያውቅ ለማድረግ ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን በማስመልከት ተጨማሪ ሐሳብ ሊሰጡ ይችላሉ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የጸና አቋም በመያዛቸው ተባርከዋል
ሲቦንጊሊ በስዋዚላንድ የምትኖር ደፋር መበለት ክርስቲያን ናት። በቅርቡ ባሏ በሞተ ጊዜ ብዙዎች ሟቹ እንዳይቆጣ ለማድረግ ይረዳል ብለው የሚያምኑበትን ልማድ ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነችም። ለምሳሌ ያህል ፀጉሯን አልተላጨችም ነበር። (ዘዳግም 14:1) ስምንት የቤተሰቡ አባላት በዚህ ድርጊቷ በጣም በመናደዳቸው ኃይል በመጠቀም ፀጉሯን ሙልጭ አድርገው ላጯት። በተጨማሪም ሲቦንጊሊን እናጽናናለን ብለው የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤት እንዳይመጡ ከለከሉ። ይሁን እንጂ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት የነበራቸው ሌሎች ሰዎች ሽማግሌዎች የሚጽፉላትን የሚያበረታታ ደብዳቤ ይሰጧት ነበር። ሲቦንጊሊ የሐዘን ልብስ መልበስ አለባት ተብሎ በሚጠበቅበት ዕለት አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። በቤተሰቡ ዘንድ ተደማጭነት ያለው አንድ የቤተሰቡ አባል ባሕሉ የሚጠይቀውን የሐዘን ልማድ ለመከተል እምቢ ስላለችበት ምክንያት ለመወያየት ሁሉንም ስብሰባ ጠራ።
ሲቦንጊሊ እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ሐዘንን ለመግለጽ የሚለበሰውን ጥቁር ልብስ ለመልበስ ሃይማኖታዊ እምነቴ ይፈቅድልኝ እንደሆነ ጠየቁኝ። አቋሜን ግልጽ አድርጌ ከነገርኳቸው በኋላ ዳግመኛ እንደማያስገድዱኝ ገለጹልኝ። ከሁሉም የሚገርመው ደግሞ ያለ ፈቃዴ ፀጉሬን በመላጨት ላደረሱብኝ በደል ይቅርታ ጠየቁኝ። ሁሉም ይቅርታ እንዳደርግላቸው ጠየቁኝ።” ከጊዜ በኋላም የሲቦንጊሊ እህት ትክክለኛው ሃይማኖት የይሖዋ ምሥክሮች እምነት እንደሆነ በመግለጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ጠየቀች።
ሌላ ምሳሌም እንመልከት:- ቤንጃሚን የተባለው ደቡብ አፍሪካዊ የአባቱን ድንገተኛ ሞት የሰማው በ29 ዓመቱ ነበር። በዚያን ጊዜ ከቤተሰቡ መካከል የይሖዋ ምሥክር የነበረው ቤንጃሚን ብቻ ነበር። የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በሚካሄድበት ወቅት እያንዳንዱ ሰው በመቃብሩ አጠገብ ተራ በተራ እያለፈ በሬሳ ሣጥኑ ላይ አንድ እፍኝ አፈር እንዲበትን ይጠበቅበት ነበር።d ከቀብር ሥነ ሥርዓቱም በኋላ የቅርብ ዘመድ የሆኑት ሁሉ ፀጉራቸውን ይላጫሉ። ቤንጃሚን እነዚህን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ባለመፈጸሙ ጎረቤቶቹና የቤተሰቡ አባላት የሟች አባቱ መንፈስ እንደሚቀጣው ተናገሩ።
“በይሖዋ ላይ በመታመኔ ምንም ነገር አልደረሰብኝም” ይላል ቤንጃሚን። የቤተሰቡ አባላት በእርሱ ላይ ምንም ነገር እንዳልደረሰ ተገነዘቡ። ከጊዜ በኋላም ብዙዎቹ የቤተሰቡ አባላት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከጀመሩ በኋላ ራሳቸውን ለአምላክ በመወሰን ተጠመቁ። ቤንጃሚንስ? በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ መካፈል ጀመረ። ላለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በመሆን የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች የማገልገል መብት አግኝቷል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
d አንዳንዶች አበባ ወይም አንድ እፍኝ አፈር መቃብሩ ላይ መበተን ምንም ስህተት እንደሌለው ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ይህ ድርጊት የሟቹን መንፈስ ላለማስቆጣት ተብሎ የሚደረግ ወይም በአንድ የሐሰት ሃይማኖት ቄስ አመራር የሚከናወን ሥርዓት ከሆነ እንዲህ የመሰለውን ልማድ ከመፈጸም ይርቃል።—የመጋቢት 22, 1977 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 15ን ተመልከት።
-
-
ጥቅምት 3, 1998 የሚደረገው ዓመታዊ ስብሰባመጠበቂያ ግንብ—1998 | ሐምሌ 15
-
-
ጥቅምት 3, 1998 የሚደረገው ዓመታዊ ስብሰባ
የፔንሲልቬንያ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር አባላት ዓመታዊ ስብሰባ ጥቅምት 3, 1998 በኒው ጀርሲ ክፍለ ሀገር፣ በጀርሲ ከተማ 2932 ኬኔዲ በሊቨርድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል። አባላቱ ብቻ የሚገኙበት ስብሰባ ከጠዋቱ 3:15 ከተደረገ በኋላ 4 ሰዓት ላይ አጠቃላይ ዓመታዊው ስብሰባ ይደረጋል።
ካለፈው ዓመት ወዲህ የፖስታ አድራሻቸውን የለወጡ የማኅበሩ አባላት መደበኛዎቹ የማስታወቂያ ደብዳቤዎችና የውክልና ማስረጃዎች በሐምሌ ወር ውስጥ እንዲደርሷቸው ለውጡን አሁኑኑ ለጸሐፊው ቢሮ ማስታወቅ ይኖርባቸዋል።
ከዓመታዊው የስብሰባ ማስታወቂያዎች ጋር ለአባላቱ የሚላኩት ውክልናዎች ከነሐሴ 1 በፊት ለማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ተመልሰው መድረስ አለባቸው። እያንዳንዱ አባል በስብሰባው ላይ ራሱ ይገኝ ወይም አይገኝ እንደሆነ በመግለጽ ውክልናውን ወዲያውኑ ሞልቶ መመለስ አለበት። በስብሰባው ላይ ማን እንደሚገኝ የሚታወቀው በዚህ መሠረት ስለሆነ በእያንዳንዱ የውክልና ቅጽ ላይ የሚሰጠው መረጃ በዚህ ነጥብ ላይ ግልጽ መሆን ይኖርበታል።
መደበኛውን የሥራ ጉዳይና ሪፖርት ጨምሮ ጠቅላላው ስብሰባ ከቀኑ 7 ሰዓት ወይም ከዚያ ብዙ ሳይቆይ ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከሰዓት በኋላ ስብሰባ አይኖርም። ያለው ቦታ የተወሰነ በመሆኑ መግባት የሚቻለው በቲኬት ብቻ ይሆናል። ዓመታዊውን ስብሰባ ወደ ሌሎች አዳራሾች በስልክ ለማስተላለፍ የተደረገ ዝግጅት የለም።
-