ተዓምር ብቻውን እምነት የማይገነባው ለምንድን ነው?
ማየት ማመን ነው። ይህ የብዙ ሰዎች አመለካከት ነው። አንዳንዶች አምላክ በሆነ ተዓምራዊ መንገድ ራሱን ቢገልጽላቸው ኖሮ በእርሱ ያምኑ እንደነበር ይናገራሉ። ይህ እውነት ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ እውነታውን መቀበል ወደ እውነተኛ እምነት ይመራልን?
ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን የተባሉ እስራኤላውያን ያደረጉትን ተመልከት። አምላክ አስገራሚ ተዓምራት ሲፈጽም የዓይን ምሥክር እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ በግብጽ ላይ አሥርቱ መቅሰፍቶች ሲወርዱ፣ የእስራኤል ብሔር ቀይ ባሕርን አቋርጦ ሲያመልጥና የግብጻውያኑ ፈርዖን ከነጦር ሠራዊቱ ሲደመሰስ ተመልክተዋል። (ዘጸአት 7:19— 11:10፤ 12:29-32፤ መዝሙር 136:15) ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን በሲና ተራራ ላይ ሆነው ይሖዋ ከሰማይ ሲናገር ሰምተዋል። (ዘዳግም 4:11, 12) ይሁን እንጂ እነዚህ ሦስት ሰዎች በይሖዋና እርሱ በሾማቸው አገልጋዮቹ ላይ ዓመፅ የቀሰቀሱት ተዓምራቱን ካዩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር።— ዘኁልቁ 16:1-35፤ መዝሙር 106:16-18
ከ40 ዓመታት በኋላ በለዓም የተባለ አንድ ነቢይ አንድ ተዓምር ተመልክቶ ነበር። መልአክታዊ ጣልቃ ገብነት እንኳን የአምላክ ጠላቶች ከሆኑት ከሞዓባውያን ጋር ከማበር አልገታውም። በለዓም ያየውን ተዓምር ከምንም ሳይቆጥር በጀመረው አካሄድ በመግፋት ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን የሚቃወም አቋም ወስዷል። (ዘኁልቁ 22:1-35፤ 2 ጴጥሮስ 2:15, 16) ይሁን እንጂ የበለዓም እምነት ማጣት ከአስቆሮቱ ይሁዳ ጋር ሲወዳደር ከቁጥር አይገባም። ይሁዳ ከኢየሱስ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበረውና በርካታ አስገራሚ ተዓምራትን በዓይኑ የተመለከተ ቢሆንም ክርስቶስን በሠላሳ ብር አሳልፎ ሰጥቶታል።— ማቴዎስ 26:14-16, 47-50፤ 27:3-5
የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ብዙ ተዓምራት ያውቁ ነበር። አልዓዛርን ከሞት ካስነሣው በኋላ “ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋል” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ዳግም ሕያው የሆነውን አልዓዛርን ማየታቸው ልባቸውን አለስልሶላቸውና እምነት እንዲያሳድሩ ረድቷቸው ነበርን? በፍጹም። እንዲያውም ኢየሱስንና አልዓዛርን ለመግደል ያሴሩ ጀመር!— ዮሐንስ 11:47-53፤ 12:10
እነዚያ ክፉ ሰዎች አምላክ በቀጥታ ጣልቃ ቢገባም እንኳ እምነት ማሳደር አልቻሉም። ኢየሱስ በአንድ ወቅት በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” ሲል ጸለየ። ይሖዋም ከሰማይ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” ብሎ በድምፅ መለሰለት። አዎን፣ ይህ ተዓምራዊ ክስተት በዚያ በተገኙት ሰዎች ልብ ውስጥ እምነት አላሳደረም። መጽሐፍ ቅዱስ “ይህን ያህል ምልክት በፊታቸው ምንም ቢያደርግ . . . በእርሱ አላመኑም” ይላል።— ዮሐንስ 12:28-30, 37፤ ከኤፌሶን 3:17 ጋር አወዳድር።
ተዓምራት እምነት ሳይገነቡ የቀሩት ለምን ነበር?
ይህን ሁሉ ተዓምር እያዩ እንዴት ማመን አቃታቸው? አይሁዳውያን በሙሉ ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ጊዜ ‘ክርስቶስን’ ወይም መሲሑን ‘ይጠባበቁት’ የነበረ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ በተለይ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን ለመቀበል አሻፈረኝ ማለታቸው በጣም የሚያስገርም ነው። (ሉቃስ 3:15) ይሁን እንጂ ችግሩ ያለው ይጠብቁት የነበረው ነገር ላይ ነው። የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ደብልዩ ኢ ቫይን አንድን የታወቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁርን ዋቢ በመጥቀስ አይሁዶች “ዓለማዊ ድል” የሚያስጨብጣቸውና “ቁሳዊ ብልጥግና” የሚያጎናጽፋቸው መሲሕ የማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው ሲሉ ጽፈዋል። በመሆኑም በ29 እዘአ እውነተኛ መሲሕ ሆኖ በመካከላቸው የተገለጠውን ትሑትና ከፖለቲካ ገለልተኛ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ለመቀበል ዝግጁ አልነበሩም። ከዚህም በተጨማሪ ሃይማኖታዊ መሪዎቹ የኢየሱስ ትምህርት በጊዜው የነበረውን ኅብረተሰብ እንዳያነሳሳና የእነርሱን ከፍተኛ ሥልጣን አደጋ ላይ እንዳይጥልባቸው ፈርተው ነበር። (ዮሐንስ 11:48) የራሳቸው ጭፍን ግምትና ራስ ወዳድነታቸው ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተዓምራት ትርጉም እንዳያስተውሉ ዓይናቸውን አሳውሮታል።
ከጊዜ በኋላም የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች መለኮታዊ ሞገስ እንዳገኙ የሚመሠክሩትን ተዓምራታዊ ማስረጃዎች ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያት ከልጅነቱ ጀምሮ አንካሳ የነበረውን ሰው በፈወሱ ጊዜ አንጀታቸው ያረረው ከፍተኛው የአይሁድ ሸንጎ አባላት እንዲህ ሲሉ መክረዋል:- “በእነዚህ ሰዎች ምን እንሥራ? የታወቀ ምልክት በእነርሱ እጅ እንደ ተደረገ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ ተገልጦአልና፣ እንሸሽገውም ዘንድ አንችልም፤ ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ አብዝቶ እንዳይስፋፋ፣ ከእንግዲህ ወዲህ ለማንም ሰው በዚህ ስም እንዳይናገሩ እየዛትን እንዘዛቸው።” (ሥራ 3:1-8፤ 4:13-17) ይህ ድንቅ ተዓምር በእነዚያ ሰዎች ልብ ውስጥ እምነት እንዳልገነባ ወይም እንዳላሳደረ ግልጽ ነው።
ብዙዎች ልባቸውን እንዲደፍኑ ያደረጋቸው የሥልጣን ምኞት፣ ኩራትና ስስት ነው። በመግቢያችን ላይ የተጠቀሱት የነቆሬ፣ ዳታንና አቤሮንም ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ሌሎች ደግሞ ቅንዓት፣ ፍርሃትና ሌሎች የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን መያዛቸው እንቅፋት ሆኖባቸዋል። በአንድ ወቅት የአምላክን ፊት እስከማየት ድረስ ትልቅ መብት የነበራቸውን አመፀኛ መላእክት ወይም አጋንንት ሁኔታም አንዘነጋም። (ማቴዎስ 18:10) አምላክ ስለመኖሩ ምንም አይጠራጠሩም። እንዲያውም ስለ አምላክ መኖር “አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል።” (ያዕቆብ 2:19) ይሁን እንጂ በአምላክ ላይ እምነት የላቸውም።
የእውነተኛ እምነት ትርጉም
እምነት እንዲሁ ነገሮችን በማስረጃ መቀበል ማለት ብቻ አይደለም። እንዲሁም አንዳንድ ተዓምራት በማየት ከስሜታዊነት የሚመነጭ ቅጽበታዊ ነገር አይደለም። ዕብራውያን 11:1 [NW] “እምነት ተስፋ የተደረጉትን ነገሮች በእርግጠኝነት መጠበቅ፤ የማይታዩ እውነታዎችን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ ነው” ይላል። እምነት ያለው አንድ ሰው ይሖዋ አምላክ የገባው ቃል በሙሉ እንደተፈጸመ አድርጎ ከልቡ አምኖ ይቀበላል። እንዲያውም የማይታዩ እውነታዎችን የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች በጣም ጠንካራ መሆን አለባቸው፤ እምነት ደግሞ እንዲህ ዓይነት ማስረጃ እንደሆነ ተገልጿል። አዎን፣ እምነት በማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ ነገር ነው። ጥንት ተዓምራት በሰዎች ውስጥ እምነት ለማሳደር ወይም ለመገንባት የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል። ኢየሱስ የፈጸማቸው ምልክቶች እርሱ ቃል የተገባለት መሲሕ መሆኑን ሰዎች አምነው እንዲቀበሉ አድርገዋል። (ማቴዎስ 8:16, 17፤ ዕብራውያን 2:2-4) በተመሳሳይም እንደ ተዓምራዊ ፈውስና በልሳን መናገር የመሳሰሉት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ስጦታዎች አይሁዳውያን የይሖዋን ሞገስ እንዳጡና በምትኩ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የተቋቋመው የክርስቲያን ጉባኤ የእርሱን ሞገስ እንዳገኘ አረጋግጠዋል።— 1 ቆሮንቶስ 12:7-11
ከመንፈስ ቅዱስ ተዓምራታዊ ስጦታዎች መካከል አንዱ ትንቢት የመናገር ችሎታ ነበር። የማያምኑ ሰዎች ይህን ተዓምር በሚያዩበት ጊዜ አንዳንዶቹ “እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው” በማለት ይሖዋን ለማምለክ ተገፋፍተዋል። (1 ቆሮንቶስ 14:22-25) ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ይህ ተዓምር የክርስቲያን ጉባኤ ዘላቂ ገጽታ ሆኖ እንዲቀጥል ዓላማው አልነበረም። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ “ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ከሁኔታው በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ሐዋርያትና እነዚህን ስጦታዎች ከእነርሱ የተቀበሉት ሰዎች ከሞቱ በኋላ ስጦታዎቹ አቁመዋል።
ይህ ማለት ግን ከዚያ በኋላ ሰዎች ለእምነት መሠረት የሚሆን ነገር አያገኙም ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፣ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምሥክር አልተወም።” (ሥራ 14:17) በእርግጥም አእምሮና ልባቸውን ክፍት አድርገው በዙሪያቸው ያሉትን ማስረጃዎች ለመመልከት ፈቃደኛ ለሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ የይሖዋ አምላክ ‘የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ስለሚታይ የሚያመካኙት የላቸውም።’— ሮሜ 1:20
አምላክ እንዳለ የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች አሜን ብሎ መቀበሉ ብቻ አይበቃም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አጥብቆ መክሯል:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) ይህንን ማድረግ የሚቻለው ይህንን መጽሔት በመሳሰሉት ክርስቲያናዊ ጽሑፎች እየታገዙ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጥናት ነው። የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት ደካማ ወይም ጥልቀት የሌለው አይሆንም። የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ያስተዋሉና በእምነት የሚያደርጉት ሰዎች ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡ ነው።— ሮሜ 12:1 NW
ሳያዩ የሚያምኑ
ሐዋርያው ቶማስ ኢየሱስ ከሞት መነሣቱን ለማመን ተቸግሮ ነበር። ቶማስ “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም” ብሎ ነበር። ኢየሱስ የተሰቀለበትን ቁስል የሚያሳይ ሥጋዊ አካል ለብሶ በታየው ጊዜ ቶማስ የተዓምሩን ማስረጃ ተቀብሏል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” ሲል ተናግሯል።— ዮሐንስ 20:25-29
ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሚመላለሱት ‘በማየት ሳይሆን በእምነት’ ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:7) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡትን ተዓምራት በዓይናቸው ባያዩም እንደተፈጸሙ በእርግጠኝነት ያምናሉ። ምሥክሮቹ በአምላክና በቃሉ ላይ እምነት አላቸው። በአምላክ መንፈስ እርዳታ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ከማወቃቸውም በላይ ዋነኛ ጭብጡ በሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት የይሖዋ አምላክ ሉዓላዊነት መረጋገጥ እንደሆነ ተረድተዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ ያለበት ምክር በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ ማድረጋቸው ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። (መዝሙር 119:105፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ዛሬ ያለንበት ጊዜ ‘የመጨረሻ ቀን’ መሆኑን በማመልከት የሚሰጡትን የማያሻማ ማስረጃ ይቀበላሉ፤ እንዲሁም አምላክ ቃል የገባለት አዲስ ዓለም በደጅ እንደቀረበ ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 24:3-14፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) አምላክ የሚሰጠውን እውቀት ለሌሎች ማካፈል በጣም ያስደስታቸዋል። (ምሳሌ 2:1-5) አምላክን ለማግኘት ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሊያገኙት የሚችሉት ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጥናት ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ።— ሥራ 17:26, 27
በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን አልበርትን ታስታውሰዋለህ? ተዓምር ለማየት ያቀረበው ጸሎት መልስ ሳያገኝ ጥቂት ቀናት ካለፉ በኋላ አንዲት በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክር ያነጋግሩትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ሰጥተውት ይሄዳሉ። ከዚያም አልበርት ነጻ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ተስማማ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጋር ይበልጥ እየተዋወቀ ሲመጣ የጠበቀው ሳይፈጸም በመቅረቱ የተሰማው ብስጭት በደስታ ተለወጠ። እርሱ በጠበቀው መንገድ ባይሆንም አምላክን እንዳገኘ እየተገነዘበ መጣ።
ቅዱሳን ጽሑፎች “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት” በማለት አጥብቀው ያሳስባሉ። (ኢሳይያስ 55:6) ይህንን ማድረግ የምትችለው በዚህ ዘመን አምላክ ተዓምር እንዲያሳይህ በመጠበቅ ሳይሆን ከቃሉ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ነው። ተዓምራት ብቻቸውን እምነት ስለማይገነቡ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአልዓዛር ተዓምራዊ ትንሣኤ እንኳን የኢየሱስን ጠላቶች እምነት እንዲያሳድሩ አላደረጋቸውም
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን ይገባዋል