ጥናት 49
አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ
አንድ ነገር ስትናገር አድማጮችህ “ይህ ነገር እውነት ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለ?” ብለው የመጠየቅ መብት አላቸው። አንተ ደግሞ አስተማሪ እንደመሆንህ መጠን በቀጥታ መልሱን የመናገር ወይም አድማጮችህ ራሳቸው እንዲደርሱበት የመርዳት ግዴታ አለብህ። ለምታብራራው ሐሳብ ወሳኝ የሆነ ነጥብ በሚኖርበት ጊዜ አድማጮችህ ከልብ እንዲያምኑበት የሚያደርግ በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርብሃል። ይህም አጠቃላዩ ንግግርህ አሳማኝ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ማስረጃ በማቅረብ፣ አእምሮአቸውን በማመራመር እንዲሁም ከልቡ በመማጸን አድማጮቹ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርጉ ለመርዳት ጥሯል። በዚህ ረገድ ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። (ሥራ 18:4፤ 19:8) እርግጥ አንዳንድ የመናገር ተሰጥዎ ያላቸው ሰዎች ሌሎችን በተሳሳተ መንገድ ማሳመን ይችላሉ። (ማቴ. 27:20፤ ሥራ 14:19፤ ቆላ. 2:4) ገና ከመነሻው የሚጠቅሱት ሐሳብ በተሳሳተ ግምት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፣ የተዛቡ መረጃዎችን እንደ ዋቢ አድርገው ይጠቅሳሉ፣ ከእነርሱ አመለካከት ጋር የሚቃረኑትን እውነታዎች ገሸሽ ያደርጋሉ ወይም አሳማኝ ማስረጃ ከማቅረብ ይልቅ ስሜታዊና ጥራዝ ነጠቅ ይሆናሉ። እኛ በዚህ መንገድ ሰዎችን ለማሳመን መሞከር አይኖርብንም።
በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ። ለሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርነውን ለማካፈል እንጥራለን እንጂ የራሳችንን ሐሳብ ማስተማር የለብንም። በዚህ ረገድ ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያወጣቸው ጽሑፎች ትልቅ እገዛ ያደርጉልናል። እነዚህ ጽሑፎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት እንድንመረምር የሚያበረታቱ ናቸው። ከዚያ እኛ ደግሞ ሌሎች ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምሩ እናበረታታለን። ይህን ስናደርግ ዓላማችን የአምላክ ቃል ምን እንደሚል ራሳቸው እንዲያስተውሉ በትሕትና መርዳት እንጂ እነርሱን መርታት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ “ቃልህ እውነት ነው” ሲል ለአባቱ ካቀረበው ጸሎት ጋር እንስማማለን። (ዮሐ. 17:17) የሰማይና የምድር ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ የበለጠ ታላቅ ባለ ሥልጣን የለም። የምንናገረው ሐሳብ አሳማኝ የሚሆነው በእርሱ ቃል ላይ የተመሠረተ ሲሆን ነው።
አንዳንድ ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም የማያውቁ ወይም እንደ አምላክ ቃል አድርገው የማይቀበሉት ሰዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። እንደዚህ ላሉት ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መቼና እንዴት ብትጠቅስላቸው የተሻለ እንደሚሆን ማስተዋል ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ በተቻለ መጠን ጊዜ ሳታጠፋ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ወደሚገኘው ማስረጃ ልትመራቸው ይገባል።
ከጉዳዩ ጋር ተስማሚ የሆነ አንድ ጥቅስ ስለጠቀስህ ብቻ አሳማኝ ማስረጃ እንዳቀረብህ ሊሰማህ ይገባልን? ሁልጊዜ እንደዚያ ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ ጥቅሱ አንተ የምትለውን ሐሳብ በእርግጥ እንደሚደግፍ ለማሳየት በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ማስረዳት ያስፈልግህ ይሆናል። የተጠቀምኸው የጥቅሱን መሠረታዊ ሥርዓት ብቻ ከሆነና በዙሪያው ያለው ሐሳብ የሚያብራራው ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ከሆነ ተጨማሪ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልግህ ይሆናል። የምትናገረው ነገር ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አድማጮችህን አጥጋቢ በሆነ መንገድ ለማሳመን ከጉዳዩ ጋር የሚዛመዱ ተጨማሪ ጥቅሶች መጠቀም ሊያስፈልግህ ይችላል።
አንድን ጥቅስ ማስረጃ አድርገህ የምታቀርብበት መንገድ የተጋነነ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። በጥንቃቄ አንብበው። ጥቅሱ ስለምታብራራው ጉዳይ ጠቅለል ያለ ሐሳብ ብቻ የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ነጥብህ አሳማኝ እንዲሆን እንደ ማስረጃ አድርገህ ያቀረብከው ጥቅስ ሐሳቡን የሚደግፍ መሆኑ ለአድማጮችህ ግልጽ ሊሆንላቸው ይገባል።
ተጨማሪ ማስረጃዎች። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት መሆኑን እንዲያስተውሉ ለመርዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ከታመነ ምንጭ የተገኙ ማስረጃዎችን መጠቀሙ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ያህል የፈጣሪን ሕልውና ለማስረዳት ግዑዙን አጽናፈ ዓለም እንደ ማስረጃ ልትጠቅስ ትችላለህ። እንደ ስበት ያሉትን የተፈጥሮ ሕግጋት በመጥቀስ የእነዚህ ሕጎች መኖር አንድ ሕግ አውጪ እንዳለ የሚጠቁም መሆኑን ልታስረዳ ትችላለህ። ያቀረብከው አሳማኝ ማስረጃ ከአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ ከሆነ ትክክል ነው ማለት ነው። (ኢዮብ 38:31-33፤ መዝ. 19:1፤ 104:24፤ ሮሜ 1:20) እንዲህ ያሉት ማስረጃዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በገሃድ ከሚታዩት እውነታዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ስለሚያረጋግጡ ጠቃሚ ድርሻ ይኖራቸዋል።
አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲገነዘብ ለመርዳት እየጣርክ ነው እንበል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያምኑ ምሁራንን እንደ ማስረጃ ትጠቅስ ይሆናል። ይሁንና ይህ ብቻውን ማረጋገጫ ይሆናልን? እንዲህ ዓይነቱን ማስረጃ አጥጋቢ ሆኖ የሚያገኙት ለምሁራኑ ትልቅ ግምት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ሳይንስን እንደ ማስረጃ አድርገህ ልትጠቅስ ትችላለህ? እንደ ትልቅ ማረጋገጫ አድርገህ የምትጠቅሰው ሊሳሳቱ የሚችሉ ሳይንቲስቶችን ሐሳብ ከሆነ ማስረጃህ ጠንካራ መሠረት ያለው አይሆንም። በሌላ በኩል ግን በመጀመሪያ የአምላክን ቃል ጠቅሰህ ከዚያ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ብታክል ማስረጃህ ጠንካራ መሠረት ያለው ይሆናል።
ማረጋገጥ የፈለግኸው ነጥብ ምንም ይሁን ምን በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርብሃል። ምን ያህል ማስረጃ ማቅረብ እንዳለብህ የሚወስነው የአድማጮችህ ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ያህል በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ ስለተጠቀሰው የመጨረሻ ቀን እያብራራህ ከሆነ ሰዎች ‘የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው’ እንደሚሆኑ የተነገረውን ትንቢት ለማረጋገጥ አድማጮችህ በደንብ የሚያውቁትን አንድ ዜና ልትጠቅስ ትችል ይሆናል። ይህ የምልክቱ ክፍል እየተፈጸመ እንደሆነ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ መጥቀስህ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።
ብዙውን ጊዜ ወሳኝ የሆነ የጋራ ባሕርይ ያላቸውን ሁለት ነገሮች ማነጻጸር ጥሩ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ንጽጽሩ በራሱ የአንድን ነገር እውነተኝነት አያረጋግጥም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚስማማ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። ሆኖም እንዲህ ያለው ንጽጽር አንድ ሰው የነጥቡን አሳማኝነት እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል። ለምሳሌ ያህል የአምላክን መንግሥት ከአንድ ሰብዓዊ መስተዳድር ጋር እያነጻጸሩ ማስረዳት ይቻላል። የአምላክ መንግሥት እንደ አንድ ሰብዓዊ መንግሥት ሁሉ ገዢዎች፣ ዜጎች፣ ሕግጋት፣ የፍርድ ሥርዓት እንዲሁም የትምህርት መርሐ ግብር እንዳለው ልትገልጽ ትችላለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ ማዋል ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለማስረዳት እውነተኛ የሕይወት ተሞክሮዎችን መጥቀስ ይቻላል። የግል ተሞክሮህንም እንደ ማስረጃ አድርገህ ልታቀርብ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ማጥናት ያለውን ጥቅም ለአንድ ሰው ስታስረዳ ይህን ማድረግህ የራስህን ሕይወት ለማሻሻል እንዴት እንደረዳህ ልትነግረው ትችላለህ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ወንድሞቹን ለማበረታታት በማሰብ በዓይኑ ስላየው የክርስቶስ ተአምራዊ መለወጥ ጠቅሶላቸዋል። (2 ጴጥ. 1:16-18) ጳውሎስም የራሱን ተሞክሮ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 1:8-10፤ 12:7-9) ሆኖም አድማጮች ለአንተ የተጋነነ ግምት እስኪያድርባቸው ድረስ አሁንም አሁንም የግል ተሞክሮህን መጥቀስ አይኖርብህም።
ሰዎች በአስተዳደጋቸውም ሆነ በአስተሳሰባቸው ስለሚለያዩ ለአንዱ አሳማኝ የሆነው ማስረጃ ለሌላኛው አጥጋቢ ላይሆን ይችላል። ስለዚህ የትኞቹን ማስረጃዎች እንደምትጠቅስና እንዴት እንደምትጠቀምባቸው ስታስብ የአድማጮችህን አመለካከት ግምት ውስጥ አስገባ። ምሳሌ 16:23 [NW ] “የጠቢብ ልብ ከአፉ ጥልቅ ማስተዋል እንዲፈልቅ አንደበቱም የሚያሳምን እንዲሆን ያደርጋል” በማለት ይገልጻል።