ውድ ወንድሞችና እህቶች:-
ከበላይ አካል የተላከ ደብዳቤ
ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ያለውን ፍቅርና አድናቆት ለመግለጽ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀም ነበር። በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች “እምነታችሁ በዓለም ሁሉ በመሰማቱ፣ ስለ ሁላችሁ አምላኬን በኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግናለሁ” በማለት ጽፎላቸዋል። (ሮሜ 1:8) እነዚህ በአንደኛው መቶ ዘመን የኖሩ ክርስቲያኖች በነበራቸው ጠንካራ እምነት እንዲሁም ምሥራቹን በቅንዓት በመስበካቸው በመላው የሮም ግዛት ተለይተው ይታወቁ ነበር። (1 ተሰ. 1:8) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹ እንዲህ ያለ ፍቅር ማሳየቱ ምንም የሚያስደንቅ አይደለም!
እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ ስለ እናንተ ባሰብን ቁጥር ይሖዋን እናመሰግናለን። ሁላችሁንም ከልብ እንወዳችኋለን! እንዲሁም ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወዳችሁ እርግጠኞች ሁኑ። አንዳንዶቻችሁ ከባድ ተቃውሞ እየደረሰባችሁ ቢሆንም ከመስበክ ወደኋላ አላላችሁም። የምታሳዩት ድፍረት የይሖዋን ልብ ደስ እንደሚያሰኘው ጥርጥር የለውም!—ምሳሌ 27:11
አስደሳችና እምነትን የሚያጠናክር በሆነው የዓመት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን፣ “በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ” የሚለውን ክፍል በጥንቃቄ ስታነቡና በዚያ ላይ ስታሰላስሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ድሉን’ ለማጠናቀቅ ‘ድል እየነሳ’ መውጣቱን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ትመለከታላችሁ። በተጨማሪም በክርስቶስ ተከታዮች ላይ እንዲደገን የተበጀ የትኛውም መሣሪያ እንደሚከሽፍ ትገነዘባላችሁ።—ራእይ 6:2 NW፤ ኢሳ. 54:17
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ‘በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ስለሆናችሁ አምላኬን አመሰግናለሁ’ በማለት ጽፎላቸዋል። (ፊልጵ. 1:3-5) እኛም የበላይ አካል አባላት እናንተን በተመለከተ ተመሳሳይ ስሜት ይሰማናል። በ2007 የአገልግሎት ዓመት በዓለም ዙሪያ በ236 አገሮች ውስጥ የሚገኙ 6,691,790 አስፋፊዎች በአጠቃላይ 1,431,761,554 ሰዓት ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ላይ አሳልፈዋል። ለምሥራቹ መስፋፋት እንዴት ያለ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታችኋል! አንድ ላይ ተባብረን በመሥራታችን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን መርዳት ችለናል፤ ይህ ሁሉ ለይሖዋ ክብር ያመጣለታል!
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ጳውሎስ የወንድሞቹን ችግር እንደራሱ ችግር አድርጎ እንደሚመለከት አሳይቷል። በተሰሎንቄ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ባላችሁ ተስፋ የተገኘውን ጽናታችሁን በአምላካችንና በአባታችን ፊት ዘወትር እናስባለን” ሲል ጽፎላቸዋል። (1 ተሰ. 1:2, 3) እርግጥ ነው፣ ሕይወት በመከራ የተሞላ ነው። ችግሮች ቢያጋጥሙንም መጽናታችን አስፈላጊ ነው። በግለሰብ ደረጃ ምን ተፈታታኝ ችግሮች አሉባችሁ? በከባድ ሕመም ሳቢያ በይሖዋ አገልግሎት የምትፈልጉትን ያህል መካፈል ባለመቻላችሁ ተስፋ ቆርጣችኋል? በጣም የምትወዱትንና ለረጅም ዓመታት አብሯችሁ የኖረውን የትዳር ጓደኛችሁን በቃኝን በማያውቀው ጠላት በሲኦል ተነጥቃችኋል? (ምሳሌ 30:15, 16) በጌታ ብቻ ማግባትን አስመልክቶ የተሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በጥብቅ ብትከተሉም እንኳ እንደ እናንተው ለይሖዋ ፍቅር ያለው የትዳር ጓደኛ ማግኘት ሳትችሉ በመቅረታችሁ ተስፋ ቆርጣችኋል? (1 ቆሮ. 7:39) ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ልጆችን ማሳደግ ሸክም እንዲሆንባችሁ አድርጓል? ያላችሁበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን መንግሥቱን የምታስቀድሙ ከሆነ ይሖዋ “ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር” እንደማይረሳ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። ወንድሞችና እህቶች እባካችሁ ‘በጎ ነገር ከማድረግ አትታክቱ’!—ዕብ. 6:10፤ ገላ. 6:9
ታዲያ ለመጽናት ምን ሊረዳችሁ ይችላል? የተሰሎንቄ ክርስቲያኖችን እንደረዳው ሁሉ ‘በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁ ተስፋ’ እናንተንም ይረዳችኋል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ “የመዳንን ተስፋ” ክርስቲያኖችን አፍራሽ ከሆነ አመለካከትና ነጋ ጠባ ከሚመላለስ የጥርጣሬ መንፈስ ሊጠብቃቸው ከሚችለው የራስ ቁር ጋር ማወዳደሩ የተገባ ነው።—1 ተሰ. 5:8
በእርግጥም፣ በደስታ በመጽናት ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነትን አስመልክቶ ሰይጣን ለሰነዘረው ነቀፋ መልስ መስጠት ትችላላችሁ። ሰይጣን ‘የአምላክ አገልጋዮች በተፈጥሯቸው ራስ ወዳዶች ናቸው፤ ከዚህም በላይ አምላክን ለተወሰነ ጊዜ ለማገልገል ፈቃደኞች ቢሆኑም እንኳ ተቃውሞ ሲበረታባቸው ወይም የዚህ ዓለም መጨረሻ እንደዘገየ ሲሰማቸው እሱን ለማምለክ ያላቸው ፍላጎት ይቀዘቅዛል’ በማለት ይሟገታል። ሰይጣን የወጣለት ውሸታም መሆኑን ለማጋለጥ የሚያስችል ልዩ መብት አግኝታችኋል! በሕይወታችሁ ላይ አንድ ቀን በጨመራችሁ መጠን ተስፋችሁ እውን ወደሚሆንበት ጊዜ ይበልጥ ቀርባችኋል ማለት ነው።
ጳውሎስ ወንድሞች ላሳዩት ጠንካራ እምነት፣ በስብከቱ ሥራ ላይ ላደረጉት ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም ለጽናታቸው እንዳመሰገናቸው ሁሉ እኛም በዚህ አጋጣሚ ልናመሰግናችሁና ለእናንተ ያለንን ፍቅር ልናረጋግጥላቸሁ እንወዳለን። መልካም ሥራዎችን መሥራታችሁን ቀጥሉ!
መጪው ዓመት በርካታ መንፈሳዊ በረከት የምታገኙበት እንዲሆን እንመኛለን። መልካሙን ሁሉ የምንመኝላችሁ
ወንድሞቻችሁ፣
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል