ሁላችንም ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር አለን
1 የሰው ልጆች ለአምላክ መስጠት የሚችሉት ነገር እንዳለ ታውቅ ነበር? አቤል፣ ምርጥ ከሆኑት እንስሶቹ መካከል አንዳንዶቹን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ ሲሆን ኖኅ እና ኢዮብም ተመሳሳይ ስጦታ አቅርበዋል። (ዘፍ. 4:4፤ 8:20፤ ኢዮብ 1:5) እርግጥ ነው፣ ፈጣሪ ሁሉም ነገር የእሱ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ስጦታዎች በምንም መንገድ እሱን ባለጠጋ አያደርጉትም። ሆኖም የቀረቡት መሥዋዕቶች፣ ታማኝ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያሉ። በዛሬው ጊዜም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ሀብታችንን ለይሖዋ ‘የምስጋና መሥዋዕት’ አድርገን መስጠት እንችላለን።—ዕብ. 13:15
2 ጊዜ:- በአገልግሎታችን ይበልጥ ተሳትፎ ለማድረግ ስንል እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች ጊዜ ‘መዋጀታችን’ አድናቆት ሊቸረው ይገባል! (ኤፌ. 5:15, 16) በዓመት ውስጥ ለአንድ ወይም ከዚያ ለሚበልጡ ወራት ረዳት አቅኚ ለመሆን ፕሮግራማችንን ማስተካከል እንችል ይሆናል። በተጨማሪም በአገልግሎት የምናሳልፈውን ጊዜ ከፍ ማድረግ እንችላለን። በእያንዳንዱ ሳምንት በአገልግሎት ላይ ተጨማሪ 30 ደቂቃ ማሳለፋችን የወሩን የአገልግሎት ሰዓታችንን ቢያንስ በሁለት ሰዓት ከፍ ያደርግልናል!
3 ጉልበት:- በአገልግሎት ላይ ለመካፈል የሚያስችል ጉልበት እንዲኖረን ከፈለግን በጣም ከመዳከማችን የተነሳ ለይሖዋ ምርጣችንን እንዳንሰጥ ከሚያደርጉን መዝናኛዎችና ሥራዎች መራቅ ይኖርብናል። አምላክን ለማገልገል የሚያስችለንን ኃይል በማሟጠጥ ልባችን ‘በሐዘን እንዲወጠር’ በሚያደርጉ ነገሮች ከሚገባው በላይ መጨነቅ አይኖርብንም። (ምሳሌ 12:25) ጭንቀታችን ተገቢ ቢሆንም እንኳ ‘የከበደንን ነገር በይሖዋ ላይ መጣላችን’ ምንኛ የተሻለ ነው!—መዝ. 55:22፤ ፊልጵ. 4:6, 7
4 ሀብት:- የስብከቱን ሥራ ለመደገፍ ቁሳዊ ሀብታችንንም መስጠት እንችላለን። ጳውሎስ የተቸገሩትን መርዳት እንዲቻል ክርስቲያን ባልደረቦቹ በቋሚነት የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ ‘እየለዩ እንዲያስቀምጡ’ አበረታቷቸዋል። (1 ቆሮ. 16:1, 2) እኛም በተመሳሳይ ለጉባኤያችንም ሆነ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ እንድንችል የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ ለይተን ማስቀመጥ እንችላለን። ይሖዋ፣ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ ከልብ በመነጨ ስሜት ተነሳስተን የምንሰጠውን ነገር ያደንቃል።—ሉቃስ 21:1-4
5 ይሖዋ ብዙ ነገር ሰጥቶናል። (ያዕ. 1:17) ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ሀብታችንን ሳንቆጥብ ለእሱ አገልግሎት በማዋል አመስጋኝነታችንን እናሳይ። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን ያስደስተዋል፤ ‘ምክንያቱም ይሖዋ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል።’—2 ቆሮ. 9:7