የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 66—ራእይ
ጸሐፊው:- ሐዋርያው ዮሐንስ
የተጻፈበት ቦታ:- ፍጥሞ
ተጽፎ ያለቀው:- በ96 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ምሳሌያዊ መግለጫዎች ሰዎችን ለማስፈራራት ታሰበው የተጻፉ ናቸው? በፍጹም አይደሉም! የትንቢቱ መፈጸም ክፉዎችን በፍርሃት እንዲርዱ ያደርጋቸው ይሆናል፤ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ግን በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት የመክፈቻ ቃላትና መልአኩ በመጽሐፉ መደምደሚያ ላይ እንዲህ ሲል ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ:- “ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ ብፁዕ ነው፤ የሚሰሙትና የተጻፈውንም የሚጠብቁ ብፁዓን ናቸው።” “የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” (ራእይ 1:3፤ 22:7) የራእይ መጽሐፍ፣ ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት ከጻፋቸው ከሌሎች አራት መጻሕፍት አስቀድሞ የተጻፈ ቢሆንም 66ቱን ቅዱሳን መጻሕፍት አሰባስቦ በያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጨረሻ ላይ መቀመጡ ተገቢ ነው። ምክንያቱም መጽሐፉ አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ የሚገልጽ ሁሉን አቀፍ ራእይ በማቅረብ አንባቢዎቹ የወደፊቱን ጊዜ አሻግረው እንዲመለከቱ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ የተስፋው ዘር በሆነው በክርስቶስ በሚተዳደረው መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ስም እንደሚቀደስና ሉዓላዊነቱ እንደሚረጋገጥ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ጭብጥ ክብራማ መደምደሚያ ይገልጻል።
2 የመግቢያው ጥቅስ እንደሚናገረው ይህ ራእይ ‘አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው፣ ኢየሱስም መልአኩን ልኮ ለአገልጋዩ ለዮሐንስ የገለጠለት’ ነው። ስለዚህ ዮሐንስ ጸሐፊ እንጂ የራእዩ ባለቤት አይደለም። በመሆኑም ዮሐንስ በመጽሐፉ ላይ ያሰፈረው የራሱን ራእይ አይደለም፤ ራእዩን የሚገልጠውም እሱ አይደለም። (1:1) አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያሉትን ድንቅ ዓላማዎች ለአገልጋዩ ስለገለጠለት፣ መጽሐፉ “የተከደነውን መግለጥ” ወይም “ሽፋንን ማውለቅ” የሚል ትርጉም ባለው አፖካሊፕሲስ (አፖካሊፕስ) የሚለው ግሪክኛ ቃል መሰየሙ ተገቢ ነው።
3 በራእይ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ጸሐፊው እንደሆነ ተደርጎ የተጠቀሰው ዮሐንስ ማን ነበር? ይህ ሰው ወንድምና የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ እንደሆነ፣ በመከራ እንደተካፈለና ወደ ፍጥሞ ደሴት በግዞት እንደተወሰደ ተገልጾልናል። ጥንት የነበሩት አንባቢዎቹ በደንብ ያውቁት ስለነበረ ማንነቱን ለመለየት ተጨማሪ ማስረጃዎችን መደርደር አላስፈለገውም። ይህ ሰው፣ ሐዋርያው ዮሐንስ መሆን አለበት። አብዛኞቹ የጥንት ታሪክ ጸሐፊዎችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የኖረው ታሪክ ጸሐፊው ፓፒያስ፣ የራእይ መጽሐፍን ከሐዋርያት የተገኘ አድርጎ ይመለከተው እንደነበር ይነገራል። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የኖረው ሰማዕቱ ጀስቲን “ትራይፎ ከተባለው አይሁዳዊ ጋር ያደረግሁት ውይይት” (LXXXI) በተባለው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ብሏል:- “በተገለጠለት ራእይ አማካኝነት ትንቢት የሚናገር፣ የክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው አብሮን ነበር።”a ኢራኒየስም ሆነ በሁለተኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በሦስተኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የኖሩት የእስክንድሪያው ክሌመንትና ተርቱሊያን የራእይ መጽሐፍን የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል። በሦስተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው ኦሪጀን የተባለው ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዲህ ብሏል:- “በኢየሱስ ደረት ላይ ስለተጠጋውና አንድ ወንጌል ስለጻፈው ስለ ዮሐንስ ይህን ለመናገር እወዳለሁ፤ . . . አፖካሊፕስንም ጽፏል።”b
4 ዮሐንስ የጻፋቸው ሌሎቹ መጻሕፍት በፍቅር ላይ ያተኮሩ መሆናቸው፣ ጠንካራና ኃይለኛ መግለጫ የያዘውን የራእይን መጽሐፍ ዮሐንስ ሊጽፍ አይችልም ብሎ ለመደምደም ምክንያት አይሆንም። በአንድ ወቅት እሱና ወንድሙ የሆነው ያዕቆብ በቁጣ ተሞልተው በአንድ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የሰማርያ ሰዎች ላይ እሳት ከሰማይ ለማውረድ ፈልገው ነበር። “ቦአኔርጌስ” ወይም “የነጎድጓድ ልጆች” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውም በዚህ ምክንያት ነው። (ማር. 3:17፤ ሉቃስ 9:54) የራእይ መጽሐፍ ርዕሰ ጉዳይ የተለየ መሆኑን ካስታወስን በአጻጻፍ ስልቱ ላይ የታየው ልዩነት ግራ አያጋባንም። ዮሐንስ በእነዚህ ራእዮች ላይ የተመለከታቸው ነገሮች ከዚህ ቀደም ካየው ከማንኛውም ነገር ፍጹም የተለዩ ናቸው። የራእይ መጽሐፍ ከሌሎቹ የትንቢት መጻሕፍት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መሆኑ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል አንዱ ክፍል መሆኑን በማያጠያይቅ መንገድ ያረጋግጣል።
5 ጥንታዊ የሆኑ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍን የጻፈው ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከ26 ዓመታት ገደማ በኋላ ማለትም በ96 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ይህ ደግሞ የንጉሠ ነገሥት ደሚሽን የንግሥና ዘመን ሊያበቃ የተቃረበበት ጊዜ ነበር። ኢሬኒየስ “ፀረ መናፍቃን” (V, xxx) በተባለው መጽሐፉ ላይ አፖካሊፕስን አስመልክቶ እንደሚከተለው ማለቱ ይህ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል:- “ራእዩ የታየው ከረዥም ጊዜ በፊት ሳይሆን በዚህ በእኛ ዘመን ማለትም በደሚሽን ንግሥና ማብቂያ ላይ ነው።”c ዩሲቢየስና ጀሮምም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ደሚሽን፣ ኢየሩሳሌምን ለማውደም የዘመተውን የሮማ ሠራዊት የመራው የቲቶ ወንድም ነበር። የራእይ መጽሐፍ ከመጻፉ ከ15 ዓመታት በፊት፣ ቲቶ ሲሞት በምትኩ ደሚሽን ነገሠ። ደሚሽን እንደ አምላክ እንዲመለክ ያዘዘ ሲሆን ዶሚነስ ኤ ዴዩስ ኖስተር (ማለትም “ጌታችንና አምላካችን”) የሚል የማዕረግ ስምም ነበረው።d የሐሰት አማልክትን ያመልኩ የነበሩ ሰዎች በንጉሠ ነገሥት አምልኮ መካፈል ግድ አልሰጣቸውም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም ለማላላት ፈቃደኞች ላልነበሩት ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች ግን ይህ የሚዋጥላቸው ነገር አልነበረም። በመሆኑም የደሚሽን ንግሥና (81-96 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ወደ ማብቂያው ሲቃረብ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። ዮሐንስን በግዞት ወደ ፍጥሞ እንዲላክ ያደረገው ደሚሽን እንደሆነ ይገመታል። ደሚሽን በ96 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲገደል ለዘብተኛ አቋም የነበረው ንጉሠ ነገሥት ኔርቫ በምትኩ ነገሠ። ከዚያም ንጉሡ ዮሐንስን በነፃ ለቀቀው። ዮሐንስ በመጽሐፉ ውስጥ ያሰፈራቸውን ራእዮች የተቀበለው በፍጥሞ ታስሮ በነበረበት በዚህ ወቅት ነው።
6 ዮሐንስ የተመለከተውና ለጉባኤዎች እንዲጽፍ የተነገረው ምንም ተዛማጅነት የሌላቸው የራእዮች ስብስብ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። ከመክፈቻው አንስቶ እስከ መደምደሚያው ድረስ መላው የራእይ መጽሐፍ፣ የአምላክ መንግሥት ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ ግልጽ እስከሚሆኑበት እስከ ራእዮቹ ማብቂያ ድረስ ራእዮቹን ደረጃ በደረጃ በማስተዋወቅ ወደፊት የሚከናወኑት ነገሮች ሕያው ሆነው እንዲታዩን ያደርጋል። ስለዚህ የራእይ መጽሐፍን ከዮሐንስ ዘመን በኋላ እጅግ ቆይተው የሚፈጸሙትን ነገሮች አሻግረን ለመመልከት የሚያስችለን እርስ በርስ ተዛማጅነትና ስምምነት ያላቸው ክፍሎች ያሉት አንድ ወጥ መጽሐፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል። መጽሐፉ ከመግቢያው ሐሳብ (ራእይ 1:1-9) በኋላ በ16 ራእዮች እንደተከፋፈለ ተደርጎ ሊታይ የሚችል ሲሆን እነሱም (1) ከ1:10 እስከ 3:22፤ (2) 4:1 እስከ 5:14፤ (3) 6:1-17፤ (4) 7:1-17፤ (5) ከ8:1 እስከ 9:21፤ (6) ከ10:1 እስከ 11:19፤ (7) 12:1-17፤ (8) ከ12:17 እስከ 13:1-18፤ (9) 14:1-20፤ (10) ከ15:1 እስከ 16:21፤ (11) 17:1-18፤ (12) ከ18:1 እስከ 19:10፤ (13) 19:11-21፤ (14) 20:1-10፤ (15) ከ20:11 እስከ 21:8፤ (16) ከ21:9 እስከ 22:5 ናቸው። ከእነዚህ ራእዮች ቀጥሎ፣ በመልእክቱ መተላለፊያ መስመር ላይ በዋነኝነት የተጠቀሱት ይሖዋ፣ ኢየሱስ፣ መልአኩና ዮሐንስ የራሳቸውን የማጠቃለያ አስተያየት ያከሉበት ስሜት ቀስቃሽ መደምደሚያ ይገኛል።—22:6-21
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
28 የራእይ መጽሐፍ፣ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ 66 መጻሕፍትን ለያዘው ለመጽሐፍ ቅዱስ ታላቅ መደምደሚያ ሆኖለታል! ምንም የቀረ ነገር የለም። ሳይቋጩ በእንጥልጥል የታለፉ ጉዳዮችም የሉም። አሁን ታላቁ መደምደሚያውንም ሆነ መጀመሪያውን በግልጽ ለመመልከት እንችላለን። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተጀምሮ የነበረውን ዘገባ ይቋጫል። ዘፍጥረት 1:1 አምላክ ግዑዙን ሰማይና ምድር መፍጠሩን ሲገልጽ ራእይ 21:1-4 ደግሞ ስለ አዲስ ሰማይና ስለ አዲስ ምድር እንዲሁም ለሰው ልጆች ስለሚዘንቡላቸው የተትረፈረፉ በረከቶች ይገልጻል። በኢሳይያስ 65:17, 18፤ 66:22 እና 2 ጴጥሮስ 3:13 ላይም ስለ እነዚህ በረከቶች ትንቢት ተነግሯል። የመጀመሪያው ሰው ካልታዘዘ እንደሚሞት ተነግሮት እንደነበር ሁሉ አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም’ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 2:17፤ ራእይ 21:4) እባብ የሰው ልጅ አሳሳች ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ባለበት ወቅት አምላክ የእባቡ ራስ እንደሚቀጠቀጥ ተናግሮ የነበረ ሲሆን የራእይ መጽሐፍ ደግሞ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው የቀድሞው እባብ በመጨረሻ የሚጠፋው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍ. 3:1-5, 15፤ ራእይ 20:10) ታዛዥ ያልነበረው ሰው በኤደን ከነበረው የሕይወት ዛፍ የተባረረ ቢሆንም በራእይ መጽሐፍ ላይ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ‘መፈወሻ’ የሚሆኑ ምሳሌያዊ የሕይወት ዛፎች ታይተዋል። (ዘፍ. 3:22-24፤ ራእይ 22:2) ገነትን የሚያጠጣ ወንዝ ከኤደን ይወጣ እንደነበረ ሁሉ ሕይወት የሚሰጥና ሕይወትን ጠብቆ የሚያቆይ ምሳሌያዊ ወንዝ ከአምላክ ዙፋን ሲፈስ የሚያሳይ ሥዕላዊ መግለጫ ታይቷል። ይህ መግለጫ፣ ሕዝቅኤል ቀደም ሲል ከተመለከተው ራእይ ጋር የሚመሳሰል ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ ‘በውስጡ የዘላለም ሕይወት ስለሚያፈልቅ የውሃ ምንጭ’ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። (ዘፍ. 2:10፤ ራእይ 22:1, 2፤ ሕዝ. 47:1-12፤ ዮሐ. 4:13, 14) እንደ መጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ከአምላክ ፊት ከመባረር ይልቅ ታማኝ የሆኑ ድል አድራጊዎች ፊቱን ያያሉ። (ዘፍ. 3:24፤ ራእይ 22:4) በእርግጥም፣ እነዚህን በራእይ የታዩ አስደናቂ ትዕይንቶች መመርመሩ አጅግ ጠቃሚ ነው!
29 በተጨማሪም የራእይ መጽሐፍ ክፉ ስለሆነችው ስለ ባቢሎን የተነገሩትን ትንቢቶች እንዴት ጠቅለል አድርጎ እንዳስቀመጣቸው ተመልከት። ኢሳይያስ የጥንቷ ባቢሎን ከመውደቋ ከረዥም ጊዜ በፊት ውድቀቷን ተመልክቶ የነበረ ሲሆን “ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች!” ሲል ተናግሯል። (ኢሳ. 21:9) ኤርምያስም ስለ ባቢሎን መውደቅ ትንቢት ተናግሯል። (ኤር. 51:6-12) የራእይ መጽሐፍ “የአመንዝሮችና የምድር ርኩሰቶች እናት” ስለሆነችና ምሳሌያዊ ትርጉም ስላላት “ታላቂቱ ባቢሎን” ይናገራል። እሷም ብትሆን መወገድ አለባት፤ ዮሐንስም ይህን ሁኔታ በራእይ ከተመለከተ በኋላ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 17:5፤ 18:2) የአምላክ መንግሥት ሌሎች መንግሥታትን ፈጭቶ በማጥፋት “ለዘላለም” እንደሚቆም የሚገልጸውን ዳንኤል የተመለከተውን ራእይ ታስታውሳለህ? ይህ በራእይ መጽሐፍ ላይ ከተጠቀሰው ከሰማይ የተነገረ አዋጅ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ተመልከት። አዋጁ እንዲህ ይላል:- “የዓለም መንግሥት፣ የጌታችንና የእርሱ ክርስቶስ መንግሥት ሆነች፤ እርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።” (ዳን. 2:44፤ ራእይ 11:15) የዳንኤል ራእይ ‘ሥልጣን ክብርና ታላቅ ኃይል ለመቀበል የሰው ልጅን የሚመስል ከሰማይ ደመና ጋር መምጣቱን’ እንደሚገልጽ ሁሉ የራእይ መጽሐፍም ኢየሱስ ክርስቶስ “የምድር ነገሥታት ገዥ” እንደሆነ፣ ‘በደመና እንደሚመጣና’ ‘ዐይን ሁሉ እንደሚያየው’ ይናገራል። (ዳን. 7:13, 14፤ ራእይ 1:5, 7) በተጨማሪም በዳንኤል ራእይ ላይ በተጠቀሱትና በራእይ መጽሐፍ ላይ በተገለጹት አውሬዎች መካከል ያሉት አንዳንድ ተመሳሳይነቶች ልብ ሊባሉ ይገባል። (ዳን. 7:1-8፤ ራእይ 13:1-3፤ 17:12) በእርግጥም የራእይ መጽሐፍ፣ እምነትን ለማጠንከር የሚረዱና ጥልቅ ምርምር ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዟል።
30 የራእይ መጽሐፍ የአምላክን መንግሥት በሚመለከት እጅግ አስገራሚና ሰፊ ገጽታ ያለው መግለጫ ይሰጠናል! የጥንት ነቢያትም ሆኑ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ መንግሥቱን አስመልክተው የተናገሩትን ነገር፣ ትኩረት በሚስብ መንገድ ግሩም አድርጎ ያቀርባል። ይህ መጽሐፍ፣ “ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” የሚለውን መግለጫ በመጠቀም የይሖዋ ስም በመንግሥቱ አማካኝነት እንደሚቀደስ የሚናገሩት ትንቢቶች ሙሉ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ያህል አድርጎ አስቀምጦታል። እሱ “ክብርና ሞገስ፣ ኃይልም” ሊቀበል ይገባዋል። በክርስቶስ አማካኝነት ‘ታላቁን ኃይሉን ይዞ በመንገሥ’ መግዛት የሚጀምረው በእርግጥም እሱ ነው። “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ” የሆነውና ግርማ ሞገስ የተላበሰው ወልድ አሕዛብን ሲመታና “ሁሉን ቻይ የሆነውን [የይሖዋን፣ NW] የብርቱ ቁጣ ወይን መጭመቂያ [ሲረግጥ]” መታየቱ ከፍተኛ ቅንዓት እንዳለው ያሳያል! ስለ ይሖዋ አገዛዝ ትክክለኝነት መረጋገጥ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ ጭብጥ ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ በመንግሥቱ ዓላማዎች ውስጥ የሚካፈል እያንዳንዱ ሰውም ሆነ ማንኛውም ነገር ቅዱስ መሆን እንዳለበት ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ‘የዳዊትን መክፈቻ በእጁ የያዘው’ በግ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ እና የሰማይ መላእክት ቅዱስ መሆናቸው ተነግሯል። በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑት “ብፁዓንና ቅዱሳን” እንደሆኑ እንዲሁም “ርኩሰትን የሚያደርግና ውሸትን የሚናገር ሁሉ” ወደ ‘ቅድስቲቱ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም’ ፈጽሞ እንደማይገባ ጠበቅ ተደርጎ ተገልጿል። በመሆኑም፣ ‘ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንዲሆኑ’ በበጉ ደም የተዋጁ ሰዎች በይሖዋ ፊት ያላቸውን ቅድስና ጠብቀው እንዲቆዩ ግሩም ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦችም’ ቢሆኑ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ ‘ልብሳቸውን አጥበው በበጉ ደም ማንጻት’ አለባቸው።—ራእይ 4:8 (NW), 11፤ 11:17፤ 19:15, 16፤ 3:7፤ 14:10፤ 20:6፤ 21:2, 10, 27፤ 22:19፤ 5:9, 10፤ 7:9, 14, 15
31 በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ የሚገኙ አንዳንድ ክንውኖችን ስንመለከት ዕጹብ ድንቅና ቅዱስ ስለሆነው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸው ራእይ ከአእምሯችን የሚጠፋ አይደለም። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ የመንግሥቱ ወራሾች ከበጉ ጋር በጽዮን ተራራ ላይ ሆነው ከእነሱ በቀር ሌላ ማንም ሊማረው ያልቻለውን አዲስ መዝሙር ሲዘምሩ የሚያሳይ የተሟላ ራእይ እናገኛለን። ወደ መንግሥቱ ለመግባት ከምድር የተዋጁት ቁጥራቸው 144,000 መሆኑንና ቁጥሩ ምሳሌያዊ ከሆኑት ከ12ቱ መንፈሳዊ የእስራኤል ነገዶች የተውጣጣ መሆኑን የሚነግረን የራእይ መጽሐፍ ብቻ ነው። ከክርስቶስ ጋር በመጀመሪያው ትንሣኤ የሚካፈሉት እነዚህ ‘ካህናትና ነገሥታት’ ከእሱ ጋር ‘ለሺህ ዓመት’ እንደሚነግሡ የሚገልጽልን ይህ መጽሐፍ ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ስላላት አንጸባራቂ ግርማ፣ ይሖዋና በጉ የዚህች ከተማ ቤተ መቅደስ ስለመሆናቸው፣ ስለ 12ቱ በሮቿና የመሠረት ድንጋዮቿ እንዲሁም ይሖዋ በሚፈነጥቀው ዘላለማዊ ብርሃን እየተመሩ ለዘላለም ስለሚገዙት ነገሥታቶቿ ዝርዝር መግለጫ የሚገኘው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ነው።—14:1, 3፤ 7:4-8፤ 20:6፤ 21:2, 10-14, 22፤ 22:5
32 ስለ “አዲስ ሰማይ” እና ስለ “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” የሚናገረው ራእይ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት የመንግሥቱን ዘር አስመልክተው ከጥንት ጀምሮ ሲተነብዩአቸው የነበሩትን ነገሮች በሙሉ ጠቅለል አድርገው የሚገልጹ ናቸው ሊባል ይቻላል። አብርሃም፣ ‘የምድር ሕዝቦች ሁሉ ራሳቸውን የሚባርኩበትን’ ዘር እና “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።” ይህች በረከት የሞላባት ከተማ፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰ አንድ ትዕይንት ላይ “አዲስ ሰማይ” ማለትም በአዲሲቷ ኢየሩሳሌም (በክርስቶስ ሙሽራ) እና በሙሽራው የተገነባች አዲስ መስተዳደርን ወይም የአምላክ መንግሥትን እንደምታመለክት በግልጽ ተቀምጦልናል። አዲሲቱ ኢየሩሳሌምና ሙሽራው በኅብረት ሆነው በመላው ምድር ላይ የጽድቅ አገዛዝ ያሰፍናሉ። ይሖዋ፣ ታማኝ የሆኑ ሰዎች በኤደን ዓመጽ ከመቀስቀሱ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ደስታ የሰፈነበት እንዲሁም ኃጢአትና ሞት የሌለበት ሕይወት እንደሚመሩና “ሕዝቡ” እንደሚሆኑ ቃል ገብቷል። የራእይ መጽሐፍ አምላክ ‘እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው እንደሚያብስላቸው’ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ሲል ይህን ሐሳብ ሁለት ጊዜ ይደግመዋል።—ዘፍ. 12:3፤ 22:15-18፤ ዕብ. 11:10፤ ራእይ 7:17፤ 21:1-4
33 አዎን፣ ይህ በመንፈስ አነሳሽነት ለተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ግሩም መደምደሚያ ነው! ‘ቶሎ ሊሆኑ የሚገባቸው [እነዚህ] ነገሮች’ ምንኛ አስደናቂ ናቸው! (ራእይ 1:1) ‘ነቢያት በመንፈስ መሪነት እንዲናገሩ የሚያደርገው አምላክ’ ይሖዋ ስሙ ተቀድሷል። (22:6 NW) በአሥራ ስድስት ክፍለ ዘመናት የተጻፉ ትንቢታዊ መጻሕፍት ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ ታይተዋል፤ እንዲሁም በሺህ በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ የተፈጸሙ የእምነት ሥራዎች ሽልማታቸውን ተቀብለዋል! “የጥንቱ እባብ” ሞቷል፤ ሠራዊቱ ጠፍቷል፤ ክፋትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግዷል። (12:9) የአምላክ መንግሥት “አዲስ ሰማይ” ሆኖ በመግዛት ለይሖዋ ውዳሴ አምጥቷል። በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ በተገለጸው የይሖዋ ዓላማ መሠረት በሰዎች የምትሞላውና የምትገዛው የታደሰችው ምድር የምታመጣቸው በረከቶች በሰው ልጆች ፊት ለዘላለም ተዘርግተዋል። (ዘፍ. 1:28) በእርግጥም ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ ‘የአምላክ መንፈስ ያለባቸውና ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር የሚጠቅሙ’ መሆናቸውን ማየት ይቻላል። ይሖዋ አገልጋዩቹ ብቁና በሚገባ የታጠቁ ሆነው እስከዚህ አስደናቂ ቀን ድረስ እንዲቀጥሉ ለማድረግ በእነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ተጠቅሟል። በመሆኑም እምነትህን ለማጠንከር ቅዱሳን መጻሕፍትን የምታጠናበት ጊዜው አሁን ነው። የአምላክን በረከት እንድታገኝ እነዚህ መጻሕፍት የሚሰጡህን መመሪያ ታዘዝ። የሚሰጡህን ምክር በመከተል ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ቀና መንገድ ላይ ተጓዝ። እንዲህ ካደረግህ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ የተደመደመበትን “አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና” የሚለውን ሐሳብ አንተም በልበ ሙሉነት ለመናገር ትችላለህ።—2 ጢሞ. 3:16፤ ራእይ 22:20
34 ‘ሁሉን ቻይ የሆነው የይሖዋ አምላክ’ ታላቅ ስም ለዘላለም እንዲቀደስ የሚያደርገው የዘሩ ማለትም ‘የጌታችንና የክርስቶስ’ መንግሥት ስለሆነ ስለዚህ መንግሥት ማወጃችን በአሁኑ ጊዜ ወደር የሌለው ደስታ ያስገኝልናል!—ራእይ 11:15, 17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዚ አንቲ-ናይሲን ፋዘርስ፣ ጥራዝ 1 ገጽ 240
b ዚ ኢክለዚያስቲካል ሂስትሪ፣ ዩሲቢየስ VI, xxv, 9, 10
c ዚ አንቲ-ናይሲን ፋዘርስ፣ ጥራዝ 1 ገጽ 559–560
d ዘ ላይቭስ ኦቭ ዘ ሴዛርስ (ደሚሽን፣ XIII, 2)